በወያኔ “ያደገችዋን” ኢትዮጵያ ዓለም እንዴ ያያታል?- ዶ/ር ዘላለም ተክሉ

ነሐሴ 25 2013

በዚህ ሳምንት መጨረሻ በኢሳት የቀረበውን “ የእሁድ ወግ” ፕሮግራም ሳዳምጥ ነበር:: በዚሁ ፕሮግራም ከቀረቡት ዋና ዋና መወያያ ርዕሶች ውስጥ ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ለኢትዮጵያ ህዝብ አጎናጸፉት እየተባለ ስለሚደሰኮረው ዕድገት የተሰጡት አስተያየቶች ትኩረቴን ስበውኝ ነበር:: በተለይ ሰውዬው (ከሳቸው የተማርኩት አባባል ስለሆነ ይቅርታ) ህዝቡን ጥጋብ በጥጋብ አደረጉት፣ ብዙ ሃብታም ገበሬዎችን ፈጠሩ፣ሚሊዮኖችን ከድህነት አረንቋ አላቀቁ ስለሚባለው አቶ ሲሳይ አጌና የሰጠው ምላሽ በጥሩ ትንተና የተደገፈ መሆኑ ያስደሰተኝ ሲሆን በዚች ትንሽ መጣጥፍ የበለጠ ማጠናከሪያ በመስጠት ፕሮፓጋንዳውን ለመሞገትና ምስኪኑ ህዝባችንም እውነታውን ራሱ ፈትሾ እውነቱን እንዲያውቅ ፈለኩ::
አቶ ሲሳይ ሙግቱን (argument) ሲያስረዳ፣ በእውነት የፕሮፓጋንዳ ማሽኖቹ በተደጋጋሚ እደሚነግሩን በእርሳቸው መጀን ኢኮኖሚያችን አድጎዋል ከተባለ ከ 80 በመቶ በላይ የሆነው ገበሬው ህዝባችን ኢኮኖሚው አድጓል ማለት ነው:: የገበሬዎች ገቢ ደግሞ አደገ ከተባለ ያ ሊሆን የቻለው ያመረቱቱትን ብዙ ምርት ወደገበያ አውጥተው ሸጠው ጥሩ ገቢ ሰብስበዋል ማለት ነው:: እነሱ ብዙ የእርሻ ምርት ወደ ሽያጭ አመጡ ማለት ደግሞ በየከተሞቹ በኢንዱትሪና አገልግሎት ዘርፎች እየሰራ የሚተዳደራው ህዝባችን ከበቂ በላይ የምግብ አቅርቦት አግኝቷል ማለት ነው:: ገበሬዎች ገቢያቸው አደገ ማለት ደግሞ ከከተማው ኢንዱስትሪና አገልግሎት ዘርፎች የሚመረቱትን ምርቶች የመግዛት ፍላጎታቸውና አቅማቸው ጨምሩዋል ማለት ነው:: የነዚህ ዘርፎች መነቃቃት ደግሞ ምርታቸውን የበለጠ እንዲያድግ ያበረታታዋል የከተሜውም ገቢ ይጨምራል ማለት ነው:: የምግብና የኢንዱስትሪ ውጤቶች ምርት አቅርቦት (supply) ከፍላጎት (demand) በላይ ከሆነ ዋጋ አይጨምርም:: ወይም ደግሞ የምርት ፍላጎት እና አቅርቦት ከገቢ መጨመር ጋር በትይዩ (parallel) ሊያድጉ ከቻሉ በዋጋ ላይ ምንም ለውጥ አያመጡም ማለት ነው:: በአሁኗ ኢትዮጵያ ያለው እውነታ በተቃራኒው ስለመሆኑ ግን ይህን ሁሉ ትንታኔ ሳያስፈልገው አንድ ተራ ኢትዮጵያዊ እንኳን ሊያስራዳው የሚችለው ነው:: እየኖረበት ስላለው ድህነቱ ለመናገር የሮኬት ሳይንቲስት መሆን አያስፈልግምና::
የከተሜው ህዝብ የሚበላውን ዳቦና እንጀራ ከዛሬ 5 እና 6 ዓመት በፊት ከሚገዛበት ከ 4 እስከ 5 እጥፍ በላይ የሚሸምትበትና ከአለፈው ዓመት እንኳን በ 20 በመቶ ጭማሬ የሚሻማበት፣ የገጠሩ ህዝባችን የሚያስፈልገውን ጨው፣ስኳር፣ ዘይትና ለእርሻ የሚያስፈልጉት ማዳበሪያና ማራሻ መሳሪያዎች በተመሳሳይ ጭማሪ ዋጋ እየተንገታገተ የሚገዛበት ዋናው ምክንያት ገቢው “በአርቆ አሳቢውና ልማታዊው” መሪ አስተዋጽዖ በማደጉ ሳይሆን በተዝራከረከው፣ በጠባብ ብሄረተኛው፣ በሙናስና በተጨማለቀውና በአድሎአዊ አመራር ድክመት ምክንያት ከፍተኛ የምርት ፍላጎትና አቅርቦት ክፍተት (Supply and Demand Gap) በመፈጠሩ ነው:: ይህም ክፍተት የምርትና የሃብት እጥረትን (scarcity) ፈጥሯል:: ይህ እጥረትም ለዋጋ ንረቱ ዋነኛ አስተዋጽዎ አድርጓል:: ስለዚህ የምግብና የኢንዱስትሪ ምርት እጥረት በሰፈነበት አንጻር ዕድገት አለ ብሎ ማናፋት “እናንተ ዓይናችሁን ጨፍኑ እኔ እንደፈለገኝ ላፏልል” እንደማለት ይቆጠራል::
የዓለም ባንክና ዓለምአቀፍ የገንዘብ ድርጅት የአገራችን ኢኮኖሚ “እንዳደገ” ቢነግሩን ሊደንቀን አይገባም:: እነዚህ ድርጅቶች በሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች ወያኔ የሚሰጣቸውን መረጃ (data) ብቻ እየወሰዱ መልሰው እንደሚነግሩን መገንዘብ ይገባናል:: አንደኛው ሁለቱም የሚታዘዙት በአሜሪካ መንግስት ፍላጎት ነው:: አሜሪካ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን የነዚህን ድርጅቶች በጀት የምትች ስለሆነች በድርጅቶቹ ህልውናና በሃላፊዎቹ ቅጥርና ዕድገት ላይ ወሳኝ ሚና አላት:: አሜሪካ ደግሞ አሸባሪነትን ለመዋጋት ወያኔን እንደ ፈለገች ስለምትጠቀምበት እሱን የሚነካባትን ሁሉ ድራሹን ማጥፋት ትችላላች:: በሁለተኛ ደረጃ ወያኔም ይህን ግንኙነትና መስተጋብር ስለሚያውቅ የኢኮኖሚ ፖሊሲህ ወይም የምታቀርበው የዕድገት መረጃህ ትክክል አይደለም ብለው የሚከራከሩ የባንኮቹ ሃላፊዎች ካሉ ከጣፋጩ ሥራቸው እንዲሰናበቱ ሊያደርግ ይችላል:: ስለዚህ ባንኮቹ ጉዳዩን ቢያውቁት እንኳን የተሰጣቸውን መረጃ ይዘው ከማዳረስ ሌላ ምንም አማራጭ የላቸው::
ለነገሩ ይህ የሚነገረን የተቀቀለና የበሰለ የዕድገት መረጃ ለጂኦፖለቲካዊ ፍጆታ ከመዋል በስተቀር ዓለም አሁንም ጠንቅቆ የሚያውቀን እስካሁን በመከራ፣ በድህነት፣ በበሽታ እንደምንማቅቅ ነው:: ይህንንም ያልኩበት ከሰሞኑ ከሥራዬ ጋር በተያያዘ አንድ የ Health Economics መጽሃፍ ሳነብ አንድ አሳዛኝ መረጃ ስላየሁ ነው:: በመጽሃፉ የኢትዮጵያ ምሳሌ የቀረበው እጥረት (scarcity) የተባለውን የኢኮኖሚ ንድፈ ሃሳብ (theory) በተግባር (Application) ለማስረዳት ታስቦ ነበር:: በዚህ ንድፈሃሳብ መሰረት የሃብት እጥረት የትም ሃገር አለ፣ በደሃውም በሃብታሙ ውስጥም አለ ይልና ነገር ግን ከእጥራትም እውነተኛ እጥረት አለ (There is scarcity and there is real scarcity) ያም በኢትዮጵያና በባንግላዴሽ በከፋ ሁኔታ ይታያል ብሎ ከነዝርዝር መረጃው ያስረዳል::

ተጨማሪ ያንብቡ:  የቅዱስ አባ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ የትንሳኤ በዓል መልዕክት

ምንጭ: Folland, S., Goodman, A. G. and M. Stano (2013). The Economics of Health and Health Care. (7th edition). New Jersey: Pearson Education, Inc.
ይህ መረጃ በተጠቀሰው መጽሃፍ ላይ የቀረበው በአለም ዙሪያ ቢዝነስን ለሚማሩና ቢዝነስን ለሚሰሩ ሁሉ ያሁንዋን ኢትዮጵያ ከሌላ ሃገራት ጋር ሲነጻጸር እንዴት ማየት እንዳለባቸው ለማስረዳት ነው:: በሰንጠረዡ እንደታየው በኢንዱስትሪ የበለጸጉት አሜሪካና ጀርመኒ የነፍስ ወከፍ ገቢያቸው ከራሻና ብራዚል ከ3 እስከ 5 ጊዜ እጥፍ፣ከቻይናና አልባኒያ ከ 6 እስከ 8 ጊዜ እጥፍ፣ ከባንግላዴሽና ኢትዮጵያ ከ 83 እስከ 133 ጊዜ እጥፍ እንደሆነ፣ በዚህም ምክንያት ጤንነታቸውን ለመጠበቅ የሚያወጡት ወጪ ከፍተኛ እንደሆነ፣ስለዚህም በበሽታ የመጠቃት ዕድላቸውና የህጻናት ሞት መጠናቸው በጣም ዝቅተኛ እንደሆነ ሲያሳይ:: ኢትዮጵያን ደግሞ በዝቅተኛና እጥረት (በተሞላበት በቀን ከ 1 ዶላር በታች ገቢ) እንኳን ለጤንነታቸው በቂ ሊመድቡ የዕለት ምግብ ፍላጎታቸውን እንኳን ሊያሟሉ ባላመቻላቸው በቲቢ (Tuberculosis) በከፍተኛ ደረጃ ለመጠቃትና ለየህጻናት ሞት መዳረጋቸውንና በዚህ የተነሳ ረጅም ዕድሜ የመኖራቸው ዕድል ዝቅተኛ መሆኑን ያሳያል:: እንግዲህ ያሁንዋን ኢትዮጵያ ዓለም የሚያያት እንደዚህ ነው:: የዓለም ባንክ ሆነ የአሜሪካ መንግስት መጥቶ ይህ የጠላት ወሬ ነው ወይም የአክራሪ ተቃዋሚዎች የተሳሳተ መረጃ ነው ሊል አይችልም፣ወይም አይሞክርም::
ወያኔ የፈለገውን ያክል ያምታታ ወይም ረጂ ሃገራትን ለማባበል የፈለገውን ዓይነት የማክሮ ኢኮኖሚ (Macroeconomic) ማስተካከያ እርምጃ ይውሰድ፣ ነገር ግን ምርት እንዲጨምር ማድረግ ካልቻለና ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል የሚፈጥር መዋቅራዊ ለውጥ ካላደረገ የሚደሰኩረውን ዕድገት በእውን ሊያሳይ በጭራሽ አይችልም:: ዳሩ የሥርዓቱ ይሄ ሁሉ ፕሮፓጋዳ ከምሩ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ዕድገትን ለማጎናጸፍ ሳይሆን በፖለቲካውና በሰባዊ መብት ረገድ የሚሰራውን ግፍ ለመሸፈንና ይህን የዝርፊያና አንድ ብሄርን ብቻ በማበልጸግ አቅጣጫ የተያያዘውን ጉዞ እንዳይሰናከል የሚከላከልበት ዋነኛ መሣሪያው ስለሆነ ነው:: ከነሱ እጅ እውነተኛ ዕድገት ይመጣል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ብቻ ሳይሆን ስንፍናና ፈሪነትም ጭምር ነው:: መፍትሄው ከቅርብ ወራት ወዲህ እየተጠናከረ የመጣውን የለውጥ እንቅስቃሴ አጣናክሮ በመቀጠል አገዛዙንና ሥርዓቱ መቀየር ብቻ ነው:: ይህ ብቻ ሲሆን ነው ዓለም አሁን የሚያውቃት መከረኛዋና ችግረኛዋ ኢትዮጵያ ልትለወጥ የምትችለው:: የፕሮፓጋዳ ዕድገት ግን ዘበት ብቻ ነው!!!

ተጨማሪ ያንብቡ:  “ከመልካም ሽቶ መልካም ስም ይሻላል” - በሰሎሞን ዳኞ

አገራችን ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!!!!

4 Comments

  1. Dr Zelaleme, you put every thing in a brief and concise statement. Expecting growth under narrow tribal administration is not only being naive but also cowardice. Woyanes are talking about double digit growth which is realised in Tigray depriving others. If we allow them to abuse us and rule us it will only be a matter of 5-7 years to witness modern and Europian standard Tigeay where rural and urban areas are invariable by any dimension. Before that happens we have to confront and resist them so that they couldn’t steal our resources any longer to build their rocky and sandy landscape Tigray.

  2. This rocky and sandy Tigray you are talking about is mine and yours Ethiopia
    STOP dividing us you are another hatemonger like woyne.

  3. What a marvelous explanation with concreat evidence but on z same time I lost my hope “አሜሪካ ደግሞ አሸባሪነትን ለመዋጋት
    ወያኔን እንደ ፈለገች ስለምትጠቀምበት እሱን
    የሚነካባትን ሁሉ ድራሹን ማጥፋት ትችላላች” if we colaborate us(Ethiopian citizen) how can we face them(U.S.A)

  4. What a marvelous explanation with concreat evidence but on z same time I lost my hope “አሜሪካ ደግሞ አሸባሪነትን ለመዋጋት
    ወያኔን እንደ ፈለገች ስለምትጠቀምበት እሱን
    የሚነካባትን ሁሉ ድራሹን ማጥፋት ትችላላች” if we colaborate us(Ethiopian citizen) how can we face them(U.S.A) ????

Comments are closed.

Share