በጀርመን የኢትዮጵያዊያን የዉይይትና ትብብር መድረክ Ethiopian Forum for Dialogue and Cooperation in Germany Äthiopisches Forum für Dialog und Zusammenarbeit in Deutschland
ከስምንት ዓመት በላይ ያስቆጠረውና መቀመጫውን ፍራንክፈርት ከተማ ያደረገው በጀርመን የኢትዮጵያውያን የውይይትና ትብብር መድረክ እንደ ሲቪክ የማህበረሰብ ተቋምነቱ በሀገራችን ጉዳይ ሁለገብ የሆነ ተሳትፎና አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ይገኛል። ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲገነባ፣ የሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን፣ የብሔረሰቦች እኩልነት እንዲረጋገጥ፣ የሃይማኖት ነጻነትና እኩልነት እንዲኖር፣ ሉአላዊነቷ የተከበረች ሀገር እንድትኖረን የበኩሉን ድርሻ በማበርከትም ያልተቋረጠ ጥረት በማድረግ ላይ ነው። ይህንን መሠረታዊ መርሆውን በመንተራስም ከወቅቱ የሀገራችን ሁኔታ ጋር የተዛመደ ተከታዩን ወቅታዊ መግለጫ አውጥቷል።
ሁሉም እንደሚያውቀው በለውጥ ሥም ሀገሪቱ መተዳደር ከጀመረች እነሆ ጥቂት ዓመታትን አስቆጥረናል። የለውጡ ሂደት ወዠቡ በዛበትና ወደፊት መግፋት ተስኖት በለውጥና በነውጥ መካከል ፍትጊያው ቀጥሎ በመንገዳገድ ላይ ይገኛል። ይባስ ብሎም ከሰሜን እዝ የመከላከያ ሠራዊታችን መመታት በኃላ ደግሞ ወደለየለት ጦርነት ተገብቶ ሀገራችን ከአንድ ዓመት በላይ በጦርነት እየታመሰች ትገኛለች። ጦርነቱ እንዴትና ለምን ተጀመረ ወደሚለው ተብሎ ተብሎ ያበቃለት ታሪክ ውስጥ አንገባም። የጦርነቱ መቋጫ ምዕራፍ ግን አነጋጋሪም እንቆቅልሽም ሆኖብናል። በተለይም ደግሞ የጦርነቱ ለኳሽ ድርጅት ነባር መሥራችና የጡት አባት የሆኑት ሰው ከእሥር መለቀቅ እርምጃው ሌሎች ተፈላጊ ወንጀለኞችንም ጭምር እንዳይፈለጉ በር የከፈተላቸው አስመስሎታል።
ጦርነቱና መዘዙ ፣ የመግለጫችን ትኩረት እና ጥያቄ ሰው ለምን ከእስር ተፈታ አይደለም። ከጦርነቱ መካሄድ ጋር ተያይዞ ከቆላ ተንቤን እስከ ሸዋ ሮቢት በሰው ሰራሽ ችግር በከንቱ ለፈሰሰ ደም፣ ለተበተነ ቤተሰብ፣ ለወደመ ንብረት ወዘተ ተጠያቂ አካል ሳይኖር በሽብርተኝነት የተፈረጀን ድርጅት ቁንጮዎች ያለ ፍትሕ እንደ ዋዛ መልቀቅ ግራ አጋቢ ውሳኔ ሆኖ እንዳገኘነው ሳንጠይቅ አናልፍም። ከጦርነቱ ጋር ተያይዞም በአንዳንድ የአማራ ክልል ሥፍራዎችና በብዛት ደግሞ በአፋር ክልል ጦርነቱ እየተካሄደ ባለበት ሁኔታ ጦርነቱ እንዳበቃ ተደርጎ የድህረ ጦርነት መዛነፎችና እርምቶች የሚል መንግሥታዊ ሰነድ አውጥቶ ሌላ አለም ውስጥ መግባት መንግሥት እየሄደበት ያለው መንገድ መሬት ላይ ካለዉ እዉነታ ጋር የተዛመደ ሆኖ አላገኘነዉም። እኛ ሲቪክ ተቋም እንጅ የወታደራዊ ሳይንስ ባለሙያዎችና የጠበብቶች ስብስብም አለመሆናችንን እናውቃለን። የሀገራችን ጉዳይ የሚያሳስበንና የሚያንገበግበንም ዜጎች እንደ መሆናችን ግን ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ የመጀመሪያው ዙር ስለ ተጠናቀቀ ሲባልም የሀገሪቱ ቀጠናዎች ሙሉ በሙሉ የሰላም አየር ሳይነፍስባቸው እንዴትና በምን መልክ ጦርነቱን ማጠናቀቅ እንዳስፈለገም ግልጽ ሆኖ አይታይም። ጦርነቱ እየተካሄደባቸው ያሉት አካባቢዎች የሀገሪቱ አካል አይደሉም ካልተባለ በቀር ለጦርነቱ የሕግ ማስከበርም ሆነ የሕልዉና ዘመቻ የሚል ሥያሜ ሰጠነው ሕግም፣ ሕልውናችንንም አስከብሮ አልተገኘም። እናም ለምን ብለን እንጠይቃለን።
በእርግጥ ክዚሁ ጋር ተያይዞ መንግስት የመጀመሪያውን ዙር የሕልውና ጦርነት ዘመቻ አጠናቅቄያለሁ ሲል ጦርነቱ በራሱ ሌሎች ቀጣይ ዙሮች እንዳሉትና እንዳላለቀም አመላካች እንጅ ችግሩ የመጨረሻ መፍትሔ አለማግኘቱን ይናገራል። ጦርነቱን የጫረውና ሀገሪቱን እያተራመሰ ያለው አሸባሪ ቡድን የመንግስት ኃይል ወደ ትግራይ ክልል አለመግባቱን ተከትሎ ለሌላ ዙር ጦርነት እየተዘጋጀ መገኘቱን እያወገዝን፣ በአንዳንድ የአማራ ክልልና በስፋትም በኣፋር ክልል እያደረገ ያለውን ግልጽ ጦርነት አቁሞ ካፈርኩ አይመልሰኝ የሚል ግትር አካሄዱንም ትቶ በመንግስት ጦርነቱን የማቆም የሰላማዊ ጥሪ ተቀብሎ ከራሱ ጋር አንዲታረቅ ወገናዊ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
በሰንደቅ አላማ ሰበብ የሰዎች ሕይወት መጥፋት፣ ሃይማኖታዊ በዓላት በሚከበሩበት፣ ሕዝባዊ የሰላማዊ ሰልፍ
ትእይንቶች ወዘተ በሚደረጉባቸው ወቅቶች ጊዜ እየጠበቁ ከሰንደቅ አላማ ጋር በተያያዘ በሚፈጠሩ ችግሮች በተደጋጋሚ የሰው ሕይወት እየጠፋ ነው። በዘንድሮው የጥምቀት በዓልም በአዲስ አበባ ዙሪያና በኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ በወይብላ ማርያም የሶስት ሰዎች ሕይወት እንደጠፋ የመገናኛ ዘዴዎች ዘግበዋል። በሰላም በዓል ለማክበር ታቦት አጅቦ በወጣ ሰው ላይ ጥይት ማዝነብና ሕይወትን መቅጠፍ አሳዛኝም፤ አሳፋሪም ድርጊት ሆኖ አግኝተነዋል። በመሆኑም ይህን አይነቱን አሳዛኝ ድርጊት እያወገዝን ለወደፊቱ ይህ አይነቱ ሰው ሰራሽ ችግርም እንዳይደገም መንግሥት ከሰንደቅ አላማ ጋር በተያያዘ የሚታየዉን ተደጋጋሚ ችግር ሕገ መንግሥታዊ መፍትሔ እንዲፈልግለት እንጠይቃለን። የየክልሉ መንግሥታት መለያ ምልክታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ የሀገሪቱ ብሔራዊ የፌዴራል ሰንደቅ አላማ ግን አንድ ወጥ ሊሆን ይገባዋል። ይገባዋል ብቻም ሳይሆን አንድ የፌዴራል መንግስቱ ብሔራዊ ሰንደቅ አላማ በሁሉም ክልሎች እና በዓለም መንግስታት መድረኮችም ከፍ ብሎ የሚውለበለብ የሀገሪቱ መለያ ምልክታችን መሆኑ ሊሰመርበትና ግንዛቤ ሊኖረንም ይገባል። ይህንንም መንግሥት ሕገ መንግሥቱን ተንተርሶ ሳያስወስን በሰንደቅ አላማ ሰበብ በተደጋጋሚ የሰዎች ሕይወት መጥፋት ከቀጠለ ለድርጊቱ ተጠያቂው መንግሥት እንጅ ሌላ አካል ሊሆን እንደማይችል ሳንጠቁም ማለፍ ይከብደናል። ለብዙዎቹ የሀገራችን ፖለቲካዊ ችግሮች የመንስኤ ምንጫቸው ሕገ መንግሥቱ እንደሆነ ስለሚታመን መንግሥት ለሕገ መንግሥት የመሻሻል ለውጥ ትኩረት እንዲያደርግ ወይም እርምጃ እንዲወስድ በአጽንኦት ሳናሳስብ አናልፍም።
ዘር ተኮርና ሃይማኖት ተኮር ጥቃትን ስለማውገዝ፣ ምድራችን በአጠቃላይ የሰው ልጆች መኖሪያ እንድትሆን የተፈጠረች ናት። አንድ ሀገር ደግሞ የአንድ ሀገርን ዜጎች ድንበርም፣ ቀለምም፣ ዘርም ወዘተ ሳይገድባቸው በፈለጉበትና በፈቀዱበት ሥፍራ ተዘዋውረው የሚኖሩበት የዜግነት የተፈጥሮ መልክአ ምድራዊ ስጦታቸው ነው። ባለመታደል ግን የሀገራችን የፖለቲካ አየር በመበከሉ ምክንያት አንድን ብሔር እንደ ባእድ መጤ ዜጋ በመቁጠር ከዚህ አካባቢ ለቀህ ውጣልኝ በሚል ዘመቻ በተደጋጋሚ የሰዎች ሕይወት ጠፍቷል። አሁንም አላቋረጠም። በቅርቡም በምዕራብ ወለጋ አካባቢ በተደጋጋሚ በአማራው ብሔር ላይ ያነጣጠረ ዘር ተኮር ጭፍጨፋና ግድያ ተፈጽሟል። ስለ ዴሞክራሲያዊ ሥርአት ግንባታ፣ ስለ ኢኮኖሚ እድገት ስለ ማህበራዊ ኑሮ ለውጥ ሲነገር መጀመሪያ ክቡር ስለሆነው የሰው ልጅ ሕይወት ሰብአዊ ክብር ቅድሚያ ልንሰጥ ይገባል።
እንደሚታውቀው ሀገራችን ለብዙ የአፍሪካ ሀገሮች በነጻነት ቀንዲልነት ትታወቃለች። ነጻነቷን ጠብቃ ለሌላው የዓለም የጥቁር ዘርም በአርኣያነቷ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ መሆኗ ይታወቃል። ታሪክም በየአምዱ ዘግቦታል። ለፓን አፍሪካ አንቅስቃሴም የመጀመሪያውን ረድፍ ከሚይዙት አገሮች ተርታ የምትመደብ የሚያኮራ አህጉራዊ ታሪክ ያላት ሀገር መሆኗ ይታወቃል። በአህጉሩም ሆነ በዓለም አንገታችንን ቀና አድርገን እንድንሄድ የሚያደርግ ታሪክ እያለን፣ ለራሳቸው የፖለቲካ አላማ ማስፈጸሚያ ሲሉ የዘር ፖለቲካን የመንግስታቸው ፖለቲካ መዘወሪያ በማድረግ እርስ በእርስ አባልተውናል። ይህም ሀገራችን ከነበራት አኩሪ የታሪክ ማማ አውርዶ በመንደርና በክልል ተርታ አሰልፎናል። በመሆኑም የዘረኝነት ኣካሄድ ለሀገራችን ፈጽሞ ኣይበጅምና መንግስትም ብቻ ሳይሆን በየደረጃው ሁሉም ዜጋ የዘረኝነትን ደዌ ሊታገለውና ሊጸየፈውም ይገባል። በኣንዳንድ የሀገሪቱ ኣካባቢዎች የሚፈጸመውን ዘር ተኮር ጥቃት ማቆም ካልተቻለ ደግሞ የወንጀሉ ወንጀለኞች ጫካ ብቻ ነው የሚኖሩትም ብሎ ማመን ይከብዳል። በመሆኑም ሰው በአጠቃላይ በዘሩ በሚከተለው እምነቱ፣ ወዘተ መሳደድም ሆነ መገደል እንደሌለበት እናሳስባለን። ከዚሁ ጋር ተያይዞ በተለይ በአማራዉ ብሔር ላይ በተደጋጋሚ በምዕራብ ወለጋ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በሰሜን ሸዋ በኦሮሞኛ ተናጋሪ ወገኖቻችንም ጭምር እየደረሰ ያለውንም ዘር ተኮር ጥቃት በጽኑ እያወገዝን መንግሥት ለችግሩ የማያዳግም መፍትሔም እንዲፈልግለት እንጠይቃለን።
ሁሉን አካታች ብሔራዊ ምክክርና ንግግር ስለማድረግ፣ ይህንን ርእስ ጉዳይ አስመልክቶ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ብሔራዊ እንቅስቃሴዎች እየተካሄዱ፣ ኮምሽኖችም እየተቋቋሙ እንደሆነ እንከታተላለን። ለውጡ ሽግሽግ ሳይሆን የሽግግር ትርጉምም እንዲኖረው የሚያስችል አንድ አርምጃ ወደፊት ነው ብለንም እናምናለን። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ግን የኮሚሽኑ አባላት ምን ያህል ከመንግሥት ፖለቲካ ውግናና ሳይኖራቸው፣ የብሔርም፣ የሃይማኖትም አድልዎ ሳይደረግባቸው ያለ ምንም ተጽእኖ ተግባራቸውን ያከናውናሉ የሚለው አካሄድ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መሆኑንም ትብብር መድረካችን ማስገንዘብ ይወዳል። በአጠቃላይ የእኛ ዓይነት ተመሳሳይ ችግር ገጥሟቸው የነበሩ ብዙ አገራት ሁሉን አካታች በሆነ የምክክር መድረክ ችግራቸዉን መፍታት እንደቻሉ ሁሉ ሀገራችንም ከእንደዚህ ዓይነት ሀገራት ተሞክሮዎችን በመውሰድም ጭምር ጉራማይሌ ለሆነው ፖለቲካዊ ችግራችን ዘላቂ የሆነ መፍትሔ እንደሚፈለግለት እንገምታለን። ፖለቲካዊ ሀገራዊ የአመለካከት ልዩነት እንደ አንድ ሀገር ልጅነት በጠረጴዛ ዙሪያ በሚደረግ ብሔራዊ ምክክር መፍትሔ መሻቱ ትውልዳዊ መዘመንን አመላካች ነው። ሁልጊዜ በጠብ-መንጃ አፈሙዝ የዴሞክራሲ ስርአት ይወለዳል የሚልን ኦሪታዊ የአስተሳሰብ ምዕራፍንም የሚዘጋ አካሄድ ሰለሚሆን ጅምሩን ከልብ የምንደግፈውና ለፍጻሜም እንዲበቃ የበኩላችንን የሚጠበቅብንንም ድርሻ የምናበረክትበት ፖለቲካዊ እርምጃ መሆኑን ሳንጠቅስ አናልፍም።
ድርድር፣ ድርድርን አስመልክቶ ከተለያዩ የመንግስት አፈቀላጤዎች እርስ በእርስ የሚቃረኑና የሚጣረሱ መግለጫዎች፣ ቃለ መጠይቆች በየጊዜው ስለሚለቀቁ ሕዝቡን ጥርጣሬ ውስጥ ከተውት ይገኛሉ። ይህም በመንግስትና በሕዝባችን መሀል ከፍተኛ የሆነ አለመተማመንን እየፈጠረ የሚሄድ ስለሆነ፣ እርምት ተወስዶ የሚሰጡት መረጃዎች ግልጽነትና ተአማኒነትን ባሟላ መልኩ ከአንድ ማዕከል ወደ ሕዝብ እንዲደርሱ ቢደረግ ተገቢ ነው ብለን እናስባለን። በአጠቃላይ ድርድር ከማን ጋር፣ እንዴትና ለምን የሚሉት ቀጥተኛ የመንግሥት ተግባራት መሆናቸዉን ብንረዳም ሀገራዊ አስተዋጽኦችንን ለማስፋትም ይሁን ለማጥበብ መንግሥት ራሱ በፓርላማው አሸባሪ ብሎ ከፈረጀው ድርጅት ጋር ሊኖረው የሚችለውን አቋምና ሊወስድ ያሰበውን እርምጃ እንደ ዜጋም፣ በኣጠቃላይ ሕዝባችንም የማወቅ መብት አለው ብለን እናምናለን። በመሆኑም ሕዝቡ በሀገሩ ጉዳይ የትም ይሁን የት በማናቸውም ዘርፍ መንግሥታዊ የፖለቲካ አካሄዱ ግልጽ ሊሆንለት ቢገባ ይበልጥ ሕዝብና መንግስት ይቀራረቡበታል እንጅ ሆድና ጀርባ የሚያደርግ አሰራር አይሆንም። ይህም ደግሞ መንግሥትን በዜጎቹ ይበልጥ ተአማኒ ስለሚያደርገው ጠቃሚነቱ የጎላ ነው።
በጀርመን የኢትዮጵያውያን የውይይትና የትብብር መድረክ በሀገራችን ዘላቂ ሠላም ሰፍኖና ዴሞክራሲያዊ ሥርአት ተገንብቶ ማየት የሚመኝ የሲቪክ ተቋም ነው። ምኞትም ብቻ ሳይሆን ዳር ቆሞ ባለመመልከትም በማናቸውም አስተዋጽኦ የማያቋርጥ ተሳትፎ እያደረገ ይገኛል። ይኸው ተሳትፎ እንዲቀጥልም የሀገሪቱ መንግሥታዊ የፖለቲካ አካሄድ ግልጽ እንዲሆንለት በማስፈለጉ የትብብር መድረኩ የአመራር ምክር ቤት ይህን መግለጫ ለማውጣት የሀገሪቱ የምትገኝበት ነባራዊ ሁኔታ አስገድዶታል።
በሀገር ጉዳይ ለመግባባት መንግስታዊ ግልጽነት !
ዘላቂ ሠላም ለሀገራችን ኢትዮጵያ!
2022
በጀርመን የኢትዮጵያውያን የውይይትና የትብብር መድረክ
ፍራንክፈርት/ጀርመን
Email: ethiopianforumfordialogue@gmail.com Tel. Nr.: +4915773912794 +491782844931
Adresse: Postfach 111423, 60049 Frankfurt am Main
በጀርመን የኢትዮጵያዊያን የዉይይትና ትብብር መድረክ Ethiopian Forum for Dialogue and Cooperation in Germany Äthiopisches Forum für Dialog und Zusammenarbeit in Deutschland