የሶማሌን ክልል ተመልከቱ፡፡ በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ተወዳጅ የሆነው ሙስጠፌ በበሳል አመራሩ (የሚጠራውም በቁልምጫ ሙስጤ/ ሙስጠፌ እየተባለ መሆኑን ልብ ይሏል) በክልሉ ያሉ ዜጎች እንዴት ተከባብረውና ተፈቃቅረው እየኖሩ እንዳሉ እያስተዋልን ነው – የኢትዮጵያ አምላክ ቀን ከሌት አይለየው፤ እንደብዙዎች ሥልጣንና ሀብት አሳዳጆች ለሆዱ አላደረምና ልጅ ይውጣለት፡፡ ዜጎችንና ሀገርን በገንዘብ የሚለውጡ፣ ከሰው ይልቅ ገንዘብ ፊታቸው ላይ እየተደቀነ በንዋይ ምትሃታዊ ኃይል የሚቸገሩ ከርሣሞች ከዚህ ዕንቁ ሰው መማር አለባቸው፡፡ ሰው መሆን እንዲህ ነው – ያዝልቅለት፡፡ ከነእንቶኔ ዲያብሎሣዊ ሠይፍም ይጠብቀው፡፡ በሙስጠፌ ግዛት ክርስቲያኖች አይታረዱም፣ የማምለኪያ ሥፍራዎቻቸው አይቃጠሉም፤ ምዕመናኑም ሆኑ ቤተ አምልኳቸው አይዋረዱም፡፡ ሞትና ስደት፣ የዘር ፍጅትና እንግልት ከሞላ ጎደል ታሪክ የሆኑበት ክልል የኢትዮጵያ ሶማሌ ነው ማለት እንችላለን፡፡ ይህ ከምን መጣ ብለን ስንጠይቅ ከመስቀያው መሆኑን እንረዳለን፡፡
አዎ፣ ከመስቀያው ነው፡፡ አናቱ ከተበላሸ ግርጌውም የመበላሸት ዕድሉ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ አናቱ ደግ ከሆነ ግርጌውም ደግ የመሆን ዕድሉ ያንኑ ያህል ነው፡፡ ስለዚህ ጥሩ አመራር የሚሰጥ ሲገኝ በህልምህም የማታስበው ድንቅ ነገር ልታይ ትችላለህ፡፡ የሶማሌ ክልል በአብዲ ኢሌና ከዚያም በፊት እንዴት እንደነበር የምናስታውሰው ነው፡፡ ሙስጤ ግን በኃይልና በጡንቻ ሣይሆን በብልኅ አመራር ክልሉ አሁን ምንም ነገር ኮሽ የማይልበት እንዲሆን አድርጓል፡፡ አራጆችን አደብ ከማስገዛት ይልቅ እያሰለጠኑ ጃዝ የሚሉ ክልሎች ከርሱ ቢማሩ ምን ያህል ባረፍን፡፡ የሀገራችንም ዕድገት ምን ያህል በተሳለጠ፡፡ ሀገር ስታረጅ ምን ዓይነት ጃርት መሪዎችን እንደምታፈራ እያየን ነው፡፡ መሪው የተበላሸ መኪና ገደል እንደሚገባ ሁሉ አናቱ የተበላሸ የሀገር አስተዳደርም አገሪቷን ገደል እንደሚከት በግልጽ እያየን ነው፡፡ እናት አባት ብልሹ ምግባር በሚያሣዩበት ቤተሰብ ውስጥ ጥሩ ልጆች የመውጣታቸው ዕድል ጠባብ ነው፡፡
ይቅርታ፡፡ የማይሞት ሰው ሞተብን፡፡ ሞት ደፋር ነው፤ ማንንም አይምርም፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ነፍሳቸውን ይማር፡፡ እያስደሰቱንም፣ እያወዛገቡንም፣ ገብተውንም፣ ሳይገቡንም … ብቻ እንደምንም ብለው እርሳቸው ሩጫቸውን ጨረሱና ተሰናበቱን፡፡ አንድ ሁለት ዓመታትን ቢቆዩና የሀገራቸውን የመጨረሻ ዕጣ ቢያዩ መልካም ነበር፡፡ የእግዜሩ በለጠና አልሆነም፡፡ ለነገሩ ለርሳቸው ይሻላቸዋል – ሞት ለማንም ባይመረጥም፡፡ ይረፉበት፡፡ በዚህች አገር ከመኖር እንደውነቱ መሞት የተሻለ ነው – በልተህ ስለጠገብህ፣ ጠጥተህ ስለረካህ፣ ለብሰህ ስለሞቀህ፣ ወጥተህ ስለገባህ፣ ተኝተህ ስለተነሣህ … እየኖርክ ከመሰለህ ተሳስተሃል፡፡ መኖርና አለመኖር ብዙ ትርጉም አላቸው፡፡ የሞቱ ወገኖቻችን በሕይወት አለን የምንለውን የሚበልጡባት የመጀመሪያዋ ሀገር ኢትዮጵያ መሆን አለባት፡፡ የፍትኅ ዐይኖች ጠፍተው፣ አንዱ ዘረኝነት በሌላው ተተክቶ እግር አውጥቶ እየተንጎማለለ፣ ሙስና በየፈርጁ ተንሠራፍቶ አገር ምድሩን በንዳድ እያነፈረ፣ ኮሮና ሀብታም ድሃ ሳይል የሁሉንም ቤት እየጎበኘና ያሻውን ወደ መቃብር እያጋዘ፣ የሀገርና የወገን ስሜት ጠፍቶ ሁሉም ማለት በሚቻል ደረጃ ወደ ግዑዝነት እየተለወጠ … ባለበት ሁኔታ በሕይወት መኖር ከሞት አይሻልም፡፡ ለማንኛውም ሰሞኑንና ባለፉ ጊዜያት የሞቱብንን የነአልማዝ ኃይሌንና ሌሎቹንም የሀገር ባለውለታዎች ነፍስ ፈጣሪ ይማርልን፡፡ ክፉዎችን እየወሰደም በበጎዎች ይተካልን፡፡ አሁንስ ጊዜው አስጨናቂ ሆነና ሊያሳብደን ነው፡፡ እባካችሁን ሁላችንም ብንጠፋ እንኳን አንድ አምስት የምትሆኑ እግዜር የሚሰማችሁ ደኅና ሰዎች ካላችሁ ጸልዩ!!…
እናላችሁ አንድ መሪ ጥሩ ከሆነ ብዙ ነገር ጥሩ ይሆናል፡፡ ባለጌና አሳዳጊ የበደለው ስድ ከሆነ ግን አሁን በኦሮሚያና አዲስ አበባን ጨምሮ በሌላዋ ኢትዮጵያ የምናየውን የመሰለ ሁከት ለማየት እንገደዳለን፡፡ አዲስ አበባ ደግሞ ይበልጥ ታሳዝናለች፡፡ የሁለት ሀገራት ዋና ከተማ ሆና ፍዳዋን እያየች ነው፡፡ አንዲት ሴት ሁለት ባል አግብታ ስትሰቃይ ይታያችሁ፡፡ አዲስ አበባም ዛሬ የግብጽ ባንዲራን በሚመስል ጨርቅ ተጠፍንጋ ትውልና ነገ ደግሞ መሀሉ የዋርካ ዛፍ ያለው ቢጫና ቀይ ባንዲራ ልትተበተብ ትችላለች፡፡ ያ ባለኮከቡ የጋራ የተባው የመለስ ዜናዊ ባንዲራማ አሁን ባለቤት ያጣ ይመስላል፡፡ የጨረባ ተዝካር፡፡ ወይ ኢትዮጵያ! እናስ አሁን አለን ማለት እንችላለን? ቀባሪ ጠፋ እንጂ አልሞትንምን? ፕሮፌሰር መስፍን ከኛ አልተሻሉም ታዲያ? እስኪ ምን ቀረባቸው? ምንም፡፡
እነዚህን ኢትዮጵያን ቀዳደው በኦሮምኛ ክር ከእንደገና እንስፋ የሚሉ ኩታራ ወንድሞቼን በቀጣዮቹ ሥነ ቃላት ላወድሳቸውና ጅማሮየን ልቋጭ፡፡
ሽመልስና አቢይ እየተባባሉ፤
በተስኪያን አናስም አናጸልይ አሉ፡፡
ሽመልስና አቢይ ምንና ምን ናቸው፤
የጆሮ ጉትቻ ያንገት ሀብል ናቸው፡፡
… ግራኝ አቢይ አህመድ እንዳነሳሱ ቢሆን ኖሮ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ የት በደረሰች ነበር፡፡ ግን እባብ ምን ጊዜም እባብ ነው፡፡ ተፈጥሮን ደግሞ ተመክሮ አይለውጠውም፡፡ ስለሆነም አቢይ የተላከበትን ሥውር ዓላማ ለማስፈጸም ሲል ከቢጤዎቹ ከነሽመልስ ጋር እያደረገ ያለውን በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ወዮልን ዘንድሮ! አያያዛቸው ሥር የሰደደ ነው፤ በሚሊዮኖች ደምና አጥንት የተገነባችን ሀገር አፍርሰው ኦሮሙማን ለመገንባት የማይፈነቅሉት ነገር የለም፡፡
ለምን አርፌ እንደማልቀመጥ ግን እኔንም ግራ ይገባኛል፡፡ ይሄ የሀገር ነገር የአእምሮ ሰላም ይነሳል፡፡ ምን እሱ ብቻ በአንዳንዶቻችንማ ገና ብዙ ነገር … ሆድ ይፍጀውማ፡፡ ይህች አገር ከሞት እስክትነሣ ብዙዎች ወንድማማቾችን በማይረቡ ተራ ነገሮች ሳይቀር እየገደለችና እያገዳደለች ናት፡፡ አሁን ያለንበትና መጪው ጨለማ ጊዜ ብዙ ሰው የገባው አይመስልም፡፡ የተደገሰለትን ባለማወቅ በተራ ነገር ሲራኮት የሚታየው ሞኛሞኝ ጥቂት አይደለም፡፡