July 4, 2022
ጠገናው ጎሹ
ደራሲና ጋዜጠኛ አቤ ጎበኛ በወቅቱ በእጅጉ እየተዛባ በመሄድ ላይ የነበረውን የመብት፣ የፍትህ እና የአኗኗር ሁኔታ ቁልጭ አድርጎ ያሳየን በ196ዎቹ አጋማሽ በፃፋት ትንሽ ግን ከፍተኛ የተፅኖ ሃይል (powerful influence) ባላት የአልወለድም መጽሐፉ አማካኝነት ነው። አዎ! አቤ ጉበኛ በማህፀኗ የተሸከመችውን ምስኪን እናቱን “ፍትህና ርትዕ በእጅጉ ወደ ጎደለው እና አንችን ለጎዳና ላይ ኑሮና ለልመና ህይወት ወደ ዳረገሽ ዓለም ለመቀላቀል ፈፅሞ ስለማልፈልግ አልወልድም” በሚል በሞገተው ህፃን ገፀ ባህሪ አማካኝነት ነበር የነፃነት፣የፍትህ፣ የእኩልነት፣ የሰላምና የጋራ እድገት እጦት የሚያስከትለውን አስከፊ ውጤት ዘመን በማይሽረው አስተማሪነቱ የነገረን ። ሳይፈልግ የተወለደውን ህፃን ከፍፁም ደሃ እናቱ ጋር መንገድ ላይ ተቀምጦ ምፅዋእት የሚለምንና የተወለደበትን ቀን እየረገመ እድሜውን የሚገፋ ደካማ ፍጡር አድርጎ አይደለም ያሳየን። አዎ!ደራሲና ጋዜጠኛ አቤ ጉበኛ ሳይፈልግ የተለደውን ገፀ ባህሪ አድጎና ጎልምሶ የሠርቶ አዳሪ ወገኖቹ ሠርቶ የመኖር መብት ተከራካሪ (መሪ) ሆኖ ሲሟገት ተወንጅሎ ይሙት በቃ የተፈረደበት የነፃነትና የመብት ተሟጋች አድርጎ ነው ዘመንና ትውልድ ተሻጋሪ የሆነ መልእክቱን አስተላልፎልን ያለፈ ።
ያለመታደል ወይም የፈጣሪ ቁጣ ሆኖብን ሳይሆን ራሳችን በፈጠርነውና እየፈጠርነው ባለው ልክ የሌለው የውድቀት አዙሪት ምክንያት ከቀድምት ትውልዶች ለመማርና የተሻልን ሆነን ለመገኘት ባለመቻላችን የእኩያን ገዥዎች ምቹ መሳቂያና መሳለቂያ ከሆን ብዙ ዓመታትን አስቆጠርን ። ከዚህ ሁሉ የከፋው ደግሞ አሁንም አስቀያሚውን የለውጥ መክሽፍ (መጭንጋፍ) ታሪክ እጅግ አስከፊ በሆነ ሁኔታ እየደገምነው የመሆኑ መሪር እውነታ ነው። ለዚህ ደግሞ ከሰሞኑ አብይ አህመድና ቡድኑ በአያሌ ንፁሃን ወገኖች የግፍ ጭፍጨፋና የቁም ሰቆቃ ላይ እየተሳለቁ ከመሆናቸው መሪር እውነት በላይ ሌላ ማስረጃ ፍለጋ ርቆ መሄድ አያስፈልግንም።
የአቤ ጎበኛን ሥራ እንደ መንደርደሪያ የጠቀስኩት ያለ ምክንያት አይደለም። ከግማሽ ምእተ ዓመት በኋላ በዚህ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተወለዱት ብቻ ሳይሆን ገና በእናቶቻቸው ማህፀን ውስጥ የሚገኙ ፍፁም ንፁህ ሰብአዊ ፍጡሮች የተፈፀመባቸውን ለማመን የሚያስቸግር ወንጀል አቤ ጉበኛ ከመቃብር መነሳትና ማየት ቢችል ኖሮ ምን ሊሰማው ይችል ነበር? የሚለውን እጅግ ፈታኝ ጥያቄ በጥሞና እና ገንቢ በሆነ ቁጣና ቁጭት ተረድተን በዚህ ባለንበት ዘመን እየገጠመን ላለው እጅግ አሰቃቂ ፖለቲካ ወለድ ግፍና መከራ የጋራ መፍትሄ እንፈለግለት ለማለት ነው።
አሁን ያለንበትን እጅግ መሪር ሃቅ ለመረዳት ከምር ማስተዋልን እንጅ የተለየ እውቀት ወይም ምርምር አይጠይቅም። ለዚህ ነው የእናቱ/ቷ ማህፀን በስለት ተርትሮ በእናቱ/ቷ ሙት ደረት ላይ የተወረወረውን/ችው ህፃን፣ ከተወለደች ጥቂት ዓመታት ብቻ የሆናትና ቤተሰቦቿ አልቀው ብቻዋን ቀርታ ከፍፁም አረመኔዎች የግፍ ግዳያ የምታመልጥ መስሏት “ወላሂ ከአሁን በኋላ አማራ አልሆንም” በሚል እጅግ ልብ ሰባሪ ተማፅኖ የተማፀነችውን ህፃን ፣ ቤተሰቦቹ አልቀው አስከሬን ከወደቀበት ሜዳ ላይ ተቀምጦ በእንቅልፍና በደመ ነፍስ ፍርሃት መካከል የሚንገላታውን ህፃን ፣ ሃያ አንድ የቤተሰብ አባሎቻቸውን ጨምሮ 61 የግፍ ግድያ ሰለባዊችን አፈር አልብሰው “ምነው ምን አልኩህ እኔን ያተረፍከኝ” የሚል ልብ ሰባሪ ምሬት የሚያሰሙ አዛውንትን ፣ ወላጆቻቸው ወይም አሳዳጊዎቻቸው በማንነታቸው ተለይተው የተጨፈጨፉባቸውንና እማዬን ወይም አባዬን ወይም እህት ዓለምን ወይም ወንድም ዓለምን አምጡልን እያሉ የደም እንባ የሚያነቡ እጅግ አያሌ እምቦቃቅላዎችን (ህፃናትን) ፣ በአራት ዓመታት ያለማቋረጥ በተፈፀመው የመከራና የሰቆቃ ግድያና የቁም ስቃይ ምክንያት ሃዘናችንን እንኳ በቅጡ ለመግለፅ እየተሳነን በእጅጉ ግራ መጋባታችን አልበቃ ብሎ አሁን በቅርቡ ደግሞ አንድ ሳምንት ባልሞላ ልዩነት ውስጥ በማንነታቸው ታርደው በቅጡ አፈር የሚያለብሳቸው ያጡትን በብዙ ሽዎችና መቶዎች የሚቆጠሩ ንፁሃን ወገኖችን በአንደ በኩል እና በሌላ በኩል ደግሞ በዚህ ሁሉ የመከራ ዶፍ የሚሳለቁ የዘመናችን ግፈኛና ጨካኝ ገዥ ቡድኖችን ከምር ልብ ለሚል ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ የአገሬ ሰው ሊያሳድርበት የሚችለውን የልብ ስብራት መገመት አያስቸግርም።
በዚህ ርእሰ ጉዳይ ላይ ሂሳዊ አስተያየቴን የምሰነዝረው ዘመን ጠገቡንና እየከፋ የሄደውን የገዥ ቡድኖች የብልግና እና የጭካኔ ፖለቲካ ቁማር በአግባቡና በዘላቂነት ለማስቆም እና እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ለውጥን እውን ለማድረግ እስካልቻልን ድረስ የግድ መነጋገር ስላለብን ነው እንጅ እነዚሁ ተረኛ ገዥ ቡድኖች እና ግብረ በላዎቻቸው በህዝብ ላይ ያወረዱትና እያወረዱት ያለው የመከራና የውርደት ዶፍ ከቶ አዲስ ወይም የማይጠበቅ ስለሆነ አይደለም።
በእውነት ስለ እውነት ከተነጋገርን ከዛሬ ሦስት አሥርተ ዓመታት በፊት የአራት ኪሎውን ቤተ መንግሥት በተቆጣጠሩት ኢህአዴጋዊያን በህገ መንግሥት ደረጃ ተደንግጎ ለሩብ ምዕተ ዓመት ((ከ1987 -2010) የዘለቀው አስከፊ የጎሳና የቋንቋ ማንነት አጥንት ስሌት ፖለቲካ ሥርዓት ከዛሬ አራት ዓመታት ወዲህ ደግሞ በተረኛ ኦህዴዳዊያን/ኦነጋዊያን የበላይነት እና ከፖለቲካ አጋሰስነት (ለሆድ አዳሪነት) ለመላቀቅ ጨርሶ የተሳናቸው ብአዴን ተብየዎች አሽከርነት በአስከፊ አኳኋን የመቀጠሉ መሪር እውነት አስገራሚ ወይም አዲስ ነገር አይደለም።
ለምን አይገርምም? የሚል ከየዋህነት የሚነሳ ጥያቄ ያለው ብዙ ሰው እንደሚኖር እገምታለሁ ። በዚህ አብዛኛው ህዝብ እጅግ አስከፊና አስደንጋጭ በሆነ የድህነት አረንቋ እና ፖለቲካ ወለድ ወንጀል ፍዳውን እያየ ባለበት መሪር እውነታ ውስጥ የጎሳና የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካን ሲችሉ ለናጠጠ ቱጃርነት ለማመቻቸትና ቢያንስ ደግሞ በኑሮ ዋስትና ምንጭነት ለመጠቀም አለ የተባለን ፖለቲካ ወለድ ወንጀል ሁሉ ከመፈፀም ይመለሳሉ (ይታቀባሉ) ብሎ ማሰብ ከዘመን ጠገቡ የመከራና የውርደት ሥርዓተ ፖለቲካ ያለመማር ድንቁርና ነው። ለዚህ ነው የትኛውንም እርምጃ እየወሰዱ መልሰው የሚሳለቁብን ።
አዎ! የመከራና የውርደት ምንጩን በቅጡ ተረድቶ ይህንኑ ምንጭ በማድረቅ ትክክለኛውን የመፍትሄ ቁልፍ ለማግኘት እስካልቻልን ድረስ ለዓራት ዓመታት እንደ ጎርፍ እየፈሰሰ ስላለው የደም ጎርፍ ሌት ተቀን እግዚኦ ማለት ከቶ ፋይዳ አይኖረውም።
ከሰሞኑ ደግሞ በብዙ ሽዎች የሚቆጠሩ ንፁሃን ወገኖች በማንነታቸው በተከታታይ ሳምንታት ተጨፍጭፈው ሬሳቸው ገና በየሜዳውና በየመንደሩ ተነስቶ ሳያልቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ተብየው በቁማቸው በሞቱ የፓርላማ አባላት ተብየዎች ፊት ቀርቦ ጤናማ አእምሮ ያለውን ወገን ህሊና የሚያቆስል ስላቅ መሳለቁ ይበልጥ የማያስቆጣንና ህዝባዊ አልገዛም ባይነትን የግድ የማይለን ከሆነ የሸፍጠኛና ሴረኛ ገዥ ቡድኖች መሳለቂያ ሆነን ብንቀጥል ሊገርመን አይገባም ።
እርግጥ ነው ይህን አይነት እጅግ አስከፊ የውድቀት መንገድ ውስጥ የገባነው የእኔ ቢጤው ተራ ሰው ብቻ ሳይሆን ተምሮ በመገኘትና በተሞክሮ የሚስተካከለው እንደ ሌለ እራሱን ሲያንቆለጳጵስ የነበረው ሁሉ “የኢትዮጵያ ትንሳኤ በሙሴው አብይና በተከታዮቹ እውን ሆነ” በሚል እጅግ አሳፋሪ ቅሌት ውስጥ ራሱን ያገኘ እለት ነበር። በምንም ምክንያት ይሁን መሳሳት ሊኖር ይችላል። እጅግ ስሜት የማይሰጠው ጉዳይ ግን ከስህተት ባለመማር ክፉ አዙሪት ውስጥ እየተርመጠመጡ እና የባለጌና ጨካኝ ገዥ ቡድኖችና ግብረ በላዎቻቸው መሳቂያና መሳለቂያ እየሆኑ እየየና እግዚኦ የማለት አስከፊ ልማድ ነው።
ዛሬም ከዚህ አይነት የዘመናት አስከፊ ውድቀት ሰብረን ለመውጣት ያለመቻላችን ጉዳይ በእጅጉ ሊያሳስበን ይገባል።
የፖለቲካ ደደብነቱ ከልጅነቱ ጀምሮ ክፉኛ ከተጠናወተው የሥልጣን ሱስና ከቁጥጥር ውጭ ከሆነው የግል ዝና ጥማት ጋር ተጨምሮ የፖለቲካና የሞራል ሰብእናውን ክፉኛ ያበላሸበት አብይ አህመድ “ከእኛ የበለጠ ሰው የሚገደልባት አሜሪካ የእኛን ግድያ ስላናፈሰች ብዙም አያሳስበንም” በሚል በማንነታቸው እየተለዩ በተጨፈጨፉና ለሰቆቃ ህይወት በተዳረጉ አያሌ ንፁሃን ወገኖች ላይ ተሳልቋል። እናም በእንዲህ አይነት ልክ የሌለው የሥልጣንና የግል ዝና ሱስ (unbelievable narcissism) የተለከፈ ግለሰብ በከባድ ቋፍ ላይ የሚገኘውን ህዝብ ወደ ባሰና ለመመለስ በእጅጉ አስቸጋሪ ወደ ሆነ አዘቅት ይዞት ከመውረዱ በፊት ሰንካላ ሰበብ መደርደሩን አቁመን ዛሬውኑ በቃ ለማለት ካልቻልን መቸውንም መነሻ አይኖረንም ።
አብይ አህመድ ለዓራት ዓመታት በአያሌ ንፁሃን የግፍ ግድያና የቁም ሰቆቃ እየተሳለቀ እንዲቀጥል ያስቻለው ሀ) ህወሃትን የተካው ድርጅቱን (ኦህዴድ/ኦነግን) ቁልፍ የፖለቲካ ማስፈፀሚያውን (state machinery) በበላይነት እንዲቆጣጠር ለማድረግ በመቻሉ ለ) ከርሳቸው (ሆዳቸው) እስካልጎደለ ድረስ ደንታ የሌላቸው ህሊና ቢስ ብአዴናዊያንን በአሽከርነት ለማስቀጠል በመቻሉ ነው።
የብአዴናዊያንን ከህወሃት በቀቀንነት ወደ የኦህዴድ በቀቀንነት የመገለባበጥን ክፉ የፖለቲካና የሞራል ደዌ ለማሳያነት ያህል የሚከተለውን ልጥቀስ ።
ቀደም ሲል የህወሃት ከአራት ዓመታት ወዲህ ደግሞ ህወሃትን ገፍትሮ ሥርዓቱን ግን ለማመን በሚያስቸግር የሸፍጥ ፣ የሴራና የጭካኔ መንገድ በማስቀጠል ላይ የሚገኘው የአብይ አህመድ የጎሳና የቋንቋ ማንነት አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኛ ቡድን ታማኝ አሸከሮች ከሆኑት የብአዴን ህሊና ቢስ ከፍተኛ ካድሬዎች አንዱ የሆነው ብናልፍ አንዷለም ከሰሞኑ ተካሄደ በተባለው የብልፅግና (የብልግና) ማእከላዊ ኮሚቴ ተብየው ስብሰባ ወቅት ”የብሔር ግጭት ተነሳ የሚባለው እርባና ቢስ ወሬ ነው። ከብልፅግና የሚጠበቀው በፅዕናት በመቆም ወደ ፊት መግፋት ነው” ሲል የነገረንን እጅግ ርካሽ የፖለቲካ ዲስኩር (rhetoric of political garbage) በተደባለቀና ህሊናን በሚፈታተን ስሜት ውስጥ ሆኘ አነበብኩት።
እንግዲህ ይህ ህሊና ቢስ ከፍተኛ ካድሬ በታማኝነት የሚያገለግለውን የአብይ አህመድን ሸፍጠኛና ሴረኛ የፖለቲካ እስትንፋስ እያዳመጠ ያዘጋጀውን ርካሽ የፖለቲካ ቅርሻት (political garbage) የሚያቀረሽብን አያሌ ንፁሃን ወገኖች እርሱ በአሽከርነት በሚያገለግለው የብልግና እና የግፍ አገዛዝ በማንነታቸው ምክንያት እየተለዩ በሚጨፈጨፉበትና ለቁም ሰቆቃ በሚዳረጉበት መሪር እውነታ ውስጥ ነው።
ለዚህ ነው እነዚህን በህዝብ መከራና ሰቆቃ የሚሳለቁ የገዥው ቡድን ፖለቲከኞችና ሥርዓታቸውን በቃ ለማለት የሚያስችል ፖለቲካዊና ሞራላዊ አቅምን መፍጠር እስካልቻልን ድረስ በየእለቱና በየአጋጣሚው የምናሰማው እየየና እሮሮ የትም አያደርሰንም ብሎ መከራከር ትክክል የሚሆነው።
በእውነት ስለ እውነት ከተነጋገርን በአንድ በኩል መልካም የተፈጥሮ ፀጋ እና እንደ ዜጋና ብሎም እንደ ሰብአዊ ፍጡር መብቱ ቢከበርለት ሠርቶ መበልፀግ የሚችል ህዝብ ያላት አገር በእንደነዚህ አይነቶች ደናቁርትና ጨካኝ ፖለቲከኞች ምክንያት የዓለም ከንፈር መምጠጫ፣ መሳቂያና መሳለቂያ ስትሆን ማየት እና በሌላ በኩል ደግሞ ከዘመን ጠገብና አስከፊ አዙሪት መንጥቆ በሚያወጣ አኳኋን መንቃትና መደራጀት የሚችል ትውልድ ለማየት ያለመቻል ግዙፍና መሪር እውነት በእጅጉ የተደበላለቀና ህሊናን የሚፈታተን ስሜት ካልፈጠረ ሌላ ምን?
ከራት ዓመታት ወዲህ የህወሃት የበላይነት ብቻ ሳይሆን ሥርዓቱም እውነት የሚለወጥ መስሎት በስሜት በሚነዳ የህዝብ ተቃውሞ አጋዥነት ሥልጣነ መንበሩን ተቆጣጥሮ ሥርዓቱን ግን ይበልጥ አስከፊ በሆነ ሁኔታ በማስቀጠል የመከራና የውርደት ዶፍ እያወረደ ያለውን ኦህዴድ/ኦነግ መራሽ ብልፅግና በቃ ለማለት ባለመቻላችን ይኸውና እንደ ብናልፍ አንዷለም አይነት ደናቁርትና ህሊና ቢስ ፖለቲከኞች መሳለቂያ ሆነን ቀጥለናል።
” የብሔር ግጭት ተነሳ የሚባለው እርባና ቢስ ወሬ ነው” ይለናል ተገኘሁበትና እወክለዋለሁ የሚለው የአማራ ማህበረሰብ በማንነቱ ምክንያት በየተገኘበት ቦታና ጊዜ ሁሉ በጅምላ ሲጨፈጨፍ ጨርሶ ህሊናቸውን ከማይገዳቸው የብአዴን ከፍተኛ ካድሬዎች አንዱ የሆነው ብናልፍ አንዷለም ። እርግጥ ነው ህዝብ እንደ ህዝብ ወይም ብሔረሰብ እንደ ብሔረሰብ በራሱ ተነሳስቶ የተገዳደለበት ዘመንና ሁኔታ የለም።
ግን መሠረቱና እድሜው በህዝብ ወይም በብሔረሰቦች መካከል ሊኖር የሚችል ልዩነትን ወደ ጥላቻና ግጭት በመለወጥ ከሚገኘው እኩይ ቀውስ ርካሽ የፖለቲካ ትርፍ የሚቸረችረው እነ ብናልፍ አንዷለም ባለሥልጣናት የሆኑበት የጎሳና የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማር ሥርዓት መሆኑን ግንፈፅሞ መካድ አይቻልም።
የኦህዴድ ታማኝ አሽከር የሆነው ብናልፍ አንዷለም ” የብሔር ግጭት ተነሳ የሚባለው እርባና ቢስ ወሬ ነው” የሚለውን እና ጨርሶ የኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎትና ጥያቄ ሆኖ የማያውቀውን አደገኛ የፖለቲካ አስተሳተሳሰብ ከአስተሳሰብ አልፎ በህገ መንግሥት ደረጃ በመደንገግ የእኩይ ፖለቲካ ቁማር ማስፈፀሚያ ያደረገው ማን ነው ? አንዳንድ የዚህ ትውልድ አባላትን ይህንን እጅግ ጭራቃዊ የፖለቲካ አስተሳሰብ መርዝ እየጋተ በገንዛ ንፁሃን ወገኖቻቸው ላይ ለማሰብ የሚከብድ እልቂት እንዲፈፅሙ ያደረገውና እያደረገ ያለው ማን ነው? ተወልጀበታለሁና እወክለዋለሁ የምትለው መከረኛ የአማራ ማህበረሰብ አንተው እራስህ በሰላም ሚኒስትርነት በተሰየምክበት ሥርዓት በሚደገፉ ጨካኝ አክራሪ ቡድኖች የገንዛ አገሩ ምድረ ሲኦል ስትሆንበት ምን አደረግህ? አሁንስ ምን እያደረግህ ነው? ለምንስ በመከረኛ ህዝብ ላይ ትሳለቃላችሁ? ወዘተ ተብሎ ቢጠየቅ ያንኑ የተጠናወተውን የክህደት ድሪቶ ከመደረት የሚያልፍ መልስ አይኖረውም።
ይህን እጅግ ርካሽና እኩይ የፖለቲካ ዲስኩር የሚደሰኩርብን አራት ዓመታት ሙሉ በመንግሥት ተብየው ድጋፍ በሚደረግለትና ሸኔ የሚል የዳቦ ስም በሰጡት አክራሪና እጅግ ጨካኝ ቡድን (የኦነግ ሠራዊት) የአያሌ ንፁሃን ልጆቿ ደም እንደ ጎርፍ በሚፈስባት እና የብዙ ሚሊዮኖች ህይወት ደግሞ የቁም ሰቆቃ ሰለባ ምድር ሆና በቀጠለች አገር ውስጥ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር የሆነው ብናልፍ አንዷለም መሆኑን ልብ ይሏል።
እናም ሸፍጠኛ፣ ሴረኛ፣ ፈሪና ጨካኝ ኢህአዴጋዊያን/ብልፅግናዊያን ይህንን ያህል ነው እራሳቸው በጫኑበት ፖለቲካ ወለድ የመከረና የውርደት ቀንበር ሥር በሚማቅው ህዝብ ላይ የሚሳለቁበት።
የርካሽና አደገኛ ዲስኩር ማጠንጠኛ ሃሳቡን ሲያጠቃልል ” ከብልፅግና የሚጠበቀው በፅዕናት በመቆም ወደ ፊት መግፋት ነው” በሚል በኦህዴድ የበላይነትና በብአዴን ምቹ አጋሰስነት (አሽከርነት) የመከራውና የውርደቱ ሥርዓተ ፖለቲካ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ቁርጡን ነግሮናል ።
እኛም እንደ ማህበረሰብ ደጋግመን ከወደቅንበትና እየወደቅንበት ካለው ሁለንተናዊ ማለትም ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ሞራላዊ፣ ሥነ ልቦናዊና መንፈሳዊ ውድቀትና ውርደት ለመገላገል ፅዕኑ የሆነና ዘላቂነት ያለው የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ ተጋድሎ ለማድረግ ባለመቻላችን የእኩያን ገዥዎች መሳቂያና መሳለቂያ ሆነን ቀጥለናል። ከሰሞኑ ብልጭ ብለው ድርግም የሚሉና ከተጠና ምክንያታዊነትና ዘላቂነት ይልቅ ስሜታዊነት የሚያጠቃቸው ጩኸቶች የሚነግሩንም ይህንኑ መሪር እውነታ ነው።
ከስምና በወረቀት ላይ ከሰፈረ የፖለቲካ ድርሰት በስተቀር ከዋነኛው ተዋናይ ከብልፅግና ባልተለየ መልኩ ኢዜማም የዚሁ በህዝብ መከራና ውርደት የመሳለቅ እጅግ አስቀያሚ የፖለቲካ ደዌ ተዋናይ ነው። አዎ! የኢዜማን ለዚህ አይነት የፖለቲካ ዝሙተኝነትና የሞራል ዝቅጠት ጉልህ ማሳያ የመሆኑን መሪር እውነትነት እንኳንስ ለማስተባበል ሸፋፍኖ ለማለፍ የሚቻል አይመስለኝም። ራሳቸው መሪዎቹ የአብይንና የቡድንኑ አስተሳሰብና አካሄድ ገና በቅጡ ባልተገነዘቡበት ጊዜና ሁኔታ ውስጥ ሆነው ከራሳቸው በላይ እንደሚያምኑ የመሰከሩ የፖለቲካና የሞራል ወራዶች ናቸውና ስለ እነርሱ ከዚህ በላይ ማለት አያስፈልገኝም ።
ይህ አስተያየቴን እየፃፍኩ ባለሁበት በዛሬው እለት የድርጅቱ መሪ ሆኖ ተመረጠ የተባለው ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ለብልፅግና በገፀ በረከትነት በተሰጠው ኢሳት ላይ ያደረገው ቃለ ምልልስ እከታተል ነበር። “እኛ የምንሠራው ከመንግሥት ጋር ነው እንጅ ከብልፅግና ጋር አይደለም “ በሚል የመንግሥትና የፓርቲ መቀላቀል በአብይ ዘመነ ንግሥና ታሪክ እየሆነ እንደመጣ ሲነግረን ጨርሶ ህሊናውን አልኮሰኮሰውም ። እናም ከእውነተኛው የመማር ትርጉምና እሴት አንፃር ሲገመገሙ መማራቸውን (ምሁርነታቸውን) ያጎሳቆሉ ፖለቲከኞች በበዙበት የፖለቲካ አውድ ውስጥ ባለጌና ጨካኝ ገዥ ቡድኖች እራሳቸው የጫኑበት ፖለቲካ ወለድ መከራና ሰቆቃ ሰለባ በሆነው መከራኛ ህዝብ ላይ ቢሳለቁበት ከቶ የሚገርም አይደለም።
መቸም ነገረ ሥራችን በአብዛኛው በየእለቱ በሚደርስብን የመከራና የሰቆቃ ዶፍ እዬዬና እግዚኦ ማለት እንጅ ይህ እጅግ ተደጋጋሚና አስከፊ የእኛነት ውድቀት ለምን፣ የትና እንዴት መጣ? ብለን በመጠየቅ ሲሆን ጨርሶ ለማስቆም ቢያንስ ግን አደብ ለማስገዛት እና ነገን ከትናንትና ከዛሬ የተሻለ ለማድረግ ለምንና እንዴት አቃተን? ለሚለው ፈታኝ ጥያቂ ተገቢና ወቅታዊ መልስ ለመስጠት አሁንም በአሳዛኝ መልኩ አልተሳካልንም። ሙከራዎቻችን ሁሉ መሬት ላለው መሪርና ፈታኝ እውነታ የማይጥመኑ በመሆናችው አሁንም አስከፊውን መላልሶ የመክሸፍ ( የመውደቅ) ታሪክ እየደገምነው ይመስላል። ይህ ደግሞ በእጅጉ አስፈሪና አሳዛኝ ነው።
ሦስቱም የመንግሥት አወቃቀር ክፍሎች (አካላት) ማለትም ህግ አውጭው (the lagitslative) ፣ ሥራ አስፈፃሚው (the executive) እና የህግ ተርጓሚው (the judiciary) በአንድ እጅግ ሸፍጠኛ፣ ሴረኛ፣ ፈሪና ጨካኝ ገዥ ቡድን ተጠርንፈው በተያዙበት መሪር ሃቅ ውስጥ በመከረኛ ህዝብ ደም የሚነግዱ ገዥ ቡድኖችና ካድሬዎቻቸው እና እበላ ባይ አድርባዮች በህዝብ መከራና ሰቆቃ እየተሳለቁ መቀጠላቸውን ማስቆም አይቻልም።
እናም እንደ ግለሰብ፣ እንደ ቤተሰብ፣ በዓለማዊውም ሆነ በሃይማኖታዊ ትምህርት ምሁር ነኝ እንደሚል፣ እና በአጠቃላይ እንደ ማህበረሰብ ወይም እንደ ህዝብ ፅዕኑ የሆነ ፖለቲካዊ፣ ሞራላዊ፣ ሥነ ልቦናዊ፣ መንፈሳዊ ህመም ታመናልና ከመሪሩ ሃቅ እየሸሸን ራሳችንን ከማታለል ይልቅ ህመሙ ይበልጥ ሳይጠናብን የሚበጀንን መፍትሄ አምጠን መውለዱ ነው የሚሻለን ። ከዚህ ያነሰ የትግል አካሄድ እንደ ብናልፍ አንዷለም አይነቶች ህሊና ቢስ ካድሬዎች መጫወቻ ከመሆን ጨርሶ አያድነንም።
በአብይ ዘመነ ንግሥና በንፁሃን ልጆቿ ደም ጎርፍ እየጨቀየችና እየፈረሰች ያለችውን አገር ለማዳን አብይና ቡድኖቹ ሥልጣን ለቀው በሽግግር ወይም በዝግጅት ጊዜ አካል ወይም መንግሥት ይተኩ ብሎ መጠየቅንና መታገልን ለምንና እንዴት እንደምንፈራው በእጅጉ የሚገርም ነው። ከመግረምም አልፎ እየወረድንበት ያለውን የውድቀትና የውርደት ቁልቁለት ጥልቀትና አስከፊነት ነው የሚያሳየው።
ጊዜያዊ ወይም የሽግግር ተልእኮን እውን ለማድረግ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን በጋራና ትብብርና ቁርጠኝነት ዝግጁ በማድረግ የአገር ይፈርሳል ጥያቄን መመለስ ሲቻል “አብይና ብልፅግና ካልመሩን አገር ይፈርሳል” እያሉ አገር ይበልጥ ስትፈርስ “እርሱ ፈጣሪ የፈቀደው ነው” የሚል እጅግ ስሜት የማይሰጥን የሰበብ ድርደራን መቀበል ቀርቶ የሚሰማ አምላክ አይኖርም። እናም ትክክለኛው የመፍትሄ መንገድ የወንጀለኞችን ሥርዓት ከሥሩ ነቅሎ በመጣል ለምድራዊውም ሆነ ለሰማያዊው ህይወት የምትመች ኢትዮጵያን እውን ማድረግ ብቻ ነው።