በምስል ወይም በተንቀሳቃሽ ምስል ማስረጃ ያልነበራቸው፣ መንግስትና ህግ ከቁብ ይልቆጠሩአቸው፣ እንደ አሁኑ ግዜ ሰው ሁሉ በማህበራዊ የመገናኛ መረብ እየተቀባበለ ሼር ያላደረጋቸው በቀደሙት ዘመናት በሀገራችን የተሰሩት ግፎች ሁሉ ተደማምረው የዛሬውን ጭካኔና እና መከራ እንዲፈጠር ምክንያት ሆነዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ በአየር ላይ ተዘርቶ በአየር ላይ የሚበቅል ዘር እንደሌለ ሁሉ የዘመናት ግፎች በሰው አይምሮና ልብ ወስጥ ተዘርተው ግዜና ሰአታቸውን ጠብቀው ለአጨዳ ደርሰው እያመሱን ነው፡፡የአሁኑ ትውልድ ክፋት፣ ዘረኝነት፣ መገዳደል የትም ይፈጸሙ በምንም ምክንያት ይደረግ በዘመናዊ መንገድ እንደ ፌስ ቡክ ያሉትን ጥበቦች በመጠቀም ያለንበት ጓዳ ድረስ እየመጣ የሀዘን፣ ቂምን ና የበቀልን ዘር ለሚቀጥለው ትውልድ ባልተረዳነው መንገድ እንድናስቀምጥ በልባችን ውስጥ ይቀበራል፡ እየሆነ ያለው ነገር ሁሉ መነሻው አሁን ነው ብሎ የሚያስብ የቀደሙትን ያልሰማ ብቻ ነው የሚመስለኝ፡፡ የነበረው በተለያየ መልክና ቅርጽ እየቀጠለ ነው እንጅ ዛሬ ከሰማይ የወረደ ቁጣ ያለ አይመስለኝም፡፡ ይህ ክፉ ዘር በየትኛው ትውልድ ላይ ይከስማል? ማንስ ያስቆመዋል?
የ2ተኛ ክፍል ተማሪ በነበርኩ ግዜ ለምንኖርበት ከተማ ገና አዲስ ነበርኩኝ፡፡ ከቤት መውጣትና ከመሰል የጉረቤት ልጆች ጋር እንኳውን ለመጫወት ገና እድሉም አልነበረኝም ነበር፣ ነገር ግን በበራችን ላይ ሁሌ ወደ ስራ ሲሄድም ሆነ ከስራ ሲመለስ “ ማሙሽ ና እንካ የሸንኮራ መግዛ” እያለ 5 ሳነቲም የሚሰጠኝ አንድ መልካም ሰው አስታውሳለሁ፡፡ ይህ ሰው ስሙ መክብብ የሚባል የግብርና መስራቤት ሰራተኛ እንደሆነ ያወኩት ከግዜ በሁዋላ ነበር፡፡ ይህን ሰው የማረሳበት አንድ ትልቅ ምክንያት አለኝ፡፡ አንድ ቀን በጠዋት ተነስቼ በፊት ለፊት ያለው የውጭ በር ስመለከት ፊት ለፊት አንድ ሰው በጀርባው ተንጋሎ ትኝቶ ተመለከትኩ፣ ፊቱና ግንባሩ በደም ተሸፍኗል ደረቱ ላይም ቀይ ሽብር ይፋፋም የሚል ጽሁፍ ተቀምጧል ይህ ሰው መክብብ ነበር፡፡ ለምን ይህ እንድተደረገ ባልረዳም የሆነ ነገር አጥፍቶ እንደተቀጣ ልጅ የሚመስል ነገር እንደተከናወነ አይነት ስሜት ነበር የተሰማኝ፡፡ በዚያ የሚያልፉ ሁሉ እንዳላየ የማዘን ምልክት እንኩዋን ሳያሳዩ የተፈጠረውን እንኳን የማወቅ ጉጉት ሳይታይባቸው ዝም ብለው ያልፋሉ፡፡ የቤት ሰራተኛችን እጄን ይዛ ወደቤት ካስገባችኝ በሁዋላ “ ምን አይነት ዘመን ነው ጋሽዬን ብቻ እሱ መድሀኒያለም ይጠብቃቸው” ማለቱዋን አስታውሳለሁ፡፡ በዚያው ቀን ከሰአት በሁዋላ አባቴ ከስራ መልስ የተረሸኑትን ሰዎች ብዛትና ማንነት አሁን ከማላስታውሰው ሰው ጋር በሹሹክታ ሲያወሩ ሰምቻለሁ፡፡ እድሜቸውና አመለካከታቸው ለዚያ አይነት መከራ ሊያጋልጣቸው ወይም ሊዳርጋቸው ይችል የነበሩ ሰዎች ምን ተሰምቷቸው እንደነበር ባላውቅም አሁን ባለኝ መረዳት ግን እጅግ አስፈሪ ሰአት እንደነበር መገመት አያዳግተኝም፡፡ እንኳን የማህበራዊ ድህረ ገጽ፣ ፌስ ቡክ ና ዩ ቲዩብ ቀርቶ ሰው በስልክ ለመገናኘት የማይችልበት ዘመን ስለነበረ ወሬው ከአንድ ከተማ ሌላ ከተማ የሚደርሰው በትራንስፖርት ነበር እሱም በመከራ፡፡ ግን ፌስ ቡክ ቢኖር ኖሮ ያ ግዜ ምን ይመስል ነበር? እንኳን አልነበረ!
ሌላ የማስታውሰው ከጥቂት አመታት በሁዋላ በዚያው ባደኩበት ከተማ አንድ ጀማል ሮበሌ የሚባል ሰው ስራውን ትቶ ሽፍታ ለመሆን ወደ ጎለልቻ ( ጀዋር መሀመድ ወደተወለደበት አካባቢ ማለት ነው) አመለጠ የሚባል ወሬ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ በሁዋላ እንደገባኝ ኦነግ ሆነ ማለት ነበር፡፡ ይህንን ተከትሎ የጀማል ሮበሌ ወንድም መሀመድ ሮበሌን አምጥተው ገበያ መሀል ተሰቅሎ ማየቴን አስታውሳለሁ፡፡ መቀጣጫ መሆኑ ነበር፡፡ ይህንን ምናልባት ጥቂት የጀማል ወዳጆችና የተወለደበት አካባቢ ህዝብ በቀር ማን ያውቅ ይሆን ? ፌስ ቡክ አልነበረምና፡፡ እንኳን ለዲያስፖራ ለጎረቤትህ የምትናግረውና የማትነግረው የምትመረምርበት ግዜ እንደነበር በግዜው መከራውን የቀመሱት ሲናገሩ ሰምተናል በሰአቱ የሆነውን ግን ከደርሰበት ቤተሰብ በቀር የሚያውቅ አልነበረም፡፡
ኢህአዲግ መራሹ ኢትዮጵያን በተቆጣጠረበት ግዜ በአንድ የምስራቅ ደቡብ ከተማ በቀድሞው የኦጋዴን ራስ ገዝ ስር የምትገኝ ከተማ (ቀላፎ) ፍሬሽ የጤና ባለሞያ ሆኜ እሰራ ነበር፡፡ በዚያች በዋቤ ሸበሌ ወንዝ ላይ በተመሰረተች ከተማ ለይ ሁለት የተለያዩ አመለካከት የነበራቸው ጎሳዎች ይኖራሉ፡፡ ዋንኛውና እና ትልቁ የከትማዋ ባለቤት ነኝ የሚለው ከኦጋዴን ሶማሌ ዝርያ የሆነው ባህገሬ የተባለ የሱማሌ ብሄር እና ሬር ባሬ የሚባለው በበታችነት የሚታየው ጎሳ ነው፡፡ ሬር ባሬ ሱማሌ ነኝ ይላል ደግሞም አይደለሁምም በሚል እሳቤ የነበረ እና በኦጋዴን(ባህገሬ) ሱማሌ እንደባርያ የሚቆጠር ህዝብ ነበር፡፡ ሌላው በከተማወ የሚኖረው ነዋሪ ከኢትዮጵያ የተለያየ የሀገሪቱዋ ክፍል የመጡ የመንግስት ሰራተኞች፣ ነጋዴዎች እና የመከላከያ ሰራዊት ናቸው፡፡ በወቅቱ ሬር ባሬ አሁን ገዜው የነጻነት ነው የከተማዋ ባለቤት እኔ መሆን አለብኝ የጭቆና ግዜ አበቃ ብሎ ከኦጋዴን ሱማሌ ጋር ከፍተኛ ግጭት ውስጥ ገባ፡፡ በወቅቱ በሀይልም፣ በመሳሪያም በብዛትም በተጨማሪ ደግሞ ከተማዋ ዙርያ የነበሩት የኦጋዴን ሱማሌዎች በመሆናቸው አናሳዎቹ ሬር ባሬዎች በአደባባይ ታረዱ፣ ተገደሉ ውደ ዋቢ ሸበሌ ወንዝ ከእነ ህይወታቸው ተወረውሩ፡፡ በቦታው የነበርን ከሌላ አካባቢ የመጣን ወደ አንድ መጠለያ ገባን፡፡ በቦታው የነበረው የህወአት ሰራዊት ጣልቃ ላለመግባት ወስኖ ሁኔታውን እንደ ፊልም ዝም ብሎ ማየት ቀጠለ፡፡ ሁኔታውን መቁዋቁም ያልቻሉ እናቶችና ህጻናት ሸበሌን አቋርጥው በመከላከያ ግቢ አካባቢ ተጠለሉ ሌሎች ከተማዋን ትተው ተሰደዱ፡፡ ሬር ባሬዎች ወደ ሶማሊይ በመጉዋዝ የፋራህ አይድድ ን ወታደሮች እርዳታ ጠየቁ ምክንያቱም በወቅቱ ሱማሊያ ላይ ብዙ ቦታዎችን ተቆጣጥሮ የነበረው ፋራህ አይዲድ የሀውያ ጎሳ በመሆኑና ከኦጋዴን ጋር ቅራኔ ስለነበረው ያንን ክፍተት በመጥቀም ሬር ባሬዎች እርዳታ ለማግኘት ስለሚያስችላቸው ነው፡፡ የመሳረያ እርዳታ አግኝተው ሲመጡ የህወአት ወታደሮች መሀል ገብተው ነገሩን ለማብረድ ደፋ ቀና ማለት ጀመሩ፡፡ ነገሩ ቢረጋጋም በመጠለያ ያሉት የሬር ባሬ እናቶእችና ህጻናት ከፍተኛ ችግር ወስጥ ወደቁ፡፡ በተከሰተው አደገኛ ተላላፊ በሽታ ህጻናት እንደ ቅጠል መርገፍ ጀመሩ፣ የስራዬ ጉዳይ ሆኖ በየቀኑ በቦታው በመገኘት የሰባዊ እርዳታ ለማድረግ ብንሞክርም ኦጋዴን መንገድ በመዝጋቱ ምግብና መድሀኒት ማድረስ ተቸገርን፡፡ በየቀኑ ከአእስር እስከ አስራምስት የሚሆኑ ህጻናትን በአንድ ጉድጉዋድ መቅበር ስራዬ ነበር፣ ጾታና እድሜ እና በቀን የሞቱትን ቁጥር ወይም ብዛት ለበላይ አለቆቻችን ከማስተላለፍ በቀር ምንም መፍትሄ የማንሰጥ ሆንን፡፡ ይህንን ጉድ እንኩዋን ለመላው ኢትዮጵያውያን ለማድረስ ቀርቶ ለቤተሰቦቻችን የመንገርያ መንገድ የለንም ነበር፡፡ ዛሬ ቢሆን ትልቅ የፌስ ቡክ እና የዩ ቲዩብ ገበያ በሆነ ነበር፡፡
የሀውዜን ጭፍጨፋ በተንቀሳቃሽ ምስል ተይዞ ህዝብ እንዲያየው በመደረጉና በፍጥነት በትግራይ ህዝብ ልብ ላይ በመዘራቱ ለመብቀል ግዜ አልወሰደበትም ነበር፡፡ በአንድ ጀንበር ሺዎችን ወደ በረሀ ለበቀል አፈለሰ፡፡ ይህ ግፍ የተፈጽመው ባለፈው የደርግ መንግስት ቢሆንም አሁንም ድረስ በተለያየ ግዜ ደርጊቱን በማሰብ አዲሱ ትውልድ ልብ ውስጥ እንደ ምርጥ ዘር እንዲቀመጥ ተደርጓል፡፡
ጎንደር በመላኩ ተፈራ የቀመሰችው መከራ፣የበደኖው ዘግናኝ መከራ፣ የአርባጉጉው እልቂት፣ በደገሀቡር መንገድ የታረዱት እና የተደፈሩት ሴቶች፣ የቀብሪደሀር ሆስፒታል ሰራተኞች ላይ የተፈጸመው ግፍ ሁሉ ፌስ ቡክ ባለመኖሩ ብቻ ሌሎች ሳይሰሙት ወይም በስእል በተደገፈ ማስረጃ ስላልታየ ብቻ ያለፈው ግዜ ካሁኑ የተሻለ መስሎ ድምጹን አጥፍቶ እያለፈ ነው፡፡
በ ሁለት ሺህ ሶስት ዓ/ም ላይ ለስራ ከጋምቤላ ወደ ፊልቱ የደቡብ ሱዳን መጠላያ ጣቢያ በመሄድ ላይ ሳለን አንድ ከተማ የነበር በሰአቱ ግን ከፈራረሱ ቤቶች በስተቀር ምንም የሌለበት ቦታ ተመለከትኩኝ፡፡ አብረውኝ የነበሩ በቦታው የቆዩ የስራ ባልደረቦቼ ስለ ከተማው ታሪክ ሲነግሩኝ ማመን እስኪሳነኝ አዘንኩ፣ ከተማው የተመሰረችው ደርግ ከወሎና ከትግራይ በሰፈራ ምክንያት ለተሻለ ህይወት ወይም እረሀብን ለማሸነፍ በሚል የመንግስት ፖሊሲ ባሰፈራቸው ምስኪን አባውራዎች ነበር፡፡ ለፍተው ሰርተው አካባቢን ለውጠው ህይወታቸውን መምራት ቢጅምሩም፣ ሀገራችን ነው ብለው ወልደው ከብደው መኖር ቢጀምሩም የደርግን መውደቅ ተከትሎ የነበረውን ክፍተት እንደአጋጣሚ በመጠቀም የአካባቤ ነዋሪዎች (አኝዋኮች) የከተማዋን ነዋሪ፣ አብሮአቸው የኖረውን ህዝብብ ያለ ርህራሄ ጨፈጨፉት፡፡ ከተማዋም ያለ መታሰቢያና ያለምልክት ቀረች፡፡ ይህንን ጉድ አዲስ አበባ አታውቅም፣ ዲያስፖራ አልሰማችም ስለዚህም ያለፈው ግዜ የፌስ ቡክ ማስረጃ ስላልነበረው እንደ መልካም ግዜ ተቆጥሮ የተሻለ ነበር ተባለለት፡፡
ያልተነገሩ ያልተሰሙ የብዙዎችን ህይወት አተራምሰው ያለፉ ብዙ ግፎች በኢትዮጵያ ተስተናግደዋል፡፡ የፌስ ቡክ አርበኞች ያላወሩለት፣ የዩቲዩብ ነጋዴዎች ያልሰሙት ሰምተውም ያላዛቡት የዘመን መጨረሻ ነው የሚያስብሉ ክፉ ግዜዎች አልፈዋል፡፡
መልካምም ሆነ መጥፎ ፍሬ የሚበቅልበት መንገድ አንድ አይነት ነው፡፡ ዛሬ የምንመገበው ፍሬ የተዘራበት ወይም የተከለበት ወቅት አለ፡፡ እንደ ፍሬው የዝርያ አይነቱ፣ ደርሶ ጎምርቶ ለመበላት የወሰደበት ግዜ አንጻር ልዩ ልዩ ነው፡፡ ዛሬ የሚተከለውም ወይም የሚዘራው ለአጨዳ የሚደርስበት ወቅትና ግዜም አለው፡፡
የቀድሞዎቹ ግፎች እንደ ዘመኑ ስልጣኔና ዘዴ ተዘርተዋል፣ ምናልባት በማስረጃ የተደገፈ ባይመስልም ፍሬው ለአጨዳ ሲደርስ የተዘራበት ግዜ እንዳለ እናውቃለን፡፡ የአሁኖቹን ፍሬዎች(ዘሮች) እየተዘሩ ያሉት በዘመናዊ መንገድ ነው፡፡ ሼር በመደራረግ በሰፊ እርሻ ላይ እየተዘሩ ያለ ይመስላል፡፡ በብርሃን ፍጥነት በምድር ዳርቻ ሁሉ ይደርሳሉ፡፡
ሁላችን የአሁኑን የኢትዮጵያ ሁኔታ የከፋ ነው እንላለን ደግሞም የምናሳብበት ሰው፣ መንግስት ወዘተ. ይኖራል፣ የሚቀጥለው ከአሁኑ እንዳይብስ ግን አልተጠነቀቅንም፡፡ ልጆቻችን የሚያጭዱት ዘር እየዘራን እንዳይሆን፡፡ ዜና መስለው ልባችንን የሚያጠለሹ፣ በቁጣና እልህ የሚሞሉን ብዙ ዘሮች አሉ፡፡
ያለፉት በቀደሙት ግዚያት የተደርጉት ዘግናኝ ድርጊቶች ያለ ነጋሪና አጨብጫቢ አክትቪስት ይህን ያህል ዋጋ ካስከፈሉን የዘመኑ ግፍ እና መከራ በዘመናዊ መንገድ ታግዞ በአክቲቪስቶች ነጠላ ዜማ ተለቆለት በሼር አርጉት አባዜ ታግዞ ለሚቀጥለው ትውልድ ምን እየተደገሰ የሆን?
ታዲያ ይህንን ማን ያስቁመው?? እኔና እናንተ
ቸር ሰንብቱ
አቤክስ ዳኛቸው
ከአይዋ