እንኳንስ ተደርጎ አያውቅም ተስምቶ
በየትኛውም ዓለም አልነበረም ከቶ
ቤት ዘግተን ጾመን፣ ዘግተንም ዐለይን
ቤተክሲያን ሳኔድ እልፍኙ ጋ ሰገድን
“ይማሩኝ አባቴ” ብለንም ደውለን
ልማድም እንዳቀር ቤት ዘግተን ደግሰን
ባካል ተለያይተን በዓላማ አንድ ሆነን
ዘንድሮም እንዳምና አምሮብን ተውበን
ትንሳኤ ለሙታን በስመ አብ ብለን
ይሄው አገደፍን በስልክ ተጎራርሰን።
ምዕመናን የካህናት ምክራቸውን ሰምተው
ካህናትም ሳይንስን ከዕምነት ጋ አስማምተው
ትውልድ ይዳን ብለው መስዋዕትነት ከፍለው
በሚደነቅ መልኩ አንድነት መስርተው
ሁሉም ተፈፀመ ጌታም ደስ ደስ አለው።
ይቻል ኖሯል ለካስ ከልብ ካለቀሱ
ትውልድ ለመታደግ ታጥቀው ከተነሡ
የከርሞ ሰው ያርገን ወግ ታሪክ ነጋሪ
አገርን ገንብቶ አዲስ ታሪክ ሠሪ።
ኢትዮጵያችን ትኑር እኛም እንድንኖር
ዓዲስ ምዕራፍ ይፃፍ እውነቱም ይነገር
ግድፈትም ይታረም ብርታትም ይወደስ
የሠራም ይሞገስ አውደልዳይ ይወቀስ
ከርሞ ጥጃ አንዳይሉ አሁንም ዋል ፈሰስ
ውስጣችን ይፈተሽ ቃልኪዳን ይታደስ።
ነጋሪት ይጎሰም ደወሉም ያቃጭል
ወፎች ይዘምሩ እንበል እልል እልል
ከንግዲህ አገሬ እድገቷም ይፋጠን
ተካፍለን እንብላ ይቅርም እንዲለን።
መንግስትም እንደሰው ይመከር ይዘከር
ሀላፊነት ይብዛ ሁሉም ይከባበር
የተቻችሎ መኖር ቀመሩም ይቀመር።
ሚያዚያ 11 2012 ዓ/ም
ዶር አኸዛ ጠዓመ