- የወንድማማቾች ጦርነት ወይስ ሐገር የማፍረስና የማዳን ጦርነት
- የአማራ ሚና
- ኢፍትሐዊና ፍትሐዊ ጦርነት
አንድነት ይበልጣል – ሐዋሳ – ጥቅምት 28 / 2013
ጦርነቱ የሚካሄደው በማንና በማን መካከል ነው?
¨አማራ (ልዩ ኃይል) ትግራይ ውስጥ ምን ይሠራል?¨ ¨ጦርነቱ ፍትሐዊ ይሁን! ወዘተ¨ ለምትሉ ወገኖች፤ ምናልባት ችግራችሁ ሌላ (እንደዲጂታል ወያኔ/ሸኔ) ሣይሆን የትርጉም (የመረዳት) ብቻ ከሆነ ጉዳዩን ገለጥ አድርገን ብናየው አይከፋም፡፡ መወያየት መልካም፡፡ እስኪ ጥያቄአችሁ በሚከተለው ጥያቄ ይወከልና እንየው፡፡
ተማሪ፡ ¨#ጦርነቱ ህወሓት ለማሸነፍ ከሆነ የአማራ ልዩ ሐይል እገዛ ለምን አስፈለገ? መከላከያ የህወሓት ልዩ ሐይል ማሸነፍ አይችልምን? ወይስ አቅም የለውም? በየትኛው ህግ ነውስ አንድ ክልል ወደ ሌላ ክልል በሐይል የሚገባው ከመከላከያ በስተቀር? ውግያው ፍትሓዊ ይሁን።¨ (የማነ ንጉስ፣ Habibul Rahman Hussen Oromo ዲጂታል ወያኔ፣ ኦነግ/ ሸኔ፣ ቅን ዜጎች ወዘተ)፡፡
አስተማሪ፡ ይህ ጦርነት የሚካሄደው በሕወሐትና በብልጽግና (በፌዴራል መንግሥት) መካከል አይደለም! ጦርነቱ የሚካሄደው በትግራይ ሕዝብና በፌዴራል መንግሥት መካከልም አይደለም፡፡ ጦርነቱ የሚካሄደው በጸረ ሰላምና ጸረ አንድነቱ፣ በጨፍጫፊውና በዘራፊው ሕወሐት እና (የትግራይን ሕዝብ ጨምሮ) በመላው ሰላምና አንድነት ወዳድ ኢትዮጵያውያን (ክልሎች/ ¨ ብሔር ብሔረሰቦች¨ …) መካከል ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሕዝብ በኩል ጦርነቱን የሚመራው፣ (ለጊዜው ሕዝቡን ወክሎ) የፌዴራል መንግሥት ነው፡፡ ጦርነቱን የጀመረው ሕወሐት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደጦርነቱ የገባበት ዋናውና ዋናው ምክንያት፣ ሕወሐት ለአሠርታት በተለይም ባለፉት 3 ዓመታት ያደረገው ክፋትና ጥፋት ሁሉ አልበቃ ብሎት፣ አሁን ደግሞ ሐገራችንን ለማፍረስ የመጨረሻ እርምጃ ውስጥ በመግባቱ ነው፡፡
ሉዓላዊነትን የማስከበር ጦርነት፡
ሕወሐት በሰሜን እዝ ጦራችን ላይ ባደረገው ድንገተኛ ጥቃት ምክንያት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በግልጽ ደፍሯል፡፡ ሉዓላዊነት ሲደፈር የሚሰጠውን ሐገራዊ (ብሔረሰባዊ አላልኩም) ምላሽ (ለምሳሌ በአድዋ ጦርነት ላይ የመላ ኢትዮጵያውያንን ተሳትፎ) ሁላችንም እናውቃለን! አሁንም ችግሩ የሉዓላዊነት እንጂ በወንድማማቾች መካከል የተፈጠረ የፖለቲካ ልዩነት ችግር አይደለም፡፡ እንድገመውና ዋናው ችግር ሕወሐት (የነግብጽንም ተልእኮ ይዞ) በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ግልጽ አደጋ መደቀኑ ነው፡፡ ሕወሐት ከጸረ ዴሞክራሲነቱና ከዘራፊነቱም አልፎ፣ ለዘመናት አምቆ የቆየውና አሁንም የደቀነብን ዋናው ፈተና የሉዓላዊነት ፈተና ነው፡፡ የኢትዮጵያ አንድነትና የሉዓላዊነት ፈተና የመላው ሕዝብ ከፈለጋችሁም የሁሉም ¨ብሔር-ብሔረሰቦች¨ ፈተና ነው፡፡ ስለዚህ ሉአላዊነታችንን የማስጠበቅ ጦርነቱ የመከላከያ ሠራዊትና የፌዴራል ፖሊሳችን ብቻ ሣይሆን የሁላችንም ጦርነት ነው! የሁሉንም ክልል ልዩ ኃይልና ሚሊሻውን ሁሉ ያገባዋል!!
ኢፍትሐዊ እና ፍትሐዊ ጦርነት፡
ጦርነት ፍትሐዊ ነው/ አይደለም ተብሎ የሚበየነው ከሚካሄድበት ዓላማ ላይ በመነሳት ነው፡፡ አንድን ሉዓላዊ ሐገር ቅኝ ግዛት ለማድረግ ወይም ለማፍረስና ለመበታተን ተብሎ ከውጭም ሆነ ከውስጥ የሚጀመር ጦርነት ኢፍትሐዊ ይባላል፡፡ ሐገርን ከውጭ ወራሪዎች ለመከላከል እንዲሁም ሐገርን ለማፍረስና ለመበታተን ከውስጥም ቢሆን ከተነሱ ኃይሎች ጋር ተናንቆ አንድነትንና ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ የሚደረግ የመከላከል ጦርነት ደግሞ ፍትሐዊ ጦርነት ይባላል፡፡
የአማራ ሕዝብ (ልዩ ሐይል) ሚና፡
የአማራ ሕዝብማ (ልዩ ሐይሉን፣ ሚሊሻውን፣ ፋኖውን ጨምሮ) በተለይ ከሕወሐት የተቃጣውን ጥቃት በመመከት ረገድ ከሌሎች ክልሎች ልዩ ኃይሎች የበለጠ ኃላፊነት ለራሱ ቢሰጥ አይደንቀኝም፡፡ ዕውነተኛ ሆነንና በመሬት ላይ ከነበረውና ካለው ሐቅ ተነስተን እንነጋገር፤ ሕወሐት የአማራን ሕዝብ ለይቶ ሲያጠቃ የኖረ ድርጅት ነው፡፡ ሕወሐት ባለፉት 45 ዓመታት በአማራ ሕዝብ ላይ ያወረደው እና አሁንም ያስቀጠለው መዓት መርሐግብራዊ፣ ሥርዓታዊ፣ ተቋማዊና መዋቅራዊም ነበር፤ ነውም! ይህን ለማረጋገጥ የሕወሐትን የመጀመሪያ ¨የፖለቲካ¨ ፕሮግራም (ማኒፌስቶ – የካቲት 1968) መመልከት ይበቃል፡፡ በዚህ መርሐ ግብር ውስጥ፣ ሕወሐት ስለአማራ ሕዝብ የነበረውን (ያለውን) አፍራሽ ግንዛቤ፣ ቀዳሚ መሻትና ውጥን፣ ራሱ ፈጥሮ የነዛውን የውሸት ትርክት፣ ክስ፣ ውንጀላና ዛቻዎችን ሁሉ በግልጽ ሠፍረው እናገኛቸዋለን፡፡ በመርሐ ግብሩ ውስጥ፣ እዚህም እዚያም፣ ¨የአማራ ብሐራዊ ጭቆና …¨፣ ¨ጨቋኟ የአማራ ብሔር (ያደረሰችብን) በደል …¨፣ ¨ጨቋኟ የአማራ ብሔር ጭቆናዋ እስካላቆመች ድረስ ሕብረተሰባዊ ዕረፍት አታገኝም¨ ወዘተ የሚሉ ውንጀላና ዛቻዎችን በተደጋጋሚ እናገኛለን፡፡ ዝርዝሩና ትርጓሜው ብዙ ነው፡፡ ይህን ተቋማዊ መሻት፣ ውጥንና ዛቻ ወደ መሬት በማውረድ ደግሞ ሕወሐት በተለይም በአማራ ሕዝብ ላይ በዓይናችን ሥር በተግባር የፈጸመውን ግፍ ጨምረን እንየው፤ ከዚህ አንጻር የአማራ ሕዝብ የሕወሐትን ግፍ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስቆም አሁን እያሳየ ያለውን ቁርጠኝነት ባያሳይ ነው የሚገርመኝ፡፡ እንዲያውም የኔ ሥጋት አንዳንድ የአማራ ጽንፈኞች እንደሚያሳዩትና ሕወሐትም እንደሚመኘው ትግሉን ወደ ሌላ ያልተፈለገ ጠርዝ ላይ እንዳይወስዱት ነው፡፡ ጽንፈኝነትን ሁላችንም ልንታገለው ይገባል፡፡ እዚህ ላይ ሕወሐት በሶማሌ፣ ኦሮሞ ወዘተ ላይ ግፍ አልሠራም እያልኩ አይደለም፡፡ እያልኩ ያለሁት፣ የአማራ ሕዝብ በዋና – ስትራቴጂክ – ተጠቂነቱ፣ በጂኦግራፊ (ቅርበቱ – ተጋላጭነት) እና በብዙ ያልተመለሱ የማንነትና የመሬት ጥያቄዎቹ ምክንያቶች የተነሣ በጸረ ሕወሐቱ ጦርነት ጎልቶ የሚታይ ተሳትፎ ቢኖረው እንደ ነውርና እንደ ልዩ ሤራ መታየት የለበትም ነው፡፡ በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ካሳለፈው አታካች የግፍና የጭቆና ተሞክሮ በመነሳት፣ ተረኛ ገዢነትንም ሆነ በቀለኝነትን ወይም ሌላ ማናቸውም ዓይነት ሤራን የሚቀበል አይሆንም!!
¨በጸረ ሕወሐት ጦርነቱ የሚሳተፈው አማራ ብቻ ነው እንዴ?¨ ለምትሉ ደግሞ፡
እዚህ ላይ ጥሩው ነገር፣ ጸረ ሕወሐት ጦርነቱ የአማራ ብቻ ሣይሆን የሁሉም መሆኑ አንዱ ማሣያ የአፋር ልዩ ኃይልም ቀጥተኛ ተሳትፎ መጀመሩን መመልከታችን ነው፡፡ በሚቀጥሉት ቀናትም በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ በቅርብ ወይም በሩቅ እንደየአመቺነቱና እንደየጠቃሚነቱ (የትግራይ ክልል ልዩ ኃይልን ጨምሮ) የሁሉንም ክልሎች ልዩ ኃይሎች በግንባር ተገኝተው አስተዋጽዖ ሲያደርጉ የምናያቸው ይመስለኛል፡፡ ዛሬ የኦሮሚያ ልዩ ኃይልም ወደዛው መትመሙን ሰማሁ፤ እንዲህ ነው! በሌላ በኩል ሕወሐት ሽብርተኛ ድርጅት ስለሆነና የትኩረት አቅጣጫ ለመቀየርም ሲል በየክልሉ በተመቸው ቦታና ጊዜ አደጋ ሊጥል (ሊያስጥል) ይችላል፤ ምልክቶች መኖራቸውን እየሰማን ነው፡፡ ይህንን ጥቃት የየክልሉ ልዩ ኃይል በየራሱ ቦታ ላይ ሆኖም መከላከል፣ መመከትና ድባቅ መምታት እንዳለበትም አንርሳ! የኦሮሚያ ፖሊስና ልዩ ኃይል ደግሞ ኦነግ/ሸኔ የሚባል የሕወሐት ጭራም አለበት …፡፡
መውጫ፡
በሌላ ጎኑ፣ በዚህ ሉዓላዊነትን የማስከበር ጸረ ሕወሐት ዘመቻ የአማራን ልዩ ኃይል ጨምሮ፣ ሁሉም ልዩ ኃይሎች ዓላማቸው እንደ መከላከያ ኃይላችን ሁሉ፣ ሉዓላዊነታችንን ማስጠበቅና ማስጠበቅ ብቻ ነው መሆን ያለበት፡፡ የማንነትና የመሬት ይገባኛል ጥያቄዎች የሚፈቱት ጊዜአቸውን ጠብቀው በሕግና በሕግ ብቻ መሆን አለበት፡፡ ራሱ የክልል ልዩ ኃይል ሕልውናና አስፈላጊነት፣ እንዲሁም ሌሎች ሕገመንግሥት ነክ ጥያቄዎች ሁሉ በጊዜውና በሕግ አግባብ ብቻ ለመወሰን ብንጠብቅ ይሻለናል!!! በዚህ መጠራጠርና መከፋፈል አይኖርብንም፡፡ እኔ እንደዚህ ነው የሚመስለኝ፡፡ በጎደለው ሙሉበት፡፡
ፈጣሪ ይርዳን!