September 6, 2013
50 mins read

ሃሳብን በነጻነት መግለጽ ከዘለፋና ስድብ ይለያል (ዳግማዊ ጉዱ ካሣ)

ዳግማዊ ጉዱ ካሣ

ይህችን አነስተኛ ግን ግልጽነት በጣም የተንጸባረቀባትን ፈታኝ ወረቀት ለመጻፍ ያነሳሳኝ ሰሞኑን ያነበብኩት የአንድ መረንና አሳዳጊ የበደለው  ወጣት ‹ጋዜጠኛ› ጽሑፍ ነው፡፡ የዚያ ዋልጌ ሰው ጽሑፍ ዋና ዓላማ ዶክተር ብርሃኑ ነጋን በተቃውሞው ጎራና በወያኔ ፊት ማሽሟጠጥና በነጻነት ታጋዩ ማኅበረሰብ ዘንድም ሣቅና ሥላቅ እንዲጎርፍበት ሙከራ ማድረግ ነው፡፡ አንድ ሰው በአንድ ሰው ላይ ሊኖረው የሚገባው የማጥላላትና ጥላሸት የመቀባት መጠን ገደብ ሊበጅለት እንደሚገባ ስለማምን ይህን በሳይጋገር ተቦካ የምዕራብ ልቅ ዴሞክራሲና የ911 የሕጻናት ወደፖሊስ መደወያ ስልክ ዓይነት ሞልቃቃነት የተበከለ ስድ አደግ ወጣት ‹ጋዜጠኛ› ልኩን እንዲያውቅ ለማድረግ ፈለግሁና ብዕሬን እያነሳሁ በ‹ይቅርብኝ›ና በ‹ጽፌው ይውጣልኝ› መንታ ሃሳብ መካከል ስባዝን ቆይቼ በመጨረሻው ተሳካልኝ መሰለኝ ይሄውና ጀመርኩ፡፡ እንደነዚህ ዓይነቶችን ሰለጠነች ሲሏት የባሏን መጽሐፍ ያጠበችዋን ሴትዮ የመሳሰሉ አሻቃባጮችንና ቅቤ ጠባሾን በጊዜ ሃይ ካላልናቸው ነገ  እላያችን ላይ ሊያቀረሹ ቢነሱ የሚከለክላቸው እንደማይኖር መገመት አይቸግርም – ሞት በእንቅልፍ እንደሚለመድ አምባገነንነትና ነፍራቃነትም እንዲሁ ከልጅነትና ከልጓምየለሽነት ይጀምራል – መሰልጠንና መማር ጥሩ ነው፤ ግን ልክንና ገደብን ማወቅ መልካም ነው፡፡ በፈረንጅ ፍርፋሪ ሆድን ቀብትቶ አለልክ በመጥገብ ባህልንና ሀገራዊ ጨዋነትን መርሳትና መደፍጠጥ ዋልጌነት እንጂ ሥልጣኔ ሊባል አይችልም፡፡ የመናገር ነጻነት አለን ብለው በፈረንጅ ሀገር የፈረንጅ በርገር በቆመጠ አፋቻው ከኢትዮጵያዊ ጨዋነት ጭራሽ ባፈነገጠ መንገድ ክቡርና ንዑድ ዜጎቻችንን እንዲህ ሲዘልፉ ዝም ማለት በትንሹ ነውር ነው – ከፍ ሲልም የመተባበር ያህል ነው፡፡

ይህ ወጣት የኢሳት ጋዜጠኛ (አሁን ድረስ በዚያ ቦታ ካለ) በጣም ያበዛዋል፡፡ የዴሞክራሲን መብት ከአቅሙ በላይ – አቅም ምን ማለት እንደሆነ ከገባው – እየለጠጠና ከኢትዮጵያዊ ዐውድ እያወጣ ሊያባልገው ስለሚፈልግ ይመስለኛል ልጁ የሚደግፈውንና የሚቃወመውን እስካለማወቅ በደረሰ ውዥንብር ውስጥ ገብቷል፡፡ በመሠረቱ መናገር መብቱ ነው – እኔ ልቅርና የሚኖርበት የካናዳ መንግሥትም ይህን መብቱን አይከለክለውም – ግን እንዴት እንደሚናገር ካላወቀበት አፍ የተፈጠረው ለምን እንደሆነ ለማስረዳት እንገደዳለን፡፡ ማንንም መተቸት መብቱ መሆኑ ግልጽ ሆኖ ሳለ ጎራ በለወጡ ቁጥር የነበሩበትን ጎራ የቀድሞ የትግል አጋር እንዳይሸጡ እንዳይለወጡ አድርጎ ለመሳደብና ባልተገራ ብዕርና አንደበት በሥራየቤታዊ አሽሙርና አግቦ ለማሽሟጠጥ መሞከር እዚያም ቤት እሳት መኖሩን ከመርሳት የሚመነጭ አጉል ተመፃዳቂነት ወይም የለዬለት ዕብደት ነው፡፡ አፍ ሲከፈት ጭንቅላት ብቻ ሣይሆን አቋምና ዓላማም እንደሚታይ መረዳት ተገቢ ነው፡፡ ሌሎቻችንም ከዚህ ነጥብ አንጻር ብዙ የሚቀረን ስለማንጠፋ የየኅሊናችንን ጓዳ እንፈትሽና ኢትዮጵያዊ ጨዋነታችንን ለማደስ እንሞክር፡፡

እኔ የብርሃኑ ነጋ አቦካቶ አይደለሁም(ለፕሮቶኮል አጠራሩ ጌታ ሲፈቅድ እንደርስበታለንና ይቅርታ፤ – እንደዚያ መደዴ ልጅ ግን ‹ዲባቶ› ብዬ ባልተለመደ ስያሜ በሰው አላላግጥም – በነገራችን ላይ ‹ዲባቶ› በዶክተር መስፍን አረጋ ከ‹ዲብ› እና ከ‹አቶ› ተቀምሮ ‹ዶክተር› የሚለውን ዓለም አቀፍ ቃል ባማርኛ ለመተካት የቆመ አዲስ፣ እንደኔ ደግሞ በ‹ሳይቸግር ጤፍ ብድር› አንድን ምሁር አለወቅቱ በከንቱ ያስጨነቀ ግራ አጋቢ ቃል ነው – ከዚያ በፊት ስንትና ስንት የመኖርና ያለመኖር ሀገራዊና ማኅበራዊ ጭንቀቶች እያሉብን ማለቴ ነው፡፡)  እውነት ታፈነች ብዬ በገመትኩበት አገባብ ግን የትም ቦታ እገባለሁ፤ ለሁሉም ስለሁሉም ሆኜ በደልን ብናገር ደስ ይለኛል፡፡ ስለዚህ ብርሃኑ በግንቦት ሰባት መሪነቱ ሳይሆን ለሁላችንም እናት ለእምዬ ኢትዮጵያ ሲል ብዙ ነገሮችን ትቶ በመሰለው የትግል መስመር ተሰልፎ እየታገለ ያለ በመሆኑ በዚያም ምክንያት ሌላው ይቅርብኝና ንፍጡን ባልጠረገ ሕጻን ሲሰደብ አላስቻለኝም፤ ወርቅ ላበደረ ጠጠር መመለስ ግፍና ስብዕናን እጅግ በጣም የሚያቀል ብልግናም ነው፡፡ ያ ልጅ የሠራው ሥራ በእኔና በመለስ የቃላት አጠቃቀም ለመግለጽ እጅግ መረን የወጣና ወራዳነትም ነው፡፡ የጎበዝ ደመወዙ ቢያንስ ምሥጋናና ሙገሣ እንጂ ስድብና አሽሙር ሊሆን አይገባም፤ አለመታደል ሆኖ ሀገራችን የምታፈራቸው አንዳንድ ፖለቲካዊ ወጣቶች  ነውር የማያውቁ፣ ከሃይማኖትም ከባህልም የወጡ ዐይን አውጣዎች እየሆኑብን መጡ – በዚያም ሳቢያ በማያውቁት እየገቡ ነገር ሲዘነኩሩ በቀናነት ለሀገራቸው የሚታሉ ዜጎችን ያስቀይማሉ፤ የነሱን ያልተገራ ስድ አንደበትና ብዕር በመፍራትም ብዙዎች ራሳቸውን እንደሰጎኒቷ በየሥርቻው እንዲደብቁና የመለኮትን ሥራ ብቻ እንዲጠባበቁ ይገደዳሉ፡፡ እግዜር ይቅር ይበለንና ስድነትንና ዋልጌነትን ከመካከላችን ያስወግድልን፡፡ እናም በጀመርኩት ባለጌን የማጋለጥ መንገድ ትንሽ ለመግፋት ያህል  ባለጌን  ባለጌ ካላሉት ጭቃ መቀባቱ፣ በተለይ በየዋሃን ዘንድ የተወሰነ ተፅዕኖም ማሳደሩ አይቀርምና በቶሎ ልንነጋገርበትና መፍትሔ ልንፈልግለት ይገባል እላለሁ፡፡ ብርሃኑ ወይም የድርጅቱ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል፣ ልጁን እንደዕብድ አይተው ወይም ዐውቆ አበድነቱን በመረዳትና በሽታው ለቀቅ ሲያደርገው የሚያበረክተውን አወንታዊ አስተዋፅዖ ከቁብ ቆጥረውለት ንቀው ሊተውት ይችላሉ እንጂ ለዚህ ቆላ ደጋ ለሚኳትን ጎልማሳ የሚመጥን አንደበት ምላሽ እንደማያጡ እገምታለሁ – ለነገሩ ለዕብዱ ሁሉ መልስ ከሰጡ መደበኛ ሥራን መሥራትም የሚቻል አይደለም፡፡ እኔ ግን ‹መሳደብ› እያማረኝ ስሜቴን አፍኜ አልቀርምና ትንሽ መተንፈሴ ነው፡፡

ጥራዝ ነጠቅ ዕውቀቴን ልጠቀምባት መሰለኝ፡፡ በሥነ ልቦና ትምህርት አካባቢ Multiple Personality Disorder (MPD) የሚሉት ነገር አለ፡፡ ይህ የበሽታ ዓይነት በአንድ ሰው ላይ የሚታይ ወይም የሚከሰት የተደበላለቀ ስብዕና ውጤት ነው፡፡ አንድ ሰው ብዙ የተለያዩ ሰዎችን ሆኖ እርስ በርስ እስከመቃረንና የሚወደውንና የሚጠላውን ለመለየት እስከመቸገር የሚደርስበት አደገኛ ሥነ ልቦናዊ ህመም ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ሰው  -mania –  paranoia –   -phobia ወዘተ. የመሳሰሉ የሥነ ልቦና ደዌያት ዋሻ ነው፤ አበደ ስትለው ይሶብራል፤ ሣቀ ስትለው ሊያለቅስ ይችላል፡፡ እየሰደበህ ሳለ አለበቂ ምክንያት በቅጽበት ተለውጦ በፍቅር ጉንጮችህን ሊስምህ ይችላል፡፡ ይህ ልጅ ከነዚህ በሽታዎች በአንዱ ወይ በሌላው አለበለዚያም ከሁሉም ከሚውጣጡ የተወሰኑት  ህመሞች የተጠቃ ይመስለኛል፡፡ በዚህን ጊዜ ታዲያ ዘመድና ጓደኛ ወሳኝ ነው፡፡ የሥነ አእምሮ ሀኪም ዘነድ ሊወሰድና ሳይብስበትና ጨርቁን ሳይጥል ወገናዊ ረድኤት ሊደረግለት ይገባል፡፡ በሽታው አሳዛኝ ነው፤ ወቅት አይመርጥም፤ የሚዘረጥጣቸውን ሰዎችም እንደዚሁ፡፡ ልጁ በወቅቱ ከታከመ የነገ የሀገራችን መመኪያ ከሚሆኑ ዜጎች ውስጥ የማይካተትበት ምክንያት የለም፡፡ እንዳሁኑ ከሆነ ግን ያስፈራል፡፡ ሰው ካልታመመ መቼስ ከመሬት ተነስቶ ለመታወቅም ይሁን ላለመረሳት ሲል ይህን ያህል በሰው ላይ ሊያውም ሳይደርሱበት እንዲህ ሊሞላፈጥ ባልተገባው ነበር፡፡ እንግዲህ ትችቴንም ሆነ የትችቴን መንስኤ – ህመሙን – ቻል ያድርገው እንጅ ምንም ማድረግ አልችልም፡፡ በግጥም ለመጣ ደግሞ በግጥም ነው መልሱ፡፡ አፉን ከመክፈቱ በፊት ሊጠነቀቅ ይገባው ነበር፡፡ ብዙ ጊዜ ቆላ ደጋ ሲዘለባብድ ስለማየው ቢያንስ አንዴ መልስ መስጠቱ መጥፎ አይመስለኝም፡፡

ብርሃኑን መሳደብ ለምን ፈለገ?

እንደውነቱ ይህ ልጅ ብርሃኑን ብቻ አይደለም የሚሳደበው(አደራችሁን አሁንም ልድገመው – ብርሃኑ የኔ ‹ጥብቅና› የማያሻው፣ ለጋራ ቤታችን የታሰረ – የተንገላታ – ሞትም ዕድሜ ይፍታህም የተፈረደበትና ለጊዜው ሀገር አልባ ከርታታ መሆኑን የማስታውሳችሁ አይበልብንና ነገ እርሱም አንዳች አሉታዊ ነገር ብሰማበት ከማንም በባሰ ባለችኝ ጎልዳፋ ብዕር የምዘምትበት አንድ ተራ ዜጋ መሆኑን በማስገንዘብ ጭምር ነው፤ አሁን ግን በአንድ ጎራ ውስጥ ነን የምንል ወገኖች በተለይ አንዳችን የአንዳችንን ስብራትና ክሽፈት ሳንመኝ በተሰለፍንበት ጎራ ወደነጻነት አምባ እንገስግስ፤ በከንቱ አንጠላላ፤ ባልተጨበጠ ሥልጣንም በምቀኝነትና በተንኮል አንጠላለፍ፤ ከእስካሁኑ ገልቱ አስተሳሰባችንና ሞኝነት የተሞላበት አካሄዳችን ብዙ እንማርና ከ‹ከብቱ ሳይገዛ ሌባው በረት ሞላ› ብሂል ገምቢ ትምህርት ቀስመን ተሰባብረን ላለመቅረት እንተባበር …፡፡) የዚህ ልጅ ወፈፌነትና የብዕር ጦር በብርሃኑ ብቻ ቢያበቃ ምንም አልነበረም፡፡ ምክንያቱም ታጋይ ብርሃኑ ቢያንስ በስሜት ወደወጣትነት ዕድሜ የሚስበው በመሆኑ የትኩስ ኃይልን የስሜት መዋዠቅና በአዳዲስ ንፋስ የመወሰድ አባዜ ስለሚረዳ ንቆ ይተወዋል የሚል ግምት አለኝ፡፡ ይህ ልጅ ግን ትልልቆቹንም ጭምር ነው የሚያንጓጥጠውና የሚዘረጥጠው – ነገረ ሥራው ሁሉ ‹ባልጠጣው ላደፍርሰው› ዓይነት አባዜ የተጣባው ነው፡፡ ዲግሪውን ያገኘው በአሽሙርና በማንጓጠጥ የሰይጣን ትምህርት ሳይሆን አይቀርም ፤ ሽሙጥ ‹is his favorite hobby›.  በዚያን ሰሞን “የመቶ አለቃ አያልነህ ደሴን ጽሑፍ አላነብም፤ ምክንያቱም ተከታታይና ረጃጅም ስለሆኑ”  ማለቱን አስታውሳለሁ፡፡ የሚገርመው በራሱ ምስክርነት መሠረት ያላነበበውን ጽሑፍ ለመተቸት መነሳቱ ነው፡፡ ምን አስፈለገው? እኔ ብሆን የማላነበውን ጽሑፍ በጭራሽ አልተችም፡፡ እሱ ግን ለተንኮሉ ሲል ምናልባት አንዲት ዐረፍተ ነገር ቦጭቆ ሰውዬውን ወርዶባቸዋል ማለት ነው፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፡፡ የልጁ ዕብደት በራሱ አንደበት ሲመሰከር – እጠቅሳለሁ – “የምጽፈው ነገር አቧራ ካላስነሳ የጻፍኩ አይመስለኝም፡፡” የጥቅሱ መጨረሻ፡፡

ታዲያ እሱ አቧራ ማጨስ ባማረው ቁጥር የኢትዮጵያ ነጻነት ታጋዮች መሳቀቅ አለባቸው ማለት ነው? በረት እንደሚያውክ ቀንዳም ሰይጣናዊ በሬ ዘወትር የሚያምሰንና በትግላችን ጥረቶች የሚያሾፍብን ለምንድነው? የሚፈልገውን ፈልጎ ያገኘ የማይመስለውና ፍላጎቱን በመፈለግ ላይ የሚገኘው ይህ ወጣት ፍላጎቱን በመፈለግ ሂደት ውስጥ ለምን እኛን ይረብሸናል? እሱን አቧራ የማቡነን ወልፉ ውል ባለው ጊዜ ሁሉ ‹ዛሬ ደግሞ የትኛውን ታጋይ ወይም ድርጅት ይዘፍንበት ይሆን?› በማለት ለምን እንሳቀቅ? በሥልትነት በያዘው እንደመጽሐፍ ቅዱስ በሚደረድራቸው ቁጥሮች ሥር በሚያሰፍራቸው ተሳዳቢና ዘርጣጭ አስተያየቶቹ እስከመቼ የነጻነት ትግል ይበጥበጥ? የለም፣ የለም፤ እቅጩ ይነገረውና መጻፉን ያቁም ወይም ትክክለኛ ህክምና አግኝቶ ወደኅሊናው ይመለስ – በስድብ የተቃኘ ሰው ለማንም አይጠቅምምና የሚመለከተው ሁሉ ያስብበት፡፡ አላማረበትም፤ ሰውም ሳቀበት እንጂ አልሳቀለትም፡፡ ‹ወያኔ ነው› መባል የደስታ ምንጩ የሆነ ሰው በሽተኛ እንጂ ጤነኛ ሊባል አይችልም፡፡ ሰው ማለት ሰው የሚለውን የሚሰማ እንጂ ችኮና ደረቅማ ድንጋይም እንደዚያ ነው፡፡

ኢትዮጵያዊው የመከባበርና የጨዋነት ባህል የት ገባ? ማን ነው ያሳደገው ይህን ልጅ? የእርሱ ብልግና ለምን ወላጆቹ ዘንድ ድረስ እንዲዘልቅ ፈቃደኛ ሆነ? ‹አሳዳጊ የበደለው› ወይም ‹በጨዋ ቤተሰብ ተኮትኩቶ ያላደገ› መባል እኮ ዘመን የማይሽራቸው የባህል ትውፊቶ እንጂ የዴሞክራሲ ግኝቶች አይደሉም፡፡ አውሮፓና አሜሪካ መሄድ ደግሞ ይህን ያህል በሰውና በሀገር ላይ የሚያዘባንን አይመስለኝም፡፡

እስካሁን ለምን እንደምጮህበት በማስረጃ የተደገፈ ጥፋት አላነሳሁም፡፡ ይህን ማድረግ ቀላል ነው፡፡ ግን የእስካሁን ጽሑፎቹን ያነበበና የተናደደ ሁሉ ለምን እንዲህ እንደምብከነከን ይረዳልና የርሱን ሞልፋጣ ሃሳብ እንደገና እዚህ እያወሳሁ የሰደባቸውን መልሼ ለሰዳቢ አልዳርግም፡፡

በብርሃኑ ላይ ሰሞኑን በጻፈው ስድ መጣጥፉ ላይ በመጥፎ ሃሳብነት የጠቀሰውን ጽሑፍ ግን ከዚህ በታች በመጨረሻው አካባቢ አስቀምጫለሁ፡፡ እሱ እንዳለው በብርሃኑ ጽሑፍ ገጽ 16 መጨረሻና ገጽ 17 መጀመሪያ ላይ የሚገኘውን ነው በራሴው ግምት ቆንጥሬ እዚህ ላይ ያኖርኩት፡፡ ምናልባት እርሱ ከሚፈልገው ውጪ ጨምሬበት ከሆነ ይቅርታውን፡፡ ይህ የብርሃኑ ጽሑፍ ግን ልጁ ልዩ አጀንዳ ከሌለው ወይም ካልታመመ በስተቀር ያን ያህል የሚያንዘረዝር ነገር አላገኘሁበትም፡፡ ለታመመ ሰው ግን ‹እንዴት አደርክ›ም ሊያናድደው እንደሚችል አውቃለሁ፡፡ ሰላም ለሰላማውያን እንጂ ለሃበሾዋም ሰው አይሆንም፡፡

ብርሃኑ በተጠራበት ታላቅ ጉባኤ የ21 ገጽ ወይም የ55 ደቂቃ ንግግር ማድረጉ ምንድነው ጥፋቱ? ረጂም ንግግር ማድረግ ያን ያህል ሊያሰድብስ ይገባ ነበር ወይ? ‹ለቦና ጥጃ ውስ ምን አነሰው› እንደምንል ቀለል ባለ አቀራረብ ንግግሩ መርዘሙን ጠቁሞ ለወደፊቱ ማስተካከያ እንዲደረግበት ቢቻል በውስጥ ለውስጥ ማስታወሻ ባይቻልም በመጣጥፍ መልክ ማቅረብ እንዴት አልቻለም? ለዚህ ቀላል ነገር  ያን ያህል አቧራ ማጨስ ለምን ዓላማ? በትግል ወቅት እንዲህ እያላገጠ ገመናን ለባላንጣ መሸጥ የጤና ነው ወይንስ የበሽታ?  ይህ ልጅ የዴሞክራሲ አዳይ ደልዳይ ቢሆን ምን ያሳየን ይሆን? ይህን የተጣባውን ዕብሪትና ትዕቢት ማን አሰረጸበት? ከካናዳ ወይንስ ከአሜሪካ? ከኢትዮጵያ ይዞት ወጣ ወይንስ እዚያው አገኘው? መተቸት ቢኖርበትስ ቀናነት በጎደለውና ትምክህት በወጠረው ሰይጣናዊ አቀራረብ እንዲያ መዘላበዱ ማንን ለማስደሰት ወይም ምን ይዞ ወደማን ለመጠጋት አስቦ ይሆን? በጣም አጠያያቂ ነው፡፡ ልጁን በዕብድነትና በእንደልቡነት መፈረጅ ብቻውን አይበቃም፤ ምናልባት he might be a mole installed by the Woyenti among the opposition,(የልጁን ደረጃ ወደዚህ ማድረሴ ምናልባት ትንሽ ለጠጥ አድርጌው ሊሆን ይችላል፤ ግን ምርጫዎቼ ጠበቡብኝና ተቸገርኩ – ሰው ወድዶ አይደለም ወዳጁን የሚያማ) ለማንኛውም ወንድሜ፣ ‹ጠርጥር ገንፎም አለው ስንጥር› ነው ነገሩ፡፡ የሆነው ቢሆን ግን የባቡሩን ፍጥነት ማንም አይቀንሰውም፤ ከባቡሩ እየተስፈነጠሩ የሚወጡት ሰዎች ቁጥርና ማንነት ምንም ያህል ቢያስጨንቀንም የባቡሩ መጓዝና በነጻነት ፌርማታ ላይ ሄዶ መቆም በቅርቡ የሚጠበቅ ታሪካዊ ጉዞ ነው፡፡ ወደፊት ኅሊናን የሚፈታተኑ ብዙ ጉዳዮች እንደሚገጥሙን የታመነ ነው፤ የነጻነት ጉዞ ረጂምና አሰልቺ፣ ብዙ መስዋዕትነትንም የሚጠይቅ፣ ብዙ ወጭ ወራጅም ያለው … ታላቅ ማኅበረሰብኣዊ ክስተት ነው፡፡ ስለዚህ እገሌ ወረደ እገሌ ተሣፈረ በሚሉ የወጭ ወራጅ ጉዳዮች በመጠኑ መታመሳችን የሚጠበቅ ይመስለኛል፡፡ ደግሞም ‹ኋለኞች ፊተኞች፤ ፊተኞችም ኋለኞች ይሆናሉ› መባሉን አንርሳ፡፡

ደግሞስ ልደቱ አያሌውንና ጃዋርን እወዳቸዋለሁ የሚለው ማን አትውደዳቸው እንዲለው ፈልጎ ወይም ምን እንድንለው ሽቶ ይሆን? ዘመድ ከዘመዱ አህያም ካመዱ የተባለው ብሂል ዛሬ መች ሆነና የተጀመረው? ለመሆኑ ብርሃኑንና ጃዋርንስ ምን አገናኛቸውና ነው ‹ከብርሃኑ ጃዋር ይሻላል› እያለ ሀገራችን ያልበላትን የሚያክላት? ዕውቀት በዝቶበት ባፍንጫው እየመጣ ሊያናፍለው ይችል ይሆናል፤ የዝነኝነት አባዜ እየወዘወዘው እንቅልፍ ሊያሳጣው ይችል ይሆናል፤  ወደ ወያኔ ጎራ ጎትቶ ሊያስገባው የሚፈልግ አንዳች አጋንንታዊ መንፈስ ተጠናውቶት ሊሆን ይችል ይሆናል፤ … በብዙ ምክንያቶች የተነሣ ይህ ልጅ በሥነ ልቦናዊ ቀውስ ውስጥ ተዘፍቆ ሊሆን ይችላል፤ በሌላም በኩል ማን ያውቃል ያደገበት ቤተሰባዊና አካባቢያዊ ዳራ በጠብና በሁከት የመስተፃልዕ አባዜ የተቀነበበ ይሆንና ከፍቅርና ከስምምነት ይልቅ በአምባጓሮና በጭቅጭቅ እንዲሁም በአግቦና በምፀት ብዙ የልጅነት ሕይወቱን አሳልፎ ሊሆንም ይችላል – ‹ችግር ነው በታዳጊ አገር መወለድ› ጎበዝ፡፡ ይሁንና ግን በፈለገው ዓይነት የውዴታም ይሁን የግዴታ  ህመም ውስጥ ቢገባ ይህን ያህል ዐብዶና ሰክሮ በንጹሓን ኢትዮጵጳያውን ታጋዮች ላይ በ‹ጠብ ያለሽ በዳቦ› እንዲፏልል ሊፈቀድለት አይገባም፡፡ ይታወቅልኝ –  ሰውን አይተች እያልኩ አይደለም – ነገር ግን እውነትን ይያዝ፤ በጨዋ ደንብ ይተች፤ ትከሻው ሊሸከመው ከሚችለው በላይ እየተንጠራራ ከፍተኛና ታላቅ ዕውቀትና ብስለትን የሚፈልጉ ታሪካዊ ኃላፊነቶችን አይሸከም፡፡ ለምሳሌ እሱ ማን ሆነና ነው የፖለቲካ መሪንና የፖለቲካ ተንታኝን ሚና ለይቶ አንዱን ለመንቀፍ ሌላውን በሌላው ወጪ ለማሞገስ የሚሞክረው? የምን መቅለል ነው? ማን ወይም የትኛው የፖለቲካ ፍልስፍና ነው ብርሃኑን ‹አንተ አፍህን ለጉመህ ፓርቲህን ምራ እንጂ የፖለቲካ ትንታኔ መስጠትም ሆነ የፖለቲካ አካሄድን መተቸት የለብህም!› ያለው? ማን ነው “ፖለቲካ ማለት ‹ግራህን ሲጠፉህ ቀኝህን ድገምለት› ዓይነት የ‹ብፁዓን ምሁራን› የሙያ ዘርፍ ነው” ያለው? ይህ ልጅ፣ ሥልጣን እንደያዘ የዛሬ አራት ዓመታት አካባቢ ‹ምሁር የነበረው ኦባማ› ዛሬ ወደ‹ደደቡ› ‹ጡንቸኛ› ቡሽነት ተለውጦ ሦርያን እንደብድብ አንደብድብ እያለ ነው የሚለን፣ ምሁር ሀገርን ሲያስተዳድር እንደብራህማና እንደክሪሽና በኢንላይትንመንት የተመስጦ ጥበብ ወይም እንደክርስቶስ በመስቀል እየተቸነከረ በመንፈሳዊ የመለኮት ፀጋ ያስተዳደር እንጂ ወታደር አያስፈልግም ማለቱ ይሆን? ዶክተር ሀገርን ሲመራ ለወራሪ እጅን መስጠት ብልህነት ነው እያለን ይሆን? ይህን የተወነጃበረ ግንዛቤ ከየት ሸመተው? የምን መቀዣበር ነው? ትንሽ ዕውቀት አደገኛ መሆኑ ተዘውትሮ የሚጠቀሰው ለዚህ ነው ለካንስ – ወዳጄ እንትናዬ እባክህን አንብብ፤ ተማር፤ ጠይቅ፤ የማትችለውን ነገር ለመሸከም ከመሞከርህ በፊት የትከሻህን ጥንካሬ ፈትን – አለዚያ ትወድቃለህና ይቅርብህ – ሰዎች ሣቁልኝ ወይም አደነቁኝ ብለህም ገደል አትግባ፤ ለዝናና ታዋቂነቱም ገና ልጅ ነህና ትደርስበታለህ፡፡ የሰውን የተከበረ ስብዕና ለማጣጣል በመሞከር የምታገኘው የመሠሪ ጠላቶች ጭብጨባና ድጋፍ ይቅርብህ – ኋላ ትዋረድበታለህ፡፡ ይህ ዓይነቱ ጣጣ ራስን ያለማወቅ ችግር የሚያስከትለው ጠንቅ ይመስለኛል፡፡ አለማወቅን በማንበብና በታጋሽነት፣ ቁም ነገርን ከሰዎች በማዳመጥ ማስወገድ ሲቻል አለልክ መንጠራራት ለትዝብት ብቻ ሳይሆን ለከፍተኛ ነቀፌታና የሰላ ትችትም ይዳርጋል፡፡

ለማንኛውም ከመጠምጠም መማር ይቅደም ይባላልና ይህ ዠብራራ ልጅ የሚሠራውን አጉል ጀብደኝነት ይተው፡፡ የተቃውሞው ጎራ ድረገጾችም በብዙ ነገሮች ላይ ማስተዋልን ቢጨምሩ መልካም መሆኑን በእግረ መንገድ መጠቆም እፈልጋለሁ – አለበለዚያ ለዐይን ይበጃል ያሉት ኩል ተመልሶ ዐይንን ማጥፋቱ አይቀርም፤ መጠን ያልተበጀለት ሃሳብን በነጻ የመግለጽ ድባብ በተለይ ዴሞክራሲ በዳዴ ደረጃ ባለበት የኛን መሰል ሀገራት ውስጥ የሚያስከትለው ጉዳት ከፍተኛ ነው – ማየት ጥቂቱን ሳይሆን አብዛኛውን ነው፤ በውነቱ ገና ብዙ ይቀረናል፡፡ … ፡፡ ይህን ሁሉ የምለው በአስተያየቴ ያ ልጅ ይማራል ወይም ያኛው ይሸልመኛል ወይም ተነብቤና ተደምጬ ለውጥ አመጣለሁ ብዬ አይደለም – በጭራሽ፡፡ ከኔ እንዳይቀር ግን እፈልጋለሁ፡፡ ዘመኑ የውልክልክና የውዥንብር መሆኑን፣ ዘመኑ የድንቁርናና የመገፋፋት መሆኑን፣ ዘመኑ የመጠላለፍና የንቁሪያ መሆኑን፣ዘመኑ የመናናቅ፣ የትምክህትና የትዕቢት መሆኑን፣ … በጥቅሉ ዘመኑ የዲያብሎስ መፈንጪያ መሆኑን አላጣሁትም፤ ከእባብ ዕንቁላል እርግብ እንደማይፈለፈል የሚረዳ ሰው ለመናገር ያህልም ቢሆን ከተናገረ በቂው ነው፡፡ በዚያውም ላይ ‹ትናንት እንዲህ ብለን ነበር› ለማለትና ‹ትናንት እንዲህ ይባባሉ ነበር› ለሚሉ የወደፊት ወገኖቻችንም መማሪያ ይሆን ዘንድ እንዲህ እንጽፋለን፤ ይህ ጽሑፍ ሰው ሊያነበው እንዲደረግ ቢደረግ እሰዬው – ያም ባይሆን ታፍኖ መቅረት ብርቃችን ባለመሆኑ የቅርጫት እራት ሆኖ መቅረት ማቅ የሚያስለብስ ነገር አይደለምና ማንኛውም ነገር ምንም ማለት አይደለም፡፡ በቃ፡፡ ይልቁንስ ታዲያን ለአዲሱ ዓመት ዋዜማ እንኳን በ‹ሰላም› አደረሰን፡፡ 2006 የድልና የነጻነት ዘመን እንዲሆን የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ይርዳን፡፡

የዘነጋሁት አንድ ነገር፡- ትግላችን እንደስካሁኑና እንዳሁኑ በሃይማኖት ማዕቀፎች ውስጥ ተጠርንፎ የሚካሄድ ከሆነ የትም አንደርስም፡፡ እስላምና ክርስቲያን በመባባል ወይም አንዱ ሌላውን በመፍራትና በመጠራጠር የሚደረግ ትግል ከመጀመሩ ይከሽፋልና ትግልን ከመስጊድና ከቤተ ክርስቲያን አውጥተን ሁሉም ሊገናኝበት በሚችል በገላጣ ሜዳ ላይ እናድርገው – አንዱ የሌላውን ትግል እያጮለቀ በጥርጣሬና በሥጋት ማየቱ ካልቆመና ሁሉም እጅ ለእጅ ካልተያያዘ የተናጠል ልፋታችን ሁሉ ከንቱ ነው፡፡ አንዱ ሲጮህ ሌላው የማያዳምጠው ባለመተማመናችን ምክንያት ትግሉ ሌላ መልክ ስለሚይዝ እንጂ ሁሉም በአንድ ሀገራዊ የጋራ አጀንዳ ቢተባበር እስካሁን ወያኔ ጠፍቶ ነበር – ያ አጀንዳ ደግሞ ‹መሪየን እኔው ልምረጥ፣ በቤተ አምልኮቴ አትግቡብኝ፣ ቀኖናው እንዲህ አይልም፣ ወዘተ.› ከሚለው ተራና አንድ ጽንፍና አንድ የእምነት መንገድ ከያዘ የትግል ማዕቀፍ ወጥቶ ሁሉን ወደሚያስከትል ትልቅ የነጻነት ኹዳድ መግባት ይገባዋል – ከዚህ መልስ ያለው ሁሉ ጉንጭ አልፋና የትም የማያደርስ ነው- በዚህ እንተማመን፤ ደግሞም አፋችን ቢክደው ልባችን ያውቀዋል፤ ወያኔ እየኖረ ያለውም ይህ በመጥፋቱ ነው፡፡ ስለዚህ ይህን የጋራ ትግል ከእምነት ቦታዎችና ከእምነት ጥያቄዎች አውጥቶ ሀገራዊና ሰብኣዊ በማድረግ ለጋራ ድል የሚያበቃን መድረክ በአፋጣኝ መመሥረት ይገባዋል፡፡ አላህም ሆነ እግዚአብሔር በኋላ አያመልጡንም፤ ቦታቸውን ሳይለቁ እዚያው ልናገኛቸው እምንፈልግበት ቦታ ተቀምጠው እናገኛቸዋለን፡፡ አሁን እየጨረሰን ያለው አላህንና እግዚአብሔርን በወኪሎቹ አማካይነት ‹ተቆጣጥሮ› የዋህነታችንንና ሃይማኖተኝነታችንን እየበዘበዘ የሚገኘው ሃይማኖት የለሹና ሃይማኖት አጥፊው ወያኔ ነው፡፡ ዝርዝር ኪስ ይቀዳል፡፡ ሁሉም ነገር ውሉን ባይስትም ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡ ሀገር ሳይኖረን ሃይማኖት ይኖረናል ብለን ካመንን ለወያኔ እንደተመቸን እንኖራለን፡፡ የ/በሃይማኖት መለያየት ነጻነትን ሊያዘገይ አይገባውም፡፡ ግን የጊዜው ችግራችን እሱና እሱም ብቻ ይመስለኛል – ወያኔ ዘርቶ ካበቀላትና ኮትኩቶ አሳድጎ ለፍሬ ካበቃት የዘረኝነት አባዜ በተጓዳኝ ማለት ነው ፡፡ ሃይማኖታችንንና ዘውጋዊ ማንነታችንን እንዳመላችን በጉያችን ይዘን በአንዲት ሀገር ልጅነት ለነጻነታችን እንታገል፡፡ ከሃይማኖታችንም ሆነ ከዘውጋዊ ማንነታችን በፊት ያገኘነው ሰውነትን በመሆኑ በሰው ልጅነታችንና በወያኔዎች እንድንጠላው እየተገደድን በምንገኝበት ኢትዮጵያዊነት ብቻ እንሰባሰብ… ያኔ መንገዳችን ቀኝ በቀኝ ይሆንልናል – የኛ የሆነን ማን ሊቀማን ይችላል? ( ይሄ ‹አማራነቴን ካልተቀበልክ እንትንነትህን ቀቅለህ ብላው!› ዓይነቱን የጅሎች ፈሊጥ አሁኑኑ እንሰርዝ! ጠላት ያሠረገብን የከፋፍለህ ግዛ ሥልት ነውና አልጠቀመንም – መቼም ቢሆን አይጠቅመንም – ማንነታችን የት ይሄዳል ማንስ ይወስድብናል? ከስሜታዊነት ወጥታችሁ በተመስጦ ስታስቡት ይህ ነገር የሞኝነቶች ሁሉ አውራ ሞኝነት አይመስላችሁም?)  ጊዜ ሳይነጉድብን እንለወጥና ሰው እንሁን፤ አሁን ብዙዎቻችን ጎደሎ ሰዎች ነን!!! ለዚህም ነው ጎደሎ መሪዎችን ፈጣ በላያችን ላይ ያስቀመጠብን፡፡ ነገርን በገርነት እንረዳ፤ ሸርን ለሸረኞች እንተው፡፡ በግልጽ ከተነጋገርን የተሟላ ስብዕና እንዲኖረን በርካታዎቻችን ብዙ ጥረት ይቀረናል፡፡…

ለምሳሌ ኢማሙና ጳጳሱ አንድ ላይ ሲበሉ፣ አንድ ላይ ሲጸልዩ፣ አንድነት ሲተቃቀፉ፣ ጠላም ይሁን ቡቅሬ ወይም ኬኔቶ የሚፈልጉትን ነገር ይዘው በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ሲዝናኑ ያሳዩን … ምን ችግር አለው? ሰው የሠራው አጥር ለምን ያግዳቸዋል? በእውኑ በየቋንቋችን በፈለግነው ቃል የምንጠራው ፈጣሪ(ያችን) “ይህን ምግብና መጠጥ ከእነእንትና ጋር ብትበሉ ወይም ባትበሉ ትቀሰፋላችሁ፤ እስላምና ክርስቲያን በሥጋ ምግቦች ካልተለያያችሁ እስላሙም ጀነትን፣ ክርስቲያኑም መንግሥተ ሰማይን አታገገኟትም!…” ብሎ ዐዋጅ ያጸደቀበት የቅዱስ ቁርዓን ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ አንድ ምዕራፍ ይኖር ይሆን? እስኪ በጋራ እንፈልግ::  እነሱ በአጥር ተቆልፈው ምዕመኖቻቸው እንዴት ግምባራቸው ሊፈታና ሊቀራረቡ ይችላሉ? … ቆይ ብቻ! ነጻነት ትምጣማ…!

 

ከገጽ 16 መጨረሻና ከገጽ 17 መጨረሻ የብርሃ ጽሑፍ የተቀነጨበ ‹ወንጀለኛ› ሃሳብ!

 

የመጀመሪያው ጥያቄ እንግዲህ ይህ እንቅስቃሴ ከዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ስርዓት መርሆች አንጻር ሲታይ ተገቢ እንቅስቃሴ ነው ወይ? የሚለው ነው:: ከላይ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ የሀይማኖትና የፖለቲካን ግንኙነት በሚመለከት ካቀረብነው ትንተና አንጻር ስንመዝነው ይህ በፍጹም የሚያከራክር ጥያቄ አይደለም:: እንቅስቃሴው በመርህም፤ እየሄደበት ባለበት አካሄድም ተገቢ የሆነ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ነው:: ስለዚህም ጥያቄው ትክክለኛ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በሀገሪቱ እንዲመጣ የሚፈልግ ሀይል ከልቡ ሊደግፈውና ሊቀላቀለው የሚገባ፤ የዜግነት ጥያቄ ነው:: ድርጅታችን ግንቦት 7ም ይህንን የሙስሊሞችን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ የምንደግፈው ከመርህ አኳያ ነው:: እንዲፈጠር የምንፈልገውና የምንታገልለት አላማችንም ይህ የእምነት ነጻነት በሀቅ ተግባራዊ ሆኖ ማየት ስለሆነ፤ የሙስሊም ኢትዮጵያውያን እንቅስቃሴ በራሱ የትም ደረሰ የት፤ ከላይ በተነሱት መሰረታዊ የመብት ጥያቄዎች ዙርያ እስከሆነ ድረስ ትግሉን የራሳችን አድርገን የምንታገልለት ነው::

ከዚህ የመርህ ጥያቄ ቀጥሎ የሚቀርበው ይህ እንቅስቃሴ በፊት ለፊት ከሚያቀርበው ጥያቄ ባሻገር የተደበቀ ለልላ አጀንዳ አለው፤ ቢሳካለት በሀገሪቱ በሙሉ የሻሪያ ሕግን ተግባራዊ ለማድረግ የሚፈልግ፤ ይህ ባይሳካለት እንኳን በጣም አክራሪ የሆነ የሳላፊስት አስተምህሮትን ለማስፋፋት የሚያልም፤ ይህን ካደረገና በሰፊው መረቡን ከዘረጋ በኋላ ደግሞ ተመልሶ የሀይማኖት መንግሥት ለማቆም የሚፈልግ ነው፤ ስለዚህም ከመስፋፋቱ በፊት በአጭሩ መቀጨት አለበት የሚለው በዋናነት በመንግሥት ባለሟሎች የሚቀርበው፤ ግን በመንግሥት ፕሮፓጋንዳ በመደለልም ሆነ ባጠቃላይ የሀይማኖት አክራሪነትን በመፍራት ጤነኛ ከሆኑ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ከሚቀበሉም አንዳንድ ሰዎች የሚቀርበው ፍርሀት ነው:: ይህንን በሁለት መልኩ መመልከት ይጠቅማል:: በመጀመሪያ የዚህ አይነቱን ፍርሀት በሚመለከት ከእንቅስቃሴው ወይንም ከመሪዎቹ የቀረበ፤ ይህን እንድንጠራጠር የሚያደርገን ምልክት አለ ወይ? የሚለው ነው:: ከዚህም አንጻር እንቅስቃሴው ግለልጽ በሆነ ቋንቋ የሰጠው መለልስ አለ:: በተለያዩ አጋጣሚዎች የእንቅስቃሴው ተመራጭ መሪዎችም ሆኑ እንቅስቃሴውን የሚደግፉ ኃይልች እንደተናገሩት፤ እንቅስቃሴው ምንም እንዱህ አይነት አሊማ እንደላለውና እምነታቸውን በላሊው ማህበረሰብ ሊይ ለመጫን አለማሰብ ብቻ ሳይሆን እንዲህ አይነት አመለካከትን ብዙ የተለያዩ ሀይማኖቶች ባለባት ኢትዮጵያ ላይ ለመግፋት ማሰብ ባመለካከት ደረጃ ጤናማ አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን በተግባርም እብደት ነው የሚሆነው በሚለል በተደጋጋሚ የገለጹት ነው:: ከዚህ አንጻር ቢያንስ የእንቅስቃሴውን ዋና አካል የምንጠራጠርበት ምንም ምክንያት የለንም:: በሁለተኛ ደረጃ ግን ይህ ጥርጣሬ እውነትነት ያለው ቢሆን እንኳን ከላይ የተነሱትን ትክክለኛ የዴሞክራሲ ጥያቄዎች የሚያጣጥል ሊሆን አይችልም:: ባይሆን ጥያቄው ዴሞክራሲያዊ መሆኑን ከተቀበልን፤ ይህንን ጥያቄ በትክክለኛ አግባቡ መልሰን ከዚያ ውጪ የሚቀርቡ ከዴሞክራሲያዊ ስርዓት አንጻር አግባብ ያልሆኑ ጥያቄዎች በሚነሱ ጊዜ ያኔ መመለስ ነው የሚገባን:: የመናገር መብቱን የጠየቀ ግለሰብ ወይንም የማህበረሰብ አካል፤ ይህንን መብት ካገኘ ለብልግና፤ ሰውን ለማዋረድ ወይንም አልፎ ሄዶ ማህበረሰቡን እርስ በርሱ ለማባላት ሊጠቀምበት ይችላል በሚል ፍርሀት የመናገር መብቱን መከልከል እንደማይቻለው ሁሉ::

ከዚያ ባሻገር ግን አሁን ያለውን አለማቀፍ የሽብርና የአክራሪነት እንቅስቃሴ ባንዴ በኩልና ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት ሀይማኖቶችን እንደወረደ የሚተረጉመው የሀይማኖት ወግ አጥባቂነት ባጠቃላይ መስፋፋት፤ በተለይም ደግሞ እንዲህ አይነቱን አለማቀፋዊ መስፋፋት የሚገፉ ከፍተኛ የፋይናንስ አቅም ያላቸው ድርጅቶችና አንዳንዴም መንግሥቶች ባሉበት ሁኔታ፤ በኢትዮጵያ ያለው የሙስሊሙ እንቅስቃሴ ዋናው አካል ባይደግፈውም እንኳን በዚህ ሰፊ ህዝባዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ያደፈጡ አክራሪ ሀይሎች ሊኖሩ አይችሉም ወይ? እንዲህ አይነት አክራሪ ሀይልች ካሉ ደግሞ የሰፊውን የሙስሊም ኢትዮጵያውያን እንቅስቃሴ ማርከው ከላይ ወደተጠቀሰው አደገኛ “የፖለቲካ እስለልምና” አይከቱትም ወይ የሚለው ፍርሀት ነው:: የዚህ አይነት አደጋ በፍጹም የለም ብል አፍን ሞልቶ ለመከራከር አይቻልም:: እንዲህ አይነት ሰፊ ህዝባዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳታፊዎቹ ሁሉ ያላቸው ግንዛቤ፤ ሊደርሱበት የሚፈልጉት የመጨረሻ ግብ ሁላም አንድ አይነት ነው ለማለት አይቻልም:: ጥግ የያዘና የጦዘ አመለካከት ይዘው፤ ግን በመለስተኛ ግብ ደረጃ እንዲህ አይነት ህዝባዊ እንቅስቃሴዎችን በስልታዊ መንገድ ለመጠቀም የሚሞክሩ ሀገር በቀልም ሆነ የውጭ ሀይልች ሊኖሩ እንደሚችሉ አለመገመት ቢያንስ አጉል የዋህነት ሲከፋም አላዋቂነት ነው የሚሆነው:: …

Latest from Blog

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። ) “ገብርዬ ነበረ

ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ?

January 3, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ዛሬ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ጥር 1ቀን 2025 ዓ/ም ነው ። አውሮፓውያኑ አዲስ ዓመትን “ሀ” ብለው ጀምረዋል ። አዲሱን ዓመት ሲጀምሩም ከልክ ባለፈ ፈንጠዚያ ነው ። ርቺቱ ፣ ምጉቡና መጠጡ

ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። )

Go toTop