ያለ ጊዜው ከሚወስድ ሞት እግዚአብሔር ይጠብቀን።አሜን።
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ
(ገላትያ 5 )
————
14 ሕግ ሁሉ በአንድ ቃል ይፈጸማልና፥ እርሱም፦ ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የሚል ነው።
15 ነገር ግን እርስ በርሳችሁ ብትነካከሱና ብትበላሉ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ።
16 ነገር ግን እላለሁ፥ በመንፈስ ተመላለሱ፥ የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ።
17 ሥጋ በመንፈስ ላይ መንፈስም በሥጋ ላይ ይመኛልና፥ እነዚህም እርስ በርሳቸው ይቀዋወማሉ፤ ስለዚህም የምትወዱትን ልታደርጉ አትችሉም።
18 በመንፈስ ብትመሩ ግን ከሕግ በታች አይደላችሁም።
19 የሥጋ ሥራም የተገለጠ ነው እርሱም ዝሙት፥ ርኵሰት፥ መዳራት፥
20 ጣዖትን ማምለክ፥ ምዋርት፥ ጥል፥ ክርክር፥ ቅንዓት፥ ቁጣ፥ አድመኛነት፥ መለያየት፥ መናፍቅነት፥
21 ምቀኝነት፥ መግደል፥ ስካር፥ ዘፋኝነት፥ ይህንም የሚመስል ነው። አስቀድሜም እንዳልሁ፥ እንደዚህ ያሉትን የሚያደርጉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።
22 የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ቸርነት፥ በጎነት፥ እምነት፥ የውሃት፥ ራስን መግዛት ነው።
23 እንደዚህ ያሉትን የሚከለክል ሕግ የለም።
24 የክርስቶስ ኢየሱስም የሆኑቱ ሥጋን ከክፉ መሻቱና ከምኞቱ ጋር ሰቀሉ።
25 በመንፈስ ብንኖር በመንፈስ ደግሞ እንመላለስ።
26 እርስ በርሳችን እየተነሣሣንና እየተቀናናን በከንቱ አንመካ።
ቃላትና ሐረጎችን እንዲሁም አባባሎችን ፣ሥልጣን ያገዘፋቸው ፖለቲከኞች ፈልሥፈው ሲጠቀሙበት ወይም በጊዜው ገዢ ከሆኑ መንግሥታት ጋር የተወዳጁ እና የተቆራኙ ምሁራን ለመወደድ ሲሉ፣ ፈጥረው በየዘመኑ ላሉ መንግሥታት ፕሮፖጋንዳ ፍጆታ እንዲውል ሲያደርጉ እናሥተውላለን።
እነዚህንም አሣሪ ቃላቶች፣ የየዘመኑ “አውርቶ አዳሪ ” (ካድሬ) እያሥተጋባ እንጅራ ሲበላበት ነበር።ዛሬም የአንዱ ሥቃይ ለአንዱ ደሥታ መሆኑ ፣ ያባራበት ዓለም ላይ እየኖርን አይደለም ።
“በኮቪድ 19” ፍራቻ የሚናጠው እና የሚቀልደው መሳ፣ለመሳ ሆኖ ነው የምናሥተውለው።(አንዳንዱማ አዲስ የገቢ ምንጭ እንደተከፈተለት በመቁጠር፣ብር፣ብር ሲል እየተሥተዋለ ነው።) ግን፣ግን ቀልድ እና የበዛ ማሥፈራርቾም የትም እንደማያደርስ ሁሉ፣ ቫይረሱን ንቆ በቫይረሱ መቀለድም የቫይረሱ ሰለባ ሊያደርግ እንደሚችልም ለዚህ ሰው፣ ለማሳሳብ እንወዳለን።
ኮቪድ 19 ከኤቦላ የከፈ አደርጎ ማየትም ተገቢ አይደለም።ግና ጥንቃቄ ያሥፈልጋል።የሀገርን መንግሥት የጥንቃቄ መመሪያ ማክበርም ተገቢ ነው።ይሁን እንጂ ከያአቅጣጫው በሚፈበረኩ በሚያሥፈራሩ፣ በሚያሸብሩና፣ በሚያሥደነግጡ ወሬዎች መደናጋጥ እና ያንኑ መልሰን ለሺ ሰው መዝራት እኛንም የበለጠ እንደሚያሸብር መገንዘቡ መልካም ነው።እንደ ቀኃሥ፣ደርግ እና ኢህአዴግ ካድሬ ለጭቆና የሚያመች ወሬ ይመሥል፣ እንደወረደ ማሥተጋባትና እንዲሥተጋባ ማድረግ ፣ያውም ነገ ወደ እኛ ሊመጣ በሚችል የተፈጥሮ ህመም መቀለድ፣ወይም ሰውን በማስደንበር ተሥፋን በማጨለም ጥቅም ለማግኘት መጣር፣ ህሊና ቢስነት ነው።
ሁላችሁም እንደምታውቁት ትላንት፣ ምሁራኑ እና የየሥርዓቱ ባለሟሎች በካድሬዎቻቸው ና በነጭ ለባሾቻቸው አማካይነት ፣ ህዝብ ፀጥ ለጥ ብሎ እንዲገዛ ፣ቻይ ጫንቃ እንዲኖረው የሚያሥችል፣ ህሊናን አሣሪ ቃላት እና አባባሎችን ይፈጥሩ ነበር።በእነዚህ የፕሮፖጋንዳ ቃላቶችም የተነሳ ቀላል የማይባለው ዜጋ አይኑ ይታወርና ቃላቱን እና አባባሎችን ማሥተጋባት ዘወትራዊ ተግባሩ አድርጎት ጭቆናውን ተለማምዶ ፣ለተቃውሞ ሳይነሳ አርፎ ለዘመናት ቁጭ ይላል።
በሦሥቱም መንግሥታት (በቀኃሥ፣በመንጌ እና መሌ) ማሃለው፣እዝጎታው፣ እና የፈንጠዝያው ዜማና ቀረርቶው ሁሉ፣ገዢዎችን የበለጠ ግብዝ እንዲሆኑ የሚያደርጋቸው ነበር።
የዛሬውን ትውልድ የሐሰተኛ ትርክት ወራሽ በማድረግ እንዴት አድርገው የጎሣ ፖለቲካውን ሲያጦዞት እንደነበር ታራክ ዘግቦታል። ( ኮረና ቀዝቃዛ ውሃ ቸለሰባቸውና አቀዘቀዛቸው እንጂ አንዳንድ ፖለቲከኞች አካሄዳቸው ቡከን ጦር አውርድ ዐይነት ነበር )።
ፍፁም የገደል ማሚቴ ና ፓሮት ሆኖ የሐሰት ወሬውን አንድ ከአንድ በመሥተጋባት ለቋንቋውና ለጎሣው በማድላት ወጣቱ አውዳሚ ሆኖ ነበር።ዛሬ ጎሳን፣ቀለምን ቋንቋን የማይለይ፣ሰው መሆን ብቻ ለሱ መሥፈርት የሆነ ኮሮ ና በዓለም ተከሥቷል ሲባል ግን ሁሉም ጎሣ እኮ አንድ ነው፣ሰው፣ሰዎ ነው።የሚያለያየው አንዳችም ነገር የለም ማለት ጀመረ።
ያኔ ፣ትላንት፣ የትውልድ ህሊና በቆዳ ማዋደድ ና በውሸት ፕሮፖጋንዳ ተሞልቶ ሰውን በጭካኔ የገደለበት መንገድ ያናድድ ነበር።
ለምሳሌ ፣በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመን፣
–ፀሐዩ ንጉሳችን ፣ ከፈጣሪ የተቀቡ ናቸው።ፈጣሪ ያነገሳቸው ናቸው እና ከመላእክት እኩል ሊሰገድላቸው የገባል። …”የጠቅል አሽከር!” ተብሎም ይፎከር ነበር።
–ሰማይ አይታረስ፣ንጉሥ አይከሰሥ።… ፀሐዩ ንጉሣችን ወዘተ። ይባልም ነበር።ይህንን የሚቃወም እጣ ፈንታው ሞት ነው።
ደርግ ከኮሚቴነት ከፍ ብሎ ፀሐዩ ንጉስን በህዝብ ብሶት እና በወሎ ድርቅ አሳቦ አውርዶ ፣” አንድ ሰው ብቻ የሚቀመጥበት ዙፋን ላይ” ኮ/ሌ መንግሥቱን ሲያነግሥ ደግሞ፣
–ከአብዮታዊ መሪያችን ከጓድ መንግሥቱ ኃይለማሪያም ቆራጥ አመራር ጋር በቆራጥነት ወደፊት!!
–ፊውዳሊዝምን፣ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝምን ኢፔሪያሊዝምን እናወድማለን!!
–ሞት ለኢህአፓ!
–ሞት ለኢዲዩ!
–ሞት ለቀኝ መንገዶችና ለአናርኪሥቶች!
–በፀረ አብዮተኞች መቃብር ላይ አብዮታዊት ኢትዮጵያን እንገነባለን!!..መንጌ!መንጌ!ጀግናው!ቴዎድሮሱ! ቅብርጥስዬ… ወዘተ።ይባል ነበር።እናም መንጌ ለሥልጣኑ ሲል እጁን በደም ታጥቧል።
በወያኔ/ኢህአዴግ ዘመን ደግሞ፣
–ነፋጠኞች፣ጠባቦች፣የደርግ ርዝራዦች፣ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ፀር ናቸው!
–ስኳር ጓዳችንን አሳስቶታል።…ሙስና አንቅዞታል።
–ቦና ፓርቲዝም ተፈጥሯል! ወያኔን አበሥብሷታል!!…
–ግመሎች ይጓዛሉ ውሾች ይጩኸሉ!!ወዘተ። የሥርዓቱ መሪዎች ሲሉ ፣ ካድሬ ቀበል አደርጎ”በዋነኝነት በቦና ፓርቲዝም በሰብሰናል።ነቅዝናል!።”ወዘተ ይላል።
ደጋግሞ “ግመሎቹ ይጓዛሉ ውሾቹ ይጮኻሉ!!”ይላል።ይኽቺን እንኳ ዛሬም ደጋግመን እንሰማታለን።
የውሾች አገልግሎት ያዩትን ለባለቤቱ መናገር እንደሆነ እየታወቀ ጩኸታቸው ችላ መባሉ ፣ማሰብ ለምንችል ጠያቂዎች አባባሉ ጥያቄ ቢጭርብንም።…
የህግ የበላይነት ባለበት ሀገር ፣ውሾች በግመሎች ላይ “ኡ!ኡ! ..”እያሉ የጩኸታቸው ሰበብ ሳይጣራ ፣ግመሎች ህግ ጥሳችሁ ሂዱ ብሎ የሚፈቅድ ባለሥልጣን የለም።የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ የማይችል ባለሥልጣን፣ ራሱም ተጠያቂ የሚሆንበት ህግ አለ።እናም በዛ ሀገር፣ግመሎቹ የኮንትሮባንድ ዕቃ ጭነው በድብቅ ቢጓዙ ፣ ውሻ በጩኸቱ ጠቁሞ በህግ ቁጥጥር ሥር በማዋል ከመንገዳቸው ያሰናክላቸዋል። የህግ የበላይነት በነገሠበት ሀገር ህግ እየጣሱ እንዳሻኝ እሆናለሁ ማለት አይቻልምና!!
“ግመሎቹ ይጓዛሉ ውሾቹ ይጮኸሉ።” ማለት ፣ከህግ የበላይነት በተፃፃሪ የቆመ አባባል ነው።…
እንደ ውሻ የተቆጠሩት አቅመ ቢሶች ፣ድሆች፣የገንዘብ እና የሥልጣን አቅም የሌላቸው ዜጎች፣እንዲሁም አናሳ ቁጥር ያላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ፣ጎሳዎች ፣ቋንቋዎች፣ ባህሎች ወዘተ ሊሆኑም ይችላሉ።
ከነዚህ በተቃራኒ የሚታዩት ግዙፎቹ ግመሎች ናቸው።በቋንቋ ፣በባህል፣በኃይማኖት፣በህዝብ ብዛት።ወዘተ።የገዘፉ።እናም የገዘፈ እና ጉልበታም ሁሉ ደቃቃዎቹን መጨቆን ፣ጩኸታቸውንም መናቅ መብቱ ነው። እንደማለት ነው።
ቃላት ምን ያህል የሰውን ልብ እንደሚሰብር እና በህሊናም እንደሚጣበቅ ከላይ ባነሳኋቸው ጭብጦች በደምሳሳው እንገነዘባለን። ይህንን ከተገነዘብን ከካድሬ አመጣሽ እና ደጋግሞ ሥለተነገረ ዕውነት ከሚመሥል ሐሰተኛ ከሆነው ሰሞነኛ አሸባሪ ፕሮፓጋንዳ ራሳችንን እንጠብቅ።
ለአንድ ደሃ አገር የአንድ ቀን ሥራ መፍታት ብዙ ያጎላታል።”በኮሮ ና ” ቫይረስ ፣ሰበብ ፣ሙሉ በሙሉ፣ ሥራን መዝጋት እንዲሁም ፣ሠዓት እላፊ ማወጅ ተገቢ አይደለም።እንዲህ ዓይነቱ እርምጃ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል። አሁን ባለንበት ሁኔታ፣ የተቀሳቃሹን ቁጥር ለመወሰን ከከተማ ወደከተማ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን መገደብ(ከነጋዴዎች በሥተቀር ማለት) ፣እምብዛም በዕለት ፍጆታ እና በውጪ ምንዛሪ ላይ ተፅእኖ የማይፈጥሩ አምራች ደርጅቶችን፣ለ15 ቀናት እንዲዘጉ ማድረግ –በየቤታቸው የተኙ ህሙማን ወደ ህክምና መሥጫ ተቋም ሄደው እንዲታከሙ ለማድረግ በየቀበሌው ታማሚ መኖሩን አሠሣ በመድረግ፣ጥቆማ በመቀበል ተግቶ መቀሳቀስ እና በመንግሥት የህክምና መሥጫ ለመታከም የሚመጣን ህመምተኛ ፣አሁን ከተቀመጠው የህክምና ዋጋ ቀንሶ ማከም፣በኮሮና ተጠርጣሪን ለይቶ በነፃ እንዲታከም ማድረግ ያሥፈልጋል።
በየቀኑ የምንሰማውን የጥንቃቄ እርምጃ ሳንዘነጋ፣በልክ የለሽ ፍርሃት በጭንቀት አንዳንሞትም ሥለ ኢንፍሎንዛ መሠሉ የመተንፈሻ አካል ሠንጎ በመያዝ ፅኑ ህመም ሥለሚያሥከትለው ኮቪድ 19 (ኮረና) በቂ ግንዛቤ ለማግኘት ጥረት እናድርግ እንጂ ጥራዝ ነጠቅ አንሁን።ይህ በሽታድንበር ተሻግሮ የመጣብን፣ በአንድጊዜ በዙ ሰውን ለመያዝ የሚችል በትንፋሽ እና ባልታጠበ እጅ ፊትን በመነካካት የሚተላለፍ በሽታ ቢሆንም ፣የተያዘ ሁሉ በበሽታው እንደማይሞትም መገንዘቡ መልካም ነው።
የኮቪድ 19 ክፋቱ፣በሀገራችን ማን እንደተያዘ እና ማን እንዳልተያዘ ለማወቅ ያለመቻሉ ነው።ወሬውን አሥፈሪ እንዲሆን ያደረገውም ይኸው ነው።ዛሬ ሁሉም ሰው ሀሉንም ሰው ነው በጥርጣሬ የሚያየው። እርስ በእርስ በጥርጣሬ መተያየት መጀመሩ መልካም ነው። ማን ይያዝ ማን ነፃ ይሁን ከቶም አይታወቅምና !!
የቫይረሱን ሥርጭት ለማወቅ እሥከ ሚያዚያ 4 (እሥከ ሆሳእና መጠበቅ ያሥፈልጋል።በእርግጠኝነት መፅናናት ላይ የምንደርሰው አልያም የበለጠ የምንጠነቀቀው ቀጣዮቹ አሥራ አምሥት ቀናቶች ሲደመደሙ ነው።
በበኩሌ በፋሲካ የምስራች እንሰማለን።ባይ ነኝ። (የአሜሪካ ፕሬዝዳንት በቻ በጎ አላሚ ይሁኑ ካላላችሁ)መልካም ማሰብን ማንም አይከለክለኝም።የእኛንም ከኃጥያት መራቅና መፀፀት፣ በይበልጥም የፃድቃንን ፆምና ፀሎት ክርስቶስ ኢየሱስ ተመልክቶ ምህረት ያደርግልናል። ብዬ አምናለሁ። እንሆ የምንሰማቸው የሳይንስ ግኝቶችም ተሥፋችንን አለምላሚ፣ሥጋታችንን ቀናሽ ናቸው።
የእሥትንፋሥ ችግር ላለው የሚረዳ ኦክስጂን መሥጪያ ቀላል የእጅ መሣሪያ እና ለዓለም ተደራሽ የሆነ ቫይረሱ እንዳለብን እና እንደሌለብን የሚያውቅ ተቀሳቃሽ መመርመሪያ መሣሪያ መፈልሰፉን እና ይሄ መሣሪያም አጠቃላይ ውጤቱን በ15 ደቂቃ ውስጥ መሥጠት እንደሚችል ተበሥሯል።የመመርመርያ መሣሪያው በሣምንታት ውስጥ ገብያ ላይ እንዲውልም የየኩባንያዎቹ ሣይንቲሥቶች እና አምራቾች ሌት እና ቀን እየሰሩ ነው።
ከሁለት ወር በኋላ ከኮቪድ 19 ፍሉ ዓለም ትረጋጋለች ተብሎም በሣይቲሥቶቹ ይታሰባል። የታሰበው ከሆነ መልካም ነው።ካልሆነ ግን የኢትዮጵያ የ2012 ሀገራዊ ምርጫ በታቀደለት ጊዜ ይከናወናል ተብሎ አይታሰብም ዝንጀሮዋ መጀመሪያ የመቀመጫዬን አለች አሉ።ወዳጄ ሥንኖር እኮ ነው መምረጥም ሆነ መመረጥ የምንችለው። …
ኮቪድ 19 የመተንፈሻ አካልን ክፉኛ የሚያጠቃው ቫይረስ ፣በቁጥጥር ሥር ሳይውል ከሁለት ወር በላይ ከፈጀ ግን ፣የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መክሮበት ምርጫውን ፣ከአቅም በላይ በሆነ እና የህዝብን ህይወት አደጋ ላይ በሚጥል ተላላፊ በሽታ አሥገዳጅነት ምርጫውን ወደ 2013 ዓ/ም ማሸጋገር መገደዱ አይቀሬ ይሆናል።
ምክንያቱም ከሰው ልጅ የመቆጣጥር አቅምና ችሎታ በላይ ሆኖ በሣይንሥ ተራቅቄያለሁ የሚሉትን አውሮፓን እና ታላቋ አሜሪካን እንኳን ክፉኛ አሥጨንቆ ያለውን ቫይረስ መናቅ ከቶም አይቻልምና!! ተቃዋሚ ወይም የመንግሥትን ሥልጣን ለመያዝ የሚፎካከሩ ወይም ሠላማዊ ውድድር የሚያደርጉ፣ ” ህዝብን ሰብስበን የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ ካልቻልንና ያለንን የተለያዩ ፖሊሲዎችን ለመራጩ ዜጋ በማሳወቅ እንዲመርጠን ካላማለልነው፣ ነሐሴ ላይ ቫይረሱ ባይኖር እንኳ ምርጫ ማካሄድ እንዴት እንችላለን ?” ብለው መጠየቃቸው ሥለማይቀር መርጫው በ2012 ላይካሄድ ይችላል።
በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ቫይረሱ በዓለም ደረጃ በቁጥጥር ሥር እሥካልዋለ ና የዓለም ጤና ድርጅት፣ ሰው ልጅ ቫይረሱን በቁጥጥር ሥር ማድረጉን በይፋ እሥካላሳወቀ ጊዜ ድረስ በኢትዮጵያ እንኳን ምርጫ ፣ትምህርትም አይኖርም።… ይሁን እንጂ እንደ አሜሪካና ኢጣሊያ አይነት ሞት በእኛ ሀገር ይከሰታል የሚል ሃሳብም ግምትም የለኝም።ምንም በሉ ምንም በግሌ በፈጣሪ ተሥፋ ቆርጬና አምላኬን ጨካኝ ብዬ አላውቅም።ነገር ግን “ነገር ሁሉ ለበጎነው ነው እላላሁ። “ወዳጄ በሜጫ እና በጠመንጃ የተደገሰልህን ድግሥ ጌታ በጥበቡ እንዳሣለፈልህም እወቅና ጥንብ ከተባለው ዘረኝነት ራሥህን አፅዳ።
አየኸ አይደል ሞትና በሽታ ኃያላንን እና ቀብራሮችን ሲያንበረክኩ ?! የኢንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒሥቴር –የእሥኮትላንድ ልኡል ቢሆኑ እንኳ ከኮሮና አላመለጡም።ነገም ከተፈጥሯዊ ሞት አያመልጡም።በጊዜያቸው ይሄዳሉ።ሁሉም በጊዜው ሞት ያግዘዋል።ያለጊዜያችን እንዳንሞት ንፅህናችንን እንጠብቅ።ርቀታችንን እንጠብቅ።ተጠንቅቀን እናሥል።ያለአለማ አንጦልጦል። በቂ እረፍት እናድርግ።ምግባችንን አብሥለን እንብላ።ቀዝቃዛ ውሃ አንጠጣ።…
ያለጊዜ ከሚወሰድ ሞት እግዚአብሔር የኢትዮጵያን ህዝብ ይጠብቅ።…