July 17, 2022
21 mins read

ችግሩ ያለው መሳሳት ላይ ሳይሆን ሰንካላ ሰበብ እየደረደሩ በቶሎ ከስህተት ያለመመለሱ ላይ ነው (ጠገናው ጎሹ)

July 16, 2022

ጠገናው ጎሹ

Abiy Ahmed 1

እንኳንስ እንደ እኛ አይነት የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ መብት ግንዛቤ (ንቃተ ህሊና) እና ትርጉም ባለው አደረጃጀት የሚመራ ተግባራዊ ሥራ በእጅጉ ዝቅተኛ በሆነበት ወይም ካለመኖር በማይሻልበት ማህበረሰብ ውስጥ በአንፃራዊነት የተሻለ የፖለቲካ ሥርዓት ለመሆን ችሏል ወይም እየቻለ ነው በሚባል  ማህበረሰብ ውስጥም በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የሚሠራ ስህተት  የመኖሩ አጠቃላይ እውነትነት ፈፅሞ  አጠያያቂ አይደለም።

ከአጠቃላይ እውነትነት (general truth) በተለየ ያጋጠመንና እያጋጠመን ያለውን እውነት ግን ከቶ መሸሽ የሚቻለን አይመስለኝም። ብንሞክርም ከቶ የሚቻለን አይሆንም። ምክንያቱም እኛ  ወደድነውም ጠላነው እየሞገተን ያለው እጅግ ግዙፍና መሪር እውነታ ይኸው ነውና።  እናም የእኛን በስህተት ውስጥ የመቆየት ብቻ ሳይሆን በእጅጉ አሳፋሪና አስፈሪ በሆነ የስህተት አዙሪትና ቁልቁለት ውስጥ የመገኘት እውነታ  በአንፃራዊነት በተሻለ ወይም በጣም በተሻለ የዴሞክራሲና የእድገት ደረጃ ላይ ከሚገኙ ወይም ትርጉም ባለው ሁኔታ ወደ ዚያው አቅጣጫና ግብ በመጓዝ ላይ ከሚገኙ ማህበረሰቦች (አገሮች) ጋር እንኳንስ ከምር ለማወዳደር  በትንሹም ቢሆን ለማመሳሰል  አይቻልም ።

በሌላ አገላለፅ ለሌሎች በርካታ የዓለም ህዝቦች ተምሳሌት ከሆንበት  የአገርነት ነፃነትና ልኡላዊነት አኩሪ ታሪክ  እና የብዙ መልካም እሴቶች ባለቤትነት ታሪክ አንፃር በዚህ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በእንዲህ አይነት እጅግ አስከፊ በሆነ የስህተትና የውድቀት አረንቋ ውስጥ ከምንገኝበት እንቆቅልሽ ከምር በመማርና በማምረር ትክክለኛውን የመውጫ መንገድ ከመፈለግ ይልቅ የአብይ አህመድ በእጅጉ እኩይ የሆነ የፖለቲካ አስትሳሰብ ፣  የሴራና የሸፍጥ ፖለቲካ ስትራቴጅና ግብ ፣ እና ይህንኑ የሚያስፈፅምበት የጭካኔ ሰይፍ አዲስ ነገር ይመስል “አብይ  አህመድ በግልብ ስሜት ኮርኳሪ ዲስኩሩ አሳሳተን ፣ አጭበረበረን ፣  አታለለን ፣ ገደለን፣ አስገደለን፣ አገዳደለን ፣ በማንነታችን  እንድጨፈጨፍ  (እንድንጠፋ) እያደረገን ነው፣ ፈጣሪን ሳይቀር  የጨካኝ ፖለቲካ ቁማሩ የበላይ ጠባቂ በማድረግ ተሳለቀበት፣  ችግኝ የምትከለው በማንነታቸው ሳይሆን በአሸባሪ አካላት ለተገደሉት ጥላ እንዲሆናቸው ነው በማለት በመከራችን ተሳለቀብን”  የሚለው ድርጊት አልባ እሮሯችን  የሚነግረን አሁንም ከገንዛ እራሳችን መሪር ተሞክሮ ተምረን ዘመን ጠገብ ስህተታችንን ለማረም ዝግጁዎች እንዳልሆን ነው። 

 

አዎ! ይህ ደግሞ ያለምክንያት የሆነና በመሆን ላይ የሚገኝ አሳፋሪና አስፈሪ ጉዳይ ሳይሆን ከሦስት አሥርተ ዓመታት በፊት ጀምሮ በጎሳና በቋንቋ ማንነት አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማር መሠረት ላይ የተተከለውንና ከአራት ዓመታት ወዲህ ደግሞ እጅግ እየከፋ በመሄድ ላይ የሚገኘውን የፍፁም ብልግና እና ጭካኔ ሥርዓተ ፖተቲካ ከሥሩ ነቅሎ በመጣል በዴሞክራሲያዊ ሥርት ለመተካት የተሞከሩ የለውጥ እንቅስቃሴዎች ሁሉ እየተኮላሹ እና የፖለቲካ ታሪካችን አካል እየሆኑ እንዲቀጥሉ በመፍቀዳችን ምክንያት የመጣና የቀጠለ የአጠቃላይ ውድቀታችን አካል ነው ።

 

ከዚህ የከፋ እንደ ማህበረሰብ (እንደ ህዝብ) አጠቃላይ ዝቅጠት ውስጥ የመገኘት አሳፋሪና አስፈሪ መሪር እውነታ የለም። በተለይ ደግሞ በዓለማዊው ወይንም በመንፈሳዊው (በሃይማኖታዊው) የትምህርት ዘርፍ ፊደል ከመቁጠር ያለፈ የምሁርነት ማዕረግና ብቃት እንዳለው በአገኘው አጋጣሚ ሁሉ እወቁልኝ የሚለው የህብረተሰብ ክፍል የዚሁ “የአሳሳቱኝ” አስከፊ  የውድቀት አዙሪት ሰለባ የመሆኑ መሪር እውነት በእጅጉ አስፈሪ ነው።  አስከፊውንና አደገኛውን የዘውግ ማንነት አጥንት ስሌት ፖለቲካ በህገ መንግሥት ደረጃ ቀምሮ ፣ ደንግጎ ፣ በቀላሉ እንዳይፈታ ቋጥሮ፣   እና በብዙ ሚሊዮኖች በሚቆጠሩና ለከርሳቸው  ባደሩ የዚህ ትውልድ አባላት ካድሬዎቹ  አማካኝነት ሥር እንዲሰድ ባደረገው መለስ ዜናዊ  አማካኝነት ሲመራ ቆይቶ  እርሱ ከሞተ በኋላ  በእርሱ  የሙት መንፈስ አዛዤነት እየተመራ  በቆየው ኅይለ ማርያም ደሳለኝ ሥር የቆየው፣  እና ከአራት ዓመታት ወዲህ ደግሞ በእርሱ (በመለስ ዜናዊ) ሞግዚትነት አስከፊውን የጎሳ ማንነት አጥንት ስሌት ፖለተካ መርዝ እየተጋተ ባደገው አብይ አህመድ (ኦህዴድ-ኦነግ) ተረኝነት በአስከፊ ሁኔታ የቀጠለው የፖለቲካ ሥርዓት በጣም ግልፅና ግልፅ እንጅ ምንም አይነት አሳሳችነት አልነበረውም   አሁንም የለውም ።

 አገር ለአራት ዓመታት ለገንዛ ልጆቿ ምድረ ሲኦል ስትሆን እያደረገ ያለውን የእኩያን ገዥ ቡድኖች ሥርዓት ለማስወገድና እራሱን ጨምሮ ከርሃብና ከባርነት ነፃ የሚያወጣ ትግል ለማድረግ ወኔው ቢከዳው እንኳ ቢያንስ በዚያው እጅግ አሰልችና ፋይዳ ቢስ በሆነ መግለጫ ተብየ መከፋቱንና ሃዘኑን ከምር ለመግለፅ ወኔ አጥቶ የቆየው የዩኒቨርሲቲ ምሁርና መምህር ከሰሞኑ “ኑሮው ከብዶኛልና ትንሽ ሳንቲሞች ካለገሳችሁኝ በአደባባይ ወጥቼ ወይም በሌላ ሰላማዊ መንገድ እሪ እላለሁ” ማለቱን ሰምተናል። የጠየቀውን ያህልም ባይሆን ትንሽ ፈረንካ እንደሚለገስለት እየተነገረው መሆኑንም እየሰማን ነው።

እኩያን ገዥ ቡድኖች ለርካሽ የፖለቲካ ጨዋታቸው ይረዳቸው ዘንድ እንኳንስ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ብሮች ከዚያችም ያነሰች ለግሰውት “በል ወደፊት ደግሞ እየየን እንለግስልሃለንና አሁን አርፈህ ሥራህን ሥራ” ብለው ዝም ጭጭ እንደሚያሰኙት መገመት አያስቸግርም። ይህ ግምቴ የተሳሳተ ቢሆን ደስ ባለኝ።   ለሩብ ምእተ ዓመት የኖረበትና ከአራት ዓመታት ወዲህ ደግሞ በተረኞች እየተመራ በቀጠለው የባለጌዎችና የወንጀለኞች ሥርዓት በየቁኑ በማንነታቸው ምክንያት የሚጨፈጨፉትንና ለቁም ስቃይ የሚዳረጉትን ንፁሃንን አስመልክቶ ምንም ያላለው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አስተማሪና  ምሁር የገዥዎችን “ምክር አዘል” ማስጠንቀቂያ በመቀበል “ይህችን አታሳጣኝ” ወይም “ጎመን በጤና” (ለነገሩ ጎመኑም በቀላሉ አይገኝም)  ብሎ ቢቀበል ፈፅሞ የሚገርም አይሆንም።

አብይ አህመድ ለሥልጠና በሚል  በአዳራሽ ውስጥ ጠርንፎ  ሲገላምጠውና ሲሳለቅበት ጭብጨባውን የሚያቀልጥ ምሁር ነኝ ባይ  ከሳንቲም ጭማሪ ጥያቄ የዘለለ ትግል ውስጥ እራሱን ማግኘት ቢሳነው የሚገርም ጉዳይ አይመስለኝም ። አራት ዓመታት ሙሉ ንፁሃንን በማንነታቸው ለይቶ በማስገደልና በማገዳደል የፖለቲካ ወንጀል ህሊናዎቻቸውና እጆቻቸው የተዘፈቁ ኢህአዴጋዊያን ስምና ቅርፅ እየቀያየሩ ያስቀጠሉት የመከራና የውርደት አገዛዝ አብቅቶ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ እውን እንዲሆን የሚችሉትን ሁሉ  የሚያደርጉ ወገኖችን  እያፈኑ ፣ እያሳፈኑ  እና የአስከፊው ፖለቲካ ድራማ አካል ባደረጉት ካንጋሮው ፍርድ ቤታችው እያመላለሱና አንዳንዶችንም  እኛን ያየህ ተቀጣ  በሚል አይነት የዝምታ ቁልፍ እየቆለፉ የቀጠሉት አብይ አህመድና  የተባባሪዎቹ  አሳሳች የሆነብንና እየሆነብን ያለው ምኑ ላይ እንደሆነ አላውቅም። እኛው እራሳችንን ተሳስተን አሳሳቱን ከሚል ስንኩል የፖለቲካ አስተሳሰብ መቸና እንዴት እንደምንላቀቅ ለመገመትም ያስቸግራል።

አዎ! ለገንዛ እራሱ ስንፍና እና ውድቀት ገዥወች አሳሳቱኝ የሚል ሰንካላ ሰበብ  እራሱን በራሱ እያሳሳተ ያለው ራሱ ይህ የጭንጋፍ ፖለቲካ ታሪክ የማይሰለቸው ትውልድ እንጅ የባለጌ፣ ፈሪና የጨካኝ ገዥ ቡድኖች ዓላማና ግብ በድርጊት የሚታይ  ግልፅ  እውነታ ስለሆነ ፈፅሞ አሳሳችነት የለውም። እጅግ ኋላ ቀርና አስከፊ የጎሳ ፖለቲካ ቁማርን ከደሙ ጋር እያዋሃደ ያደገው አብይ አህመድ ለዚሁ ቁማሩ ስኬታማነት ባሰለጠነው አንደበቱ ሲሰብከውና የሸፍጡና  የሴራው ሰለባ ሲያደርገው ለምና እንዴት  ብሎ ሳይጠይቅ እጅግ ወራዳ በሆነ ግልብ ሜት እየተነዳ “የዘመናችን ሙሴ በማለት የተሳሳተው እና የነፃነትና የፍትህ  ፍለጋ ትግሉን እያኮላሸ ፋይዳ ቢስ የምሬት ጩኸት እየጮኸ ያለው  እራሱ ይህ ትውልድ እንጅ የገዥዎች ርካሽና አደገኛ ፕሮፓጋንዳማ  ግልፅ ነው።

የለየለት የድንቁርና ወይም የአድርባይነት ጥቁር መጋረጃ ካልጋረደን በስተቀር ቢሮውን በአዲስ አበባ ላይ በማድረግ እና ለገዳይ ሠራዊቱ  ሸኔ የሚል የዳቦ ስም በመስጠት በኦሮሚያና ቤንሻንጉል ክልሎች ብቻ ሳይሆን የአማራ ክልል አካል በሆነው ሰሜን ሸዋ  እየተዘዋወረ  የዘር ማፅዳትና ፍጅት ሲፈፅም እንደ መንግሥት ተገቢውን እርምጃ አለመውሰድ አልበቃ ብሎ በማንነታቸው ምክንያት በተጨፈጨፉት  ንፁሃን ወገኖች ላይ መሳለቅን በምን አይነት ቃላት ለመግለፅ እንደሚቻል አላውቅም።  ይህንን አይነት ፍፁም ኢሰብአዊ የፖለቲካ ጨዋታ “እውነት መስሎን የደገፍናቸው ተረኞች ጉድ ሠሩን” በሚል እጅግ ስሜት የማይሰጥ እሮሮ ለማለፍ ከመሞከር የከፋ የውድቀት አባዜም የለም።
እናም ይህንን እገር የሚያውቀውንና ፀሐይ የሞቀውን የእኩያን ገዥ ቡድኖችና የዓላማ ተጋሪዎቻቸውን እጅግ አስከፊ ፖለቲካ ወለድ ወንጀል በስሙ በመጥራት (አፋን አካፋ በማለት) ፅዕኑና ዘላቂ አገራዊ መፍትሄ አምጦ ለመውለድ የሚቸገር ትውልድ የአስከፊና አስፈሪ የክሽፈት ወይም የጭንጋፍ ፖለቲካ ታሪክ ተሸካሚና ለትውልድ አስተላላፊ ሆኖ ቢቀጥል ሊገርመን አይገባም። በጨካኝ አምባገነኖች የማስመሰል ወይም የማታለል ወይም የማሳሳት ፖለቲካዊ ዲስኩር mischievous political rhetoric) እጅግ ለተወሰነ ጊዜ መሳሳት ወይም መዘናጋት ወይም መታለል ፈፅሞ አይኖርም ማለት ትክክል አይሆንም ። የእኛ ግን ከጊዜ ርዝማኔና ከአገራዊው ሰቆቃ ስፋትና አስከፊነት አንፃር ከምር ልብ ካልነው በእጅጉ የሚያሳዝንና የሚያስፈራ አይነት የስህተት አዙሪት ውስጥ ነው ያምንገኘው።

እናም ከትናንት እስከ ዛሬ በተጠናወተን መላልሶ  የመሳሳትና የመውደቅ አዙሪት ውስጥ እየተርመጠመጥን እኩያን ገዥ ቡድኖች  አሳሳቱን የሚል ሰንካላ ሰበብ የመደሬደርን ክፉ የፖለቲካ አስተሳሰብ ልማድ ዛሬውኑ በቃን ማለት ይኖርብናል። ይህ ጥረት ግቡን ይመታ ዘንደ ግን በአገር ደረጃ (በኢትዮጵያዊነት ጥላ ሥርር) እንደ ተደራጁ የሚነግሩንና ነገር ግን የየራሳቸውን የንግሥና ዘውድ በየኪሳቸው ይዘው የሚዞሩ የተቀዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች  መሪዎች ህይወት አልባ መግለጫ ከማውጣትና ጥቁር የሃዘን ልብስ እየለበሱ ሻማ ከማብራት ፖለቲካ በማለፍ የጋራ ትግል ማድረግ በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ከምር መመካከር  ይኖርባቸዋል። የያሳስበናል መግለጫ ማውጣት ፣ ከግፍ ግድያና ከቁም ሰቆቃ የማይታደግ የሃዘን መግለጫ ሻማ ማብራት ፣ ቆሞ እያስገደሉ ነፍስ ይማር የሚል አስቀያሚ  ዲስኩር መደስኮር ፣ በገዳይና አስገዳይ ገዥ ቡድኖች ላይ ከምር ሳይቆጡ በግፍ የተገደሉትን ሰመዓትነትን የተቀበሉ የሚል አፋዊ ሙገሳ የማዥጎድጎዱ ልማድ የትም አያደርሰም ። እያልኩ ያለሁት ከተግባር ጋር ያልተገናኘ ቃል ፋይዳ የለውም ነው እንጅ ሃዘንና  ሙገሳ አያስፈልግም አይደለም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በእውቀቱ ስዩም ስለ ድምፃዊዉ ኢዮብ መኮንን ይህ ወጣት ትውልድም ወይ ይሻሉኛል የሚላቸውን የፖለቲካ ድርጅቶች በመቀላቀልና ውጤታማ እንዲሆኑ በማስቻል ወይንም ደግሞ የእራሱን ድርጅታዊ ሃይል በመፍጠርና በማጎልበት  የወርቃማ ጊዜ እጣ ፈንታውን በእጅጉ ያበላሹበትንና እያበላሹበት ያሉትን ደናቁርትና ጨካኝ ገዥ ቡድኖች በቃችሁ ሊላቸው ይገባል። በተልካሻ ሰበብ አስባብ እራሱን  ከሃላፊነትና ከተጠያቂነት እያሸሸ “ባለጌና ጨካኝ ገዥ  ቡድኖች እያሳሳቱ የመከራና የውርደቱን ዘመኑን አራዘሙብኝ ፤  የረባ ተቀዋሚ ድርጅትም የለም ፣ እና ፈጣሪም አልሰማኝ አለ”  በሚል የሚያስተጋባው እሮሮ ፈፅሞ ስሜት አይሰጥም።

እናም እልህ አስጨራሹ የጋራ ትግል ለዘመናት የዘለቀውን የመከራና የውርደት ሥርዓተ ፖለቲካ  ከሥሩ በመንቀል በጋራ የመሸጋገያ ጊዜ መንግሥት ወደ እውነተኛ  ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚወስደውን ራእይና ዓላማ እውን በማድረግ  ላይ መሆን ይኖርበታል።   ከዚህ ያነሰው አማራጭ የሸፍጠኛ ሴረኛ ገዥ ቡድኖች ምቹ የባርነት ኮርቻ ሆኖ  መቀጠል ነው የሚሆነው ። ከዚህ አልፎ  የጋራ አገር እስከ ማጣትና በመንደር መንግሥታት ፖለቲካ ነጋዴዎች  መካከል በሚነሳ ግጭት እስከ መጠፋፋት ሊደርስ እንደሚችልም  ልብ ማለት ያስፈልጋል። ።

 ልብ ያለው ልብ ይበል!!!

 

https://youtu.be/mX2IajF0PvY

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
Go toTop