ከወደ መቀሌ ለወራት ስንሰማው የነበረ ጦር አምጣ የሚመስል ነጋሪት አዕምሮዬ ውስጥ ጥያቄ አጫረብኝና ትግራይን እንዴት አውቃት እንደነበር መፈተሽ ጀመርኩ፡፡ ሕወሐት ሃያ ሰባት አመት ኢትዬጵያን በብቸኛነት ሲዘውር ቆይቶ መቀሌ እራሱን ካጋዘ ሁለት አመት ሊሞላው ነው፡፡
አዲስ አበባ በነበረበት ጊዜ የወያኔ ጸሐፊዎች(ደራሲዎች) ያ ህዝብ እነዴት ታላቅ እንደሆነ ደጋግመው አሰነብበውናል፡፡ የ ዶ/ር ሀብተማርያም አሰፋ “የኢትዬጵያ ታሪክ ባህሎችና ወጎች”ና የቀድሞው የአዲስ አበባ ደህንነት ኃላፊ የነበረው ብስራት አማረ የደረሰው “ፍኖተ ገድል” መጽሐፍት ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ዶ/ሩ የትግራይ ህዝብ ልዩ የሆነ ህዝብ መሆኑንና ሌላው ህዝብ በተለይ አማራው የትግሬ ቅጂ መሆኑን በመጽሐፋቸው አሰነብበውናል፡፡ ምንም እነኳን ደራሲው በኢትዮጵያ ስም መጽሓፋቸውን ቢጽፉም የመጽሐፋቸው ጥቅል ሃሳብ የትግራይን ህዝብ ታላቅ መድረግና አማራውን እስከነ ቋንቋ(የአህዮች ቋንቋ በእሳቸው ትረጓሜ) የትግራይ ጭማቂ መድረግ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የአክሱም ስልጣኔ የትግሬዎች ብቻ መሆኑን ገልጾ ሌላው ህዝብ ዝቅተኛ መሆኑንና አንድ የትግራይ ተወላጅ በጦርነት ግዜ ለሌላው አምስት ስድስት ኢትዮጵያዊ በቂ መሆኑን በትዕቢት ጽፏል፡፡ ከእነዚህህ መጽሐፍት በተጨማሪ ወያኔ ስልጣን ላይ በቆየበት ዘመን ፀረ አማራና ኢተዮጵያ የሆኑ ግጭት ቆስቆሽና ነገር ለኳሽ መጽሐፍት የትግራይ ተወላጅ የሆኑ ሰዎች ጽፈዋል፡፡ እንዲህ ያሉ ጽሁፎች የትም ይጻፉ የት የተጻፈበትን ህዝብ ይወክላሉ ማለት ባይቻልም ዛሬ የምናየው ችግር ላይ የእነሱ የዞረ ድምር ውጤት እነዳለ አሌ የሚባል ነገር አይደለም፡፡
እንዲህ ያሉ ከበታቸኝነት ስሜት(Inferiority complex) የሚመነጩ ጽሁፎች ዛሬ ላይ ህያው ሆነው፣ ግዝፍ ነሰተው ከወደ መቐሌ በመሪዎቻቸው ዘንድ ሲቀነቀኑና በሚዲያ ሲሰተጋቡ ይታያል፡፡ ወያኔ አሁን ተልሞት የተነሰው የፖለቲካ ቅዠት የሞት ጣር መጀመሪያ መሆኑ ቆይተን የምናየው ቢሆንም ኋላ ግን እንደለመዱት በቆሸሸ አፋቸው አማራ ድረስ፣ ኦሮሞ ድረስ…( አማራ አሎ በሎ፣ ኦሮሞ አሎ በሎ…) ቢሉ የሚዋጣቸው አይሆንም፡፡ የሕወሃት ይለይልንና እንገነጠላለን ዲሰኩርን ስሰማ ከሃያ አመት በፊት የነበብኩትን ግጥም ያስታውሰኛል፤
ድንኳኔን ትከሉ፣
ፍራሼን አውርዱ፣
ዘመድ አዝማድ ይምጣ ሁሉም ተቀስቅሶ
ለገዛ እራሴ ሞት ልቀመጥ ነው ለቅሶ፡፡
አሁን ጥያቄው መሆን ያለበት ሕዝቡስ ምን ይላል ነው፡፡ ወያኔው እነደሆነ ሕዝቡን በመጡብህ ተከበብክ ፍርሃት ቀይዶ ለእኩይ አላማው ሊያሰግደው እነደታተረ ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ሰሞኑን የአማራና የትግራይ ሙህራን በህዝቦች መካከል ያለውን መራራቅና ግጭቶቾች ችግርን ለመፍታት የጀመሩት መነጋገር የሚበረታታ ቢሆንም የችግሩን ምንጭ አድምቶ ያልመረመር ሆኖ አግኘቼዋለሁ፡፡
አሁን ወደምኖርበት ካናዳ ከመምጣቴ በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ከሃያ አመት በላይ መምህር ሆኜ አገልግያለሁ፡፡ በግሌ ወደ ትግራይ ከተጓዝኩት ግዜያት ውጭ ያኔ ኢህአድግ በተከፈለበት ግዜ በ1993ዓ.ም. እና 1994ዓ. ም. የ 2ኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ተቆጣጣሪ ሆኜ ትግራይ ሄጄ ነበር፡፡
1993 ዓ. ም. ወደ አዲ ረመጽ የፈተና ጣቢያ ከጎንደር የተንቀሳቀስነው ባለ ሁለት ጋቢና ፒክ አፕ ከሽሬ ይዘው በመጡ ሁለት ፖሊሶችና አንድ የት/ ቢሮ ተወካይ ታጅበን ነበር፡፡ በግዜው በአርማጮና ወልቃይት-ጠገዴ የአርበኞች ግንባር ይንቀሳቀስ ስለነበር ነው እጀባው ያስፈለጋቸው፡፡
መጀመሪያ ወደ ሁመራ ሄደን ፈተናውን ሁመራ ፖሊስ ጣቢያ አሳደርነው፡፡ በዚያ ወደ አስራ ሁለት የሚጠጉ የአርበኞች ግንባር ወታደሮች ጋጣ በሚመስል ማጎሪያ ውስጥ ታስረው አይቼአለሁ፡፡ በጣም የሚገርመው አጋጣሚ ደግሞ ከተሳሪዎቹ መካከል አራት ኪሎ ዩንቨርሲቲ የማቀው የኔ ጁኒየር የነበረ አራት ኪሎ የኢትዮጵያ መጽሐፍት ድርጅት አካባቢ የማይጠፋ የባህርዳር ልጅ ነበር፡፡
እነደተያየን ትንሽ ወረቀት ጠቅልሎ ቢወረውርልኝም፤ ለእይታ የተጋለጥኩ እንደሆንኩ ስለተስማኝና ታሳሪዎቹ በጠቅላላ አንድ ዓይነት ናቸው ብዬ ስላለመነኩ ምንም ነገር ላደርግ አልሞከርኩም፡፡
በበነጋታው ባኽርን አልፈን ቃፍታ ያአካባቢው ሰዎች አንደሚጠሯት “ናይ ትግራይ ሓፍቷ”(የ ትግራያ እህቷ) አመራን፡፡ ከዚህ በኋላ እሰከ አዲ ረመጽ የነበረው መንገድ አይረሳኝም፡፡ የዚያኔ መንግዱ ያሳልፍ የነበረው አንድ መኪና ብቻ ነበር፡፡ በግራና በቀኙ ያሉ፣ እግዚአብሄር እንዲህም መስራት እችላለሁ ብሎ የሰውን ልጅ ለማሰፈራራት የፈጠራቸው የሚመስሉት፣ ጫፋቸው ሾሎ ዳመና የታከከ ተራሮች ደፍሮ ለማይት የከተማ ወኔ በቂ አንዳልነበር ያኔ ውስጤ የተሰማኝ ፍርሀት ያስታውሰኛል፡፡
የቀድሞው ታጋይ ሹፌራችን ነበር የደህንነት ኃለፊ ክንፈ ገ/መድኅን መገደሉን ከመኪናው ሬዲዮ በትግርኛ ከሚተላለፈው ዜና ሰምቶ በከፍተኛ ቁጭት ተሞለቶ የመኪናውን መሪ ደጋግሞ እየመታ የነገረን፡፡
አንደማይደርስ የለም አዲ ረመጽ ከሰአት በኋላ ደረስን፡፡ ፈተናውን ለመራገፍ መኪናው ሲቆም በአካባቢው የነበሩ በግምት ከአስራ ሁለት እስከ ሃያ አመት የሚሞላቸው ልጆች መጡ፣ መጡ ይሉን ጀመር፡፡
“ይህ ሁሉ ወጣት የኛን መምጣት ይጠባበቅ ነበር እንዴ?” ስል እራሴን ጠየቅሁ፡፡ ግራ መጋባቴን ያየው የት/ቢሮው ሰው ፣አባዲ፣ ትግሬዎቹ መጡ ነው የሚሉት ብሎ አብራራልኝ፡፡
በባድሜ ጦርነት የተሰዉት የአዲ ረመጽና አካባቢው ልጆች የዚያን ሰሞን ነበር መንግስት ለወላጆቻቸው መርዶ ያረዳቸው፡፡ ምንም እንኳን የትግራይ ክልል ውስጥ የተካለሉ ቢሆኑም እርማቸውን በገበያ ስፍራ ላይ የወጡ የነበረው ግን በአማርኛ ቋንቋ እያለቀሱ ነበር፡፡
በግንቦት ቃጠሎ ባየኋት በለምለሚቷ አዲ ረመጽ አልሞ ተኳሸነት፣ የወንድነት መገለጫ እነደሆነ ነው ወልቄዎች ሳይጠራጠሩ እሚናገሩት፡፡ በደርግም ይሁን በኢሕአዲግ ጊዜ ወታደር የነበሩ ሁሉ አመሻሽ ላይ የወታደር የደንብ ልብሳቸውን ለብሰው ቢራን ጨምሮ “ ፍርቃፍርቂ”(ግማሽ ማር ግማሽ ጠላ) የሆነውን የማር ጠላ ለመጠጣት በየመሸጪያው ቤት ይታደማሉ፡፡ እኔም ፍርቃፍርቂ ለመጠጣት በታደምኩበት ስፍራ ሁሉ አዘውትሮ ሲዘፈን የሰማሁት የአማርኛ ዘፈን እዚያው ጎነድር ውስጥ የተቀነባበረ(ይመስለኛል) “አልማዜ” የሚል ዘፈን ነበር፡፡
እራሳቸውን ወልቄ-ጎንደሬ ብለው በኩራት የሚጠሩት አዲ ረመጾች በአማርኛ ዘፈኖች ሲውረገረጉ በፍጹም ከውስጣቸው መሆኑን ለተመለከታቸው ሁሉ ግልጽ ሆኖ የሚታይ ነው፡፡ በቆይታዬ ወልቄዎች ህወሓት ኢድዩን እንዴት አባሮ አካባቢውን እንደተቆጣጠረ ገልጥውልኛል፡፡ የእርስ በርስ ጦረነቱ ትቶቸው የሄደው ምልክቶችም በየቦታው ይሰተዋላሉ፡፡ እማልረሳው የኪዳነ ምህረት ቤ/ክርሰቲያን ደውል ከአውሮፐላን የተጣለ ቦምብ የላይኛው ክፍል ነበር ፡፡
ለሁለተኛ ግዜ የ2ኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ይዤ ወደ ተግራይ የተጓዝኩት መቀሌ- ኩዊኻ 1994 ዓ.ም. ነው፡፡ ግዜው የነ ስዬ ቡድን ተሸንፎ መለስ የበላይነቱን የአረጋገጠበት ወቅት ነበር፡፡ በአንድ መስመር ላይ የነበርን የፈተና ጣቢያ ተቆጣጣሪዎች በአንድ አውቶቢስ ነበርን የተጓዝነው፡፡ ገና ራያና ቆቦን ጨርሰን ትግራይ ክልል ውስጥ የሆነውን ራያና አዘቦን ጀምረን አውቶቡሳችን ትንሽ መንደር ላይ ሲቆም ትንንሽ ልጆች መጥተው አውቶቡስን በመክበብ ወለዬ መሆናቸውን ይነግሩን ጀመር፡፡ በኋላ የማይጮው ጣብያ ኃላፊ የነበረው የያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት መምህር ጋር ሆነን ማይጮው ላይ ሆቴል ውስጥ ያገኘናቸው ነዋሪዎች እንዲሁ እራሳቸውን ከትግራይ ለይተው ከላይ ከትግራይ የመጡ ሰዎች እያሉ ሲያወሩ ሰምቼለሁ፡፡
በቀጥታ ወደ መቀሌ ሄደን ነበር ወደ ኩዊኻ የተመለስነው፡፡ ከአዲስ አበባ ከሄድነው ሌላ አንድ የፈተና ጣቢያ ተቆጣጣሪ ከመቀሌ ዩንቨርሲቲ ተመድቦልን እሱን ይዘን ወደ ወደ ኩዊኻ ተመለስን፡፡ ፈተናውን ፖሊስ ጣቢያ ስናራግፍ አንድ ሽማግሌ ሰው በዚያ ታስረው አየን፡፡
ከመቐሌ የመጣው መምህር እኚህ ሰው መምህርና የስዬ ደገፊ መሆናቸውን ነገረን፡፡ የመለስ ደጋፊዎች የእህል ክምራቸውን አቃጥለውባቸው ስለነበር እሳቸውም በተመሳሳዩ የነዚያን እህል ክምር አቃጠሉ፡፡ በዚህን ግዜ ጠላቶቻቸው እሳቸው የሚያሰተምሯትን የአስራሁለት አመት ልጅ ደፍረዋል በሚል በተቀነባበረ ሴራ አሳሰሯቸው፡፡
በትግራይና ኤርትራ በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ የቀድሞ ወታድር ልጆች አሉ ለሚባለው ነገር ኩዊኻ አይነተኛ ምሳሌ ትሆናለች፡፡ ይህንነ የተገነዘብኩት ተማሪዎችን በየመፈተኚያ ክፍላቸው ከቼክ ሊስቱ ላይ መመደብ ስንጀምር ነው፡፡
ገ/እግዚአብሔር ደቻሳ፤ ኪሮስ ጥጋቡ…የመሳሰሉ ስሞች በተደጋጋሚ አጋጥሞኛል፡፡ በኋላ ጠይቄ እነደተረዳሁት በደርግ ግዜ ኩዊኻ ላይ የቀድሞው ጦር ካምፕ ነበር፡፡ አሁንም ቢሆን መቐሌ የሚገኘው አየር ኃይል በኩዊኻ ነው የሚገኘው፡፡
ዛሬ ላይ ሆኜ ሳስበው ደራሲ ሰለሞን ደሬሳ በአንድ ወቅት በኢቲቪ ቀርቦ የተናገረውን ቁም ነገር ያስታውሰኛል፡፡ ይኸውም አንድ ሰው እንዴት ንጹህ አማራ ወይም ትግሬ ነኝ ሊል ይችላል ስንት የኦሮሞ ከብት አርቢ በአማራና ትግራይ መሬት ላይ ከብቶቹን ነድቷበታልና፡፡ እንዲሁም እንዴት ንጹህ ኦሮሞ ነኝ ማለት ይቻላል ስንቱ ነፍጠኛ በሴት አያቶቻችን ደጅ መሳሪያውን እየነቀነቀ አልፎልና የሚለው ነው፡፡እውነት ነው ተጠየቁ(Logic)፤ብሔሮች በታላቋ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚያንፀባርቁ ዕንቁዎች እንጂ ታላቋ ኢትዮጵያ ከብሔር ብሔረሰቦች ውስጥ ተፈልቅቃ የምትወጣ ጥፍጥሬ አለመሆኖን ነው የሚያስረግጥልን፡፡ ቢያንስ ላለፉት አንድ ሺህ አመታት በኢትዬጵያ ውስጥ በጦርነት፣ ረሃብና ስደት ማን ያልተደባለቀ ህዝብ አለና?
ዲቃላ ለሚለው የዘመኑ አክራሪ ብሄርተኞች፤የየትም ፍጪው ሥልጣኑን አምጪው ፈላስፋዎች ፣ የሰለሞን አባባል ማለፊያ እውነት ነው፡፡ አሁን ባለንበት ወቅት ለሚያልፍ ግዜ ህዝብን ከህዝብ ጋር አጋጭተው የማያስፈልግ መስዋትነት ለሚያሰከፈሉ፣ በዝቃጭ ታሪክ ተዋናይነት የልጅ ልጆቻቸውን አንገት የሚያስደፋ ታሪክ ለሚተዉ ፖለቲከኞችና አክቲቪሰቶች፤ ሳይንስ በዘረመል(ዲኤን.ኤ)ጥበቡ እነደሚፋረዳቸው እርገጠኛ ነኝ፡፡
ፈተናው እንዳለቀ ወደ አዲስ አበባ ከመመለሳችን በፊት የሁለት ቀናት ግዜ አግኝቼ ስለነበር ፈተናውን ፖሊሰ ጣብያ ቆለፈንበት እኔ አክሱም ደርሼ ወደ ውቅሮ እንዳ አብርሃወ አጽብሃ ውቅር ቤ/ክርሰቲያን ለጉብኝት አመራሁ፡፡
አዲግራት ላይ ያገኘኋት የሰታትሰቲክስ ሰራተኛ ጉዞዋ ወደ አብርሃወ አጽብሃ ከተማ ስለነበር ከውቅሮ እስከ አብርሃወ አጽብሃ ከተማ ድረስ ያለውን ሃያ አራት ኪ. ሜ. እየመራችኝ በእግራችን ተጉዘን እከተማው ደረስን፡፡ በዚያ ወጣት ወንዶችና ሴቶች የአንደኛ ደረጃ መምህራን ተቀበሉን፡፡ መቼም የትግራይ ህዝብ ደግና እንግዳ ተቀባይ መሆኑን በቀደሙት ጉዞዎቼ አውቅ ስለነበር አልተገረምኩም፡፡ እነሱ መደብ ላይ ተቀምጠው የመሃል አገር ሰው ስለሆንኩ ብቻ ከጎረቤት ወንበር አስመጥተው አሰቀመጡኝ፡፡ ከሚበላውም ከሚጠጣውም ያላቸውንና የተሻለውን ለእኔ እንሆ አሉኘ፡፡ እንዲህ አይነቱ መስተንግዶ በኢትዮጵያ ገጠራማ አካባቢዎች የተለመደ ቢሆንም የትግራዩ ግን ለየት ይላል፣ እግር እንጠብ እስከ ማለት ይደርሳል፡፡
ውቅር ቤተ ክርሰቲያኑን ጎብኝቼ ከተመለስኩ በኋላ የቅዳሜ ከሰዓት በኋላ ፐሮግራማቸውን ተቀላቀልኩ፡፡ ነገሩ በሳምንት አንድ ቀን አማርኘን ይጫወታሉ፡፡ ጨዋታው ሃሳብን አሟልቶ በአማርኛ መግለጽ ነው፡፡ ተሳስቶ ትግርኛ የደባለቀ ይቀጣል፡፡ ነጭ የሃውዜን ጠላችንን እየጠጣን ጨዋታው ሞቀ፡፡ ይህ ሁሉ የሚሆነው አስተናጋጂያችን መርዓዊት የምትባል አንዲት የጥቁር ቆንጆ ቤት ነበር፡፡
መርዓዊት በመሃል ጨዋታችንን አቋርጣ ”ከመይ ገይሬ…“ (ይህን እንግዳይን እንዴት አድርጌ ብላ ልበለው?) አለቻቸው፡፡ እሷ አማርኛ መናገር የዳግታታል፡፡ ሁሉም በአንድነት ይሰማል አሏት፡፡ አንድ ቤተሰቦቹ የኤርትራ ተወላጅ የነበሩ የልጅነት ጓደኛዬ ቤት የለመድኩትን ትግርኛ አሞጥጬ ስናገር ስለሰሙ ነበር እንዲህ ያሉት፡፡ ከዚያም መርዓዊት “ብልዓ” አለች፡፡ በልቤ አይ ትግርኛና አማርኛ እያልኩ በቲማቲም ከተፈረፈረው እንጀራ ላይ አንድ ሁለቴ አነሳሁለት፡፡
በመሐል ልጆቹ በሚመረጡት የተግረኛ ዘፈን ተጨቃጨቁ፡፡ ይሰማ የነበረው የኤርትራ ሙዚቃ ነው፡፡ የ አድዋ ተወላጅ የነበረው ርዕሶም ትንሽ ስለ ድንበር ግጭቱ ተናግሮ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ምን ግድግዳ ቢሰራ ትንሽ መስኮት ያሰፈልጋል አለ፡፡ ይሄን ግዜ ለምን የሚል ጥያቄ አቀረብኩለት፡፡ ያው የትግርኛ ሙዚቃ እንዲያቀብሉን ነዋ ብሎ ሁላችንንም በአንድነት አሳቀን፡፡
ወሬ እየሞቀ ሲመጣ ስለ ጥንት ትግራይ ማንነት ሲወራ ሙሉጌታ የሚባል የእንደአባጉናን ልጅ እናንት የላሰታ ወታደሮች ዝርያ ናቸው ብለው በታሪክ ሃዲድ ስምንት መቶ አመታት ወደ ኋላ መልሰው ጥንተ ምነጩን ነገሩት፡፡ እሱም መልሶ ለርዕሶም የአድዋ ሰው አባቱን ጠርቶ አያቱን አይደግም ብሎት አረፈ፡፡ ለካስ ነገሩ ሲገባኝ፣ በአድዋ ጦርነት ግዜ ከመሀል ሀገር የሄዱ ብዙ ወታደሮች እዚያው ቀርተው ከሀገሬው ጋር በመደባለቅ አያቶች ሆነዋል፡፡
እኔና የፈተና ጣቢያ ኃለፊው መቐሌን ለቀን ወደ አዲሰ አበባ ከመምጣታችን በፊት በአንድ የምሽት ክበብ ታድምን ነበር፡፡ የሰከኑና ቀለም የዘለቃቸው የሚመስሉ ታዳሚዎች በየሶፋ ላይ ተቀምጠው ይጫወታሉ፡፡ ከምሽቱ አንድ ሰአት የገባው ማሲንቆ ተጫዋች ግጥም እየተቀበል ይዘፍን ጀመር፡፡ ነገሩ ወደ ፖሊቲካ ተቀይሮ የመለስ ደጋፊዎች “እሸው፣ ደግመህ እሸው እሽት እሽት…” የሚል ግጥም ያቀብሉ ጀመር፡፡ በነበረው ሂደት እዚያ ቤት ውስጥ ስዬ አብርሃ ብዙ ደጋፊዎች እነደነበሩት መገንዘብ ችዬለሁ፡፡
ከዚህ ጉዞ ሁለት አመት በኋላ የማሰተምርበት የቴክኒክና ሙያ ተቋም ውስጥ ከሶስት የትግራይ ተወላጅ መምህራን ጋር ጠዋት ስራ ከመጀመራችን በፊት ፀሐይ እየሞቅን ስናወራ፣በትግራይ ካደረግኳቸው ጉዞዎች ተሞክሮ በመነሳት በትግርኛ አነጋገር ዘይቤ ውስጥ ስላለው ልዩነቶች እንዲያስረዱኝ ጠየኳቸው፡፡ የአድዋ ተወላጅ የሆነችው መምህርት ፈጠን ብላ የኛ ትግርኛ ልክ እንደ ኤርትራ ነው፡፡ የእነዚህ ግን፣ የአዲግራቱን ተወላጅ እያሳየች ንግግራቸው አይገባንም በማለት አብራራችልኝ፡፡
ሌላ ሁለት አመት አልፎ የ1997- 98ቱ ግርግር ሆነ፡፡ በ1998ዓ.ም. መጨረሻ ላይ የተቋሙ የመምህራን መለያያ ግብዢያ ላይ መምህራኑን ያሰተናግድ የነበረው የአዲግርዓት ተወላጅ መምህር ወደ እኔ ጠጋ ብሎ “በትግርኛ በግ ማለት ምንድን ነው?” ብሎ ጠየቀኝ፡፡ እኔም የቀዳልኝን ድራፍት እየተጎነጨሁ ወደ ኋላ በሃሳብ ነጉጄ ደጓን መርዓዊት እያስታወስኩ “በግዒ“ ብዬ አልኩት፡፡ እሱም መልሶ “ታነቅክ እንጂ ምን አመጣህ? ” አለኝ፡፡
ይህ መምህር ታላቄ ቢሆንም ዝም ብዬ ማለፍ አልፈለግኩም፡፡ እኔም በተራዬ እጁን ያዝ አድርጌ አንድ የወሌዬዎች ታሪክ ልንገርህ አልኩት፡፡ ተስማማ፡፡ በወሎ ሼህ ሁሴን ጅብሪል የሚባሉ ሰው ነበሩ፡፡ የወደፊቱን ትንቢት ተናጋሪ ናቸው ይባላል፡፡ ታዲያ ይሄን የሚያደርጉት የማር ብርዝ እየጠጡ ነው፡፡ ሽንታቸው ሲመጣ ትንሽ ገበቴ ላይ ይሸኑና ለካደሚያቸው ወስዶ እንዲደፋ ይሰጡታል፡፡ ምልልሱ የሰለቸው ካዳሚ ኤጭ ሲል ሰሙት፡፡ እሳቸውም፣ ከዚህ ወዲያ እኛ እንጠጣለን አንተ ትሸናለህ አሉት ይባላል፡፡ እንዳሉትም ሆኖ ሽንታቸው ሲመጣ እሱ እየወጠረው ይሸና ጀመር፡፡ ይህ መምህር ቀልድ አዋቂ ስለነበር ጣቱን አወዛውዞብኝ እየሳቀ ሄደ፡፡ በዚህ አባባሌ ጥርስ የነከሰብኝ ሌላ መምህር እንደነበር ኋላ ነው ያወቅኩት፡፡
አሁን ትግራይ ክልል ውስጥ የሚሰማው፣ልጡን ሁሉ እባብ ነው እያሉ ፣ህዝብን በፍርሀት ቀይዶ እራሳቸውን ላጋዙ ሙሴ-ጦርአምጣዎች( ሙሰኛ ጦርአምጣዎች) ፖለቲካዊ መደላድል መፍጠር እኩይ ትርክት፣ መችየቱ ካልታወቅ መፍትሔውን መፈለግ ቀላል አይሆንም፡፡ እባብም ካለ በልጥም ከተበረየ የመጀመሪያው ጥያቄ መሆን ያለበት ለረጅም ዘመናት አብሮ የኖረውን ህዝብ ለመጋደል ትንታግ ያደረገውን ርዕዬት በዚህች ዘመናዊቷ ኢትዬጵያ እነማን ቀድመው ዘሩት ነው፡፡ ይህ ሲመለስ ሃቅና እርቅ ይከተላል፡፡ ለእውነተኛ ይቅርታ መንገዱን ይከፍታል፡፡
ሙሑራን በርቱ እንደ ብስራት አማረ ያሉ ደራሲያንን( ሰውዬው መጽሐፉን ሲጽፍ የ ፒ.ኢች.ዲ ተማሪ እነደነበር አምብቤለሁ) እንደ እራሳቸው አፈ ቀላጤ የሚቆጥሩ ከአዲስ አበባ ተመላሽ ህወሃቶች ላይ የሰላ ብዕራችሁን ማንሳት ብቻ ገዜው የሚጠይቀው መፍትሄ አይደለም፡፡ በተደራጀ መልክ ሃሳባቸው ሊሞገት ይገባል፡፡ ለሃያ ሰበት አመታት ለፖለቲካ ትርፍ ሲባለ የተነዛውን እኩይ ሞገድ ደግም አየር ላይ እንዳይውልና እንዳይሰተጋባ ካላመከንነው መቼም ሰላም ማግኘት አንችልም፡፡ እኒህ መቐሌ የጦርነት ነጋሪት ሲጎስሙ የምንሰማቸውና የምናያቸው ሁሉ ”ፍኖተ ገድል“ አዲስ አበባ ላይ በተመረቀበት ቀን በቦታው ላይ ተገኝተው አሁን ገና እውነተኛው ገድላችን ተፃፈ ሲሉ የነበሩ ናቸው፡፡ መለስ ዜናዊ እምረቃቱ ላይ መገኘቱን እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ በዚያው አመት መሞቱን ግን አስታውሳልሁ፡፡ የልዩነት ግድግዳን አፍርሰን ወደፊት ለመንጎድ መስፈንጠሪያው የመቀሌ ጆሴፍ ጎበልሰች አሰተሳሰብን መቀበር ነው፡፡ ከዚያም እነሱን ተከትለው የሚያሰተጋቡ የገደል ማሚቱዎች ሁሉ ፀጥ ረጭ ይላሉ፡፡ ከዚያም እንሆ ብዙ ሰላም ለኢትዬጵያ…
ተዛማጅ ንባብ semnaworeq.blogspot.com/2012/05/semnaworeq.html
አስቻለው ከበደ አበበ ሜትሮ ቫንኮቨር ካናዳ