August 25, 2013
25 mins read

የግብፅና ኢትዮጵያ መጪው ዘመን ምን ሊመስል ይችል ይሆን?

ከደምስ በለጠ
ግብፅ (ምስርእንደሃገር ከምትታውቅበት ማለትም ከፈሮኦኖች ዘመን ጀምሮ ፤ የታሪኳም ሆነ የህልውናዋ መሰረት አባይ ነው። አባይ ባይኖር የግብፅ የቆየና ጥንታዊ ታሪኳ የለም ፤ የፈርኦኖች ታሪክ የለም፤ አባይ ባይኖር የክሊዮፓትራ ታሪክ የለም ። ባጠቃላይ አባይ ባይኖር ግብፅም ታሪኳም፤ ጥንታዊ ስልጣኔዋም፤ የአለማችንን እውቅ የታሪክ ምርምር መፃህፍት ገፆች ባላጣበቡ ነበር ። ታላቁ የግሪክ የታሪክ ሰው ሄሮዶቱስ ግብፅ የአባይ ስጦታ ነች ያለውም ለዚህ ነበር ። ታላቁ አሌክሳንድር ከግሪክ ተነስቶ መካከለኛው እስያ የሚባለውን ምድር ወርሮ ወረራውን በጊዜው ታላቅ አገርና አስፈሪ ጦር የነበረውን ፐርሽያን በዛሬው አጠራር ኢራንን ድል አድርጎ ወደ ህንድ ድንበር ከተጠጋ በሁዋላ በድንገት አረፈ ።
ከታላቁ አሌክሳንደር ሞት በኋላ ጀነራሎቹ የአሌክሳንደርን ግዛት ለአራት ከፍለው እጣ ተጣጥለው ፤ ግብፅ ፕቶሎሚ ለተባለው የጦር ጀነራል ደረሰችው ። የሮማውያንን ታሪክ የለወጠችው ክሊዎፓትራ ይሕ ግሪካዊው ጀነራል የመሰረተው ፕቶሎሚያዊ ስረወ– መንግስት የመጨረሻዋ ወይም 11ኛዋ ልጅና ገዢ ነበረች ፤ በሷ ዘመን ደግሞ ሌላ ሃያል አገዛዝ ከሮም ተነስቶ ግብጽን ይወርራል ። በፍቅሯ ከወደቀው ከመጀመሪያው የሮማ ቄሳራዊ ዲክታተር ጁሊየስ ቄሳርም ልጆች ትወልዳለች አንዱን ልጇንም ለሮማ ገዢነት እሷም ሆነች አባቱ ጁሊየስ ቄሳር ያዘጋጁት ነበር ። ጁሊየስ ቄሳር በሮም ከተገደለ በኋላ ፤ የሮማ ጀነራሎች የሮማን ግዛት ለሶስት ከፍለው ግብፅ ለማርክ አንቶኒ ደረሰችው ። ማርክ አንቶኒ በክሊዎፓትራ ፍቅር ወድቆላት እዚያው ከግብፅ መንቀሳቀስ ያቅተዋል ። እሷና አዲሱ ሮማዊ ወዳጇ ፤ በአውግስጦስ ቄሳር ጦር ድል ሲሆኑ ፤ ክሊዎፓትራ ብዙ ገንዘብ አስይዛ ከቄሳር የወለደችውን ልጇን የላከችው ወደ ኢትዮጵያ እንዲሸሽ ነበር ። ክሊዎፓትራ እንዳሰበችው ልጇ ኢትዮጵያ ሳይደርስ በጠላቶቹ ተይዞ በ17 አመት እድሜው ታንቆ ተገደለ።
ግብፅ በታሪክ የምትታወቅባቸው ሁለት ስሞች አሏት ። በመፅህፍ ቅዱስ “ምስሪያም” ይላታል ፤ በኛ “ምስር” ( “ስ” አይጠብቅምሌላው ደግሞ ከግሪክ የተወረሰው “ኤጊፕቶስ” የሚለው መጠሪያ ስም ራሱ ከአባይ ጋር የተያያዞ የወጣላት ስም ነው ፤ ጥቁር አፈር ማለት ነው። የግብፅ ምድር በተፈጥሮው አሸዋና የምድሩም ቀለም ሽሯማ ነው ። አባይ ወንዝ ግብፅ ደርሶ ግራና ቀኝ ሞልቶ ሲፈስና ዳርቻዎቹ ከኢትዮጵያ በመጣው ደለል ሲሞሉ መሬቱ ይጠቁራል ። በዚህ ምክንያት ነው “ኤጊፕቶስ” የሚለውን ግሪካዊ መጠሪያ ያገኘችው ግብጽ ። ይህ ጥቁር መሬቷ በየአመቱ በደለል ተሞልቶ ለዘር ስለሚዘጋጅ ፤ ለጥንታዊት ግብፅ ፤ የፈርኦኖቹ መለኮታዊነትም ምስጢር መገለጫም
ነበር። ስለዚህም አባይ ለግብፅ የህልውናዋም ፤ የአንፀባራቂ ታሪኳም ፤ ያለፈውም ሆነ መፃኢ ህልውናዋ መሰረት ነው።
የግብፅ ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ታሪኳ ፤ ከፈሮኖች የ4500 አመታት ግዛት በኋላ በግሪኮች ወደመቶ አመታት ፤ ቀጥሎም በሮማውያን ለ3መቶ አመታት ፤ ከዚያም በቢዛንቲያ ለ3መቶ አመታት ፤ በመቀጠልም ለ1100 አመታት አረቦችና ማምሉኮች በፍርርቅ ፤ ቀጥሎም የትውልደአልባኒያዊው የሞሀምድ አሊ ስርወመንግስት በቀጥታ ወደ ሰማኒያ አመታት ከገዟት በኋላ ፤ ቀሪዎቹ የመሃመድ አሊ ልጆች የእንግሊዝን ቅኝ ገዢነት ተቀብለው እስከ 1922ድረስ ቀጥሎም የእንግሊዝ ከባድ እጅ ቢኖርበትም የመሃመድ አሊ ልጆች እስከ 1952 ድረስ በንጉስነት ገዝተዋታል ። በዚህ አይነት ግብፅ ከፈሮኖች በኋላ ፤ ወደ 2500 አመታት ገደማ ግብፃዊ ባልሆኑ ባዕዳን ተገዝታለች ። ከዚህ የባእዳን ግዛት በኋላ ግብፅ የመጀመሪያውን ግብፃዊ መሪ ፤ በወታደራዊ መፈንቅለመንግስት አገኘች ።”የሪፐብሊክ ዘመን” የሚል መጠሪያ ስም በመስጠት ወታደሮች ፤ 1ኛ ጀማል አብደል ናስር ፤ 2ኛ አንዋር ሳዳትና 3ኛው ሆስኒ ሙባረክ ለ60 አመታት እስከ 2012 ድረስ በይስሙላ ምርጫ ገዝተዋታል ። ከሶስቱ ወታደራዊ መሪዎች ዘመን ከግማሽ በላይ የሚሆነውን የሆስኒ ሞባረክ አገዛዝ ነው የፈጀው። ይህን ከላይ ለማስገንዘብ የወደድኩበት ዋናው ምክንያት ለዘመናት በበእዳንና በአምባገነኖች ሲገዛ የኖረው የግብፅ ህዝብ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በዲሞክራሲያዊ ምርጫ የመጀመሪያውን መሪ መርጦ ነበር ።
በግልፅና በዲሞክራሲያዊ መንገድ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመረጡት መሃመድ ሞርሲ ለአንድ አመት ሃገሪቱን ካስተዳደሩ በኋላ በወታደራዊ መፈቅለመንግስት ከስልጣናቸው ተውግደዋል ። በምንም መለኪያ ይሁን ፤ ባለፈው አመት ለግብፅ ፈንጥቆ የነበረው ዲሞክራሲያዊ ብርሃን ዛሬ ጨልሟል ። ወታደሮች በፈለጉት ሰዓትና ጊዜ ምክንያት ፈጥረው የግብፅ ህገመንግስት ከሚያዘው ውጪ የግልበጣ እርምጃ ወስደዋል ። ይህ እርምጃ ግብፅን ቀጣይ ወደሆነ የመንግስታዊ አስተዳደር ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት አዙሪት ውስጥ ለወደፊትም የሚከታት ይሆናል ።
በአለማችን ዘመናዊ የመንስታት ግልበጣ ታሪክ እንደሚታየው መጀመሪያ አንድ ጀነራል ወይም የጦር መኮንን መንግስት ይገለብጥና የሃገሪቱን መሪ ያስራል ፤ ህገመንግስቱን ይሽራል ፤ ፓርላማውንም ይበትናል ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም ያውጃል ፤ ህዝብ የሚቃወም ከሆነ በደም ህገሪቱን ያጥለቀልቃታል ። ግብፅም ከዚህ አላመለጠችም ። ጀነራል አብዱል ፋታህ አልሲሲ በውሻ ገመድ አስሮ እንደፈለገ ከኋላ ሆኖ የሚሽከረክረው ሲቪል መሰል ጊዜያዊ መንግስት አቋቁሟል ። ይህ መንግስትም እስካሁን የተገደሉት ግብፃውያን ቁጥር ከስምንት መቶ አይበልጥም እያለ ነው ፤ መረጃዎች የሚያሳዩት ግን ከዚያ በላይ ነው ። ገለልተኛ አቋም አለው ይባል የነበረው የግብፅ
ሴኩላር ህብረተሰብና እስላማዊ ፓርቲዎች መካከል ተፈጥሮ ነበር የሚባለው የፖለቲካና የአይዲዎሎጂ ግብግብ ዛሬ መልኩን ቀይሮ ፤ የሙባረክ ዘመን ሰዎች ወደስልጣን የተመለሱበት ትያትር ሆኗል ። የሴኩላሩ ህብረተሰብ ቁንጮ ይባል የነበረውም ሞሃመድ አል ባራዳይ ፤ በህዝቡ ላይ በደረሰው ጭፍጨፋ ምክንያት የጊዜያዊው መንግስት ምክትል ፕሬዝደንትነቱን በፈቃዱ ለቅቆ ከግብፅ ውጥቶ ስዊዘርላንድ ገብቷል ። በዚህ አይነት ሴኩላሩ ህብረተሰብ በሙባረክ ሰዎችና በጀነራል አልሲሲ ተሸውዷል ። ሃገሪቱን ለ32 አመታት በፈላጭ ቆራጭነት ያስተዳደረው ሙባረክም ከወንጀሎቹ ሁሉ ነፃ ሆኖ ከእስር ተፈትቷል ። የሚገርመው ሙባረክ ሃገሪቱን ባስተዳደረባቸው 32አመታት ጥሎት የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከስልጣን እስኪወርድ ድረስ ተነስቶ አያውቅም ነበር ። አሁንም ጀነራል አልሲሲ ሞርሲን ከገለበጠ በኋላ መጀመሪያ ያደረገው ይህንኑ አዋጅ መመለስ ነበር።
የእስላማዊ ወንድማማችነት ፓርቲ በሞሃመድ ሞርሲ አማካይነት ወደስልጣን ከመጣ ጀምሮ ተከታታይ የፖለቲካ ስህተቶች ሰርቷል ። ከ70 አመታት በላይ እድሜ ያስቆጠረው እስላማዊ ወንድማማችነት ፓርቲ ፤ ብዙ የግብፅ ምሁራንን ከተለያዩ የሙያ መስኮች ያካተተ ድርጅት ቢሆንም ፤ የመንግስት አስተዳደራዊ መዘውር ላይ ባለፈው አንድ አመት ተሞክሮው ደካማነቱ ተጋልጣል ። ያም ሆኖ ግን ተቃዋሚዎቹ እንደሰለጠነው አለም የምርጫውን ጊዜ ጠብቀው በምርጫ ቢጥሉት ኖሮ ፤ ለራሳቸውም መፃኢ እድል ይበጃቸው ነበር ። አሁን ያለው የግብፅ ሁኔታ እንደሚያሳየው ግብፃውያን ተከፋፍለዋል ። የጨሰው አቧራ ሲረጋና ጭጋጉ ሲገፈፍ የግብፅን ህዝብ እንደገና ለአንድነቱ መስራቱ አይቀሬ ነው የሃገር ጉዳይ ነውና ።
መጪው የግብፅ መንግስት ወታደራዊም ሆነ ወይም በወታደሮቹ ከኋላው የሚገፋ ጋሪ ፤ በአምባገነኖች እንደተለመደው ፤ የህዝቡን ትኩረት አቅጣጫ ማስለወጫ አንድ ዘዴ መፍጠር ይኖርበታል ። ይህ ዘዴ ደግሞ የቆየ ታሪካዊ መሰረት ያለውና የአገሪቱ ቁስል መሆን ይኖርበታል ። ለማንም የፖለቲካ ታዛቢ በግልፅ እንደሚታየው የመጀመሪያውን ትኩረት የሚስበው ፤ ግብፅ ከእስራኤል ጋር ያላትን የቆየ አረባዊ ችግርን በመቆስቆስ የህዝቡን እኩረት አቅጣጫ ማስለውጥ ይሞከር ይሆናል ፤ ሆኖም ግን በወታደራዊ አቅሟም ሆነ ባሏት ጡንቸኛ ወዳጆችና ምክንያት እስራኤልን ለዚህ አላማ ለማዋል መሞከር የሚያስከፍለው ዋጋ ከፈተኛ ሊሆን ስለሚችል የማይሞከር ይሆናል ።
ሁለተኛውና ቀጣዩ የአቅጣጫ ማስለወጫ የቆየና ታሪካዊ የግብፅ ቁስል አባይና ኢትዮጵያ ይሆናሉ ። ከላይ እንደገለፅኩት አምባገነኖች የሚጠቀሙበት ዘዴ ነውና ፤ በኢትዮጵያም የአካባቢው አገሮች ህዝባዊ አመፅ ጣራ በነካበት ጊዜ ሟቹ አምባገነን የኢትዮጵያን ህዝብ ትኩረት የሳበውና ሊመጣ ይችል የነበረውን የህዝባዊ አመፅ ሰልፍ ወደአባይ ግድብ ግንባታ የድጋፍ ሰልፍ የቀየረው በዚሁ
አይነት ዘዴ ነበር ። አሁን ደግሞ በተራቸው የግብፅ አምባገነኖች ይህን ዘዴ የማይጠቀሙበት ምክንያት አይኖርም ። ለዚህም አራት ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል ።
1– አባይ ለግብፅ ህይወቷም ህልውናዋም ነው ። ህዝቧንም በቀላሉ ወደአንድ የሰልፍ መስመር ሊያመጣ የሚችል ጉዳይም ነው ። ሌላው ቀርቶ ብዙ መከራ እየተቀበሉ ያሉት የግብፅ ክርስቲያኖች ዛሬ ወታደራዊውን መፈንቅለ መንግስት ደግፈው ይገኛሉ ፤ እንዲያውም ባለፈው አርብ የኦርቶዶክሱ ፅ/ቤት ሙሉ ድጋፉን የገለፀበትን መግለጫ አውጥቷል ። እነሱም ቢሆኑ ግብፃዊ ናቸውና ወደሰልፉ መቀላቀላቸው አይቀርም ። በአባይ ጉዳይ ላይ ሊይዙት የሚችሉት አቋም ከሙስሊሙ ግብጻዊ አይለይም ። ለማሳያ ያህል ክርስቲያን የሆነውና የቀድሞው የግብፅ የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር (በኋላ ላይ የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሁፊ ሆኖ ያገለገለውቡትሩስ ቡትሩስ ጋሊ ፤ “የአካባቢያችን ቀጣዩ ጦርነት የሚደረገው በፖለትካ ሳይሆን በአባይ ምክንያት ነው ፤ ወደዚያ ደረጃ ከተደረሰ ደግሞ ጄቶቻችንን ልከን ግድቡን በአንድ ቀን እናፈነዳውና ወዲያው እንመለሳለን ፤ ጉዳዩ ይህን ያህል ቀላል ነው ፤ ሲል የተናገረው የሚረሳ አይደለም ።
2– የግብፅ ወታደራዊ ሃይል ከኢትዮጵያ ጋር ሲወዳደር ጠንካራ ነው በተለይ የአየር ሃይሉ። የግብፅ አየር ሃይል በአሁኑ ጊዜ 240 ተዋጊ አውሮፕላኖች አሉት ፤ ከነዚህ ውስጥ አብዛኛዎቹ አሜሪካን ሰር F16 የተለያዩ ሞዴሎች ሲሆኑ በቅርቡም እጅግ ዘመናዊ የሆኑትን ተዋጊዎች ከአሜሪካ አግኝቷል ። የምእራቡ አለምም የሚቆመው ለጥቅሙ ነውና ከኢትዮጵያ ይልቅ ግብፅ ላይ የበለጠ ጥቅም ስላለው ከግብፅ ጋር መቆሙ አይቀሬ ነው ።
3– የኢትዮጵያ ጎረቤቶችም ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው ግንኙነት አስተማማኝ አይደለም ። በዚሁ የፈረንጆች አመት ኤፕሪል ላይ ፤ ኤርትራ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሯን እና የኢሲያስ አፈውርቂን የፖለቲካ አማካሪ የማነ ገብረአብን ካይሮ ድረስ በመላክ ፤ የግብጽን የቅኝገዢነት ዘመን የአባይ ውሃ ስምምነት እንደምትደግፍ ፤ ከስልጣን ለተወገዱት ሞሃመድ ሞርሲ አሳውቃ ነበር ። ሰሜን ሱዳንም በተለዋዋጩ የፖለቲካ ባህሪዋና አረባዊ ተባባሪነቷ የተነሳ በተለይ ደግሞ ካላት የአባይ ጥቅም ጋር ተደማምሮ ፤ የገልፍ አረብ አገሮችም ተጨማሪ ግፊት ካደረጉባት ባልተጠበቀ ጊዜ ግልብጥ የምትል ሃገር ናት ። በተለይ ደግሞ የሳውዲው ልዑል በአረቦች የውሃ ሚኒስቲሮች ስብሰባ ላይ የሰነዘረውን አይነት ፤ ማለትም ጥቃቱ ሁሉ በመላው አረቦች ላይ እየተሰነዘረ ነው የሚለውን ሃሳብ ፤ ከተለያዩ አረብ ሃገራት ከተደረገባት አሁን የለበሰችውን ቆዳ ቀለም በቀላሉ የማትቀይርበት ምክንያት የለም ።
4– ግድቡ እየተሰራ ያለበትም ስፍራ በቀላሉ ለአደጋ የተጋለጠ ያደርገዋል ፤ በተለይ ለአየር ሃይል ድብደባ ። ከኢትዮጵያ ድንበር በ40 .ሜ ወይም በ25 ማይል ርቀት ላይ ነው ግድቡ የሚገኘው ። በቀላሉ የሰሜን ሱዳንን አየር ክልል አቋርጦ ወደግራ እጥፍ ያለ F 16 ተዋጊ አውሮፕላን በደቂቃዎች ውስጥ የአየር ድብደባውን አከናውኖ ሊሄድ ይችላል ። ኢትዮጵያስ የአየር መከላከያ አቅሟ ምን ያህል ነውአጸፋውን ለመመለስ የሚያስችል ብቃትስ አላት ወይ ከስልጣን የተወገዱት ሞሃመድ ሞርሲ እንኳን ከመገልበጣቸው 10 ሳምንታት በፊት “ የአባይን ውሃ እያንዳንዷን ጠብታ በደማችን እንከላከላለን” ሲሉ ተናግረው ነበር :: እስከ አለፈው አመት ድረስ የግብፅ የውሃና የመስኖ ሚኒስትር የነበረው ሞሃመድ ናስር ኤል አላም “ ሚሊዎኖች እንራባለን ፤ የውሃ እጥረት በየቦታው ይከሰታል ፤አደጋውም ከፍተኛ ይሆናል” ብሎ ነበር ። አሁን ደግሞ ወደ ስልጣን እየተመለሱ ያሉት የቀድሞዎቹ የሙባረክ ዘመን ሰዎች ናቸው ። የሁለቱ ተቃራኒ የፖለቲካ ቡድኖች ሰዎች አባባል የሚያመለክተን አባይ ላይ የሚያስማማ ነጥብ ያላቸው መሆኑን ነው ።
እናም ይህን በተመለከት እትዮጵያዊው ህብረተሰብ ምን እየሰራ ይገኛል ግብፃውያኑን የማስተባበሩ ተግባር በመጪው የግብፅ መንግስት በኩል ሲጠናቀቅ በኛስ በኩል ምን መደረግ አለበት ጦርነት አይቀሬ የሚሆንበት ሁኔታዎችም ሊመጡ ይችላሉ ። እንደዜጎች እያንዳንዳችን ልናስብበት አይገባም ወይ ወይስ የፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያምን የቅርብ ጊዜ የፅሁፋቸውን አባባል ልዋስና “በግብፅና በኢትዮጵያ ውዝግብ የሚያሸንፈው አሜሪካ መሆኑን የሚጠራጠር ይኖር ይሆን?” ስለዚህ አሜሪካ ለሚያሸንፈው ጦርነት እኛ ለምን እንለፋለን ብለን እጃችንን አጣጥፈን እንቀመጥ?
በእኔ በኩል ፅሁፌን አበቃሁ ።
ተጨማሪ
ትንሽ ለዲያስፖራው ትግል ማሳሰቢያ !
ቀጥሎ የምገልፀው የቅርብ ጊዜ ትዝታየን ነው ። በተለይ እንዲህ አይነት ሁኔታዎች ሲፈጠሩ በቋፍ ያለው የዲያስፖራ ትግል መሰንጥቅ ይጀምራል ። በኢትዮኤርትራ ጦርነት ወቅት የደረሰውን ማስታወሱ በቂ ማስረጃ ይሆነናል ። ዛሬ የውጪውን ትግል ክፉኛ የሚታገሉት እዚሁ ከኛው ጋር አብረውን የነበሩና በኤርትራወያኔ ጦርነት ወቅት ወደ ባንዳነት የተቀየሩ የዲያስፖራው ሰዎች ናቸው ። ምሳሌዎችን ማንሳት ይቻላል ። ዛሬ በየአቅጣጫው የዲያስፖራው ትግል ተቀናቃኝ ሚዲያዎች በዲያስፖራው ድጋፍ እግራቸውን የተከሉና በኢትዮኤርትራ ጦርነት በኩል “አገራችን
ስትደፈርማ ቁጭ ብለን አናይም” በሚል ምክንያት እጃቸውን የሰጡ ናቸው ። የሰሜን አሜሪካ
አመታዊ የእስፖርት ፈደሬሽንን ለመገንጠል ያሰቡትና በተመሳሳይ ጊዜም ለሁለተኛ ጊዜ ውድድር በተደራቢ ያዘጋጁት ወገኖች ፤ እንዴ !! አገራችን ተወራለች እንዴት ነው ነገሩ ብለው ፤ ተዉ ሲባሉ ፡ እኛ ደሞ ከወያኔ ጋር ልንሰራ አብዳችኋል እንዴ እያሉን ገብተው ፡ ቀልጠው የቀሩ ወገኖች ናቸው ። እናም በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል ሊነሱ የሚችሉ ሁኔታዎችን ተጠቅመው ለመግባት የሚንደረደሩ አይጠፉምና ጠንቀቅ ማለት ይገባል ። መግባቱን ሊገቡ ይችላሉ አትግቡም ብንላቸው አይቀሩም ፤ ሆኖም ግን እንደተላከ ውሻ ጩሀታቸውን መጥተው እንዳይለቁብን በማለት ነው ይህን ማሳሰቤ ለሁሉም መዘጋጀቱ ተገቢ ይመስለኛልና ፡፤

Latest from Blog

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። ) “ገብርዬ ነበረ

ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ?

January 3, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ዛሬ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ጥር 1ቀን 2025 ዓ/ም ነው ። አውሮፓውያኑ አዲስ ዓመትን “ሀ” ብለው ጀምረዋል ። አዲሱን ዓመት ሲጀምሩም ከልክ ባለፈ ፈንጠዚያ ነው ። ርቺቱ ፣ ምጉቡና መጠጡ

ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። )

Go toTop