ሲና ዘ ሙሴ
ይኽ አገር በቢሮክራሲ ረገድ ሥርዓት የማይከበርበት ፣ ሥርዓት አክባሪ የሚናቅበት ፣ የሚበሻቀጥበት ፣ ፋራ ፣ ያልባነነ ፣ ሠገጤ ወዘተ ። የሚሰኝበት ፣ አገር እየሆነ በመሄድ ላይ ነው ። ያሳዝናል ። በቢሮክራሲ ረገድ ጨዋነት ፣ ጠንከራ ለፍትህ የመገዛት አቋም ፣ ለህግ የመገዛትና ህጉን አክብሮ በሥርዓት መኖር ፣ ሌባ ጥዩፍነት ፣ ሥርቆት ጠልነት ፣ ቀጣፊን ናቂነት ፣ አታላይና አጭበርባሪን አግላይነት እና ጠቋሚነት ፣ አሉባልተኛን እና ነገር ጎንጎኝን ኮናኝነት እና አጋላጭነት እያከተመ በመሄድ ላይ ነው ። በአገር በመደሩ ሁሉ ቀጣፊ ነግሶል ።
በየመንደሩ ፣ በየጎጡ ፣ ሌባና ቀጣፊ ብልፅግናንን ተገን አድርጎ ፤ የእርስ በእርስ ጦርነቱን ምሽግ አድርጎ ይፈነጫል ። በመከላከያ እና በሚሊሻ ሥም ” ገንዘብ ውለዱ ፣ በአይነት አዋጡ ። ወዘተ ። ” እያለ በግላጭ ይዘርፋል ። ያለ ህጋዊ ( በገቢዎች ባልታወቀ ደረሰኝ )፤ ያለ አንዳች ህጋዊ አካሄድ ፣ ከየመንደሩና ከነጋዴው ላይ ብር ይወስዳል ። በጠራራ ፀሐይ ከህዝቡ ከተሰበሰበው ከግማሽ በላዩ ለግል ጥቅም ይውላል ።
ይህ ህገወጥነት በግላጭ ና በጠራራ ፀሐይ እየተፈፀመ በግላጭ እየታየ ፣ ከፍተኛ አመራሩ አጥፊውን መካከለኛ አመራር ባላየ ያልፈዋል ። መካከለኛ አመራሩም ዝቅተኛ አመራሩን ዘረፋህን አጠናክረህ ቀጥል ይለዋል ። በተዋረድ ሌባ እርስ በእርሱ ይደጋገፋል ። ልቅ ያደረገውን ከፍተኛ የመንግሥት አመራር በማወደሥ መልካም አሥተዳደር እንዳይሰፍን በኔት ወርክ ይደራጃል ። በሥራው ብልፅግናን አፈር ድሜ እያሥጋጠ በአፉ “ብልፅግናዬ ! የእኔ ፓርቲ ! ልዘርጋልህ ፣ ልነጠፍልህ … ፣ መሬት አይንካህ “ በማለት እየፎገረ ፣ የቀበሌ መታወቂያ ሳይቀር ከፓስፖርት እና ከቪዛ የበለጠ እንዲታይ እና በሺ ብሮች እዲቸበቸብ ያሻጥራል ። በዚች ጥቂት ጉዳይ ሰበብ እንኳን ህዝብ መንግሥትን ሲረግም ይደመጣል ።” መንግሥት የለም !” እያለም ያማርራል።
የመንግሥት የለም ጩኸት በኦሮሚያ ውሥጥ በሁሉም ከተሞች እጅግ በርክቷል ። በአዳማ ደግሞ ብሷል ። በአዳማ ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ ህዝብ የትራንሥፖርት እጥረት እንዲያጋጥመውና የበለጠ መንግሥትን እንዲጠላ ተደርጓል ። በቂ የህዝብ ማመላለሼ አውቶቢስ ሳያዘጋጅ ባጃጆች ኗሪውን ወደሥራው እና ወደትምህርቱ ብሎም ወደየጤና ተቋሙ እንዳያደርስ ተደርጓል ። መኪና በሌለው ደሃ ዜጋ ላይ የማሰቃያ ና የማበሳጫ ጦርነት ተከፍቷል።
ህዝብ ቢጮኽ ሰሚ የለውም ። ህዝብ ቁራ ሆኗል ። እያንዳንዱ ክ/ከ የሚሊሻ / የታጣቂ ምልመላ እና ለመለመለው ታጣቂ ሥንቅ ከህዝቡ አንገቱን አንቆ አመጣ ይላል ። ለምን የመደበኛ ፖሊሥ ምልመላ በሰፊው እንደማይካሄድ አይገባኝም ። ህገወጥ አደረጃጀት ነው ህጋዊ አደረጃጀት ለዚች አገር የሚያሥፈልገው ? አንዳችም ህጋዊ ከለላ የሌለው ፤ የመከሰስም ሆነ የመክሰስ መብቱ ያልተረጋገጠ ፤ አንዳችም ህጋዊ ቀጠሪ ተቋም የሌለው ታጣቂ እና ሚሊሻ በከተማ ጥበቃ ላይ ማሠማራት ከህግ አንፃር ምን ማለት እንደሆነ በወጉ የተማሩትን የህግ ባለሙያዎች መንግሥት ጠይቆ ይረዳ ። ዛሬ በአዳማ ሰው ተጣልቶ ለመገላገል ገብተህ ታጣቂ ከደረሰ አንተንም ጨምሮ በጥፊ እና በእርግጫ እየነረተህ ፖሊሥ ጣቢያ ካደረሰህ በኋላ እዛም ሄደህ በእልህ እና በንዴት ባለማልቀስህ “ ፈጣጣ ! ደሞ አያለቅስም ። “ ተብለህ ከሥንት ውትወታ በኋላ በተደባዳቢዎቹ ምሥክርነት ከእሥር ትለቀቃለህ ። ይኽንንም ግፍ ይወቅ ። ሥርዓቱ ከጎሣ ፖለቲካ እሥካልወጣ ጊዜ ድረሥ ነገ የህዝብን ሠላም የሚያደፈርስ ጊዜውን ጠብቆ የሚፈነዳ የዘረኞች ቦንቦ በኦሮሚያ ክልል በሁሉም ከተሞች እንደተጠመደ ከወዱሁ ይረዳ።
መንግሥት ሆይ ! ዛሬም በዚህ በዘመነ በ21 ኛው ክ/ዘ ውሥጥ ሆነን ፣ ቋንቋ አምላኪና ለጀርመን ቅኝ ገዢዎች ፊደል አርጋጅ ና ሠጋጅ መሆናችን ተገቢና ትክክል ነው ወይ ? የቀኃሥ ጊዜ የጨቋኝና የተጨቋኝ ፣ የቆዳ ማዋደድ ፊውዳላዊ ድርጊት ተባብሶ መቀጠሉሥ የዚችን አገር ልማት አፍራሽ ወይም አደናቃፊ አይሆንም ወይ ? ይህን አገር አፍራሽ መንገድ ህዝብ ሳይሆን ጥቂት በህዝብ ሥም የሚነግዱ ግለሰቦች እንደፈጠሩት እና ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ እንዳስፋፉት ግንዛቤ አለ ወይ ? ክልል በራሱ አጥር እንደሆነና አግላይ ፖለቲካዊ ሂደቱስ ዜጎችን የማያቀራርብ እንደሆነ በብልጽግና መንግሥት ይታወቃል ወይ ? ይህ ከታወቀ እና አንድነት በአንድነት ፓርክ ብቻ ከቀረ ጦሱ ለአንድነት እና ለወዳጅነት ፖርክ ብቻ አይሆንም ። እናም መንግሥት ዛሬውኑ ሊነቃ ግድ ይለዋል ። መቼም በመንግሥት ውሥጥ ያሉ ባለሥልጣናት በሙሉ ሥለህግና ፍትህ ደንታ የሌላቸው የለየላቸው እንቅልፋሞች ናቸው ብሎ መደምደም ተአማኒነት ባይኖረውም ጥቂት ቱባ ባለስልጣናት ግን በጥጋብ እያንኮራፉ እነደሆነ የአደባባይ ምስጢር ናት።
በእርግጥ በምቾት ብዛት ያንቀላፉ ጥቂት አይባሉም ። በእነዚህ እንቅልፋም ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች ሰበብም ፣ በተዋረድ የተፈቀደላቸው ሌባ የመንግሥት ባለሥልጣናት ( ፊውዳሎች ) በርክተዋል። አለአንዳች ይሉንታ ሥልጣንን መከታ አድርገው በጠራራ ፀሐይ የሚዘርፉ ። በከበርቴነትም የሚደላቀቁ ። በአጭሩ ወደላይ የሚሸኑ። በዚህ አሥጠ ፣ ዲሲፕሊን አልባ የእንቅልፋሞች አመራር ሰበብም ፣ ህዝብ ከቀበሌ ጀምሮ ሥርዓትና ህግን በማይከተልና በማያከበር ቢሮክራሲ እጅግ ተማሯል።
ቀልቡ የተከፈለው ሆኖም ያላንቀላፋው መሪው መንግሥት ( የፌደራሉ ) በወያኔ ጦርነት ሰበብ በዝባዥ ክልላዊ ቢሮክራሲውን ለማየት ዓይኑ አልቻለም ። የወያኔ ወከባና የአሜሪካና የአጋሮቿ ጫና አይኑንን የጋረደውም ይመስላል ። እናም በዚህ እውነታ ተተግኖ ከቀበሌ እሥከ ክልል ያለው ፣ በመንግሥት ጉያ የተሸጎጠ ሌባ ሁላ እልል በቅምጤ እያለ ዘረፋውን አጧጡፏል ። በህዝቡ ውሥጥ ቁጭት ፣ ንዴት ፣ የመገፋት ፣ የመገለል ድባብ ነግሶል ። “ብቻ ይኽ ጦርነት ይለቅ እንጂ የብልፅግናንም ፍፃሜ እናያለን “ ከማለት ውጪ ተቃውሞ ማሰማት አልቻለም ። በምን አንጀቱ ? “ እዬዬም የሚያምረው ሲደላ ነው ። “ ልክ እንደ ቲክ ቶኮች ። ሥቆቃዊ እና ጥዩፍ የሆነ ሞራለ ቢሥ ድርጊትና ቃላት በእንጪጭ ዩቲዩበሮች እንደ ቀልድ በቲክ ቶክ ይደለቃል ። ጥቂት የማይባለው ፋራ ትውልድም በማያሥቀው ይገለፍጣል ። ኢትዮጵያን አንድ እብድ “ ጋለሞታ “ አለት ህዝቧንም “ እጓለሞታ “ አለው ። ብለህ መቆጨት ሲገባህ እንዴት የአንድ እብድን ከንቱ ሃሳብ ታሥተጋባለህ ? ጥቂት የማይባለው ዘመነኛውና የነቃው “ አራዳው ትውልድ “ እንዴት ይታዘበኛል አትልም ? እሥቲ በአራዳው በባነነው ትውልድ ቋንቋ ልንገርህ …
“ እያንዳንዳችን ከሞትን በኋላ አፅማችን ብቻ ሲቀር የአንዳችን አጥንት ከሌላችን በምንም ላይለይ ፣ ዛሬ ባለን መልክና ቋንቋ በግብዝነት በመመፃደቅ ፣ የቅኝ ገዢዎችን የከፋፍለህ ግዛ መርህ ለማሥቀጠል ፖለቲከኞች አውቀውም ሆነ ሳያውቁ በተዘፈቁበት ሤራ ጥቂት የማንባለው የሥሜታችን ተገዢዎች እሥከ አንገታችን በክፋት ባህሪ ውሥጥ መሥጠማችን ፋይዳው ምንድነው ?
መከላከያው የኢትዮጵያን መልክ ይዞ ሥለኢትዮጵያ ሲዋደቅ ፣ እዚህ ብልፅግና ሥለ ዘመነ ከፋፍልቲ የቋንቋ ከበሮ መደለቅ ነበረበትን ? የእርሱን ቋንቋ ጨቋኝ በማድረግ ያልተቋረጠ ጅብነቱን ለማንበር መቀላመድስ አግባብነት አለውን ? ሰውን ሳይሆን ፣ ዜጋን ሳይሆን ቋንቋን ማሥቀደም ለዘመነኛው ትውልድና ለዘመነው ዓለም ይመጥናል ወይ ?
_ ቋንቋህ ቋንቋዬ ነው ፤ ዘርህ ዘሬ ነው ። … አንተ ታላቅ ነህ ። ሌላው ውዳቂ ነው ። ፈሪ ነው ። መሞት እንጂ መግደል የማይችል ነው ። ቧቅቧቃ ነው ።
_ የእኔ ዘር ሴጣን የማይወዳደርህ አረመኔ ነህ ። አንገት ቆራጭ ነህ ። የእርጉዝን መሐፀን ዘርጋፊ ነህ ። ሰው በላ ነህ ።
እያለ አገር ሲዖል እንድትሆን ይኽን መንጋ ህዝብ ለጥፋት ማነሳሳት የእብድ ሰው ተግባር አይደለም ወይ ?
በነገሬ ላይ ዛሬ በየከተማው በዘረፋ ገንዘብ ፣ ሥጋ እና ቢራ ልቡን የደፈነው ። ጫት እና አረቄ ያደነበሸው ትውልድ እልፍ አእላፍ እንዲሆን ያደረገው ይኸው ሥርዓት ዓልባው “ የአትድረሱብኝ ፣ እራሴን በራሴ እንደፈለገኝ ዋልጌና ጨምላቃ ሆኜ አሥተዳድራለሁ ክልሌ ነው ። ምን አገባችሁ ። …” የሚል የጥቂት ፊውዳሎች ፀረ ዜግነት የዘመነ ከፋፍልቲ አሥተሳሰብ ነው ። ወያኔዊ የቋንቋ ፖለቲካ ነው ። በቅኝ ገዢዎቹ የተጠመደው ቦንብ ፍንዳታ ነው ፤ እንዲህ አገርን የሚያተራምሰው ።
ዛሬ የፖለቲካው አማርኛ “ የእኔ ጅብ ይብላኝ “ ሆኗል ። “የእኔ ጅብ ይብላኝ ። “ የሚሉት አማርኛ አገር አውዳሚ ነው ። ትላንት ወያኔ አገረ መንግሥቱን ሲያሥተዳድር ፣ ጥቂቶች እየበዘበዙ መላው ትግሬ እንደሚበዘብዝ ያህል በመቁጠር በሥሜት በመነዳት ጥቂት የማይባሉ የትግራይ ዜጎች “ የእኔ ጅብ ይብላኝ ። “ ብለው ነበር ። ይኸው ዛሬ በተግባር እየበላቸው ነው አውራው ብልፅግናም ፣ በኢህአዴግ አጥር ውሥጥ ሆኖ ፣ በኢህአዴግ የመዋኛ ገንዳ እየተቦራጨቀ የቸከ የለውጥ መዝሙር እየዘመረ ፣ ከፈረሱ በፊት ጋሪውን አሥቀድሞ ፣ በቀቢፀ ተስፋ አሸሸ ገዳሜ እያለ ነው ። ከፖለቲካው አንፃር ሲፈተሽ ።
ከፖለቲካው አንፃር ታጭዶ የተከመረው የብልፅግና መልካም የ ቲዎሪ ፍሬ ሌቦች ከሥር ከሥር እየወሰዱ ፣ በፍሬው ነግደው አትርፈውበታል ። (ጠቅላዩ እና ባለቤታቸው ለሚታይ ለውጥ እየጣሩ ነው ። በአንፃሩ ደግሞ አገር ለማፍረስ ፣ አገር ለመሸጥ ከጎናቸው ሆነው የሚያሤሩ ጥቂት አይደሉም ። ) አሁን እና ዛሬ ብልፅግና እንደ ፓርቲ የለም ማለት ይቻላል ። ያለው ኦህዴድ ነው ። ያለው ብአዴን ነው ። ያለው ሲዳማ ነው ። ያለው ሱማሌ ክልል ነው ። ክልል ። ክልል ። ብቻ ። ብልፅግና ፓርቲ ብሎ ነገር የለም ። እንደ ቀድሞው ኢህአዴግ እንኳን እነዚህን ጠርንፎ በማዕከል ማሥተዳደር አልቻለም ። ወሳኝ አካላቸው ሳይሆን ተቀጥያ አካላቸው እንደሆነ በግልፅ እየታየ ነው ።
በራሱ ፓርቲ ውሥጥ ህልውና ያጣ እና ፍፁም ዲሲፕሊን አልባ ፤ የእዝ ሠንሰለት ብሎ ነገር የሌለው ፓርቲ ብልፅግና ነው ። በእውነቱ ጠ/ሚ አብይ ( ዶ/ር ) ወታደር ባይሆኑ ኖሮ ፓርቲው አንድ ቀንም መንገሥ ባልቻለ ነበር ። ይሁን እንጂ ጠቅላዩ እርሳቸው በሚያውቁት የቋንቋ ክልላዊ ድርጅቶቹ በማያውቁት መንገድ መከላከያውን ይዘው ብልፅግናንን እየመሩት ነው ። ከጦርነቱ ማብቃት በኋላ ሰውየው ምን እንደሚፈጥሩ አናውቅም ። የከተማው ፖለቲካ ግን እጅግ የተበሻቀጠ እና የሆዳሞች መሰባሰቢያ እንደሆነ ከደህንነት ሹሞቻቸው የተሰወረ አይሆንም ።
የሥርዓት ማጣቱ በፊደራል ዩኒቨርሰቲዎች ውሥጥም እንዳለ አያውቁም ማለት አይቻልም ። ከምግብ ከመጠለያ ከመፀዳጃ ቤት አንፃር እንኳን ብንቃኝ ፣ እጅግ የሚያሥመርሩ እና “ የተማረ ሰው በሥርዓት የሚኖርበት አይደለም እንዴ ?! “ የሚያሰኙ እውነቶች በአንዳንድ የፊደራል ዩኒቨርስቲዎች ይታያሉ ። ይኽ የሆነው እራሳቸውን እንኳ ማሥተዳደር የማይችሉ የፖለቲካ ሹመኞች ዛሬም በየትምህርት ተቋሙ በከፍተኛ የኃላፊነት ወንበር ላይ ሥለተቀመጡ ነው ።
በኢትዮጵያ በየተቋሙ ተጠያቂነት የሌለው አሠራር ሥለተንሰራፋ ከቀበሌ ጀምሮ ያለው ፣ ትንንሹ ሹም ሳይቀር ፣ የግል ምቾቱን በመንግሥት ሀብት ፣ በሀገር ሀብት እና የህዝብን መቀነት በመፍታት እያደላደ ነው ። በዚሁ አግባብ ምድረ ሌባ ነው የተማሪን ምግብ ለየዩኒበርስቲው የሚያቀርበው ። ቢፈልግ ሸክላ የተቀላቀለበት በርበሬ ፣ አፈር እና አሸዋ የተቀላቀለበት ጤፍ ከበቆሎ ጋር ቀላቅሎ በማሥፈጨት ለተማሪ ያቀርባል ። ( ተፈታኞቹን ሥሟቸው እሥቲ ? የዩኒቨርስቲው ወጥ እና እጀራ ምን አይነት ነው ? ወይሥ ራቁቱን ለተወለደ ልጅ ጥብቆ መች አነሰው ነው ። ነገሩ ። )
ነገሬን ሥደመድም ፣ በማንኛውም የመንግሥት ተቋም ሌብነት እና ዲሲፕሊን አልባነት ሰፍኗል እና በዚህ አሥረአንደኛ ሠዓት ካልታረመ የወያኔንን ግብዓተ መሬት ብንፈፅምም የብልፅግና ግብዓተ መሬት መቀጠሉ አይቀሬ እንዳይሆነ ፓርቲው ከዘር እና ከቋንቋ ፖለቲካ ቶሎ ብሎ እንዲወጣ እመክራለሁ ። መልከ ጥፉን በሥም እየደገፉ በተረት ተረት ነፃነት ፣ ፍትህ ፣ እኩልነት ፣ ወንድማማችነት ፣ የዜግነት ክብር እያሉ ከንቱ እና ምድር ላይ የሌለ ዲስኩር ማብዛቱ ከውድቀት አያድንም ። ይልቁንስ “ ሰው ሁሉ እንደ እኔ ያሥባል ነገ በእኔ ላይም ሊነሳብኝ ይችላል ፣ በዓለም ላይ እጅግ አሥገራሚው እና ተአምረኛው ፍጡር ሰው ነው ። “ ብሎ ሳይረፍድበት ሥህተቱን ቢያርምና ከመሞቱ በፊት ለዘላቂ ታሪኩ ድምቀት ቢያሥብ መልካም ነው ።
ከጦርነቱ በኋላ ( መከላከያው ለራሱ ታላቅነት እና ፊት ለፊቱ ላለ ታላቅ ክብር ሲል ጦርነቱን በድል ከደመደመው …) ጠቅላዩ ፊታቸውን ወደ ፀረ ሌብነት ትግሉ ይመልሳሉ ብዬ አሥባለሁ ። ሌብነት ፣ ፍትህን ለፖለቲካ ጥቅም ሲባል ብቻ መጨፍለቅ ፤ዘረኝነት ማንበር ፤ ዜጋን በቋንቋ ማበላለጥ ፤ እውነተኛ ችሎታ እና ዕውቀትን ከማየት ይልቅ ፣ የምሥክር ወረቀትን ( የትምህርት ማሥረጃን ) ከባዶ ጭንቅላት ሳይለዩ ሥልጣን እና እድገት መሥጠት ፤ ወዘተ እሥካልተወገዱ እና በተሻለ አሻጋሪ እና ለሀገሪቱ ጠቃሚ በሆነ መመሪያ እሥታልተተኩ ጊዜ ድረስ ፤ ትርፉ ይኽቺን አገር ዘርፎ ፤ በሆዳምነትም ኖሮ በሞት ከዚች ምድር እብስ የሚል ከንቱ ፍጥረት መራቢያ ማድረግ ብቻ ይሆናል ።