“ጣልያንም መጣ፤ ሄደ ተመለሰ፤
እንግሊዝም መጣ ሄደ ተመለሰ፤
ግብፅም ከጀለ ሄደ ተመለሰ፤
ህወሓትም ካደ፤ ሄደ ተመለሰ፤
ማን ቀረ ኢትዮጵያን እያተራመሰ?”
ቅይጥ ጥቅስ
ስለ ውክልና ጦርነት አደገኛነት በተከታታይ ሳቀርብ የነበረውን ሃተታና የመርህ አቅጣጫ ለጊዜው ወደ ጎን ትቸዋለሁ። የማፈቅራትና የምሳሳላት ትውልድ ሃገሬ ኢትዮጵያ ለአማራው ሕዝብ ሲዖል እና የእልቂት መናኸርያ ሆናለች። እንኳን ኢትዮጵዊ ነኝ ለሚል የሰው ፍጥረት ቀርቶ መላውን ዓለም የሚያሳዝን፤ ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን አሳፋሪ እልቂት እየተካሄደ ነው።
ተስፋ ያላት ኢትዮጵያ ሁሉን አሳታፊ፤ በሕግ የበላይነት የሚመካና የሚገዛ፤ ግልጽነት፤ ሃላፊነትና ተጠያቂነት የሚያንጸባርቅ የመንግሥት አመራር የላትም ለማለት የሚያስደፍር ገጽታ ታሳያለች። ያለ ጉቦ፤ ሙስናና አድልዎ የሚሰራ አንድም ነገር የለም ለማለት እደፍራለሁ።
ለመሆኑ መንግሥት አለ ወይንስ የለም? የሚለው ጥያቄ አግባብ አለው። ከዚህ በላይ ግን እኔን የሚያሳስበኝና የሚያሳዝነኝ፤ እኛ ኢትዮጵያዊያን እንዴት እንደዚህ ጨካኝ ሆንን? ይህችን ታሪካዊና ገና ያልተዳሰሰ እምቅ ኃብት ያላትን አገር ወደ የት እየወሰድናት ነው? የሚለው ጥያቄ መመለስ አለበት።
ይህ ሃተታ ስለ ዘውጋዊው የፌደራል ስርዓት ትችትና አማራጭ ለማቅረብ አይደለም (The imperative of reforming ethnic-federalism). ሃተታየና ትችቴ የዚህ ዘውጋዊ ስርአት የአገዛዝና የአስተዳደር አሳፋሪነት፤ አጥፊነት፤ ሙሰኛነት፤ አድሏዊነት፤ ጸረ-ሰላምነት፤ ጸረ-አብሮነት፤ ጸረ-ብሄራዊ አንድነት፤ ጸረ-የህግ የበላይነት እና አገር አፍራሽነት ፍጹም አደገኛ ወደ ሆን ደረጃ ተሸጋግሯል የሚል ነው።
በአሁኑ ወቅት፤ ማንም ሊክደው በማይችልበት ደረጃ እጅግ የሚዘገንን ዘውግ ተኮር እልቂት በአማራው ሕዝብ ላይ እየተካሄደ ነው። ከታች እንደሚታየው እናቶች፤ ልጆች፤ ዘመድ አዝማዶች እያለቀሱ ነው። በአጠቃላይ ስገመግመው የዐማራ ሆነ፤ የኦሮሞና ሌላ፤ በአገር ደረጃ ራሱን ኢህአዴግን ተክቻለሁ ብሎ የሚጠራው የብልፅግና ፓርቲ፤ የኦሮምያ ብልፅግና ፓርቲ፤ የዐማራ ብልፅግና ፓርቲና ሌሎች ባለሥልጣናት ይህንን የሚዘገንን የአማራ ሕዝብ እልቂት ሲያወግዙ፤ ገዳዮቹን በማያሻማ ደረጃ ሲያሳድዱና ለፍርድ ሲያቀርቡ አይታይም። ታሪክ ግን ባለሥልጣናቱን እንደሚፋረዳቸው አልጠራጠርም።……..ሙሉውን ያንብቡ – የወለጋ እልቂትና የፌደራል መንግሥት ተጠያቂነት.docx
—