November 24, 2024
34 mins read

ምን ውስጥ ነው የገባነው?

Killer Abiy Ahmed

ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected])

ዘጠነኛ ክፍል ስገባ 14 አመቴ ነበር፣ 15 የሞላሁት ዘጠነኛ ክፍል ገብቼ የመጀመሪያውን ሴምስተር ፈተና ስፈተን ነው። ከሀሁ እስከ አራተኛ ክፍል የተማርኩት ከሻሸመኔ 10 ኪሎ ሜትር ርቀር ላይ በሚገኘው ኩየራ ሱዳን ኢንቲሪየር ሚሺን(SIM) ግቢ ውስጥ በሚገኘው ትምህርት ቤት ሲሆን፣ ከቤተሰቦቼ ጋር የኖርነውም እዚያው ሚሺን ግቢ ውስጥ ነው። አራተኛ ክፍል ስጨርስ ቤተሰቦቼ ኩየራን ትተው አዋሳ ሲሄዱ ከ5ኛ ክፍል እስከ ስምንተኛ ክፍል ያለውን ትምህርቴን አዋሳ ካቶሊክ ሚሺን (ኮምቦኒ) ት/ቤ ተማርኩ። ስምንተኛ ክፍል ስጨርስ ደብረዘይት የሚገኘው የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ኮሌጅ አዳሪ ት/ቤት(EEC) የነጻ ትምህርት ዕድል ሰጠኝና ለመጀመሪያ ግዜ ከቤተሰቦቼ ተለይቼ ደብረዘይት ሄድኩ። ከአዋሳ ደብረዘይት ያደረኩት ጉዞ በህይወቴ የመጀመሪያው ረጂሙ የመኪና ጉዞ ነበር፣ ከዚያ በፊት በመኪና ትልቅ ተጓዝኩ የምለው ፈረንጆቹ ከኩየራ ላንጋኖ ሲወስዱን ነበር(40ኪሜ)።

ደብረዘይት ለመጀመሪያ ግዜ ቴሌቪዥን ያየሁባት፣ ዳንስ ቤት የገባሁባት፣ሻይ ቤት ገብቼ ሙዚቃ የሰማሁባትና date የወጣሁባት ከተማ ናት። እኔ ከ9ኛ እስከ 11ኛ ክፍል ድረስ የተማርኩበት ደብረዘይት የሚገኘው የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ኮሌጅ ደርግ እስኪወርሰው ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ውስጥ እጅግ በጣም ከፍተኛ የትምህርት ጥራት ደረጃ የነበረው፣ማትሪክ የተፈተነ ሁሉ የኮሌጅ መግቢያ ውጤት የሚያገኝበትና (ያውም ማቲሪክ Essay based exam በነበረበት ዘመን) የኋላ ኋላ ሻዕቢያ፣ኦነግና ህወሓት ውስጥ ገብተው የብሔርና የመገንጠል ትግል ያካሄዱ ልህቃንን ያፈራ ትምህርት ቤት ነው። እኔም በህይወቴ ለመጀመሪያ ግዜ ከፖለቲካ ጋር የተዋወኩት፣ የኢትዮጵያ ፓለቲካ ምን እንደሚመስል በአይኔ ያየሁትና ኢትዮጵያ በምትባለው አገር ላይ ከኔ ፍጹም የተለየ አቋም ያለው ኢትዮጵያዊ እንዳለ ለመጀመሪያ ግዜ ያወኩት ደብረዘይት ነው። አዋሳ ሳድግ ትምህርት ቤትና መንደር ውስጥ ኳስ፣ቢይና ሰኞ ማክሰኞ ስንጫወትና አንዳንዴም በሴቶች እንጣላ እንደሆን ነው እንጂ ኢትዮጵያዊያን ነን በሚለው ሃሳብ ላይ አንዳችንም ጥያቄ አልነበረንም።እኔ ያደኩባት አዋሳ አማራው፣ወላይታው፣ትግርኛ ተናጋሪው፣ጉራጌው፣ሲዳማው፣ኦሮሞው፣ከምባታውና ሃዲያው አንድ ላይ ቁጭ ብለን የተማርንባትና ጧት ጧት “ደሙን ያፈሰሰ” እያልን አረንጓዴ ቢጫ ቀዩን እየሰቀልን፣ ወደ ማታ ደሞ “ተጣማጅ አርበኛ” እያልን ጧት የሰቀልነውን ባንዲራ እያወረድን ያደግንባት አዋሳ ናት።

የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ኮሌጅ ተማሪዎች አብዛኛዎቹ የሚመጡት ከአዲስ አበባ፣ከሲዳሞ፣ከትግራይ፣ከኤርትራ፣ከወለጋ፡ከሐረርና ከጋሞጎፋ ነበር። ዛሬ ላይ ወደኋላ ዞር ብዬ የደብረዘይት ቆይታዬን ስመለከት፣ ደብረዘይት እኔ የተማርኩበት ት/ቤት ዛሬ ኢትዮየጵያን እያተራመሰ ያለው የብሔር ፖለቲካ ዘር ከተዘራባቸው ትምህርት ቤቶች ውስጥ አንዱ ነው ማለት እችላለሁ። ለምሳሌ፣ አባዲ ዘሙ የዚህ ትምህርት ቤት ተማሪ ነበር፣ ተክለ ሐይማኖት ገ/ሂወት አብሮኝ ጋር ጎን ለጎን ተቀምጦ የተማረና፣ በ1980 ዓም ሺራሮ ላይ በተደረገው ጦርነት ህይወቱን ያጣ ተጋሩ ጓደኛዬ ነበር። የጄኔራል ጻድቃን ሚስት ኤልሳቤት አስፍሃ ክላስሜቴ ነበረች። በፖለቲካ ባንስማማም ጀብሐ፣ሻዕቢያና ኦነግ ውስጥ ገብተው የታገሉ ኤርትራዊያንና የወለጋ ልጆች ብዙዎቹ ዛሬም በህይወት የሚገኙ ጓደኞቼ ናቸው።

እኔ ዘጠነኛ ክፍል ከገባሁበት ግዜ ጀምሮ ዛሬ እስካለንበት ዘመን ድረስ የኢትዮጵያ ፖለቲካ እጅግ በጣም ጠመዝማዛና ውስብስብ የሆነ ጉዞ ተጉዟል። የ66ቱን አብዮትና የ70ዎቹን ቀይ ሽብር አሳይቶናል። የደርግን፣የኢህአፓንና የመኢሶንን የከተማ ውስጥ የርስበርስ ዕልቂትና ከጀብሃ፣ከሻዕቢያና ከህወሓት ጋር የተደረገውን እልህ አስጨራሽ ጦርነት አሳይቶናል። ህወሓት በ1983 ዓም አዲስ አበባን ተቆጣጥሮ ኢትዮጵያን በታሪኳ ለመጀመሪያ ግዜ የብሔር ፖለቲካ መድረክ ሲያደርጋትም ተመልክተናል። እነዚህ የተለያዩ ኩነቶች እኔ በቀጥታም በተዘዋዋሪም እያየኋቸው የሆኑ ኩነቶች ናቸው። ሆኖም እኔ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ሀሁ ከቆጠርኩበት ከወጣትነት ዕድሜዬ ጀምሮ እቺ የምወዳት አገር ዛሬ እንደሚታይባት ፖለቲካዊ፣ማህበራዊና ኤኮኖሚያዊ ምስቅልቅል ውስጥ ገብታ በሞትና በህይወት መሃል ስትንገዳገድ አይቼ አላውቅም። ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ የምትገኝበት ሁኔታ በታሪካችን አይተነውም ሰምተነውም የማናውቀውና፣ እንደ አንድ አገር ህዝብ ተሰባስበን ለዚህ ድሃ ህዝብ ካልደረስንለት ነገና ከነገ ወዲያ “ኢትዮጵያ የምትባል አገር ነበረችን” ከማለት የሚያድነን ምንም ነገር የለም። ይህንን የምለው ያለምክንያት አይደለም። ንጉሰ ነገስት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሤ የተዋጉት ከጣሊያን ፋሺስቶችና ከኢትዮጵያ ላይ ግዛት ቆርሼ ካልወሰድኩ ከሚለው ከሱማሌ መንግስት ጋር ነው። ወታደራዊው ደርግ የተዋጋው ከተስፋፊ የሶማሊያ ኃይሎችና ከኢትዮጵያ እንገነጠላለን ካሉ ኃይሎች ጋር ነው። ዛሬ የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት የሚዋጋው በአንድ ወቅት ኢትዮጵያን ከትልቅ አደጋ አዳናት ብሎ እሱ እራሱ ደጋግሞ ካሞገሰው ኃይል ጋር ነው፣ወይም የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት ጦርነት ውስጥ የገባው ከአማራ ህዝብ ጋር ነው።

ሰኞ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓም ጠሚ አቢይ አህመድ የአገር መሪነት ሥልጣን የተረከቡበትን አጋጣሚ ምክንያት በማድረግ ፓርላማ ውስጥ ያደረጉት የመጀመሪያው ንግግር፣ 27 አመት ሙሉ የኢትዮጵያ ህዝብ ከመሪዎቹ አንደበት በፍጹም ሰምቶት የማያውቀው ኢትዮጵያን ማዕከል ያደረገ ታሪካዊ ንግግር ስለነበረ ጠሚሩ በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ህዝባዊ ድጋፍ ውጭም አገር ውስጥም ካለው ኢትዮጵያዊ እንዲያገኙ አድርጓል። ነገር ግን ጠሚሩ ይህንን ትልቅ ህዝባዊ ድጋፍ እንደ ፖለቲካ መሳሪያ ተጠቅመው የኢትዮጵያ ህዝብ ላለፉት 50 አመታት ለጠየቀው የፍትህ፡የነጻነት፡የእኩልነትና የዲሞክራሲ ጥያቄ ከተለያዩ የአገራችን ባለድርሻዎች ጋር ሆነው አግባብ ያለው መልስ መስጠት መጀመር ሲገባቸው፣እሳቸው ጭራሽ የኢትዮጵያ ህዝብ በገፍ የቸራቸውን ድጋፍ ተጠቅመው የአንድ ብሔር የበላይነት የነገሰበት ሥርዓት መገንባት ጀመሩ። ሁለት ሺ አስር፣ 2011፣ 2012፣ 2013 እና 2014 እያለ አመት አመትን ሲተካ፣አገራዊ የነበረው የጠሚ አቢይ አጀንዳ እየተሸረሸረ ሄዶ የአንድ ክልል አጀንዳ ሆኖ አረፈው። በህወሓት ዘመን እስር ቤቱ ነበር የኦሮሞዎች ሆነ የሚባለው፣ አሁን ላይ ግን ሥልጣን፣መሬት፣ኃብትና ንብረት የኦሮሞዎች እየሆነ መጣ። ህወሓት ሥልጣን ላይ እያለ በየምሽት ክለቡና በየቡና ቤቱ እየዞሩ የሚዝናኑትና ብር በሻንጣ ይዘው ሻሞ እያሉ የሚበትኑት የህወሓት ጅሎች ነበሩ፣ ዛሬ ይህንን የሞኝ ስራ የሚሰሩት ባጭር ግዜ የከበሩት  የኦሮሞ ቅንጡዎች ናቸው።  ሁላችንም ሳንሰስት ድጋፋችንን የሰጠነውና ህወሓትን ከሥልጣን ለማስወገድ ኢህአዴግ ውስጥ በተደረገው መራራ ትግል ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈለው በተለምዶ “ቲም ለማ” የሚባለው ቡድን እየሟሟ ሄዶ ዛሬ  “ቲም ለማ” አባሉም፣መሪውም እንድ ሰው ብቻ ሆነ።

የኢትዮጵያ ጥምር ኃይሎች ከህወሓት ጋር ያደረጉት ከሁለት አመት በላይ የፈጀ አውዳሚ ጦርነት (የህወሓቶች ችኮነትና ክፋት እንዳለ ሆኖ) ሚኒልክ ቤተመንግስት ውስጥ ጠንቃቃ፣የወደፊቱን መመልከት የሚችሉ፣አስተዋይና ጥበበኛ ሰዎች ቢኖሩን ኖሮ ወይ ጦርነቱ አይጀመርም፣ አለዛም የፌዴራሉ ኃይል ጦርነቱን በመጠነኛ የሰው ኃይልና የፋይናንስ ወጪ ቋጭቶ ዛሬ ህወሓት ፀጉሩን እንደተሸለተው የመጽሐፍ ቅዱሱ ሳምሶን አድርግ የሚባለውን ሁሉ የሚያድርግና ሁን የተባለውን የሚሆን ድርጅት ይሆን ነበር። ነገር ግን ባለመታደል መሆን የሚገባው ሳይሆን መሆን የማይገባው በመሆኑ፣ አገራችን ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሰው ህይወት፣የፋይናንስና የመሰረተ ልማት ኪሳራ ደረሰባት። ጦርነቱ በቀጥታ የተካሄደባቸው የአፋር፣ የወሎና የሰሜን ሸዋ ህዝብ ከፍተኛ የኤኮኖሚና የስነልቦና ዉድቀት ውስጥ ገባ።

ከህወሓት ጋር የተደረገው ጦርነት ደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ውስጥ ድርድር ተደርጎ በስምምነት ሲቋጭ፣ ጦርነት ባህላችን ነው ከሚሉ ጥቂት የዕብድ ክምሮች ውጭ ልቡ በደስታ ያልተሞላ ኢትዮጵያዊ አልነበረም። ነገር ግን በተደጋጋሚ በግልጽ እንደታየው ከአራት ኪሎ የመነጨ ደስታ ግዜያዊ ነውና፣የፕሪቶሪያው ስምምነት ሲፈረም የነበረውን ህዝባዊ ደስታ የሃላላ ኬላው ስምምነትና የወዳጅነት ፓርክ ሠርግና ምላሽ ቀዝቃዛ ውኃ ቸለሰበት። ጠሚ አቢይ አህመድ የህወሓትን መሪዎች ሃላላ ኬላ ወስደው የተዋዋሉት የክህደት ውል፣ በኢትዮጵያ ጥምር ኃይሎች ተቀጥቅጦ እንኳን ትጥቄን ሱሪዬንም እፈታለሁ ብሎ ሲወተውት ለነበረው ህወሓት ‘እንዲህም አለ እንዴ’ የሚል የተስፋ ጭላንጭል ሰጠው። በፕሪቶሪያው ስምምነት ላይ የተፈጸመው ክህደት ሁሌም እንዳንገበገኝ የሚኖር ቢሆንም፣ ዛሬ ከሱ በላይ የሚያንገበግበኛና ለአገራችን ለኢትዮጵያ ትልቅ የህልውና አደጋ ነው ብዬ የማስበው የሃላላ ኬላው ክህደት ሲፈጸም አብሮ የተፈጸመው ሌላ ትልቅ ክህደት ነው። ይህ ክህደት የአማራ ህዝብ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ያለውን ትልቅ ቦታ ለማሳነስና የዚህን ህዝብ ስነልቦና ለመስበር ከህወሓት ጋር የተሸረበው ሴራ ነው። ይህ ሴራ ነው የክልል ኃይሎች ትጥቅ መፍታት አለባቸው በሚል ሰበብ የጠሚ አቢይ አህመድ ሠራዊት አማራ ክልል ውስጥ ትርጉም የለሽ ጦርነት እንዲጀምር ያደረገው።

በአለም አቀፍ ደረጃ ድርድር ተደርጎ ትጥቁን ሙሉ በሙሉ እንዲፈታ የተወሰነበትና፣ ለአማራ ብቻ ሳይሆን ባጠቃላይ ለኢትዮጵያ ህዝብ ትልቅ ስጋት የሆነው ህወሓት ሙሉ በሙሉ ትጥቁን እንደታጠቀና ወልቃይትና ራያን አስመልሳለሁ እያለ በሚፎክርበት ግዜ፣ ለምንድነው የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት ሰኞ ልዩ ኃይሎች ትጥቅ መፍታት አለባቸው የሚል ህግ አውጥቶ ማክሰኞ ህጉን በኃይል ተግባራዊ ለማድረግ መሳሪያ ተሸክሞ አማራ ክልል የዘመተው?

የጠሚ አቢይ አህመድ አፈቀላጤዎች፣ደጋፊዎችና ጥቅመኞች አማራ ክልል የሚካሄደው ጦርነት ህግ የማስከበር ጦርነት መሆኑን ለማስመሰል የማይሄዱት ርቀት የለም። አማራ የህልውና ሥጋት ስላለበት ሳይወድ በግዱ ነው ጦርነት ውስጥ የገባው ስንላቸው፣ አማራው ከሌላው ኢትዮጵያዊ የተለየ የህልውና ስጋት የለበትም ይሉናል፣ አንዳንዶቹማ ጭራሽ አማራ ምንም የህልውና ስጋት የለበትም ይሉናል።የጠሚ አቢይ አህመድን መንግስት ጨምሮ፣ አማካሪዎቹና ደጋፊዎቹ ማወቅ ብቻ ሳይሆን በጥልቀት ሊረዱት የሚገባቸው አንድ ትልቅ የፖለቲካ እውነት አለ። እሱም እንደ ኢትዮጵያ የብሔር ፖለቲካ ፈልቶ በገነፈለባቸው አገሮች ውስጥ ትልቁ ጥያቄ የአማራ ህዝብ የህልውና ስጋት አለበት ወይስ የለበትም የሚለው ጥያቄ ሳይሆን፣ የአማራ ህዝብ የሚያስበው ምን ብሎ ነው የሚለው ጥያቄ ነው።

እንደ ድርጅት ሲደራጅና ማኒፌስቶውን ሲጽፍ አማራን እንደጠላት የፈረጀው ህወሓት ማኒፌስቶውን ከጻፈ ከ17 አመት በኋላ ሥልጣን ላይ ሲወጣና አሁን ያለችውን በዘር የተከፋፈለች ኢትዮጵያን ዲዛይን ሲያደርግ አማራን ከፖለቲካው መድረክ ላይ አግልሎ ነው። የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ሁለተኛው ዙር ሲጀመርና፣ የህወሓት ኃይሎች ወደ አማራና አፋር ክልል ሲዘምቱ ከተናገሯቸውና እንደቃላቸው ተግባራዊ ካደረጓቸው ኃይለ ቃሎች ውስጥ አንዱ “ከአማራ ጋር ሂሳብ እናወራርዳለን” የሚል ነው። ጠሚ አቢይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡበት ግዜ ጀምሮ፣ ወለጋ፣አርሲ፣ሸዋና ቤኒሻንጉል-ጉሙዝ ውስጥ አማራው ህጻን፣ሽማግሌ፣ ወንድና ሴት ሳይለይ በግፍ ተጨፍጭፏል፣አሁንም እየተጨፈጨፈ ነው። እነዚህ ሁኔታዎች ናቸው አማራው የህልውና ስጋት አለብኝ ብሎ እንዲያምን ያደረጉት። እስኪ ይታያችሁ በአንድ በኩል አማራው በየቦታው በግፍ እየተጨፈጨፈ፣ በሌላ በኩል ደሞ መንግስት ጭፈጨፋውን ማስቆም ቀርቶ ጭራሽ የማስቆም ፍላጎቱም በሌለበት ሁኔታና፣ በተለይም ጭፍጨፋውን በቀጥታም በተዘዋዋሪም የሚፈጽሙት አካላት እስካፍንጫቸው በታጠቁበት ሁኔታ አማራውን ብቻ ነጥሎ ትጥቁን ለማስፈታት የሚደረገውን ሴራ አማራው እንዴት ሊቀበለው ይችላል?

ሌላው የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት የረሳውና ከግምት ውስጥ ያላስገባው የሰሜን ኢትዮጵያ ህዝብ በተለይ የአማራው ማህበረሰብ ከተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች ጋር ተያይዞ በረጂም ግዜ ቆይታው የገነባውን ከመሳሪያ ጋር በቅርብ የተቆራኝ ባህል ነው። አማራውን የህልውና ስጋት አለብኝ ብሎ ሲያምን ቀርቶ፣ ሙሉ በሙሉ ሠላምና መረጋጋት ባለበት ግዜም ትጥቅህን ፍታ ስንለው አግባብተን፣ ዋስትና እና ማበረታቻ(Incentive) ሰጥተነው መሆን አለበት። እንዲህ አይነት አሰተዋይነትና አርቆ አሳቢነት የተሞላበት አገር አድን እርምጃ ባለመወሰዱ፣ የጠሚ አቢይ መንግስት በንቀት በአንድ ወር እንጨርሰዋለን ብሎ ዘሎ የገባበት ጦርነት ዛሬ አመት ከመንፈቅ ሊሞላው ትንሽ ነው የቀረው።

ኢትዮጵያ በቀላሉ የማትወጣው የህልውና አደጋ ውስጥ ገብታለች ሲባል የህልውና አደጋ ውስጥ የከተተን የእርስበርስ ውጊያው ብቻ አይደለም። ከህወሓት ጋር የተደረገው ሁለት አመት የፈጀ ጦርነት ከ3000 አመት በላይ የዘለቀ ታሪክ አላት በምትባለው ኢትዮጵያ ውስጥ አብረው የዘለቁትንና ቋንቋ፣ባህል፣ሐይማኖትና ወሰን የሚጋሩትን የአማራና የትግራይ ህዝብ እንደ ጠላት እንዲተያዩ አድርጓል፣ አሁን ደሞ የአገር መከላከያ ሠራዊት አማራ ክልል ውስጥ የሚያካሄደው ውጊያ በሠራዊቱ ጭንቅላት ውስጥ ከማን ጋር ነው የምዋጋው የሚል ጥያቄ ፈጥሮ የመከላከያ አገራዊ ተቋምነት ትልቅ ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ አድርጓል። የአማራው ያለምንም መከልከል በየቦታው መገደል ምንም አይነት መንግስታዊና አገራዊ ቁጣ አለመፍጠሩ አማራው ካሁን በኋላ አማራነቴን ማዳን አለብኝ ብሎ ከኢትዮጵያዊነት ማማ እንዲወርድ አስገድዶታል። የኦሮሞ ብልጽግና ፓርቲ አገርን ያክል እጅግ በጣም ትልቅና ውስብስብ ክስተት ከኦሮም ጥቅም አንጻር ብቻ ማየት መጀመሩ አብዛኛውን ኢትዮጵያዊ ግራ አጋብቶት የርስ በርስ መተሳሰብንና ማህበራዊ ትስስርን አላልቶታል።

በቅርቡ በአለም አቀፍ ደረጃ የወጡ የተለያዩ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ኢትዮጵያችን በአንዳንድ አንደኛ መሆን አሳፋሪ በሆነባቸው ክስቶች የአለማችን መሪ ናት፣ አንደኛ መሆን በሚያኮራባቸው ክስተቶች ደሞ የአለማችን መጨረሻ ናት። ለምሳሌ፣ኢትዮጵያ failed States ከሚባሉ አገሮች ውስጥ የመጀመሪያዋ ናት፣ኢትዮጵያችን ደስተኛ ያልሆነና በተከታታይ ኃዘንና ስጋት ውስጥ የሚኖር ህዝብ በብዛት የሚኖርባት አገር ናት፣ኢትዮጵያ በአለማችን ውስጥ እጅግ በጣም ከፍተኛ ቁጥር ያለው የአገር ውስጥ ተፈናቃይና አገሩን ጥሎ የሚሰደድ ህዝብ ያለባት አገር ናት። ጋዜጠኞችን በማሰር፣ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት በመርገጥና በዘፈቀደ ግዲያ የአለማችን መገናኛ ሜዲያዎችና የመብትና የነጻነት ተሟጋች ድርጅቶች በተደጋጋሚ ከሚጥቅሷቸው አገሮች ውስጥ ኢትዮጵያ ቀዳሚዋ ናት። በዋጋ ንረት፣ በኑሮ ውድነት፣በድህነትና በወጣት ስራ አጥነት ቀዳሚ ናቸው ከሚባሉ አገሮች ውስጥ አንዷ ናት። ኢትዮጵያ በቀላሉ የማትወጣው የህልውና አደጋ ውስጥ ናት ስንል እነዚህን በተከታታይ የተጠቀሱትን ፖለቲካዊ፣ማህበራዊና ኤኮኖሚያዊ ኩነቶች ሁሉ ገምግመንና አስልተን ነው እንጂ የጠሚ አቢይ አህመድን አገዛዝ ስለምንቃወም ብቻ ወይም እንደ ብልፅግና ካድሬዎች በሉ ስለተባልን የምንለው የመላ መላ ወሬ አይደለም።

ዛሬ አማራው ብቻ ሳይሆን እራሱን ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ የሚጠራ ሰው ሁሉ ወንድ ሴት ሳይለይ ለምንድነው አማራ ክልል ውስጥ ጦርነት የሚደረገው ብሎ የጠሚ አቢይ አህመድን መንግስት መጠየቅ መጀመር አለበት፣ ለምንድነው እኔው እራሴ በከፈልኩት ግብር በተገዛ መሳሪያ የኔው የራሴ ወንድምና እህት የሚገደሉት ብሎ እራሱንም መንግስትንም መጠየቅ አለበት፣ከሁሉም በላይ ደሞ ለምንድነው አባቴ፣ወንድሜ፣ አጎቴና የአጎቴና የአክስቴ ልጆች በግድ እየተመለመሉ የራሳቸውን ወገን እንዲገድሉ የሚደረጉት ብሎ መጠየቅ አለበት። እያንዳንዱ የመከላከያ ሠራዊት አባል ለምንድነው ከ2013 እስከ 2015 ድረስ ከህወሓት ጋር ስንፋለም አብሮኝ ከጎኔ ቆሞ ከተዋደቀ ኃይል ጋር የምታዋጉኝ እያለ የቅርብ አለቃዎቹን መወትወት መጀመር አለበት።

በሌላው ወገኑ ላይ ግፍና መከራ ሲደርስና ኢፍትሃዊነት ሲፈጸም ዝም ብሎ የሚመለከት ኢትዮጵያዊ የሱ ተራ ሲደርስ የሚሟገትለት ሰለማያገኝና እንደዚህ አይነቱ ከሰው ልጆች ባህሪይ ውጭ የሆነ ዝምታ ደሞ ሁላችንንም ተራ በተራ የፋሲካ በግ ስለሚያደርገን፣ ነግበኔን አስበን ችግሩና መከራው ቤታችንን ከማንኳኳቱ በፊት፣ግፍ፣በደልና ኢፍትሃዊነትን በሌሎች ላይ ሲፈጸም ከተመለከትን ጥብቅና ልንቆምላቸው ወይም ልንደርስላቸው ይገባል። ይህንን ጽሁፍ የሚያነብ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ይህንን ሊንክ በመጫን ቭዲዮውን እንዲመለከት በኢትዮጵያ ስም እማጸነለሁ-

https://www.facebook.com/share/r/17tGXfJoDu/?mibextid=UalRPS

የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት እንደ ኮሎኔል መንግስቱ መንግስት የውርደት ካባ ተከናንቦ ከመፈርጠጡ በፊት፣ አማራ ክልል ውስጥ የጀመረውን ጦርነት አካታች፣ነጻ፣ ግልጽና ለተግባራዊነቱ ዋስትና በሚሰጥ ድርድር መፍታት አለበት። ጠሚ አቢይ ፓርላማ በቀረቡና ማይክሮፎን ፊታቸው ላይ በተደቀነ ቁጥር የበለጸገችና የግዛት አንድነቷ የተጠበቀ፣ የባህር በር ያላት ጠንካራ ኢትዮጵያን እውን እናደርጋለን እያሉ  የሚወተዉቱን ነገር ከልባቸው ከሆነ፣አማራው በግንባር ቀደም ያልተሳተፈባት ጠንካራ ኢትዮጵያ ኖራ አታውቅም፣ ወደፊትም አትኖርምና፣መጀመሪያ ከራሳቸው ህዝብ ጋር የገቡትን ጦርነት ማቆምና ከአማራ ኃይሎች ጋር ያላቸውን የፖለቲካ ልዩነት በውይይት ለመፍታት አስፈላጊውን እርምጃ ሁሉ መውሰድ አለባቸው፣ እስካሁን ለደረሰው ጥፋትም የኢትዮጵያን ህዝብ በተለይም የሳቸውን ያለፉት አምስት አመታት የተሳሳተ የፖለቲካ ስሌት ገፈት ቀማሽ የሆነውን የአማራ ህዝብ በግልጽ ወጥተው ይቅርታ መጠየቅ አለባቸው። ከዚህ ውጭ ሰሞኑን በየማህበራዊ ሜዲያው በሚዘዋወረው ቪዲዮ ላይ የሚታየውን አይነት አሰቃቂ ወንጅል እየፈጸሙ ህዝብን ከህዝብ ጋር ለማጋጨትና ለማባላት የሚደረገው ሙከራ ኢትዮጵያን ያፈርሳት እንደሆን እንጂ እንኳን ጠንካራና የበለጸገች ኢትዮጵያ ሊፈጥር፣ አሁን በመንገዳገድ ላይ የምትገኘውን ኢትዮጵያም ከውድቀት ማዳን አይችልም።

አንዳንድ ነገሮችን በግልጽ መናገር ያለብን ይመስለኛል። ወታደራዊው ደርግ የሶማሊያን ተስፋፊዎች ካሸነፈና ኢህአፓን ከየከተማዎቹ ካጸዳ በኋላ እስከ ግንቦት 1981ዱ መፈንቅለ መንግስት ድረስ ተደላድሎ ኢትዮጵያን ገዝቶ ያሰኘውን ሁሉ ማድረግ ችሏል። ህወሓቶች ከጠቅላላው የኢትዮጵያ ህዝብ 5% የማይሆን ህዝባዊ መሠረት ይዘው ነው የዛሬዋን በዘር የተሸነሸነች ኢትዮጵያን ብቻቸውን ፈጥረው 27 አመት ሙሉ ቁም ስቅላችንን ያሳዩን። ዛሬ የኢትዮጵያን ፖለቲካ የሚዘውረውን ኃይል እንደ ደርግና ህወሓት እንዲደላደል ግዜ ከሰጠነውና ከተደላደለ በ30 እና በ40 አመት የምንገላገለው ኃይል አይደለም። ይህንን ያለፈውን የኢትዮጵያ ታሪክ በምሬትና በክፋት አይን ብቻ የሚመለከት፣ያየውንና ያለፈበትን ሁሉ የኔ ነው የሚልና ኢትዮጵያን በኔ አምሳያ እንደገና መፍጠር አለብኝ ብሎ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የ19ኛውን መቶ ክፈለ ዘመን እሳቤ ይዞ የተነሳ ኃይል እንኳን ተደላድሎ ኢትዮጵያን እንዲገዛ አንድ ቀንም ብቻውን የኢትዮጵያን በትረ ሥልጣን እንዲቆጣጠር መፍቀድ የለብንም። ኢትዮጵያ ውስጥ ከብልፅግና በኋላ አንድ ብሔር ወይም የአንድ መንደር ልጆች ተሰባስበው የፖለቲካ ሥልጣን ላይ እንዲወጡ መፍቀድ የለብንም። ኢትዮጵያ የሁላችንም አገር ናት፣ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሥልጣንም ሁላችንም የምንጋራው መሆን አለበት። ይህ ሥልጣን መጋራትና ኢትዮጵያን እኩል የሁላችንም አገር ማድረግ ግን በቀላሉ አይመጣም፣ አሁን እየተጓዝን ባለው መንገድም አይመጣም!

ይህንን ጽሁፍ የሚያነብ ሰው ታዲያ ኢትዮጵያን ፍትህ፣ነጻነትና ዲሞክራሲ የሰፈነባት የእኩሎች አገር ማድረግና ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ሥልጣን መጋራት እንዴት ነው የሚመጣው የሚል ጥያቄ ሊያነሳ ይችላል። ትክክለኛ ጥያቄ ነው። ብሩህና አደርጋለሁ የሚል ብርታትና ጥንካሬ ያለው አዕምሮ ሲጨነቅና ሲጠበብ መልካም ነገር ይወልዳልና፣ ይህንን እንዴት ነው የሚለውን ጥያቄ ማንሳትና ጥያቄው በእያንዳንዳችን አዕምሮ ውስጥ እንዲጸርጽ ማድረግ የዚህ ጽሁፍ ተቀዳሚ አላማ ነው።

 

 

1 Comment

  1. አቶ ኤፍሬም አንተ ገጽ ላይ ለጠፍኩ ብዬ በፎቶግራፉ ተመሳሳይነት እላይ ጠገናው ጎሹ ላይ ለጥፌዋለሁ።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
Go toTop