እንዳነበብሁትና እንደተረዳሁት ከሆነ፣ ዕርቁ ወያኔን ከጣረ ሞት ነው ያዳነው። ፕሮፌሰር ኀይሌ ላሬቡ
ወያኔ ከባድ ጦር መሣርያውን ለማእከላዊ መንግሥት ያስረክብ ቢባልም፣ ድርጅቱና አባላቱ በምንም መልኩ አልተነኩም ብቻ ሳይሆን፣ በሁለቱ ፀረ ኢትዮጵያ በነበሩ ድርጅቶች ማለትም ወያኔና ኦነግ የተጻፈውና ኢትዮጵያን ማፍረስ የመጨረሻ ግቡ የሆነው ሕገመንግሥት ዓለምዐቀፍ ዕውቅና አግኝቶ ቁጭ ብሏል። ወያኔም ካልፈቀደ ማንም ንክች አያደርገውም፤ አይሞክረውም። ባንድ ቃል ወያኔና ኮተቱ ሕያው ሁነዋል ብቻ ሳይሆን ለዋስትናቸው ዓለምዐቀፍ ጥበቃም ጭምር ተሰጥቶዋቸውል። ሐቁና ጭብጡ ይኸ ሁኖ ሳለ፣ ያ ሁሉ የመንግሥትና የማኅበራዊ መገናኛ ጋጋታና ማጀላጀል ፋይዳው ምን እንደሆነ አይገባኝም።
ኀይሌ
እዚህ በዝርዝር መናገር ቦታው አይደለም። በሰፊው ለመናገር ለየት ያለ ስብሰባ ያስፈልገው ይሆናል። ግን በአጭሩ ማለት የምፈልግ ነገር ቢኖር፣ ኂስም ነቀፈታም ይሁን፣ በጭፈናና በስሜት ተመርኲዞ ሳይሆን በተጨባጭ ማስረጃና በመሬት ላይ ካለው ነባራዊና ግልጽ ሁናቴ በመነሣት ካልሆነ ፋይዳ ቢስ ናቸው። እኔም አሳቤን የሰጠሁት ከዚህ ተጨባጭ ሁናቴ በመነሣትና፣ ያለፉትን ግንዛቤዎች በመንተራሰስ እንደሆነ ሊሰመር ይገበዋል።
እኛ ኢትዮጵያውያን በስሜትና በምኞት የመመራት፣ በውጭ ኀይል ዋስትና የመተማመን ዝንባሌ አለን። ካንድ ተጨባጭ ሁናቴ ልጀምር። ቅንጅትና ወያኔ ከተወዳደሩበት የምርጫ ወቅት ቀደም ሲል፣ አንድ የቅንጅት ከፍተኛ መሪ ወደአካባቢዬ መጥቶ ነበርና፣ በአንድ ስብሰባ ላይ፣ አሁን እየታየ ያለውን ሁናቴ እግምት ካስገባነው ቅንጅት እንደሚያሸንፍ አያጠራጥርምና፣ ወያኔ ሥልጣኑን አልለቅም ቢል፣ ድርጅታችሁ ያወጣ ዕቅድ አለወይ ብዬ ለጠየቅሁት ጥያቄ፣ የኋላ ኋላ የተሰጠኝ “ከፍተኛ የምዕራባውያን ግፊት ስላለ፣ ኢሕአዴግ ከተሸነፈ በኋላ፣ ደፍሮ ሥልጣን አልለቅም ሊል አይችልም” የሚል መልስ ነበር። ነገሩ እጅግ ገርሞኝና ከንክኖኝ፣ በትምህርታቸው የመጠቁ ናቸው ይባሉ የነበሩት የቅንጅት መሪዎች፣ ምን ዐይነት የጅላጅሎች ስብስብ ነው እስከማለት አደረሰኝ ብቻ ሳይሆን፣ ከዚያ በኋላ ምንም ዐይነት ተስፋም እንደሌላቸው ደመደምሁኝ። ይሁንና ሁላችንም የቅንጅት ታሪክና መጨረሻ ምን እንደሆነ በደምብ ስለምናውቅ እዚህ ላይ መድገም አስፈላጊ አይመስለኝም። እዚህ ላይ ኢብን ካልዱን የተባለው ታላቅ አፍሪቃዊው የታሪክ ፍልስፍና ሊቅ፣ “ምሁራን የማይረቡ ፖለቲከኞች ናቸው” ያለውን አስታወሰኝ።
የአሁኑ ድርድር ችግሩ በሰላም እንዲፈታ ሁለቱንም ጐባኖች ወደስምምነት ማምጣቱ የሚወደስ ቢሆንም፣ ታሪክ በተከታታይ የሚነግረን ጉዳይ ቢኖር ለሕወሓት ድርድር “ሠርጉና ምላሹ” ብቻ እንደሆነ እንጂ ምንም ዐይነት ትርፍ እንደሌለው እንደሆነ የማይካድ ሐቅ ነው። ስለዚህም ኢትዮጵያን በሕይወት አቈያታለሁ የሚል መንግሥት፣ ወደድርድር የሄደው ድርጅቱ ራሱን እንደተመታ እባብ እየጣረ ባለበት ወቅት መሆኑ እጅግ ያስገምታል። ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ደምስሶት እንደመገላገል፣ ይልቅስ የአገሪቷ ህልውና ራሱ በጣሩ እንዲቀጥል ወስኗልና። በዚህ ተግባሩ መንግሥት ያሳካው ጉዳይ ቢኖር፣ የኢትዮጵያን ህልውና እከፍተኛ ዐደጋ መጣልና ደጋግሞ ከስሕተቱ የማይማር አለመሆኑን ብቻ ነው ለማለት የማያስደፍር ምክንያት የለም። ሁለቱም የኢትዮጵያን ሕዝብንም ሆነ አገሪቷን የሁለትዮሽ የፖለቲካ መጫወቻ ኳስ ሜዳ ከማድረግ ውጭ ሌላ ዓላማ ያላቸው አይመስሉም።
በኔ ዕይታና ምርምር መሠረት፣ የትግራይም ሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጣሩ የሚያቆመው፣ ከዚህ በፊት እንዳልሁት፣ አሁንም እደግመዋለሁ፣ ወያኔና ኰተቱ፣ ከነዝግንትሉ፣ ማለትም ለእኩይ ዓላማው ሲል ከፈጠራቸው ሕገመንግሥትና ክልል ከነአርማቸው ከኢትዮጵያ ምድር ወደማይመለሱበት ዓለም ሲሸኙ ብቻ ነው። መንግሥት ግን የመረጠው ወያኔን ለማስደሰት፣ የኢትዮጵያንና የኢትዮጵያውያንን ጣር አለቅጥ ለማራዘም ብቻ ነው ከማለት ውጭ ሌላ ምን ሊባል ይቻላል። ለወያኔ ድርድር ሠርግና ምላሹ ነው ብያለሁ። ሲደክም ይደራደራል፤ እንዳገገመ ደግሞ እኩይ ዓላማውን ለማሳካት ትግሉን በማጧጧፍ ይቀጥላል። የድርጅቱ ዓላማ ደግሞ ምን እንደሆነ በማያፋልም መንገድ በግልጥ በጽሑፍ ተከትቦ ሰፍሯል። ይኸውም፣ በገሃድ ከአገሪቷ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በመተባበር እናት አገሩን ከመውጋትና ከማዳከም ዐልፎ ተርፎ፣ ኢትዮጵያ የምትባል አገርና ኢትዮጵያዊ የተባለ ሕዝብ የለም ማለት ብቻ ሳይሆን፣ ይኸንን ምኞቱን ለማሳካት ሲል ሕዝቡን በጐሣና በሃይማኖት ከፋፍሎ የመንደር ጉጅሌና (ፓርቲ) መንግሥት አቋቁሞ፣ ሕገመንግሥት ቀርጾ፣ አገሪቷን ለማፈራርረስ በተቀናጀ ሁናቴ ትግሉን ማፏፏም ነው። መንግሥት በዓለም መድረክ ያጸደቀውም ይኸንኑ ዓላማና ሰነድ ነው። ያደረገው ለሕዝብ ጥቅምና ብልፅግና፣ ለአገር ልዕልና፣ ለሠራዊቱ ውክልና የቆመ መንግሥት ነው ከተባለ ጤንነቱ መጠየቅ አለበት ለማለት ሁናቴው ያስገድዳል ባይ ነኝ።
ኀይሌ