ሉሉ ከበደ
ዋናው የኢትዮጵያ ህዝብ ችግርና መፍትሄ ያልተገኘለት ነገር፤ የህውሀት ገዢ ቡድን፤ አሁን አለማችን ካለችበት የስልጣኔና የአስተሳሰብ እድገት ደረጃ እጅግ ወደ ኋላ በቀረ እምነትና ፍልስፍና ላይ ተጣብቀው በመቅረታቸው፤ የሁሉ ነገር መፍትሄ ጉልበት ብቻ ነው፤ ጡንቻ ብቻ፤ ጡንቻን አፈርጥሞ መገኘት ብቻ ነው። ብለው በመደምደማቸው፤ በምንም መልኩ ለአንድም አይነት የህዝብ ጥያቄ መልስ ለመስጠት አለመዘጋጀታቸው እንዳለ ሆኖ፤ ይዘው ከተነሱት የጥፋት አላማ ጥቂቱን እንኳ በበጎ ነገር ቀይረው የተስፋ የለውጥ ጭላንጭል ማሳየት አለመቻላቸው የሚያስገርምም፤ የሚያስቆጣም፤ ቀጠሮ የማይሰጠው እርምጃ መውድ የሚያስፈልግበት ጊዜ መዘግየቱንም አመላካች ነው።
ሲፈጠሩ ጀምረው እንዳመኑት፤ እንደወሰኑት፤ “አማራ የሚባል ህዝብ ጠላ ነው። ሰው በላ ነው። መጥፋት አለበት። መውደም አለበት” ብለው እንደተነሱ፤ እነሆ ሀያ ሁለት አመት በሽታቸው ጋብ እያለ እያገረሸ፤ ጋብ እያለ እያገረሸ፤ በአርሲ አርባ ጉጉና በበደኖ የጀመሩት በጉራፈርዳ አድርገው ቤኔሻንጉል ጉሙዝ ላይ ደርሰው ህዝቡን በሺዎች እየዘረፉና እየገደሉ በገዛ ምድሩ ላይ ማሳደዳቸውን ቀጥለዋል። ሀያ ሁለት አመት ሊያስቆማቸው የቻለም የሞከረም ሀይል ከኢትዮጵያ ምድር ውስጥ አልተገኘም።
የሆነው ይሁንና ተስፋ የሚፈነጥቁ እንቅስቃሴዎች ገና አሁን መታየት የጀመሩ ይመስላል። ኦነግ የሻእቢያና የወያኔ የባህሪ ወንድም ሆኖ ግማሽ ምእተ አመት ለሚጠጋ ዘመን ዘልቆ ኢቮሉሽንም በሉት ሪቮሉሽን፤ አሁን የደረሰበት የአስተሳሰብ፤ የአቋም ደረጃ እድገቱ ኢትዮጵያንና ህዝቧን የሚወድ ሁሉ የሚመኘው የሚናፍቀው ተስፋ በመሆኑ ይህች ሀገር በሻእቢያና በወያኔ የተማሰው መቃብሯ ለራሳቸው መቀበሪያ ሊሆን መቅረቡን የሚያመለክት ክስተት ነው። በኦሮሞ ህዝብ፤ በአማራ ህዝብ፤ በትግራይ ህዝብ፤ በሌላውም ሁሉ አንድነት የኢትዮጵያ አንድነት ትንሳኤ መባቻው አሁን የደረሰ ይመስላል። ኦነግ ያን ሁሉ ስህተቱን አርሞ፤ “ ኢምፓየሪቷ…ኢምፓየሪቷ…ኢምታየሪቷ.. ሚኒሊክ..ሚኒሊክ..ሚኒሊክ…” የሚለውን አታካች ትርጉም የለሽ የፕሮፓጋንዳ ለቅሶ ከላንቃው አውጥቶ ጥሎ፤ ኢትዮጵያን ሀገሬ እምዬ ካለ ኢትዮጵያ ዳነች። ኦነግ ላንድነቷ፤ ለሉአላዊነቷ፤ ለድንበሯ እንነሳ ካለ ባፋጣኝ ህዝባዊ ምላሽ ያስፈልገዋል። ተነጣጥሎ ሞት እዚህ ላይ ያበቃል። የህውሀት መቃብር አሁን አፉን ከፍቷል። የህውሀት ጠላትና የጥቃት ኢላማ አማራ ብቻ አይደለም፤ ኦሮሞ፤ ሶማሌ ፤ ራሱ የትግራይ ህዝብ፤ አኝዋኩ…ሁሉም….
የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር ምስረታን አስመልክቶ የወጣው ማኒፌስቶ ተስፋ የሞላበት ለመሆኑ ዋቢ አንዲቷን አንቀጽ ላሳያችሁና፤
“ እኛ የኦሮሞ ዲሞክራቲክ ግንባር መስራቾች፤ ለሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች ፍትህ፤ ነጻነት፤ እኩልነትና የዲሞክራሲ መብት መከበር፤ መታገልን መሰረታዊ አላማው ያደረገ፤ አዲስ የኦሮሞ የፖለቲካ ንቅናቄ መመስረቱን በይፋ እናበስራለን.”……”
“ይህን አዲስ የኦሮሞ የፖለቲካ ንቅናቄ ስንመሰርት፤ መነሻ ያደረግናቸው ግንዛቤዎች አሉ። ከግንዛቤዎቹም አንዱ፤ የዛሬዋ ኢትዮጵያ የብሄር ብሄረሰቦች እስር ቤት የመሆንዋ እውነታ ነው። በዚህ መሰረት ኦሮሞን ጨምሮ በሌሎችም ብሄር ብሄረሰቦች ላይ የሚደርሰው ሰቆቃ፤ ጭቆና፤ አድሎ፤ እንግልት ውርደትና ብዝበዛ ከምን ጊዜውም በላይ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ ይገኛል። ይህን እጅግ ዘግናኝ ሁኔታ በህዝቦች የተቀናጀ ትግል እንዲቆም ማድረግ ያስፈልጋል። ይቻላልም። ለሁሉም የሀገሪቱ ህዝቦች ነጻነት እኩልነትና የዲሞክራሲ መብት መከበር መታገል የሚያስችለንን አዲስ የፖለቲካ ንቅናቄ የመሰረትነውም በንዲህ አይነቱ የፖለቲካ ንቅናቄ ስር ተደራጅተን ብንታገል ለሁሉም የሚበጅ ውጤት ማስመዝገብ እንደምንችል እርግጠኛ በመሆን ነው……….”
“…..የኦሮሞ ህዝብ የራሱን እድል በራሱ ለመወሰን የሚያደርገውን ትግል በማስፋት፤ ለሁሉም ህዝቦች ፍትህ፤ ነጻነትና የዲሞክራሲ መብቶች መከበር መታገል የሚያስቸለው እንዲሆን አድርገን የመተርጎም አዲስ አቋም ወስደናል…..”
ይህ ለኢትዮጵያ ህዝብ ታላቅ የምስራች ነው። ኦሮሞ ለኢትዮጵያ የበኩር ልጇ ነው። የቤተሰቡ አንጋፋ ልጅ ነው። አማራ ሁለተኛ ልጅ ነው። ትግሬ ሶስተኛው ነው። እያለ እያለ የተለያየ ብዛት ያላቸው ኢትዮጵያ ሰማንያ አንድ ልጆች አሏት። እዚህ ላይ የምናገረው ስለ ህዝብ ብዛታችን እንጂ ስለ ዜግነታችን አይደለም። ሁላችንም እኩል ኢትዮጵያን ነን። ያ የሞተው የወያኔ የጥፋት መሀንዲስ ያስብ እንደነበረው ወርቅ የምንለው ጨርቅ የምንለው ዘር የለንም። ኢትዮጵያ የወርቅ ህዝብ እናት ነች።
ኢትዮጵያ ማለት ግኡዝ ምድር ነች። ኢትዮጵያ ማለት እግዚአብሔር ሁሉንም አሟልቶ፤ በወንዞች በተራሮች በለምለም አፈር መስኮች በማእድናት በዱር አራዊትና ብርቅዬ አእዋፍት፤ ይህ ቀረው በማይባል ሀብት ከሽኖ ሰማኒያ አንድ ቋንቋ የሚናገር ልዩልዩ ባህል ያለው ጠንካራ ታታሪ ህዝብ ያላት፤ ግን ለመሪ ያልታደለች የተስፋ ምድር ነች። ኢትዮጵያ እንዲህ አድርጋን፤ ኢምፓየሪቷ እንዲህ አርጋን … ሲባል ለራሴ ይገርመኛልም ይነደኛልም። ይህች የተቀደሰች ምድር አይደለችም ልጆቿን የምትበድለው፤ በየጊዜው ወንጀል እየሰሩ፤ ህዝብ እየገደሉ፤ በጠመንጃ አፈሙዝ ስልጣን ላይ የሚወጡ ድኩማን ናቸው። እስቲ የወያኔን መንግስት ከውስጧ አውጡና ኢትዮጵያን ብቻ ተመልከቱ። ምን ይቀራል? ምድርና ህዝብ። ደርግንም እንደዚያው አውጡና ተመልከቱ። ምን ይቀራል? ምድርና ህዝብ። በዚህች ምድር ላይ ለሚኖረው ህዝብ እድል ስጡት። “ይሆነኛል የምትለውን መሪ በየጊዜው እየመረጥክ እራስህን አስተዳድር። የመረጥከው ሰው እርባን ከሌለውና መምራቱን ካላወቀበት እሱን አውርደህ ሌላ ተካ….”
ኦባንግ ሜቶ “ Commitment for a democratic Ethiopia” በሚለው ጽሁፉ ውስጥ አንድ ቦታ ላይ አሳምሮ ያስቀመጠው እንዲህ ይላል “…ማወቅ የሚገባን ነገር ደግሞ አንድም ብሄረሰብ ባንዱ ወይ በሌላ ወቅት ሳይጨቆን የቀረና ተጨቁኛለሁ የማይልም የለም። የሆነው ሆኖ ኢትዮጵያ የሚለው ስምና የኢትዮጵያ ባንዲራ ህዝብን ጨቁነው አያውቁም። ስልጣን ላይ የሚወጡት ጥቂት ልሂቃን የሚያዋቅሩት አንባገነናዊ ስርአት ነው የሚጨቁነን። በዚህች ምድር ላይ እኛ፤.. እነሱ የሚባል ነገር የለም። ሁላችንም አንድ ሕዝብ ነን። ችግሮቻችንን በጨዋ ውይይት መፍታት እስከቻልን ድረስ ሀገሪቱን መበታተን የሚያስፈልገን አይደለም። የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር አሁን ይህን ሊያደርግ ቃል ገብቷል…..”
እሰየሁ ነው። ኦነግ የራስን እድል በራስ መወሰን የሚለውን ጠባብ አስተሳሰብ አስፍቼ ኢትዮጵያውያን በጋራ የሁላችንንም እድል አንድ ላይ እንድንወስን እታገላለሁ ካለ፤ ሁላችንም አብረን ቶሎ መነሳት ይጠበቅብናል። ከንግዲህ ወያኔ እየከፋፈለ የሚያባላው ኢትዮጵያዊ ላይኖር ነው።
ቀደም ሲል በአንዳንድ ዜጎች ዘንድ ያ የሞተው የወያኔ አለቃ ከስልጣን የሚወገድበት ሁኔታ ቢኖር በህውሀት ቡድን ውስጥ ያስተሳሰብ ለውጥ ሊመጣና መንግስቱ የለውጥ አቅጣጫን ሊከተሉ የሚችሉ ለዘብ ያለ አቋም ያላቸው አባላት ከውስጣቸው ብቅ ሊሉ ይችላሉ የሚል ምኞት ነበረ። ይሁንና የጥፋት መሀንዲሱ እስከወዲያኛው ቢወገድም በህይወት የተረፉት የሱ ቫይረስ ተሸካሚዎች ሌጋሲውን፤ ቃሉን፤ እያሉ ያወረሳቸውን የጥፋት ተልኮ እየፈጸሙ ለዘለአለሙ ይህችን ሀገር እየዘረፉና ህዝቧን እየገደሉ ለመቀጠል መቁረ ጣቸው ይታያል።
ይህ የማይለዝብ፤ የማይታጠፍ፤ ለዚህች አገርና ህዝብ ያላቸው ጥላቻና ክፉ ምኞት እየገፋቸው የሚሰሩት አደገኛ ስራ፤ እየባሰ እንደሚሄድ አለቃቸው ከሞተ በኋላም የተረፉት የወያኔ መሪዎች በየጊዜው የሚወስዱት እርምጃ ያስረዳል።
ባለፈ ወር አንድ ኢትዮሚድያ ያወጣው ከመለስ ዜናዊ ቢሮ የሾለከ የሚስጢር ሰነድ ደግሞ ደጋግሞ ላነበበው ሰው ምን አይነት መቀመቅ ውስጥ እንዳለን ምን አይነት ሰዎች እንደሚገዙን እጅግ አጉልቶ የሚያሳይ ነበር። የሙስሊም ወንድሞቻችንን ሰላማዊ ተቃውሞ በተመለከተ ተቃውሞውን ለማምከን የሸረቡት ሴራ ሁሉ በመክሸፉ የተደናገጠው መለስ ዜናዊ ያኔ ብሄራዊ የጸጥታ ቡድኑን ሰብስቦ ምን እንዳደረጉና ለምን ተቃውሞውን ማዳፈን እንዳልተቻለ ሲገመግማቸው፤ ተሰብሳቢዎቹ ሲናገሩ ፖሊሱም ደህንነቱም የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትሩም የሰሩት ስራ ስልጣናቸውን ለመጠበቅ ሲሉ ህዝብን ወደከፋ አደጋ መግፋት ትክክል ነው ብለው የሚያምኑ ማኪቬሊያን መሆናቸውን ቁልጭ አድርጎ ያሳይ ነበር። ያ ሀላፊነት የጎደለው ተግባር መንግስት ነኝ ከሚል ሀይል የሚጠበቅ ሳይሆን ማናቸውም በአለማችን የሚገኝ የወንጀለኞች ቡድን የሚያደርገው ተግባር ነበር።
ያ ሁሉ የሸረቡት ሴራ ውጤት አለማምጣቱ የኢትዮጵያን ህዝብ ታላቅነት እስከዘለአለሙ ይመሰክራል። የሙስሊም ወንድሞቻችንን ታላቅነት እስከዘለአለሙ ይመሰክራል።
ያን ቀን ሰኔ 15/ 2004 ከምሽቱ 3 ሰአት በቤተመንግስት አስቸኳይ ስብሰባ ጠርቶ መለስ ዜናዊ መመሪያና ሀላፊነት የጣቸውን የብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤት አባአባላቱን፤
የሙስሊሙን ተቃውሞ ለማምከን ስራ ላይ ያዋሉትን ስልት እንዲያስረዱት ተራ በተራ ይጠያቃል።ዶክተር ሺፈራው የፌዴራሎች ጉዳይ ሚኒስትሩ የሚከተለውን ማብራሪያ ይሰጣል፤ በዋናነት የተከተለው ስልት፤
1. ሁከቱን በመፍጠር ላይ ያሉትን ግለሰቦችና ቡድኖች ከህዝበ ሙስሊሙ እንዲነጠሉ ማድረግ፤( ይህ እንግዲህ አንድ የሆነን ወገን የመነጣጠል የውሸት ፕሮፓጋንዳ ማሰራጨት መሆኑ ነው)
2. ተቃውሞውን በማካሄድ ላይ ባሉት ሙስሊማን ማለትም በህዝቡ መካከል ልዩነት እንዲፈጠር ማድረግ( ይህ እንግዲህ አንድ የሆነ ህዝብ የሚቃረንበትን የሚጋጭበትን ዘዴ ተጠቅሞ ማበጣበጥ ማለት ነው)
ይህንንም በተግባር ለማዋል ዶክተሩ ያደረገውን ነገር ሲናገር፤ከማስታወቂያ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ከፍተኛ የፕሮፓጋንዳ ስራ መስራቱን ሲያስረዳ፤
1.የተቃውሞውን እንቅስቃሴ ጥቂት ጸረ ሰላምና ጸረልማት ሀይሎች ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳቸውን ለማስፈጸም የፈጠሩት እንጂ ሀዝበ ሙስሊሙን የሚወክል አለመሆኑን ለማሳመን መሞከሩን፤
2. በመፍትሄ አፈላላጊው ኮሚቴ እና በህዝበ ሙስሊሙ መካከል ልዩነትና ጥርጣሬን ለመፍጠር ልዩ ልዩ ስራ መስራቱን፤
3. በኮሚቴው አባላት ላይ የስነልቦና ጫና ለመፍጠርና በፍቃዳቸው ኮሚቴውን ጥለው እንዲወጡ ለማድረግ መሞከሩን፤(ይህ እንግዲህ እስረኞቹ በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንዲሰቃዩ ቶርች እንዲደረጉ፤ ማስፈራራት፤ በህይወታቸው መዛት፤ መደብደብ…..ወዘት መሆኑ ነው)
4. በየሳምንቱ የአርብ ስግደትን ተከትሎ የሚደረገውን ተቃውሞ ለማስቀረት በተደጋጋሚ ልዩ ልዩ መግለጫዎች በመጅሊሱ አማካይነት እንዲሰጡ መደረጉን ዶክተሩ ለአለቃው አስረድቷል።
ተቃውሞው የውጭ ሀይሎች እጅ እንዳለበት ለማስመሰልም የተሰራውን ትያትር ሲናገር፤
1 ከመጅሊሱ ጋር በመተባበር ሶስት የውጭ አገር ሰዎች በአንዋር መስጊድ ውስጥ ሙስሊሙን ለአመጽ የሚያነሳሱ ጽሁፎች ሲበትኑ እንደተያዙና ከሀገር እንደተባረሩ የሚያሳይ ዜና መሰራቱንና ያም በደንብ የተሳካ እንደነበር አስረድቷል።
2.መንግስት የአክራሪነት አደጋን ለመመከት እያደረገ ያለውን ወሳኝ ትግል የህዝበ ክርስትያኑን ድጋፍ ለማግኘት በቀጥታም በተዘዋዋሪም የተሰሩ ስራዎች መኖራቸውንም አስረዳ፤
ይህ እንግዲህ እስላምና ክርስቲያኑን ለማጋጨት ጥረት እንዳደረጉና እንዳልያዘላቸው የሚያመለክተው እውነታ ነው።
እዚያ የግምገማ ስብሰባ ላይ በቀጣይ ሊያደርግ የተዘጋጀለትን አኬልዳማ ሲያስረዳ ምን ያህል የጋሸበ አእምሮ እንዳላቸው የሚያሳየው አኬልዳማን ሲያዘጋጁ ያሰቡት ነገር ነበር።
የእንቅስቃሴውን መሪዎች ከህዝቡ ለመነጠል ብሎም የሌላውን ህብረተሰብ ድጋፍ ለማግኘትና ከመንግስት ጎን ለማሰለፍ ያስችላል ተብሎ የታመነበት አንድ ዶኩመንታሪ ፊልም በፖሊስ፤ በደህንነትና በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ትብብር ስራው መጀመሩን አስረድቶ ነበር።ያም ለወያኔ የኢትዮጵያን ህዝብ ድጋፍ ያስገኛል የተባለለት ድራማ አኬልዳማ መሆኑ ነው።
አቶ ሙክታር (የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ሀላፊ) ይህ መጅሊስ ለምን ስልጣን ላይ እንዲቆይ እንደ ተፈለገ ጥያቄ ያቀርባል እዚያው ስብሰባ ላይ፤
አቶ ጌታቸውና(የመረጃና ደህንነት ሀላፊ) ዶክተር ሺፈራው በየተራ መልስ ይሰጡታል። በመጀመሪያ ደረጃ የደህንነት ሀላፊው ሲናገር፤ ከስምንት አመት በፊት ለመንግስት ታማኝ መሆናቸው በደህንነት በኩል ተጣርቶ ተመልምለው መቀመጣቸውን ያስረዳል (ውድ አንባቢያን እግዚአብሄር ያሳያችሁ መጅሊሱን የወያኔ ደህንነት መልምሎ ሲያስቀምጠው፤ ሲኖዶሱን የወያኔ ደህንነትን መልምሎ ሲያስቀምጠው፤ ምርጫ ቦርዱን የወያኔ ደህንነት መልምሎ ሲያስቀምጠው……..) ከዚያ በመቀጠል ሰዎቹ ለምን መንግስትን እንደሚያስፈልጉት ዶክተሩ ሲዘረዝር፤
1. የጠለቀ ሐይማኖታዊ እውቀት እና በቂ ትምህርት የሌላቸው በመሆኑ ከሙስሊሙ ጋር በተገናኘ መንግስትና ኢህአድግ የፈለጉትን መመሪያና ፕሮግራሞች ያለምንም ችግር ለማሰራት ስለሚችሉ፤
2. አብዛኛዎቹ የመጅሊሱ አባላት በሙስና የተዘፈቁ መሆናቸውና የሙስና ተግባራቸውን በተመለከተ መንግስት በቂ መረጃ እንዳለው የመጅሊሱ አባላት ስለሚያውቁ ከተጠያቂነት ለመዳንና የመንግስትን ከለላ ለማግኝት ፍጹም ታዛዥ ሆነው በመገኘታቸው፤
3. ሙስሊሙን በተመለከተ መንግስት አልፎ አልፎ ለሚያወጣቸው መመሪያዎች የመጅሊሱ አመራሮች ሙሉ ድጋፍ ማድረጋቸው በዚህም የሙስሊሙ ተቃውሞ ወደ መንግስት መሆኑ ቀርቶ በመጅሊሱ ላይ እንዲያርፍ ለመንግስት ከፍተኛ ሽፋን በመሆናቸው፤
4. የማስፈጸም አቅማቸው ውስን በመሆኑ ከአረቡና ከሙስሊሙ አለም ጋር በሀይማኖታዊውም ሆነ በልማት ዙሪያ ያላቸው ግንኙነትና ትብብር ደካማ መሆኑ ለመንግስት ጠቃሚ ስለሆነ፤
5. ባለፉት ሀያ አመታት የሙስሊሙ የትምህርት ተሳትፎ በከፍተኛ ሁኔታ ከመጨመሩ አንጻር ጠንካራ በውጭም በውስጥም ተቀባይነት ያለው መጅሊስ ቢቋቋም፤ ሀብት በማሰባስብ የሙስሊሙን የትምህርት ሽፋን በከፍተኛ ደረጃ ሊያሳድግ ከቻለ የሙስሊሙንም አጠቃላይ እድገት ሊያፋጥን ስለሚችል ይህም ለመንግስት ጥሩ እናዳልሆነ ተነገረ።
የህውሀት መሪዎች ተራ ቅናት። እነሱ እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብ በምንም መልኩ ተምሮ ሰልጥኖ የላቀ ደረጃ ላይ መድረስ የለበትም። እነሱ በመጠኑለት ልክ ኢኮኖሚውም፤ እውቀቱም፤ መብቱም፤ ነጻነቱም ተገድቦ እነሱ የበላይ ህዝብ የበታች ሆኖ ዝንታለም እየገዙ መኖር እንዳለባቸው ያምናሉ።
ልብ ይሏል እዚህ ላይ “ለረጅም ጊዜ ለመንግስት ስጋት ሆነው የቆዩ ጥቂት ሰዎች እንዲወገዱ ተደርጓል” እንደዋዛ እንደቀላል እቃ የተወገዱት ወንድሞቻችን አርሲ አሳሳ ላይ ሱገደሉ፤ ወያኔ አስቦ ተዘጋጅቶ በዜጎች ላይ እንዴት ወንጀል የመፈጸም ልምድ እንዳለው ሲያረጋግጥ፤ ወንጀላቸውን ህዝቡ እንዳይረዳ ያሰራጩት ውሸት ሙስሊማኑ ሁከቱን እንዳስነሱና ገጀራም ሳይቀር ይዘው እንደነበረ ነው። በአዲስ አባባም ሆነ በመላው የሀገሪቱ ሙስሊማን ተቃውሞ ላይ አንድ ግርግር የሚፈጠርበት ሁኔታ ከተከሰተ ብዙ የሚገደሉ ዜጎች ስም ዝርዝር ተይዟል ማለት ነው። ሙስሊም ወንድሞቻችን የሚያካሂዱት ፍጹም ጥበብ ብስለትና ዘመናዊ አስተሳስብ የሞላበት ተቃውሞ ይህንን በር መቼም መቼም አይከፍትላቸውም። ልክ እንደሙስሊሙ ህዝብ መጅሊስ፤ በደህንነት ተመልምለው የተሾሙበት ሲኖዶስና ጳጳስ ስር የሚተራመሰው ህዝበ ኦርቶዶክስ ዛሬ የተጋረደው አይኑ እስኪገለጥ ምን ያህል ጊዜ እንደሚወስድ ባይታወቅም፤ መቼም ይሁን መቼ የሀይማኖት ነጻነቱን ለማስከበር ሙስሊም ወንድሞቹን በአርአያነት ተከትሎ መነሳቱ ስለማይቀር፤ እስከዚያው ድረስ ሙስሊማን ወንድሞቻችን የሚያደርጉትን እያየ እለት በእለት እንዲማር መልክት ላስተላልፍ እወዳለሁ።
ኢትዮጵያ ለዘለአለም ትኑር!
ሞት ለወያኔ ስራት!