ከሊሊ ሞገስ
በማንኛውም የስራ መስክ ስኬታማ ለመሆን ከሰዎች ጋር ተግባብቶ አብሮ የመስራት ብቃት ሊኖረን ይገባል፡፡ ከሰዎች ጋር አብሮ ለመስራትና የፈለጉትን ለማግኘት ደግሞ የሰዎችን ባህሪና ፍላጎት ቀድሞ የመገንዘብ ችሎታ ያስፈልጋል፡፡ በተጨማሪም የሰዎችን ባህሪ ለመገንዘብ የዓመታት ጥረት እና ልምምድን ይጠይቃል፡፡ ጥረት እና ልምምዱን የምናደርገው እንዲሁ በደመ ነፍስ ሳይሆን የሰዎችን ስነ ልቦና በማጥናት ነው፡፡ የሰዎችን ስነ ልቦና በማየት ወይም አብሮ በመሆን በቀላሉ የምንገነዘበው ቀላል ነገር ሳይሆን ጥበብን፣ የረጅም ዓመት ጥናትና፣ ምርምርን የሚጠይቅ ውስብስብና ድብቅ ነገር ነው፡፡
እንግዲህ እርስዎም የሰዎችን ባህሪ ለመረዳት እና ሰዎችን እንደባህሪያቸው ለመያዝ ከፈለጉ ይህንን ሁሉ መንገድ ማቋረጥ አለቦት፡፡ ወይም ደግሞ ሰዎችን መረዳት የሚችሉበት አቋራጭ መንገድ መፈለግ፡፡ ምን ጊዜም ረጅሙን መንገድ ከመጓዝ አቋራጩን መንገድ መጠቀም እደሚያፈጥን የታወቀ ነው፡፡ የሰዎችን ባህሪና ማንነት ለመረዳት የሚያስችሎት አቋራጩ መንገድ ረጅምን መንገድ የተጓዙ ሰዎች ያቀረቡትን መረጃ፣ ሀሳብ እና መርህ መዳሰስ ነው፡፡
ለዛሬ ከሰው ልጅ ባህሪ ውስጥ ብዙዎችን የተጠናወተውን የኃያልነት ስሜት እንዴት መቋቋም እንዳለብን እና ኃያል የሚባሉ ሰዎችን ምን አይነት ብልጠት ተጠቅመን ከእነሱ የፈለግነውን ነገር ማግኘት እና ያሰብነውን ነገር ማሳካት እንድንችል የሚረዳንን የመጀመሪያውን መርህ እናቀርብሎታለን፡፡
ሁሉም ሰው ኃያልነትን ይፈልጋል፡፡ ደካማ መሆንንም ሆነ መምሰልን ማንም አይፈልግም፡፡ በሰዎች ላይ ተጽዕኖ የመፍጠር አቅም ወይም ኃይል የሌለን መስሎ ሲሰማን ሁላችንም ስሜታችን ይጎዳል፡፡ ሆኖም ግን በዘመናችን በየትኛውም የዓለም ክፍል ኃያል ለመሆን ያለንን ፍላጎት እና የኃይል ጥማታችንን በሚያሳብቅ መንገድ ካንፀባረቅን አደገኛ ችግር ሊያጋጥመን ይችላል፡፡
በዚህም የተነሳ ምን ጊዜም ቅን ባንሆንም ቅን መሆን በሚገባን ስፍራ ቅን መስለን መታየት፣ ኃያል መሆን የምንፈልግ ቢሆንም ኃያል ሆኖ መታየታችን የሚጠላና የሚያስጠቃን ከሆነ ደካማ ሆነን መቅረብ ይገባናል፡፡
በዘመናችን በየሀገሩ ሲነገሩ የምንሰማቸው አያሌ መፈክሮችና መርህዎች ተጨባጭ የሆነውን እውነታ የተቃረኑ ናቸው፡፡ ‹‹ዓለም በልጽጋለች፣ ዘመን ተለውጧል፣ በዚህ በበለፀገ ዘመን የሀገር መሪዎች ፍትሃዊ፣ ለዴሞክራሲ ተገዥና የህዝብን የበላይነት የተቀበሉ መሆን አለባቸው፡፡ ማንኛውም ሰው ምንም ሆነ ምንም እኩል መብት አለው›› የሚሉና መሰል መርህዎችና መፈክሮች በብዛት ሲደሰኮሩ ይደመጣል፡፡
እርሶ በቅንነት እነዚህን ለመሳሰሉ አባባሎችና መርሆዎች በሙሉ ሳያወላውሉ ከተከተሉ እና ለመርህዎች ተገዥ ከሆኑ ሁልጊዜ በዙሪያዎት ያሉ እንደ እርሶ ሞኝ ያልሆኑ ብልጣብልጦች ወደ ታች ይጫንዎታል፡፡ ሁሉንም ሰው በስራው፣ በእውቀቱ በችሎታው የላቀውንም እውቀት የሌለውንም በተመሳሳይ መንገድ ማስተናገድ ማለት በሰዎች መሀከል ያለውን ልዩነት አለመገንዘብ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ምንም ችሎታ የሌላቸውን ደካማ ሰዎች ከሚገባው በላይ መካብ፣ ጠንካራ እና ብርቱ የሆኑትን ደግሞ እንደ ማንኳሰስ ይቆጠራል፡፡ ሰዎችን እንደ እውቀታቸው፣ ችሎታቸው እና ስራቸው ልዩነት ፈጥሮ መመዘንና መንከባከብ ደግሞ ለድካማቸውና ለስራቸው ዋጋ እንደመስጠትና እንደማበረታታት ይቆጠራል፡፡
ኃያል ሰዎችን መቆጣጠሪያ መርህ
‹‹ምን ጊዜም ከእርሶ በላይ ኃያል የሆኑ ሰዎች የኃያልነት ስሜት እንዲሰማቸው ያድርጉ፡፡ የእንዲህ አይነት ሰዎችን ቀልብ ለመማረክ ወይም በእነሱ ዘንድ ለመደነቅ ችሎታዎትንና ብቃትዎን አጉልተው አያውጡ፡፡ ምክንያቱም እንዲህ አይነቱ ነገር በተቃራኒው በእነኚህ ሰዎች ላይ ፍርሃት ሊያሳድር ስለሚችል ሊጠሉ እና ለብቀላ ሊዳረጉ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ከእርስዎ በላይ የሆኑ ሰዎችን በመማረክ ኃያል ለመሆን ከፈለጉ እነዚያ ሰዎች ካላቸው ኃያል በላይ ኃያል መሆንዎን በጥበብ ይግለፁ፡፡
ከዚህ መርህ በተቃራኒው መንገድ ከተጓዙ ግን በህይወትዎ ላይ አስከፊ ጉዳት ለሚያስከትልቦት አደጋ ሊጋለጡ ይችላሉ፡፡ በአንድ ወቅት የፈረንሳይ የገንዘብ ሚኒስቴር የነበረው ኒኮላስ ፎኩዌት ይህንን መርህ በመጣሱ የገጠመውን እናካፍልዎት፡፡
ፎኩዌት ሉዊስ አስራ አራተኛ የፈረንሳይ ንጉስ ሆኖ ሲመረጥ የገንዘብ ሚኒስቴር እንዲሆን ተሰየመ፡፡ በዚህ ስራው ባገለገለበት የመጀመሪው ዓመት በጣም ለጋሽ፣ ድል ያለ ግብዣ ማዘጋጀት እና ውብ ሴቶችን የሚወድ እና መምራት ለሚፈልገው የቅንጦት ህይወት ገንዘብና ስልጣን ፈላጊ ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በስራው ትጉህ እና በንጉሱም ዘንድ ተቃሚ ሰው ተደርጎ ይቆጠር ነበር፡፡ በ1661 የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስቴር የነበረው ዳላስ ማዝሪን ሲሞት ፎኩዌት እሱን ቦታ ንጉሱ እንደሚሰጠው ተማምኖ ነበር፡፡ ንጉሱ ግን የጠቅላይ ሚኒስቴርነት የስልጣን ቦታ እንዲቀር አደረገ፡፡ ፎኩዌት ንጉሱ ይህን ያደረገው ለእሱ የነበረው ክብርና ግምት ስለቀነሰ ስለመሰለው አስደናቂ ነገር የመስራት ችሎታውን ሊያሳየው ወሰነ፡፡
በነጋታው ስራውን የጀመረበትን አንደኛ ዓመት አስመልክቶ ድል ያለ ፓርቲ አዘጋጀ፡፡ ፓርቲው በዚህ ሰበብ ቢዘጋጅም ዋነኛ አላማው ግን ተጋባዥ እና ታላቅ እንግዳ ለነበሩት ለንጉሱ ግብር እንዲሰባሰብላቸው ለማድረግ ነበር፡፡ በግብዣው ላይ በሀገሪቱ ታዋቂ እና በጣም ተወዳጅ የነበሩ ገጣሚያን ተጋብዘው ቀረቡ፡፡ ፓርቲው በሰባት ደረጃ በተመደበ የእራት ስነ ስርዓት ተጀመረ፡፡ በግብዣው ላይ በፈረንሳይ ተወዳጅ ከሚባሉት ምግቦችና መጠጦች ውስጥ የቀረ አልነበረም፡፡ በፈረንሳይ ውስጥ ከዚያ በፊት ተቀምሰው የማይታወቁ አዳዲስ ምግቦች ለመጀመሪያ ጊዜ ተዘጋጅተው ነበር፡፡ ፎኩዌት ለንጉስ ክብር የመረጠው የክላሲካል ሙዚቃ ምግቡን ለማወራረድ በሚመች መልኩ ከክላሲካል ሙዚቃ ተጫዋች ተቀነቀነ፡፡
ፓርቲውን የታደሙት ሹማምንቶችና መኳንንቶች ዝግጅቱ ግሩም እንደሆነ ሲያወሩና ፎኩዌትን ሲያደንቁ አመሹ፣ ምሽቱ በሰላም ተጠናቀቀ፡፡
በነጋታው ፎኩዌት በንጉሱ ትዕዛዝ ዘብጥያ ወረደ፡፡ ከሶስት ወር በኋላ የሀገርን ገንዘብ ያለ አግባብ በማባከንና በመዝረፍ ተከሰሰ፡፡ (በእውነቱ ብዙውን ገንዘብ ከንጉሱ ጋር ተነጋግሮ እና ንጉሱ ፈቅዶለት አብረው የዘረፉት ነበር) ፎኩዌት ጥፋተኛ ሆኖ ስለተገኘ ቀሪውን የ20 ዓመት ዕድሜውን በፈረንሳይ በተራራ ላይ ተገልላ በምትገኘው እስር ቤት እንዲያሳልፍ ተፈረደበት፡፡
የፈረንሳይ ንጉስ የነበረው ሉዊስ አስራ አራተኛ ሲበዛ ኩሩ እና ትእቢተኛ ስለነበር ሁል ጊዜ በዙሪያው ያሉ ሰዎች አትኩሮት እና ክብር ለእሱ ብቻ መስጠት እንዳለባቸው ያምን ነበር፡፡ ፎኩዌት ፓርቲውን ያዘጋጀው ለንጉሱ ያለውን ታማኝነትና ክብር እንዲሁም ጉብዝናውን፣ ታታሪነቱን፣ በሌሎች ዘንድ ያለውን ክብር በማንፀባረቅ ለጠቅላይ ሚኒስቴርነት እንዲታጭ በማሰብ ነበር፡፡
ሉዊስ ግን ፓርቲውን የተካፈሉ መኳንትና ሹማምንቶች ፎኩዌትን ሲያሞግሱና ሲያደንቁት ሲመለከት ጓደኞቹ ከእሱ ይበልጥ የበታቹ የሆነውን የገንዘብ ሚኒስቴሩን ሲያወድሱ፣ ፎኩዌትም የንጉሱን ኃያልነት ማሳየትና ንጉሱን ማላቅ ሲገባው ራሱን በማላቁ ተንገበገበ፡፡ በእርግጥ ንጉስ ሉዊስ መንገብገቡን ለማንም አልተናገረም፡፡ የውስጡን በውስጡ ይዞ ደህንነት እንዳይሰማው ያደረገውን ሰው ሰበብ ፈልጎ ከአቅራቢያው አራቀው፡፡ ከዚህ በኋላ ጂን ባብቴዝ የተባለውን አማካሪ በመቅጠር ከፎኩዌት የበለጠ ስሙን ሊያገንለት የሚችል አስገራሚና አስደናቂ ቤተመንግስት አስገነባ፡፡ ቤተ መንግስቱን ሲያስመርቅ የፎኩዌት የህዝብን ገንዘብ ያለ አግባብ በመበዝበዝ በሚል ሰበብ ህይወቱን እንዲከፍል ካደረገው ፓርቲ የበለጠ ገንዘብ የፈሰሰበት ትልቅ ፓርቲ አዘጋጀ፡፡
ታሪኩ እንደሚያስረዳን ልክ እንደ ሉዊስ ሁሉም ሰው ኃያልነት እነጠቃለሁ የሚለው ስጋት ያስጨንቀዋል፡፡ እርስዎም ራስዎ በጥበበኛ ሆልሆኑ ችሎታዎና ሰብራዎ እውቅናን ቢያገኙ እውቅና ማግኘቶን ተከትሎ መከፋት፣ መጨነቅ፣ ጥላቻ እና ደህንነት የማጣት ስሜት ይፈጠርቦታል፡፡
ስለዚህ እንዲህ አይነት ባህሪ እውቅና እና ዝና ባላቸው ሰዎች ላይ በጠቅላላ እንደሚኖር መጠበቅ አለቦት፡፡ በእርግጥ ከእርሶ በላይ የሆኑ ሰዎችን ላለማስከፋት ከመጠን በላይ መጨነቅና መጠበብ አይገባዎትም፡፡ ነገር ግን ከበላዮት ካሉ ሰዎች ጋር በሚፈጥሩት ግንኙነት የተለየ አቀራረብ መከታተል አለቦት፡፡ ብቃትዎንና ችሎታዎን ለፈለጉት ሰው ማሳወቅ ይችላሉ፡፡
ከበላይዎት ባለስልጣን ለሆነ ሰው ወይም ለአለቃዎት ችሎታዎን ለማሳየት መሞከር ግን በጣም ትልቅ ስህተት ነው፡፡
ምናልባት ዘመን ተሻሽሏል፡፡ በአሁኑ ጊዜ እንደ ሉዊስ አይነት አመለካከት ያለው ሰው የለም ብለው ያስቡ ይሆናል፡፡ ሆኖም ግን በአሁኑ ዘመን የስልጣን እርከን የጨበጡና ዝነኛ የሆኑ ሰዎች አስተሳሰባቸው ልክ እንደ ጥንት ንጉስ እና ንግስቶች ነው፡፡ እነኚህ ሰዎች የያዙትን ስልጣንና ዝና እንዳይነጠቁ ዋስትና ይፈልጋሉ፡፡ በዙሪያቸው ካሉ ይበልጥ አትኩሮትን የሚስቡ፣ የሚሞከሹ እና የሚወደሱ መሆን እንዳለባቸው ያምናሉ፡፡
ብዙ ሰዎች ለአለቆቻቸው ወይም ከበላያቸው ላሉ ባለስልጣናት የስራ ብቃታቸውን፣ ተሰጥኦዋቸውን እና ተወዳጅነታቸውን በማሳየት ከበላያቸው ባሉ ሰዎች አድናቆትንና ተወዳጅነትን ለማትረፍ እንደሚችሉ ያምናሉ፡፡ ብቃትዎንና ችሎታዎን ለአለቃዎት ሲያሳዩት ያደነቆት መስሎ ሊቀርብ ይችላል፡፡ የመጀመሪያ እርምጃው የሚሆነው ግን ልክ እንደ ሉዊስ እርስዎን ከእሱ ያነሰ እውቀት፣ ተሰጥኦና ችሎታ ባለው ሰው መተካት ነው፡፡ ልክ እንደ ሉዊስም እውነታውን ደብቆ እርሶን ያስወገደበትን ሰበብ ይፈጥራል፡፡
‹‹ብቃትዎንና ችሎታዎን ከበላይዎት ላሉ ሰዎች አያሳዩ›› የሚለው መርህ ሁለት ነገሮችን ያስገነዝቦታል፡፡ አንደኛ ራስዎን ሆነው በመቅረብ ብቻ በተዘዋዋሪ ለአለቃዎም ሆነ ከበላይዎት ላሉ ባለስልጣን ችሎታዎን ማሳየት እንደሚችሉ ነው፡፡ ሁለተኛ ከበላይዎት ያለው ባለስልጣን ወይም አለቃዎት ቢወዶት እንኳ የፈለጉትን ነገር መስራት እንደማይችሉ እንዲገነዘቡ ነው፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው በአስራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን ሂዲዮሽ ለተባለው የጃፓን ንጉስ አማካሪ የነበረውና ሊኪ የተባለ ሰው ላይ የደረሰ አደጋ ነው፡፡
ሊኪ በቤተመንግስት ውስጥ የግሉ መኖሪያ ህንፃ የነበረው፣ በንጉሱ እና በህዝቡ ዘንድ የሚወደድ ሰው ነበር፡፡ በ1591 ባልታወቀ ምክንያት ንጉሱ እስር ቤት እንዲገባና ወዲያውኑ በሞት እንዲቀጣ ወሰነበት፡፡ ኋላ ላይ ምክንያቱ ሲጣራ በቀድሞ ጊዜ የተራ ገበሬ ልጅ የነበረው ሊኪ ቤተመንግስት ከገባ በኋላ በገዛ ፈቃዱ ሳንዳልስ የተባለውን የንጉሳዊ ቤተሰብ መለያ አጠለቀ፡፡ ይህ በንጉሱ ሊኪ ወሰን የሌለው መሆኑን አሳየው፡፡
ሊኪ ያን ያደረገው ተወዳጅነትና ስልጣኑን ሊያገኝ የቻለው በራሱ ጥረትና ልፋት ስለመሰለውና ያለበት ደረጃ በንጉሱ እንደሚወሰን ስለሚዘነጋ ነው፡፡
ራሱን በጣም ከፍ ከፍ አድርጎ በመመልከቱ ላጠፋው ጥፋት ህይወቱን እንዲከፍል ተደረገ፡፡
እንግዲህ እርስዎም ከበላይዎት ላሉ ባለስልጣናት ችሎታዎን ማንፀባረቅ የሚያስከትልቦትን ጉዳት በመረዳትና በተቃራኒው መንገድ በመጓዝ ተጠቃሚ ይሁኑ፡፡ ለምሳሌ ከአለቃዎት የበለጠ አዋቂ እና አስተዋይ ከሆኑ ተቃራኒውን ሆነው ይቅረቡ፡፡ አለቃዎት ከእርስዎ የሚበልጥ እንዲመስለው ያድርጉ፡፡
– ለወደፊትም ሆነ በአሁኑ ወቅት ብዙም የማይጎዳዎትን ስህተት ሰርተው አለቃዎት እንዲተባበሮት ይጠይቁት፡፡ ብዙዎቹ ራሳቸውን አግዝፈው የሚመለከቱ ሰዎች እንዲህ ያለውን ትብብር ማድረግ የበላይነታቸውን ስለሚያረጋግጥላቸው ያስደስታቸዋል፡፡
– ከአለቃዎ የተሻለ ጥሩ ሀሳብ ካሎት ለአለቃዎ ነግረው እንዲጠቀምበት ያድርጉ፡፡ የእርሶ ምክር ምንጩና ስር መሰረቱ የእርስዎ ምክር እንደሆነ ያሳውቁት፡፡
– በተፈጥሮዎት ከሰው ጋር ተግባቢና ተጫዋች ከሆኑ አለቃዎትን ወይም ከእርሶ የበላይ የሆነውን ባለስልጣን ከጨዋታ ውጭ እንዳያደርጉት ይጠንቀቁ፡፡ አለቃዎት ልክ እንደ ንጉስ ሉዊስ የሁሉንም አትኩሮት በእሱ ላይ እንዲሆን እንደሚፈልግ አይዘንጉ፡፡ ከሰዎች ዘንድ ያሎትን ተወዳጅነት ወይም የመግባባት ችሎታዎን ለአለቃዎ ለማሳየት መጣር እንደ ፎኩዌት ችግር እንደሚያስከትልቦት ይገንዘቡ፡፡
– ችሎታዎንና ብቃትዎን መደበቅ ደካማ መሆን ሊመስልዎ ይችላል፡፡ ነገር ግን ደካማ መስሎ መታየት ለፈለጉት ስልጣን የሚያበቃዎ ከሆነ ድክመት ሳይሆን ጥንካሬ ነው፡፡
ከበላይዎት ያሉ ሰዎች ኃያልነታቸውን እንዲያንፀባርቁ በመፍቀድ የደህንነት ስሜት በማጣት እርስዎ ሊቃጡቦት ከነበረው አደጋ ይጠበቃሉ፡፡ አለቃዎን ሊገለብጡት የሚችሉት አይነት ከሆነ ግን ችሎታዎን በማሳየት እንደሚበልጡት ያሳውቁት፡፡ ያገኙበትን ችግር በማስፋትም ውድቀቱን ያፋጥኑ፡፡ አለቃዎ በጣም ደካማና ሊወድቅ የደረሰ ከሆነ ግን በራሱ ጊዜ እስኪወድቅ ይታገሱ፡፡
ከበላይዎ ያለውን ሰው ስልጣኑን ሊነቀንቁት የማይችሉት አይነት ከሆነ ግን ከእርሱ እንደሚበልጡ ልቦናዎት ቢያውቅም ማንፀባረቁ አደጋ ስለሚያስከትልቦት ባይበልጦትም የሚበልጦት እንዲመስለው ይፍቀዱለት፡፡S
ይህ ጽሁፍ በዘ-ሐበሻ ጋዜጣ ላይ ታትሞ የወጣ ነው