በላይነህ አባተ ([email protected])
መጤ ባህል እንደ እከክ ገላችንን አበላሽቶና አይምሯችንንም እንደ ሐሽሽ በርዞ አደናብሮናል፡፡ ክርስቶስ ሞቱንና ትንሳኤውን እንድናስታውስ ቢያዝዝ ምእራባውያን ገባያቸውን ለማድራት በፈጠረቱ የልደት ባህል ተዘፍቀን በፉክክር ሰፊ አዳራሽ ተከራይትነንና ሰንጋ አርደን አስረሽ ምቺው እየጨፈርን የልደት ቀናችንን በእብደት ማክበር ተጀመርን ስንብተናል፡፡
በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ አሁን አሁን ደሞ ልጆቻችን እንደምንም ተንከባለው ተህፃናት ማሳደጊያ፤ ተአንደኛ ደረጃና ተሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲመረቁ እየተፎካከርን ሰንጋና ሙክት አርደን፤ ከሰርግ የበለጠ ድግስ ደግሰን፣ በኪነት ልብስ ተለብደን መዝሙርና ዘፈንን እንደ እብድ እያቀላቀልን ዳንኪራ እየመታን በሚያባክንና በሚያስኮንን ባህል ተጠምደናል፡፡
ዛፍ ሥሩን ሲቆረጥ ይወድቃል፤ ቅጠልና ቅርንጫፉም ይደርቅና የመጣ የነፋስ ሽውታ ሁሉ እንደ ብናኝ እያንሳፈፈ ጠርጎ ይዞት ይሄዳል፡፡ የራሱ ማንነትና ባህል ተሰውነቱ የወጣ ሕዝብም የመጣው የባህል ሽውታ ሁሉ እንደ ገለባ ይዞት ይነጉዳል፡፡ እንደሚታወቀው ክርስቶስ የተወለደበት ቀን በትክክል አይታወቀም፤ የተወለደውም በስቃይ ኖሮ በስቃይ ለማለፍ እንጅ እንደ እኛ “እንኳን ተወለድኩ ብሎ ደረቱን እንደ ጋራ እየነፋ” የተወለደበትን ቀን እያስታወሰና ድግስ እየዛቀ ሲጨፍር ለመኖር አልነበረም፡፡ አባቶቻችን ይኸንን በመገንዘብ የልደት በአልን ወይም ገናን በጸሎትና በጥሞና፤ ትንሳዔን ወይም ፋሲካን ደግሞ በፌስታና በደስታ ያሳልፉት ነበር፡፡ እኛ ፈረንጅ ሸቀጥ ለመቸብቸብ እንዲያመቸው የፈጠረው የገና የዛፍ አምልኮና ልደት የማክበር ውቃቤ እንደ ጋኔን በጥፊ ደጋግሞ ጠፍጥፎን ከልደት ቀን አልፈን ምረቃ ምንትስ ቅብጥሶ እያልን ጊዜ፣ ገንዘብ፣ ባህልና ትውልድ ስናባክንና ስናጠፋ እንውላለን፡፡
የሰው ልጅ ልደቱን ማክበር እንደማይኖርበት ለማስጠንቀቅ መጽሐፉ በኢዮብ 3-3 “ያ የተወለድኩበት ቀን ይጥፋ” ይላል፡፡ ኤርማያስ 20፤ 14-15 እንደዚሁ “የተወለድሁባት ቀን የተረገመች ቀን ትሁን” ይላል፡፡ ልደታቸውን ድል ባለ ድግስ ሲያከብሩ የነበሩ እንደ ኢዮብና ኤርሚያስ ያሉ ቅዱሳና ሳይሆኑ ቅዱሳንን ሲፈጁ የኖሩት ፈርኦንና ሄሮድስ ነበሩ፡፡ ዘፍጥረት 40፤20-22 እንደሚያተምረው ፈርዖን የልደት ቀኑን በፌስታ በሚያከብርበት ቀን ታዛዡን የእንጀራ አቅራቢውን ሰቅሎ ገሏል፡፡ በተመሳሳይ መንገድ ማርቆስ 6፤21-28 እንደሚያስተምረው ሄሮድስ የልደት ቀኑን ሲያከብር የመጥምቁ ዮሐንስን አንገት ቆርጧል፡፡ እኛ የዛሬዎች ትውልዶችም ክርስቶስ ሞቴን አስታውሱ ያለውን ትዕዛዝ (ሉቃስ 2፤20) ጥሰን፤ የቅዱሳንና የአባቶቻችንን አደራ ቁርጥም አድርገን በልተን የፈርዖንና የሄሮድስን መንገድ ተከትለናል፡፡ ይኸንን ሙሴን ያሰቃየውን የፈርዖንና የዮሐንስንም አንገት የቀላውን የሄሮድስን የጥንቆላ ልደት ባህል ስናክብርም ዓለም በቃኝ ብለው የመነኮሱ መነኩሳትና የክርስቶስ ሐዋርያ ነን ብለው መስቀል የተሸከሙ ቀሳውስትም መጥተው “ይባርኩልናል”፡፡ ቀልጠናል!
ሕዝብ ሆይ! ቀጥ ብለህ ለመቆም ወደ ሃይማኖትህና ባህልህ ተመለስ፡፡ ቅድም አያቶችህ ለምን ልድትን እንድላከበሩና ለምንስ ተዝካርና ወይም ሙተ ዓመትን ያክብሩ እንደነበር ፈትሽ፡፡ ተዝካር መታሰቢያ መሆኑ እወቅ፡፡ ተስካር የሰማእታት ማስታወሻ መሆኑን ተገንዝበህ ሰማእታትን እንደ ፈርዖንና ሄርዶስ በልድታቸው ቀን ሳይሆን በሙተ ዓመታቸው አስታውስ!
ሰማእታትን መዘንጋት አድራን መብላት ነው፡፡ አደራን መብላትም እርምን መብላት ነው፡፡ እርምን መብላትም መረገም ነው፡፡እርማችንን እየዋጥን የሰማእታትን ነፍስ እንደ ትንኝ ነፍስ ቆጥረን “ያለፈውን በይቅርታ መላፍ በሚል!” የሆዳምና የአረመኔ ፈሊጥ እኛ ከርሳችንን ስንቆዝር ለፍትህ ከተሰውት መቃብር ቆመን የወደፊት እንጀራችንን ለመገጋር የምንቋምጥ የትዬለኔ ነን፡፡ ለእነዚህ እርማቸውን ከበላነውና ነፍሶቻቸው ፍትህን በመጠበቅ ላይ ካሉት ሰማእታት መካከል ለእኛ ሲል እንደ እስጢፋኖስ ተቀጥቅጦ የተገደለው የሕዝብ ጠበቃው ሳሙኤል አወቀ አንዱ ነው፡፡
ሰማእቱ ሳሙኤል አወቀ ተሰውቶ ፍትህን ሳያገኝ ስድስት ዓመታት አለፉት፡፡ ሳሙኤል ሮጦ ሳይጠግብ ያለፈ ሰማእት ነው፡፡ እንደ ሌሎች ሰማእታት ሳሙኤል የተሰዋው ግፉዓንን ከግፍ ቀንበር ለማላቀቅ ሲጥር ነው፡፡ ሳሙኤል የተሰዋው እንደ ጳጳሳት ከግፈኞች ጀርባ ማረጥረጥ፣ እንደ ልማታዊ ሐኪሞች ከገዳዮች ጋር መዳራት፣ እንደ ምሁራን ተብዮዎች አድርባይነትን ተከናንቦ ህሊናውን መግፈፍ ተስኖት ነው፡፡ ለግፉዓን ራስን አሳልፎ መስጠት ቅድስናና ብጽእና ነው፡፡ ቅድስናንና ብጽእናን የሚቀልቧቸው ምዕመናን ሲረሸኑ ለማይተነፍሱ እንዲያውም ከረሻኙ ጀርባ ለሚቆሙ አቡንና ጳጳሳት እየሰጡ ብጹእ ቅዱስ ማትያስ፣ ብጹእ ቅዱስ ገብርኤል፣ ብጹእ ቅዱስ ፋኑኤል ወዘተርፈ እያሉ መጥራት በእምነት ማፌዝ ነው፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ የተጻፉትን ታሪኮችም ሆነ ገድሎች እርግጠኝነት የሚጠራጠር በጦቢያ የሚፈጸሙትን ሰቆቃዎች በጥሞና ቢመለከት በቅዱሱ መጽሐፍ የተመዘገቡ የቅዱሳትን ተጋድሎና የደረስባቸውን ግፍ ወደ ማመን ይጠጋል ብዬ እገምታለሁ፡፡
እንደሚታወቀው እስጢፋኖስ ለእምነቱ ሲል በድንጋይ ተወግሮ የሞተ ክርስቲያን ነው፡፡ እስጢፋኖስ ልቡን ለሚያምንበት ክርስቶስ ሙሉ በሙሉ ሰጥቶ በርትዑ አንደብቱ ስለክርስቶስ ሲሰብክ ከሀዲና ቀጣፊ ፈሪሳውያን “በሙሴ ላይ፤ በእግዚአብሔርም ላይ የስድብን ነገር ሲናገር ሰምተዋል የሚሉ ሰዎች አስነሱ ፡፡ ሕዝቡንና ሽማግሌዎችንም፣ ጻፎችንም፤ አናደዱ፤ ቀርበውም ያዙት፣ ወደ ሸንጎም አመጡትና ይህ ሰው በዚህ በተቀደስው ስፍራ በሕግም ላይ የስድብን ነገር ለመናገር አይተውም፣ ይህ የናዝሬቱ እየሱስ ይህንን ሥፍራ ያፈርሰዋል፤ ሙሴም ያስተላለፈልንን ሥርዓት ይለውጣል ሲል ሰምተነዋል የሚሉ የሐሰት ምስክሮች አቆሙ፡፡፡” ሐዋ ሥራ ፮፡ ፲፩-፲፬
ሶፋ ላይ ተንፈላሶ ቁርጡን እየቆረጠ ወይም ውስኪውን እየጨለጠ “አርፎ አይቀመጥም” ለሚል የኔ ቢጤው ክብር የለሽ አሳማ ወይም ቅንቡርስ እንደ ሰማእት ላይታይ ቢችልም ሳሙኤል አወቀም እንደ እስጢፋኖስ ለሚያምንበት ተወግሮ የተሰዋ ጀግና ነው፡፡ ሳሙኤል ልቡን ለሀገሩና ለነፃነቱ ሰጥቶ በርትዑ አንደበቱ ስለ አገሩ፣ ስለፍትህንና ነፃነት ሲሰብክ የበፊቶቹ ፈሪሳውያን በእስጢፋኖስ ላይ “ሙሴንና እግዚአብሔርን ሰድቧል፣ ሙሴ ያስተላለፈልንን ሕግን ይለውጣል” የሚሉ ስም አጥፊ ሰባኪዎች እንዳሰማሩበት የዛሬዎቹ ፈሪሳውያንም “ሳሙኤል አወቀ ሰላምን ያናውጣል፣ ሽብርን ይነዛል፣ ሕገ-መንግስትን ይንዳል” የሚሉ ቀጣፊ ካድሬዎችን አሰማሩበት፡፡ ሕዝብ ግን እውነተኛውን እስጢፋኖስ በተመስጦ እንዳዳመጠው ሁሉ ባለማተቡን ሳሙኤልንም በጥሞና ያዳምጥ ነበር፡፡
እስጢፋኖስ የኦሪትን ሕግና የነባያትን መጻሕፍት እየጠቀሰ ቢያስረዳቸውም ፈሪሳውያን አልሰማ ስላሉት “እናንተ አንገተ ደንዳኖች ልባችሁም ጆሯችሁም ያልተገረዘ እናንተ መንፈስ ቅዱስን ትቃወማላችሁ፤ አባቶቻችሁ እንደ ተቃወሙት እናንተ ደግሞ፡፡ ከነብያትስ አባቶቻችሁ ያላሳደዱት ማን ነው? የጻድቁን መምጣት አስቀድመው የተናገሩትን ገደሏቸው፤ በመላእክት ሥርዓት ሕግን ተቀብላችሁ ያልጠበቃችሁት እናንተም አሁን እርሱን አሳልፋችሁ ሰጣችሁ፡ ገደላችሁትም፡፡” አላቸው፡፡
ሳሙኤል አወቀም በሐሳብ ክርክርና በህሊና መኖር የማያምኑትን ጭራቅ አሳዳጆቹ ስላልሰሙት ” እናንተ የሰውነትም ሆነ የመንግስትነት ባህሪ የሌላችሁ በድንቁርና ልባችሁን ያደነደናችሁ እውነትን፣ ፍትህንና ነጻነትን ትቃወማላችሁ፤ ባንዳ አባቶቻችሁ ከጠላት አብረው የጦቢያን አርበኞች እንዳሳደዱት፤ እናንተም የሞሶሎኒን ሐውልት ስንቃወም፣ የአርበኞቻችንና የሰማእቶቻችንን ቀን ስናከብር ታሳድዱናላችሁ፡፡ በአገር ውስጥ በግፍ የታሰሩት ወገኖቻችን እንዲፈቱ፤ በውጭም ዜጎቻችን ተከብረው እንዲኖሩ ስንጠይቅ ወህኒ ትከቱናላችሁ፡፡ ሕገ-መንግስት የሚል ቃል እያነበነባችሁ እናንተ ግን ሕግን እየጣሳችሁ በሕገ- አራዊት ትኖራላችሁ” አላቸው፡፡
በእስጢፋኖስና በሌሎችም ሐዋርያት ትምህርት የክርስትና ተከታዮች ቁጥር እጅግ እየበረከተ መጣ፡፡ ይህንን የክርስትና ተከታዮችን መብዛትና የእስጢፋኖስንም እውነተኛነትና ቁርጠኝነት የተመለከቱ ፈሪሳውያን ቀኑ፤ ተበሳጩ፡፡ “የተበሳጩት ፈሪሳውያን በልባቸው በጣም ተቆጡ፣ ጥርሳቸውንም አፋጩበት፡፡ በታላቅ ድምጽም እየጮሁ ጆሯቸውን ደፈኑ፣ በአንድ ልብ ሆነውም ወደ እርሱ እሮጡ፤ ከከተማም ወደ ዉጪ አውጥተው ወገሩት፡፡ ምስክሮችም ልብሳቸውን ሳውል በሚሉት በአንድ ጎብዝ እግር አጠገብ አኖሩ፡፡ እሲጥፋኖስም ጌታ እየሱስ ሆይ ነፍሴን ተቀበል ብሎ ሲጠራ ይወግሩት ነበር፡፡ ተንበርክኮ ጌታ ሆይ ይህንን ኃጢአት አትቁጠርባችው ብሎ በታላቅ ድምጽ ጮኸ፡፡ ይህንንም ብሎ አንቀላፋ፡፡ ሳውልም በእርሱ መገደል ተስማምቶ ነበር፡፡” የሐዋ ሥራ ፯፣፵፬-፵፭.
እንደ እስጢፋኖስ የእምነት ተከታዮች ሁሉ የሳሙኤል ተከታዮች ቁጥርም እየበዛ መጣ፡፡ ይህንን የሳሙኤል ተከታዮች መብዛት፣ የሳሙኤልን እውነተኝነትና ቁርጠኝነት የተመለከቱ ፈሪሳውያን እጅግ ተበሳጩ፡፡ ጥርሳቸውምንም እያፋጩ ዛቱበት፣ ከስራ አባረሩት፣ በግሉ ሰርቶ እንዳይበላ ከለከሉት፣ አሰሩት፣ ገረፉት፣ አገሩን ጥሎ እንዲሸሽም አስጠነቀቁት፡፡ ሳሙኤልም “የምከፍለው ዋጋ ለሀገሬና ለነፃነት ነው፤ ከታሰርኩም ኅሊናዬ አይታሰርም፤ ከገደሉኝም ትግሌን አደራ! በተለይ የኔ ትውልድ አደራ!!!” ብሎ በታላቅ ድምጽ ጮኸ፡፡ ፈሪሳውያንም በአንድ ልብ ሆነው ወደ እርሱ እሮጡ፤ ከመነሐሪያ ወደ ውጪ አውጥተውም ወገሩት፡፡ ሳሙኤልንም ይህችን ግፍ እንደ ዶፍ የሚወርድባት ምድር ለመልቀቅ ሽልብ አለ፡፡ በሳሙኤል መወገር የተሰማሙት ሰዎች ቁጥርም ሆነ ሳሙኤል በሚወገርበት ሰዓት የተናገረው ለጊዜው አይታወቅም፡፡ እውነቱ ተመርምሮ ዘግይቶ እንደተጻፈው የእስጢፋኖስ ገድል የሳሙኤል ገድልም ተመርምሮ ዘግይቶ ይጻፋል፡፡
እስጢፋኖስ ተወግሮ ቢሞትም የሞተለት ክርስትና በምድር ተስፋፍቷል፡፡ ከአጠገቡ ቆሞ ያስቀጠቀጠው ሳውልም ንስሃ ገብቶ ክርስትናን አስፋፍቷል፤ ክርስትናን በመስበኩም አንገቱን ተቀልቷል፡፡ በዚህ ግብሩም ቅዱስ ጳውሎስ ተብሏል፡፡ እንደ እስጢፋኖስ ሳሙኤልም ለእምነቱ ተወግሮ ቢሞትም የሞተለት የነፃነትና የፍትህ እምነት ይስፋፋል፡፡ ተቀናቃኙ ስንታየሁ ወልደሚካኤልም ከነፍሰ-ገዳዮች ፓርላማ እንደ ድንጋይ መጎለቱን ትቶ ንስሃ በመግባት ሳሙኤል ለተሰዋለት የነፃነትና ፍትህ እምነት አንገቱ እስከሚቀላ እንደሚሰብክ እስካሁን ይጠበቃል፡፡ ከሶስት ዓመታት ወዲህ ከሳሙኤል ገዳይ ድርጅት ጋር ቀለበትና ሰርግ የፈጠሙት የድሮ የሳሙኤል የትግል ጓዶችም ንስሐ ገብተው ለሳሙኤል ፍትህን እንዲጠይቁ የሰማእቱ ደሞ ይጮኻል፡፡
በክርስትና ታሪክ እስጢፋኖስ በሰማእትነቱ እንደሚዘከረው ሁሉ በኢትዮጵያ የሀገር፣ የነፃነትና የፍትህ ታሪክም ሳሙኤል ሲዘከር ይኖራል፡፡ እስጢፋኖስን የገደሉትና የከደዱት እርኩሶች በሰማይና በምድር ሲረገሙ እንደሚኖሩት ሁሉ ሳሙኤልን የገደሉትና የከዱት እርኩሶችም በምድር ስማቸውና ስጋቸው በሰማይም ነፍሳቸው ሲቃጠል ይኖራል፡፡ እስጢፋኖስን ለማዳን ያልጣሩት አድር ባዮች ስም የለሽ ሆነው እንደ ቀሩት ሁሉ ሳሙኤልን ለማዳን ያልጣርን አድር ባዮችም ስማችን ሳይጠራ ይኖራል፡፡ ከእስጢፋኖስ ገዳዮች ጋር ሲሞዳሞዱ የነበሩት ከርሳሞች ሲረገሙ እንደሚኖሩት ሳሙኤልን ካስገደሉት ጋር በጥቅም ምላስ የምንሞዳሞድና ክብራችንን ጥለን ደጅ የምንጠናም ሥጋችን ሲቦጨቅ፣ ነፍሳችንም ሲረገም ይኖራል፡፡
በኤፍሬም ይሳቃዊ ወስላታ “አገራዊ እርቅ” እያሳበብን ፍትህን ረግጠን በእነሳሙኤል አወቀ መቃብር ላይ እንጀራችንን ከመጋገር መለኮት ይጠብቀን፡፡
እንደ እስጢፋኖስ ተወግሮ የተገደለውን የሳሙኤልን ነፍስ ይማር፡፡
የሞተን አትርሳ የወደቀን አንሳ ነውና ምን ጊዜም ሰማእታትን አንርሳ!
መጀመርያ ሰኔ ሁለት ሺ ሰባት ዓ.ም. ከዚያ በኋላም በየዓመቱ መታተም ቀጠለ፡፡
ሰኔ ሁለት ሺ አስራ አራት ዓ.ም.