በእርግጥ ነው በተቻለ መጠን እቤት መቀመጥ ለሚችሉ እቤታቸው ቢሆኑ ጥሩ ነው፡፡ ሆኖም በኢትዮጵያ የኑሮ ሁኔታ እቤታችሁ ተቀመጡ የሚለው አማራጭ አዋጪ ሆኖ አላየውም፡፡በሌሎች አገሮች እቤታችሁ ተቀመጡ ቢባል የሚበሉትና የሚጠጡትን ለመግዛት ገበያ ካልሄዱ በቀር ለሚገዙበት ገንዘብ በሂሳብ ቁጥራቸው ስለሚደርሳቸው ነው፡፡ አሁን ያለው የአደጉት አገሮች የገበያ ምቹነት የሚበሉትና የሚጠጡትንም ቢሆን በኦንላይን የሚፈልጉትን ገዝተው የመኖሪያ በራቸው ላይ የገዙትን የምግብም ሆነ ሌላ ነገር ተቀምጦላቸው ያገኙታል፡፡ ይሄ ሁሉ ሆኖ ግን አሁንም ቢሆን የምግብ ገበያ በዋናነት እየተካሄደ ያለው በአካል በመሆኑ እነዚህ ገበያዎች ክፍት ናቸው፡፡ በገበያዎቹ ግን ርቀትን የመጠበቅ ሥርዓት ተደርጎላቸዋል፡፡ በወሳኝ የገበያው ውስጥ መንቀሳቀሻ ቦታዎች መስመሮች ተበጅተውም ይታያሉ፡፡ ይሄ አይነት አማራጭ የሚሰራው የተደራጀ የገበያ ማዕከል ሲኖር ነው፡፡ በኢትዮጵያ ይሄ የለም (ጥቂት በታ አዲስ አበበ ውስጥ መኖሩን አሳምሬ አውቃለሁ)፡፡ የአብዛኛው የሕዝባችን ገበያ እንደምናውቀው መርካቶ፣ ጉሊቶች ና፣ የሰፈር ኪዮስኮች እንደሆነ አሳምረን እናውቀዋለን፡፡ገንዘቡን እንኳን ተገኝቶ ዜጎች የሚበሉትን ለማግኘት የግድ እነዚህን ገበያዎች መጠቀም ግድ ነው፡፡ ከዚሁ ሁሉ በላይ ግን መጀመሪያውኑ የእለት ጉርስን ለመግዛት የግድ ገንዘብ ያስፈልገዋል፡፡ ስለዚህ እቤት ተቀመጥ የሚለው በቀጥታ ከሌሎች የተወረሰ ስልት በኢትዮጵያ የሚሰራበት እድል አለመኖር ብቻም ሳይሆን የከፋ አደጋንም ሊያስከትል ይችላል፡፡
ስለዚህ ከሌሎች ከምንሰማቸው ቫይረሱን ለመከላከል ከሚወሰዱ አማራጮች በተለይ ለእኛ አኗኗር ዘይቤና አቅም የሚስማሙ ስልቶች በደንብ ማሰብና ተግባር ላይ ማዋል ግድ ይላል፡፡ ከወዲሁ ዛይዘጋጁ የሌሎችን በተለይ በጣም የአደጉና የተመቻቸ ሁኔታ ያላቸውን አገራት ስልት ብቻ እያራገብን ችግሩ ገፍቶ ሲመጣ ለእኛ እርባና ላይኖራቸው እንደሚችል ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ እኔ የሚከተሉትን አማራጮች አስባለሁ፡፡
- እቤት ውስጥ መቀመጥ፡- ይሄ አማራጭ በጣም ጥቂት ለሚባሉ ምን አልባትም በመንግስትና ጥቂት ድርጅቶች ብቻ ተቀጥረው ለሚሰሩ ሊሰራ የሚችል ስልት ነው፡፡ ለቀሪው አብዛኛው ሕብረተሰባች ግን አይሰራም፡፡ የሌላውን እንደወረደ ከመኮረግ ይልቅ ለእኛ የሚሆን እናስብ፡፡
- በገበያ ቦታ፡- ይሄ በተለይ እርቀትን ከመጠበቅና መተፋፈግን ግርግርን ከማስወገድ አኳያ ሊታሰብበት የሚገባ ነው፡፡ በተቻለ ሁሉ ጉሊትም ይሁን ሌሎች የእኛ አይነት ገበያዎች በመስመር በመስመር ቢሆኑና ሰዎች በተቻላቸው ሁሉ ርቀታቸውን ጠብቀው ሊገበያዩ የሚችሉበት ሁኔታ ቢፈጠር፡፡ ለዚህ ከሌሎች አገራት ይልቅ ለእኛ ሊቀርብ የሚችል የሕንድ አኗኗር ነው፡፡ ስለዚህ ከእነሱ ብዙ ስልቶች ልንቀስም እንችላለን፡፡ የራሳችንንም እንደራሳችን ብናክልበት፡፡
- በሥራ ቦታ፡- በገበያ ቦታ ከተሰማሩ ለእለት ጉርሳቸው ያገኙዋትን ሸጠው ለውጠው ለሚኖሩ ከላይ የጠቀስኩት የገበያ ሥርዓት ጋር አብሮ ማስተካከል ነው፡፡ ከእነዚህ ውጭ የሆኑ ሥራዎች ለምሳሌ በየግንባታ ቦታዎች ተቀጥረው የሚሰሩ በተቻለ መጠን ርቀታቸውን መጠበቅ ይችላሉ፡፡ ለዚህ አሰሪዎች ኃላፊነት ወስደው ሥርዓት እንዲጠብቁ ማድረግ ነው፡፡ ሆኖም ይሄ በወጥነት የርቀቱን መጠንና ሌሎች ሥርዓቶች በመንግስት በኩል በጽሁፍና በሌሎች አማራጮች ጭምር ለሁሉም ማድረስ ነው፡፡
- በእግር መንገድ ላይ፡- አሁንም የእኛ መንገዶች በብዛት ሰው ስለሚበዛባቸው በተቻለን አቅም ሁሉ መንገድ ላይ መውጣትን ባናዘወትር የመንገዶቹን መጨናነቅ ይቀንሰዋል፡፡ ይሄ ሁሉ ሆኖ ግን አሁንም ርቀታችንን መጠበቅ ዋነኛው ነው፡፡
- በትራነስፖርት፡ ይሄ ከምዕራባውያኑ ብዙም የተለየ ስላልሆነና አሁንም በከተማ በባሶች የሰው ቁጥር እንዲቀንስ ተደርጓል ስለተባለ እሱኑ መጠቀም ነው፡፡
- የከተማ ባስና ባቡር፡- የከተማ እንደሰማሁት እንደድሮው መታጨቅ ቀርቶ በወንበር ሆኗል ነው፡፡ ይሄ አይነቱ አልሸሹም ዞር አሉ አይነት እርምጃ በጣም አዘናጊና አደገኛ ነው፡፡ በባስ ውስጥ ያለውን ሰው ቁጥር መቀነስ አንድ ነገር ሆኖ በባስ ውስጥ የተሳፋሪዎችን ርቀጥ መጠበቅ ግን ከምንም በላይ ወሳኝ ነው፡፡ በወንበር በሚል ባለ ሁለት ወንበር መቀመጫ ላይ ጎን ለጎን ማስቀመጥ ከሆነ ምኑን ጥንቃቄ ተደረገ?ለከተማ ባስ የሚከተሉት ቢደረጉ
- የከተማ ባስ ቢያንስ አንድ ወንበር ላይ ከአንድ ሰው የበለጠ መቀመጥ የለበትም፡፡ ቀሪውን ወጭ መንግስት መሸፈን ይኖርበታል፡፡
- ተሳፋሪዎች ቲኬት ቀደም ብለው ቢገዙና ለእለት ወይም ረዝ ላለ ጊዜ የሚሆናቸው ቲኬት ቢኖራቸው በየቀኑና በየሰዓቱ ቲኬት ለመግዛት በሚል ከሚኖሩ ንክኪዎች ከመጋለጥ ያድናል፡፡ ቫይረሱ ከምንም በላይ በንክኪ ነውና የሚተላለፈው፡፡ ንኪኪው በምንገበያይበት ገንዘብም ጭምር ስለሚሆን
- የከተማ ባስና ባቡር፡- የከተማ እንደሰማሁት እንደድሮው መታጨቅ ቀርቶ በወንበር ሆኗል ነው፡፡ ይሄ አይነቱ አልሸሹም ዞር አሉ አይነት እርምጃ በጣም አዘናጊና አደገኛ ነው፡፡ በባስ ውስጥ ያለውን ሰው ቁጥር መቀነስ አንድ ነገር ሆኖ በባስ ውስጥ የተሳፋሪዎችን ርቀጥ መጠበቅ ግን ከምንም በላይ ወሳኝ ነው፡፡ በወንበር በሚል ባለ ሁለት ወንበር መቀመጫ ላይ ጎን ለጎን ማስቀመጥ ከሆነ ምኑን ጥንቃቄ ተደረገ?ለከተማ ባስ የሚከተሉት ቢደረጉ
- በሰልፍ ቦታዎች ርቀትን ጠብቆ መጠበቅ
- በሹፌሩ በር በኩል ለሹፌሩ ደኅንነት ሲባል ማንም እንዳይገባ ማድረግ
- ሌሎች የምታስቡበትን ብትጨምሩበት
- የክፍለሀገር ተጓዦች፡- አሁንም ሲወጡና ሲገቡ ርቀትን መጠበቅና እርጋታን እንዳለ ሆኖ እንደ ከተማ ባስ ወይም ባቡር ጎን ለጎን ባሉ ሁለት ወንበሮች በአንድ ሰው ብቻ ማስያዝ አዋጭ ስለማይሆን፡፡ በተቻለ መጠን ጎን ለጎን ባሉ ወንበሮች ቤተሰብ የሆኑ ሰዎች ካሉ አብረው ቢሆኑ፡፡ ይሄ እስካሁንም የተለመደ ነው፡፡ አሁን ግን አሳፋሪዎቹ እንደዛ ያሉ ሰዎችን በመጠየቅ አንድ ላይ ማድረግ ቢችሉ፡፡ ከሁሉም በላይ እንደነዚህ ባሉ ትራነስፖርቶች ከአውቶ ጉዞ ላይ ሁሉ አፍንና አፍንጫን በአፍ መሸፈኛ ወይም በለበስንው ጨርቅ መሸፈን፡፡ እቤታችንም ስንገባ የአፍ መሸፈኛችንና ከወንበርም ይሁን ከሌላ ጋር ንኪኪ ይኖራቸዋል የምንለውን ልብሶች ሁሉ አውልቀን ቢያንስ ለሁለት ቀናት ራቅ ያለ ሌሎች ሊደርሱበት የማይችሉበት ቦታ ማስቀመጥ፡፡ ባዶ ሳጥን ውስጥ መቆለፍም ሊሆን ይችላል፡፡ ቫይረሱ እስካሁን ቫለው መረጃ በልብስ ላይ ከሁለት ቀን በላይ አይቆይም፡፡ የበለጠ ለመተማመን ለተጨማሪ ቀናት ማቆየት ነው፡፡ ከጉኦ አንደተመለስን ቢቻለን መላሰውነታችንን ቢያንስ ግን ምንም ሌላ ቤት ውስጥ ያለ እቃ ከመንካታችን በፊት እጃችንን ለ20 ሰከንድ ገደማ በሳሙና በማሸት መታጠብ ነው፡፡
- ሚኒባሶች፡- በአገራችን ሚኒባሶች ዋና መጓጓዣ እንደመሆናቸው ክፍለሀገር የሚሰሩት ከላይ የጠቀስኩትን የክፍለሀገር ተጓዥ ስልት ሊጠቀሙ ይችላለሁ፡፡ በታከሲነት የሚሰሩት ግን አሁንም ከሚወጣው ከሚገባው ሰው ብዛት አንጻር ለየት ያለ ሌላ ስልት ያስፈልጋቸው ይመስለኛል፡፡ ርቀትን ለመጠበቅ ምቹ አደሉም፡፡ ምን አልባት ለዚህ ወሳኝ ጊዜ መንግስት ቢደጉማቸውና ጎን ለጎን ማስቀመጥ ቢያቆሙ፡፡ ከመንግስት ድጎማ በተጨማሪ መጠነኛ ታሪፍ መጨመር ነው፡፡ ይህ ማለት ለትርፍ ሳይሆን የጊዜውን ሁኔታ በመረዳዳት ለማለፍ ፍጹም መተሳሰብ በተሞላበት ሁኔታ ማለት ነው፡፡
- ከከተማ ከተማ የሚደረጉ ጉዞዎች እቀባ፡- ችግር የታየባቸው ወይም ስጋቱ ያለባቸውን ከተሞች ከወዲሁ ከሌሎች ከተሞች ጋር የሚኖራቸውን እንቅስቀሴ መገደብ ሳይቃጠል በቅጠል ነው፡፡ ዛሬ ከናዝሬት/አዳማ የሚወጡም የሚገቡትንም መኪናዎች ታግደዋል ሲባል ነበር፡፡ ወሳኝ የአቅርቦት እንቅስቃሴዎች ካልሆኑ እንዲህ ያሉ እርምጃዎች በእርግጥም ያስፈልጋሉ፡፡ አላስፈላጊ መዘናጋትና የላላ አቋም መያዝ ብዙ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ሕዝቡም የጊዜውን ሁኔታ ከግንዛቤ በማስገባት ሊተባበር ይገባል፡፡ በሁኔታዎች በምንም መልኩ መዘናጋት አያስፈልግም፡፡ ይሄ የመብትና የፍላጎት ጉዳይ ሳይሆን የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ ነው፡፡ ይህ በሽታ መጀመሪያ ተከስቶባት ከሰማኒያ ሺ በላይ ዜጎቿን ከለከፈባት በኋላ ዛሬ በሽታውን በደንብ እየተቆጣጠረቸው ያለቸው ቻይና ቁርጠኛ በሆኑ እንደዚህ ያለ እርምጃዎችን በመከተል ነው፡፡ በአንጻሩ በሌሎች ዲሞክራሲ ነው በሚል የዜጎችን መብት እንጠብቃለን በሚል ግዴታን እንዲረሱ ባደረጉ አገራት ዛሬ በሽታውን ለመቆጣጠር ተስኗቸው ትልቅ አደጋ ፈጥሮባቸዋል፡፡
- አጋጣሚውን ተጠቅመው ሕዝብን የሚጎዱ እንቅስቃሴዎችን መቆጣጠር፡- በእኛው አገር በተለይ ነጋዴዎችና የመንግስት ስልጣን ላይ ያሉ ብዙ ጊዜ አጋጣሚን ተጠቅመው በሕዝብ ላይ ሌላ ጫና መፍጠር የተለመደ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ለሕዝብ አስባለሁ የሚል ሁሉ ይሄን አጋጣሚ ተጠቅሞ የግል ጥቅም ሊያጋብስ ወይም ከነጋዴ ጋር ሊሞዳሞድ የሞከረን ሰው ወሳኝ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል፡፡ ገንዘብ አለን ብላችሁ ገንዘብ ስላላችሁ ብቻ ገበያን ለማናር የምትተባበሩ ተጠቃሚዎች ሳይቀር በዚህ ወቅት የተለይ ክፍያ ለሻጭ ባለመክፈል ግዴታችሁን ብትወጡ፡፡ መንግስት በሻጭም በገዥም እንዲሁም ተያያዥነት ባላቸው ባለስልጣናትም ጠበቅ ያለ ክትትል ቢያደርግ፡፡ አጥፊዎችንም ከፍተኛ ቅጣት ቢቀጣ፡፡ ትልቁ ችግር የሚሆነው የመንግስት ግድ የለሽነት እንደሚሆን እሰጋለሁ፡፡ እስካሁን በምናቃቸው እውነቶች መንግስት ስልጣን አናት ላይ ያሉ ለራሳቸው ፖለቲካ ሴራ እንጂ ለእንዲህ ያለ ዋሳኝ ተልኮ እንደማይሆን በተደጋጋሚ ክደው ያየንበት እውነት ስላለ ማለቴ ነው፡፡
- በገጠር የሚኖር ወገናችን፡- የሚከተሉትን ቢያደርግ
- ወደ ከተማ ወሳኝ ለሆኑ ጉዳዮች ካልሆነ መንቀሳቀሱን ቢገታ
- በከተማ ቆይቶ ወደ ገጠር ለመሄድ ያሰበ ራሱን ለተወሰነ ጊዜ(14 ቀን) ነጥሎ ችግር እንደሌለበት ሲያውቅ የገጠር ዘመዶች ለመጠየቅ ቢሄድ፡፡
- በተለይ በመኪና መንገድ ዳር ያሉ የገጠር አካባቢዎች ከከተማ ከሚመጡ ሰዎች የሚሰጣቸውን ማንኛውንም ነገር ቢያንስ በእጃቸው ሳይነኩ ለ3 ቀን ካላደረ በቀር ባይጠቀሙ፡፡ ለዚህ አይነተኛ ምሳሌ አንድ ጓደኛዬ በፌስቡክ ስለጠቆመችው ትዝ ያለኝ የታሸገ ውያ ላስቲኮችን ውሀውን ጠጥተው ለገጠር ልጆች መስጠት የተለመደ ነው፡፡ ይሄ ከአሁን በኋላ ቢቆም፡፡ ከምንም በላይ ቫይረሱ በፕላሰቲክ ነገሮች ላይ ለረዥም ጊዜ ይቆያል፡፡ በእነዚህ የላስቲክ ውሀ መያዣዎች ላይ ብዙ ጊዜ ሊቆይ እንደሚችል ቢታሰብበት፡፡ ይሄንና ሌሎች ከከተማ የሚነሱ ሰዎች ለገጠር በሚሰጧቸው ማናቸው ቁሳቁሶች ዙሪያ የአገሪቱ መገናኛ ብዙሀኖች ግንዛቤው እንዲኖር ማድረግ ቢችሉ፡፡
- ድንገት በገጠር ችግሩ ቢከሰት የተያዘውን ሰው ዳስ ቢጤ ለብቻው በመስራት ማቆየት፡፡ ምግቡንና መጠጡን መቀራረብ ሳይኖር የሆነ ቦታ ቢያስቀምጡለት/ላት ታማሚው/ዋ ከተቀመጠለት/ላት ቦታ እነስታ ብትበላ፡፡ ምን አልባት ታማሚው የተመገበበት እቃ ሊበከል ስለሚችል ቢያንስ እስከ ሶስት ቀን ድረስ ተማሚው ከራሱ ራቅ አድርጎ ባስቀመጠበት ቦታ እንዲቆይ ቢደረግ፡፡ እስከ ሶስት ቀን ድረስ በአዳዲስ አቃዎች በመስጠት በሶስተኛው ቀን ከሶስት ቀን በፊት የተጠቀመበትን በማጠም እንደገና መጠቀም ይቻላል፡፡ ምን እልባት ይሄኛው ለከተሜ ተለይተው ላሉ ታማሚዎችም ይሰራል
- ሌሎች ጨምሩበት
- መጠንቀቅ እንጂ አለመፍራት፡– አስፈላጊውን ሁሉ ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ሲሆን በዛው ልክ በቫይረሱ ተይዘዋል የተባሉን ሰዎች ሲያዩ መበርገግ ከፍተኛ አደጋ ሊያስከትል ይችላል፡፡ ምክነያቱም በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን በአግባቡ መርዳትና ወደሌላ ሰዎ እንዳይሰራጭ ማገዝ ከምንም በላይ ወሳኝ ነውና፡፡ ድንገት ሕመም ቢጸናባቸውም በቀላሉ መዳን የሚችሉን ሰዎች እርዳታ በማጣት ሊያሳጣ ይችላልና፡፡ በሽታው 80 በመቶ በሚሆኑ ላይ ቀላል ሲሆን በአንዳንዶች ላይ ከእነጭርሱም ምልክትም ላያሳይ ይችላል፡፡ ይሄ ማለት ግን ቀላል ነው ተብሎ የሚዘናጉለት አደለም፡፡ የመዛመት አቅም በጣም ከፍተኛ ስለሆነ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን በጥቂት ጊዜ የመያዝ አቅም አለው፡፡ ከሚያዙት ወደ ሶስት በመቶ ይገድላል ይባላል፡፡ ይህ ማለት 100 ሚሊየን ሰው ቢይዝ ሶስት ሚሊየን ይገድላል ማለት ነው፡፡ ከዚህም በላይ ብዙ ታማሚዎች ስለሚኖሩ ሊድኑ የሚችሉትን እንኳን በግባቡ በመርዳት ለማዳን ይቸግራል፡፡ ዛሬ በኢጣሊያ እየሆነ ያለው ይሄ ነው፡፡ የቫይረሱ የመዛመት ፍጥነት ከዚህ በፊት ከታዩት ሁሉ እጅግ የከፋ ነው፡፡
- የራስ የመከላከያ ዘዴዎችን መጠቀም፡- ከላይ ከጠቀስናቸው በተጨማሪ በተደጋጋሚ የሚነገሩ የእኝ መታጠብ የአፍ መሸፈኛ መጠቀም የመሳሰሉ አሉ፡፡ በተለይ የአፍ መሸፈኛ የሚለው እስካሁን ከታመሙስ ሰዎች በቀር ርቀት ጠብቀው ለሚንቀሳቀሱ ሰዎች ላያስፈልግ ይችላል፡፡ ሆኖም አንዳንድ ሰዎች የሚበዙባቸው በተለይ በትራነስፖረት ውስጥ ወሳኝ ነው፡፡ የግድ በዘመናዊ መልክ የተዘጋጀ መሸፈኛ አደለም፡፡ የራሲን አንገት ልብስ፣ ፎጣና ነጠላ መጠቀም ይቻላል፡፡ አላስፈላጊ ዘመናዊነት አያስፈልገውም፡፡ የዚህ ቫይረስ ብልሀቱ ወደ ሰውነት እንዳይገባ ብቻ ነው፡፡ ከማስኩ በተሳል አንገት ልብሱና ነጠላው ሊያስቀረው ይችላል፡፡ ሆኖም አንገት ልብሱና ነጠላው በስሱ ሳይሆን በስነስርዓቱ ለአፍና አፍንጫ በሚሆን ሁኔታ በማጠፍ ቢሆን ይመረጣል፡፡ ቫይረሱ እሰካሁን በታው ባህሪው እንደ ልብስ ባሉ ነገሮች ላይ በተለይ እንደፎጣና ነጠላ ያሉ ልሙጥ ያልሆኑ ነገሮች ላይ የሚኖረው አጭር አድሜ ነው፡፡ ግፋ ቢል እሰክ 24 ሰዓት፡፡ ሆኖም ነጠላና አንገት ልብሱን አንዴ አጥፈው አፍላይ ካደረጉ በኋላ እንደገና በሌላው ውጭኛው በኩል አዙሮ መጠቀም ቫይረሱ ያረፈበት ስለሚሆን መቆጠብ ነው፡፡ ቤት ስንደርስ እነዚያን ልብሶች ለተወሰነ ጊዜ አርቆ ማኖር (ማንም እንዳይነካ) እጃችንን መታጠብ፡፡
- ከማይረቡ መረጃዎች መቆጠብ፡- አንዳነዶች ስለኮረና ለማውራትና አዋቂ ለመሆን ብዙ ያልተገቡ መረጃዎችን ሲያስተላለፍ ይገኛሉ፡፡ በአብዛኛው ከሩቅ ያሉን ግዙፍ ችግሮች ማውራት አስተዋጾ የሚመስላቸውም አሉ፡፡ የችግሩን አውነትነት የምናያቸው መረጃዎች በቂ ናቸው፡፡ ግን መፍትሄ ላይ ያተኮሮ መልእክቶችን ቢዘወተሩ ጥሩ ነው፡፡ በመድሀኒቶች ዙሪያ የሚሰራጩ ወሬዎች ሌላው በጣም የተምታታ ነው፡፡ በእኛው አገር የገዳም አባቶች ፌጦና ሽንኩረት ጠጡ ብለዋል ካሉን የማህበራዊ ድረገጾች፣ ፎረው ተገኘና፣ መድሀኒት በምርምር አገኘን ካሉት የዋና መገናኛ ብዙሀንና የመንግስት ባለስልጣኖች ሳይቀር ያልተገቡ መልዕክቶች ሲተላለፉ አይተናል፡፡ እስኪ የለመድንውን ልማድ ይሄ ቀን እስኪያልፍ እናቆየውና አሁን በማስተዋልና ኃላፊነት ተሰምቶን መልዕክቶችን እናስተላልፍ፡፡
እነዚህ እንግዲህ እኔ የታዩን ናቸው፡፡ ትክክል ናቸው ማለት ግን አይደለም፡፡ ከዚህ የተሻለ አማራጭ ይኖራልና፡፡ እባካችሁ ሌሎች የምታስቡትን አዳዲሰ ሀሳብ አቅርቡ፡፡ ሆኖም ዝም ብለን ደግሞ የሀሳብ ጋጋታ እንዳይሆሀንና ሌላ ግር መጋባት እንዳይፈጥር እየተጠነቀቅን፡፡ ሆኖም የተዘነጉ የሚጠቅሙ ወይም ከምታስተውሉት አንጻር ትኩረት መሰጠት ያለባቸው የምትሏቸውን አካፍሉ፡፡
ቅዱስ እግዚአብሔር ለዓለሙ ሁሉ ምህረቱን ያውርድ! አገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ! አሜን
ሰርፀ ደስታ