May 23, 2022
24 mins read

 የሰሞኑ መንግሥታዊ ሽብርተኝነት ምንድነው የሚነግረን? – ጠገናው ጎሹ

May 21, 2022
ጠገናው ጎሹ

ለአጠቃላይና አስከፊ የውድቀት አባዜ ከዳረጉን ዋነኛ ምክንያቶች አንዱ ዘመን ጠገብ የሆነውን የመከራና የውርደት ፖለቲካ ሥርዓት እንደ ሥርዓት ፅዕኑ በሆነና ዘላቂነት ባለው የጋራ ተጋድሎ አስወግደን የሚበጀንን ሥርዓት እውን ከማድረግ ይልቅ ከክስተቶች የትኩሳት መጠን ጋር ከፍና ዝቅ እያልን በፈረቃ ለሚገዙን የጎሳና የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች የተመቸን ሆነን መገኘታችን መሆኑን ማስተባበል የሚቻል አይመስለኝም።

የሰሞኑ መንግሥታዊ አሸባሪነት (state terrorism) ከፊታችን የደቀነብን ከባድ ፈተና የሚሽከረከረው “አሁንስ ቢሆን እውን ከዚህ ክፉ የፖለቲካ አስተሳሰብና የሞራል ዝቅጠት አዙሪት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሰብሮ ለመውጣት ዝግጁዎችና ቁርጠኛች ነን ወይንስ ክፉኛ የተጠናወተን ከመከራና ከውርደት አገዛዝ ጋር የመለማመድ አስቀያሚ ልማድ ሰለባዎች ሆነን እንቀጥላለን?” በሚል እጅግ አስፈሪ ግን ወሳኝ ጥያቄ ዙሪያ ነው።

ምንም እንኳ እንደዚህ ወይም እንደዚያ ይሆናል ብሎ ለመተንበይ ከሁኔታዎች በፍጥነት የመለዋወጥ ባህሪ አንፃር አስቸጋሪ ቢሆንም የመንግሥታዊ ሽብር ቀጥተኛ ሰላባ እየሆኑ ባሉ አካባቢዎች በተለይም በአማራ ክልል የምናያቸው የህዝባዊ እምቢተኝነት እንቅስቃሴዎች ከላይ ለሰነዘርኩት  ፈታኝ ጥያቄ ወቅታዊና ውጤታማ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ አይመስለኝም።

ይህ ማለት በአንገዛም ባይነት ትግል ውስጥ እስከ ህይወት መስዋእትነት የከፈሉ ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ ወገኖችን ማሳነስ ማለት በፍፁም አይደለም። ጥያቄው እነዚህ ወገኖች መስዋእትነት የከፈሉበትን ምክንያት (የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ) በታቀደ፣ በተደራጀ፣ በተቀነባበረ እና ዘላቂነት ባለው ትግል ለድል እናበቃለን ወይንስ የተሰውቱን የምናስታውስ የቁም ሙቶች ሆነን እንቀጥላለን? ነው።

አሁን እያየናቸው ያሉት እንቅስቃሴዎች በአብዛኛው ግብታዊ (ስሜታዊ) እና ለሸፍጠኛና ሴረኛ ገዥ ቡድኖች ርካሽ ፕሮፓጋንዳና ጨካኝ ሰይፍ የተጋለጡ ናቸው። ምክንያቱም ከምር በታሰበበት፣ በታቀደ፣ ፅዕኑ ዓላማና ግብን መሠረት ባደረገ፣ በሸፍጠኛና ሴረኛ ብልፅግናዊያን የማደንዘዣና የማክሸፊያ አጀንዳ በማይዘወር፣ ማድረግና አለማድረግ ያለበትን ጠንቅቆ በሚያውቅ ፣ እና ከሁሉም በላይ በጠንካራና ዘላቂ ድርጅታዊ ሃይል የማይመሩ ህዝባዊ እንቅስቃሴዎች ለክሽፈት የተጋለጡ ናቸውና ። የዚህ አይነት እንቅስቃሴዎችን ድክመት ለመረዳት ከእኛ ከራሳችን የፖለቲካ ታሪክ በላይ አስረጅ የሚኖር አይመስለኝም።

አሁንም በተለይ በቀጥታ የመንግሥታዊ አሸባሪነት ሰለባ ከሚሆኑ ክልሎች ውጭ  የምንታዘባቸው “የምን አገባኝ አይነት” ዝምታዎች (silences of  who cares) በእጅጉ አስፈሪዎች ናቸው ። አደባባይ ወጥቶ የጋራ ጩኸት ማስማት እንኳ ባይቻል በተገኘው የመገናኛ ዘዴ ሁሉ ጉዳታችሁ ጉዳታችን፧ ደህንነታችሁ ደህንነታችን፧ የነፃነትና የፍትህ ትግላችሁ ትግላችን ነው ለመባባል ያለመቻል ወይም ያለመፈለግ  ክፉ ስሜት የሚነግረን ሸፍጠኛና ሴረኛ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች የዘሩት የመለያየትና የጥላቻ መርዝ ምን ያህል ሥር የሰደደና ከባድ ተጋድሎ የሚጠይቅ መሆኑን ነው። ለዚህም ነው ከሰሞኑ እየተፈፀመ ያለውን መንግሥታዊ አሸባሪነት በመቃወም የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን በነቃና በተደራጀ መልኩ መርቶ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ እውን መሆን መጠቀም ይቻል ይሆን ወይንስ …? የሚለው ጥያቄ በእጅጉ አስጨናቂ የሚሆነው።

አዎ! የሰሞኑ ሁኔታችን የሚነግረን እንቅስቃሴዎቻችንን ከክስተቶች ትኩሳት መውጣትና መውረድ ጋር ሳይሆን ዘላቂ ከሆነ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን መሆን ጋር አቆራኝተን ካላየናቸው (ካላስኬድናቸው) ዘመን ጠገቡን የፖለቲካ ውድቀት አዙሪት እንቆቅልሽ ፈፅሞ መፍተት እንደማንችል ነው።

ሌላ ማሳያ (ምሳሌ) ልጥቀስ ። በአዲስ አበባ የምንታዘበውን የምን አገባኝ ይሁን ወይም የፍርሃት በቅጡ ያለየለትን ዝም ጭጭ ከምር ለሚታዘብ ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ የአገሬ ሰው የሁላችን ናት የምንላት ውብ አዲስ አበባ እና ለጋራ መብት በጋራ መነሳት የተሳነው አዲስ አበቤ የተደበላለቀ ስሜት ቢፈጥሩበት ከቶ የማይጠበቅ አይደለም። “ስልታዊ የአልገዛም ባይነት ዝግጅት እንጅ የምን አገባኝ ወይም የፍርሃት አይደለም” ከተባለም እሰየው። አዲስ አበባ የባለጌና ግፈኛ የጎሳ አጥንት ስሌት ቁማርተኞች የአፈና እና የወከባ ማእከል ስትሆን ቢያንስ እጅን ወደ ላይ ዘርግቶ አታፍኑን፣ አታዋክቡን፣ አታሳዱን፣ ባይተዋር አታድርጉን፣ ከባዱንና አደገኛ የተረኝነት እጃችሁን አንሱልን፣ እና በአጠቃላይ እንኳንስ አዲስ አበባ የትኛውም የኢትዮጵያ ግዛት በጋራ ደምና አጥንት የተሠራና ተጠብቆ የኖረ የጋራ ቤታችን ነውና ከገባችሁበት አደገኛ የእኛ ብቻ እና የእናንተ ብቻ የሚል የፖለቲካ ልክፍት እራሳችሁን ገድቡ ብሎ መጮህና ማስጠንቅ ለምንና እንዴት የማይቻል እንደሚሆን አሳማኝ ምክንያት የሚቀርብለት አይመስለኝም።

የሰሞኑ አስከፊ የገዥዎች የአሸባሪነት ዘመቻ የሚነግረንም ከእንዲህ አይነት መያዣና መጨበጫ ከሌለው የነፃነትና የፍትህ ፍለጋ ትግል እስካልተላቀቅን ድረስ የትም መድረስ እንደማንችል ነውና የሚሻለው ቆም ብሎ በማሰብ የሚበጀውን የእርምት እርምጃ መውሰድ ነው።

የራስን ምንነት፣ ዓላማና ግብ ጠንቅቆ የማወቅ (self-consciousness) ፣ለዚሁ ተግባራዊነት በሚያስፈልግ ደረጃ ተደራጅቶ የመገኘት (the necessity of creating and developing organizational networks and capacities) እና ሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች መሬት ላይ ካለው መሪር ሁኔታ አንፃር በእጅጉ ወደ ኋላ የቀሩ በመሆናቸው አሁንም ጨካኝ ገዥዎች የጭካኔ ሰይፋቸውን በመዘዙብን ቁጥር በስሜት ከመብከንከንና እየየ ከማለት ክፉ የፖለቲካ ልማድ አልወጣንም ።

አሁንም አብዝተን የተጠመድነው በአብዛኛው ተሞክሮ በወደቀ የፖለቲካ አስተሳሰብና ሥራ ላይ ነው። ይህ ባይሆንማ ኖሮ ላለፉት አራት ዓመታት በጅምላና በግፍ የተፈናቀሉ፣ ታገተው የቁም ስቃይ ሰለባ እንዲሆኑ የተፈረደባቸው ፣ በርሃብና በጥም የሚጠበሱ፣ ታክሞ ሊድን በሚችል ህመም (በሽታ) ህይወታቸው ያለፈ፣ ለማየት ቀርቶ ለመስማትም በሚያስችግር ሁኔታ የተገደሉ ፣ እና ይህም ሁሉ ሆኖ ከጠቅላይ ሚኒስትር ተብየው “አዝናለሁ” የሚል ይፋዊ ቃል የተነፈጋቸው እና እንዲያውም “ቅጠል በጨው እና ሙዝ በዳቦ ተመገቡ” የሚል እጅግ ጨካኝ ስላቅ የተነገራቸው የአያሌ ሚሊዮን ንፁሃን ዜጎች ሁኔታ መሪር ትምህርት በሆነንና ዛሬም ሰሚ ከሌለው የለቅሶና የእየየ ፖለቲካ ነፃ በወጣን ነበር።

እናም ይህ ሊያሳስበንና ይበልጥ ሳይመሽ አስፈላጊውንና ወቅታዊውን የማስተካከያ እርምጃ እንድንወስድ ግድ ይለናል።  የማስተካከያው እርምት ወይም እርምጃ አንድና አንድ ብቻ ነው። ለዚህ ሁሉ ዘመን ጠገብ የመከራና የውርደት ማንነት ዋነኛ ምክንያት የሆነውን የጎሳና የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞችንና የህሊና ቢስ ግብረ በላዎቻቸውን ሥርዓት እንደ ሥርዓት በላቀ ንቃትና አደረጃጀት በሚመራ የፖለቲካ ሃይል እና በሲቪል ድርጅቶች ጠንካራ ድጋፍ ሰጭነት በማስወገድ ለሁሉም ዜጋ የሚስማማ ሥርዓትን እውን ማድረግ ነው እውነተኛው የነፃነትና የፍትህ መንገድ።

ከዚህ ያነሰውን እንቅስቃሴ ደጋግመን ሞክረነው ደጋግመን የወደቅንበት እና የባሰ መከራና ውርደት አዙሪት ውስጥ የገባንበት የመሆኑን መሪር ሃቅ ከምር ተረድተንና ተቀብለን ይህንን ክፉ አዙሪት ሰብሮ ለመውጣት የሚያስችል ቁመና እና አቅም እስካልፈጠርን ድረስ ከዚህ በባሰ የመከራና የውርደት ማጥ ውስጥ እያለቀስንና እየተላቀስን እንቀጥላለን። ለነገሩ ለቅሷችንና መላቀሳችን ራሱ ትርጉም እያጣብን ከመጣ ወራት ሳይሆኑ ዓመታት ተቆጠሩ። ገዳይና አስገዳይ ፣ አሳሪና አሳሳሪ፣ አፋኝና አሳፋኝ፣ ባለጌና አባላጊ፣ የሃሰት (የውሸት) መምህርና ደቀ መዝሙር ፣ ወዘተ የሆኑ ተረኛ የጎሳና የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች ዓላማና ግብ ግልፅና ግልፅ ነው።

ለመሆኑ የፖለቲካውን መዘውር በተረኝነት የሚዘውሩት ኦህዴዳዊያን (ብልፅግናዊያን) ለሩብ ምእተ ዓመት በህወሃት አሽከርነት የፈፀሙትንና ያስፈፀሙትን እጅግ አስከፊ ፖለቲካ ሠራሽ ወንጀል ለመስማት በሚያስቸግር ሁኔታ ለማስቀጠል ለምንና እንዴት ወሰኑ? ለግፍ እና ለዝርፊያ የፖለቲካ ሥልጣናቸው ማስፈፀሚያ ይሆን ዘንድ በቀመሩትና ሥራ ላይ ባዋሉት ህገ መንግሥት ላይ ጥያቄ የሚያነሳ ወዮለት የሚሉት ለምንድን ነው?   የሚሉና የመሳሰሉ ጥያቄዎችን በስሜታዊነት ሳይሆን ከመሪሩ የፖለቲካ እውነታ አንፃር ለመመለስ ሞክረን እናውቃለን?

አስከፊ የፖለቲካ ቁማራቸውን ለምን የሙጠኝ አሉ? ዋና ዋናዎቹን ምክንያቶች እንደሚከተለው ልጥቀስ፦

ሀ) እነዚህ ገዥ ቡድኖች የተነሱበት የፖለቲካ አስተሳሰብ (ርዕዮተ ፖለቲካ) ይህን ትውልድ ከመበከል አልፎ መጭ ትውልዶችንም በተራ የፖለቲካ ትርክት ብቻ ሳይሆን በትምህርት ካሪክለም እየቀረፁ፣ ሃውልት ቀርፀው በየአደባባዩ እየተከሉ ፣ በሚቆጣጠሩት ሚዲያ የሚተላለፍ ርካሽና አደገኛ  ፕሮፓጋንዳ  እየነዙ፣ እና ይህ በሚፈልጉት ፍጥነትና መጠን የማይሄድ ሲመስላቸው ደግሞ ጨካኝ ሰይፋቸውን እየመዘዙ አገዛዛቸውን እያስቀጠሉ ያሉት ይህን ካላደረጉ የለመዱት ልክ የለሽ የየግል አኗኗራቸው ሊጓደል የመሆኑ ሥጋት ህሊናቸውን ስለሚያቃዣቸው፣

ለ) እንደ የብአዴን አይነት ፖለቲከኞች ደግሞ ለዘመናት የተዘፈቁበት አጅግ አስከፊ ወንጀል የሚያቃዣቸው የመሆኑ እውነታ እንደ ተጠበቀ ሆኖ ሌላው ሥጋታቸው የበላይነቱን ከሚቆጣጠሩ ጌቶቻቸው የሚሠፈርላቸው የአሽከርነት ምንዳዕ (ክፍያ) እስካልተቋረጠ ድረስ እንወክለዋለን የሚሉት መከረኛ ህዝብ እጣ ፈንታ ጉዳያቸው ባለመሆኑ፣

ሐ) እንደ አብይ  አህመድ ያሉት አንዳንዶች ደግሞ የሆዳቸው መጉደል የሚፈጥርባቸው ሥጋት እንዳለ ሆኖ ገና  በልጅነት እድሜያቸው የተጠናወታቸው ክፉ የሥልጣን ጥም እና ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚመጣ የግል ዝና (narcissist personality/behavior) ህሊናቸውን ስለሚጋርደው ፣

) ዴሞክራሲ እውን ሆነ ማለት ለቁማር መቆመሪያነት የፈጠሩትና የዘረጉት እኩይ ሥርዓት አብቅቶለት ለሥስት አሥርተ ዓመታት በፈፀሙት እጅግ ኢሰብአዊ ፖለቲካ ወለድ ወንጀል ፍትህ ፊት ቀርበው እንደ የሥራቸው መጠንና አስከፊነት ሊጠየቁ እንደሚችሉ ትዝ ባላቸው ቁጥር ስለሚያቃዣቸው፣

መ) ከፖለቲካ ድንቁርና የሚመነጨውን የመከረኛውን ህዝብ ስስ ሥነ ልቦና አሳምረው ስለሚያውቁትና ለማታለያነት ባሰለጠኑት አንደበታቸው ጠልፈው ስለሚጥሉት፣

ሠ) የስለላና የአፈና መረባቸውን ተቋቁሞ መከረኛውን ህዝብ በዴሞክራሲያዊ አርበኝነት አስተባብሮና መርቶ ለድል የሚያበቃ የፖለቲካ ሃይል አለመኖሩን አሳምረው ስለሚያቁ ነው።

ለዘመናት በኖረበት እና በፖለቲካ ሠራሽ ወንጀል የተጨማለቀ ሥርዓት ባስከተለበት ከባድ ሁለንተናዊ ሰቆቃ ምክንያት ሸፍጠኛውና ሴረኛው አብይ አህመድ የፖለቲካ ብልግና ዙፋኑን በተረከበበት ጊዜ ለማታለያነት ባሰለጠነው አንደበቱ የደሰኮረው ዲስኩር ሁሉ እውነት መስሎት እልል ብሎ የተቀበለው የአገሬ ህዝብ ከአራት ዓመታት በኋላም እየተፈፀበት ያለውን እጅግ አስከፊና አዋራጅ ሥርዓት ከሥሩ ለመንቀል የሚያስችል የንቃት ልእልና እና የአደረጃጀት አቅም ለመፍጠር አልተቻለውም።

ከገዥዎች ቀጥሎ ለዚህ አስከፊ ውድቀት ተጠያቂው በቀጥታ የሥርዓቱ አገልጋይ የሆነው፣ በአድርባይነት የፖለቲካ አመንዝራነት የተለከፈው፣ የሚጣልለት ልዩ ልዩ ፍርፋሪ የእናቱን ወይም የአባቱን ወይም የእህቱን ወይም የወንድሙን እና በአጠቃላይ የንፁሃን ወገኖችን የቁም ሰቆቃና የግፍ ግድያ የጋረደበት፣ በተቀዋሚነት ስም የግፍ ሥርዓት ሽፋን ሰጭ የሆነውና እና እጅግ ወራዳ በሆነ የምን አገባኝ ዝምታ ራሱን የደበቀ የሚመስለው ምሁር ተብየ ነው።

ከሰሞኑ እየሆነ ያለው የለየለት የአፈና፣ የሰቆቃና የግድያ ዘመቻ የሚነግረን ይህን ሁሉ የውድቀትና የውርደት ፖለቲካ መሪር ሃቅ ነው። አሁንም ይህ እጅግ መሪር የሆነ መንግሥታዊ ሽብርተኝነት ከምር እያስተማረን አይመስልም።

ቢሆንማ ኖሮ በየአካባቢውና በተናጠል መዋከቡ፣ መታፈኑ፣ መሳደዱ፣ መገደሉና መገዳደሉ ከምር አስቆጥቶን እና በአንድነት ቆመን ለዘመናት ተዘፍቀን የኖርንበትን አስከፊ ሥርዓታዊ ሰቆቃ ሰብረን የነፃነትና የፍትህ አገርን እውን ለማድረግ በቻልን ነበር ። ባለጌና ጨካኝ ገዥ ቡድኖች እንኳንስ በቅጡ ያልነቃንና ያልተደራጀን ይበል የሚያሰኝ ንቃትና ድርጅታዊ አቅም ያለውን ህዝባዊ እንቅግቃሴም “የመሪውን (የመሪዎችን) አከርካሪ ከሰበርነው ተካታዩ የትም አይደርስም” የሚል እጅግ እኩይና ጨካኝ የፖለቲካ ሰብእና የተላበሱ ናቸው።

ወደ መቶ የሚጠጋ የመንደር (አንዳንዱ የቤተሰብ እና የጓደኛሞች ከመሆን አያልፍም) የፖለቲካ ፓርቲ ነኝ ባይ ባለባትና አገራዊ ነኝ የሚለውም በአንደበቱ ስለ ለእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አብዝቶ አየደሰኮረ በልቡ ግን የንግሥና ወይም የሌላ ሥልጣን ህልሙን እየፈታና እየቋጠረ እድሜውን በሚገፋባት አገር ውስጥ ዴሞክራሲን እውን ማድረግ በእጅጉ ፈታኝ ቢሆን ከቶ የሚያስገርም አይደለም።  ይህ ባይሆንማ ኖሮ በዚህ እጅግ አስከፊ ወቅት የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ እምቢተኝነት ከአስከፊ ክሽፈት በመታደግ የሸፍጠኛ ፣ሴረኛ፣ ፈሪና ጨካኝ ገዥ ቡድኖችን ሥርዓት ወደ ታሪክ ሙዚየም ልኮ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊት አገርን እውን ለማድረግ በተቻለ ነበር።

ለዓመታት የዘለቀውና ከአራት ዓመታት ወዲህ ደግሞ ለማመን በሚያስቸግር አኳኋን እጅግ አስከፊ እየሆነ የመጣው የመከራና የውርደት ሥርዓት  ጨርሶ ሃላፊነትና ተጠያቂነት በማይሰማቸው ብልፅግናዊያን (አብያዊያን) ፖለቲከኞች አመራር (መሪነት) ይለወጣል ብሎ እንኳን ለማመን ለማሰብም ይከብዳል። በአሁኑ ወቅት እየታዘብነው ያለው የለየለት መንግሥታዊ አሸባሪነት ከዚሁ እጅግ አስከፊ የፖለቲካ እብደት የሚመነጭ ነው።

እናም መፍትሄው በቅጡ ባልተደራጀና ባልተቀነባበረ  እንቅስቃሴ ምክንያት በተናጠል ከመመታት እና ትግልንም ከማኮላሸት ይልቅ በቅጡ የተደራጀ፣ የታቀደ፣ የተቀናጀ፣ እና ዘላቂነት ያለው ወይም ግቡ የሥርዓት ለውጥ የሆነ ህዛባዊ እንቅስቃሴ ብቻ ነው። የሰሞኑ መሪር ኩነት የሚነግረንም ይህንኑ እውነታ ነው።

ይህ እንደሚሆን እየተመኘሁ አበቃሁ!

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
Go toTop