በመስፍን ሀብተማርያም (ከኖርዌይ) 14.03.2013
ሙሴ እስራኤላዉያን በግብፅ ሀገር ባርነት ወድቀዉ በነበረበት ዘመን ከእግዚአብሄር በደረሰዉ ጥሪ ህዝቡን ከባርነት ነፃ እንዲወጡና እግዚአብሄር የገባላቸዉን የተስፋይቱን መድር እንዲወርሱ እንደመራቸዉ ቅዱሱ መፅሀፍ ይነግረናል፡፡
እኛም ኢትዮጵያዉያን ከወያኔ እኩይ ተግባራት የሚያላቅቀን፣ የባርነቱን ቀንበር የምንሰብርበትን እና ከአንገታችን ቀና ብለን በሀገራችን ተከብረን እነደዜጋ እንድንኖር ሊያረጋግጥልን፣ ሊያሳየን፣ ሊመራንና ሊያስተባብረን የሚችል መሪ እንፈልጋለን፡፡
እንግዲህ እንደሚታወቀዉ ወያኔ መራሹ የዘረኛ ግብረ ሀይል ኢትዮጵያን በሀይል ከወረረ የፊታችን ግንቦት 20.2005ዓም ድፍን 22 አመት ሊሞላዉ ነዉ፡፡ በዚህ ጊዜ ዉስጥ እኛ ኢትዮጵያዉያን እንደ ሀገር የመቆም ህልዉናችን ተንዶ፣ በመልካም አስተዳደር፣ በዲሞክራሲ እና በሰበአዊ መብት እጦት እየተሰቃየን እንገኛለን፡፡ እንደ ዜጋ ከዜግነት የሚጠበቅብንን እና እኛም እንደዜጋ የምንፈልገዉን ለማድረግ ተሻግሮ የሚያሻግረን መሪ ማግኘት አላደለንም፡፡ ይልቁንም በተቃራኒዉ ተወልደን ባደግንበት፣ እተብታችን በተቀበረበት፣ በቄያችን በነፃነት እንዳንኖር ወያኔ መራሹ ግብረሀይል በኢንቨስትመንት ስም ለዉጪ ወራሪዎች መሬታችንን ያለከልካይ እየቸበቸበ፣ እኛንም የበዪ ተመልካች እንድንሆን፣ እንድንፈናቀል እና እንድንሰደድ አድርጎናል፡፡
በወያኔዎች የብሄር ፖለቲካ መርዝ ሀገራችን ተበክላ አንዳችን በአንዳችን እንድንነሳ፣ ህብረት እንዳይኖረን፣ በጎሪጥ እንድንተያይ አድርገዉናል፡፡ እኛ እርስ በእርስ ስንበላላ፣ ስንጠላለፍ እነሱ ጊዜ እንዲገዙ ዝርፊያቸዉን እንዲያጧጡፉ ሀገር እንዲያጠፉ አድርጓቸዋል፡፡ እንደ ምሳሌ ብጠቅስ ከተራዉ ዜጋ ባሻገር የተለያዩ የተቀዋሚ ፓርቲዎችን ማንሳት ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያ ዉስጥ እስከ ዛሬ ድረስ በቁጥር መቁጠር እስከሚያዳግት የተለያዩ የፖለቲካ ድርጁቶች ተቋቁመዋል ነገርግን አንድም እርባና ያለዉ ነገር ለራሳቸዉም ለሀገራቸዉም ሳይሰሩ ፈርሰዋል እየፈረሱም ይገኛሉ፡፡ አንድ መሆን አልቻሉም ምክንያቱ ደግሞ ወያኔዎች ስልታዊ በሆነ መንገድ ሰርገዉ በዉስጣቸው በመግባት የመከፋፈልና አንዱ ባንዱ ላይ እንዲነሳ የሚያደርግ መርዛቸዉን ስለሚረጩ ፀንተዉ መቆም እንዲችሉ አላደረጋቸዉም፡፡ ይህ ደግሞ ለወያኔ መንግስት እንጂ ለፖለቲካ ድርጅቶችም ሆን ነገን የተሻለን ነገር ይመጣልኛል ብሎ የሚጠብቀዉን የኢትዮጵያ ህዝብ አይጠቅምም፡፡
ስለዚህ አሁን የኢትዮጵያ ህዝብ በቃን ብሏል፣ በትክክል በመልካም አስተዳደርን፣ በዲሞክራሲና በሰባአዊ መገኛ የሆኑ አዲስ ስርአትን በመገንባት ለሌሎች ምሳሌ ልትሆን የምትችልን ኢትዮጵያን ማየት የሚያስችሉ መሪዎች ይፈልጋል፡፡ ወያኔ ካፈረሳትና እያፈረሳት ያለችዉን ኢትዮጵያን ሰይሆን፣ ተዋርዳ እና አንገቷን በአለም ፊት ዝቅ አድርጋ እንድትሄድ ያደረጋትን ኢትዮጵያን ሳይሆን፣ ዜጎች በሰዉ ሀገር በስደት እንደ ሰዉ ሳይቆጠሩ የሚንገላቱባትን ሀገር ሳይሆን፣ በቅጡ መኖር ያልጀመሩ ህፃናት በማደጎ ስም ለምእራባዉያን የሚቸበቸቡባትን ሳይሆን፣ዜጎች በቀን አንድ ጊዜ በልተዉ ማደር እየከበዳቸዉ ያለችዉን ኢትዮጵያን ሳይሆን፣ በዲሞክራሲ፣ በሰበአዊ መብት ጥሰት እና በፕሬስ ነፃነት እጦት የምትገላታዋን ኢትዮጵያን ሳይሆን፣
ዲሞክራሲ የሰፈነባት፣ መሰረታዊ የሰበአዊ መብት የሚከበርባት፣ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት የሚከበርባት፣ የመሰብሰብ የመደራጀት መብት የሚከበርባት፣ ከቦታ ወደ ቦታ የመንቀሳቀስ ንብረት የማፍራት መብት የሚከበርባት፣ ዜጎች እንደ ዜጋ የሚቆጠሩባት፣ የመምረጥና የመመረጥ መብት የሚከበርባት፣ ሁሉም ዜጎች በሀገራቸዉ ጉዳይ ለይ እኩል የመወሰን መብትን የሚረጋግጥባት ሀገር እንድትሆንና ታፍራና ተከብራ የኖረችዉን ከአባቶቻችን የተቀበልናትን፣ ለራሷ ብቻ ሳይሆን በአለም ፊት የአፍሪካ ኩራት እንድትሆን እና በነበረን ታሪክ ላይ ሌላ ታሪክ ሰርተን የዳበረ የአብሮነት ባህላችንን አጎልብተን ታዋቂዎች እንድንሆን ሊያደርገን የሚችል መሪ እንፈልጋለን፡፡
በመጨረሻ ከላይ በርዕስ እንደጠቀስኩት እንደ ሙሴ ሊመራን፣ ሊያሻግረን፣ ከወያኔ አገዛዝ ነፃ ሊያወጣን የሚችል መሪ እንፈልጋለን፡፡ በሀገር ዉስጥም በዉጪም ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ልዩነታቸዉን አስወግደዉ እርስ በእርስ መገፋፋታቸዉን ትተዉ በአንድነት ሀገራቸዉ ኢትዮጵያ ከመፍረሷ በፊት ሊደርሱላት፣ ሊታደጓት ይገባል፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ የአፍሪካ ራስ ሆና በአለም ዘንድ ስምዋ ከብሮ እና ገኖ እንዲኖር፣ በአለም አቀፍ ደረጃ እምነት የሚጣልባት ሀገር እንድትሆን የሚያስችል አሻግሮ ነገን የተሸለች ኢትዮጵያን የሚያይ፣ ራዕይ ያለዉ መሪ ትፈልጋለች፡፡
ኢትዮጲያችን ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር! አሜን
መስፍን ሀብተማርያም
mesfinabt@yahoo.com