በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)
በድሮው ዘመን በኢትዮጵያ ሐብት ከጸጋ፣ ጸጋም ከመለኮት ጋር የተያያዘ ነበር፡፡ እንደ ዛሬው ሳይሆን ድሮ ሐብት ሳይሰርቁ፣ ሳይቀጥፉ፣ ሳያጭበረብሩ፣ ጉቦ ሳይሰጡ፣ የገዥ እግር ሳይስሙ እግዚአብሔር ጥረህ ግረህ ወይም ላብህን አንጠፍጥፈህ ብላ ባለው መሰረት ሌት ተቀን ማስኖ የሚገኝ ሲሳይ ነበር፡፡ በዚህ መልክ ለሲሳይ የበቃ ባለሐብትም አብለጭላጭ ልብስ የማይለብስ፣ እዩኝ እዩኝ የማይል፣ ብዙ ተመናገርና ተመቅለብለብም የተቆጠበ በመንፈስ ልእልና የተሞላ ነበር፡፡ በዚህ መልክ ላቡን አንጠፍጥፎ ሐብታም የሆነ ሰውም ባለጠጋ እየተባለ ይጠራ ነበር፡፡
በአንጣሩ በልፋት ሳይሆነ በሚታጠፍና በሚዘረጋ ምላሱ እያጭበረበረ በልቶ እሚያድር፣ በአፉ እያቆላመጠና እያደነዘዘ የፈለጋቸውን ሴቶች ሁሉ እንደ ቆቅ የሚያጠምድ ከይሲ ደግሞ አውደልዳይ አፈኛ እየተባለ ይጠራ ነበር፡፡ ተእለታት አንድ ቀን አንድ ሴት “ባል ያለው ያግባሽ ወይስ አፍ ያለው?” ተብላ ስትጠየቅ ሳታቅማማ “አፍ ያለው!” አለችና አረፈች፡፡
በዚህ ዘመን ኃጥያትን የጎረሰ ንብረት እንጅ ጠጋን የለበሰ ሐብት እንደሌለ፤ ባለጠጋ ሊባል የሚችል ባለንብረትም እንደሌለ ይታወቃል፡፡ በሥርቆት፣ በሙስና፣ በማጭበርበር፣ የሰማእትን እሬሳ እረግጦ የገዳይ ገዥዎችን በደም የተነከረ እግር እየሳመ በንብረት የናጠጠውን ባርባን ሁሉ አለአዋቂ ባለሐብት እያለ ይጠረዋል፡፡ እንደ ምሁርነት፣ ሽምግልና፣ ዳኝነት፣ ምስክርነት፣ ሽክና፣ ክህነት፣ ጵጵስና ፕትርክና ሁሉ የሐብትም ትርጉም ቅጥ አጥቷል፡፡ ዛሬ ባለንብረቱ ላቡን አንጠፍጣፊው ሳይሆን ነፍሰ-ገዳዩ፣ አጪበርባሪው፣ ሌባው፣ ወሮበላውና አፈኛው መሆኑ እየታወቀ አምታቶና ሰርቆ ዲታ የሆነው ሁሉ ያለምንም ሀፍረት ባለሐብት እየተባለ ይጠራል፡፡
በተመሳሳይ መንገድ ከጥንት ጀምሮ ተቀባይነትና ተደማጭነት ያለውም የእውቀት ወይም የመንፈስ ልእልና ጠጋ የተጎናጸፈው ሳይሆን ሲዋሽ አፉን ቅንጣት የማይዘው የእውቀትና የመንፈስ ልእልና ምንዱብ ድሀ የሆነው አፈኛ ሆኗል፡፡ የውሸት ስብከት ሲሰብኩ ምላሳቸውን የማይዛቸው አፈኛ ፈሪሳዊ ካድሬዎችን ክስ ሕዝብ ተቀብሎ “ስቀለው ስቀለው ብሎ” ክርስቶስን እንዳሰቀለው ይታወቃል*፡፡ “አፍ ያለው ያግባኝ” እንዳለችው ያልበሰለች ሴት ሁሉ መንጋው ሕዝብ መለኮት የሰው ስጋ ለብሶ ወደ ምድር መጥቶ በግብር ያስተማረውን ክርስቶስን ትምህርት ትቶ አፈኛ ፊሪሳውያን የለፈለፉትን የውሽት ክስ ተቀብሎ ጲላጦስን የስቅላት ፍርድ እንዲፈርድበት በጩኸት እንደጠየቀው ቅዱሱ መጽሐፍ ያስተምራል፡፡
የፍልስፍና ታሪክ እንደሚያሰምረው ሶቅራጥስን መርዝ ጠጥቶ እንዲሞት የወሰነው በፈራጅነት (ጁሪ) የተቀመጠ 501 ሕዝብ ነበር**፡፡ በሶቅራጥስ ዘመን ሶፊስት ይባሉ የነበሩ በስብከት ገንዘብ እያካበቱ የሚኖሩ አፈኞች በሙስና ብልሽሽት ታሉ ባለስልጣኖች ጋር ተሻርከው ሶቅራጥስ የግሪክን አምላካት አይቀበልም፣ ወጣቱን አበላሽቷል ወዘተፈ በሚሉ የውሸት ወንጀሎች ተችሎት እንዳቀረቡት ታሪክ ያስተምራል፡፡ ፕሮፌር አስራትን ጨምሮ ስንቱን ባለመንፈስ ልእልና በሐስት ከሶና በቅጥፈት አስመስክሮ እንደፈጀው ይህ አድግ ቁጥር አንድና ቁጥር ሁለት ፈሪሳዊ ሶፊስቶች ምስክር በገንዘብ ገዝተው በሶቅራጥስ አስመሰከሩበት፡፡ ለራሱ ጠበቃ ሆኖ የቆመው የፍልስፍና አባት የሚባለው ሶቅራጥስ በታወቀበት የሐሳብ ሰንሰለት (ሎጅክ)ና መጠይቃዊ ትምህርቱ መልስ ሊሰጥና ሊያፋጥጥ ሲጀምር ድምጡ እንዳይሰማ አፈኛ ሶፊስቶችና እነሱ ያሉትን ብቻ የሚሰሙ መንጎች አውቀው እየተንጫጩ ድምጡ እንዳይሰማ አደረጉት፡፡ ሶቅራጥስ ከጫጫታው በላይ ድምጡን ከፍ ለማድረግ ሲሞክር እነሱ ድምጣቸውን ከእርሱ እጥፍ ድርብ እየጨመሩ ለክሱ የሰጠው መልስ እንዳይሰማ አደረጉት፡፡ በመጨረሻም የመከላከያ ክርክሩ ችሎት ሳይሰማ አፈኞች አስገደሉት*፡፡
ኢትዮጵያን እንደ ቅርጫ ሥጋ ለመቆራረጥ በምእራባውያን ፈቃድ ተወንበር ቁጢጥ ላለው የትግሬ ነፃ አውጪ ባርያ ሆነው ያገለገሉ ሰላዮችና ካድሬዎች “ኢትዮጵያ ሱስ ናት፤ ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስሞት ኢትዮጵያዊ” እያሉ የበግ ለምድ ለብሰው ከስድስት ዓመታት በፊት ሲመጡ ፈሪሳዊ ምሁራን “እነ ዳግማዊ ሙሴና ኢያሱ መጡ፤ ከእነሱ ጋርም ተደምረናል” ብለው ያለመታከት ሰበኩ፡፡ በዚህ የፈሪሳውያን ስብከትም የዋሁን የከተማና የገጠር ሕዝብ አሳስተው በነቂስ ወጥቶ እየደለቀ እነዚህን የይሁዳ ልጆች ከክርስቶስ በላይ እንዲቀበል አደረጉ፡፡ እነዚህ ፈሪሳዊ ምሁራንም ተይሁዳ ልጆች ጋር መደመርን የተጠየፉትንና ሕዝብን ያስጠነቀቁትን ሰዎች “ወያኔ፣ ጸረ- ኢትዮጵያ፣ ፅንፈኛ፣ ደርግ” ወዘተፈ የሚል የአሉቧልታ ስም እየሰጡና በለመደ አፋቸው እንደ ሶቅራጥስ ዘመን አፈኞች (ሶፊስቶች) እየጮኾሁ መልእክታቸው ለሕዝብ እንዳይደርስ አደረጉ፡፡
ብዙዎቹ የሕዝብ መገናኛ ራዲዮ፣ ቴሌቪዥን፣ ዩ ቱዩብና ጋዜጣ አለን የሚሉት ጋዜጠኛ ተብዮዎችም ይኸንን የፈሪሳዊ ምሁራን የዳግማዊ ሙሴ መምጣትና የመደመር ስብከት ደጋግመው እንደ ወናፍ አራገቡ፡፡ አማራ በላንባ ዲና እየተፈለገ ተሚያመልክበት ቤተክርስትያንና መስጊድ ሳይቀር ሲታረድና ሲቃጠል “በሽግግር ወቅት እንደዚህ ዓይነት ችግር የሚጠበቅ ነው” እያሉ በታረዱትና በተቃጠሉት ነፍሰ-ጡሮች፣ ሕጻናት ባልቴቶችና አዛውንት ተሳለቁ፡፡ የዘር ማጥራትና የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጥሟል እሚሉትን ዜጎች አሁንም እነዚሁ አፈኛ ፈሪሳዊ ምሁራን በእየ ሕዝብ መገናኛ መድረኮት እየቀረቡ “ዜጎች ሞተዋል የዘር ማጥራት ወይም ማጥፋት ወንጀል ግን አልተፈፀመም” እያሉ አጣጣሉ፡፡ በዚህ በሕዝብ ነፍስ የመቀለድ ስብከታቸውም አንዳንዶቹ እንደ ሶቅራጥስ ዘመን ሶፊስቶች ስልጣን፣ ገንዘብና ሌላም ሌላም መቅቡጥ ተቀበሉ፡፡ ሕዝቡም አፍ ያለው ያግባኝ ብላ እጇን ለለፍላፊ እንደሰጠችው ብኩን ሴት በአፈኛ ፊሪሳውያን ተወናብዶ የጭራቆችን ሴራ ተገንዝቦና ተዘጋጅቶ ራሱን ለመከላክል ብዙ ጊዜ እንዲፈጅበት፤ በሌላ በኩል ደሞ አጥፊዎቹ በቂ የመዘጋጃ ጊዜ እንዲኖራቸው አደረጉ፡፡
ዘመን ቁጥሩን ጨመረ እንጅ የሰውን ከንቱ ባህሪ ከስፍራው ትንሽም ንቅንቅ አላደረገው፡፡ እንደ ሶቅራጥስ ዘመን ዛሬም ሕዝብ የሚሰማው በእውቀት ወይም በመንፈስ ልእልና የበለጠገውን ሳይሆን ሶፊስቱ ወይም አፉን መተዳደሪያ ያደረገውን አውደልዳይ አፈኛ መሆኑን በየቀኑ የምንታዘበው ነው፡፡ አፉን መተዳደሪያ ያደረገ ወይም በአፉ ስልጣን ወይም መታወቅን የሚሻ አውደልዳይ አፈኛ ደሞ በራሱ ትችት ሲደርስበት ትችቱ በእርሱ ሳይሆን በወጣበት ማህብረሰብ ወይም ጎጥ ያነጣጠረ እያስመሰለ ክርስቶስን እንዳስገደሉት ፈሪሳውያን ቅጥፈት እየሰበከ ማህበረሰብ ሲያሳስትና ሲያጋጭ የሚውል ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነቱ በራሱ ላይ የደረበትን ትችት ወደ ዘውግ፣ መንደር ወይም ጎጥ የሚያላክክ ለፍላፊ አንዴ ተክርስቶስ ደጃፍ ሌላ ጊዜ ከሳጥናኤል ወይም ከይሁዳ ጓዳ የሚገኝ መርህ የሌለው ፈናፍንት ነው፡፡
እንደ ጥንቱ ሁሉ በዛሬውም ዘመን እንደነ ቅዱስ ፤ጳውሎስና ቅዱስ ጴጥሮስ ተዘቅዝቆ አንገቱን የሚቀላው በሐሰት ከሳሽ አፈኛ ፈሪሳዊ ሳይሆን እውነትን የተከተለ ጻድቅ ነው፡፡ ባለጸጋ ጠፍቷል እንጅ ዛሬም ከንቱ ሴት “ባለጠጋ ያግባሽ ወይስ አፍ ያለው?” ብላ ብትጠየቅ በፍጥነት “አፍ ያለው!” ብላ መመለሷ እማይቀር ነው፡፡ ምናልባትም የጠቢቡ ሰለሞን “ከፀሐይ በታች አዲስ ነገር የለም” አባባል ተመሬት ጠብ እማይል ብሂል ነው፡፡ አመስግናለሁ፡፡
*የዮሐንስ ወንጌል፡-፲፱፡፮ ሊቃነ ካህናትና ሎሌዎቻቸውም ባዩት ጊዜ “ስቅለው ስቀለው” እያሉ ጮሁ
**How to Think Like Socrates, Chapter I The Trial by Donald J Robertson, 2024
ኅዳር ሁለት ሺ አስራ ሰባት ዓ.ም.