October 23, 2020
29 mins read

ይድረስ ለደባልቄ ቢተው   ( ዘ-ጌርሣም)

ክፍል ሁለት

ይድረስ ለምንወድህና ለምትናፍቀን ልጃችን ደባልቄ ቢተው

እንዴት ከረምክ ልጀ? እኛማ ባለፈው ስናወጋ እመጣለሁ ባልከን መሠረት መምጣትክን እየተጠባበቅን እንዳለን ለአንተ ምኑን እነግርሃለሁ በአሁኑ ወቅት ወሬውን ከእኛ ቀድማችሁ ስለምትሰሙት አገሩ ሁሉ ታምሶ የመንግሥት አልጋም ተናውጦ በመክረሙ ያገርህ ገበሬ በነቂስ ሞፈርና ቀንበሩን ሰቅሎ ቤት ያፈራውን መሣሪያ እየወለወለ ዱር ገብቷል።እኛ ግን አቅምና ጉልበታችን ቤት ስለዋለ ትመጣ ይሆናል በማለት በር በሩን እያየን በናፍቆትህ እንደተሰየን አለን፤የሊቦው ጌወርጊስ የተመሰገነ ይሁንና እስካሁን የደረሰብን አንዳችም ክፉ ነገር የለም።እናትህ ግን ክስት ጥቁር እንዳለች በየደብሩ እየዞረች ያልተሳለችበት ታቦትና ያልቋጠረችለት የስለት ገንዘብ አይገኝም።ሌትና ቀን ዓይንህን እንዲያሳያት ያን የምታውቀውን የሊቦ ጌወርጊስን አቀበትና ቁልቁለት ደከመኝ ሳትል ስትወጣ ስትወርድ ከረመች፤ምን እሱ በቅቷት ጣራ ገዳምና ዘንግ ሚካኤል ድረስ ሳይቀር ትመላለሳለች።

አንድዬ እሱ ያለው አይቀርምና ከጧት ማታ ሳይታሰብ ነገሩ ሁሉ እንደ ክረምቱ ጊዜ የእርብ ውሃ ድፍርስርስ አለብን፤ህዝቡም ከሽማግሌ እስከ ኮበሌ በነቂስ በመንግሥት ላይ አምጦ ተነሳ።መንግሥት ተብየውም ለነገሩ ሲገባም አላማረበት ነበር አሁን ደግሞ ሲወጣ የከፋ ዕጣ ክፍል ገጠመው፤”ሲገባ ያልተቀበሉት ሲወጣ ሸኝ የለውም” ይባል የለ፥ያለ ቀልብ ገብተው ቀልበ ቢስ ሆነው መውጣታቸውም እውን እየሆነ ነው።የድሮው መንግሥት ወድቆ አሁን በመጥፋት ላይ ያሉት ሲተኩ ወገንህ በሙሉ ከላይ እስከ ታች ተከፍቶና ሆደ ባሻ ሆኖ ስለነበር በግልጥና ጠባቂ በሌለው ኬላ ሰተት ብለው እንዲገቡ ፈቀደላቸው፤ከዚያማ ድፍን አገሩን ባለቤት አልባ አደረጉትና ለወሬ ነጋሪ እንዳይተርፍ አርገው ሀብትና ንብረቱን ቀምተው ጥሪት አልባ አርገውት ቆዩ፤አፈር ገፊውም ከርስት ጉልቱ ተነቅሎ ሁሉም ወደ ከተማ ፈለሰ።

ኤዲያ ! ከዚያማ ምን ልበልህ ያልፍልኛል ብሎ ከተማ የገባው ሁሉ የሚልስ የሚቀምሰው የሌለው የበይ ተመልካች ሆኖ ከረመ።ብሶቱ ውስጥ ለውስጥ አገናኝቶት ኑሮ ወንጭፍ እንደተወረወረበት የወፍ መንጋም በአንድ ላይ ግር ብሎ ተነሣ፤ወጣቱ ወንድና ሴት ሳይለይ የኔ ቢጤ አዛውንቶች ሳይቀሩ እናቶችን ጨምሮ የአመጡ ተካፋዮች ሆኑ።በድሮው ጊዜ ህዝብ ሲያምጥ ውስጥ ውስጡን ተሰማምቶ በነቂስ ያለውን መሣሪያ እየወለወለና ጀሌውም ዱላና ቆንጨራውን እየመዘዘ ጫካ ይገባ ነበር፤ሴቶችም በምስጢር ስንቅ ያቀብላሉ፤እንደዚህ ነበር የአባት አደሩ በመንግሥት ላይ ሲታመጥ።የአሁኑ የእናንተው ዘመን ደግሞ ፊት ለፊት እንደ ሻምላና ገና ጨዋታ ውረድ እንውረድ ተባብሎ ነው የሚሞሻለቀው።

የሕዝቡ አመጥም እንደ ውሃ ሙላት ነጎደ፤እናማ የመንግሥት መሃያ ተቀባይ የሆነው ወታደሩ ከኪሱ ምንም ሳያወጣ በታጠቀው ነፍጥ ወገንህን በየቦታው ክፉኛ ፈጀው።በአንዳንድ ቦታማ ጥቃቱ የፈሪ ዱላ ዓይነት ነበር፤ፎቅ ላይ በመውጣትና ቤት ውስጥ ተደብቀው በመስኮት እያነጣጠሩ ብዙ ሕዝብ ጨረሱ።ሕዝቡም ይኽን መሳይ የግፍ ጥቃትና ጭካኔ ሲያይ ሞቱን ተጠይፎ እየፎከረና እያቅራራ በጨበጣ ፍልሚያ የሞት ሽረቱን ተያያዘው።ባለ መሃያው ወታደርም ነገር ዓለሙ ከአቅሙ በላይ ሆነበት፣አለቆቹም መሸሽና በደበቅ ጀመሩ።በየጎበዝ አለቃው የሚመራው አሻፈረኝ ባይነት የጋራ አለቃና አዋጊ እንዲኖረው አስፈለገው።ሦስት ብልህ የተባሉ ስዎች ውስጥ ውስጡን መክረውና ዘክረው በመስማማት ብቅ አሉ፤ሦስቱም ወደ ገደል በመንክርባለል ላይ ካለው መንግሥት ጋር አብረው የሰሩና ውስጥ አዋቂወች ናቸው ይባላል።

ኤዲያ! ከዚያማ አንድ ቁመቱ የፋርጣውን ሽፍታ አመሸ ትርፌን የሚያክል ቆፍጣና ወጣት አለቃ ወጥቶ ሕዝቡን በማረጋጋት እኛን ተከተሉን አለ።በድሮ አለቆቹም ላይ ቂም ቋጥሮ ኖሮ ክፉኛ ዛተባቸው፣ንቀቱንም በሕዝቡ ፊት ገለጠላቸው።ወገንህ በሙሉ ለአያሌ ዓመታት አጥቶትና ናፍቆት የነበረውን የሀገርና የባንዲራ ፍቅሩን እንደ ቡናና ዕፀ ፋርስ ሱስ ነው ሲለው በደስታ ፈነደቀና ሞቴን ከአንተ ጋር ያርገው ብሎ ተማምሎ ሆ! ብሎ ተንሣ።

ሁለተኛውና የእርሱ ባልንጀራ የሆነው አለቃ ገንባሩን እንደ ነብር ፊት ኮስትሮና ቋጥሮ ብዙም ሳይናገር ሙያ በልብ ነው ያለ ይመስላል እንደ ኮርማ በሬ እየትንጎራደደ በልበ ሙሉነት ተከታዩን አሰባስቦ ለድሮ አለቆቹ የጉሮሮ አጥንት ሆነባቸው።

ሦስተኛው አለቃ ግን እንኳንስ አንተ ጨቅላው እኔ ይህን ያህል ዘመን ፈጣሪየ የዕድሜ ባለጠጋ ሲያደርገኝ ያላየሁት አንደበቱ ርዕቱና ንግግሩ እንደ ማር የሚጥም ትንሽና ትልቁን አክባሪ፣ሴትና ወንዱንም በእኩል ዓይን የሚያይ፣በአፍህ ማር ይዝነብ አስብሎ እረኛንና አዝማሪን ያዘፈነ እጡብ ድንቅ የሆነ አንጎሉ ክፍት ያለ ሰው ነው።የእሱን ንግግር ያዳመጡ የየአድባራቱ ቃለ እግዚአብሔር አስተማሪና ሰባኪ መምህራንና ቀሳውስትም እኛ አፍ የለንም፣ምንስ አውቀን እንዲሉ አሰኝቷቸዋል።ያገሩንና የወገኖቹን ፍቅር ሲገልጥም እኛ ስንኖር ኢትዮጵያውያን ስንሞት ደግሞ ኢትዮጵያ ነን አለ።ወገንህም ከደስታው ብዛት በእንባ ተራጨ፤እሱም በእያንዳንዱ ልብ ውስጥ በፍቅር ጥቅልል ብሎ ተኛበት፣በሀገሩ ሕዝብም ተኩራራ።

ደባልቄ

እንደ እኔ አባትህ እኮ የታደለ የለም።ብዙዎች ባልንጀሮቸ የዕድሜ ዘልዛላ አረከን እያሉ ፈጣሪያቸውን ሲያማርሩ ለእኔ ግን አንተን ፈረንጅ አገር የላከልኝ ሳያንሰኝ ይህን የዛሬውን ደስታ በአካል ቁሜ እንዳይ አብቅቶኛል።ሰውየው እኮ በዚህ ይብቃህ አልተባለም ፤ገና ዘውድ ጭኖ ንጉሥ ትሆናለህ የተባለለትና ትንቢት የተነገረለት ነው አሉ።እሱም ይህን ያውቃል፥ገና በሰባት ዓመቴ ለናቴ በራዕይ ተገልጦላታል ብሎ በሕዝቡ ፊት በጠራራ ጠሃይ ተናግሮታል፤” የሚያድግ ጥጃ ከገመዱ የሚያጠግብ ቂጣ ከምጣዱ”ይባል ይህ አይደል።ለእኔም እኮ አንተ ኑሮህና ግንባርህ ፈረንጅ አገር እንደሚሆን ግልጥ አርጎ አሳይቶኝ ነበር፤ግልጥ ያልሆነልኝ ነገር ቢኖር መተዳደሪያህን አልነገረኝም ።ይሁን አገር ባትገዛም የሚያይህ ስለሌለ” ሾላ በድፍኑ” እንደሚባለው ሰለ አንተ ሳወጋ ግልጥልጥ ሳላደርግ ለአገርህ ሰው በሞላ ደግ ደጉን ብቻ እናገራለሁ፤የኛ ሰው እንደሁ አገሩን የለቀቀ ሁሉ ደልቶትና ተመችቶት የሚኖር ነው የሚመስለው።

የጧት ግንባርህና እህል ዉሃህ እንዲህ ፈረንጅ አገር ሊሆን ቻለ እንጅ እንደኔና እንደ እናትህ ምኞትና ጠሎትማ ከዚሁ አገርህ ላይ ተድረህና ተኩለህ፣ወልደህ ከብደህ፣ተከብረህና እኛንም አሰብረህ እንድትኖር ነበር።ገበሬ ሆኖ አርሶና አፍሶ መኖሩ ጌጥ ቢሆንም ድካሙ ጭንቅ ስለሆነ ያሁኑ ኑሮህ ይሻላል።እንኳንም ከአፈር ገፊነት አመለጥክ።ከዚህ ያሉት ያንተ ባልንጀሮች አፈር ገፊ እንደሆኑ አፈር እየሆኑ ነው ያሉት፤ለመሆኑማ ሁሉም አልቀዋል እኮ፣ማንስ ተርፎ እከሌ ልበልህ

ደባልቄ

ወደ ጀመርነው የአገራችን መደፍረስ ጉዳይ ልመልስህና አሁን መጨረሻ ላይ ደሞ አንድ ልባም የሆነ ቁመናው ዘለግ ብሎ ሰውነቱ ደልደል ያለ አራተኛ አለቃ ከሦስቱ ጋር ተዘንቋል።አሁን አራት ሁነዋል ማለት ነው።በጠንካራ የእርሻ በሬዎች ብናሸርፋቸው እኮ ሁለት ጥንድ ጥማድ ሆነዋል።ጠንካራ የእርሻ በሬ ያለው ገበሬ ምርቱ በረከት ያለው ነው፤ማሳውንም አልሞ ነው የሚያርሰው።

አሁን እነዚህ አራት ጠንካራ አለቆች ሕዝቡን ተከተለን ብለው ኬላ ኬላ ቢያስይዙትና በአዝማች በአዝማች ቢያሰልፉት አገሩን ከጫፍ እስከ ጫፍ ያረጋጉታል ብለን ተስፋ ጥለንባቸዋል።ተባራሪ ሽፍታ ብቅ ጥልቅ ማለቱ ስለማይቀር በስማ በለው ልናጠፋቸውና ልንማርካቸው አይጨንቀንም።

ደባልቄ

ይህ በዲስኩር ጎበዝ ነው ያልኩህ አለቃ ሁኔታው በመጥሐፍ ቅዱስ ላይ ስላለውና መምሬ ይባቤ ከቀዳሴ በሁዋላ አንድ ሰሞን ያስተማሩን ትዝ አለኝ።ሙሴ የሚባል ሰው ነበር፤የዘመኑ ንጉሦች ሊያስገድሉት ሲያሳድዱት በሽሽት ላይ እንዳለ ፈጣሪው ተገለጠለትና ከአደጋ አድኖ እንዲስብክና እንዲያስተምር እረኞችና የኔ ቢጤዎች ወዳሉበት ላከው፤እሱም ስለ ሰላምና ስለ ፍቅር እየሰበከ አያሌ ተከታዮች አገኘ ብለውን ነበር።የአሁኑ የኛው ሰውም ነገራ ነገሩ ይህን ይመስላል።ሕዝቡ በነቂስ ደግፎታል አሉ።ሦስቱ አለቆች ተመካክረው እሱን የነሱ ሁሉ አለቃና የጦሩ ፊታውራሪ እንዲሆን መርጠውታል።እናቶች በሙሉ ያንተን እናት ጨምሮ እየመረቁትና ጠሎት እያረጉለት ይገኛሉ፤እሱም ይህን ተርድቶ ይመስላል አያሌ እናቶችን ትልልቅ አለቃ አርጎ ሹሟቸዋል፣እንድየ ያውቃል እናትህም ትሾምና ትሸለም ይሆናል፤የሷ ጠሎትና ምህላ እንድሁ ለፈጣርዋ የቀረበ ነው።

እሱም ምንም አንኳን አንተ ከኔ አብልጠህ ነገሩን ብታውቀውም ፈረንጅ አገር ድረስ በመሄድ የተጣላውን አጎናብሶና አስማምቶ፣የታሰረውን አስፈትቶ፣ያኮረፈውን አለስልሶና አሳምኖ፣ተከፋፍለው የነበሩ የቤተስኪያን አለቆችንም  አግባብቶና ይቅር አባብሎ  ወደ አገራቸው መልሷል ይሉታል።የሞት ፍርድ ተበይኖባቸው ዓለም በቃኝ የከረሙትን ሁሉ ተራ ሌባንና ሽፍታን ሳይቀር በነጣና ምህረት አርጎ ለቋቸዋል።ማንም እሱ የሚናገረውን የሚያጣጥልና ጎረበጠኝ የሚል አይሰማም፤ሁሉም የልቤን ነው የሚናገረው ይላል።

እሱ ያልተመቻቸው ቢኖሩ የድሮ አለቆቹ ሲዘርፉና ሲሰርቁ የነበሩት ብቻ ናቸው።እናማ የሱን ዲስኩር የሰሙና ሀገራቸውን የናፈቁ በሙሉ ሸፍተው የከረሙት ሳይቀር አገራቸው ተመልሰዋል።አንተም በዚህ አጋጣሚ አብረህ ትመጣለህ ብለን ብንጠብቅም ችግርህን ስለምናውቀው አልፈረድንብህም።አንድየ ባለው ዕለት ትመጣልናለህ ብለን ተስፋ ሰንቀናል።

እናማ በየቦታው ፍሪዳ እየተጣለ ሕዝቡ ፍቅር አሳይቶ ወንዱ በሆታ፣ሴቱ በዕልልታ ካህናቱ በውዳሴና በዝማሬ፣ወጣቱም በጭፈራ እየቦረቀ ተቀበላቸው።ባላንጣ ሆነው የቆዩ የጎረቤት አገር ስወችም የደስታው ተቋዳሽ ሊሆኑ ችለዋል።ዕድሜና ጤና ለአንተ ይሁንና ልከህልን በገዛነው ራዲወና ቴሌቢዥን ጧት ማታ እያየን ተጎልተን እንውላለን።ዛሬ ሁሉም ከቴሌቢዥን ላይ ዓይኑን ተክሎ እየዋለ ሥራ ፈት ሁኗል።አንዳንዴማ እረኛውና ገበሬውም ጭምር ሳይቀሩ ቤት ስለሚዉሉ ጥጆችና ፍየሎች ታስረው፣በሬዎችም ተፈተው ይውላሉ።

ደባልቄ

የኔ ነገር ሥራ መፍታት ስለማልወድ በአርጅና ቦለቲከኛ ሁኘልሃለሁ፤የአባት አደሩን ረሳሁና ስለ አንተ ጤንነትና ስለ አኗኗርህ ጭምር ጭውውት ማድረግ ሲገባኝ እኔ ለማልገዛው ጉዳይ ቦለቲካ አወራለሁ።ለነገሩማ ቤት መዋሌና ጉልበት ባጣ እንጅ እኔ ያንተ አባት ካማን አንስ ነበር? አሁን አሁንማ የሚነሽጠኝ ድሮ እኛ አገር ስንጠብቅና አካባቢያችን በሽማግሌ ዳኝነትና በጎበዝ አለቅነት ስንመራ በነፍስ ወከፍ የነበረን መሣሪያ ቢበዛ አንድ ፍሻሌ ሽጉጥና አንድ ናስማስር ጠምንጃ ነበር።አሁን አሁንማ ከክላሽ አልፎ ሃያና ሰላሣ ጥይት የሚጎርስ ጠመንጃ በየገበያው ይሸጣል።ዋጋው የትየለሌ ባይሆንብኝ እኔም አምሮኝ ነበር።ያው መቸም አንተኑ ማጣፋትና ማስቸገሩ እየከበደኝ እንጅ እኔ አባትህ ጠመንጃ አያያዝና አተኳኮሱን ከሆነ አምጡ ድገሙ ቢባል የማኮራህ እንጅ የማሳፍርህ አይደለሁም።ቢሆንማ ብትችልና ቢመችህ ሳልሞት አንድ ማለፊያ ዘመናዊ መሣሪያ ብትገዛልኝ ምርቃቴ እስከ ወዲያኛው ይጠብቅሃል።ሌላው ቢቀር ለመቃብር ቤቴ ማሠሪያ ታስበው የነበረውን ትተህ መሣሪያውን ከበቂ ጥይት ጋር ብታደርግልኝ እመርጥ ነበር።ዛሬ ማንም ከዚህ ዉደቅ የማይባለው ሁሉ ዘመናዊ ነፍጥ ሲታጠቅ እኔ የአንተ አባት በአንድ ጎራሽ ናስማስር መቅረብ ሃፈሬታው ለኔ ብቻ ሳይሆን ለአንተና ለሁሉም ልጆቸ ነው።አለበለዚያማ በልበ ሙሉነትና በቆፍጣና ወንድነት ከሆነ ከማንም እልቃለሁ እንጅ የሚበልጠኝ ቀርቶ የሚስተካከለኝም እንደሌለ አውቃለሁ፤እንዲያው ለእናንተ ኩራትና መከበሪያ ቢሆን ብየ እንጅ።

ደባልቄ

የእኔ ነገር አንዱን ሳልጨርስ ሌላውን ጨበጥ ለቀቅ እያረኩ መሰለኝ።ስለ ጀመርኩት አዲሱ አለቃ እንዲያውም አሁንማ የሁሉም ሕዝብና የሀገሪቱ መሪ ስለሆነ ገና ባይነግሥም መሪያችን ልበለውና የማወጋህን ልብ ብለህ አድምጥ።

ሰውየው እንዳልኩህ አንጎሉ ክፍት ስለሆነ ለሚናገረው ሁሉ አፍህን ክፍት አርገህ አንድትሰማው ያደርግሃል፤እየዋለ እያደረ ግን ያው ወገንህ እንደምታውቀው የሚያወጋውና ልቡ የሚሸፍትበት ውስጥ ወስጡንና  ከራሱ ጋር ስለሆነ የሰውየውን የፍቅር ወግና ዲስኩር ወደ ጉርምርምታ ለውጦታል።ችግር ነው ተብሎ የሚወጋውም ቆራጥና ቆፍጠን ያለ ትዕዛዝና ብይን አይሰጥም፤ወይ ይፈራል አለዚያም አልቻለበትም የሚሉ ሀሜቶች ናቸው።በመሆኑም እሱ ቀን የሰራውን ሌሊት ያፈርሱበታል፣እሱ ስለ ፍቅር ሲሰብክ ጥላቻንና መበታተንን ሲያስፋፉ ይታያሉ፣ወንጀለኞቹን በሰላም እጃችሁን ለህግ አቅርቡ ሲላቸው እነሱ በየቀበሮ ጉድጓዱ ተደብቀው ሕዝቡን ለአመጥ ያነሳሳሉ፣እሱ ስለ አብሮነትና መከባበር ሲሰብክ እነሱ አሻፈረን ለአንተ አንገዛም ይሉታል።

ይኽውልህ በዚህ መካከል ደግሞ ሌላ የከፋ ነገር መጣ።ምንም እንኳን እኔ ከዚህ በፊት ሂጀ ባላውቅም ደርሰው የመጡት እንዳወጉኝ አዲስ አበባ የሚባለው የንጉሦቹ መቀመጫ ከተማ እንደ ጣና ሐይቅ የተንጣለለና ያንድ ራሱን የቻለ ምክትል ወረዳ ግዛት የሚያክል ስፋት ያለውና የሀገራችን ሰው ከየቦታው ተሰብስቦ የሚኖርበት፣ በሀብትና በስልጡንነት ብልጡግ የሆነ ከተማ ነው አሉ።የፈረንጁ አገር መንግስትና እንግዳ ሲመጣ የሚያርፈውም ከዚያው ነው ይባላል።ነዋሪው ሕዝብ ሸምቶ አዳሪ ነው ቢባልም እንግዳ ሲመጣበት መስተንግዶው ከሞሰቡ ተርፎና ተትረፍርፎ እስከሚነሳ ድረስ ነው ብለው ሲያወጉኝ በአገሬና ወገኔ ኮራሁበት።መቸም ሳልሞት አዲስ አበባን አንድ ቀን እንደምታሳየኝ ተስፋ አለኝ።

ምንም እንኳን በግብርና አይተዳደሩ እንጅ መስተዳድራቸው በራሳቸው ነው ይባላል፤አሁን እኛ እንኳን በአቅማችን በወረዳው መስተዳድር ሥር እንሁን እንጅ የሚያስተዳድረን ሌላ ሳይሆን የራሳችን ገበሬ ማህበር ነው።በይፋግ ከተማችን ውስጥም ዕድሩ፣የሴቶችና የወጣቶች ማህበር ቢኖርም ሃላፊው ገበሬ ማህበሩ ሲሆን የገበሬ ምህበሩ አለቃ ደግሞ ምክትል ወረዳው ነው።በከተማችን ውስጥ የሚገኘው ጥቅማ ጥቅምም በሙሉ ለከተማችንና ለነዋሪው ሕዝቧ ብቻ ነው።አዲስ አበባም ከንቲባ የሚባል የኛን ገበሬ ማህበር የሚመሳሰለ መስተዳድር አለው አሉ።

ታዲያማ እንዲህ እያለ የከተማው ዕድሜ ሲሰላ የአምስትና ስድስት ትውልድ ዕድሜ ነው ይባላል፣ያውም ከዚያ ባይበልጥ አይደል? ይህን ዕድሜ እንግዲህ የእኔ ቅድመ አያትና ያንተ ምንዝላት ደርሰውበታል ይባላል፤አጤ ዳዊት የሚባሉ ንጉሥ ናቸው አሉ የቆረቆሩት፤ያስኳላ ትምህርት ስለሌለኝ በዘመን ቆጠራ ላይ እምብዛም ነኝና አንተው አስላው።

ይኽውልህ እንዳንተ ፈረንጅ አገር በመኖር አማሪካ ከሚባለው ቦታ የመጣ አንድ ኮበሌ ቢጤ ወጣቱንና ጨዋውን ሕዝብ ሰብስቦ በዲስኩር በማደናገር አዲስ አበባ የእናንተ ብቻ እንጅ ከዚህ እንጀራ ፍለጋ ለመጡትና ተወልደው ላደጉት አይደለችም፤እነሱን ማስወጣትና ማባረርም መብት አላችሁ ብሎ ስላነሳሳቸው ከፍተኛ አምባጓሮ በተደጋጋሚ ደርሷል እየተባለ ይወጋል፤ነፍስም ጠፍቷል አሉ።አምባጓሮ ፈጣሪው ሕዝብ ጎራዴና ገጀራ ይዞ በመምጣት ሲያምሰው እንደሰነበተ በሃዘኔታ ይተረካል።ደግነቱ የሀገር ሽማግሌዎችና ነገር አዋቂዎች ደርሰው ለጊዜውም ቢሆን ባያበርዱት ኖሮ ጭንቅ ያለ ችግር ይፈጠር ነበር።ነገራ ነገሩም ገና ስለአለየለት ውስጥ ውስጡን እየታመሰ አሁን ድረስ አለ፤የቤታችን ራዲወና ቴሌቢዥንም ይህኑ ነግረውናል።

በአዲስ አበባው ሕዝብ ወገን ደግሞ አንድ ብልህና የህግ አንቀጥ አዋቂ ከዚህ በፊት የሕዝቡን መብት አስከብራለሁ ብሎ የተሟገተና መንግሥት ተናዶበት ዘብጥያ ለአያሌ ዓመታት ያጎረው አሁን በድጋሜ ሕዝቡ ሲንገላታ ቁሜ አላይም በማለት ዋቢ ጠበቃ ሆኖ ቆሟል ይላሉ።በዚህ ሰው ገጥም በጣም ብዙ ሕዝብ አብሮት ቁሟል ተብሎ ይወጋል።ይሁን እንጅ ያ ዲስኩር አዋቂና ክፍት አንጎል አለው ያልኩህ መሪ በዚህኛው ሰው ላይ ክፉኛ የሆነ ቅያሜ አድሮበታል እያለ ሰውና ራዲወን ቴሌቢዥኑ በየገበያውና ሰንበቴው በስፋት ያወጋል።አስማምቶና ድንጋይ አሸካክሞ የሚያስታርቅ ካልመጣ አስጨናቂ የሆነ የሕዝብ ለሕዝብ መራበሽ ይመጣ ይሆናል ብለን በጣም ስጋት ተሰምቶናል።መቸም እውነተኛ ጠሎት ማለት በዚህ ጊዜ ስለሆነ እኔና እናትህም ሕዝቡን አስማማው፣የመንግሥቱንም አልጋ አጥናው  ለማለት ሱባዔ ገብተናል።አንተም ብትሆን መጠለይ አለብህ፤በአሁኑ ጊዜ ሽማግሌ ስለሌለ የእናንተ የህጣናቶቹ ጠሎት ነው ይህችን አገር ሊያረጋጋትና ሊጠብቃት የሚችለው።

ሁሉን አዋቂው የሊቦው ጌወርጊስ አንተም ሆንክ እኛ የምናደርገውን ጠሎትና ምህላ ይስማን ዓሜን።

ሳትሰለች ጣፍልን፣ከቻልክም በስልኪ ድምጥህን አሰማን

ቸር ይግጠመን

አባትህ ባላምባራስ ቢተው አደፍርስ

እናትህ ወይዘሮ ዓለሙሽ ማንያዘዋል

ተፃፈ  እንደ ኤሮፓ አቆጣጠር   2018 ዓ.ም

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

ከነፃነት ዘገዬ የአራት ኪሎው ኦነግ ሸኔ ከቁጥር ጋር እንደተጣላ ዕድሜውን አገባደደ፡፡ ኦነግ/ኦህዲድ ዛሬም ሆነ ዱሮ፣ በቤተ መንግሥትም ይሁን በጫካ ቁጥር ላይ ያለው አቋም ምን ጊዜም ያስደንቀኛል፡፡ ደግሞም እየባሰባቸው እንጂ ሲቀንሱ አይታዩም፡፡ ጥቂት

80 ቢሊዮን ብር ስንት ብር ነው?

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

Go toTop