“ለሁሉም ጊዜ አለው”
ልራመድ ስል እግሬን
ልናገር ሥል አፌን
ልፅፍ ሥል እጄን…
ከያዝከኝ ወንድሜ
ከያዢሺኝ እህቴ
ሥልጣን አለኝ ብለሽ።
ነፍጥ አነገትኩ ብለህ።
(ቴሌቪዢን አለኝ ብለህ።)
ሰብአዊ
ዴሞክራሲያዊ
ነፃነቴን
መብቴን
ከቀማኸኝ
እኔ ከቶ ማነኝ ?
መናገር ያቃተኝ
መፃፍም ያቃተኝ
መራመድ የማልችል
ያንቺ ና የእሱ ታዛዥ
እሺ ባይ ተገዢ…
ለከላዮች አጎብዳጅ…
ለዘረኞች ሰጋጅ…
እምኖር ለሆድ
በግድ የምሰግድ ።
……………………..
የምኖር እንደእንሳ
ጥያቄ ሣላነሳ !
የምኖር አፌን ዘግቼ
በሆድ ተገዝቼ።
እዛና እዚህ
በሁሉም ክልል…
……………….
መንግሥት እንደሌለ
ሀገር እንደሌለ
ሁሉም ሀገር ሆኖ …
በየቋንቋው ገኖ
የወል ሥም ተረሥቶ
ቋንቋ ብቻ ተሰምቶ….
ሁሉም በየቋንቋው
ጥላቻን ሢያነግሠው።
ሌላውን እያሥፈራራ
እሱ ብቻ ሲያወራ…
በየቲቪ እሥክሪኑ
ቋንቋ በመግነኑ
ለምን ከቶ ይለናል …
እኔ ብቻ ሥሙ ? !
ለምን ከቶ ይለናል
ሀገር እንደሌለን
ባለአገር እኛ ነን ።
………………
ባንዲራችንን ረግጦ
ከባህላችን አፈንግጦ
ለምን “መጤ” ይለናል?
በተወለድንበት
እትብታችን በተቀበረበት
ባልጠፈጠፈው መሬት
በኖርን በዜግነት…
ለምን ከቶ ይለናል?
ቋንቋዬን ባለመናገራችሁ
ሂዱ ወደ ክልላችሁ።
ክልል ከሌላችሁ…
አፋችሁን ዝጉ!
እጃችሁንም አትዘርጉ
ሥገዱ፣አደግድጉ።
ያለፍቃዴም…….
አንዳች አታድርጉ።
ሀገር ሠንደቅም አትበሉ
አረጓዴ፣ቢጫ፣ቀዩንም ጣሉ።
እጃችሁን አጣምሩ
እግራችሁን እሰሩ።
…………….
እኔ ብቻ ላውራ
እኔ ልንጠራራ
ዝም ብሎ ማየት
ጭጭ ብሎ መሥማት
ነው የእናንተ ሥራ
ነው እኳ፣ የእኛ ተራ…
ማጨብጨብ ብቻ ነው
የመጤዎች ሥራ።
በማለት ለጥቅሙ
ቋንቋ ሆኖ ደሙ…
ብሎ እኔ ብቻ ልብላ
ለእኔ ይሁን ተድላ።
ይለናል…
የቋንቋ ፖለቲከኛ
የቋንቋ ጋዜጠኛ
ሰው መሆኑን ረሥቶ
በቋንቋ ራሱን ጠርቶ…
ዘወትር…
ጥላቻን ቢያውጅም
ጥላቻን ቢደግሥም።
ይህን “የጥላቻ” ድግሥ
ለሱ ይሆናል እንጂ ምሥ
የሀገሬ ባለአገር
የሚያምነው በፍቅር
“ጥላቻን” አይበላ
ይብላውእንጂ…
የቋንቋ ዕድምተኛው
ለሆዱ ተግዝቶ ዘረኛ የሆነው።
…………….
አንተ ዘረኛው …
የቋንቋ አምላኪው…
በል እንደለመድከው…
በይ እንደለመድሽው…
ታሪክን እጥቢው
ታሪክን አርክሺው
እውነትንም ካጂው።
ሰው ፣ ወንድማማች
ሰው፣ እህትማማች
አይደለም እያልክ
በአማርኛ ሥበክ።
በኦሮምኛ ቀድስ
በትግሪኛ አንኳስስ…
………………….
በዋሾ አንደበትህ
ምላሥህ ሳያዳልጥህ…
“ይህ ሰው የሚሉት
የበቀለ ከመሬት
መሆኑን እወቁት
ትግሬ ከትግሬ መሬት
ኦሮሞ ከኦሮሞ መሬት
አማራም ፣ደቡብም
ሱማሌ፣ቤንሻጉል ፣አፋርም
ጋምቤላ፣ሐረሪም።
ወዘተ።ወዘተ።ከምድር በቅለዋል
ቋንቋቸውንም ፣አውቀው ተወልደዋል።”
እያልክ ሐሰት ብትናገር
በየቲቪ መሥኮቱ ቅጥፈት ብታወራ
ብትጀምር፣(ብትጀምሪ) የምርጫ ሽቀላ
እኛ አይደለንም ሞኝና ተላላ።
ትላንት ተምረናል፣ ከደርግ ሽንገላ !
ትላንት ተምረናል ፣ከወያኔ የብዝበዛ መላ!
ዛሬም ተምረናል፣ከጮሌዎች ድለላ !
እባክህ…..
አንተ የቋንቋ ፖለቲከኛ አፍህን ዝጋው
ይብቃህ፣(ይብቃሽ) ፣የጥላቻ ሰበካው።
እወቅ ለሁሉም ጊዜ አለው።
ሁሉም በሰዓቱ ነው የሚገለፀው።
ሲደወል ነው ቅዳሴ የሚጀመረው።
ሥግደትም ቢሆን ከአዛን በኋላ ነው።
እብሪትም ሲያይል ሲባባሥ ረገጣ
ይከተላል እወቅ የባለአገር ቁጣ።
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ
የካቲት 13 /2012 ዓ/ም