ህዳር 25 ቀን 2013ዓም (04-12-2020)
የብረትም ሆነ የድንጋይ አሎሎ በክብደት ሊለያይ ቢችልም በቅርጽና በጠባዩ እንዲሁም በተግባሩ አንድ ነው።እየተንከባለለ መደፍጠጥ።አሎሎ ሲንከባለል ቢውል ቅርጹን ለውጦ ዲስኬት ወይም ዝርግና ጠፍጣፋ አይሆንም፤ያው ክብና ሙልሙል አሎሎ ነው።ቢወረውሩት የሚያርፍበት መሬት ከመቦደስና ሳሩም ከመደፍጠጥ ያለፈ ለውጥ በአሎሎው ላይ አይታይም። ስለ አሎሎ ይህንን ካልኩኝ እንደ አሎሎ ቅርጽና ይዞታቸውን ሳይለውጡ ግን እዬተንከባለሉ፣የስልጣን ጉልበትን ተጠቅመው በዋሉበት ቦታ ላይ ፍትህን ደፍጥጠው በሕዝብ ላይ እንደ ሣሩ ጉዳት የሚያደርሱትን ለማነጻጸሪያነት ልጠቀምበት ተገድጃለሁ።
ቀደም ሲል “መልከጥፉ በስም ይደግፉ” በሚል ዕርእስ ባቀረብኩት ጽሁፍ እንዲሁ የስም ለውጥ ውስጣዊና ውጫዊ ይዘቱንም ሆነ ቅርጹን እንደማይለውጠው ለማመልከት ሞክሬ ነበር።አሁንም በዚህ ጽሁፌ ለማሳዬት የምሞክረው ያንኑ ነው። ከአንድ ወር ወዲህ በአገራችን የተካሄደው የእርስ በርስ ውጊያ ለምንና በማን መካከል የተደረገ መሆኑንና የሚያመጣውንም ውጤትና ለውጥ “ጦርነቱና ከጦርነቱ ማግስት” በሚለው ጽሁፌ በጥቂቱም ያህል የበኩሌን ሃሳብ ሰንዝሬ ነበር ።አሁንም ያንን ሃሳቤን የሚያጠናክርና አሳሳች ሁኔታ በመከሰቱ ይህንን ጽሁፍ ለማዘጋጀት ተገድጃለሁ።በፍርሃት፣በጥቅም ወይም በምን አገባኝነት ዝም ብዬ መቀመጥ እችል ነበር፤ ግን ህሊና የሚባለው ውስጣዊ አካሌ ብሎም ኢትዮጵያዊነቴ ከዚያም በላይ ሰውነቴ ስለማይፈቅድልኝ ዝምታን ሰብሬ ድምጼን እንዳሰማ ያስገድደኛል። ላለፉት ሃምሳ ዓመታትም አብሮኝ የኖረው የለውጥ ፍላጎቴ ልተውህ ብለው አይለቀኝም።ለአንድ ዓላማ ተሰልፈን በትግሉ ሜዳ ያጣዃቸውም ጓዶች ቃል ኪዳን እንዳልዘናጋ ያሳስበኛል።አድርባይነትና ፍርሃት የሚሉት ደካማ ጎንም ስለሌለብኝ የሚሰማኝንና የማምንበትን ከመግለጽ ወደዃላ አልልም።አካፋውን አካፋ፣ሌባውን ሌባ ማለት፣ለማንም ስል የማልለውጠው የምኮራበት መታወቂያዬ ነው።
ባሳለፍናቸው ሳምንቶች የተካሄደውን የእርስ በርስ ግጭት፣የእርስ በርስ ግጭት ስል ሕዝብ ለሕዝብ አለማለቴ እንደሆነ ይሰመርበት!በአገርና በሕዝብ ስም የሚነግዱ የሁለት ጎሰኛ ሃይሎች የሥልጣንና የጥቅም ግብግብ ማለቴ ነው።ይህንን የሁለት ተቀናቃኞች ግብ ግብ የአገርን ህልውና ለማስከበር የተደረገ ዘመቻ አድርገው በመቁጠር አንዱን አገር ወዳድ ሌላውን አገር ከሃዲ አድርጎ የማቅረቡ ጫጫታ ትክክለኛ ገጹን ሸፍኖታል።አሁን ላይ በአንዱ በኩል ማለትም ባሸነፈው በኩል የተሰማው የእምነት ቃል ጥቂት ሌቦችን ለማሶገድና ለፍርድ ለማቅረብ የተደረገ ተጋድሎ ነው በማለት አገር አድን ዘመቻ አለመሆኑን በግልጽ ያረጋግጣል።ችግሩ አንንበረከክም፣በነበርንበት የዘረፋ፣የጭቆና ፣የጭፍጨፋ ወንበር ላይ ለዘለዓለም እንቀመጣለን ያሉ የሰላሳ ሰዎች መኖር እንጂ የስርዓት አለመሆኑን አምኖበታል።የነበረው የስርዓት አወቃቀርም ሳይነካ፣የሕወሃት ዓላማ ሳይለወጥ ፣ቢሮውም ሰራተኛውም እንደነበር ሆኖ በትናንሽ ጥገና ኦህዴድ/ ብልጽግና በሚባለው የህወሃት ውልድ በሆነው የጎሳ ድርጅት ፊትአውራሪነት እንደሚቀጥል ገልጿል።በስርዓቱ ላይ የተመዘዘ ሰይፍ ቢሆንማ ኖሮ ለስርዓት ለውጥ የሚታገሉትን ሁሉ በጠላትነት ፈርጆ ለእስራትና ለግድያ ባላበቁ ነበር።ለዚህ የጎሰኞች መተካካት ነው እንግዲህ አገር የታመሰችው፤ሕዝብም በጭንቅና በስጋት ሲናጥ የከረመው።
በዚህ የመነጣጠቅ ግብግብ የደረሰው የሕይወትና የንብረት ውድመት ዝርዝሩ በይፋ ባይታወቅም ከፍተኛ እንደሚሆን ዝግጅቱንና አሰላለፉን በማዬት ለመገመት ይቻላል።አገራችን ለአያሌ ጊዜ ያመረተችው ሃብት በሦስት ሳምንት ባልበለጠ ጊዜ ጦርነት መውደሙ ሊሸፍኑትና ሊክዱት የማይቻል ጉዳት ነው።አያድርስ እንጂ አገራችን በውጭ ሃይል ብትወረር ለመመከት የምትችልበት አቅሟን ያሳነሰ ጦረነት ነው።አሁንስ ላለመወረሯ ማረጋገጫው ምንድን ነው? አፍራሾችና ጸረ ኢትዮጵያና ጸረ ኢትዮጵያዊነት ሃይሎች በውስጣችን እስካሉ ድረስ የውጭ ጠላት ሰርጎ አይገባም ብለን መዘናጋት አይኖርብንም።በጉጉት የሚጠብቁትም እነዚህኑ ጸረ ኢትዮጵያ የሆኑትን አገር በቀል ጠላቶች ተስፋ በማድረግ ነው። በዬቦታውም የሚፈጸመው በማንነት ላይ ያነጻጸረ፣በተለይም የኢትዮጵያ ጋሻና መከታ ሆኖ የኖረውን የአማራ ተወላጆችና የኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኞች በሆኑት ኢትዮጵያውያን ላይ የሚፈጸመው ወንጀል፣የሕዝብ ማፈናቀል፣ጭፍጨፋ ለዚያ መንደርደሪያ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም።ይህንኑ ግፍና በደል፣ጀኖሳይድ ግን መንግሥት ተብዬው ሲያቃልለውና ሲሸፋፍነው ይታያል።ምክንያቱ ግልጽ ነው።የአጋርነትና እራስንም የሚመለከትና የሚያስጠይቅ ወንጀል ስለሆነ ነው።
በሁለቱ ውጊያ የአንዱ መሸነፍ በአንድ በኩል ለአገራችን የጠላቷ ጎራ መዳከሙና መቀነሱ መልካም ቢሆንም ችግሯ ግን እስከነአካቴው ተወገደላት ማለት አይደለም።ይልቁንም አንደኛው ጎሰኛ እንደልቡ ተንፈራጦ ለመቀመጥና ያሻውን እንዲያደርግ ዕድል ሊፈጥርለት መቻሉን ከአሁኑ አመላካቾች ብቅ ብቅ እያሉ ነው።ያሻውን ይሾማል ፤ያሻውን ይነቅላል።ግጭቱ ከላይ እንደተገለጸው የሥልጣን መሆኑን የሹም ሽሩ ሂደትም ያረጋግጣል።ከዚያም በላይ የስርዓት ለውጥ አለመሆኑ የነበረው ፖለቲካዊ ቅላጼ መልክና ጣእሙን ሳይቀይር በቦታው ላይ ቀርቷል።ብሔርና ብሔረሰቦች፣ሕዝቦችና ክልሎች የሚሉት ጸረ አገርና ጸረ አንድነት ቅራቅንቦ አባባሎች በነበረው የተገንጣይ አስገንጣይ ፈቃድ ሰጭ ሰነድ ታጅቦ ስርዓቱ በቀጣይነት እንደሚኖር በጠቅላይ ሚንስትሩና በተከታዮቹ አንደበት በይፋ ተደጋግሞ ሲገለጽ ተሰምቷል።አገራችንንና ሕዝባችንን በጎሰኝነት እርኩስ አስተሳሰብ የበከለ ስርዓት የ30 ሰዎች በስልጣን ላይ መኖር ብቻ አድርጎ መቁጠርና በነሱ መወገድ የተሻለ ሁኔታና ለውጥ ይፈጠራል የሚል የተሳሳተ አመለካከት ማናፈሱ ሌላ ባለተረኛ በግፍ ዙፋኑ ላይ እንዲቀመጥ የማመቻቸት ዘመቻ ነው።
ሕዝብ ይገባኛል ብሎ የታገለለትና መስዋእት የከፈለለት ጥያቄ ተጨፍልቆ ነገም እንደትናንቱ በነበረው የጭቆና በረት ውስጥ የመማቀቁ ዕድል በይፋ ተደንግጓል።ከአርባ ዓመት በላይ በጉልበት የተነጠቁት የወልቃይትና ራያ መሬቶች እንዲመለሱለት ለሚጠይቀው ሕዝብ የተሰጠው መልስ ቢኖር እንደ ህወሃቶች በሕገመንግሥቱ መሰረት የሰፈረው ሕዝብ ድምጽ ይስጥበት ወደሚለው ጨዋታ ያዘነበለ ይመስላል።ይህንን ሁሉም የትግራይ ተቃዋሚ ነን የሚሉ ፓርቲዎች ጭምር የሚያስተጋቡት የጋራ አቋም ነው።በድንበር ኮሚሽን ይወሰን የሚለውም የጠ/ሚኒስትሩ አባባል ወልቃይትንና ራያን በጉልበት የያዘው የህወሃት ማኒፌስቶ አዘጋጅና የጦር መሪ የነበረው፣ አሁን በድንበር ኮሚሽን ውስጥ የተመደበው፣የቀጣዩ የትግራይ አስተዳደር እጩ ፣የታላቁ ህዳሴ ግድብ አስተባባሪ ዳሬክተር ሆኖ የተሾመው አረጋዊ በርሄ ካለው አቋም የተለዪ አይሆንም።የሕዝቡን ጥያቄ እሱና መሰሎቹ ይወስኑበት ብሎ አሳልፎ መስጠት ነው። ውጤቱም ምን ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ መገመት አያቅትም። ይህ በአማራው ማህበረሰብ በኩል ተቃውሞ ብቻ ሳይሆን ጦር የሚያማዝዝ ጉዳይ ነው።
ይህም ስለሆነ ነው አሎሎ ቢንከባለል ያው አሎሎ የሚጎዳው ግን ሣሩ ለማለት ያበቃኝ።ኢትዮጵያ አገራችንንና ሕዝቧን ለዘለቄታው አንድነት፣ሰላምና እድገት የሚያበቃው ላለፉት ሰላሳ ዓመታት ተንሰራፍቶ የኖረው፣አሁንም ለወደፊት ለመቀጠል የሚያስበው የጎሰኞች ስርዓትና ሕገመንግሥት ተብዬው የጥፋት ሰነድ ሲወገዱና አገር በክልል ሳይሆን ፉጹም ዴሞክራሲያዊ በሆነ ክፍላተሃገራዊ አወቃቀርና በእውቀት ፖለቲካ ስትመራ ብቻ ነው።
ግራ የሚያጋባው ነገር ቢኖር ፕሬዚዳንታዊ አመራር አለ ተብሎ በሚነገርበት አገር የአንዱ ጎሳ ድርጅት የኦህዴድ መሪ ጠ/ሚንስትር ሆኖ የአገሪቱ ጦር ሃይሎች ዋና አዛዥ ሆኖ ያለአግባብ ያሻውን ሲያደርግ መታዬቱ ነው።የፕሬዚዳንቷ/ቱ ሚና ምኑ ላይ ነው?በሌላ አነጋገር ያገሪቱን ጦር ሃይል የሚያዘውና የሚያንቀሳቅሰው ኦህዴድ የተባለው የጎሳ ድርጅት ነው ማለት ነው።ያም ከነበረው የህወሃት ቦታና ስልጣን የተለዬ አይደለም ማለት ነው።ለዚያም ነው አሎሎ ቢንከባለል ያው አሎሎ ፣የሚጎዳው ግን ሣሩ ያልኩት።ወይም በቀድሞው አባባል ጉልቻ ቢለወጥ ወጥ አያጣፍጥም ወይም መልከ ጥፉ በስም ይደግፉ የምለው።
ወንጀለኞችንና ሌቦችን ሊይዝና ቅጣታቸውን እንዲያገኙ ሊያደርግ የሚችለው አካል ከወንጀል የጸዳና የሚታመን ተቋም እንዲሁም መንግሥት ሲኖር ነው።የዚያ ተቋም ደግሞ በአድልኦና በወገንተኝነት ሳይሆን ለሙያው ያደረና ቃል ኪዳን የገባ ዜጋ ሲመራው ነው።አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ እንደሚባለው ኦህዴድ/ብልጽግና በህወሃት ኢህአዴግ ላይ ክንዱን ያሳርፋል ብሎ መጠበቅ ጅልነት ይሆናል።ወንጀለኞቹንም ማንቆለባበስ መጀመሩ የዚያ ምልክት ነው። ከሁለቱም ነጻ የሆነ አጣሪ አካል ቢመሰረት የሁሉም ጉድ በአደባባይ በተዝረከረከና ተያይዘው ቂሊንጦ በገቡ ነበር።ለዚያ ግን ሕዝባችንም አገራችንም አሁን ለጊዜው አልታደሉም።ያ ቀን እስኪመጣ ድረስ ግን ቀበቶን ጠበቅ አድርጎ፣ካለፉት ስህተቶች ተምሮ፣በውሸት ፕሮፓጋንዳ ሳይወናበዱ ለዘላቂው ድልና ስር ነቀል የስርዓት ለውጥ መታገል ነው።
የፍትሕ መደፍጠጥ ሌላው ትልቁ ማሳያ በተለያዩ ቦታዎች በቄሮ/ኦነግ አሸባሪ ቡድኖች በገጀራና በድንጋይ ተጨፍጭፈው የተገደሉት ዜጎች ደም በከንቱ ፈሶ እንዲቀር የማድረጉ የመሸፋፈንና ትኩረት እንዳያገኝ ወንጀለኞቹም ለፍርድ እንዳይቀርቡ በማከላከል፣ለይምሰል ብቻ ጥቂቶችን በማገት የሚደረገው ማጭበርበር፣ከዚያም አልፎ ተርፎ በቄሮ/ኦነግ አሸባሪ ቡድኖች ታፍነው ከዓመት በላይ ድካቸው የጠፋው ወጣት የአማራ ልጆች እጣ ፈንታ ምን እንደሆነ አለማሳወቅ ብቻ ሳይሆን አድበስብሶ ማለፉ ነው፤ጥያቄ ያቀረቡትንም ማሳድድና ማስፈራራቱ የስርዓቱን ፍትሕ አልባነትን ያሳያል። ሌሎችም ብዙ ማሳያዎች መጥቀስ ይቻላል።ከነዚህ ውስጥም በባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ አመራሮችና ደጋፊዎች፣በአቶ ልደቱ አያሌው፣በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝና በሌሎቹ፣ በሃሳብ ልዩነትና የመንግሥትን አካሄድ በመቃወማቸውና በማጋለጣቸው ብቻ አገር ለማፈራረስ የተነሱ አድርጎ መፈረጁ፣በእስር ማሰቃዬቱና ማሳደዱ የዚያ የፍትህ አልባነት ማሳያ ነው።
አገራችን በውዝግብና በነውጥ እዬታመሰች ነው ሲባል ውዝግቡ በህወሃትና በኦህዴድ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን በተለያዩ የጋላ ድርጅቶችም መካከል የሚነሳ የስልጣን ሽኩቻ በመካሄድ ላይ መሆኑን በማመን ነው።ከወዲሁ ካልተቀጨ ሲውል ሲያድር ለአገር አንድነት አደጋ ይሆናል፤ነውም።፣ በሁሉም ክልል በተባለው ዙሪያ የሚታዬውም የመሬትና የድንበር መገፋፋትም የዚያው አካል ነው።
ሌላው ስጋት በጎሰኞች መካከል በሚፈጠረው ሽኩቻና ውዝግብ አገር ከታመሰች ፣የአገርን ሰላምና አንድነት ለማረጋገጥ በሚል ሽፋን አሁን ስማቸው እዬገነነ በመጣው ወታደራዊ መኮንኖች ግልበጣ ተካሂዶ የወታደራዊ ጁንታ መንግሥት እንዳይቋቋም ነው።ያልተደራጀና መሪ አልባ የሆነ ሕዝብ እጣ ፈንታው ከዚያ አያልፍም።ሱዳን ለዚህ ምሳሌ ትሆናለች።
ከዚህ አይነቱ አደጋ ለመውጣትም ሆነ ለዘላቂ ድልና አገራዊ አንድነትና ሰላም የጎሳ ፖለቲካ በእውነተኛ አገር ወዳድና በእውቀት ላይ ያረፈ የፖለቲካ ራዕይ ባለው ስርዓት ሲተካ ብቻ ነው።ለዚያም መዳረሻ
1 በተገንጣይና አስገንጣይ ጎሰኞች የረቀቀው ሰነድ በእውነተኛ ሕገመንግሥት መቀዬር
2 በጎሳና በእምነት የተደራጁ የፖለቲካ ድርጅቶችን ማገድ
3 በቋንቋና በጎሳ ተዋረድ የተዘረጋው የክልል አወቃቀር ፈርሶ አገራዊ መልክ ባለው ክፍላተሃገራዊ አስተዳደራዊ አወቃቀር መተካት
4 በኢትዮጵያዊነታቸው የሚያምኑ፣ከሲቪክና ከፖለቲካ ድርጅቶች የተውጣጣ ጊዜያዊ ወይም የሽግግር ካውንስል መቋቋም
የካውንስሉ ተግባርና የዕድሜ ዘመን
የዚህ ካውንስል የስልጣን ዕድሜ ከሁለት ዓመት ባይበልጥ ይመረጣል።
የሚመራበት ጊዜያዊ ህግ ወይም ቻርተር በሕግ ባለሙያዎችና በምሁራን በቅድሚያ ቢዘጋጅ የተሻለ ነው። የተዘጋጀም ካለ አሁን ይፋ ቢሆንና ሕዝቡ ሃሳብ ቢሰጥበት ጥራትና አቅም ይኖረዋል።ሰርገኛ መጣ የሚሉት አይከሰትም።
የሽግግር ካውንስሉ ተግባራት
1 ለሁለት ዓመታት ወይም ለተሰዬመበት የጊዜ መጠን አገሪቱን ይመራል።ተቋማት ሥራቸውን በሚገባ እንዲሠሩ ይከታተላል፤የተዳከሙትን ያጠናክራል።
2 ከውጭ አገራት ጋር ግንኙነት ቢኖረውም አዲስ ውሎችና ስምምነቶች አይፈርምም።
3 በአገርና በሕዝብ ላይ በደል የፈጸሙት ለፍርድ እንዲቀርቡ አጣሪ ኮሚሽን ይሰይማል።አጣሪ ኮሚሽኑም አጣርቶ ለፍርድ የሚቀርቡትን ለይቶ ለፍርድ ያቀርባል።
3 ቋሚ ሕገመንግሥት በሕዝብ ተሳትፎ እንዲረቅ ያደርጋል፤ይህ የሕግ እረቂቅ ምርጫ ከተደረገ በዃላ በፓርላማ አባላት እንዲጸድቅ ይሆናል።
4 ሰላምና መረጋጋት ያረጋግጣል፤ምርጫ እንዲካሄድ ያደርጋል
5 ከተወሰነለት ጊዜ በዃላ ለተመረጠው አካል ሥልጣኑን ያስረክባል።
አሁን ያለው ስርዓት ይቀጥል ከተባለ አገራችን ይበልጥ ወደ ከፋ አዘቅት ትገባለች የሚለው ስጋት ብቻ ሳይሆን ሊሆንም የሚችል ቁልጭ ብሎ የሚታይ አደጋ ነው። ያለው ስርዓት ይቀጥል ከተባለ ጎሰኝነትና ተረኝነት ለዘለዓለሙ ቀጣይ ባህል ሆኖ እንዲቀር መፍቀድ ማለት ይሆናል። በጫጫታ ሳይወናበድ፣ ለከፋ ውድቀት ተባባሪ ሳይሆን፣ሁሉም ነቅቶ እስከመጨረሻው መታገል ከአገር ወዳዱ ይጠበቅበታል።
የነቃና የተደራጀ ሕዝብ ለአገር አንድነት፣ሰላምና እድገት ዋስትና ነው።
ኢትዮጵያ ከጎሰኞች መዳፍ ተላቃ በአንድነት ለዘለዓለም ትኑር!
አገሬ አዲስ