የልጆች ዕቃ ዕቃ ጫዎታ ይመሥላል የኢትዮጵያ ፓለታካ።እንደምታውቁት የልጆች ጫዎታ አሥሬ ይፈርሳል።ዳቦም አሥሬ ይቆረሳል።የውሸት ዳቦ…የውሸት ቆሎ…የውሸት እንጀራ እና ወጥ ወዘተ።በልጆች ጫወታ ሁሉ ነገር በሽ በሽ ነው።በምናብ የማይፈጠር የሚበላ እና የሚጣጣ ነገር ከቶ የለም።የማይኖርህ ቁሥም አይኖርም።ቪላ ቤት፣መኪና፣መርከብ፣አውሮፕላን ጭምር ይኖርሃል።በፖሊሥ እና ሌባ ጫዎታ ላይ ሲሆን ደግሞ በገደልከው ሌባ መጠን ተጨማሪ ነፍስ ይኖርሃል።በጭቃ ወይም በሣር የሰራሃዋውን ቪላ ይሁን የሣር ቤትህን ገንብተህ ሥታበቃ፣ በአፍታ ታፈርሳለህ።በመፍረሱም አትፀፀትም። ሥለሪሶርሥ አትጨነቅም። ሁሉ ርካሽና ዋጋ የማይጠይቅ ቁሥ በእጅህ ነው። የምታጣው ነገር የለም። እናም ማፍረሥ እና መገንባት ለአንተ እጅግ ቀላል ነው።በጣም ቀላል ነው።
በልጅነትህ ዕቃ፣ዕቃ ተጫውተህ ካወቅህ፣መገንባት እና ማፍረሥ ቀላል ሥራ እንደሆነ ታውቃለህ። ብቻህን የጭቃ ወይም የእንጨት ሚጢጢ ቤቴ ገንብተህ ሣለ ፣ ” ና ! ከእኛ ጋ’ ቤት እንሥራ።” ሲሉህ የራሥህን አፍርሰህ ከልጆቹ ጋር ሌላ ቤት ለመሥራት ትስማማለህ። የገነባኸውን ሚጢጢዬ የጭቃ ቤት ያለአንዳች ሃይ ባይ ታፈርስና በጋራ አፍርሶ ለመገንባት ሰፊውን መድረክ ትቀላቀላለህ። እናም ማፍረሥና መገንባቱን በሥፋት ትያያዘዋለህ።
“ማፍረስ ና መገንባት ” ለለልጆች የጫወታ ጉዳይ እንጂ የቁምነገር ጉዳይ አይደለም። የልጅ ጫወታ ላይ የማፍረሥም ሆነ የመገንባት ድርጊት ከቁብ አይቆጠርም !?
ማፍረስና መገንባት በህፃናት ዓለም ራሱን የቻለ እርካታ ይሰጣል።ደጋግመው አፍርሰው በገነቡ ቁጥር የመገነባትም ሆነ የማፍረሥ ጥበባቸው ያድጋልና ይወዱታል። አንዳአንድ ማሃንዲሶችም አሥገራሚ ቅርጽ ያለው ቤት የሚነድፉት ከህፃንነት ህልማቸው ተነሥተው እንደሆነ ይናገራሉ።(በዘመኑ በኮፒዊተር የሚሰራ የማፍረሥና የመገንባት ጫወታ እንዳለ አትዘንጋ!እሱም ዘመናዊ የዕቃ፣ዕቃ ጫዎታ ነው።)
ብዙዎቹ በመለማማድ ብዛት እንዳይፈርስ የሚፈልጉት ዓይነት ቤት ሠርተው በአቻዎቻቸው “አጀብ!” ይባልላቸዋል። በየደቂቃው ማፍረሥ ና ፣ሳያሰለቹም መገንባታቸው ወደ ተሻለ ፈጠራ እንዳደረሳቸው ልብ ይሏል።
የተሻለ ፈጠራ ሥኬትን ለመጎናፀፍ ፣ህፃናት በየቀኑ ይተጋሉ።ይህ አፍርሶ የመገንባት ድርጊት የሚከናወንበት፣ ፣በታላቅ ተመሥጦ የሚከናወን የህፃናቱ የቤት ማፍረሥ እና የመገንባት ድርጊት ፣ማንንም የማይጎዳ የልጅነት ጫዎታ ነው። ህፃናቱን ከወዲሁ፣ ተግባራዊ ዕውቀት እንዲያገኙ የሚያግዝ የህይወት ትምህርት ቤት ትምህርትም ነው።
ከዚህ በተቃራኒው የቆመ ፣በገሃዱ ዓለም አዋቂዎች ሆን ብለው የሚያከናውኑት፣አሥቀያሚ የማፍረሥና የመገንባት ጫዎታ በሀገሬ እንዳለ መንገር ለቀባሪው ማርዳት ነው። ሣንወድ በግድ እየኖርንበት ሥለሆነ ማለቴ ነው።
ጫዎታው ፣ ግለሰብን ፣ ሀገር እና ህዝብን ለማንኳታኳት የታለመ በቋንቋ ላይ የተንጠለጠለ የማፈራረስ የፖለቲካ ጫዎታ ነው።
ለሥንት ሺ ዘመን በጀግኖች ኢትዮጵያዊያን ታፍሮ እና ተከብሮ የኖረውን ግዛት ለማፈራረሥ እና ብቻውን ሚጢጢ ሀገር ሆኖ ለመኖር የሚሻ የጎልማሳ እና የሽማግሌ ሥብስብ ከንቱ ጨዋታ ነው። ህብረትን የጠላ፣ፍቅርን የጠላ ፣የመላው ሰው ልጅ ብልፅግና የሚያሳምመው ፣የንፉጎች እና የሥግብግቧች ቆሻሻ ጫዎታ ነው።
ይህ ፍቅርን የጠሉ ፣ህብረትን የጠሉ ፣ ማፍረሥ እንጂ መገንባት የማይታያቸው ሥብስቦች አደገኛ ጫዎታ ነው። የጫዎታው ህግ መነጣጠልን ፣ሾኬን፣ሽፍትነትን፣ውንብድናን ማሥመሰልን፣ቅጥፈትን፣ሌብነት እና ማጭበርበርን ይፈቅዳል።መልካም ተግባራትን ይከለክላል። “ከሌላው ቋንቋ ተናጋሪ ጋር ቋንቋውን ብትችል እንኳ በቋንቋው አታናግረው “የምትለው ትዕዛዝም ዋነኛ የጫዎታው ህግ ናት።
የዚህ ጫዎታ ተጫዎች ሲጀመር፣ፍቅር እና አንድነት የለውም። ድሮስ ኢትዮጵያን ለማፈራረሥ ያለማቋረጥ የፖለቲካ ሤራዎችን የሚጠነስሱ ሰዎች ተቧድነው የሚጫወቱትን ጫዎታ የሚጫወት፣ እንዴት ፣ፍቅር፣ አንድነት እና ሰብአዊ ርህራሄ ይኖረዋል?
የጥላቻ መርዞችን፣የቆዳ ማዋደድ እኩይ ድርጊቶችን፣ የህቡ የጥፋት እንቅስቃሴዎችን ሥልታዊ በሆነ መንገድ ሲፈፅሙ የሚሥተዋሉበት ኩንን ጫዎታ እየተጫወተ እንዴት ሥለ ሰው ሁሉ ተመሣሣይነት ሊያሥብ ይችላል?
ከ70 በላይ ለሆኑት ለሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ደንታ ቢሥ ሆኖ፣ የራሱን ቋንቋ የሚያዋድድ ሆኖም ግን ብሔር፣ብሔረሰቦች እያለ ምድር ላይ ባሌለ ሃቅ ጮቤ የሚረግጥ የእኩይ ሰዎች ሥብሥብ ከቶም የሀገር ፍቅር ሥሜት አይኖረውም።
ይህ ከጥበብ የራቀ ሥብሥብ ፣ ትላንት ከጅምሩ ሦሥቱን ቋንቋ አግዝፎ ሲያበቃ፣ብዝበዛውን ያለሀፍረት አጧጡፎ ነበር። ፣አማራ(ብአዴን)፣ትግሬ(ህወሃት )፣ኦሮሞ(ኦህዴድ) በማለት በየክልሎቹ የህግ የበላይነትን ሣይሆን የቋንቋ የበላይነትን አሥፍኖ ነበር።
“ሰው”የተሰኘ የወል ሥምን አደባብሶ ፣የሰው ማህበራዊ ኑሮ ናፋቂነትን እና በፍቅር ተሳስሮ መኖርን አሽቀጥሮ ጥሎ ፣አትደራረሱ ፣በየቋንቋችሁ፣ለቋንቋችሁ ሥገዱ በማለት ሰውን የሚከፋፍል የቋንቋ ጣኦት ፈጥሮ ነበር።
(አንተን እና ሚሥትህን ያሥተሳሰረው እና ቤተሰብ እንድታፈሩ ያደረገው፣ፍቅር እንጂ ቋንቋ አይደለም። ፕሬዝዳንት ነጋሶ ጀርመናዊ ያገባው በፍቅር እንደሆነ እመን።ከያዘህ የቋንቋ አምልኮ እንድትወጣ።)።)
ይህ በዓለም ላይ የሌለ የቋንቋ አደረጃጀት በፍቅር፣ ሥለፍቅር የሚኖረውን ፍቅር የሆነ የሀገሬን ህዝብ ክፉኛ አደናግሮታል።ይህ ከፋፋይ የሂትለር እና የሞሶሎኒ መሥመር፣ ሀገሬን የማፍረስ አደጋ ላይ እንደጣለት ፣ብዙዎች ይረዳሉ።
በነገሬ ላይ… ማነህ ፤ “ኢትዮጵያ አትፈርስም ሥለ ተባለ ከመፍረሥ አናድናትም።ትፈርሳለች ሥለተባለም እንዳትፈርስ ለማድረግ አንችልም።በቃል ብቻ ምንም ማድረግ አይቻልም። እንድትፈርስም ሆነ እንዳትፈርስ ተግባራዊ ሥራ መሥራት ያሥፈልጋል።በሥራ ነው ሀገሪቱን ማፍረሥ የሚቻለው።በሥራ ነው ይህቺ ሀገር የይጎዝላቪያ ዕጣ ፈንታ እንዳይገጥማት ማድረግ የሚቻለው ። “ያልከው?
ልክ ነህ ።አንተ አፍራሾች እንዳሉ ሁሉ እንዳይፈርስ ተካላካዮች እንዳሉ ገብቶሃል። ብራቮ! ግን ማነው ነገር ሁሉ ከቃል ይጀምራል ያለው? ልክ እንደ ቅዱስ መፅሐፉ ማለት እኮ ነው፣ “በመጀመሪያው ቃል ነበረ፣ቃልም በእግዛብሔር ዘንድ ነበረ ።ቀልም እግዛብሔር ነበረ።”ዮሐ 1:1 …
ሀገር ለማፍረሥ፣ሀገርን አፍጋኒሥታን፣የመን፣ሶሪያ አድርገው፣ለጠላቶቾ አሣልፎ ለመሥጠት፣ በየቋንቋቸው የተደራጁ ፖለቲከኞች ፣ “እኔ ከሞት ሠርዶ አይብቀል።” በሚል ሥሜት በሀገር እና በህዝብ ላይ ዕቃ፣ዕቃ ሲጫወቱ ማየት ግን በእጅጉ ያሳዝናል።
ይህንን ከፋፋይ ጨዎታ ዳር ሆኖ መመልከት እጅግ ያሳምማል።ያቆስላል።ህሊናን ያደማል። ያበሳጫል። ያሳፍራል ።ያናድዳል። “ኡ!ኡ!በህግ አምልክ !!” ያሠኛል።…
ሀገር ወዳዱ ፣ብዙሃኑ፣ሠርቶ አደር ፣አርሶ አደር፣አርብቶ አደር፣ነጋዴ፣ወዘተ ዳር ቆሞ ቢያይም ፤ ሀገር በቋንቋ ፖለቲካ ፣በግጭት ሥትናጥ ፣ጥቂት የክልል ባለሥልጣናት ኢትዮጵያን ያህል በአለም የገነነች ሀገር የይጎዝላቭያ ዕጣ እንዲደርሳት ለማድረግ ሲጥሩ ፣ጠመንጃውና እሥርቤቱ በእሱ እጅ ባለመሆኑ ፣ አሣፋሪ እና አብጋኝ የማናለብኝ ድርጊቶችን እና እንቅስቃሴዎችን በቁጭት እያሥተዋለ “ኡ!ኡ! የህግ ያለ ማለቱን ግን አላባራም።
ትላንት እዚህ ግባ በማይባል ደሞዝ ሆኖም ግን በገዘፈ ሀገር ወዳድነት የምሩን “አጥንቴም ይከስከስ፣ ደሜም ይፍሰስላት፣ይኽቺ ሀገሬን ጭራሽ አይደፍራትም ጠላት።” ብሎ፣ “ህይወቱን የሰዋላት ጀግና የመከላከያ ሠራዊት ወይም የጦር ሠራዊት ሀገሬ ነበራት።ዛሬም ሀገሬ እንዲህ ዓይነት ሠራዊት ቢኖራትም፣ የፌደራል ሥልጣን የሣሣ በመሆኑ፣ በየክልሉ ያሉ አሥተዳደራዊ መንግሥታት ራሳቸውን እንደምኒልክ ዘመን ንጉሶች በመቁጠር፣ የራሳቸውን ጦር አደራጅተውና እሥከ አፍንጫው አሥታጥቀው፣ከልቡ ባያምንበትም፣ አላዋቂውን እና የዳቦ ተገዢውን ዜጋ “ለቋንቋህ ሙት!” እያሉት ነው። …
በተለይም የትግራይ ክልል መንግሥት፣ ራሱን ከኢትዮጵያ የገነጠለ እሥኪመሥለን ድረሥ በሚያሳዝን መለኩ፣ በቁም ነገር የማፍረሥን ተግባር ለመከወን ዕቅድ አውጥቶ፣ እና የጊዜ ሰሌዳ ነድፎ እየተንቀሳቀሰ ነው። የጥፋት እንቅሥቃሴዎቹም በየጊዜው ሲተገበሩበቁጭት እያሥተዋልን ነው።
” በቃ ማለት በቃ ነው!” ብሎ የሚያሥቆመው ፣በህግ የበላይነት አምኖ የሚያሳምን ጠንካራ መንግሥት እንደሌለ የሚያምነው ይህ ሃይል፣ ከትላንቱ እጅግ የባሰ የማፍረሥ ተግባር ለመፈፀም መነሳቱን “ሣንጃ ባፈሙዝ”አሥገብቶ ሥልጣን ወይም ሞት በማለት፣ በሥልት እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ እየተመለከትን ለምን አይቆጨንም???
ለህግ ተገዢ የሆነ ፣በሀገር ሉአላዊነት የማይደራደር ፣በቋንቋ ፓለቲካ ያልተጠመቀ የሀገር መከላከያ ሠራዊት እንዳለን ባምንም፣ የሀገሪቱን የወንጀል እና የፍትሐ ብሔር ህግን አክብረው ያለአንዳች ማጭበርበር፣ህጉን እንዲተገበሩ ኃላፊነት የተሰጣቸው፣በየክልሉ ያሉ ፖሊሶች በየክልሉ ንጉሦች መዳፍ ውሥጥ መውደቃቸውም እጅግ ያሰጋኛል ።
የፌደራል ፖሊሥ የገዘፈ አቋምና የላቀ ዝግጁነት ፣(በሰው ኃይልና በአደረጃጀት)ቢኖረው ኖሮ የክልል ባለሥልጣናት ከህግ በላይ ሆነው፣ህግ ደግሞ ከእነሱ ጫማ ሥር ባልዋለ ነበር።ፍትህ ተረግጣ ተፈጥሯዊው የመናገር መብት እንኳን የታፈነበት ክልል በዋናነት የትግራይ ክልል እንደሆነ ለትግራይ ሰው ምሥጢር አይደለም።
በየክልሉ፣ ወንጀልን አሥቀድመው የሚከላከሉ፣ ከተፈፀመም ወንጀለኛውን አድነው ለፍርድ የሚያቀርቡ ህግ አሥከባሪዎች እና የህግ አሥፈፃሚ አካላት በመላው ሀገሪቱ እንደሠንደቅ ከፍ ብለው እሥካልታዩ እና ማንም ሰው በየክልሉ ያሉ ቁንጮ ባለሥልጣነት ሳይቀሩ ከህግ በታች እንደሆኑ ለማረጋገጥ የሚያሥችል አቅምና ቁመና እሥከሌላቸው ጊዜ ድረስ ፣ በዚች ሀገር የተሞላ ፍትህን ለማሥፈን አይቻልም።ነፃነትም ለትግራይ ህዝብ ብርቅ እንደሆነች ጥቂት ቆይታ ለመላው የኢትዮጵያ ዜጋ ሁሉ ብርቅ ትሆናለች።(የፊታችን ሰኞ የነፃነት ቀን ነው።4/5/2012።ነፃነትን የሚወድድ ባርነትን መጠየፍ አለበት።ነፃነትን የማይጨቁን መንግሥት ያለበት ሀገር ውስጥ ህይወትን ማጣጣም ይቻላል።)
እርግጥ ነው። “ሰላምን ፍትህን በጠረጴዛ ዙሪያ ፣ በመደራደርም ሆነ፣ በጠመንጃ ማምጣት አይቻልም።ሰላምና ፍትህ የሚመጣው በእውቀት፣በክህሎት እና በጠንካራ ዲሰፕሊን የተሞሉ ለመርህ የቆሙ ምሥጉን የህዝብ አሥተዳደር፣ የፍትህ ፣የፖሊሥ፣ የማህበራዊ አገልግሎት ተቋማት በተጨባጭ መገንባት ሢቻል ነው ።
በተጨባጭ ጠንክረው፣እና በፌደራል ደረጃ ጎልተው መታየት ያለባቸው የህግ አውጪው፣የህግ ተርጓሚው እና የህግ አሥፈፃሚው ተቋማት ፣ዛሬ ላይ ህግን በማሥፈፀም አኳያ እጅግ ተዳክመው የሚታዩት አሥቀድሞም ጠንካራ እንዲሆኑ ሥላልተፈለገ መሆኑ ከታወቀ እንሆ ሁለት ዓመት ሊሞላው ነው።
ከ2008 ዓ/ም ጀምሮ በመላው ኢትዮጵያ የኢህአዴግን ሥርዓት በመቃወም የተቃውሞ ሰልፎች ተደርገዋል። ኢህአዴግ መራሹ መንግሥትም ተቃውሞውን ለመቀልበሥ ጥረት አድርጓል።ተቃውሞው “የሻይ ሲኒ ማዕበል ” ሆኖ አልቀረም። ጠ/ሚ ኃይለማሪያምን የካቲት 8/2010 በራሳቸው ፍቃድ ሥልጣናቸውን እንዲለቁ አሥገድዶ፣ ፣መጋቢት 18/2010 ዓ/ም ጠ/ሚ አብይን የአሻጋሪው መንግሥት መሪ በማድረግ ተደምድሟል።(ብሥራቱ በእኩለ ሌሊት መነገሩን አትዘንጉ።…)
በሥንጠቃውም ወቅትም ኢህአዴግን ከመሰረቱት አራቱ ግንባሮች ዋንኛው እና ትልቁ ግንባር ፣ኢህአዴግ ጥገናዊ እንጂ መሠረታዊ የአይዶሎጂ ለውጥ እንዲያደረግ ከቶም አልፈለገም።አሻጋሪው ጭቆናን አሥቀጣይ እንዲሆን እንጂ ጠንካራ ሰው እንዳይሆን ፍላጎት ቢኖራቸውም ፍላጎታቸው አልተሳካም።
ይህ ጭቆናን አሥቀጣይ አመራር ናፋቂ ግንባር የህወሓት ግንባር እንደሆነ ይታወቃል። ግንባሩ፣ “አብዮታዊ ዴሞክራሲ ወይም ሞት !” ባይ እና ህዝብን እኛ እንጂ ህዝብ እኛን ከቶም ሊመራን አይችልም።ይህ ወቅታዊ እና “የሻይ ሥኒ ማዕበል ኃላፊ ነው። አትደናገጡ። አትልፈስፈሱ። የአብዮታዊ ዴሞክራሲን ችካል ቸክላችው አትንቀሉ።ኋላ መዘዝ ታመጣላችሁ።”። ብሎ ከመሟገቱም በላይ፣አያሌ ሥልጣን ያለመልቀቅ ሤራ በማድረግ ከወንበሩ ላለመውረድ ጥሯል።
ኦህዴድ እና ብአዴን “በህዝብ ሥም፣በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ሥም፣በብሔር ብሔረሰቦች ሥም መነገድ ይብቃ።ብዝበዛችሁ ይቁም።ቶርቸራችሁ ያብቃ።ሉጋማችሁን እና፣ የአፈና መሣሪያችሁን ጣሉ። በግፍ የታሰሩት ይፈቱ። እናንተን ተገን አድርገው ህዝብና ሀገርን የበደሉ፣የዘረፉ እና የሰረቁ ለፍርድ ይቅረቡ “በማለት ተሟገቱ።የደቡብ ህዝቧች አመራር ኒውትራል ሆነ። ህወሃት ብቻውን ቀረ።በብአዴን ግንባር ቀደም መሥዋትነት ዶ/ር አብይ መጋቢት 24/2010 ጠ/ሚ መሆናቸው በምክር ቤቱ ይፋ ሆኖ፣ቃለ መሐላ ፈፀሙ።ከኦህዴድ።
ይህ ማለት በውስጥ ታዋቂነት ኢህአዴግ ፈረሰ ማለት ነው። በይፋ ባይታወጅም ኢህአዴግ በውስጥ ታዋቂነት ፈርሶ ነበር።(እርግጥ የኢህአዴግ ጭንቅላት ህወሃት ነበርና አናቱ መቆረጡ እሙን ነው። ጭንቅላቱ ተቆርጦ ህይወት ባይኖረውም የኢህአዲግ መልካም ትዝታ የሚንጣቸው ከቀበሌ እሥከክልል ዛሬም የለውጡ ደንቃራ መሆናቸው ይታወቃል።)
ትላንት፣በማጋጨት፣እና በመከፋፈል የሚታወቀው ኢህአዴግ ከጅምሩ ቢፈርሥም፣ዛሬም አንዱን በማንኮታኮት ና አፈር ድሜ በማሥጋጣ ጮቤ የሚረግጡ የሉም ማለት አንችልም።
በቡድናዊ ሴራቸው፣ ሸር እና ተንኮላቸው ዜጋው በጥረቱ የገነባው ንብረት፣ ያፈራው ሃብት ገደል ሲገባ እልል በቅምጤ የሚሉ ዛሬም አሉ።
ዛሬም በደባ እና በደቦ ፍርድ ዜጎች ሙልጫቸውን ሲቀሩ፣እስከነቤተሰባቸው ጎዳና ላይ አዳሪ ሲሆኑ እያየን ትንሽ እንኳ አይፀፅተንም። ለእኛ የሚታየን ንቃተ ህሊናው ዝቅተኛ የሆነውን በሐሰት ትርክትና በላም አለን በሰማይ እያጓጓን ፣ በአንሥሣዊ ድርጊት ፣በንፁሐን ሰዎች ደም፣ ሥልጣን ኮርቻ ላይ ለመቀመጥ መቋመጥ ነው።
በኢትዮጵያ ውሥጥ ፣ ከቀኃሥ ጀምሮ የሥልጣን እርካብን ተቆናጦ፣በሥልጣን ኮርቻ ላይ መቀመጥ የሚቻለው ጠልፎ በመጣል ነው።
ሥልጣን የሚያዘውና እርካቡን ተቆናጦ ኮርቻው ላይ ለመቀመጥ የሚቻለው ፣ በከፍተኛ ውጣውረድ የተገነቡትን እና ጠንካራ መሠረት ያላቸውን ጠቃሚ የአብሮነት መሥተጋብሮች፣ በአለፈው ትውልድ በጥቂት ግለሰቦች በተፈፀመ ወንጀል እና ያላዋቂ ድርጊት ፣የዛሬውን ንፁህ ሰው በመኮነን ነው። ወንጀሉን የፈፀመው እየታወቀ እና አፈር ከሆነ ዘመናት መንጓዳቸውን እየተገነዘብን የሟች ቋንቋን ተናጋሪን ወንጀለኛ እናደርጋለን። ቋንቋን ወንጀለኛ እናደርጋለን።ቋንቋውን በመናገሩ ብቻ፣እንደጠላት እንዲታይ እንሰብካለን። ትላንት ማለት ዛሬ እንዳልሆነ ብናውቅም፣ ትላንትን በማንሳት፣ሰው ሆን ሳለ ፣ሰውን እንደአውሬ እንዲታይ በጅምላ እንፈርጃለን።ባናውቀው እንጂ አውሬዎቹ እንዲህ ዓይነት የጭፍን ጥላቻ አሥተሳሰብ ያለን ነን።ትላንት የጥላቻ ሐውልት የገነባነውም በሂትለራዊ ጭንቅላታችን የተነሳ ነው።
የጥላቻን ማንገሻ ሐውልት መትከል ሂትለርነት ነው። ።የጥላቻ ሀውልት ትላንት ምሥራቅ እና ምእራብ ጀርመንን ከፍሎ ከነበረው ግንብ የባሠ የመለያየት ምልክት ነው።አፍራሽ እንጂ ገንቢ አሥተሳሰብ አይደለም።የእዛን ዘመን ኦሮምኛ ተናጋሪ እናቶች ጡት መቆረጥ በዚህ ዘመን ያሉ ኢትዮጵያዊ እናቶችን በሙሉ የሚያሳዝን እና የሚያንገበግብ ሆኖ ሣለ በነዚህ እናቶች ላይ ሂሳብ ለማወራረድ ማሰብ የለየለት እብደት ነው።ጭፍን ጥላቻ የወለደው ሂትለራዊ አሥተሳሰብ ነው።
ጭፍን ጥላቻ፣ከሀገራችን እንዲወገድ ጠንካራ የፌደራል ፣ሥርዓት ያሥፈልገናል።ጠንካራ የፊደራል ሥርአት ጠንካራ የፊደራል መንግሥት ይኖረዋል።ጠንካራ ህግ አውጪ፣ህግ ተርጓሚ እና ህግ አሥፈፃሚ ብቻ ሣይሆን ጠንካራ ፕሬሥ ይኖረዋል።እናም እንደዛሬው ዓይነት ዕቃ ፣ዕቃ ጫዎታ እንዳይኖር ፍትህን ያነግሣል።ፍትህ ከነገሠች ደግሞ ማንም ከህግ በላይ በመሆን አይፈነጭብንም።…