አክሎግ ቢራራ (ዶር)
ኢትዮጵያ ሃገራችን በአሁኑ ወቅት፤ ከመቸውም ጊዜ በባሰ ሁኔታና ደረጃ፤ በውስጥ ተደራጅተው፤ በውጭ ኃይል በገንዘብ፤ በቴክኒክ፤ በመረጃ፤ በመሳሪያና በሌሎች ግብአቶች ተደግፈው፤ ጠባብ ብሄርተኞች፤ ጽንፈኞች፤ ሽብርተኞች፤ ቅጥረኞች፤ ከሃዲዎችና በተደጋጋሚ የፈፀሟቸውና አሁንም በንፁሃን እናቶቻችንና እህቶቻችን ላይ በተቀነባበረ ደረጃ የሚያካሂዱቸው የተቀነባበሩሩ የዘውግ ዘውግና ኃይማኖት ተኮር እልቂቶች፤ አገራችን ኢትዮጵያንም ወደ ጥፋት አፋፍ እያሸጋገሯት ነው።
በ 10/23/2016 “የአማራው ሕዝብ ህልውና” በሚል እርእስ” በጻፍኩት ማሳሰቢብያ፤ ፀረ-ኢትዮጵያና ፀረ-ኢትዮጵያዊነት ሴረኛው ህወሓት በማኒፌስቶው በጸነሰው አቅድ መሰረት በመሰብሰብ ሽብርተኞች አደጋውን እንደሚያስፋፉትና ለሕዝቡ ብቻ ሳይሆን ለኣገራችንም ህልውና ጭምር አደጋው እንደሚያሰጋት ጠቁሜ ነበር።
ዛሬ ሰፋ አድርጌ ስመለከተው፤ የትግሉ ጎራ ግልጽ ነው። በአንድ በኩል ቀና ደፋ የሚለው፤ ግን ገና አስተሳሰቡን፤ ኃይሉንና አቅሙን፤ ከኢትዮጵያ ፍላጎት ጋር ያላመጣጠነው ክፍል፤ በሌላ በኩል ባለፉት አርባና አምሳ አመታት ዘውግንና ኃይማኖትን ለይቶ ሲንቀሳቀስ የቆየው፤ ግዙፍ የውጭ ድጋፍ ያለው፤ ጠባብ ብሄርተኛነትን፤ ዘረኛነትን፤ ጽንፈኛነትን፤ “እኛና እናንተ” ባይነትን፤ “ክልላዊነትን” ባጭሩ፤ ፀረ-ኢትዮጵያና ፀረ-ኢትዮጵያዊነትን መለያው ያደረገው የብሄርተኞች ስብስብ ተዘጋጅቶ፤ ታጥቆ የተደራጀና የተቀነባበረ እልቂትና አገራችንን የማፍረስ ስራዎች በማካሄድ ላይ ይገኛል።
የመጀመሪያውን ክፍል ለምንደግፍ አገር ወዳዶች፤ ይህን ፈተና እንደ ወሳኝ እድል አይተን ተበታትኖና ሳይናበቡ ከመጨነቅ አለማችን ወጥተን ወደ ብሄራዊ አንድነት ከመሰብሰብ ውጭ ሌላ አማራጭ እንደሌላን ለማሳሰብ እፈልጋለሁ። ይህን ካደረግን፤ ረዢምና አስደናቂ ታሪክ ያላት፤ ለጥቁር ሕዝቦች ሁሉ የነጻነት ተምሳሌት የሆነችው፤ በፍጥነት ለማደግ የመቻል እድሏ ሰፊ የሆነችው፤ የአፍሪካ መዲና ኢትዮጵያ በምንም አትጠፋም እላለሁ። ይኼ ግን በምኞች ብቻ እንደማይሳካ ካለፉት ዓመታት ታሪካችን ልንማር እንችላለን። ኢትዮጵያን ለመታደግ የምንችለው በኢትዮጵና በኢትዮጵያዊነት የምናምነው ብቻ ነን። ፈረንጆችን ባናምናቸው እመርጣለሁ። በቅርቡ የሚያስተጋቧቸውን ሁኔታዎች ብቻ መመራመሩና መመልከቱ በቂ ነው።
እንደገና ላሰምርበት የምገፈልገው፤ የአማራው ሕዝብ ህልውና ከኢትዮጵያ ህልውና ጋር የተያያዘ መሆኑን ነው።
በሁለተኛው ክፍል ያስቀመጥኳቸው ኃይሎች ከውጭ መንግሥት (መንግሥታት ጋር) ተቀናጅተው፤ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን በማያሻማ ደረጃ በማፈራረስ ላይ ይገኛሉ። ዝግጅታቸውና አቀነባበራቸው ስር-ነቀል ለውጥን ስኬታማ ለማድረግ መሆኑ በግልጽ ይታያል። “አገር ሲፈርስ ጃርት ያበቅላል” እንዲሉ፤ ሌላው ቀርቶ፤ በነጻነቷ ኮርታና ተከብራ በምትታወቀው አገራችን በኢትዮጵያ የግብፅን ባንዲራ ይዘው ሰልፍ የወጡ ግለሰቦች የሚታዩባት አገር ሆናለች። መለያችን ግብፅ ናት የሚሉ ግለሰቦች ጦርነት ቢካሄድ፤ ግብፅን ደግፈው ኢትዮጵያዊያንን ለመግደል ዝግጁ ናቸው ማለት ነው። እነዚህ ፀረ-ኢትዮጵያና ፀረ-ኢትዮጵያዊነት መመሪያቸው የሆኑት ግለሰቦች ኢትዮጵያን ጠልተው ግብፅን የሚያፈቅሩ ከሆነ የምመክራቸው ወደ ካይሮ ይሂዱና የተሻለ ኑሮ ትስጣቸው እላለሁ። ታሪካችንና እሴቶቻችን ሙሉ የክብርንና የነጻነትን እሴቶች የያዙ መሆናቸውን የሚያዩት ይህን ሲያደርጉ ብቻ ነው።
ለነዚህና ተመሳሳይ አመለካከት ላላቸው ሁሉ የምመክረው፤ ቅጥረኛና ሎሌ ሆኖ ከመኖር በድህነትና በነጻነት መኖርን እንመርጣለን ብሎ መስዋእት የሆነውን የኢትዮጵያን ጀግኖች ታሪክ ማወቅ ይበጅ ነበር የሚል ነው። ይህን እሴትና ፈለግ የሚከተለው ትውልድ ብቻ ነው ኢትዮጵያንና ኢትዮጵዊነትን ሊታደግ የሚችለው። ህብረትንና አንድነትን እንምረጥ፤ ለብሄርተኝነት፤ ለዘረኝነት ቦታ አንስጥ የምለው ለዚህ ነው።
ኢትዮጵያን ከድህነትና ከኋላ ቀርነት አሮንቃም ነጻ የሚያወጣት ይህ የማህበረሰብ ክፍል ብቻ ነው። ህብረት ይኑረን የምለው ለዚህ ነው። ግብፅን ተቃውሞ የሕዳሴን ግድብ ስኬታማ ለማድረግ የሚችለው ኃይልም ይኼው ነው። ህብረት ይኑረን የምለው ለዚህ ነው። ተራው ኢትዮጵያዊ ካለችው ገንዘብ እያወጣ ህዳሴን ለመገንባት የቻለው ህብረት ስላለው ነው። ከሃዲዎችና ቅጥረኞች እንኳን ይህን ለማጤንና ለማድረግ ቀርቶ ሰብአዊ ፍጥረት ምን እንደሆነም አያውቁም። የሚተባበሩት ለጥፋት እንጅ የተራውን ሕዝብ ኑሮ ለማሻሻል አይደለም።
ቢሆንማ በሻሸመኔ ሆነ በሌላው ክፍል ታታሪዎች አርባ ዓመት ጥረው ግረው የመሰረቱትን የኢኮኖሚ ተቋም፤ ለብዙ ድሃዎች የስራ እድል የፈጠረውን ብሄር እየለዩ አያወድሙትም ነበር።
የዘውግ ጥላቻ ውድመት ነው።
የህወሓት ቡድን መለያው በማኒፌስቶው ላይ “የአማራውን ሕዝብ የትግራይ ሕዝብ ጠላት ነው” ብሎ በመበየን፤ ይህን ታላቅ ሕዝብ ለአደጋ አጋልጦት ወደ መቀሌ መግባቱ ነው። የኢትዮጵያን ሕዝብ ከቋንቋ ውጭ ለመለየት አይቻልም። አማራውና ትግሬው፤ አማራውና ኦሮሞው፤ ኦሮሞውና ሌላው ወንድማማች ሕዝብ ነው። ሰማንያ በመቶ የሚሆነው ድብልቅ ነው። ከቋንቋው ውጭ ይህን ታላቅ ሕዝብ እንዴት ለመለየት ይቻላል? አይቻልም። የሚለዩት ልሂቃን፤ ጽንፈኞች፤ ጠባብ ብሄርተኞችና የኢትዮጵያን አንድነት የማይፈልጉ ፈረንጆች ናቸው። የሚለዩት ግብጾች ናቸው። ለምን? ለራሳቸው ጅዖፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ብቻ። የግብፅ ዋና ዓላማ አባይን በበላይነት መቆጣጠር ነው። ይህን ለማድረግ የምትችለው የኢትዮጵያን ሕዝብ በመከፋፈል፤ አገራችን ደክማና ኋላ ቀር ሆና እንድትቆይ በማድረግ ብቻ ነው።
ግብፅ የውክልና ጦርነት እድምታካሂድ በተደደጋጋሚ እኔ ብቻ ሳልሆን የታወቁ ተመራማሪዎችና የታሪክ ምሁራን ዘግበውታል። ወደ አገር ውስጥ የሥልጣን ግብግብና እልቂት ስሄድ፤ ለኢትዮጵያ ደህንነትና ብልጽግና የሚመኝ ኃይል አንዱን ዘውግ ወይንም ኃይማኖት ከሌላው እየለየና ድጋፍ እየሰጠ እርስ በርሳችሁ ተፋጁ አይልም። ይህን ሲያደርግ የሚያገልግለው የኢትዮጵያን ጠላት መንግሥታት፤ በተለይ ግብፅጽን ነው። የውጭ ጠላት፤ ቅጥረኞችን እየመለመለ፤ በገንዘብ እያባበለ፤ የውጭ መገናኛ መሳሪያ እየሰጠ እልቂት እንዲያካሄድ ማድርገጉ ባያስደንቅም፤ የሚያስደንቀው በተከታታይ፤ የውስጥ አርበኞችን ለማደራጀት፤ ለማስታጠቅ፤ ለማስልጠን ተቀባይነት የሚያገኝበት ምቹ ሁኔታ ማግኘቱ ነው። ማን አመቻቸው? ይህን ለሌላ ጊዜና ለሌሎች ልተወው።
የተቀነባበረው አመጽና እልቂት ገጽታ ምን ይመስላል?
የዝነኛው አርቲስት የኃጫሎ ሁንዴሳ አስቃቄና ኢ-ሰብ አዊ ግድያ ታስቦበት፤ ታቅዶበት የተፈጸመ ወይንጀል ነው። ገዳዮቹ ምህረት ሊደረግላቸው አይገባም። ይህ ግድያ ብቻውን ሊታይ አይገባም። በተከታታይ የተካሄዱ የፖለቲካ የግድያ ሙከራዎችና ግድያዎች ሊጠቀሱ ይገባል። እነዚህን በጅምላ “የሰኔ ግድያዎች” ልበላቸው።
- በጠቅላይ ሚንስትር ዶር ዐብይ አህመድ ላይ የተደረገውን የነፍስ ግድያ ሙከራ ማን አደረገውና ለምን?
- ከአንድ ዓመት በፊት በሰኔ በነ ዶር አምባቸው መኮነንና ጓዶቹ፤ ብርጋዴር ጀኔራል አሳምነው እና በኢትዮጵያዊው የጦር መኮነን እና ኢታ ማጆር ሹም ሳእረ ላይ የተካሄደውን ጭካኔ የተሞላበት ግድያ ማን ጠነሰሰውና ማና አካሄደው?
- ለሶስተኛ ጊዜ በሰኔው ወር፤ በኃጫሎ ላይ የተካሄደውን የነፍስ ግድያስ ማን ጠነሰሰው፤ ማን አቀነባበረው፤ ማን ፈጸመውና ለምን?
እነዚህና ሌሎች ተመሳሳይ የፖለቲካ ግድያዎች ለፖለቲካ ሥልጣን ዓላማ የተቀናጁ እንጅ የግል የቂም በቀል ግድያዎች አይደሉም። ቸልተኛነት ያስበላል የምለው ለዚህ ነው። በመጀመሪይው የግድያ ሙከራ ላይ ፈጣንና የማያሻማ እርምጃ ቢወሰድ ኖሮ ተደጋጋሚነት ሙሉ በሙሉ ይጠፋል ለማለት ባልችልም፤ ይቀንሳል። የሕግ የበላይነት ትርጉም ይኖረዋል። ሌሎችም ግድያዎች፤ ለምሳሌ፤ ዘውግን ወይንም ኃይማኖትን ኢላማ ያደረጉ በቀላሉ ከታለፉ፤ የተመለመዱ ይሆኑና ግድያዎቹ ተከታታይ ይሆናሉ።
ለማንኛውም፤ የኢትዮጵያ መሰረታዊ ጠንቅና ችግር የውስጥ መሆኑ በተከታታይ ይታያል ። ተራው ሕዝብ አይደለም። የኢትዮጵያ እናቶችና ወጣት ሴቶች እንጨት እየተሸከሙ ግብፅን እንደግፋለን፤ ዓባይን መገደብ አያስፈልግም የሚሉ ግለሰቦችና ስብስቦች አሁንም የሚኖሩባት አገር የምታሳየቸው ግድፈቶችና ክፍተቶች አሉ። ብሄርን ከብሄር፤ ኃይማኖትን ከኃይማኖት ጋር የሚጋጩ ግለሰቦች፤ ስብስቦች፤ በየክልሉ ደሞዝ እየተከፈላቸው ለአጥፊዎች ተገንና ሽፋን የሚሰጡ ባለሥልጣናት ያሉባት ክፍተትና እደጋ የተሸመከች አገር መሆኗን ያሳያል። ጠብ ጫሪዎች፤ ሕዝብን ከሕዝብ ጋር አጣልተው የሚሸሹ ወይንም የሚደበቁ፤ በውጭ ሆነው ያለምንም ስጋት ራሳቸው በነጻ አገር እየኖሩ ለተራው ድሃ ህዝብ ደንታ የሌላቸው ከሳት ላይ ቤንዚን የሚነሰንሱን ግለስቦች በቸልተኛነት ስትመለከት የቆየች አገር ናት ኢትዮጵያ። ዘውግና ኃይማኖት እየለዩ ብቻ እናቶቻችን፤ አክስቶቻችን፤ በአገራቸው የስራ እድል ሲያጡ፤ በርሀና ባህር ተሻግረው አሰቃቄ በሆነ ደረጃ በመካከለኛው ምስራቅ ተሰደው የቀን ሰራተኛ እንደሆኑ እያየዩ በአገራቸው የተሻለ የስራ እድል በመፍጠር ፋንታ ብሄርተኞችና ጽንፈኞች ልዩነቶችን ያበረታታሉ። ግጭቶችን ይፈጥራሉ፤ ንጹሃንን በዘውግ እየለዩ ይገድላሉ። ለግብጽ አገግጋይ እንሁን ይላሉ።
የፖለቲካ ልሂቃንም፤ በአብዝኛው ገንቢ የሆኑ አማራጮችን ሲያቀርቡ አላይም። በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት እናምናለን የሚሉትም ቢሆኑ እስካሁን ድረስ በአንድነት ለአንድ አገር ብሄራዊ አላማና ልማት አማራጮችን ለሕዝብ ሲያያቀርቡ አላየሁም። በተጻራሪው ክፍል የተሰብሰበቡት አፍራሽ ስብስቦች፤ ማለትም፤ ጠባብ ብሄርተኞች፤ የብሄር አክራሪዎችና ትምክህተኞች፤ የእነዚህ ኃይሎች የውጭ ደጋፊዎችና አቅም ገንቢዎች፤ ጦር አቀባዮች፤ የማህበረሰብ ሜድያ አርበኞች ወዘተ የችግሩ ዋናው አካል ናቸው። ጥላቻንና እልቂትን የሚያካሂዱት እነዚህ ናቸው።
ድሃው ተራ ሕዝብ ለጎረቤቱ ጠላት ሆኖ አያውቅም። ዛሬም እንዳለፉት የኢህአዴግ አመታት፤ የዘውግ ጥላቻን ጽንሠ ሃሳብ ማን መሰረተው፤ ማን ያራግበዋል፤ ማን እንደ መርዝ አስራጨው፤ ማን ይጠቀምበታል፤ ማንን ይጎዳል? ብለን መጠየቅ ተገቢ ነው። ምክንያቱም ችግሩን በሚገባ ተረድተን መፍትሄ ካልፈለግንለት፤ ጥላቻው ለንጹሃን ሞትና ለግዙፍ ንብረት ውድመት ጠንቅ ከመሆኑ ባሻገር፤ አገርንም ያጠፋል። አሁን ያለንበት ደረጃ ይኼው ነው።
የኢህአዴግ መንግሥት ሲመሰረት፤ ህወሓት መራሹ ቡድን የኢትዮጵያዊያንን ብሄራዊ አንድነት (እኛ ኢትዮጵያዊያን በሚል ስያሜ) መሰረት በማድረግ ፋንታ “የብሄር፤ ብሄርሰብና ሕዝቦችን” መለያ አድርጎ ያዋቀረው ሕገ መንግሥትና የክልል አስተዳደር ልዩነቶች እንዲሰፉና እየተካረሩ እንዲሄዱ ገደብ የሌለበት ማንነትን እያመረተ ቆይቷል። የዜግነት መብት ተቀዳሚ አለመሆኑ በየክልሉ ለተፈለፈሉ የፖለቲካ ልሂቃን ኑሮ አመች ሁኔታን ከመፍጠሩ በስተቀር ለነዋሪው ሕዝብ ያስገኘው መብትና ጥቅም የተወሰነ ነው። የክልሉ አስተዳደር ያስከተለው አሉታዊ ውጤት ግዙፍ ነው።
በዘውግ የተዋቀረና በዘውግ ርእይቱ የሚያምን ቡድን፤ ይህን ሕዝብን የሚያጨራርስ፤ አገርን የሚያጠፋ ጠንቅ ፈጥሮ ሊፈታው አልቻለም። ስር ነቀል መፍትሄ በመፈለግ ፋንታ፤ ችግሩን ሲያስታምመው ቆይቷል። በሳቱ ላይ ቤንዚን የሚረጩቱን አጥፊዎች በእንዝህላልነት ቸል ብሏቸው ወይንም ትቷቸው ቆይቷል። አጥፊዎቹ ይጠብቁት የነበረው እድል እስከሚፈጠር ድረስ ነበር። እድሉን ራሳቸው ፈጥረዋል፤ የውጭ ኃይሎችም፤ በተለይ ግብጽ ፈጥራላቸዋለች። ይህን የህዳሴ ግድብና የአባይ ወንዝ መዘዝ ልበለው።
ግብፅ ኢትዮጵያን ለማጥቃት ከጥንት ጀምራ ልዩ ልዩ ዘዴዎችን ተጠቅማለች። ከእነዚህ መካከል የአገር ውስጥ “አርበኞችን” መመልመልና በገንዘብ ደጉሞ ማሰማራት አንዱ ዘዴዋ ነው። በሃይማኖት ስም፤ በፖለቲካ ስም፤ ወዘተ። ዘዴው ብዙ ነው። ስንት ትከፍላለች? አባይ ወንዝ በገንዘብ አይተመንም። ዓባይ የህልውናና የብሄራዊ ደህንነት፤ የኑሯችን መሰረት ጉዳይ ነው። ግብፅ የአባይን ወንዝ በበላይነት ለመቆጣጠር መቶ ሚሊየን ዶላር በአንድ ጊዜ ፈሰስ ብታደርግ አልደነቅም። አስር ሽህዎች ንጹህ ኢትዮጵያዊያን ቢሞቱ ግብፅ ደንታ የላትም። የኢትዮጵያ መንግሥት ፈርሶ አገራችን መንግሥት አልባ ብትሆን ትመርጣለች። ለዚህ ነው፤ ግብፅ ኢትዮጵያን በቀጥታ በጦርነት ለመዋጋት አቅም ባይኖራትም የውክልናውን ጦርነት በምንም ደረጃ አታቆምም የምለው።
የእንግሊዙ መገናኛ ቴሌግራም ዩኬ July 4, 2020, ባቀረበው ዘገባ፤ አንድ የግብፅ አውሮፕላን ከግብጽ ተነሰቶ በብዙ ሽይዎች የሚገመት ካላሽንኮብ፣ ሮኬትና ሌሎች ልዩ ልዩ መሳሪያዎች ጭኖ ወደ ሞቃዲሾ፤ ሶማልያ በረረ። የሶማልያ መንግሥት ይህን መሳሪያ መልሱት እንጂ ከጎረቤት አገር ከኢትዮጵያ ጋር ለመጋጨት አነፈልግም ብሎ ወደ ካይሮ እንዲመለስ ያደረገው በቂ ምሳሌ ነው።
ግብጽ ኢትዮጵያን በቀጥታ ለመዋጋት ሞክራ በተደጋጋሚ ተሸንፋለች። ያላት ሌላ አማራጭ የውክልና ጦርነት ማካሄድ ነው። ለዚህ ደግሞ እድል አላት፤ ቅጥረኞችን ማባበል፤ ገንዘብ ብቻ ሳይሆን መሳሪያም እያቀበለች ኢትዮጵያን ማዳከም ነው። የርስ በርስ ጦርነት እንዲካሄድ ታመቻቻለች ማለት ነው። በሰሜን ህወሕት መራሹ ቡድን “የእርስ በእርስ ጦነት አዋጅ አውጇል” እየተባለ ይወራል። በምስራቅና በደቡብ፤ በአዲስ አበባና በዙሪያዋ፤ የሽኔ ኦነግ፤ የአል-ሸባብ፤ የቄሮና ሌሎች አክራሪዎችና አመጸኞች ንጹሃንን እየገደሉ “የነፍጠኛውን መንግሥት” ማንበርከክ አላማችን ነው ብለው ቅንብሩን የሚያካሂዱት። ቀደም ብለን ስራ አለመስራታችን አደጋውን አባብሶታል።
ለማጠቃለል፤ ቅጥረኞች ዘውግንና ኃይማኖትን እየለዩ በተከታታይ እልቂት ማካሄድ የተለመደ የሆነው ህወሓት መራሹ ኢህአዴግ ሥልጣን ከያዘበት ወዲህ መሆኑ የታወቀና በመረጃዎች የተደገፈ ነው። ስርዓት ወለድ ነው የምልበት መሰረታዊ ምክንያት ይኼው ነው።
የዘውግ ተኮሩ ሕገ-መንግሥትና የክልሉ አስተዳደር መለያዎች ጭካኔ፤ አንዱን ብሄር ከሌላው እየለዩ ማሳደድ፤ መግደል፤ ኃብትና ንብረቱን፤ እሴቱን፤ ተቋሙን፤ ምልክቱን ማፈራረስና በስነልቦናው ላይ ተከታታይ ዘመቻዎችን ማካሄድ የተለመደ ሆኖ ቆይቷል።
ይህ ተከታታይ የማውደምና የማጥፋት ዘመቻ ትኩረት የተደረገበት የብሄር ማጥቃት ሰቆቃና የጭካኔው መጠን በመረጃዎች ተደግፎ ይፋ እየሆነ ሲሄድ፤ አረመኔነትን፤ ኢ-ሰብ አዊነትን፤ አውሬነትን፤ “ከኔ ዘውግና ከኔ እምነት ውጭ” መኖር የለብህም፤ የለባትም የሚል እብሪተኛነትን የሚንጸባርቅበ እልቂትን የሚያሳይ ገጽታ ይታያል።
ኢትዮጵያ ገና ሩዋንዳ ከደረሰችበት ደረጃ ላይ አልደረሰችም ለማለት አልችልም፤ ከደረሰች ብዙ አመታት አልፈዋል። የሩዋንዳ አይነት እልቂት ደሩሷል የምንለው ስንት ንጹህ አማራዎች፤ ወላይታዎች፤ ጉራጌዎችና ሌሎች ንጹህ ወገኖቻችን ሲሞቱ ነው? ብዙ ወገኖቻችን ታርደዋል፤ ሞተው ያልተቀብሩም አሉ፡፡ ይህ ጭፍጨፋ ሩዋንዳ፤ ኮሶቮና ሌሎች የዘውግ እልቂቶች የተካሄዱባቸውን አገሮች ታሪክ የሚሳይ ኢ-ሰብ አዊ ተግባር ነው፡፡ ወንጀል ነው፡፡ ጾታ፤ እድሜ፤ የገቢ መጠን፤ እናት፤ ህጻን፤ ሽማግሌ፤ እርጉዝ ሴት፤ ወንድ፤ ቦታ ወዘተ በማይለይ ብሄር ተኮር ግድያ በተደጋጋሚ ተካሂዷል ማለቴ ነው። ኢላማው በተለይ አማራውን እየለየና ስም እየሰጠ፤ “ነፍጠኛ ነህ” እያለ፤ ኢላማ የሆነውን ለይቶና አስቀድሞ ጠቁሞ፤ ግድያዎችና አካሂዶበታል፡፡ በቅርቡ፤ በወላይታው፤ በጉራጌውና በሌሎች ብሄር አባላት ላይም ጭካኔ የሞላበት ጭፍጨፋ ተካሂዷል። ግለሰሰቦችና ቤተሰቦች ጥረው ግረው ከሰላሳ እሰከ አርባ ዓመታት በፈጀ ጊዜ ያካበቱትን መዋእለንዋይ ኢላማ ተደርጎ እንዲወድም ሆኗል። ይህ ለወገኖቻቸው የስራ እድል፤ የገቢ እድል፤ የኑሮ መሻሻል እድል ውድመት፤ የኢኮኖሚ ወንጀል ነው።
ለማጥዕቃለ፤ ምን ለማድረግ እንችላለን?
የትግሉን ጎራ ለይቸ ለማሳየት ችያለሁ የሚል እምነት አለኝ። ባጠቃላይ ስመለከተው፤ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት ላይ እምነትን ያለን ሁሉ ያለን አማራጭ አንድ ብቻ ነው። በአንድነት ተሰብስቦ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን መታደግ ወሳኝ ነው። ዘውግና ኃይማኖት ተኮር ግድያዎችን ሁሉ ማውገዝ አለብን።
ችግሩ እየተባባሰ ሂዷል የሚሉ ብዙ ታዛቢዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ፤ በሰሜን፤ ህወሓት የኢትዮጵያን ሕዝብ ለክተት አዋጅ የሚቀስቅስ አዋጅ አውጇል። ይህ አዋጅ የትግራይን ሕዝብ ይወክላል የሚል እምነት የለኝም። ሰፊው የትግራይ ሕዝብ ከሌላው ወንድሙ ጋር ወደ እልቂት ለመሄድ አይፈልግም። የህወሃትን አጥፊነትና አገር አፍራሽነት የሚቀበሉ ሁሉ በአንድ ላይ ሆነው ይህን ሽብርተኛና የውጭ ጠላት አጋር ቡድን መታገል አለባቸው፡፡ በተጨማሪ፤
- አንደኛ፤ ህወሓት የወገነውና የዶሎተው፤ በውጭ ከግብፅ ጋር ነው። በውስጥ ደግሞ አጋሬ ነው ከሚለው ከሽኔ ኦነግና ከቄሮ ጋር ነው። ለምሳሌ ዘውግን ለይቶ እልቂት ከሚያካሂደው ከሽኔ ኦነግና ከቄሮ ጋር ሆኖ ግፍና ጭካኔ በሚያሳይ ወንጀለኛነነት ከሚያንጸባርቀው ጨካኙ ወንጀለኛ ጋር የተቀናጀ ግፍና እልቂት በሻሸመኔ፤ በሃረር፤ በድሪዳዋ፤ በባሌ ይካሄዳል። እነዚኅ ግፎችና እልቂቶች በድምራቸው ስገመግማቸው የጀኖሳይድይ ወች መስራችና መሪ ዶር ግሬገሪ ሃንተን ያወጧቸውን አስርት መስፈርቶች የሚያሟሉ መሆናቸውን የሚያሳይ ሁኔታ ይታያል። SAGE ያቀረበውን ትንተና እጋራለሁ፤ እደግፋለሁ።
- የህወሓት ረዥም ክንድ በነዚህና በሌሎች እልቂቶች በደም የተቀባ መሆኑን ለማሳየት የሚቻልበትን መረጃ ለመሰብሰብና ለዓለም የወንጀል ተቋማት ለማቀረብ የሚቻልበት ሁኔታና እድል እለ። ይህን ለማድረግ የሚችሉ የህግ ባለሞያዎችን መሰብሰብና በገንዘብ መርዳት ወሳኝ ነው።
- በተጨማሪ ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ብሄራዊና አስኳል ጉዳይ ህወሓት፤ ሽኔ ኦነግና ቄሮ በአሁኑ ወሳኝ ወቅት ከግብፅ ጋር ወግነው፤ የሕዳሴ ግድብ ሙሌት እንዲኮላሽ ለማድረግ የሚያደርጉትን ሴራ፤ በሁሉም ዘርፎች ድምጻችንና አቤቱታችን ማሰማት ብሄራዊ ግዴታችን ነው። ይህን ከሃዲ ተግባር አወግዛለሁ።
- ይህ ሴራ ስኬታማ እንዳይሆን ከፈለግን፤ ኢትዮጵያ መሪዎችና መንግሥት አልባ እንዳትሆን አግባብ ያለው አቋም መውሰድና በማያወላውል ደረጃ ድጋፋችን የምናሳይበት ወቅት ዛሬ መሆኑን ለማሳሰብ እፈልጋለሁ።
- እኢትዮጵያና እኢትዮጵያዊነት ኩራታችን፤ ክብራችን፤ መለያችን፤ የአቅም መንስ ኤያችን ናቸው፡፡ ከመሳሪያና ክምችት ይልቅ፤ ለኢትዮጵያ ሃገራችን ዋና መከታችን፤ ክንዳችን፤ ሃይላችን፤ መከታችን፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ስርጭትና ብሄርዊ አንድነትና ጀግናነት ነው፡፡
- በመጨረሻ፤ ግዙፉ የኢትዮጵያ ምሁራንና ልሂቃን ጥቃቅን ልዩነቶችን ወደ ጎን ትቶ ለብሄራዊ አላማ እየተናበበ የሚሰራበት ወቅት አሁን ነው;፡
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!! ብሄር ተኮር እልቂትን ባስቸኳይ እናስቁም!!፤ የኢትዮጵያዊያንን አንድነት እንደግፍ!!
July 10, 2020