ሚኪያስ ጥላሁን – ኢሜይል
[email protected]
ይህች መልዕክት የተጻፈችበት መነሻ ሃሳብ አንድ ነው፤ ወይንም አንድ ሆኖ በሁለት ተከፍሎ የሚታይ ነው፡፡
አንደኛው፤ ‹‹ባልደራስ ለዕውነተኛ ዴሞክራሲ›› የፓርቲነት ህልውናውን (ከምርጫ ቦርስ ሰርተፊኬት ባያገኝም) በመስራች ጉባዔው ማወጁን ተከትሎ የሚጠበቅበትን ውዝፍ የቤት ስራ ማስገንዘብ ነው፡፡ ማለትም ሊያቃልላቸው ግድ የሚሉትን ግዴታዎችን በስሱ ማሳወቅ አስፈላጊ መስሎ ስለታዬኝ ነው፡፡
ሁለተኛው እና አንገብጋቢው፤ ‹‹ባልደራስ ተዓማኒ ዓላማ ይዞ፣ በውስጡ ያቀፋቸው አንዳንድ አባላት ግን ለክቡር ዓላማው የማይመጥኑ ናቸው፡፡›› የሚል፣ ቆጥቋጭ ዕይታን ለማጋራት ነው፡፡ ይሕም ማለት ‹‹አካፋን አካፋ የማለት›› ገንቢ የትችት ይትበሃልን ተጠቅሞ፣ ‹‹ባልደራስ››ን ማንቃት የደጋፊነት ግዴታ ‹‹አለብኝ፡፡›› ብዬ ስለማምን ነው፡፡
ስለዚህ ሁለቱንም ነጥቦች በዙሪያ መለስ እንገምግማቸው፡፡
‹‹ባልደራስ›› ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ለአዲስ አበባ እና ነዋሪዎቿ ሲታገል ከርሟል፡፡ ብሔርተኛ ልሂቃን ለመቀራመት በርካታ የሃሰት ትርክቶችን በሚያዛምቱበት ጊዜ፣ ከፊት ቀድሞ የተከላከለው ‹‹ባልደራስ›› ነበር፡፡ ለብሔተኞቹ የመደራጀትን ዕድል እየቸረ፣ ለ‹‹ባልደራስ›› ሲሆን እክል የሚፈጥረው፤ የከተማዋ አስተዳደር የተለያዩ የእመቃ ተግባራትን በእንቅሳቃሴው ላይ ቢፈጽሙም ቅሉ፣ እንቅስቃሴው አድጎ የፓርቲነትን እርከን ሊያገኝ በቅቷል፡፡ ቢሆንም፣ የሲቪል ስብስብነት ሚናውን ለውጦ በፓርቲነት የመጣው ‹‹ባልደራስ››፣ ከፊት ለፊቱ መጻዒ ፈተናዎች ተጋርጠውበት ይገኛሉ፡፡
አንዱ ፈተና ከገዢው አካል የሚሰነዘርበት ትንኮሳ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚነስትር አቢይ አህመድ ‹‹‹ባላደራ› የሚባል ጨዋታ አይመቸኝም፡፡›› ብለው ከተናገሩ በኋላ፣ ግላጭ የትንኮሳ ተግባራት ግዘፍ ነስተው ታይተዋል፡፡ ትንኮሳው ዓይነቱን የቀያየጠ እንደመሆኑ መጠን፣ ያልተገመቱ ጉዳቶችን በቡድኑ ላይ ሲያደርስ ባጅቷል፡፡ ከእስር አንስቶ የስብሰባ አዳራሽን እስከመከልከል የደረሱ ትንኮሳዎች ተስተውለዋል፡፡ በዚህም ብቻ ሳያበቁ፣ ቀጣዩ ምርጫ ላይ ተጨማሪ የትንኮሳ ስልቶች ገዢው ቡድን ሊገለገል እንደሚችል ይገመታል፡፡ ‹‹ባልደራስ›› ይህንን ፈተና በድርብ ብርታት ተቋቁሞ ለማለፍ ዝግጅት ማድረግ ያሻዋል፡፡
ሁለተኛው ደግሞ፣ ከፖሊሲ ሃሳብ ቀረጻ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ እንደሚታወቀው፣ ምሁራን በፓርቲ ፖለቲካ ውስጥ የራሳቸውን ጉልህ አበርክቶ ያነብራሉ፡፡ የፕሮግራም ዝግጅትን አካትቶ ፓርቲው የመንግስትነትን ሚና በሚቀዳጅበት ጊዜ የሚከተላቸውን ፖሊሲዎች ማሰናዳት ላይ የአንበሳ ድርሻ አላቸው፡፡ ለጥቅም ያላጎበደዱ ምሁራን የሃሳብ አድባራት ስለሆኑ፣ በቂ የፖለቲካ ልምድ ባኖራቸውም እንኳ ድርሻቸው ሰፊ ነው፡፡ ‹‹ባልደራስ›› ምሁራንን አሳትፎ መጠነ-ሰፊ የፖሊሲ ሃሳቦችን የማርቀቅ፣ አርቅቆም ህዝብን የማወያየት፣ የማነቃቃት እና የማስተማር ስራ ጎን ለጎን የመፈጸም ግዴታ አለበት፡፡ ፓርቲ አቋቁሞ መምራት ቀላል ሃላፊነት እንዳለመሆኑ መጠን፣ የወደፊት ዕቅድን አጢኖ ግራ – ቀኝ ተመልክቶ መጓዝ ያሻል፡፡ ፖሊሲ እና ስትራቴጂ የወደፊቱን መጪ ሁነት መተለሚያ ስለሆኑ፣ በምሁራን ያላሰለሰ ጥረት እና ብርታት የፖሊሲ ቀረጻው ከወዲሁ መጀመር ይኖርበታል፡፡ የፖሊሲዎቹ ዋና ማጠንጠኛ አዲስ አበባ እና አዲስ አበባውያን ሆኖ፣ በኢኮኖሚ – በማህበራዊ እና በፖለቲካዊ ጉዳዮች ሊያተኩሩ ይገባል፡፡ ‹‹ባልደራስ›› ይህንን ፈተና በድል ካለፈ፣ ምርጫውን በዝረራ እንደሚያሸንፍ እርግጥ ይሆናል ማለት ነው፡፡
ሶስተኛው ፈተና፣ ተገዳዳሪ ብሔርተኞች የሚፈጥሩት አግባብ ያልሆነ ፉክክር ነው፡፡ ‹‹ባልደራስ›› ስለአዲስ አበባ እና አዲስ አበባውያን አብዝቶ በመሟገቱ ሰበብ የተገዳዳሪ ብሔርተኞች የትንኮሳ ዒላማ ሆኗል፡፡ እነዘህ ብሔርተኞች – በአብዛኛው ‹‹የኦሮሞን ህዝብ እንወክላለን፡፡›› የሚሉ ሲሆኑ፣ የአዲስ አበባን ነዋሪ እንደመጤና ሰፋሪ የሚቆጥሩ ናቸው፡፡ እዚህ ላይ አስተሳሰባቸው በግላጭ ከ‹‹ባልደራስ›› አቋም ጋር እንደሚጋጭ መገንዘብ ይቻላል፡፡ እናም፣ ብሔርተኞቹ በሃሳብ ሲሸነፉ፣ የጉልበትን መንገድ ሊመርጡ እንደሚችሉ፣ አንዳንዴ ጥላቻቸው ሲገነፍል ከሚያደረጉት ነውረኛ ድርጊት መረዳት ይቻላል፡፡ ሲደብረው መንገድ የሚዘጋ፣ ሲርበው መጋዝን የሚዘርፍ ሃይል ካላቸው – ከእነዚህ ቡድኖች ጋር ያለውን ውጥረት፣ ‹‹ባልደራስ›› አግባብነት ባለው መንገድ መፍታት ግድ ይለዋል፤ መፍታት ካልቻለ ደግሞ፣ ባለው አቅም ብሔርተኞቹን መዋጋት አለበት፡፡ ማለትም ሰላማዊነትን እና ዲፕሎማሲያዊ መንገድ መጠቀምን ማዘውተር አለበት፡፡ ‹‹ባልደራስ›› አጠቃላይ አስተሳሰቡን አጠንክሮ፣ የbargaining አቅሙንም አጎላብቶ ወደ ድርድር እነርሱን መጫን አለበት፡፡ ለብሔርተኞቹ ዱላ የሚያቀብል ስሀተት አለመስራትም ወሳኝ ነጥብ ነው፡፡ ይህም ሲብራራ፣ ‹‹ባልደራስ›› በአንዳንድ አመራሮቹ በኩል በአፍ እልፊት ይሁን በሌላም ምክንያት ለተፎካካሪዎቹ ፎርፌ የሚያሰጥ ንግግር አለመናገሩ ይጠቅማል፤ አንዳንዴ የወደረኛን ወሬ ማዛመት ከትርፉ ኪሳራው ስለሚያመዝን!
ለመልዕክቴ መጠነኛነት ስል፣ ፈተናዎችን በዚሁ ቋጭቼ ወደ ሁለተኛው ነጥብ ልንደርደር፡፡
‹‹ባልደራስ›› ከተቋቋመበት ዕለት ጀምሮ፣ በርካታ ወገኖች ባላቸው አቅም እያገዙት ነው፡፡ በአባልነት የሚሳተፉም አሉ፡፡ ነገር ግን የአመራር ቦታ ላይ የሚገኙ ግለሰቦች አቅማቸው ለፖለቲካ ስራ ኢምንት ነው፡፡ ይልቁንም በ‹‹ባልደራስ›› ስም ግለሰባዊ ዕውቅናቸውን እያገዘፉበት ነው፡፡ በስም መጥቀሱ ባያስፈልግም፣ በተግባራቸው ግን እነማን እንደሆኑ መንጥሮ መለየት ይቻላል፡፡
በእስክንድር ዙሪያ የተሰባሰቡት እነዚህ ግለሰቦች፣ ‹‹ባልደራስ›› ወደ ፓርቲነት ሲያድግ አብረው እንዳይቀጥሉ ይመከራል፡፡ ምክንያት አለኝ፡፡ ትልቅ ተስፋ ተጥሎበት፣ ግን ረዥም ጉዞ ያልተጓዘው ‹‹ቅንጅት›› በአጭሩ እንደከሸፈው ሁሉ፣ የ‹‹ባልደራስ››ን ንዑድ ዓላማ፣ የህዝቡንም ግዙፍ ተስፋ መሸከም አቅቷቸው፣ እነዚህ ግለሰቦች ወደ ትቢያ እንዳይወረውሩት ስለምሰጋ ነው፡፡ አንድም በዕውቀት ደረጃቸው፣ ሁለትም በፖለቲካ ተሳትፏቸው ውራ መሆናቸው ሳይበቃ፣ ተራ የእወደድ-ባይነት ፖለቲካን ስለሚያዘወትሩ ጭምር ነው እንዲህ ማለቴ፡፡ ስለሆነም ‹‹ባልደራስ›› ያልተሟሸ የመሪነት አቅም ያላቸው፣ ይልቁንም የፖለቲካ ልምዳቸው በሰል ያለላቸውን ግለሰቦች ወደ ድርጅታዊ መዋቅሩ አስገብቶ ቢጓዝ፣ ጥሩ ይመስለኛል፡፡ ካለበለዚያ፣ አሁን በተያዘው ጉዞ፣ ልክ እንደፓርቲ ለመቀጠል ማሰብ ዘበት ነውና፡፡
መልዕክቴ ሲጠቃለል እንደሚከተለው ነው፣
‹‹ባልደራስ ሆይ!
መነሻ ሃሳብህ እና መርኆህ ተወዳጅ ነው፡፡ ነገር ግን ብዙ ወለፈንዲዎች ከፊት ለፊትህ ተደቅነዉብሃል፡፡ አስተውለህ ከተራመድክ ታልፋቸዋለህ፡፡ ተጠላልፈህ ከወደቅክ ግን በህዝብ ተስፋ ላይ እንዳሸሞርክ ይቆጠራል፡፡ እናም፣ እርምጃህን አስተካክል! አስተውል!››