ዕንባ የድረሱልኝ ጥሪ ነው። ዕንባ የችግር አዋጅ ነው። ዕንባ የፈተና ነጋሪት ነው። ዕንባ የሰቀቀን ውስጣዊ እሳታዊ መግለጫ ነው። ዕንባ የመንፈስ ጭንቀት ረመጣዊ ተፋሰስ ነው፤ ዕንባ የጭምትነት ቁስለት እዢ ነው። ዕንባ የታመቀ ነበልባላዊ ጎመራ ነው። ዕንባ ውስጥን መለኪያ ነው። ዕንባን ለማስቆም ለመነሳት ሆነ፤ ለዕንባ ለመድረስ ደግሞ „ቅድመ ሁኔታ“ አያስፈልግም። እራሱ „ቅድመ ሁኔታ“ የሚለው ቃል ዕንባን ፈጽሞ አይመጥንም። ፍሉ ዕንባ ጥሪውን ሲያስተላልፍ ብስል ከቀሊል ሳይለይ ለሁሉም ሆኖ፤ ግን የሚማገዱት ጥቂቶች የቆረጡት ብቻ ናቸው። ሁላችንም መቆስቆሻ እንፈልጋለን። መቆስቆሻ ባያስፈልገው እንኳን ለዬግል የመንፈስ ምቾት አብዛኛዎቻችን እናዳላለን። ታዲያ ዕንባና ጥሪው ዬት – ከምን ይጠጉ? በዘመነ – ጠቀራ።
እጅግ የማከበራችሁ የሐገሬ ተስፋዎች፤ ይህን ዘመነ – ህማማት መመርምር ማገናዘብ አቃተን ማለት ባላችልም ጊዜው ያልደረሰ የግንዛቤ ችግር ግን ያለብን ይመስለኛል? ሰሞኑን የደንበር ጉዳይ በሚመለከት ተዘውትሮ የምስማው መሰረታዊ ጉዳይ አለ …. „የጎንደር መሬት፤ ጎንደሬ በሱዳን ተመታ“ ወዘተ …. ህም! እም! አደዋ የትግራይ ነበርን? ማይጨውስ የትግራይ ነበርን? ሐረርስ የሐረር ሰው ነበርን? ጎሬስ የኢሊባቡር ነበርን? ይህን መመለስ ስንችል ዛሬ መስጥረን የምንደልቅ እብኖች አይናችን ይከፈታል። ደንበሩ ሲጣስ ማህሉ ደንበር ይሆናል። የሱዳን ይሁን የግብጽ ዘመን የተሻገረ ፍላጎት የአውሮፓ ራዕይ ነው። ቀደምትን ሀገረ – ኢትዮጵያን ለማከሰም የተተለመ። ወያኔ የባንዳነቱን ተግባር እዬፈጸመ ስለሆነ ነገ እንደ ኩርድሾች የቁራጭ አፈር ለማኞች መሆን አይቀሬ ነው በዚህ ከቀጠለ። „የፉክከር ቤት ሳይዘጋ ያደራል“ ….. እንደሚባለው ….
ከዚህ ጋር ተያይዞ ያን ድንቅ ሰላማዊ የዕምነት እኩልነት ትግል „የድምጻችን ይሰማ እንቅስቃሴ“ ለማስቆም በምሽት የተበተነ በራሪ ጹሑፍ የሚያጨፋጭፍ ነበር። ባለቤቱ ማን ነበር? ተከትሎም ሳውዲ ላይ እህትና ወንድሞቻችን ተለይተው „ኢትዮጵያዊ“ እዬተባሉ በባዕድ ሀገር ደመ ከልብ ሲሆኑ ተባባሪው ማን ነው? የኢትዮጵውያን ከጽንፍ እስከ ጽንፍና ቁጣ „ኢትዮጵዊነትን“ አጉልቶ ሲወጣ ከነፃነት ታሪካችን ፍቀት ጋር የተላተመው ዘመቻስ ማን ነበር ያዘጋጀው? አሁን ትናንት አንቦ አካባቢ የሚኖሩ ወገኖች አካላቸው ዓይኑ በቢላዋ ገብያ ላይ አደባባይ ወጥቶ እንደ ሀሞራቢ ዘመን ተቀጥቅጦ ሲገደል፤ እንዲሁም ወደ 600 አባወራዎች ተፈናቅለው ልምና ሲፈረድባቸው ሴረኛው ማን ነው? „የኦሮምያን አዬር ከባዕዳን ወረራ አድነነዋል ስለዚህም ቀጣይነቱ በእጃችሁ ነው ያለውና ጠብቁት“ ተብሎ የተሰጠው ግንጥል ስሜትስ ጅረቱ ዬት ይወስደናል? ይህ ጥቃትን እዬጠጡ መኖርስ አንድነትን ፈጥሮ ትብሺ ትብስ ብሎ ለመሰለፍ አቅምን ካለይግባኝ ወና ማደረጉስ ምን ሊባል ይሆን? በእርግጥም ዕንባው ጎርብጦናልን? መሮናል? አንገፍግፎናል? ከቶስ ይህ አረሮ ዘመንስ አልሰለቸንም ይሆን? ስደቱስ?! —-
ለወጡ ወደ ወያኔ ከመሄድ በፊት እያንዳንዱ የወገኔ ዕንባ – ዕንባዬ ነው፤ የአካሌ ሰቆቃ – ሰቆቃዬ ነው? የአካሌ ችግር – ችግሬ ነው የሚል ሁሉ በብራና ላይ የሚኩለውን መግለጫውን ይዋጠውና እራሱን ሰለመለወጡ በቅድሚያ ያረጋግጥ? ከራስ ሲነሱ ሙሉዑ ብቃት ያለው አቅም ይኖራል። እራስን መለወጥ ሲቻል አብነቱ ሃይልና ብርታት ያስገኛል። እራስን መቅጣት ሲኖር ድፈረት ይፈጠራል። እራስን ከስህተት አርሞ ይቅርታን ተላብሶ ሲነሱ እርግጠኝነት ይኖራል። በስተቀር ግን ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ ነው። ክብሮቼ ወገኖቼ፤ ጠላትን መብለጥና በጠላት መበለጥ ዬት ላይ ስለመስከናቸው እስኪ እባካችሁን መዝኑት – በህሊና አደባባይ።
ኢትዮጵያ ሀገራችን ህዝቦቿ ከስሜን ወደ ደቡብ፤ ከደቡብ ወደ ስሜን፤ ከምስራቅ ወደ ምዕራብ፤ ከምዕራብ ወደ ምስራቅ በሽግሽግ – በውርርስ – ከቦታ ቦታ በመዘዋወር – ተዋህደው የኖሩባት የአብሮነት ተምሳሌት ሀገር ናት። ይህ የዘመናት ሂደት የታሪኳ እንብርት ነው። የጥንካሪያዋ ምንጭም ይሄው ነው። እያንዳንዱ ልጅ ሲወለድ መክሊት ይዞ ይወለዳል። ስለሆነም የእያንዳንዱ መክሊት መስተጋብር ተዋህደው፤ በተፈጥሮ ተቀምረው፤ በጋብቻ አደብ ገዝተው፤ በማህበራዊ ኑሮው ተመክሮ መስኖ ለምተው፤ በፈቃደ እግዚአብሄር ተመርቀው ገናናዋን ታላቅ ሀገር ኢትዮጵያን ገነባ – መሰረተ።
እናት ሀገራችን ኢትዮጵያን የዛሬ ታላላቅ ሀገሮች በዲታነት በቁስ ቢበልጧትም፤ በመንፈስ ሀብታትና በውስጥ ብቃቷ ሆነ ጥራቷ እንዲሁም ከፈጣሪያዋ ጋር በአላት የቀረበ ግንኙነት ልዑቅ መሆኗን እነሱው እራሳቸው ጠንቅቀው ያውቃሉ – ባዕዳኑ፤ አፈር በቀል አንጡራ ጠላት ባንደዎችም ጭምር። ኢትዮጵውያን የትም ይሁን የትም ውስጣቸው ፍሬ ዘለቅ ዕንቁ ነው። ሀገራቸው ኢትዮጵያ ወተቷን አጠጥታ እንደማሳደጓ፤ እሷም በልጃቿ አቻ የሌላት ሀገር መሆኗ ልብ ልክ ነው። ይህ ደግሞ በመንፈስ ብቃትና ብልህነት እያዬነው ነው። ሰለጠነ ከሚባለው ሀገር ከተማራው ዜጋ ያልተማረ አንድ ኢትዮጵዊ፤ በተፈጥሮ የፈጠራ ብቃቱ ሆነ አዳዲስ ሃሳቦችን በማፍለቅ አቅሙ ሆነ ችሎታው ዬት እዬሌለ ነው … አይገናኝም። ባያስመካም፤ ባያስኮራም ሥልጡኑ ጸጋው ሃብቱ ስለመሆኑ ግን መዘለል የለበትም።
የኢትዮጵዊነት የአብሮነቱ ፍቅሩም በሸቀጥ የተገዛ አለነበረም። መከባባሩ ገብያ አልነበረም ለአፍታ ሞቅ ብሎ የሚፈታ፤ ዬእናት ሀገራችን የኢትዮጵያ ታሪካዊ የአርበኝነት ጥንካሬዋ ምድራዊም አልነበረም። ዘንበል ብሎ የሚያደምጣት አምላክ ያላት ሀገር ከመሆኗ ላይ ነው – ረቂቁ አንድምታ። በህገ ልቦና አምላኳን አምና ከነበረችበት ዘመን ጀምሮ እምነቷ ሆነ ትምክህቷ በፈጣሪዋ ነው። በእኛ ዕድሜ እንኳን ዝናብ ሲጠፋ ለእስልም እምነት አባቶች ይነገራል። እባካችሁ „ድዋ“ ያዙ ተብሎ፤ መዕት ሲመጣም „ምህላ“ እንዲያዝ ለተዋህዶ አባቶች ይነገራል።
ደስታውንም ሀዘኑንም በእትብት ሀዲድነት ልባዊነት ጎልብቶ ገቢራዊ የሆነባት የጥቁር በዕት – ኢትዮጵያ እመቤት ነበረች። ወያኔ ሀገርን ለማፍለስ ሲነሳ ይህን አስፈሪ የውህደት ጥንካሬ መበተን ነበረበት – ለስትንፋሱ። በፋሳ ከሰሰከሰው። ኮሳሳ ኢትዮጵያን አልሞ እዬሄደበት ነው። ዛሬ እኮ „ኢትዮጵያዊ“ ማለት ወንጀል ነው። አረንጓዴ ቢጫ ቀይን ሰንደቅአላማ መልበስ ያሳስራል። ያሰድዳል፤ ያስደበድባል። አሳሬ ህግም ተደንግጎለታል – ለሰንደቅአላማ …. የዘመን አረማሞ ወያኔ – ግባዕቱ መቼ ይሆን ?ወደ ሄሮድስ መሪው አፈር ሊያጫውት የሚሄደው በእጅጉ ይናፍቃል —- መሬት ስትርድበት ወያኔን ማዬት —–
ጥንካረዋና ብርቷቷ የኢትዮጵያ እንቅልፍ የነሳቸው የውጪ ኃይሎች አጋጣሚውን ይጠብቁ ስለነበር ብቃቷን ሊሸረሽር የሚችል ሥርዓት ለማምጣት ተግተው ሲሰሩ ኖሩ። በለስ ቀናቸውና አሁን የልባቸውን የሚያደርስ ሽፍታ ወያኔ በማግኘታቸው ትራሳቸውን ከፍ አድርገው በመተኛት የእርስ በርስ ጦርነት ሊያስነሱ የሚችሉ ጥቃቶችን ወሸኔ እያሉ፤ እያጀቡ እርዳታ ለሽፍታው ወያኔ ያጎርፋሉ።
አዬን አኮ ከሰሞናቱ ለአንዲት ወንዝ ገብ ክሪሚ ምን ያህል ጊዜ፤ መንፈስ፤ ገንዘብ፤ አቅም እዬፈሰስ እንደ አለ ….. የኃያላን ሀገር መሪዎች ከዙፋናቸው ወርደው ለክሪሚ ሲያሸበሽቡ ….ፕሬዚዳንት ፑቲን አርቀው መተንፈሻ ቧንቧ ለመንሳት ፊት ለፊት ወጥተው ሲፋለሙ …. በተጨባጭ ተመለከተን። እኛማ እንደ ሰው መታዬታችንም እንጃ ነው …. ያቺ ገናና የነፃነት አንባ፤ የአፍሪካ የነፃነት ተቋም፤ ኢትዮጵያማ …. ማን አስታውሷት? የተከበሩትን ኔልሰን ማንዴላ የነፃነት አባትነትን የሸለመች ድንቅ ሀገር – ኢትዮጵያ፤ መላ አፍሪካን ከቅኝ ግዛት ያወጣች የሞገዳማ ጥንካሬ ብቸኛ ባለቤት ምንጩ – ከሰው ፍጥረት መገኛ ከምንጩ ነበር።
ታዲያ እኛ ምን እንጠብቃለን? ስለ እኛ ዋቢ ጠበቃ የሚሆን ባዕድ ማግኘት ይቻላልን በዚህ አያያዝ? የኢትዮጵያን ታላቅነት ለማን ሲመቸው ነው? ይህነን መርምሮ ማግኘት እንዴት ይሳነን? ይህንን ብናውቅ እኮ የምናቀርበው የድርድር ቅድሚያ ሁኔታ ባልነበረ? ሰው ልህሊናዊ ጉዳዩ የምን „ቅደመ ሁኔታ ነው“ ዕንባው ቅርባችን አይደለንም?! ብናውቅስ የምንመካበት ሰበብ ባልነበረ? ለስበብ የምናጠፋው ጊዜም ባልኖረ? ለጥሎ ማለፍ ሽኩቻም የምናቃጥለው ቆራጣ ጊዜ ባልኖረን? ያገባኛል ለምንልለት „ኢትዮጵያዊነት“ ዕንባ ጥሪውን በምን ክህሎት ይሆን ምላሽ ሰጥቶ ለስኬት የሚበቃው? ማናቸውም የወያኔ ጥቃት የእኔ ጥቃት ብሎ የመንፈስ መስማማት እንዴት ይፈጠር?! ግልጽነት ዘመኑን እንዲመራን መቼ ይሆን ይለፍ https://zehabesha.info/archives/13892 የሚያገኘው?!
እኔ እንደ ሥርጉተ እማስበው ማሸነፍ ከወያኔ በፊት እራስን ነው። ሙሉ ትጥቅና ስንቅ የጎደለው መንፈስ እሽሩሩ እያልን አብዛኞቻችን እስከመቼ? …. ጥቃቱ ይቀጥላል …. ዕንባውም ይጎርፋል …. ሽንፈቱም ይናኛል ….. እግዚአንሄር እኮ ነው በኪነጥበቡ ጠብቆ ያቆያት ኢትዮጵያን እንጂ እንደ እኛማ መትበስበስ እንደ ወያኔ የጥፋት ዕወጃ ቢሆን አልነበረችውም።
እጅግ የሚያሰፈራ ነገር ፊት ለፊት ደግሞ አለ። …. በዬቦታው ዜጋ አይደለህም እዬተባለ የሚነቀል፤ የሚሰቀል መንፈስ ብድሩን ለመመለስ ከተሰናዳ የሚያቆመው አይኖርም። አንድ የማወቀውን ነገር እስኪ ልንገራችሁ። ጎንደር የጓንግን ወንዝ ተከትሎ በአርማጭሆና በጭልጋ መካከል „የጋላ አገር“ የሚባል አለ። ስለ ቃሉ ይቅርታ እኔ የሰጠሁት አይደለም። በጣም ብዙ ቦታዎች በተለያዬ ሁኔታ ዘመኑ የፈቀደው ስያሜ ተሰጥቷቸዋል። ለነገሩ አሁን የእስራኤላውያን ስም ሥልጣኔ ይሁን አላውቅም ሥራዬ ብለን ተያይዘነዋል። የባዕድ ፊደላትንም እንዲሁ፤ ድምጸቱ ፍሰቱ የእኛ ያልሆኑ እንደ እራስ አድርገን ተቀብለናል። „ጨጸ“ በቁቤኛው የሉም። እነዚህ ከነድምጻቸው ደግሞ ከእኛ ተፈጥሮ ጋር ኖረዋል በአንድ ምድጃ።
ስለሆነም የባዕዱ ሲመጣ አናውቅህም ብለው ትርጉም አልባ ያደርጉታል ወይንም የስያሜው መንፈስ ጥንዙልና ፍዙዝ ይሆናል። „ጸጋዬ“ የታላቁ የቅኔው ልዑል ሥያሜ ነው። ልዩ ስጦታ፤ መንፈሳዊ ሃብት፤ የውስጥ ክበረቴ፤ የማንነቴ ረድኤት ከአምላኬ ብቻ የተሰሰጠኝ እንደማለት ነው። ይህን ተፈጥሯዊ ጌጣችን እያፋለሰው ግን ተቀበልናል በዚህ ዘመን። ስለሆነም የቦታው ስያሜ እኔ ተቀብዬ የጻፍኩት አይደለም – ከቀደመው ዘመኑ የሰዬመው እንጂ።
…. ለማንኛውም በዚህ አካባቢ ለዘማናት የኦሮሞ ልጆች ተዋልደው ተጋብተው ኑሯቸውን መስርተው ያሉ እጅግ ብዙ ወገኖቻችን አሉ። ዋልድባ ገዳም ሲመሰረት ሆነ ከግራኝ ጥቃት በኋላም አባቶቻችን የመጡት ከሽዋ ነው። ሌላ ጊዜ ታሪኩን እምለስበታለሁ። የዘመነ መሳፍንት ታሪኩ መሰል ነው፤ የክፈለ-ጦሮች ሰራዊት አሰፋፈርና ኑሮም በመሰል ሁኔታ ተከናውነዋል። አሁን ጎንድር ከተማ አዬር ማርፊያ አዘዞ ጡረታ ሰፈር ወዘተ በጣም በርካታ ቅይጥ ሁኔታ ነው ያለው፤ በጣሊያኑ ንድፍ አስፈፃሚ በወያኔ ደግሞ „በታላቋ ትግራይ“ ዶክተሪን ጎንደርና ወሎ ተመሳሳይ የህዝብ ሰፈራ ተከናውኗል። ይህ ሁሉ እሳት ቢነሳ ማነው ማጥፋት የሚችለው ነው ጥያቄው? መተላለቅ ብቻ።
… እሳት የሚተፋ ዕንባ ይንቀለቀላል … ሁሉም ነገር የዶግ አመድ ነው የሚሆነው። አብሶ የቆላማ አካባቢ ነዋሪዎቹ ተዋጊዎች ናቸው። ቦታውም እራሱ ተዋጊ ነው። እንቅልፍ ወስዶታል ብላችሁ „አያ እከሌ“ ብላችሁ ውድቅት ሌሊት ላይ ብትጠሩት ትራሱ ያዘጋጀውን መሳሪያ መዥልጦ ብድግ ነው …. ቆለኛ ተረጋግቶ ተኝቶ አያውቅም፤ ከትዳር አጋሩ ይልቅ አቅፎ የሚተኛው መሳሪያውን ነው። አልሞም አይስትም። ቆቆች ናቸው። የቆለኛ ሴቷ እራሷ አለባበሷ እንደ ደገዋ አይደለም። ነጠላዋን በቀኝ እጇ አውርዳ ታደገድገዋለች። ስትቀመጠም ቁርጢጥ ብላ እንጂ ዘርፈጥ ብላ ሙሉ አካሏን አደላድላ አይደለም። ዝግጁ ናት …. ለማናቸውም ጉዳይ … ይህ እንግዲህ የአንድ በጣም ውስን አካባቢ ምስል ነው። ሌላውም አካባቢ መሰል ጉዳዮች አሉ። …. ዕንባው ፈንድቶ እሳት መትፋት ሲጀምር የሚያስቆመው አጋዚ የለም።
በሌላ በኩል መቼም ሽማግሌ ግራጫማ መካሪ የጠፋበት ጠፍ ዘመን ላይ እንገኛለን። ነገር ግን በትእግስት – በአርምሞ – በተደሞ ሆነው የሚኖሩት ኢትዮጵውያን በደሉ ሲባዛ፤ እንዲህም ሲከረፋ የነገ ተስፋዎች ወጣቶቹ በውስጣቸው ሽበት ያበቅሉ ናቸውና የተገባ አይደለም፤ ግፉ በዝቷል ወገኖቻችን እዬተገፉ ነው በማለት፤ በነቂስ እየተለቀሙ ሀገር አልባ፣ መሬት አልባ፣ ዜግነት አልባ፣ ማንነት አልባ፣ መኖሪያ አልባ ሆኖ ከሚጠቃው „አማራ ብሄረሰብ“ ጎን ይቆማሉ። በተጨማሪም አማራ አካባቢዎች እትብታቸው የተቀበሩውም ማዕከላዊ ግንዛቤ ያላቸው ወደ ጎሳዊ ስሜትና ግንዛቤ አንወርድም በማለት እራሳቸውን በተዕቅቦ ያቆዩትም ቢሆኑ የለዬለት ድርሻቸውን ለመወጣት ይቆርጣሉ …. ይወስናሉ። ሲበዛ ይገለማል። ሲከርም ይበጠሳል። የማይቻለውን አስኪ ሻግት ተቻለ —- ቀጣዩ መራራ ኮሶ፤ አሰንጋላ እንዳይሆን ሙሴዎችን በትዝብት ይጠብቃል።
ፍትጊያው – ትግሉ – ጦርነቱ – ተከትሎ ሀገርና ህዝብ፤ ትውልድና ታሪክ፤ ከሁሉ በላይ አብሮነትና ፍቅር አፈር ድሜ ይግጣሉ። ኢትዮጵያ ወያኔ የሳላት ኢትዮጵያ ብጥቅጥቅ እንድትል ታጥቆ የዶለተባት ኢትዮጵያ አይሆኑ ትሆንና …. የወያኔ ፍላጎት ሳይሸራረፍ ተግባር ላይ ይውላል። የጣሊያንም ህልም ይሳካል። የባዕዳን ራዕይ ይመሾራል። ግን እኛ ሀገርና መሬት አያስፈልግንም? አትናፍቅም ያቺ ውድ ሀገር ኢትዮጵያ!?!
ለመሆኑ መሰሉ እርምጃ ቢወሰድ፤ በእጥፍ ድርብ ቢወራረድ፤ ይህ ለነገ ይጠቅማል ወይ? ሀገር አልባነት – አፈር አልባነት – ኩራት አልባነት – መመለሻ ቤት አልባነት – ዘር አልባነት – ውርስ ቅርስ ትውፊት አልባነት – መሳቂያነት መኖር ወይንስ ምን ይባል ይሆን? …. ወላጅ አባቴ ሲበዛ ጭምት ነበር። ተራማጅም አስተሳሰብ ነበረው – ያው መምህርነት ልዑቅ ሙያ ነውና። አልፎ አልፎ ምን እዬታዬው እንደሆነ አላውቅም በልጅነቴ ደጋግሞ ያዜመውና ይወደው የነበረ ስንኝ ነበር ሙዚቀኛው ማን እንደ ነበር አላውቅም … ይቅርታ
„እናት አባት ሲሞት በሀገር ይለቀሳል
እህት ወንድም ሲሞት በሀገር ይለቀሳል
አክስት አጎት ሲሞት በሀገር ይለቀሳል
ሀገር የሞተ እንደሆ ወዴት ይደረሳል?“
ሀገር አልባነት ውርዴት ነው፤ አደራ መብላት ነው፤ አንገት መድፋት ነው፤ በራስ መተማመን እንደ አወጣ ገብያ ላይ አውጥቶ መሸቀጠም ነው ፤ ሰንደቅአላማን መጠቅጠቅ ነው። ይህ የሚያረመጠምጥ ከሆነ መከራን ለማስቆም እራስን መለወጥ በእጅጉ ለምን ያቅተናል? ለእኔ ይህ ገና ነው። ፍላጎቱ ብቻ እንጂ መሳሪያውም ማሳውም አልተሰናዳም። በደሉም ሰርስሮ ውስጣችን ገና አልገባም፤ ለዚህም ነው ነገሮችን ሁሉ ሳንመረምር እንደወረደ እያዋህድን መንፈሳችን የሚታወከው። ቁጣችን ቁስለትን የማያተርፈው። ቁሰለት ትርፍ ከሆነ መሸነፍ ያከትምለታል።
መሬት ላይ ያለው እውነተኛ ነገር በወያኔ ላይ ድል ያደረገው እኔ የማልደግፈው ድርጅት ከሆነ ጆሮ ማን ሲሰጠው። ቃለ ምልልስም ከሆነ ማን ቁብ ሰጥቶት ሲያዳምጠው። ማንስ ውጤቱን ሲያደንቀው – ሲያከበረው። ወገኖቼ – የኔዎቹ ቢያንስ „አክሱም ለጋንቤላው ምኑ ነው?“ ሲሉ ሄሮድስ መለስ ሲሳለቁ ያን ጊዜ በነፍስ ወከፍ የነፃነት ትግሉ ቤተሰቦች ቆሰልን። ግን ይህነን ንጹህ ቁስለኝነት እኛ ሸፍነን ወይንም አከናንበን ወይንም ሸጉጠን ከምናስተናገደው የዛሬ ጉድ ጋር ፊት ለፊት ተቀመጠን እስኪ እንመዝነው …. ሃቅን አንፍራ! ቢያንስ ለህሊና። ለእኛ ሲሉ ባሩድ ኑሯቸውን የነጠቀው፤ ትዳርና ቤታችን፣ ልጅና ኑሯቸውን ወጣትነታቸውን፤ የማይጠገበውን የልጅነት ክፈለ ጊዜያቸውን ለካቴና ለፈቀዱትም ትንሽ እንሰብ …. ምስጋናው፤ ዬክበር ቀኑ ማሰናዳቱ መልካም ሆኖ ሳለ ውስጥን አሸንፎ ወቅቱ ለሚጠይቀው ሁኔታ መገዛት አለመቻል ጥሬ ነገር ነው – ጠጠር። ፍልሚያ —-
ሌላው ሳቢያ ተኮር መሆናችንም ሊመረመር የሚገባው መሰረታዊ ጉዳይ ነው። ጊዜ እንዲበላ የምንፈቅድለት እንደ እውነቱ ከሆነ ለሳብያ ነው። ስምምነቱም – ድርድሩም – ውሉም – ቃል ኪዳኑም ለሳቢያ የሰገደ ነው። ለዚህም ነው አድሮ ጥጃ የሚኮነው። „ቂም ይዞ ጸሎት ነው“ ነገሩ። አቅም ማጣትን የፈቀድንለት እኛ እንጂ ዕንባማ የዘወትር ጥሪው አቅም ለድል እንደሚያበቃ ጠንቅቆ ያውቃል። ለድል የሚየበቃው ወሳኝ ነገር የችግሩን ምክንያት ማወቅ ነው።
አጀንዳውም መሆን ያለበት ይሄው ነው። አቅምም – ጊዜም – ገንዘብም – መደመጥም ያለበትም ምክንያታዊ ጉዳይ ላይ መሆን አለበት። ይህ ከሆነ ከሽንፈት ጋር ሳይሆን የቀጠሮ ዝርዝር መርኃ – ግብራችን ከማሸነፋችን ሚስጢር ጋር ይሆናል። ማለምና መከወን ፍሬ ማዬትም ይሆናል ሰነዳችን። ይህን ነው በውስጣችን መዋጥ ያለብን አምክንዮ። የመደራጀትም አስኳል፣ የሩጫውም መስመር ዬድካሙም ዲካ መለካት ያለበት ከዚህ አንጻር ይመስለኛል። ይህ ከሆነ አቅም ሳይባክን፤ ወቅትም ሳያመልጥ፤ ምቹ ጊዜም ሳይሾልክ ሁሉ ነገር ምክንያታዊ ከሆነው ፍላጎታችን ላይ ከዋለ ነገን ማግኘት ይቻላል። ይህ ማለት መቁረጥ መወሰን መሆን መቻል ሦስቱ ሥላሴዎች ማሸነፍን አምጠው ይወልዳሉ …. በተረፈ አንድነት ከአንቦ ለተፈናቀሉ የዕንባ ቤተኞች ለወገኖቻችን ብቸኛ መጠለያ ጥግ ዕንባን አድማጭ በመሆናችሁ አመሰግናችኋለሁ። እንደ እናታቸው ጓዳም ቤት ያፈራውን ማካፈላችሁ ውስጥን ይመረምራል።
ክውናዬ ለዛሬ „ከቶ ዬት ይሆን ዬፍላጎታችን ሴሉ ያለው?“ ብዬ በ23.03.2014 በጻፍኩት ላይ የተከበሩ አቶ ምስክር እውነቱ የሰጡት ገንቢ አስተያዬት ይሆናል። „ዲቃላ አታድርጊው“ እሺ ብያለሁ የእኔ ጌታ። ሲቸገር ነው እንጂ እኔም አልወድም። 17 ዓመት ተግቼ ስጽፍ አይደለም ጋዜጣ ላይ የዋሉት፤ ያልዋሉትን ጌጠኛ ቃላትም ተግቼ መጠቀሜ ለቋንቋው ካለኝ ቀናዒነት ነው። መጻህፍቶቼም በሙሉ ይህን መርህ የተከተሉ ናቸው። ነገር ግን አማርኛ ቃላት የሌላቸው ፊደላት አሉ። „ጰ ና ፐ“ ከሁለቱም የሚፈጠሩ ቃላት የትውስት ናቸው። በተጨማሪም ከዘመን አመጣሹ ኢንተርኔት ጋርም ተዛመጆች አቻቸውን በአማርኛ ማግኘት ይቸግራል። ቃላት እንደ ሥልጣኔ ይሰደዳሉ፤ ይወራረሳሉ፤ ከዚህ ሌላ በሥነ – ግጥም ዘርፍ ገጣሚ በአንድ የግጥም እርእስ ሥር የፈለገውን ቋንቋ ቀላቅሎ የመጠቀም ሙሉ ዓለምዓቀፋዊ መብት አለው። ሌላው ፎንቱ ደቀቀ ስላሉት የድህረ ገጹ ባህሪ ነው። ኢትዮ ዛሬ እኮ ከዘሃበሻም የከሳ ፊደላትን ይጠቀማል። እጅግ የማክብረዎት የሀገሬ ልጅ እኔም እማነበው በመነጸር ነውና እርሰዎም እንዲሁ ያድርጉ ። በተረፈ እኔ በምመራው ድህረ ገጽ ያሉትን ገባ ብለው የቀደሙትና ዋጋቸው ያልቀነሱትን ይመልከቱ፤ በፒዲኤፍ የተሰሩ ናቸውና ማዬት ይችላሉ። www.tsegaye.ethio.info በርከት ያሉ አውዲዎችም አሉ፤ ጊዜ ካለዎት የዳምጧቸው። በተለይ „ተስፋ“ ላይ የመስቀል ባዕልን ምክንያት በማደረግ በ2001 የተሰራ ልዩ አውድዮ አለ …. ይወዱታል። „ስለ ድርጅት“ ጽንሰ – ሃሳብም „ማዕዶት“ ላይ … እርሰዎን ይጠብቃሉ – በተጠንቀቅ ….
የኔዎቹ ላበቃ ነው ፍቅርን ከውስጤ ሰጥቼ። መቆዬት መልካም ነው የምለው ኢትዮጵያን ለማዬት ካበቃ ብቻ ነው ለእኔ።
የዕንባ ቋሚ ጠበቃ መዳህኒዓለም ብቻ ነው።
እልፍ ነና እልፍነታችን እልፍ እናድርገው – በተግባር!
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።