ኢትዮጵያዊያን አባይን አባታችን ፤ አባ፤ አባዬ ፤ አባይ ፤ በማለት በእውነተኛ ሥሙ ዛሬ እየጠሩት ነው ። አባትነቱን በተግባር በማሥመሰከሩ ።
” አባት ” በኢትዮጵያዊያን ባህል ውሥጥ ታላቅ ክብር አለው ። “አባት ሣለህ አጊጥ ፤ ጀንበር ሳለች ሩጥ ።” ይላል ሥነ _ቃላችንም ። የአባት ክብር የመነጨው ከተሸከመው ኃላፊነት አንፃር ነው ። የመሰረተውን ቤተሰብ መሰረታዊ ፍላጎት ለማሞላት ጠንክሮ የመስራት ግዴታ አለበት ። የተሻለ ኑሮ ቤተሰቡ እንዲኖር ቁር ና ሀሩሩ ሳይበግረው ፣ ሌት ተቀን መልፋት ይጠበቅበታል ። ይህንን ኃላፊነቱን የማይወጣ ከሆነ ግን ቤተሰቡ ሊፈርስ ፣ ልጆቹ ጎዳና ሊወጡ ይችላሉ። እናም አባይ ብለህ የምታቆላምጠው እንዲህ አይነቱን ለቤተሰቡ ሟች የሆነውን አባት ነው ፡፡
” አባይ ፤ አባዬ ” ለኢትዮጵያዊያን ዛሬ የቁልምጫ ሥም ነው ። ጠበቅ አድርገው ፣ በፍቅር የሚጠሩት ሥም ። “አባይ! አባይ ‘__አባዬ ! _ የእኔ ውድ አባት ። ” እንደማለት ። እናም አባይ ዛሬ እና አሁን ፣ የኢትዮጵያውያን አባት መሆኑን በተግባር እያስመሰከረ ነው ። በተባረኩ ልጆቹ እየታገዘ።
ዛሬ ኢትዮጵያ አገሬ በውስጥና በውጪ እጅግ የተባረኩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የአባይ ልጆች እንዳሏት ፣ ለወዳጆቿ ና ለጠላቶቿ በተግባር እያሳየች ነው ። እፍኝ የማይሞሉትን የነጭ ቱጃሮችና የእኛዎቹን ቅጥረኛ በንዳዎች ፣ የሐሰት ፕሮፖጋንዳ አክሽፈው ፤ በአደባባይ እውነታችንን በማሳወቅ ፤ የጠላቶቻችንን ሴራ በማጋለጥ የእውነትን ብርሃን ለዓለም ህዝቦች በማሳየት ከኢትዮጵያዊያን ጋር የሚያሰልፉ ፡፡
” ናይል የግብፅ ሥጦታ ሊሆን ይችላል ። አባይ ግን የኢትዮጵያዊያን አባት ነው ። አባይ እያልን የምናቆላምጠው ፡፡ ” በማለት ፣ ዓለምን ሥለ አባይ እውነተኛ ማንነት የሚሳውቁ ። …
እውነት ነው ።አባይ የኢትዮጵያውያን አባት ነው ። አባይ ከፈጣሪ የተሰጠን መጋቢያችን ፤ አባታችን ነው ። ትላንት ግብፆች ከእኛ ሄዶ ሰው ላረጋቸው ለመጋቢያቸው ለእኛ አባት ፣ በጎ አድራጎት በቢሊዮን በዶላር የሚቆጠር ብር ሊከፍሉን ይገባ ነበር ። እነሱ ግን ያጎረሳቸውን ጣት ደግመው ደጋግመው ከመንከስ ውጪ አንድም ቀን አመሥግነው እንኳን አያውቁም ። የኢትዮጵያን አፈር እየጠራረገ በመውሰድ ያጎረሳቸውን አባታችንን ሲያመሰግኑና ልጆቹን ለመካስ አንዳችም በጎ ጥረትም በታሪክ አጋጣሚ እንኳን አላደረጉም ። ደጋግመው በሱዳን በኩል በጦር ሊያስፈራሩን ፤ በኃይማኖት ሽፋንም ሊያቄሉን ግን በተደጋጋሚ መጣራቸውን ታሪክ ዘግቦታል ።
የዛሬውም የግብፅ በአባይ የኤሌትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ሰበብ ፣ የምታሥነሳው አቧራ ደግሞ ፣ አንዳችም ሣይንሣዊ መሠረት የሌለውን የክፋት ና የተንኮል አድራጎቷን የሚያሳብቅ ነው ። ግብፅ ይህንን ተደጋጋሚ የተንኳል መንገድ የምትከተለው ፣ ” ኢትዮጵያ በልፅጋ ከማይ ሞቴን እመርጣለሁ ።” የሚሉ መሪዎች ሥላሏት ነው ።እነዚህ መሪዎቿ ሰማይ ጥግ በደረሰ ምቀኝነት እና በሥግብግብነት ሴራ ላይ ያጠነጠነ ተንኮላቸውን ለሱዳን መንግሥትም አጋብተዋል ። ምንም እንኳን የሱዳን መንግሥት እንደ ግብፅ መንግሥት ባይቀጥፍም ።
የግብፁ የውሃና መስኖ ሚኒሥቴር በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ፊት ቀጥፈዋል ። ይህ ቅጥፈት የሚያመለክተን የግብፅን መንግሥት የተንኳል ና የምቀኝነት አረማመድ ነው ። አባይ ወይም ናይል ውሃው ተርፎ ወደ ሜዲትራኒያን ባህር የሚገባ ሆኖ ሣለ ” አሥዋን ግድባችን ውሃ አጥቶ ሀይቅ ሆነ ። ” ብለው በአደባባይ ሲናገሩ የሰማ ሁሉ ፤ የግብፅ የአባይ ዲፕሎማሲ በቅጠፈት የተሞላ መንገድን የሙጥኝ እንዳለ ይገነዘባል ።
ኢትዮጵያ ዛሬም በትህትና አብረን እንልማ ፤ በትብብር እንደግ ፤ የሁላችንም አገር ዜጎች በእኩልነት ይበልፅጉ ነው ። ይህንን ቅን አመለካከትና በጎ አሥተሳሰብ የግብፅ መንግሥት ለፖለቲካ ግቡ ሲል ፈፅሞ አይቀበለውም ። ለዚህም ነው ሁሌም በሃሰት ፕሮፖጋንዳ የግብፅን ህዝብ የሚያደናግረው ።
ግብፅ ቀና መንግሥት ቢኖራት በፈጣሪ ውሃ እንዲህ አትሥገበገብም ነበር ።ስግብግብ እና ብልፅግና ጠል መሪዎች ባይኖሯት ኖሮ ፤ የአባይ ተፈጥሯዊ ፍሰት ሳይቀየር እና ዛሬም አሥዋን የተሰኘ ግድቧ ፣ ጢም ብሎ ሞልቶ ፣ ” ሐይቅ ሆነብኝ ፡፡ ” በማለት በሐሰት አታወራም ነበር ።የእግዘብሔርን ውሃ ያለሥግብግብነት ከተጠቀምን እኮ አባይ ለሁላችንም በቂ ነው ። እንኳን ለግብፅ ለሜዲትራኒያን ባህርም ይተርፋል ።
የግብፅ መንግሥት ይህንን አሳምሮ ያውቃል ። ይሁን እንጂ የኢትዮጵያን ብልፅግና ፈፅሞ የማይሹ ለብዝበዛቸው ብቻ የሚያሥቡ የምእራቡ ና የአሜሪካ ቱጃሮች ድብቅ አጀንዳን ለማራመድ ሲል በውሸት ፕሮፓጋንዳው ዘልቆበታል ። አሳሪ ሥምምነት እያለም የቅኝ ገዢዎች ሃሳብ ተግባራዊ እንዲሆን ይጮሃል ። አሳሪ ሥምምነት ሳይፈረም የኃይል ማመንጫው ውሃ ሁለተኛው ዙር ውሃ ሙሌት መሞላት የለበትም ። ” እያለ ያሻጥራል ።
ይህ አሳሪ የሆነ በሻጥር ና በተንኮል የተቀነባበረ የሥምምነት ሃሳብ ፣ ለኢትዮጵያዊያን ብልጽግና የማይመች ልማታችንን የሚያደናቅፍ የሴራ እቅዶች በአያሌው የተጎነጎኑበት ነው ። ኢትዮጵያ ይህንን አሳሪ የሚለውን ቃል በራሱ አትቀበለውም ።እንኳን ለትፈርም ይቅርና ! ታሥራ የማታቅን አገር በሉአላዊነቷ ጣልቃ ገብቶ ፤ በራሷ ወንዝ “ ካላሰርኩሽ ?! ፈላጭ ቆራጭ ካልሆንኩብሽ ?! “ ማለት ትልቅ ድፍረት እንደሆንም በዲፕሎማሲ ቋንቋ ደጋግማ ገልጻለች ። በራሷ ልጆች የሰራችውን የኃይል ማመንጫ ግድብ ግብጽ ፤ ” እንደፈለኩ ልክፈትና ልዝጋ ! ” ማለት በራሱ ግብዝነት ነው ። ይህንን የግብዞች መንገድ ለመከተል የሚፈልግ ልብ ግን ኢትዮጵያዊያን አልፈጠረባቸውም ና የግብጽ ሃሰብ ከንቱ ነው ። አንቀበለውም ፡፡
አባይ ፤ አባት ፤ አጉራሽና አልባሻቸን ለመሆን መቃረቡን በግልጽ እያዩ ፣ ህሊና ቢስ በመሆን ፣አንድ አንድ የኃያላን መንግስታት መሪዎች ፣ ከብዝበዛ አንፃር ብቻ ፣ የአፍሪካን ህዝቦች በመመልከት ፤ በየጊዜው የማስፈራርያ ቃላትና ያልተገባ ማዕቀብ ማድረጋቸውን ኢትዮጵያውያን አምርረን እንቃወማለን ፡፡ የሱዳን እና የግብፅን ህዝቦች ከቶም የማይጎዳ በሆነው የኃይል ማመንጫ ግድባቸን ፣ ከቶም አንደራደርም ። ሆኖም ለጋራ ብልፅግና በትብብር ከሁሉም የተፋሰሱ አገራት ጋር ለመሥራት ዝግጁ መሆናችንን ደጋግመን መግለጻችንን ግን ልብ ሊሉት ይገባል ።