August 17, 2020
44 mins read

ጥያቄ፦ ከእኛ ለእኛ – ጠገናው ጎሹ

የአገራችን ፖለቲካ በሸፍጥና በሴራ አስተሳሰቦችና አካሄዶች የተበከለ በመሆኑ ከመሬት ላይ ካለው መሪር ሃቅ ለሚነሱ (ለሚሰነዘሩ) እጅግ አስፈላጊና ፈታኝ ጥያቄዎች የሚሰጣቸው ምላሾችም በዚያው ልክ በሸፍጥና በሴራ የተሞሉና ከእውነታው ጋር የማይገናኙ ናቸው። እንዲህ አይነቶች አስከፊ አስተሳሰቦችና አካሄዶች ደግሞ የተጠናወጡት የተወሰኑ ባለሥልጣናትን ወይም የመንግሥትና የፓርቲ አካላትን ብቻ ሳይሆን እራሱን ሥርዓቱን ነው ከላይ ከአናቱ እስከ ታች የእግር ጥፍሩ የተንሰራፉበትና ሥር የሰደዱበት ። ይህን ለማወቅ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ ከላይ እስከታች ያሉ ባለሥልጣናት ፣ በሥራቸው የሚገኙ ሃላፊዎችና ካድሬዎች በየጊዜው የሚደሰኩሩትን ዲስኩርና የሚሰጡትን መግለጫ ወይም ሃተታ ወይም ማብራሪያ ከመሬት ጋር ካለው መሪር እውነት ጋር በማመሳከር ልብ ማለት ብቻ በቂ ነው።

እርግጥ ነው እንኳን እንደ እኛ ባለ አገር በአንፃራዊነት አድጓል በሚባል ዴሞክራሲያዊ አገርም ፖለቲካና ፖለቲከኛ ከእንዲህ አይነት ችግር ጨርሶ ነፃ ሊሆን አይችልም። የገሃዱ ዓለም እውነታም አይደለም። በአንፃራዊነት ባደገ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ ችግሮቹ የሚፈጠሩት በግለሰቦች ወይም በተወሰኑ ቡድኖች እንጅ በአጠቃላይ በሥርዓት ብልሹነት አይደለም ። ከዚህ በላይ ደግሞ የህግ የበላይነት እና የነፃ ሚዲያ ሃያልነት ለወስላቶች የሚመች አይደለም ።

በተቃራኒው እንደኛ ባለ አገር ያለው የፖለቲካ ሥርዓት ምን አይነት እንደሆነና በአገር ላይ እያስከተለ ያለውን መከራና ሰቆቃ በጥያቄዎቼ ሥር ለመግለፅ ስለምሞክር እዚህ ላይ ብዙ አልልም።

ጥያቄዎችን የማቀርባቸው የማይታወቁና አዳዲስ የውይይት መነሻዎች የሚሆኑ ናቸው በሚል አይደለም። ምክንያቶቼ ሀ) ምንም የሚታወቁ ቢሆንም አብዛኛው የፖለቲካ ነገረ ሥራችን ፖለቲከኞች በሚሰጡን አዳዲስ አጀንዳና ስሜት ኮርኳሪ ክስተቶች እየተጠመድን ለመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ ቁልፍ ናቸው ያልናቸውን ጥያቄዎችና ጉዳዮች ወደ ጎን የመግፋታችን ወይም ጨርሶ የመርሳታችን ክፉ ልማድ አላስፈላጊ ዋጋ እያስከፈለን መሆኑን ለማስገንዘብ ፤ ለ) የመከራና የውርደት ፖለቲካ ሥርዓት ተወግዶ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን መሆን ካለበት በግልፅና በቀጥታ ለመወያየት የምንፈራው

ወይም የምንሸሸው ጥያቄ ወይም ጉዳይ ጨርሶ ሊኖር እንደማይገባው ለመግለፅ፤ ሐ) በተለይ ከመሠረታዊና ፈታኝ ጥያቄዎችና ጉዳዮች እየሸሹ መንበረ ሥልጣን ላይ የወጣንና የሚወጣን ፖለቲከኛ ዲስኩርና ፕሮፓጋንዳ እየተቀበሉ ከተራ የመንግሥት ጋዜጠኛ ወይም የገዥ ቡድኖችን ፓርቲና መንግሥት ከሚያገለግል ነፃ ጋዜጠኝነት ባይ ባልተሻለ አኳኋን የሚያስተጋቡ ምሁራን ቢያንስ የመማራቸውን ትርጉምና እሴት ላለማኮስመን ሲሉ ህሊናቸውን መመርመር ግድ ይላቸዋል ለማለት እና መ) በአጠቃላይ የምናደርገው ፖለቲካዊ ፣ኢኮኖሚዊና ማህበራዊ ውይይት ወይም ክርክር ወይም ምክክር ከመሠረታዊ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግርና ምሥረታ ጥያቄዎቻችን ጋር በአግባቡ ካላያያዝናቸው አንዱን አንስትን አንዱን ስንጥል ምንም ሳንጨብጥ (ሳንይዝ) ስለምንቀር ቆም እያልን ከምር እናስብ ለማለት ነው።

ወደ ጥያቄዎች ልለፍ ፦

ፖለቲካ ምንድን ነው? ፖለቲካ ሥርዓተ መንግሥትን የመመሥረትና የማስኬድ ሳይንስና ጥበብ መሆኑ ቀርቶ የባለጌና ግፈኛ ገዥ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች መሣሪያ እና የብዙሃኑ ህዝብ የመከራና የውርደት ቀንበር የሆነው ወይም እየሆነ ያለው ለምንድን ነው?

ፖለቲካን በእውቀትና ችሎታ ላይ ከተመሠረተበት ምንነቱ (ከሳይንስነቱ) እና በአይነቱ ብዙና በይዘቱ ውስበስብ የሆነውን የሰው ልጅ ባህሪና ፍላጎት በአግባቡ ከመረዳትና ከማስተናገድ ምንነቱ (ከጥበብነቱ) ቁልቁል አውርደን ከኦህዴድ (ከኦሮሞ ብልፅግና) ባለሥልጣናት አንዱና የኦሮሚያው ገዥ ሽመልስ አብዲሳ እንደሚለን ለምን “ተራ ቁማር” አደረግነው? ተራ ቁማር ያደረገው፣ ያስደረገው፣ እያስደረገውና እያደረገው ያለውስ ማን ነው? የህወሃትን የበላይነት በተረኝነት በተካው ኦህዴድ/ኦዴፓ የሚዘወረውና ስሙን ከኢህአዴግነት ወደ ብልፅግናነት (ብልግናነት ቢባል ይመጥነዋል) የቀየረው ገዥ ቡድን እና እንደ አሸን የፈሉትና የእራሳቸው የሆነ ዴሞክራሲያዊ መርህ ፣ ዓላማና የተግባር ማንነት የሌላቸው ተፎካካሪ ተብየ የፖለቲካ ድርጅቶች ወይም ስብስቦች አይደሉም እንዴ ፖለቲካን ተራ የቁማር ጨዋታ ያደረጉትና እያደረጉት ያሉት?

ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን በህወሃት የበላይነት በሚመራው የግፍና የዝርፊያ ፖለቲካ ቁማር ታማኝ ተጫዋቾች በመሆን በህዝብ ላይ የመከራና የውርደት ዶፍ ሲያወርዱ የኖሩትና ከፈፀሙት አስከፊ ፖለቲካ ወለድ ወንጀል ከምር የመማር ሞራላዊም ሆነ ፖለቲካዊ ሰብእና ፈፅሞ የሌላቸው ኦዴፓዊያን /ብልፅግናዊያን

የህወሃትን የበላይነት አስወግደው ተመሳሳይ ብቻ ሳይሆን የበለጠ ፈጣንና አስከፊ የሆነ የፖለቲካ ቁማር ጨዋታቸውን እንዲቀጥሉ ለምንና እንዴት ፈቀድንላቸው? ይህ ትውልድ ሸፍጠኛ ፖለቲከኞች ባዥጎደጎዱለት ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን የሚያወድስ ዲስኩር ወይም ስብከት ምክንያት የምክንያታዊነት አስተሳሰቡን ልክ የሌለው የስሜታዊነት ትኩሳት ሰለባ በማድረጉ ምክንያት የሆነውንና እየሆነ ያለውን ከሰብአዊ ፍጡር በታች የሚያወርድ የሞራልና የሰብእና ቀውስ ቆም ብሎ ለማስተዋልና የሚበጀውን ለማድረግ ለምንና እንዴት ተሳነው? ይህ ትውልድ የሸፍጠኛና ሴረኛ ገዥ ቡድኖችን እና የተዋርዶ አዋራጅ ተፎካካሪ ተብየ ፖለቲከኞችን የመድብለ ፓርቲ ፖለቲካ ቁማር ጨዋታ በቃ የሚል የፖለቲካና የሞራል ወኔውን ከወደቀበት ማንሳት እንዴት አቃተው?

ሸፍጠኛና ሴረኛ ገዥ ቡድኖች ቤተመንግሥት ድረስ እየጠሩ መመሪያን ከስድብ ጋር የሚያሸክሟቸው ተፎካካሪ ተብየ የፖለቲካ ድርጅቶች ወይም ስብስቦች ለመድብለ ፓርቲ ፖለቲካ ቁማር መቆመሪያነት በሚያገለግሉበት መሪር የፖለቲካ እውነታ ውስጥ የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግርን እንኳን እውን መሆን ማሰብስ እንዴት ይቻላል?

የፖለቲካን ትክክለኛ ትርጉም ወይም ምንነት በሚመጥን ሁኔታ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የመድብለ ፓርቲ ፖለቲካ ጨዋታ የተጀመረ መስሎት የለውጥ አራማጅ ተብየዎችን “እልልልል!”ብሎ ተቀብሎ ለነበረው የዋህ የአገሬ ህዝብ

 

“ፖለቲካ ማለት ተራ የቁማር ጨዋታ በመሆኑ ቁማሩን በበላይነት

(በአጥቂነት) ለመቆመር የሚያስችለንን የመጫወቻ ሜዳ በተሳካ ሁኔታ እያመቻቸን ነው። ህወሃት ኢህአዴግ በሚል እንደተጫወተብን እኛም ብልፅግና በሚል የቁማሩን ጨዋታ በሚገባ በመጫወት ላይ እነገኛለን”

 

የሚል መርዶ ከማርዳት የከፋ ምን አይነት እኩይ ፖለቲከኛነት ይኖራል?

በእንደዚህ አይነቶች የለየላቸው የጎሳ/የመንደር/የቋንቋ ደምና አጥንት ስሌት ፖለቲካ ነጋዴዎች በሚዘወር ሥርዓተ መንግሥት (ፖለቲካ) ውስጥ ያየናቸውና እያየናቸው ያሉ እጅግ ከሰብአዊ ፍጡራን በታች የሚያውሉ ጎሳና ሃይማኖት ተኮር ሰቆቃዎችና ጭፍጨፋዎች (የዘር ማፅዳት/ማጥፋት ወንጀሎች ) እና የንብረት ውድመቶች ቢፈፀሙ ለምን ይገርመናል?

ሸፍጠኛና ሴረኛ ኦህዴዳዊያን/ብልፅግናዊያን ለሩብ ምእተ ዓመት የመጣንበትን የመከራና የውርደት ፖለቲካ ሥርዓት በተረኝነት ለማስቀጠል እየሄዱበት ያለውን እጅግ አደገኛ ሁኔታ ጨርሶ ከቁጥጥር ውጭ ከመሆኑ በፊት ለማስቆምና ወደ

 

ትክክለኛው የጋራ መፍትሄና አቅጣጫ እንዲመለሱ ለማድረግ እስካልቻልን ድረስ እስካሁን ካየነውና እያየነው ካለነው በእጅጉ አስከፊ የሆነ መከራና ውርደት እንደማያጋጥመን ምን ዋስትና አለን ? ቢያጋጥመንስ እንዴት ሊገርመን ይችላል?

 

ግፈኛ ገዥ ቡድኖች በህዝብ ላይ ለዘመናት ካደረሱት የህይወት ጥፋትና የማቴሪያል ድህነት በላይ ከፖለቲካ ወለድ አስከፊ መከራና ውርደት ጋር እንዲለማመድ ያደረጉበት መንገድ ምነው አልታየን አለ? ህዝብ የወቅቱ ተረኛ ቡድን (ኦህዴድ/ኦዴፓ) በሚመራው የመንግሥት መዋቅሮች ውስጥ በሚገኙ ባለሥልጣናትና ካድሬዎች ተባባሪነት በሚፈፀምበት አስቃቂ ወንጀል እየየ ከማለት፣ የደም እንባ ከማንባት እና ምፅዋዕት ከመለመን ለማለፍ ያልቻለበት ምክንያት እውነተኛ የመድብለ ፓርቲ ፖለቲካ ባለመኖሩ መሆኑን ከመሬት ላይ ካለው ግዙፍና መሪር እውነት በላይ ማን ይንገረን? ገዥ ቡድኖችስ የሸፍጥና የሴራ ፖለቲካቸውን እያለማመዱን ያሉት ይህንኑ እጅግ አስቀያሚ ደካማ ጎናችንን ጥርሳቸውን ነቅለው ካደጉበት እኩይ የፖለቲካ ሥርዓት ባካበቱት እኩይ ተሞክሮ አሳምረው ስለሚያዉቁብን አይደለም እንዴ?

 

ጠቅላይ ሚኒስትሩስ እንደ አካባቢውና እንደ ታዳሚው አንደበቱን እየቃኘና እየተቃኘ የሚደሰኩረው ዲስኩር ወይም የሚሰብከው ስብከት አልበቃ ብሎ የአጭር ጊዜ የማስታወስ አቅም (short memory) ማለቱ ይህኑ ሲነግረን አይደል እንዴ? ተፎካካሪ ፖለቲከኞች ተብየዎችን ጽ/ቤቱ ድረስ እየጠራ እንደ ሰነፍ ተማሪዎቹ እየገሰፀ (እየሰደበ) በሚያደርጋቸው ዲስኩሮቹ ውስጥ በወቅቱ በነበረው ዓለም አቀፋዊና አገራዊ የፖለቲካ ርእዮተ ዓለምና አሰላለፍ የተሻለ አማራጭና ለአገራዊ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ለውጥ የሚበጅ መስሎ የታየውን ጎራ ተቀብሎ ጎሳና ሃይማኖት ሳይለይ አብሮና ተነባብሮ የወደቀውን ያን ትውልድ የሚያብጠለጥልበት ህሊናው ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን ጥርሱን ነቅሎ ያደገበትንና አሁንም በእርሱ መሪነት በተሃድሶ ስም ትውልድን እየገደለና እያጋደለ የቀጠለውን በጎሳ/በመንደር/በቋንቋ ደምና አጥንት ስሌት ፖለቲካ ላይ የተመሠረተውን ወንጀለኛ ሥርዓት ዘወር ብሎ እንዲያስተውል ለምን አልፈቀደለትም?

 

ለሩብ ምእተ ዓመት ትውልድን በየጎሳውና በየቋንቋው ከረጢት በመጠርነፍ ፖለቲካ እያናከሰ ፣ እየገደለ፣ እያስገደለና እያገዳደለ በዘለቀ የፖለቲካ ጨዋታ ውስጥ ጉልህ የአገልጋይነት ተሳትፎ የነበረውና አሁንም ጉልቻ እየለዋወጠ የቀጠለው የኦዴፓ /ብልፅግና ፓርቲና መንግሥት መሪ የሆነ ፖለቲከኛ ያን የ1960ዎቹን/70ዎቹን ትውልድ እጅግ በደምሳሳው ለአገራችን የፖለቲካ አስተሳሰብና አካሄድ ብልሹነት

 

 

ሃላፊና ተጠያቂ በማድረግ በንፁሃን መከራና ደም የጨቀየውን የእራሱን ገዥ ቡድን የለውጥ ሃዋርያነት ለማሳየት መሞከሩ የህዝብን የግንዛቤና የማመዛዘን መሠረታዊ ችሎታ ወይም እውቀት የመናቅ ክፉ ልክፍት ካልሆነ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል?

 

ለመሆኑ ከየትኛው ወደ የትኛው ሥርዓተ መንግሥት ነው እየተሸጋገርን ያለነው? ሥርዓቱንስ የሚመራው ማን ነው/የሚመሩት እነማን ናቸው?

 

ለዘመናት በመከራና በውርደት ሥርዓት ውስጥ ከመኖሩ የተነሳ የሚሰማቸው በጎ ቃላት እና ለርካሽ የፖለቲካ ጨዋታ ፍጆታ የሚውሉ አንዳንድ አወንታዊ እርምጃዎች የምር እየመሰሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩን እንደ ብቸኛ በአገርነት የመቀጠል ዋስትና አድርጎ የሚመለከተውን የዋህ የአገሬ ህዝብ አንቅቶና አደራጅቶ ከሸፍጠኛ ፖለቲከኞች የፖለቲካ ቁማር ሰለባነት የሚታደገው በማጣቱ ለዘመናት ወደ መጣበት አዙሪት ተመልሶ ሲወርድ ከማየት የከፋ የትውልድ ውድቀት የትኛው ነው?

 

እንደ ደመ ነፍሱ እንስሳ (ውሻ) ከቤተ መንግሥት ቁራሽ ወይም ፍርፋሪ ከሚጣልላለት ተፎካካሪ ፖለቲከኛ ተብየ በተቃራኒ “መከረኛውን ህዝብ ከሸፍጠኛና ሴረኛ ፖለቲከኞችና ከተባባሪዎቻቸው የጎሳ/የቋንቋ ደምና አጥንት ስሌት ፖለቲካ ልክፍተኞች እንታደገው ዘንድ የመልካም ዜግነታችን ብቻ ሳይሆን ሰው የመሆናችን መሠረታዊ ትርጉምና እሴት ግድ ይለናል” በሚል ፅዕኑ አቋም ፀንተው የሚችሉትን የሰላማዊና ህጋዊ ተጋድሎ ከማድረግ ውጭ ሌላ የጎደፈና የሚያጎድፍ ሥነ ምግባርም ሆነ ተግባር የሌለባቸውን ወገኖች

 

(እነ እስክንድርን ነጋን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል) ጦርነት እንደሚያውጅባቸው ሲዝት የነበረ ጠቅላይ ሚኒስትር በእራሱ ፓርቲና መንግሥት ሰዎች ተባባሪነት የተፈፀመውን አስከፊ ፖለቲካ ወለድ ወንጀል ሰበብ በማድረግ በቁጥጥር ሥር ካዋለ በኋላ ያሰለጠናቸውን ምሥክሮች ተብየዎች ያጠኑትን ከመጋረጃ በስተጀርባ እንዲናገሩ በማድረግና ፖለቲካ ወለድ ፍርድ በማፍረድ ፍትህ በአፍ ጢሙ እንዲደፋ ከማድረግ የከፋ የፖለቲካ ቁማር ይኖር ይሆን?

 

 

ሸፍጠኛና ሴረኛ የለውጥ አራማጆችን “መቶ በመቶ አምናቸዋለሁ” ከሚለው ጀምሮ ቆሜለታለሁ የሚለውን ህዝብ ጨርሶ በመርሳት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ዕደሜ እንደ ማቱሳላ ያረዝምለት ዘንድ እስከሚለምነው ተቀዋሚ ነኝ ባይ በሚተራመስበት የፖለቲካ አውድ ውስጥ ከህዝብ፣በህዝብና ለህዝብ የሆነ የመድብለ ፓርቲ ፖለቲካ የቅዠት እንጅ እንዴት የእውን ይሆናል?

 

 

መከረኛው የአገሬ ህዝብ ቤተ መንግሥት ግቢን የማስዋብ ሽር ጉድን ፣ ችግኝ የመትከል ዘመቻን፣ አብዛኛዎቹ ኗሪወቿ መሠረታዊ ፍላጎታቸውን ማሸነፍ የተሳናቸው የሆኑባትን አዲስ አበባ ገፅታ የማስዋብ ሽር ጉድን እና እዚያና እዚህ የሚታዩ ስሜት ኮርኳሪ ክስተቶችን ሲያይ የእውነት ለውጥ መጣ መስሎት እልልል! ብሎ ሳይጨርስ ማቆሚያ የሌለው የመከራና የውርደት እንባ እንዲያነባ እየተደረገ መሆኑን ለማስተባበል መሞከር የለየለት የፖለቲካ ቁማር ጨዋታ ካልሆነ ሌላ ምን ይሆናል ? የቱሪዝምና የፓርክ መሥሪያ ቤትና ባለሞያ በአገር የጠፋ ይመስል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቸኛ ተዋናይ (ተራኪ) የሆነበት ፕሮጀክት በፊልም መልክ ተዘጋጅቶ ለህዝብ እይታ መብቃቱን በደምሳሳው (በደፈናው) የሚያጣጥል ኢትዮጵያዊ ባይኖርም የአገራችን ፖለቲካ የቅድሚያ ትኩረት የሚባል ነገር በማያቁ ፣ ቢያውቁም ደንታ በሌላቸውና በሁሉም ጉዳይ ውስጥ እየገቡ ካላንቦጫረቁና የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ ካላስመዘገቡ ሥራ የሠሩ ከማይመስላቸው ፖለቲከኞች ክፉ አዙሪት አለመውጣቱን እንዴት ማስተባበል ይቻላል ? ከዚህ የበለጠ አስቸጋሪ በሆኑንና ጊዜ በማይሰጡ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ከማተኮር ይልቅ ለሩብ ምእተ ዓመት አደንቁረው ሲገዙት በኖሩትና አሁንም በተሃድሶ ስም በሚገዙት ህዝብ ላይ የሥልጣንና የግል ዝና ፍቅር ጥማትን (narcissit political ambition and self-agrrandizemet) የማስጠበቅና አይገሰሴ የማድረግ የፖለቲካ ጨዋታ የት ያደርሳል?

 

በእውነት ከተነጋገርን እንኳን የቤተ መንግሥትንና የከተማ ፓርክን መላ ኢትዮጵያን ምድረ ገነት ማድረግ የሚገባቸውና ማድረግም የሚችሉ ወጣቶች በእኩይና ጨካኝ በፖለቲከኞች አነሳሽነት ወገናቸውን አርደው በሬሳ ላይ የሚሳለቁባትን ፧ በገዥው ቡድን ውስጥና ከገዥው ቡድን ውጭ የሚገኙ እኩይ የጎሳ/የቋንቋ ደምና አጥንት ስሌት ፖለቲካ ልክፍተኞች በእነርሱ ጥቅምና ፍላጎት ተፅዕኖ ሥር የማትገዛ አገር ፍርክስክሷ ይውጣ በሚል ያዙንና ልቀቁን የሚሉባትን ፣ ከራሳቸው አልፎ ለሌላ ይተርፉ የነበሩና ከሞት የተረፉ አያሌ ወገኖች ከነቤተሰቦቻቸው በየቤተ እምነቱና በየጎዳናው ምፅዋዕት የሚጠይቁባትን፣ ድህነትን የሚቀርፍላቸው ባያገኙም ከድህነት ጋር እየታገሉ አድገውና ተምረው አገራቸው ኢትዮጵያን እውነተኛ አገረ ሰላምና አገረ ገነት ማድረግ የሚችሉ እጅግ አያሌ ቁጥር ያላቸው ህፃናት ወላጆቻው በማንነታቸው በመፈናቀላቸውና ሃብትና ንብረታቸው በመውደሙ ምክንያት መግለፅ በሚያስቸግር ሰቆቃ ውስጥ እንዴኖሩ የተገደዱባትን ፣ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወገኖች በድርቅና በሌላ የተፈጥሮ አደጋ ምክንያት የህይወት ማቆያ ምፅዋዕት የሚማፀኑባትን አገር እመራለሁ የሚል ጠቅላይ ሚኒስትር በአገር ሰው

 

 

የጠፋ ይመስል የፓርክ ፕሮጀክት ፊልም አዘጋጅና ተራኪ በመሆን የፖለቲካ ሰብእና ግንባታ ሲተውን ማየት ላለንበት ሁለንተናዊ ፣ግዙፍና መሪር እውነት እንዴት ይመጥናል?

 

በሸፍጥና በሴራ ፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ ጥርሳቸውን ነቅለው ያደጉ እና አሁንም በዚያው የልክፍት አዙሪት ውስጥ ሆነው መሬት ላይ ካለው መሪር ሃቅ ጋር ጨርሶ በማይገናኝ አደንቋሪ ዲስኩራቸው ወይም ስብከታቸው የሚያደነቁሩን የለውጥ አራማጅ ተብየ ደናቁርትና ግፈኛ ኦህዴዳዊያን/ብልፅግናዊያን በምን አይነት የፖለቲካና የሞራል ሰብእናቸው ነው የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አሸጋጋሪዎች የሚሆኑት?

 

ለሩብ ምእተ ዓመት እንደ ደመ ነፍሱ እንስሳ (አጋሰስ) እየጫነ እና ሲያስፈልገው ደግሞ ጠመንጃ አሸክሞ ነፍሰ ገዳይ እያደረገ ወሰን በሌለው የበላየነቱ ሥር ታማኝ አገልጋይ አድርጓቸው የኖረውን ህወሃትን በማስወገድ በኦህዴድ/ኦዴፓ የበላይነት የሚመራና በይዘቱ የኢህአዴግ ግልባጭ (ካርቦን ኮፒ) የሆነን “ብልፅግናን አምጠን ወልደናልና የምሥራች ብላችሁ ተቀበሉን ፥ተፎካካሪወቻችም ለምለም የወይራ ዝንጣፊና ሌላም ስጦታ በመያዝ ‘አማን በአማን’ እያላችሁ ተደመሩ (ተለጠፉ)” የሚል ርካሽ ፕሮፓጋንዳ ወደ የትና እስከ የት ይወስደናል?

 

ካየነውና እያየነው ካለነው ማቆሚያ ያልተበጀለትና እጅግ አሰቃቂ ድርጊት ጀምሮ በየትኛውም ጊዜና ሥፍራ ኮሽ ባለ ቁጥር “ሃላፊነቱና ተጠያቂነቱ የህወትና መሰሎቹ ነው” እያሉ የማላዘን ወይም ስሜት አልሰጥ እስኪል ድረስ የማመንዠክ ፖለቲካ እንዴት የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ማሸጋገሪያ ስትራቴጅና ሥልት ሊሆን ይችላል?

 

ሥልጣን ለምንና እስከ ምን ድራስ? በማን ፈቃድና ስምምነት (ይሁንታ) ? የፓርቲ ፖለቲካ ምንድን ነው ? የመድብለ ፓርቲ ፖለቲካስ? በእኛ አገር እውን

 

መድበለ ፓርቲ ፖለቲካን የሚያስተናግድ የፖለቲካ ሥርዓት ኖሮ ያውቃል? አሁንስ አለ ወይ? የዚህን መልስ ለማወቅ የቅን ፣ የአስተዋይ ፣የመልካም ዜግነት እና የሚዛናዊ ህሊና ባለቤት ከመሆን በላይ ልዩ መረጃ የማግኘት ምርምርንና እውቀትን ይጠይቀን ይሆን ?

 

የጋራ ቃል ኪዳን ሰነድ (ህገ መንግሥት) ተብየው ምን ይላል? በምን ዓይነት የይሁንታ ሂደት አልፎ የህጎች ሁሉ የበላይ ህግ ሊሆን ቻለ ? እንዴትስ ሥራ ላይ ዋለ? ከግፍ የፖለቲካ ጨዋታ ሽፋን ሸጭነት በማያልፉ የዴሞክራሲያዊና የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌዎች ታጅቦ የተደረሰን (የተፃፈን) ፣ የተቀረፀንና ሥራ ላይ የዋለን ትውልድ

 

 

ገዳይ ህገ መንግሥት ጨርሶ ለማስወገድና በአዲስ ለመተካት ወይም መርዘኛ ክፍሎቹን ከነመርዛቸው ነቅሎ መሠረታዊ ማሻሻያ ለማድረግ ለምን አልቻልንም ወይም ለምን ወኔው ከዳን?

 

ይህንን ወይም ያንን ፖለቲካዊ እርምጃ ብንወስድ እገሌ የሚባለው ቡድን ይረብሸናል ወይም አገር ላፍርስ ይላል” በሚል እጅግ አሳፋሪ ወይም ወራዳ የፖለቲካ ሰብእና እና ቁመና እንዴት አገር ይመራል? አገርስ እንዴት ከመፍረስ ይድናል? ንፁሃን ወገኖችን በጭካኔ ገድሎ መቀበሪያ በማሳጣት ለውሻና ለዱር አራዊት ከማስበላት የከፋ አገር የማፍረስ ወንጀል አለ ወይ?

 

 

ግዙፍና መሪር ዋጋ የተከፈለበትን የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ ተጋድሎን ለሸፍጠኛ፣ ለሴረኛና በይቅር በሉን የአዞ እንባ ህዝብን ላታለሉ ወይም ለሚያታልሉ የኢህአዴግ (የብልፅግ) ፖለቲከኞች እና ግብረ በላወቻቸው አሳልፈን በመስጠታችን አይደለም እንዴ ለዘመናት የመጣንበት የመከራና የውርደት ፖለቲካ ታሪክ በአስከፊ አኳኋን እራሱን በመድገም ላይ የሚገኘው?

 

ከህዝብ፣ በህዝብና ለህዝብ ያልተሠራ ህገ መንግሥት የዜጎችን መብት ሲደፈጥጥ የሚዳኘው (በህግ አምላክ የሚባለው) በምን አይነት የፍትህ ተቋም (አካል) ነው? የጎሳ/የቋንቋ አጥንትና ደም ስሌት ፖለቲካ ሥርዓት ገዥ ቡድኖችና ፖለቲከኞች ወደ መቃብር ሳንወርድ ህገ መንግሥታችን ፈፅሞ አይነካም” በሚል ያዙንና ልቀቁን የሚሉት ለምንድን ነው? በማይናወጥ ዴሞክራሲያዊ መርህና የተግባር ተጋድሎ መሠረት ላይ በመቆም እነዚህን የእኩይ ፖለቲካ ልክፍተኞች ለመገዳደር የሚያስችል የመድብለ ፓርቲ ፖለቲካ ሥርዓት ባለመኖሩ ምክንያት አይደለም እንዴ ?

 

የዜግነት እውነተኛ ትርጉሙና እሴቱ ምንድን ነው? ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን ዜጋን በዜግነቱና በሰብአዊ ፍጡርነቱ ሳይሆን ከተወለደበት ጎሳ/ዘውግ ማንነት ጋር ብቻ እያጣበቀና እየጨፈለቀ የዘለቀውና አሁንም ለወሬ በማይመች አኳኋን ከሰብአዊ ፍጡር በታች እያዋለን ያለው እኩይ የፖለቲካ ሥርዓት በዜግነት ላይ የተመሠረተ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እውን ለማድረግ ከሚያስችል የመድብለ ፓርቲ ፖለቲካ ጋር ምን ጉዳይ አለው?

 

የአገርን ሃብትና ንብረት የሚቆጣጠረው ማነው? የአገር ሃብትና ንብረት የሚከፋፈለው (ሥራ ላይ የሚውለው) በምን አይነት ዘዴ ወይም መስፈርት ነው? ይህስ የሚወሰነው በማንና እንዴት ነው? በውሳኔ አሰጣጥና አፈፃፀም ላይ ማን ምን

 

 

አይነት ሚና አለው? በዚህ ረገድ ለሦስት አሥርተ ዓመታት የሆነው መሪር ሃቅ ምን ነበር? አሁንስ ከተረኝነት ያለፈ ምን ልዩነት አለ? በአንድ በኩል የነፃነትና የፍትህ ያለህ እያልን በሌላ በኩል ግን ይህን የኖርንበትንና አሁንም እየኖርንበት ያለውን መሪር ሃቅ በመሸሽ የመጫወቻ ሜዳውን ለሸፍጠኛና ሴረኛ ገዥ ቡድኖችና ፖለቲከኞች በማስረከብ የግፍና የመከራ ሥርዓት ጨካኝ በትር ወይም ጅራፍ ባረፈብን ቁጥር ማማረርና መላቀስ ምን ፋይዳ ይኖረዋል?

 

በአንድ በተወሰነ የፖለቲካ የአሠራር ሂደት ውስጥ ማን ምን ያገኛል ? ማን ምን ያጣል? እንደ ጉልቻ እየተለዋወጡ መንበረ ሥልጣን ላይ ከሚወጡ እኩይ የጎሳ/የቋንቋ ደምና አጥንት ስሌት ፖለቲካ ገዥ ቡድኖችና ግብረ በላወቻቸው በስተቀር ማን ተጠቃሚ ሆኖ ያውቃል ? አደንቁረውና የመከራ ቀንበር አሸክመው ሲገዙት ከኖሩትና አሁንም በዚያው ክፉ አዙሪታቸው ሰንገው የያዙት መከረኛ የአገሬ ህዝብ አገርን ጨምሮ የሁሉም ነገር ደሃ ቢሆን ምን ይገርማል ?

 

የህግ የበላይነትና ፍትህ ምንድን ነው? ለምንና ለማን ? ለመሆኑ በአሁኑ ወቅት እየታዘብን ካለነው በፍትህና በህግ የበላይነት ስም ከሚተወነው ርካሽ የፖለቲካ ተውኔት በላይ ምን ዓይነት መረጃና ማስረጃ ነው የምንፈልገው? ታዲያ ይህ ለብዙ ዓመታት በሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ፣ ቀጥሎም በአቶ ሃይለ ማርያም ደሳለኝ ላይ ባደረው የአቶ መለስ የሙት መንፈስ አማካኝነት እና አሁን ደግሞ ከሸፍጥ ዲስኩር በስተቀር በዚያው ክፉ ሌጋሲ (ቅብብሎሽ) በቀጠለው የኢህአዴግ (የብልፅግና) መሪና ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መካከል ምን አይነት መሠረታዊ ልዩነት አለ? ከገዥ ቡድኖችና ከጠቅም ተጋሪ ባለሃብቶቻቸው ፣በአሽቃባጭነት ጭራቸውን ከሚቆሉ ምሁራን ተብየዎች እና እንደ ደመነ ፍስ እንስሳ ሆዳቸው ከሞላ “እናቴን ያገባ ሁሉ አባቴ ነው” ከሚሉ ፖለቲከኞች በስተቀር ይህንን መሪር ሃቅ ለማስተባበል ወይም ለመካድ የሚሞክር ወገን ይኖር ይሆን ?

 

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና ጓዶቹ ጥርሳቸውን ነቅለው ያደጉበትንና በንፁሃን ዜጎች የቁም ሰቆቃና ደም የተጨማለቀውን ሥርዓተ ህወሃት/ ኢህአዴግ በኦህዴድ/ብልፅግና የበላይነት ተክተው አጋር ብለው የሚጠሯቸውን የጎሳ /የቋንቋ አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ማንነት ድርጅቶችን አጃቢ አድርገው እና ለዓመታት ታገልንለት የሚሉትን የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግርና ምሥረታ ዓላማ ገና የለውጥ ተብየው ዶሮ ሳይጮህ በአፍ ጢሙ ደፍተው በቤተ መንግሥት ፖለቲካ እልፍኝ አስከልካይነት እጥፍና ዘርጋ የሚሉትን (ኢ.ዜ.ማን የመሰሉ) ተፎካካሪ

 

 

ተብየዎች በፍፁም ታማኝነት ባሰለፉበት መሪር እውነታ ውስጥ ስለ መድብለ ፓርቲ የፖለቲካ ሥርዓት (multi-party political system) የምንሰማው ዲስኩር ከርካሽ የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳነት በላይ ምን ትርጉም አለው?

 

ገዥ ቡድኖች እና የእራሳቸውን የፖለቲካ መርህ፣ ዓላማና ግብ በአፍ ጢሙ ደፍተው ተደማሪ (ተለጣፊ) የሆኑ ተፎካካሪ ተብየ ፖለቲከኞች በግልፅ የሚታየውን ሸፍጠኛና እኩይ የፖለቲካ ተውኔት የእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ መድብለ ፓርቲ ገፅታ ለማላበስ የሚያደርጉትን አይን ያወጣ አካሄድ ብዙ ርቀት ከሄድን በኋላ መመለሻው ስለሚቸግር በወቅቱ ነውር ነው የማለትን አስፈላጊነት የማይቀበል ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ ይኖር ይሆን?

 

በመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ዴሞክራሲያዊት አገርን እውን ለማድረግ ከምር የምንፈልግ ዜጎች ከሆን አካፋን አካፋ ብለን ለመጥራትና ለመሞገት ለምንና እንዴት እንሽኮረመማለን ወይም ወኔው ይከዳናል? በእራሳችን የፖለቲካና የሞራል ውድቀት ምክንያት ለዘመናት ስለ ዘለቅንበትና አሁንም በአስከፊ አኳኋን እየቀጠለ ስላለው ሁለንተናዊ ቀውስ በግልፅና በቀጥታ እየተነጋገርን ተገቢውን ሥራ በተገቢው ጊዜ ከመሥራት ይልቅ “ችግርን ያባብሳል” በሚል እጅግ የኮሰመነ (የወረደ) ሰበብ መደርደር መከራና ውርደትን ከማራዘም በስተቀር ሌላ ምን ትርጉም ይኖረዋል ?

 

 

ህወሃት/ኢህአዴግ በጎሳ/በቋንቋ አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ማንነት ላይ ተመሥርቶ ለሩብ ምእተ ዓመት የዘለቀበትን የሰቆቃና የውርደት አገዛዝ በስመ ተሃድሶ ተረኞች ነን በሚሉ ኦህዴዶች የበላይነት እና ከታዛዥነት መላቀቅ በተሳናቸው ብአዴናዊያንና ደህዴናዊያን አጃቢነት ብልፅግና የሚል የክርስትና ሳይሆን የርክሰት ስም በመለጠፍ በህዝብ መከራ የመሳለቅ ፖለቲካ ጨዋታ መቆም የለበትም እንዴ?

 

ስለ እውነት በእውነት ከተነጋገርን ግልፅና ርካሽ የሆነውን የኦህዴድ/ብልፅግና የፖለቲካ ጨዋታ ማየትና መገንዘብ የሚችል ህሊና የሚጎለው የአገሬ ሰው ካለ ወይ የተውኔቱ አካልና ታዳሚ ወይም የሸፍጠኞች አደንቋሪ ፕሮፓጋንዳ ሰለባ ወይም ከተውኔቱ ርካሽ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ጭራውን የሚቆላ ተፎካካሪ ፖለቲከኛ ተብየ ወይም “ጠቅላይ ሚኒስትሩና ጓዶቹ ከሌሉ አገርም አትኖርም” የሚል ወራዳ (ሃፍረተ ቢስ) ትርክተኛ ከመሆን ውጭ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል?

 

እንዲህ አይነቱ ላለንበት ዘመንና ፈታኝ ሁኔታ ጨርሶ የማይመጥን ብቻ ሳይሆን እንደግለሰብ ዜጋም ሆነ እንደ አገር ቁልቁል ይዞን እየወረደ ያስቸገረንን አስተሳሰብ

 

 

ነገ ሳይሆን ከዛሬ ጀምሮ ወደ ትክክለኛው መዳረሻ የሚወስደውን አቅጣጫ ማስያዝ አይኖርብንም እንዴ?

 

ታዲያ ይህ እውን መሆን ካለበት ከአስከፊ ፖለቲካ ወለድ ወንጀሉ ጋር በሸፍጥ ተሃድሶ ተቀባብቶ እንዲቀጥል የተደረገው ሥርዓት በመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ አግባብ ተወግዶ ባለ ድርሻ ከሆኑ የፖለቲካ ሃይሎችና ዜጎች ጋር በሚደረግ ምክክር ፣ የጋራ እቅድ ነዳፊነትና እቅድ ፈፃሚነት ወደ ትክክለኛው የሽግግር መስመር መግባትን ግድ አይልም እንዴ? እንዲያ ከሆነ አይደል እንዴ ስለ የሸፍጥና የሴራ መድብለ ፓርቲ ፖለቲካ ሳይሆን ስለ እውነተኛው መድብለ ፓርቲ ፖለቲካ በኩራት መነጋገር የምንችለው ?

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

ከነፃነት ዘገዬ የአራት ኪሎው ኦነግ ሸኔ ከቁጥር ጋር እንደተጣላ ዕድሜውን አገባደደ፡፡ ኦነግ/ኦህዲድ ዛሬም ሆነ ዱሮ፣ በቤተ መንግሥትም ይሁን በጫካ ቁጥር ላይ ያለው አቋም ምን ጊዜም ያስደንቀኛል፡፡ ደግሞም እየባሰባቸው እንጂ ሲቀንሱ አይታዩም፡፡ ጥቂት

80 ቢሊዮን ብር ስንት ብር ነው?

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

Go toTop