ፕሮፌሰር ጌታቸው መታፈሪያ
መግቢያ
የአባይ ውሃ ሁኔታ በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል ለረዥም ዘመናት መነጋገሪያ ነበር። ለምሳሌ የጥንት የግብፅ መሪዎች ግብፅ ውስጥ በሚኖሩ ግብፃውያን ክርስቲያኖች ላይ ጫና ሲፈጥሩ ክርስቲያኖችን በመደገፍ የኢትዮጵያ ነገሥታት የአባይን ውሃ እናቆምባችኋለን በማለት ያሰፈራሩበት ጊዜ ነበር። እንዲሁም አሌክሳደሪያ የሚገኘው የቅዱስ ማርቆስ መንበረ ፓትሪያሪክ እንደ ኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ከ፬ኛው ክፍለ ዘመን እስከ ዓ.ም (1954) ለኢትዮጵያ የሚላክ ፓትሪያሪክ ካስተጓጎሉና ጫና ለመፍጠር ከሞከሩ አሁንም
የኢትዮጵያ መሪዎች ወደ ግብፅ የሚወርደውን የአባይ ውሃ እንደማስፈራሪያ ይጠቀሙ ነበር።
ግብፅም ከቅርብ ጊዜያት በኋላ የጦር መሣሪያ በበቂ ሁኔታ አለኝ በማለት ኢትዮጵያን ታስፈራራ ጀመር። የአባይን ምንጭም ለመያዝ እኤአ በ1870ዎቹ ውስጥ ሁለት ጊዜ በጉንደትና በጉራዕ ጦርነት ከኢትዮጵያ ጋር ገጥማ በአፄ ዮሐንስ ድል ተመታለች። በተለይ በሁለተኛው ጦርነት ላይ ጦሯን በማጠናከር ወደ ሃያሺ ወታደርና በተለይም በአሜሪካ እኤአ በ1861 – 1868 ዓ.ም የእርስ በርስ ጦርነት የጦር ልምድ ያካበቱትን የአሜሪካን ቅጥር ወታደሮችን ብታካትትም የአፄ ዮሐንስ ጦር የግብፅን ጦር ደምስሶ ነበር። አፄ ዮሐንስም ከግብፆች በስድስት ሳጥኖች የተሞላ ወርቅ ለመማረክ ቻሉ። በወርቁም ስለታቸውን በማድረስ በኢየሩሳሌም የኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን አስጀምረው አፄ ምኒሊክ ቦታውን አስፍተው ህንፃውን በአማረ ሁኔታ አስጨረሱት። ለመነኮሳቱና ለካህናቱ ቀለብና ልብስ እንዳይጓደልባቸው ገንዘብ በባንክ አስቀመጡላቸው።
አባይን የመገደብ ዕቅድ
ሁኔታዎች እየተለዋወጡ ስለ መጡ አፄ ኃይለሥላሴ እንደ አፄ ምኒሊክ አገሪቷን በሁሉም መስክ ዘመናዊ ለማድረግ የተነሱ መሪ ነበሩ። ከሥራዎቻቸውም ንድፍ አንዱ የአባይን ውሃ ገድቦ ለኢትዮጵያ ዕድገትና ልማት ማዋል ነበር። ስለዚህ የአውሮፓ አገሮችን ስለማያምኑ፣ ኢትዮጵያም በእነሱ ቅኝ ግዛቶች የተከበበች ስለነበርና በተጨማሪም አውሮፓዎቹ ኢትዮጵያን ለመቆጣጠር ሁሉም ይሻኮቱ ስለነበር ፊታቸውን ወደ አሜሪካ አቀኑ። አውሮፓዎቹም በሀገሪቱ ውስጥ የሚካሄዱትን ሁሉ በቅርብ ይከታተሉ ነበር። ከዚህ ሁሉ ደባ ገለልተኛ የሆነችና ከ1903 ዓም ጀምሮ የወዳጅነትና የንግድ ውል (Treaty of Amity and Commerce) ተዋውላ ግንኙነቷም እየጠነከረ የመጣችውን አሜሪካን አባይ ላይ ግድብ እንድትሠራ በኒውዮርክ ከተማ የሚገኘውን ኩባንያ (J.G. White Engineering Corporation) ጋር ተዋዋለች። የውሉ ውይይት እኤአ በ1927 ዓ.ም ተጀምሮ በሁለተኛው ዓመት ከኩባንያው ፕሬዝደንት ጋኖ ዱን (Gano Dunn) ጋር አዲስ አበባ ውስጥ ውሉን ተፈራረሙ። በዚያን ጊዜ የግድቡ ማሠሪያ ሃያ ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ነበር (Getachew Metaferia, Ethiopia and the United States: History, Diplomacy and Analysis)።
አሜሪካኖቹ ከኢትዮጵያ ጋር መሥራትን የፈለጉትም አገሪቷ በብዙ መንገድ ልታድግና በአፍሪካም ታላቅ እንደምትሆን አምነው ለወደፊት ሥራቸው በር ከፋች አድርገው በግድቡ ሥራ ላይ ተስፋ ጥለው ነበር። ሦስቱ የአጎራባች አገሮች ቅኝ ግዛት ገዢዎች (እንግሊዝ፣ ኢጣሊያና ፈረንሳይ)ኢትዮጵያ ከአሜሪካን ጋር መወዳጀቷን ስለማይፈልጉ የውሉን ይዘት ለማወቅና እንከን ለመፍጠር ብዙ ጥረው ነበር። በተለይ እንግሊዝ ሱዳን ውስጥ ያላትና ብዙ ጥሬ ገንዘብ የሚያስገባላት የገዚራ የጥጥ ፋብሪካ ውሃ እንዳይቀንስባት ትሰጋ ነበር። የጥጥ እርሻውም በዓለም ላይ ትልቁ የመስኖ እርሻ ነበር። በተለይ የእርሻው ሕይወት ውሃ ብቻ ሳይሆን አባይ የሚቆልለው ደለል ነበር። ይህ የጥጥ ሽያጭ ጥሬ ገንዘብ ብቻ ሳይሆን የሚያስገባላት እንግሊዝ አገር የሚገኘው ከተማ የማንቼስተር የልብስ ፋብሪካ ህልውናም የተመሠረተው በዚህ ጥጥ ላይ ነበር። ከተማዋም “የጥጥ ከተማ” ትባል ነበር። ስለዚህ እንግሊዝ የአባይ ውሃን ለመቆጣጠር አጥብቃ ትፈልግ ነበር። ግብፆችም ከእንግሊዝ በ1952 ዓ.ም ነጻ ከወጡ በኋላም የእንግሊዝን ህልምና ቅዠት ወርሰው ቀሩ።
የዚህ የአባይ ግንባታ በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት እንዳይሳካ የሆነው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት መነሳት ምክንያት ነበር። እንደሚታወቀው በጊዜው የነበረው የዓለም መንግሥታት ማህበር (League of Nations) አባል የሆነችውን ኢትዮጵያን የኢጣሊያኑ የፋሺስት መሪ ቤኒቶ ሙሶሊኒ የአድዋን ጦርነት ሽንፈት ህፍረት ለመወጣት ጦርነት አወጀባት። አፄ ኃይለሥላሴም ”የአባይን ግድብ ወደፊት ልጆቻችን ይሠሩታል“ በማለት ትኩረታቸውን ወደ አገራቸው ህልውና ጥበቃ ላይ አዞሩ። ኢትዮጵያም በጦርነት ለአምስት ዓመታት ስትታመስ ቆየች።
በመጨረሻም በአርበኞቻቸን ብርታትና በእንግሊዝም ዕርዳታ ኢትዮጵያ ነፃነቷን ተቀዳጀች። እነሆ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኢትዮጵያ የግፍ ጦርነት ተጀምሮ አሁንም በኢትዮጵያ ነፃነት ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተገባደደ ማለት ይቻላል።
ከጦርነቱ በኋላ የኢትዮጵያ መሪዎች ከአፄ ኃይለሥላሴ ጀምሮ፣ ግብፆች በተቀነባበረ ሁኔታ ውሃው እንዳይገደብና አገሪቷ ከድህነት አረንቋ እንዳትላቀቅ ከአገራትም ሆነ ከዓለም አቀፍ የብድር ተቋማት ገንዘብ እንዳታገኝ ደባ እየሠሩ ኖረዋል። እኤአ በ1978 ዓ.ም በግብፅና በእስራኤል መካከል የተፈራረሙት የካምፕ ዴቪድ ውል ሁኔታውንም የበለጠ የተወሳሰበ አድርጎታል።አሜሪካም አረቦች እስራኤል ላይ የለሰለሰ አቋም እንዲወስዱ ግብፅን ትጠቀም ነበር። ስለዚህም ምንም እንኳን የውሃው ባለቤት ኢትዮጵያ ብትሆንም ግድብ መሥራቱ ላይ በአካባቢው ፖለቲካዊ (geopolitics) ሁኔታና በዓለም አቀፍ ግንኙነት (international relations) ምክንያት የተወሳሰበ አድርጎታል።
ኢትዮጵያ ከዚህ አጣብቂኝ የወጣችው በመዳፈር ከኤኮኖሚ ኋላ ቀርነት ለመውጣት፤ የኢንዱስትሪ ተቋማትን በሰፊው ለመገንባት፤ አስከፊ ድህነትን ለመቀነስ፤ ለማገዶ ተብሎ የሚጨፈጨፈውን ደን በመታደግና የአየር ንብረትን ለመንከባከብ ፤ ለእርሻም ዝናብን አንጋጦ ከመጠበቅ ለመዳን፤ በተለይ የሴቶችን ልፋትና ስቃይ ለመቀነስና የመብራት አቅርቦትን በሀገሪቱ ለማዳረስ የአባይን ወንዝ ገድቦ ለአገር ዕድገት ለማዋል ሥራውን በድፍረት ጀመረች። ለዚህም የመሪዎች ቆራጥ አቋምና የህዝቡ ንቁ ተሳትፎ ወሳኝ ነበረ። እንሆ አሁን የእግዚአብሔርም ፈቃድ ሆኖ ታሪካዊው የውሃ ሙሌት ተጀምሯል።
የግድቡ የውሃ ሙሌትና የግብፅ የወደፊት አቋም በተመለከተ
ግብፅ ሁኔታው ከእጇ እንዳመለጠና ኢትዮጵያም የውሃው ባለቤት መሆኗን እያስመሰከረች መሆኑን በመረዳት ከእንግዲህ ወዲያ ግብፅ የሚከተሉትን ብታደርግ ለአካባቢው ሁሉ ሰላምና መረጋጋት ታመጣለች ብዬ አስባለሁ።
፩ኛ)ወደደችም ጠላችም ግብፅ የአካባቢዋ መልከዓ ምድር እስረኛ ነች። በአካባቢው ፖለቲካ፣ በመልክዓ ምድር አቀማመጧ ምክንያት ከአካባቢዋ አገሮች ጋር ሁሉ በጥሩ የፖለቲካ ሂደት፣ በመልካም ጉርብትና፣ የኤኮኖሚና የህብረተሰብ ትሥሥር ፈጥራ መኖር ይጠበቅባታል። አገራት ግብፅን ጨምሮ፣ አንድ ጸሐፊ በቅርቡ እንደዘገበው፣ ወደዱም ጠሉ የአካባቢያቸው መልከዓ ምድር እስረኞች ናቸው (Tim Marshall, Prisoners of Geography)። እንግዲህ ከክርስቶስ ልደት በፊት የግሪክ የታሪክ ሰው ሄሮዶትስ እንደጻፈው “ግብፅ አባይ ነች እንዲሁም አባይ ግብፅ ነች“ ያለው አሁን የአባይ መፍለቂያና መሠረት እንዲሁም የአፍሪካ ”የውሃ ማማ“ ከሆነች ከእማማ ኢትዮጵያ ጋር በትምክህተኝነት ሳይሆን የሚገባትን የመልካም ጉርብትና ሚና መጫወት አለባት። እንደ ጎረቤትም እጣ ፈንታችን እንደተቆራኘ መገንዘብ አስፈላጊ ነው። አንዱ አገር በሌላኛው የጎረቤት አገር ኪሣራ ትርፍ እያስቆጠረ መኖር የለበትም (zero – sum game)።
ስለዚህም ግብፅ የበላይነት ስሜቷን አስተንፍሳ የጋራ ጥቅም ማራመድ ይጠበቅባታል። ነገርግን የአሁኑም ሆኑ የወደፊት የኢትዮጵያ መሪዎች ዓይናቸውን ከግብፅ ላይ ማንሳት የለባቸውም። በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ግብፅ የአባይን ምንጭ ለመቆጣጠር ያላትን የቆየ ፍላጎቷን ለሟሟላት ከማሴር ወደ ኋላ አትልም። አሁንም ቢሆን ሁኔታው ያለቀለትና የተደላደለ አይደለም። የጀርመኖች አስተምኽሮ እንደሚለው የእውነታ ፖለቲካ (realpolitik) መሠረት በማድረግ ሁኔታዎችን በሰላምና ብልህነት ካለው ተጨባጭ ሁኔታ ተነስተን ፖሊሲአችንን መቅረጽ አስፈላጊ ነው። ስለዚህ አንሞኝ፣ አንዘናጋ፣ ቆቅ እንሁን፣ የዛሬ የቅርብ ወዳጅም የነገ ጠላት ሊሆን ይችላልና ።
፪ኛ)ምንም እንኳን በአንድ ወቅት የግብፅ መሪ ፕሬዚደንት ጋማል አብደል ናስር የግብፅ አብዮት አስመልክቶ በ1955 ዓ.ም እንዳጻፈው ግብፅ በአፍሪካዊነቷ፣ በመካከለኛው ምሥራቃዊነቷ (ዓረባዊነቷ)፣ በእስላማዊነቷ (concentric circles) ውስጥ ማንነቷ (identity) ተገላጭ ነው ቢልም በአፍሪካ አህጉር ውስጥ የምትገኝ በመሆኗ አፍሪካዊነቷን በደንብ አጥብቃ አፍሪካውያንን በእኩል ዓይን ማየት ይጠበቅባታል። በአባይ ላይ ያላትም ችግር ኢትዮጵያን ከመናቅና የአባይ ባለቤትነቷን ካለመቀበል የመነጨ እብሪተኝነት ነው። የአባይ ግድብ ውይይት “የአፍሪካውያን ችግር በአፍሪካ መፍታት” የሚለውን መርህ በተመለከተ በአፍሪካኖች ላይ እምነት አጥታ ይሆናል የአፍሪካ ማኅበርን ወደ ጎን ብላ በተለይ የመወላወል ልምድ ያለውን ዶናልድ ትራንፕን ለአደራዳሪነት የሙጢኝ ያለችው። ሰውዬው በተለይ ለአፍሪካና ለአፍሪካኖች ጥሩ ዕይታ የለውም። አፍሪካዊቷ ግብፅ ይህን ማመዛዘን አለመቻሏ (አለመፈለጓ) የጥያቄ ምልክት እንድናኖርባት ይጋብዛል።
፫ኛ)የግብፅ መሪዎች የፖለቲካ ፍልስፍናቸው በጣሊያናዊው ጸሐፊ ኒኮሎ ማካቬሊና በእንግሊዛዊው ቶማስ ሆብስ በተባሉት የጥንት የፖለቲካ ፈላስፋዎች (classical realist) ላይ የተመሠረተ ይመስላል። ይህም ፍልስፍና በሥራ ሲገለጥ እራስ ወዳድነት፣ በኃይል የመተማመን፣ እራስን ከፍ ከፍ ማድረግ፣ ለትንሹም ለትልቁም፣ በተለይ ጎረቤት አገሮች ላይ፣ ጦር የመስበቅና የማስፈራራት ፀባይ ነው። እንግዲህ የግብፅ መሪዎች የፖለቲካ ድርጊታቸው የአባይ ግድብን በተመለከተ ይህንን ያሳየናል። አሁን መድኋኒቱ በኢትዮጵያ በኩል የግብፅ ህዝብ አቃፊ የሆነ ስልታዊና አስተማሪ የሆነ ህዝባዊ ዲፕሎማሲ (public diplomacy) ማጠናከር ሲሆን የፕሬዘዳንት አልሲሲን መንግሥትም የመጨረሻው ምዕራፍ መጀመሪያ ላይ ማድረስ ይሆናል። በዚህ ረገድ በወቅቱ ፈጥነው የደረሱ፣ ዐረብኛ ተናጋሪ ልጆቿ፣ እህቶቼና ወንድሞቼ አገራዊ ግዴታቸውን እየተወጡ ነው። ለዚህም ጥንካሬ እንዲሰጣቸው ዱአ (ፀሎት) ማድረግ አለብን።
፬ኛ)የግብፅ ኢትዮጵያን የማዳከምና የንቀት ተግባሯ ከጥንት ጀምሮና በቅርቡም ጎልቶ የመጣው ኢየሩሳሌም ውስጥ በሚገኘው ጥንታዊቷ የኢትዮጵያ ይዞታ ላይ ነው። ልክ ኢትዮጵያ ውስጥ አገሪቷን ለማወክ ባንዶችን እንዳሰማራችው ሁሉ በኢየሩሳሌምም እንዲሁ ቤተ ክርስቲያኗን የሚበጠብጡና ይዞታዋም ይገባናል የሚሉ የህወሃት ካድሬዎች ቀሳውስት መስለው ሲያውኩ ቆይተዋል። ከጎናቸውም ግብፆች ተሰልፈዋል። የኢትዮጵያው ፓትሪያሪክም በእነኝህ በጥባጮች ላይ ሲኖዶስ የወሰነውን ተግባራዊ አለማድረጋቸውና ዝምታን በመምረጣቸው ምዕመናን አልተደሰቱባቸውም። ፓትሪያሪኩም በትረ ሙሴውን የሥልጣን፣ የሚዛናዊነትና የፍትህ ተምሳሌት የሆነውን ይዘውትም በአግባቡ ግዴታቸውን ሊወጡበት አልፈለጉም። እንዲሁም በወቅቱ የኢትዮጵያ ኤምባሲም ከበጥባጮቹ ጎን በመቆሙ አዝነው በኢየሩሳሌም የሚገኙት ኢትዮጵያውያን ምዕመናንና ወዳጆቻቸው፣ አንዳንድ ቤተ እስራኤላውያንን ጨምሮ፣ ታሪክና ቅርስን በማስጠበቅ ሥራ ላይ ተሰማርተዋል።
ግብፅ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ በመግባት በተለይ ለተገንጣይ ኃይሎች ሥልጠና በመስጠት፣ በማደራጀት፣ የሬዲዮ ሞገድ እንዲከፍቱ በማመቻቸት ሀገሪቱን በማተራመስ ባህር አልባና ወደብ አልባ እንድትሆን አድርጋለች። ያንንም ደባ አሁንም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሥራ ላይ እያዋለች ነው። ስለዚህም ኢትዮጵያ በግብፅ ላይ በምንም ዓይነት የጥርጣሬ ዓይኗን እንዳታነሳ የፖለቲካ ፍልስፍናውም (realism) ያስተምራል። መሬት ላይ ያለው እውነታም ይህንን ያመላክታል።
፭ኛ)በዓለም ላይ ወደፊት የሚነሱት ጦርነቶች በሞላ በተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነትና አጠቃቀም ላይ የተመሠረተ ይሆናል ሲል ሚካኤል ክሌር በመጽሐፉ ገልጾ ነበር (Resource Wars)። በተለይም ለዘመናዊ የኢንዱስትሪ እንቅስቃሴ የሚውሉትን በዋናነት ጠቅሶ ለአንድ አገርም የደህንነት መድህን (security) የሚሆኑት የተፈጥሮ ሃብቶች በተለይ የጦርነት መንስኤ ይሆናሉ ብሏል። እነኚህም የጦርነት መንስኤ የሚላቸው ጎረቤት አገሮችን ብቻ ሳይሆን የሩቅ አገሮችን ትኩረት ይስባሉ ይለናል(resourcecurse)። ዋናው ቁም ነገር በእነኚህ የተፈጥሮ ፀጋ ምክንያት ወደ ጦርነት ከመሄድ ይልቅ በዓለም አቀፍ ደረጃ የጠነከረ ሥነ ሥርዓት ተበጅቶለት የተፈጥሮ ሀብትን በመተጋገዝ እንክብካቤ ማድረግና ትብብር ወሳኝ ነው እንጂ የጦርነት እንቢልታ መንፋቱ እርባናቢስ ነው በማለት ያስረዳል። ሚካኤል ክሌር ከነዚህ ጦርነት የሚጋብ፣ ነገር ግን ለአገር ቁልፍ ዋስትና የሚሰጡ፣ ብሎ ከጠቀሳቸው ውስጥ የእኛው አባይ ይገኝበታል። አሁን ለዘመናት አንጃቦ የነበረው ጦርነት ጋብ ብሎ ኢትዮጵያ ለእድገቷ የውሃውን ሙሌት መጀመሯ እልል የሚያሰኝ ቢሆንም አሁንም ወደፊትም የግብፅን አቋም በተመለከተ መዘናጋት የለብንም።
የወደፊት ዕይታ
በመጨረሻ በመንግሥትና በህዝብ እርብርቦሽ የአባይ ግድብ ከፍጻሜ ቢደርስም አሁንም የቤት ሥራዎቻችን አላለቁም። እፎይ ለማለት ብዙ ብዙ የቤት ሥራዎች አሉብን። በቅርቡ በዝነኛው የኦሮሞ ዘፈን አቀንቃኝ በሆነው ሃጫሎ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ የብዙኃን ንጹህ ደም በግፈኞች እጅ መፍሰስና አሳዛኝ ሞት፣ የንብረት መውደም፣ የህዝብ መፈናቀል፣ የሥነ ልቦና ቀውስ መፈጠር አገራችንን በብዙ እርቀት ወደ ኋላ መልሷታል። አዝማሚያዎቹ በየአድማሱ ጥላዎቻቸውን ቢያጠሉም በአግባቡ ቀደም ተብሎ ተገቢው እርምጃዎች ባለመወሰዳቸው (proactive) ለዚህ ሁሉ ዳርጎናል። እንደ መንግሥት፣ እንደ ሃይማኖት፣ የትምህርትና ሌሎችም ተቋማት፣ እንደ ግለሰብና ማህበረሰብ ሁላችንም ወድቀናል። ከዚህ የባሰ ወደ ፊት እንዳይመጣ ሁላችንም የፖለቲካ አክሮባት ወይም መገለባበጥ ከምናደርግ ሁሉም እራሱን መፈተሽ፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታትና ከዚያም በፊትም ምን ተደርጎ፣ ምን አድርገንና ምን አድርጌ ነው የዛሬው ውድቀት የመጣብን ብሎ በመጠየቅ እንድንወያይበት መንግሥት አገራዊ አጀንዳ መቀየስ ይጠበቅበታል። እሳትን ማጥፋት ብቻ ሳይሆን የእሳቱን መንስዔ አጥንቶና ገምግሞ ወደፊትም እንዳይከሰቱ ገንቢ እርምጃዎችን መውሰድ ከሁሉም የሚጠበቅ ነው። ለተጎዱትና ንብረታቸው ለወደመ ሁሉ እንደ አባይ ግድብ ሥራ መረባረቡና ግልጽነት በተሞላበት ቀጥታ ለተጎዱት ወገኖቻችን ማከፋፈልና ማቋቋም ግዴታችን መሆን አለበት።
ሁሉም በየግሉ፣ በየማህበረሰቡና በየተቋማቱ አማካኝነት ቀደም ብሎ ተወያይቶበት አገራዊ ሸንጎ ተጠርቶ የወል ችግሮቻችን ላይ መፍትሔ ሀሳቦችን ማንሸራሸር በብዙዎች ሲጠየቅ እንደቆየው አሁን ሥራ ላይ ለማዋል መንግሥትም ሁኔታዎችን ማመቻቸቱ ወቅቱና ጊዜው ይመስለኛል። ተፈጥሮን ተቆጣጥረን ለአገር ዕድገት እናውላለን የተባለው የአባይ ግድብ ከሥራ ላይ በሚውልበት ወቅት ህዝብ ለህዝብ፤ ትውልድ ለትውልድ፤ ሃይማኖት ለሃይማኖት፤ ወዘተ የሚያገናኘውና የሚያስተሳስረው ድልድይ ግን እየፈረሰብን ነው። አገር ሸክላ ነች። አንዴ ከተሰባበረች በምንም ተዓምር እንደቀድሞ አንመልሳትም። ዮጎዝላቪያን፣ ሊቢያን፣ ኢራቅን፣ ሶሪያንና ጎረቤት አገር የመንን እንመልከት፣ እናስተውልና ልብ እንበል። ሁላችን ለመማማር፣ ሀሳብ ለመለዋወጥ፣ ለመደማመጥ፣ ለመቀራረብ፣ ለመረዳዳት፣ ለመተዛዘንና ለመግባባት ከልብ ይቅርታ ለመጠየቅና ለመቀበል ልባችን ክፍት ይሁን፣ አእምሮዓችን ዝግጁ ይሁን። ተቻችለን ካልኖርን በማንነት ላይ ያነጣጠረ ጦርነት ከተከፈተ ማቆሚያ የለውም። ፀጉር መሰንጠቅ ላይ ሊገባ ይችላል። በመሐከሉ ታሪካዊ ጠላቶቻችን እያናከሱን ያተረፉ ይመስላቸዋል። ይህ የወደፊቱ ዕይታና ትኩረታችን መሆን አለበት።
ለሁሉም ፈጣሪያችን አገራችንንና ህዝቧን ይጠብቅልን።
ሐምሌ ቀን ፪ሺ ዓ.ም
July 20, 2020