October 17, 2021
21 mins read

የሰሜኑ ጦርነትና የመላ ኢትዮጵያዊያን ኃላፊነት !   እስክንድር ነጋ! የህሊና እስረኛ፣ ቂልንጦ አዲስ አበባ !!

Eskinder

1.1 —ረሃብ ወደ መሥራቱ መሸጋገር

በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ያለው ጦርነት ያለ ምክንያት የዓለም አቀፉን ማበረሰብ ትኩረት አልሳበም፡፡ ሶስትና አራት ከባድ ከበድ ከበድ ያሉ ምክንያቶች አሉ ።ግን እንዳቸውም ከአንዣበበው ረሃብ በላይ አይደሉም፡፡ ልብ እንበል፡፡ ያንዣበበው አደጋ ድርቅ አይደለም፡፡ ዘንድሮ የዝናብ ችግር የለም፡፡ ድርቅ የሌለበት ረሃብ ነው ያንዣበበው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ረሃብ፣ “ሰው ሰራሽ ረሃብ” ይባላል፡፡ ድሮ የምናውቀው ረሃብ፣ ተፈጥሮ (ማለትም፣ ድርቅ) የሚያመጣብንን ነበር፡ አሁን እኛ ራሳችን ረሃብ ወደ መሥራቱ ተሸጋግረናል፡፡

ያለንበትን አውድ እናስቀምጠው፡፡ የአው ዱ እውነታ፣ ፈረንጆቹ “Subjective truth – ሃሳባዊ እውነት” የሚሉት ዓይነት አይደለም፡፡ መሬት ላይ የተደረገ ውጊያ ውጤት ነው፡፡ በዚያ ውጊያ፣ ሕወሓት የሰሜን እዝን አስቀድሞ በማጥቃት ጦርነት ጭሯል፡፡ የፌድራል መንግሥቱ የተከፈተበትን ጦርነት ከመከላከል ውጭ አመራጭ አልነበረውም፡፡

ሻዕቢያ ጣልቃ ባይገባ ኖሮ፣ በዐቢይ አህመድ የሚመራው የኢትዮጵያ መንግሥት ይወድቅ ነበር፡፡ ምንም እንኳን ሁሉም ሀገራት የውጭ ጦርን ወደ የግዛታቸው የማስገባት ሉዓላዊ መብት እንዳላቸው ባያከራክርም፣ የውጭ ጦር ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ የመፍቀድ ሥልጣን ያለው ሥራ አስፈፃሚው ነው? ወይስ ህግ አውጪው? ለሚለው ጥያቄ ያለው መልስ ግልፅ አይደለም፡፡ ወደፊት ማከራከሩ አይቀርም፡፡

1.2—የአሸናፊዎች ፍትህ

ጦርነቱ ከተቀጣጠለበት ግዜ አንስቶ ከሰሜኑ የሀገራችን ክፍሎችትግራይ፣ዐማራና አፋር የወጡ ዜናዎች የጅምላ ግድያዎችና አስገድዶ መድፈሮች፣ መጠነ ሰፊ የንብረት ውድመቶች መድረሳቸውና እየደረሱ መሆናቸውን አብስረዋል፡፡ እነዚህ ዜናዎች በስመጥር የሰብዓዊ መብት ተቋማት በከፊል ተረጋግጠዋል፡፡ ሙሉ ስዕሉ ጦርነቱ ካለቀ በኋላ የሚወጣ ይሆናል፡፡

ለሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ግኝቶች የተሰጠው ምላሽ ጉራማይሌ ሆኗል፡፡ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በኩል፣ አብዛኞቹ ሀገራት ዝምታን ቢመርጡም፣ ምዕራባዊያንን በከፊል በድንጋጤ፣ በከፊል “በቀጣይነት ምን ሊመጣ ይችላል?” በሚል ስጋት ተቀብለውታል፡፡ በአሜሪካ በኩል (ሌሎችን ምዕራብያዊያንን ሳይጨምር)፣ በአባይ ጉዳይ የኢትዮጵያን እጅ ለመጠምዘዝ እንደ አንድ ተጨማሪ ግብዓት ልትጠቀምበት አትፈልግም ማለት አይቻልም፡፡

የትራምፕ አስተዳደር በአባይ ጉዳይ ገለልተኛ አልነበረም፡፡ በተለይ በመጨረሻዎቹ የሥልጣኑ ወራት፣ ግብፅ  ወታደራዊ እርምጃ እንድትወስድ እስከማደፋፈር ደርሷል፡፡ የባይደን አስተዳደር የትራምፕን ያህል ፅንፍ ይሄዳል ተብሎ ባይገመትም፣ በጂኦ ፖለቲካው ሂሳብ ከኢትዮጵያ ይልቅ ለግብፅ የላቀ ዋጋ እንደሚሰጣት ይታወቃል፡፡

በኢትዮጵያ መንግሥትም የተሰጠው ምላሽ የተደበላለቀ ነው፡፡ በአብዛኛው፣ ይጠቅሙኛል ያቸውን እያጎላ፣ ይጎዱኛል  ያላቸውን ደግሞ፣ “የምዕራብያዊያን ሴራ ነው” በማለት አጣጥሏቸዋል፡፡ በሌላ በኩልም፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈፀማቸውን በማመን፣ ወታደሮችን አስሮ ክስ እንደመሰረተባቸፈው ገልጿል፡፡ በተጨማሪ፣ የተባበሩት መንግሥታት የምርመራ ቡድን ወደ ሀገር ውስጥ ገብቶ እንዲያጣራ አድርጓል፡፡ ከምር ይሁንም አይሁንም፣ ተጠያቂነት መኖር እንዳለበት ተቀብሏል፡፡

በአንፃሩ ሕወሓት፣ ተዋጊዎቹ ፈፀሟቸው የሚባሉትን የመብት ጥሰቶች ካለመቀበሉም ባሻገር፣ ለይስሙላ እንኳን ጉዳዩን ለማጣራት ምንም ዓይነት እንቅስቀሴ አላደረገም፡፡ ሆኖም፣ ገለልተኛ አካላት ቢያጣሩ ተቃውሞ እንደማይኖረው ተናግሯል፡፡ ወደደም ጠላም፣ በዚህ ጉዳይ በእነ ዐቢይ ተበልጧል፡፡

ግን፣ በሕወሓትም በኩል ሆነ በቀሪዎቹ ተተላሚዎች ዘንድ፣የተሟላ ተጠያቂነት ለማስፈን ልባዊ የሆነ ፍላጎት የለም፡፡ አሁን እንዳለው አካሄድ ከሆነ፣ በመጨረሻ “የአሸናፊ ፍትህ– victor’s justice” የሚሉት ነወ እውን የሚሆነው፡፡ ይህ ማለት፣ ተሸናፊው ተጠያቂ ይሆናል፡፡ የአሸናፊው ግፎች ግን ተሸፋፍነው እንዲታለፍ  ይደረጋል፡፡ ይህ እንዳይሆን፣ለፍትህ የቆሙ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ብርቱ ትግል ይጠብቃቸዋል፡፡

1.3 —-የእጅ አዙር ጦርነት (Proxy war) አደጋ

በዚህ አውድ፣ ቻይናና ሩሲያ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር፣ አብዛኞቹ ምዕራብያዊያን ደግሞ ከሕወሓት ጋር ተሰልፈዋል፡፡ ቻይናና ሩሲያ ጦርነቱ በድርድር እንዲያልቅ ቢፈልጉም፣ እነሱንም ከሰብዓዊ መብት ጋር በተያያዘ ከምትጨቃጨቃቸው አሜሪካ ጎን ተሰልፈው መገኘት አልፈለጉም፡፡ እነ ዐቢይ ምንም አሉ ምንም፣ ምዕራብያዊያን ሕወሓት ወደ ሥልጣን እንዲመለስ ፍላጎት የላቸውም፡፡ ቀደም ብለን ያነሳናቸው ነጥቦች እንደተጠበቁ ሆነው፣ ዋናው ጉዳይቸው ኢትዮጵያም እንደ ሶሪያ የታራዘመ አውዳሚ ጦርነት ውስጥ ልትገባ ትችላለች የሚለው ስጋታቸው ነወ፡፡ እነ ዐቢይም ሆነ ሕወሓት፣ጦርነቱን የማሸነፍ ብቃትና አቅም አላቸው ብለው አያኑም፡፡ ትክክል ይሁኑ አይሁኑ፣ በሂደት ይታያል፡፡

ኃይማኖትን፣ ታሪክን፣ ባህልን፣ ቋንቋን እንደ መለኪያ የምንወስዳቸው ከሆነ፣ ኢትዮጵያ ከጥቁር አፍሪካ ይልቅ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ታጋድላለች፡፡ በ19ኛው ክፍለ ዘመን አውሮፓዊያን እስከሚተኳቸው ድረስ፣ አረቦችና ኦቶማኖች( ቱርኮች) በአፍሪቃ ቀንድ ያሉትን የባህር በሮች (ወደቦች) በሙሉ ለአንድ ሺህ ዓመታት በእጃቸው አስገብተው፣ አካባቢውን በበላይነት ተቆጣጥረው ኖረዋል፡፡

በመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት ድጋፍ ኤርትራ ከኢትዮጵያ መገንጠል መቻሏ፣ በ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ከአፍሪቃ ቀንድ መልቀቅ በጀመሩበት አውሮፓዊያን እግር፣ የአረብ ሀገራት እየተተኩ መሆናቸው አመላክቷል፡፡ በአሁኑ ግዜ፣ ቱርክ፣ ሳውዲ አረቢያና የተባበሩት ኤመሪትስ በአፍሪቃ ቀንድ ያሏቸው የጦር ቤዞች ስድስት ደርሰዋል፡፡ የሰሜኑ ጦርነት በፍጥነት ካልተቋጨ፣እነዚህ ኃይሎች በተዘዋዋሪም ቢሆን ጣልቃ መግባታቸው አይቀርም፡፡ ይህ ከሆነ፣ ጦርነቱ በቀላሉ የሚቋጭ አይሆንም፡፡  አደጋው ከፍ ያለ ነው፡፡

እውነት ለመናገር፣ ከእኛ ይልቅ ምዕራብያዊያ አደጋውን በተሻለ ደረጃ ተረድተውታል፡፡ በየመን፣ በሶሪያና በሊቢያ የሆነው ይታወቃል፡፡ በየመን አላልቅ ባለው ጦርነት፣ በአንድ በኩል ሳውዲና ኤመሬትስ፣ በሌላ በኩል ኢራን ተሰልፈው ቅልጥ ያለ የእጅ አዙር ጦርነት (Proxy war) ላይ ይገኛሉ፡፡ የሊቢያው ጦርነት፣ ቱርክና ግብፅ በተዘዋዋሪ የሚፋለሙበት መድረክ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ይባስ ብሎ፣ ምዕራብያዊያና ሩሲያም ተደርበውበታል፡፡ በሶሪው ጦርነት እጃቸውን ያስገቡ ብዙ በመሆናቸው፣ ሶሪያዊያን ሀገራቸውን በቀላሉ አያስመልሱም፡፡

በእኔ ዕይታ፣ ምዕራብያዊያኑ፣ “የሰሜኑ ጦርነት ወታደራዊ መፍትሄ የለውም” የሚሉት ከፖለቲካዊ  ይልቅ ወታደራዊ ግምገማ አድርገው የደረሱበት ድምዳሜ ነው፡፡ ግምገማቸው ትክክል ነው፡፡ ያልተረዱት ስሜታችንን፣ ሥነ ልቦናችንን፣ ባህላችንን ነው፡፡ ፖለቲካችንንም አልተረዱትም፡፡ በእኛ በኢትዮጵያዊያን በኩል በፌድራልም ሆነ በሕወሓት ወታደራዊ መፍትሄ እንደሌለ በተግባር መሬት ላይ እስካልተረጋገጠ ድረስ፣ ስሜታችን፣ ሥነ ልቦናችን፣ ባህላችንና ፖለቲካችን እውነታውን ቀድም ብለን እንድናምን አይፈቅዱልንም፡፡ ተዋግተን ሳንደክም አንገላገልም።

1.3 — ያተሰወረ እውነታ

መሬት ላይ ያውን እውነታ እንቃኘው፡፡ ሕወሓት ጦርነቱን  በወታደራዊ ኃይል የማሸነፍ አቅም የለውም፡፡ ወደ አዲስ አበባ ቢገፋ፣ ሻዕቢያ ከበስተጀርባ ውጊያ ይከፍትበታል፡፡ ወደ አሥመራ ቢገፋ፣ መከላከያ ከበሰተጀርባ ውጊያ ይከፍትበታል፡፡ መከላከያና ሻዕቢያ ተጣምረው ጥቃት ከሰነዘሩበት ደግሞ፣ ወይ ይደመሰሳል፣ ወይ ከተሞችን ለቆ ወደ በረሃ ለመሸሽ ይገደዳል፡፡ጥቃቱን በመሥመራዊ ውጊያ የመመከት ዕድሉ የጠበበ ነው። በደቡብ ጎንደር የደረሰበት ሽንፈት፣ የማጥቃት አቅሙ (offensive capability) ጦርነቱን ለማሽነፍ በቂ እንዳልሆነ አሳቷል፡፡ የጥይት፣ የከባድ መሣሪያ፣ የነዳጅና የመድኃኒት እጥረት አለበት፡፡ ከሱዳን ጋር የሚያገናኘው ኮሪደር እስካልተከፈተ ድረስ፣ ከማጥቃት ይልቅ የመካከል አቅም ነው የሚኖረው፡፡

እነ ዐቢይ ላስተላለፉት የተጠናጠል የተኩስ ማቆም ውሳኔ አዎንታዊ ምላሽ ባልሰጠበት ሁኔታ መጠነ ሰፊ ረሃብ ከተከሰተ ደግሞ፣ ከትግራይ ህዝብ ጋር የመቃቃር እድሉ እየሰፋ ይሄዳል፡፡ በቀኝም በግራም አጣብቂኝ ውስጥ ነው ያለው፡፡ ሁለቱም ወገኖች የሚያከብሩት የተኩስ ማቆም ስምምነት ቢኖር፣ ከእነ ዐቢይ ይልቅ ሕወሓት ይበልጥ ይጠቀማል፡፡

በእነ ዐቢይ በኩል፣ ትግራይን በሁለት መንገድ ዳግም መያዝ ይችላሉ፡፡ ከውጊያ አኳያ ብቻ የሚታይ ከሆነ፣ መከላከያና ሻዕቢያ ተቀናተው ትግራይን መያዝ ይችላሉ፡፡ ግን ከሻዕቢያ አኳያ፣ ጦርነቱ የሚያስከፍለው የሰውና የቁስ ዋጋ ስለሚኖር፣ በአንድ በኩል፣ የኤርትራ ህዝብ ጦርቱን ይደግፈዋል ወይ? የሚለው ጥያቄ ከምር መታየት አለበት፡፡ ወደ ትግራይ ገባ ብሎ መውጣት አይቻልም፡፡ መሬትን ቆንጥጦ መያዝና መቆየት ይጠይቃል፡፡ በሌላ በኩል፣ የኤርትራ የተዳከመ ኢኮኖሚ ለጦርነቱ የሚያስፈልገውን ወጪ ለመሸፈን ስለሚቸገር፣ የጉዳዩ ዋና ባለቤት ከሆነችው ኢትዮጵያ ጋር ወጪን ለመጋራት ስምምነት ላይ መድረስ ያስፈልጋል፡፡

ስለዚህም፣ በቀላሉ የማይፈቱ ጥያቄዎች ባሉበት አውድ ከሻዕቢያ ጋር ተቀናጅቶ ትግራይን ከመያዝ ይልቅ፣ በመከላከያ ብቻ የሚፈፀም ተግባር ቢሆን ለእነ ዐቢይ ተመራጩ መንገድ ይሆናል፡፡ የሁለትና ሶስት ወራት ሥልጠና ብቻ በተሰጠው  ጦር ይህን ማድረግ እንደሚቻል በኢትዮሱማሊያ ጦርነት ታይቷል፡፡ ግን ይህን ታሪክ መድገም ቢቻል እንኳን፣ ሕወሓትን ከእያንዳንዱ ዋሻ ማጽዳት አይቻልም፡፡ ይህን ማድረግ እስካልተቻለ ድረስ ደግሞ፣ ከህዝብ ካለው ድጋፍ አንፃር፣ ቀስ እያለ ማደጉ አይቀርም፡፡ ብቃት ያላቸው የጦር አዛዦች፣ ታማኝና ዲሲፕሊንድ የሆኑ ተዋጊዎች አሉት፡፡ በረዥም የግዜ ሂደት፣ ከእነ ግብፅ ጋር መቀናጀቱም አይቀርም፡፡ ይህ እውነታ ከእነ ዐቢይ የተሰወረ አይደለም፡፡

1.4—የኃያላት ትብብር

እውነት ለመናገር፣ እነ ዐቢይ የተናጠል የተኩስ ማቆም ውሳኔ በማስተላፍ ለድርድር ዝግጁ መሆናቸውን ቀደም ብለው በተግባር አሳይተዋል፡፡ የትግራይ ህዝብ በረሃብ አለንጋ እየተገረፈ መሆኑን የሚናገረው ሕወሓት፣ ለህዝቡ ሲል ተመሳሳይ እርምጃ አለመውሰዱ፣በታሪኩ ከፈፀማቸው መሰረታዊ ስህተቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ በሕወሓት ወታደራዊና ፖለቲካዊ አቅም መካከል ክፍተት እንዳለ አመላክቷል፡፡

የጦርነቱ መልክ በትንሽ ሳምንታት ውስጥ ይለያል፡፡ እነ ዐቢይ ለረዥም ግዜ የተጠበቀውን የማቃት ዘመቻቸውን በቅርቡ ይጀምራሉ፡፡ ያኔ፣ ወይ ህወሓት ተንዶ ወደ ዋሻዎቹ ይመለሳል፣ ወይ በተዓምር መክቶ ይዞታዎቹን እንደያዘ ይቆማል፡፡ ጦርነቱ በዚህም ሄደ በዚያ፣ ከማጥቃት ዘመቻው በኋላ ቢያንስ አንዱ ወገን ለድርድር ዝግጁ ይሆናል፡፡ ሁለቱንም ወገኖች የድርድር ጠረጴዛ ላይ ለማስቀመጥ ግን፣ መሬት ላይ ካለው እውነታ ይልቅ፣ የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ጫና ይበልጥ ውጤታማ የመሆን ዕድል አለው፡፡ ግን ይህም ቢሆን ለግዜው የሚቻል አይደለም።

ግዜው ሲደርስ፣ በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ በኩል የሚኖረው ግፊት፣ አሜሪካ፣ቻይና፣ሩሲያና የአውሮፓ ህብረት ካልተባበሩ ሙሉ ለሙሉ ውጤታማ አይሆንም፡፡ በእነዚህ ኃይሎች መካከል ከባድ ፉክክር ያለ ቢሆንም፣ ፈፅመው ሊተባበሩ የሚችሉ አይደሉም የሚባሉ አይደሉም፡፡ አሁን እንዲተባበሩ የሚያስችላቸው ጉዳይ አለ። ረሃብ በሞት ከሚቀጥፋቸው ሰዎች መካከል፤ ከአራቱ ሶስቱ ከአምስት ዓመታት በታች የሆኑ ህፃናት ናቸው፡፡ አራቱ ኃይሎች (አሜሪካ፣ ቻይና፣ ሩሲያ፣ የአውሮፓ ህብረት) የእነዚህን ህፃናት ህይወት ለመታደግ መተባበር ካልቻሉ፣ በምን ጉዳይ ሊተባበሩ እንደሚችሉ ማሰብ ይከብዳል፡፡

በአሁኑ ግዜ፣ አራት ኃይሎች ጦርነቱን ለማስቆም መተባበር እንደማይችሉ ተቀብለው፣ ቢያንስ ቢያንስ ግን፣ ጦርነቱ ኖረም አልኖረም፣ ለተራቡት እህል ለማድረስ እንዲተባበሩ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊማፀናቸው ይገባል፡፡

የተራቡ ወገኖቻችን ከፖለቲካ ይበልጣሉ፡፡ ይህን ታሳቢ ያላደረገው የአሁኑ ሀገራዊ አካሄዳቸውን፣ በምድርም በሰማይም የሚያስጠይቀን ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

ከነፃነት ዘገዬ የአራት ኪሎው ኦነግ ሸኔ ከቁጥር ጋር እንደተጣላ ዕድሜውን አገባደደ፡፡ ኦነግ/ኦህዲድ ዛሬም ሆነ ዱሮ፣ በቤተ መንግሥትም ይሁን በጫካ ቁጥር ላይ ያለው አቋም ምን ጊዜም ያስደንቀኛል፡፡ ደግሞም እየባሰባቸው እንጂ ሲቀንሱ አይታዩም፡፡ ጥቂት

80 ቢሊዮን ብር ስንት ብር ነው?

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

Go toTop