Sport: የፊርማ – ከገነነ መኩሪያ (ሊብሮ)

July 1, 2014

የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ በታህሳስ 1928 ዓ.ም ተመሰረተ፡፡ የመጀመሪያውን ጨዋታ አራራት ከተባለ የአርመን ኮሚኒቲ ቡድን ጋር በየካቲት ለመጫወት ቀጠሮ ያዘ፡፡አራራት ጨዋታው ህጋዊ በመሆኑ ተሟልተው እንዲመጡና ሰዓት እንዲከበር አሳሰቡ፡፡የጊዮርጊስ ተጫዋቾች ወደ ጨዋታው ለመሄድ ዶሮ ማነቂያ በሚገኘው በአቶ ዱካስ ቤት ተሰባሰቡ፡፡

(ጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ)

ነገርግን አንድ ሰው ቀረ፡፡ ካልተሟሉ መጫወት እንደማይችሉ አውቀውታል፡፡ይሄን ቦታ የሚሸፍን ሰው እየፈለጉ ተክሌ የሚባል የትምህርት ቤት ጓደኛቸውን አገኙት ሀሳቡን ነገሩትና በጎደለ ቦታ እንዲገባላቸው ጠየቁት፡፡እሱም በሀሳቡ ተስማማ ፡፡ወፍጮ ቤት ተልኮ እየሄደ በመሆኑ ‹‹እስክጨርስ ትጠብቁኛላችሁ?›› አላቸው ፡፡እነርሱም በነገሩ ተስማሙ፡፡ቢጠብቁት ቶሎ ሊመጣ አልቻለም ፡፡ሰዓት እየደረሰባቸው ሄደ፡፡ በዚህን ጊዜ ይድነቃቸው ተሰማን በዚያ ሲያልፍ መንገድ ላይ አገኙት፡፡ ብዙዎቹ ልጆች ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ግቢ የቄስ ትምህርት ስለሚማሩ ያውቁታል፡፡እንዳገኙት ሰው ስለጎደላቸው እንዲጫወትላቸው ፈለጉና ጠየቁት፡፡‹‹ ለናንተ ስሰለፍ ምን ታደርጉልኛላችሁ?››አላቸው፡፡እነርሱም ‹‹ቆሎ እንገዛልሀለን››አሉት፡፡በነገሩ ተስማማ፡፡ በቂ ገንዘብ ባይኖራቸውም በችሎታው ስለሚያደንቁትና ስለፈለጉት ነበር ቆሎ የገዙለት፡፡ቆሎው ለሙያው የተከፈለ ነበር፡፡በኢትዮጵያ እግር ኳስ የፊርማ ክፍያ ተብሎ የሚወሰደው ይሄ እንደሆን ይታመናል፡፡ በነገራችን ላይ የቆሎው ነገር ብዙ ግዜ ክርክር አስነስቷል፡፡ሸዋንግዛው አጎናፍር ጊዮርጊስ እያለ ምንም ደሞዝ አያገኝም፡፡እሱ ብቻ ሳይሆን እነመንግስቱ ወርቁ በብላሽ(በነጻ) ነው የሚጫወቱት፡፡ሸዋንግዛው‹‹ለሙያችን ሊከፈለን ይገባል››ብሎ ከአቶ ይድነቃቸው ጋር ሲከራከር እሳቸው‹‹ የሀገሪቱ ህግ አማተሪዝም በመሆኑ ተጫዋች ለሙያው ገንዘብ አይከፈለውም ››ሲሉ እሱም‹‹ጋሼ!!አንተም እኮ ጊዮርጊስ ለመጀመሪያ ጊዜ ተጫወትልን ሲሉህ ምን ታድርጉልኛላችሁ ብለህ ቆሎ ያስገዛኸው ለሙያህ ነው ፡፡እኛም ለሙያችን ሊከፈለን ይገባል ››ብሎ ብዙ ጊዜ ይሞግታቸው ነበር፡፡፡

ከዚያ በኋላ በተለያየ ጊዜ ለሙያቸው ጥቅም እየጠየቁ ለሚፈልጓቸው ክለቦች የተጫወቱ ብዙ ናቸው፡፡ፓቼ የተባለ የሀማሴን ተጫዋች ወደ ክላባቸው እንዲገባ ሲጠይቁት‹‹ ምን ታደርጉልኛላችሁ›› ብሎ ላቀረበው ጥይቄ ሻይ ቤት ከፍተው ሰጡት፡፡ ደጋፊው ፉል የሚበላው እዛ ስለሆነ ተጠቃሚ ነበር ፡፡ጀሚል ሀሰን የተባለ የቴሌ ተጫዋች ለመፈረም ሲደራደር ቴሌ ከሀገር ውጭ ስልክ በነጻ እንዲደውል ተስማማሙ፡፡ ነገር ግን ውጭ ሀገር ዘመድ አልነበረውም ( ከውሉ በኋላ ወደ ሀገር ቤት ስለተመለሱ)፡፡ጌታቸው ወልዴ የኮተን ደጋፊዎች የቤት እቃ ስለገዙለት ሌላ ክለብ ሳይሄድ እዛው ለመቀጠል ተስማማ፡፡ዳኛቸው ደምሴ ኮተን ሊወስደው ስለፈለገ የቅዱስ ሚካኤል ሀላፊ አምስት ታኬታ ስጡኝና ለቅላችኋለው ስላለ ተስማሙ፡፡ሰለሞን የተባለ ተጫዋች አውራ ጎዳና በጥብቅ ስለፈለገው የአባቱን መኪና ጋራዥ ውስጥ በነጻ እንዲሰራላቸው ስለተስማሙ ፈረመ፡፡ተስፋልደት ወደ ሀማሴን ቡድን ለማምጣት ሙከራ ተደርጎ አልተሳካም፡፡ ለቴሌ ሊፈርም ጫፍ ደረሰ፡፡ ለጋብቻ ሽማግሌ ወደ እጮኛው ቤት ላከ፡፡ አባት ልጃቸውን ለመስጠት አንገራገሩ፡፡ጭራሽ አሻፈረኝ አሉ፡፡ አባትየው የሀማሴን ደጋፊ ስለነበሩ ለክለቡ ካልፈረመ ልጄን አልሰጥም አሉ፡፡አባትየው ብቻ ሳይሆኑ ክለቡ እዚህ ነገር ውስጥ እጁን እንዳስገባ ስለወቀ ለሀማሴን ፈርሞ የሚወዳትን ልጅ አገኘ፡፡የዚህ ፊርማ ደግሞ ለትዳር የተከፈለ በመሆኑ ዋጋው ከፍ ያለ ነው፡፡ለነገሩ ክለቡ ሰርጉን ከፍ አድርጎለታል፡፡በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ውስጥ ውጤት በማምጣት ትልቅ ድርሻ ያላቸው ዶክተር ወልደመስቀል ኮስትሬ ናቸው፡፡

ዶክተር ወልደመስቀል በአትሌቲክስ ብቻ ሳይሆን በእግር ኳስ ላቅ ያለ ነገር እንደሰሩ ታውቃላችሁ? ፡፡የኢትዮጵያ ብሄራዊ እግር ኳስ ቡድን ለሰባተኛ አፍሪካ ዋንጫ ካሳለፉት አሰልጣኞች አንዱ ናቸው፡፡የጊዮርጊስንም ቡድን በማሰልጠን ሁለት ጊዜ ሻምፒዮና አድርገዋል፡፡ለክለቡ ዋንጫ ማምጣት ብቻ ሳይሆን የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋቾች እነ ሸዋንግዛው ፍሰሃና አምስት ተጫዋቾች በአንድ ላይ ለትምህርት ወደ አሜሪካ ሲሄዱ ቡድኑ ባዶ ስለሆነ ከታችኛው በድን እነ ስዩም አባተ፤ተስፋዬ ጥላሁን ፤ዘሪሁን ፤ቱርክን በማሳደግ ቡድኑን እንደገና ጠንካራ ያደረጉ ሰው ናቸው፡፡ወልደመስቀል ተማሪ እያለ ለጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ በተጫዋችነት በሁለተኛው ቡድን ሊያስፈርሙት አነጋገሩት ነገርን የአንበሳ ቡድን በጣም ስለፈለጋቸው ምን ታደርጉልኛላችሁ ብለው ሲጠይቁ ‹‹የአመት የአውቶብስ ቲኬት እንሰጥሀለን››ሲሉት ወጣቱ ወልደመሰቀል ለአንበሳ ቡድን ፈረመ፡፡አሸናፊ ግርማ ኮተን ክለብ ስለፈለገው በአስር ኳስ ልዋጭ አስፈረሙት፡፡

… እንግዲህ ከጅማሬው ለሙያ ክፍያው በገንዘብ፤ በቁሳቁስ፤ በትዳር እያለ ዛሬ ድረስ መጥቷል፡፡ እነዚህ ሁሉ ለመፈረም በሚቀርበው ጥያቄ ስምምነት የተደረገባቸው ነበሩ፡፡እነዚህ ነገሮች ቀደም ሲል በአማተሪዝም ህግ ተጫዋቾች ገንዘብ መቀበል ስለማይችሉ በቁሳቁስና በተደበቀ ጥቅማጥቅም ይፈጸም ነበር፡፡በ1988 ዓ.ም ቀደም ሲል የነበረው ህግ ፈርሶ ተጫዋች በኮንትራት አንዲጫወቱ በመደረጉ ክለቦች የሚፈልጓቸውን ተጫዋቾች ሲያነጋግሩ ድርድሩ ወደ ጥቅም ስምምነት እየተሸጋገረ መጣ ፡፡ፋሲል አብርሃ የተባለ ተጨዋች ኒያላ ሲጠይቁት ተስማማ፡፡ ደሞዙንም ተነጋገረና ለክለቡ ለመጫወት መፈረም ነበረበት፡፡ቴሴራ ላይ ፈርም ሲሉት‹‹ለመፈረም ስንት ትሰጡኛላችሁ ››አላቸው፡፡ከብዙ ክርክር በኋላ አንድ ሺህ ብር ተስማሙ፡፡ጌታቸው ከሳ በተመሳሳይ ቡና ለመፈረም 2 ሺህ ተስማማ፡፡ፋሲል‹‹ለመፈረም ክፈሉኝ››ካለ በኋላ ወሬው ተራባ‹‹ምን አይነት ስግብግብ ነው? ለመፈረም እኮ ገንዘብ ስጡኝ አለ››በሚል ተወራ፡፡ በዚህ የተነሳ ስያሜው‹‹ የፊርማ›› ተባለ፡፡ፋሲል በሚቀጥለው አመት መድን ሲገባ‹‹ ባለፈው አመት(በ1988) ኒያላ ለመፈረም 1 ሺህ ከፍለውኝ ነበር፡፡ እናንተ ስንት ትሰጡኛላችሁ››አላቸው፡፡ መድን የፊርማ የሚባለውን ነገር ስለማያውቁ ብዙ ተከራከሩት ነገር ግን ስለፈለጉት ብቻ የጠየቀውን ለመፈጸም ተስማሙ፡፡አንዳንድ ተጫዋቾች ፋሲልን ‹‹ፈጣጣ ነው›› ሲሉ የነበሩ እነርሱ ራሳቸው እሱ በቀደደው መንገድ ገቡና ክለብ ሲጠይቃቸው ‹‹የፊርማ ››ማለት ጀመሩና እነሆ በቆሎ የተጀመረ የፊርማ ጥያቄ በ1988 ዓ.ም ወደ ገንዘብ ተቀይሮ ‹‹የፊርማ ››የሚል ስም ወጠወቶለት ከ1 ሺህ ተነስቶ 20 አመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ 1 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡ገንዘቡ ቢያድግም በእግር ኳሱ ላይ ለውጥ የለም፡፡ለውጡ ባይኖርም በክፍያ ደረጃ እኛ ሀገር ያሉ ተጫዋቾች ምስራቅ አፍሪካ ካሉ ተጨዋቾች እንኳን በጣም ያነሰ ክፍያ ነው የሚያገኙት……….

ብዙዎቹ ሰዎች ከፊርማ ጋር በተየያያዘ ተጫዋቹ ሙሉ ገንዘቡን አያገኙም የሚል እምነት አላቸው፡፡ሀሜቱ ከፍ እያለ መጥቶ የስፖርት ቤተሰቡ ይሄ ነገር እንዲጣራና እውነቱ እንዲወጣ ግፊት እያደረጉ ነው፡፡በተጨዋቹ ስም ከጀርባ ሌሎች የሚጠቀሙ በመሆኑተጨዋቹ ስም ብቻ ነው ያተረፈው የሚሉም አልጠፉም፡፡ይሄን ሀሜት ለማስቀረትና ተጨዋቹን አመቱን ሙሉ በንቃት እንዲጫወት ደሞዝ ተመራጭ እንደሆነ ይታመንበታል፡፡ለምሳሌ ተጨዋቹ በ800 ሺህ ቢስማማና ለሁለት አመት ቢፈርም ይሄን በደሞዝ መልክ እንዲያገኝ ማድረግ ይቻላል፡፡ 800 ሺህ በ24 ይከፋፈልለታል፡፡ ይሄ ማለት በወር 33 ሺህ ይደርሰዋል፡፡ደሞዙን በወር ከባንክ ሄዶ ይወስዳል፡፡ስለዚህ ሙሉ ገንዘቡ በወራት ተከፋፍሎም ቢሆን ያገኛል፡፡ይሄ አካሄድ የሚባለውን ወሬ በሙሉ ያስቀራል፡፡ እዚህ ውስጥ ፐርፎርማንሱ ታስቦ ደሞዙ ቢደላደል አዋጭ ይሆናል፡፡በየጊዜውደሞዙን ታሳቢ አድርጎ ይሰራል፡፡ትሬኒንግ ከቀረ፤ስርዐት ከጣሰ፤የመሳሰለውን ጥፋት ከፈጸመ ከደሞዙ ጋር ይነጋገራል(ሊቆረጥበት ይችላል) ይሄ በደንቡ ተፈጻሚ ሊሆን ይችላል፡፡አሁን ግን የፊርማ ይወስድና በየወሩ ሁለት ሺህ ብር ያህል ደሞዝ ይቀበላል፡፡ይሄ ደግሞ ምንም አያጓጓውም፡፡በወር 33 ሺህ መጠበቅና ሁለት ሺህ መቀበል ልዩነት አለው፡፡ በሌላ በኩል እንዲህ አይነቱ ክፍያ ደግሞ ችግር አለው፡፡ኮንትራቱ ወደ ማለቂያ ጊዜ ልጁና ክለቡ ከተቀያየሙ ለመበቀል ምክኒያት ፈልገው በቅጣት መልክ ግማሹን ደሞዝ ሊቀጡት ይችላሉ፡፡ክለቡን እንዳይለቅ በግዳጅ ቀጣይ ኮንትራት እንዲፈርም በቅጣት ደሞዙን ሊይዙበት ይችላሉ፡፡

አንዳድ ሰዎች ‹‹ይሄን ያህል ብር ለፊርማ እየወጣ ለምን ጠንካራ ፉክክር አይደረግም? በሚል ሲጠይቁ ይደመጣሉ፡፡ በርግጥ ጥያቄው ሲታይ ትክክል ሊመስል ይችላል፡፡አሰልጣኙ ስድስትና ሰባት ተጨዋች ለፊርማ አስከፍሎ ተጨዋቾችን ከሰበሰ ጠንካራፉክክር ማድረግ ይጠበቅበት ነበር፡፡ግን ጥሩ ጨዋታና ተመልካቹን የሚያረካ ፉክክር የለም፡፡ተጨዋቹ አንድ ቦታ ስለማይቆይመግባባትናመዋሀድ ሲጀምር ኮንትራቱ አጭር ስለሆነ ወደ ሌላ ክለብ ይገባል፡፡ የዛሬ አስራ አምስትና ሀያ አመት የክለቦች ፉክክር ጠንካራ የነበረው አንድም ተጫዋቾች ለረጅም ጊዜ አንድ ክለብ በመቆየታው ነበር፡፡አንድ ላይ ቢያንስ ከአምስት አመት በላይ ይቆያሉ፡፡እነሙሉጌታ ፤ገብረመድን፤አዲሴ፤ጌቱ…የመሳሰሉት ጊዮርጊስ አንድ ላይ ለብዙ አመት ተጫወቱ( በተለይ ሙሉጌታና ገብረመድን አንድ ላይ ለአስር አመት ተጫውተዋል) ቡና ደግሞ ሚሊዮን፤ዮናስ፤ሙሉጌታ፤አሸናፊ የመሳሰሉት ከስድስት እስከ አስር አመት አንድ ላይ የነበሩ ናቸው፡፡ እነዚህ ተጫዋቾች ለብዙ አመት የሚተዋወቁ በመሆናቸው አሰልጣኝ ቢቀያየር እንኳን እነርሱ ለብዙ ጊዜ የተግባቡ በመሆናቸው ክለባቸው በጥሩ አቋም ላይ ስለሚገኝ ጥሩ ፉክክር ያሳያሉ፡፡ከታች የሚያድጉትም የነርሱን ፈለግ በመከተል ከዋናዎቹ ልምድ እየወሰዱ እዚያው ቡድን ውስጥ ለረጅም ጊዜ ስለሚቆዩ የክለቦቹ ቅርጽ ሳይቀየር የጠንካራ ፉክክር ይታያል፡፡፡ይህ ብቻ ሳይሆን ደጋፊውም ተጨዋቾቹ ክለቡ ውስጥ ብዙ አመት በመቆየታቸው የኔ ናቸው ስለሚል እንደ ቤተሰብ ነው የሚያያቸው፡፡አሁን ግን በያመቱ ተጫዋች ከክለብ ወደክለብ ስለሚዘዋወር ዛሬ የኔ ነው ያለው በአመቱ የሌላ ክለብ በመሆኑ ቤተሰባዊ ነገሩን በደጋፊው በኩል አይገኝም፡፡

….. በመቆየት በሚፈጠረው መግባባት የተሻለ ቡድን ከመገንባቱ በተጨማሪ ቡድኖች በያመቱ በአዳዲስ ተጫዋች ሲገነቡ ከሚፈጠረው ትርምስምስ የጸዳ እንዲሆን አሰራራሩ መቀየር ይኖርበታል፡፡ውድድሩ የፌዴሬሽኑ በመሆኑ በዚህ ላይ ህግ ማውጣት ይኖርበታል፡፡አንደኛው ነገር ዝውውሩ ተጨዋችና ክለብ መሆኑ ቀርቶ ክለብ ለክለብ ይሁን፡፡የፊርማ የሚለው በሽያጭ ይተካና የሽያጩን ክለቡ ይቀበል፡ በዚህ ስምምነት ከተደረሰ አንድ ተጫዋች ለአምስት አመት እንዲፈርም ይደረግ (እድሜው የገፋውን አንድና ሁለት አመት ወጣቶችን ደግሞ የረጅም ጊዜ ኮንትራት ይሁን) አንድ ተጫዋች ለአምስት አመት ለመፈረም ሲስማማ ደሞዙ ቢያን እስከ ሰላሳ ሺህ ይደረግ፡፡(በፊት በፊርማየሚያገኘውን አሁን በደሞዝተከፋፍሎ ያገኘዋል፡፡ደሞዙ 35 ሺህቢሆን በአምስት አመት ከሁለትሚሊዮን ብር በላይ ያገኛል)በዚህ መንገድ ልጁ እዚህ ክለብ ተረጋግቶ ይጫወታል፡፡ አምስት አመት ፈርሞ በሁለተኛው አመት ሌላ ክለብ ቢፈልገው እንኳን ስምምነት ይደረጋል፡ለምሳሌ አንድ ጎበዝ ተጫዋች መብራት ውስጥ ቢኖር ይሄን ልጅ ባንክ ሊወስደው ቢፈልግ ልጁ የፈረመው ለአምስት አመት ከሆነ ጥያቄው ከባንክ የመጣው በሁለተኛው አመት ከሆነ ባንክ ልጁን ሳይሆን የመብራት ሀይል ክለብን ያነጋግራል፡፡መብራት ከተስማማ ልጁ ደግሞ ከባንክ ጋር ደሞዝ ስንት ትከፍሉኛላችሁ ብሎ ይደራደራል፡፡ስምምነት ላይ ከተደረሰ መብራት የዝውውሩን ሂሳብ ከባንክ ጋር ተስማምቶ ልጁን ማዛወር ይችላል፡፡ በዚህ መንገድ ቢሆን ሀሜቱን፤መተራመሱን፤ውስብስብነቱንና ሌላንውም ነገር ያስቀራል፡፡አንዳንድ ተጨዋች ለሁለት አመት ይፈርምና በመጀመሪያው አመት በተለያየ ሰበብ ሳይጫወትወይም ጥሩ እንቅስቃሴ ሳያደርግይቆይና በሁለተኛው አመት በመጨረሻው ስድስት ወር በደምብ ይጫወታል፡፡ምክኒያቱ ኮንትራቱ ስላለቀወደ ሌላ ክለብ በከፍተኛ ብር ለመዛወር በመፈለግ ነው ይላሉ ይሄ ሀሜት እየሰፋ ስለሄደ እነዚህ ነገር ለማስቀረትና አንድ ተጨዋች ለብዙ አመት በጥሩ ፕርፈፎርማንስ እንዲጨዋት ረዘም ያለ ጊዜ ቢፈርምና ዝውውሩ ክለብ ከክለብ ቢሆን የተሸለ ሊሆን ይችላል፡፡ አሁን ግን 1 ሚሊዮን የፊርማ ወስዶ ለሶስት ሺህ ብር ደሞዝ መጫወት ምን ይባላል?፡፡በወር ሰላሳ ሺህ ብር ደሞዝ መጫወት ግን ትርጉም ይኖረዋል ነቃ ያደርጋል፡፡(ፊርማው ዝሆን ደሞዝ ትንኝ) እስኪ አስተያየት ስጡበት፡፡የተሻለ የምትሉትን ጠቁሙ፡፡ዋናው ነገር የተጫዋቹን ጥቅም የጠበቀ ቢሆን ይመረጣል፡፡ምክንያቱም ሜዳ ላይ ዋናው ተዋናይ ተጫዋቹ በመሆኑ ነው፡፡

1 Comment

  1. አወ መሆን ያለበት አንተ እንዳልከው ነው በዓለም ዙሪያም የሚደረገው ይሄው ነው። አንድ ክለብ አንድን ተጫዋች ለ3 ዓመት 10 ሚሊውን ቢስማማው። አንድ ዓመት እንደተጫወተ ሊላ ክለብ ቢፈልገው መጀመሪያ በ10 ሚሊውን የገዛው ክለብ ትርፍ ካገኘ እና ተጫዋቹ ደግሞ ከሚገዛው ክለብ ጋር በክፍያ ከተስማማ ክለቡ ሽጦ ትርፍ ያገኛል። ይሄው አስራር ተጫዋቹቹን የበለጠ እንዲመኙ ያደርጋቸዋል የበለጠ ተመኘህ ማለት ደግሞ የበለጠ ገንዘብ ያስፈልግሃል ያን ገንዘብ ለማግኘት ደግሞ ተግተህ መስራት ይኖርብሃል። በዚሁ መልኩ የሃገራችን እግርኮስ ሊሻሻል ይችላል። በጣም የሚያሳዝነው ወንድሜ የሃገራችን እግር ኮዋስ ሞቶ እንደተቀበረ የሚያስረዳ ዳኞቻችን አለማቀፋዊ በሆኑ ውድድሮች ላይ በአራጋቢነት ደረጃ እንኮዋን መሰየም አለመቻላቸው ነው። እንደ ፊፋ እና እንደ ካፍ ያሉ አለማቀፋዊ እና አሁጉራዊ የስፖርት ፊደሪሽኖች ዳኞችን ለመምረጥ የመጀመሪያው መስፈርታቸው ሃገር ውስጥ የሚደረገው ፍክክር እና የአንድ ሃገር አሁግራዊ የክለቦች እንቅስቃሴ ነው ። ይህን ያየን እንደሆነ መልሱ ትልቅ ዜሮ ነው። እናመሰግናለን ወንድም

Comments are closed.

Previous Story

የነፃነት ትግል ሁሉንም መራራ መከራ ለመቀበል መፍቀድ ነው። (ሥርጉተ ሥላሴ)

Next Story

“የየመን መንግሥት የወያኔ እድሜ አጭር መሆኑ የተገነዘበ አይመስልም” – ግንቦት 7 (መግለጫ በአንዳርጋቸው ዙሪያ)

Latest from Blog

ህገ መንግስታዊ ዲዛይን ምርጫዎቻችን የትኞቹ ናቸው?

ኤፍሬም ማዴቦ (emadebo@gmail.com ) እኛ ኢትዮጵያዊያን እራሳችንን ስንገለጽ የረጂም ግዜ ሥልጣኔና ታሪክ ያለን፣በነጭ ያልተገዛን፣ከ2000 አመት በላይ ተከታታይ የመንግስት ሥርዓት ያለን፣የሦስቱ ዘመን ያስቆጠሩ አብርሃማዊ ሃይማኖቶች አገር ነን እያልን ነው። ነገር ግን ባለፉት ሃምሳ አመታት

የኢካን ዓላማ በኔዘርላንድ የሚኖረውን ትውልደ ኢትዮጵያውያንን እና ኢትዮጵያውያንን ኮምዩኒቲይ የማሰባሰብ ሳይሆን የመከፋፋልና የማዳከም ተልኮን ያነገበ ነው።

አገር ! ለየአንድ ሠው ቋንቋው፣ ልማዱ፣ ባሕሉ፣ እምነቱ፣ አስተሳሰቡ፣ ወጉና በአጠቃላይ እሱነቱና ማንነቱ የሚከበርበት ብቸኛ ሥፍራ ነው። ኢትዮጵያውያንም በስደት በሚኖሩባቸው አገራት ሁሉ እነኝህን በስደት ያጧቸውን የግልና የጋራ ማንነቶቻቸውን በአንድ ላይ ሆነው ለመዘከር

ፋኖ ምሽጉን ደረመሰው ድል ተሰማ | ” ስልጣን እለቃለሁ ” ፕረዚዳንቷ | ህዴድ ድብቅ ስብሰባ በአዲስ አበባ | “ተመስገንን በመዳፌ ስር አስገብቼዋለሁ” አብይ

-966+9-የኦህዴድ ድብቅ ስብሰባ በአዲስ አበባ “ተመስገንን በመዳፌ ስር አስገብቼዋለሁ” አብይ – ስልኩ ተጠለፈ “እኛ የምን’ዘጋጀው ለፋኖ ሳይሆን ለኤር-ትራ ነው” አበባው|”በጊዜ ቦታ አዘጋጁልኝ” አረጋ

አንድ በኢኮኖሚና በሌሎች ነገሮች ወደ ኋላ የቀረች አገር አንድን ኃያል መንግስት በመተማመንና ጥገኛ በመሆን ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ማምጣትና የተሟላ ነፃነትን መቀዳጀት ትችላለች ወይ?

ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር) ሰኔ 4፣ 2016 (ሰኔ 11፣ 2024)   በዚህ አርዕስት ላይ እንድጽፍ የገፋፋኝ ዋናው ምክንያት ሰሞኑኑ ዶ/ር ዮናስ ብሩ የቻይንንም ሆነ የቬትናምን በኢኮኖሚ ማደግ አስመልክቶ ሁለቱ አገሮች እዚህ ዐይነቱ የዕድገት ደረጃ ላይ ሊደርሱ የቻሉት ከአሜሪካ ጋር

ፋኖ አንድ ሌሊት አያሳድረንም” የአማራ ብልፅግናየኢሳያስ ግዙፍ ጦር ወደ ወልቃይት

ፋኖ አንድ ሌሊት አያሳድረንም” የአማራ ብልፅግናየኢሳያስ ግዙፍ ጦር ወደ ወልቃይት አብይና ዳንኤል ክብረት ጉድ አሰሙ-|ጀነራሉ በቁ*ጣ ተናገሩ-‘ህዝቡ ጉድ ሰራን’-|“ብልፅግናን ራ*ቁቱን አስቀርተነዋል”-|ታዳሚው ባለስልጣናቱን አፋጠጠ
Go toTop