August 27, 2013
20 mins read

“ምን አዲሱ ትውልድ ብቻ የነገውም ዕዳ ውስጥ ተነክሯል”

ከሱሊማን አህመድ/ከለንደን

ወያኔ እንደወትሮው ሁሉ ለሥልጣኑ ማቆያ ወዳጅ ለማፍራት የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ግዛት በድብቅ እየተደራደረ የመሸጡን ተግባር ትልቁ ሥራው አድርጎ ገፍቶበታል። ይህንን አደገኛ የወያኔ ፕሮግራም መላው ኢትዮጵያዊይም ሆነ አለን የሚሉ የፖለቲካ ድርጅቶች (ትንሹም ትልቁም) በቸልታ የሚያዩት አገራዊ ጉዳይ እንዳልሆነ በጣም ግልፅ እየሆነም ነው።

ወያኔ በገፀ-በረከትነት ለሱዳን መንግሥት የሰጠው 1600 ኪ/ሜ ርዝመትና ከ30 እስከ 50 ኪ/ሜ የጎን ስፋት ያለው ለምና ማዕድን ያረገዘ መሬት “እባክህን ድሮ ለእኔ እንዳደረከው ዛሬ ደግሞ ለጠላቶቸ መከታ፣ ከለላና መተላለፊያ እትሁንብኝ” ብሎ የሰጠው ገፀ-በረከት ብቻ ሳይሆን ብዙዎቻችን እንደምንገምተው ዶላርም ተከፍሎት እንደሆነ አዳዲስ መረጃ እየተገኘ ነው።
ዛሬ ስልጣን ላይ ያሉት ነፍሳት በግልም በቡድንም ሲገመገሙ በፍቅረ-ነዋይ የሠከሩ፣ ራስ ወዳድና ይሉኝታ ቢስ በመሆናቸው ደረቅ ጡቷን እያጠባች ያሳደገቻቸውን ኢትዮጵያን እስክታልቅ ድረስ በካሬ – ሜትር እየሸነሸኑ ለመሸጥ ቆርጠው የተነሱ ለመሆናቸውም በየቀኑ እያየን ነው። ይህን አያደርጉም የሚል ካለ አንድም ሞኝ ነው፣ አለበለዚያም የወያኔ ሽርካ መሆን አለበት።
በጣም አሳዛኙ ነገር ግን ይህን በዓለም ታሪክ ታይቶም፣ ተሰምቶም የማይታወቅ ጭካኔ የተመላበት አገር ሽያጭ ሌላው ቢቀር እንደ – አንድ አገሩን፣ ክብሩንና ኩራቱን እንደሚወድ ማንኛውም የዓለም ሕዝብ ማስቆም አለመቻላችን ነው። በእኔ እምነት ይህን ማድረግ ያልቻልንበት ትልቁ ምክንያት በጥላው ሥር ሕዝብን ማሰባሰብ የሚችል አገራዊ ራዕይ ያለው/ያላቸው፤ ወይም የተሣካለት ገለሰብም ሆነ ድርጅት መውለድ ያለመቻላችን እንደሆነ ዛሬ – ዛሬ ብዙ ኢትዮጵያውያን የምንስማማበት ገሃድ እውነታ ነው ብይ አምናለሁ።
ሌላው፣ የኛ ነገር ፈርዶብን ግራ የተጋባን ሆንና ወያኔ ትናንት ሣይሆን ዛሬ በአገራችንና በሕዝቡ ላይ የፈፀመውንና እየፈፀመ ያለው አገር የመሸጥ ዘመቻ አዕምሯችንን ክፉኛ አቁስሎት “እህህ” እያልን ቁስላችንን በማስታመም ላይ እያለንና ይኼው ከፍተኛ ቁስል ሳያገግም ሌላ አዕምሯችንን ቀስፎ የሚይዝ የተንኮል መላ እየፈጠረ የኅሊና እሥረኞች ሆነን በየጓዳችን እየተብተከተክን እንድንደበቅ ማድረግ መቻሉ ነው።
ከዚህ አንፃር የወያኔ ትልቁ መሣሪያው፣ ከሕዝብ በጉልበት፣ ከአገር ሽያጭና ከፈረንጆች በድርጎ በሚያገኘው ገንዘብ፣ ለሆዳቸው ያደሩና ለማጭበርበሪያ ያህል ትንሽ ፊደል የቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ምንደኞችን ቀጥሮ በሐቀኛና ቁርጠኛ የኢትዮጵያ ልጆች መሀከል የዓላማና የተግባር አንድነት እንዳይፈጠር ሣይታክቱ የሚሠሩ ባንዳዎችን በማሠማራት ነው። ለመከፋፈሉ ዘመቻ ኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን በገንዘብና በኢንቨስትመንት ሽፋን የአገሪቱን ጥቅም አሳልፎ በመስጠት በሚገዙ ተሰሚነት ያላቸውን ምዕራባውያን ባለሥልጣናትን፣ ጋዜጠኞችን፣ የፓርላማ አባላትን፣ ልዩ – ለዩ ባለሙያዎችና ሀብታም ነጋዴዎች አማካይነትም የሚከናወን ነው።
ወያኔ በነዚህ አገር በቀልና ፀጉረ – ልውጥ አጭበርባሪዎች አማካይነት እየፈፀመ ያለውን አገር የመሸጥ ዘመቻ አሣሦቦት በፅናት የሚቃወም፣ በትግል አጀንዳው ውስጥ አካቶ ሕዝብን የሚያስተባብርና የሚመራ የፖለቲካ ድርጅት እስከአሁን ያለመኖር ጉዳይ ወያኔን ያለሥጋት የሚፈነጭበት አገርና ሕዝብ ያገኘ ዕድለኛ ድረጅት አድርጎታል።
ወያኔ የኢትዮጵያን 1600 ኪ/ሜ ርዝመትና ከ30 -50 ኪ/ሜ የጎን ስፋት ያለው ለም መሬት ለሱዳን በርካሽ ሲሸጥ ሕይዎታቸውን ድንበራቸው ላይ ለማሳለፍ ቆርጠው ከተነሱ ጥቂት ገበሬዎችና ደባውን ለሕዝባችን በተከታታይ መግለጫው ለሕዝብ ይፋ ካደረገው የኢትዮጵያ ድንበር ኮሚቴ በስተቀር ሌሎቻችን ምን መሠረታዊ ሥራ ሠራን? ስለመሬታችን መሸጥስ የተቆጨን ስንቶቻችን ነን? ለትውልድ እያካበትን ያለውንስ አበሣ የምንገነዘብ? ይቅርታ ይደረግልኝና በጣም ጥቂቶች ነን!!
ለሱዳን ተገምሶ ስለተሸጠው አገር መቃወም ቀርቶ ስለመሸጡም ገና ሳናውቅ ወያኔ ከቀረው የኢትዮጵያ ግዛት 1/3ኛውን ከነውሃው ለሕንድ፣ ለቻይና ለሣዑዲና ለሌሎች በብሣና ሥር ውል ማንም ሳያውቅ በሚስጥር መሸጡን፣ የሽያጩንም ገንዘብ በደቡብ መሥራቅ እስያ ባንኮች በመለስ ዜናዊ ስም በተከፈተ የባንክ ሂሣብ ታጭቆ እያቃሰተ ስለመሆኑ እየሰማን እኛ ኢትዮጵያውያን ምን አልን? የፖለቲካ ድርጅቶችስ? መምራት የሚገባቸው ምሑራንስ? ምንም! ጉዳዩ በሁለተኛ ደረጃ እየታየ።
ይሀን በዘዴና ባለማቋረጥ በሚደረግ ትግል ወያኔን ከወንጀል ድርጊቱ ትንሽ እንኳን ሰቅጠጥ የሚያደርግ እርምጃ መውሰድ ቀርቶ ገና አውርተን ሳንጨርስ የዛሬውም የነገውም ትውልድ ሕይዎቱን አሳልፎ እንዲሰጥ የሚጠይቅበትን ትልቅ አገራዊና ትውልዳዊ ጉዳይ ማንም ሳያውቅ፣ ማንም ሳይመክርበት ሌላ የቤት ሥራ ይዞ ከተፍ አለ።
የኢትዮጵያን ለም መሬት፣ ታይቶ የማይጠገብ ውብ ሸለቆና ሸንተረር፣ ማዕድንና ውሃ ባለቤት እንደሌለው ለድርቡሽ አሣልፎ የሰጠ ወያኔ፣ የሽሬን፣ የሽራሮን፣ የተከዜን፣ የዓዲያቦንና የባድመን፣ የዋልድባንና የበረሃሌን ፖታሽ አሳልፎ የሰጠ ወያኔ፣ የአሰብን ወደብ ለሸዓቢያ ሸጦ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ለጂቡቲ የሚሰጥ ወያኔ (ከወደቡ ገቢ ወያኔ ሼር አለው) ዛሬ ማንንም ሳያማክር ከድሆች ኢትዮጵያውያን በጉልበት እየነጠቀ፣ አገርንና ሕዝብን እያስራበ ትልቅ ግድብ እገነባለሁ ብሎ ተነሣ። “ትንሣኤ ግድብ”። አሳፋሪው ጉዳይ ወያኔ ይህንን ሲያደርግ የጠየቀም ሆነ በፅኑ የተቃወመ ያለመኖሩ ሳይሆን፣ ግማሻችን ደጋፊ፣ ግማሻችን ተቃዋሚ ሆነን ቁጭ ማለታችን ነው።
በዚህም ወያኔ በመበራታቱ የደገፈውን ብር/ዶላር አምጣ ለማለት፣ የተቃወመውን ወይንም ትንሽ ያንገራገረውን በብሔራዊ ስሜት አልባነትና በሐሞተ ፈሣሣነት እየከሰሰና አግጣጫ እያሣተ እኛ ስንጨቃጨቅ የቀረውን አገር ለመሸጥ ሰፊ ጊዜ ገዛበት።
የአገራችንን ጉዳይ በቸልታ የምንመለከት፣ ዝንጉዎች፣ የተካፋፈልንና በአንድነት መቆም የማንችል መሆናችንንም በደንብ ስለተረዳ ክፋትና ተንኮል የማያልቅበት ወያኔ ዛሬ ደግሞ አዲስ አገር የመሸጥ አጀንዳ ይዞ ከተፍ ብሏል።
ሰሞኑን ስለዓባይ ግድብ ሥራ መፋፋምና ከጅረቱ አግጣጫ መለወጥ ጋር ተያይዞ ተፈጥሮ የነበረው ግርግር፣ የግብፁ ሙርሲም “ወንዜን በደሜ እጠብቃለሁ” ድንፋታ የሁላችንንም ደም ያንተከተከ አገራዊ ጉዳይ ሆኖ እንደሰነበተ ይታወሳል። ይህ በወያኔና በግብፅ መሪዎች ተዋናይነት ይካሄድ የነበረው ቲያትር ዛሬ ከቶ ምንም እንዳልነበረ፣ ምንም እንዳልልሆነ ጭራሽ ደብዛው መጥፋቱን እየታዘብን ነው። ለምን መሠላችሁ? ወያኔ አገሪቷን ለሌላ ሽያጭ በመደራደር ላይ ስለሆነ ነው። ሌላ የቤትሥራ፣ ሌላ የምናወራው ዜና፣ ሌላ ዕዳ እያዘጋጀልን ነው ማለት ነው። ወያኔ!
ይህ ዓባይን የመገደብ ጉዳይ በድንገት የወያኔ ግንባር ቀደሞ የኢትዮጵያዊ አርበኝነት መግለጫ ሆኖ የቀረበበት ዋና ምክንያት ወያኔ እንደሚያወራውና እንደሚያስወራው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ዕድገትና ብልፅግና ራዕይ ኖሮት አስቦ ያደረገው ሣይሆን የግብፅን ሕዝብ በተለይም የአክራሪ ሙስሊሙን እንቅስቃሴ አግጣጫ ለማስለወጥ ሆን ተብሎና ግዜ ተጠብቆ በአሜሪካና በ፳ኤል (በእሥራኤል) አማካይነት ለወያኔ በተሰጠ ትዕዛዝ የሚካሄድ ፕሮጀክት እንጅ (የዓስዋን ግድብ በሶቪየቶች መገደብ ጋር የተያያዘ የቆየ ታሪካዊ ምክንያትም አለው)። የግድቡ ሥራ ሲጀመር ምዕራባውያን በተለይም አሜሪካውያን አይተው እንዳላዩ የመሰሉትም ለዚህ ነበር። ሥራው ከተጀመረና አሜሪካና ፳ኤልም ለግብፅ ማድረስ የፈለጉትን ፖለቲካዊ መልዕክት ካስተላለፉና ግብፅን የመጉዳት አቅማቸውን ካሳዩ በኋላ “ችግሩን በውይይት ፍቱ/ጨርሱ ማለታቸው ወያኔ አደብ እንዲገዛና አርፈህ የሚሰጡህን ተቀበል” ትዕዛዝ ማስተላለፋቸው ፕሮጀክቱ የእነሱ እንጅ የወያኔ ያለመሆኑን ያራጋግጣል።
ስለሆነም ተንበርካኪው ወያኔ ከአሜሪካ በተሰጠው ትዕዛዝ በመልካም ጉርብትና፣ ልማትና የኢኮኖሚ ጥቅም ስም የግድቡን ሥራ አቀዝቅዞ ኢትዮጵያን እስከወዲያኛው የሚጎዳ ሌላ የሚያሥር ስምምነት ከግብፅ ጋር ለማድረግ ላይ ታች ማለት መጀመሩን እያየን ነው። ስለሆነም ነው ዛሬ ያ – ሁሉ ሩጫና ግርግር ቀዝቅዞ፣ ዜናው ከዓለም አቀፍ ሚዲያ፣ ከኢትዮጵያና ከግብፅ ፕራዮሪቲ (ርዕሠ – ዜና) ውጪ እንዲሆን የተደረገውም። በአሁኑ ወቅት የግብፅና ዓለም – አቀፍ ቱጃሮች ከወያኔ ጋር በሚደረግ ሽርክና፣ ለህንድ፣ ለቱርክ፣ ለቻይናና ለሣዑዲ … ወዘተ. የኢትዮጵያ ለም መሬት፣ ውሃና ማዕድን እንደተሸጠ ሁሉ፣ ዛሬም የኢትዮጵያን ለም መሬት፣ ውሃ፣ ደንና ማዕድን ወደፊት ከግድቡ የሚመነጨውንም የኤሌክትሪክ ኃይል በሽርፍራፊ ሳንቲም ለመሸጥ፣ የግድቡንም መጠን ለመቀነስ እየሠሩና እየተደራደሩ ያሉት።
የግብፅ መሪዎችና ቱጃሮች በብዙ ምክንያት ውሃውን ድሮ ሲጠቀሙበት እንደነበረው ሁሉ በፍፁም ባለቤትነት ዝንተ-ዓለም ሊጠቀሙ እንደማይችሉ ይረዳሉ። ውሃም በትነት፣ በተለይም ወደፊት በዓለም ሙቀት መጨመርና በተፈጥሮ ፀጋ መመናመን፣ አብዛኛውን ውሃ በምታመነጨው በኢትዮጵያ አስተማማኝ ዝናብ ያለመኖር፣ የግብፅም እንደ አገር ሊኖራት የሚችለው አስተማማኝ ሠላምና መረጋጋት… ወዘተ. የሚያሳስባቸው ቢሊየነር ግብፃውያንና ሌሎች ሃብታቸውን ለማሸሽና ሌላ አገር ኢንቨስት ለማድረግ እየመከሩና እየሠሩ ሲሆን፣ ከመረጧቸውም አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ነች። አዲስ አበባም በአሁኑ ወቅት በግብፅ ሀብታሞች ተጨናንቃለች።
ይህ ማለት ምን ማለት ነው? ይህ ማለት ኢትዮጵያ ከግብፆች ጋር በመልካም ጉርብትና፣ በሠላምና በጋራ ልማት ስም ወያኔ የሚያደርገው ሕዝብ የማያውቀው፣ ያልመከረበትና ያልተስማማበት ልፍስፍስ ስምምነት አንዴ ከፀደቀና ዓለም – አቀፍ ዕውቅና ካገኘ ለዛሬው ሳይሆን ለነገውም፣ ለተነገ ውዲያውም፣ ቀጥሎ – ቀጥሎ ለሚመጣውም ወያኔም እኛም ትተነው የምንሄድ “የተውልድ አበሣ” ማለት እንደሆነ ግልፅ ነው። መፍትሄውም ዛሬ – ነገ ሳንል በአንድ ሆነን ይህንን የአገር ሽያጭ ማስቆምና ሕገወጥ ነጋዴውንም ማስወገድ መቻል ነው። ይህንን ማድረግ ካልቻልን የወደፊቷ ኢትዮጵያ ምን እንደሚጠብቃት ማሣሠብ ያንባቢዎቼን ዕውቀት መጠራጠር ይመስልብኛልና አላነሳውም።
ወያኔ ጊዜ እየጠበቀ በሚቀይስልን ተለዋዋጭ ተንኮል እየተመራን አንዱን እያነሳን ሌላውን እየጣልን፣ ያለፈውን እየረሣን አዲሱን እያዳነቅን እርስ -በርሣችን ከመነታረክና “የትውልድ አበሣ” ከመሆን እራሣችንን ማዳን ካልቻልን፣ የአገራችን ፖለቲካ መላው እየጠፋ፣ እዳችንም እየከበደ፣ መፍትሄውም ከሰማይ እየራቀ እንደሚሄድ ግን አያጠራጥርም።
ስለሆነም አለን የሚሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ትግላቸውን በያዝ ለቀቅ ሣይሆን በግልፅ አገራዊና ሁሉን አቀፍ እስትራቴጂካዊ ፕሮግራም፣ መሪና አሠባሳቢ መፈከር ነድፈው ሕዝቡን ማስተማር፣ ማሳወቅና (ኢንፎርም ማድረግ) መምራት ተቀዳሚ ዓላማቸውና ትልቁ ሥራቸው መሆን ይገባዋል። ፕሮግራማቸውንም መንደፍ ያለባቸው ይሄኛው እከሌን ያስደስታል፣ ያኛው እክሌን ያስቀይማል – ያስቆጣል ሣይሉ፣ ለጊዜያዊ ታክቲክና ጥቅም ሣይታለሉ ለረጅሙ ግብ ሕዝብን ማዘጋጀት የሚችል አግጣጫ ጠቋሚና አሠባሣቢ ትልም መሆን አለበት።
በመርሐ – ግብራቸው ውስጥም መካተት ካለባቸው ዋናና ቀዳሚ ጉዳዮች አንዱ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛትና ዳር ድንበር ከየት እስከየት እንደሆነ የማስቀመጥና ለመጠበቅም ያለባቸውን አደራና ሃላፊነት በግልፅ መያዝ ይገበዋል።
ነገ መምጣቱ ለማይቀር አገራዊ ጉዳይ ፖለቲካዊ ድርጅቶች በቅድሚያ ራሣቸውን ቀጥሎም ሕዝቡን አሠባሣቢ በመሆን መርሐ – ግብር አደራጀተው መጠበቁ ወሳኝና ለሚቀጥለው ሥራቸውም ጠንካራ መሠረት ነው።
ፖለቲካ ድርጅቶችና መሪ ኤሊቶች ይህን መሠረታዊ ጉዳይ ለጊዜያዊ ፖለቲካዊ ጥቅምና መሽኮርመም ወይም ፖለቲካዊ ይሉኝታ ወይም ታክቲክ ወይም በቸልታ የሚያልፉት ከሆነ እንደ ኢትዮጵያ ድንበር ኮሚቴ መግለጫ “አዲሱ ብቻ ሣይሆን የነገውም ትውልድ ከማይሸከመው ዕዳ ውስጥ መነከሩ” አይቀርምና ከአሁኑ አካሄድን ማሣመር ለነገ የሚተው ሃላፊነት አይደለም።

Latest from Blog

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። ) “ገብርዬ ነበረ

ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ?

January 3, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ዛሬ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ጥር 1ቀን 2025 ዓ/ም ነው ። አውሮፓውያኑ አዲስ ዓመትን “ሀ” ብለው ጀምረዋል ። አዲሱን ዓመት ሲጀምሩም ከልክ ባለፈ ፈንጠዚያ ነው ። ርቺቱ ፣ ምጉቡና መጠጡ

ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። )

Go toTop