October 28, 2024
31 mins read

በኢትዮጵያ፤ የኦሮሞ ገዢው ቡድን የሥልጣን ህልውና፤

አንዱ ዓለም ተፈራ
ጥቅምት  ቀን፣    ፯ ዓ. ም. (10/14/2024)

 

የህልውና ትግላችን በድል የሚጠናቀቀው፤ ባስቀመጥነው ግልጥ የሆነ የህልውና ራዕይ፣ በፋኖ ተቋማችን እየተመራን፣ አሠራርና ደንብ ገዝቶንና ባለ በሌለ አቅማችን በአንድነት በምናደርገው ጥረት ነው። 

መንግሥት፤ ባንድ አገር ያለ ሕዝብን የሚያስተዳድር አካል ነው። ይህ አካል እንደሌሎች የኅብረተሰብ ተቋማት ሁሉ፤ አሠራሩ ከአንድ አጽናፍ እስከሌላው አጽናፍ ድረስ የተዘረጋ ነው። ዴሞክራሲያዊ አሠራርን የሚከተሉ፣ ዴሞከራሲያዊ አሠራርን እንከተላለን የሚሉ፣ ዴሞክራሲያዊ አሠራር አንፈልግም የሚሉ፣ እና ዴሞክራሲያዊ አሠራር መጥፎ ነው! ብለው የዘመቱበት አሉ። መንግሥት የተባለ ሁሉ ትክክል ነው! ወይንም መጥፎ ነው! ማለት ስህተት ነው። እያንዳንዱ በመንግሥት ሥልጣን ላይ የተቀመጠ ገዢ ቡድን፤ የራሱ የሆነ ምንነት፣ ባህሪ፣ ዕድገት፣ የአስተዳደር ይዘት፣ እና የፖለቲካ ፍልስፍና አለው። ያ መንግሥት የሚመዘንበት በዚያ እምነቱና፤ በተለይም በተግባሩ ነው። በኢትዮጵያ ያለው ገዢ ቡድን፤ የራሱ የሆነ ምንነት፤ አመጣጥና መንግሥታዊ አሠራር አለው። ያንን አጥርቶ መረዳት፤ ማንነቱን ማወቅና ተግባሩን መገንዘብ፤ ተከትሎ ለሚመጣው ሁኔታ ያዘጋጀናል። አሁን በቀጥታ በኢትዮጵያ ስላለው ስለዚህ ገዢ ቡድን የሥልጣን ህልውና እተነትናልሁ።

በኢትዮጵያ ያለው የገዢ ቡድን፤ አሁን አገራችንን ከመቼውም ጊዜ በከፋ ሁኔታ ላይ አስቀምጧታል። በትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር አገዛዝ ያለፈ ሁሉ፤ ይሄን መስማት ሊያስደነግጠው ይችላል። ሀቁ ግን፤ አሁን ያለንበት ሁኔታ፤ በዚህ ሚዛን ላይ የተቀመጠ ነው። አገራችን የደም ምድር ሆናለች። ገዢዎቹ አገር ሳይሆን መንደር ማስተዳደር የማይችሉ ሆነው ተገኝተዋል። ወገናችን፤ ነገ ምን ይሆናል! ሳይሆን፤ ዛሬን እንዴት አድራለሁ! በሚል እሳቤ ውስጥ ነው። በተለይ ዐማሮች የህልውናችን ጉዳይ ሰቅዞ ይዞን፤ ውሎ ለማደር የምናደርገው ጥረት፤ ከሁሉም ጉዳይ በላይ ከብዶ ተጭኖናል። እናም ይሄን የህልውና ትግል፤ ባለ በሌለ አቅማችን እየተጋፈጥን ነው። በሚገርም ሁኔታና ባልታለመ ግስጋሴ፣ ባጭር ጊዜ ውስጥ፣ የትግሉ ሚዛኑ፣ የኛ ድል እንዲሳካ፣ አመቺ መንገድ ላይ አስቀምጦታል። የዚህ ማሳያው፤ ባለፈው አንድ ዓመት ብቻ፤ በኔ እምነት፤ የህልውና ትግላችን በጣም በትልቅ እመርታ ማደጉ ነው። ከዚህ እድገቱ ጎን ለጎን ደግሞ፤ በጣም ትልቅ ፈተና ከፊታችን ተደቅኗል። ተስፋ የሚያስቆርጥ ሳይሆን ተስፋ የሚሠጥ፣ አለቀ ደቀቀ! ብሎ ለመጨፈር ከመዘጋጀት ይልቅ፤ ወገብን ጠንከር፤ ቀበቶን ጠበቅ አድርጎ! ለትግሉ መጠናከር የበለጠ ቆርጠን የምንነሳበት ሀቅ፤ የሚገዛን ነው።

ማንኛውም የፖለቲካ ትግል፤ በተለይም የህልውና ትግል፤ የየራሱ የሆነ ሀቅ አለው። እንዲህ ነው! ወይንም እንዲያ ነው! ብሎ ቀድሞ በተቀመጠ ፈርጅ ውስጥ የሚከተት፤ አንድ ወጥ ገዢ ቀመር የለም። የኛ የህልውና ትግል፤ በጣም በፈጠነ ደረጃ ቢገሰግስም፤ ከላይ እንደጠቀስኩት፤ በመንገዱ እንቅፋት ሊገጥመውና ግስጋሴውን ሊያስተጓጉል የሚችሉ ጉዳዮች ይኖራሉ። አጠቃላይ ጉዞው ግን፤ ወደ ድል የሚወስድ፤ ቀጥ ያለ መስመር ነው። የመንግሥትን ሥልጣን ከጨበጠ ገዢ ቡድን ጋር የሚደረግ ትግል፤ በርግጥ እጅግ ውስብስብና አድካሚ ነው። በተለይም አገራችን ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ካለፈችበት ተጨባጭ እውነታና፤ በአገራችን በተለያዩ ቦታዎች ባሉት ነዋሪዎች መካከል ያለው የየራሳቸው ግንዛቤ፤ የዐማሮች የህልውና ትግላችን፤ በብዙ መንገድ የተሰለፉ ፈተናዎቻችን ጠንካሮች ናቸው።

እስኪ የዐማሮችን ህልውና ጥያቄ ውስጥ ያስገባው ገዢ ቡድን፤ ምን ዓይነት መንግሥት እንደሆነ፣ ወደ ሥልጣን እንዲወጣ ያስቻለውን ሀቅና የህልውናውን ጉዳይ እንመርምር። ይሄ የአክራሪ ኦሮሞ ገዢ ቡድን፤ መሠረታዊ የሆኑ ስድስት ክፍሎች ያሉት አጓጓዝና ተግባር አሳይቷል። እንሂድባቸው። ለምን እንደፈተሽኩትና ድምዳሜዬን፤ ከታሪክ አጣቅሼ ከታች አቀርባለሁ።

 

ክፍል ይህን ገዢ ቡድን ወደ ሥልጣን እንዲወጣ የፈቀደለት የወቅቱ የፖለቲካ ሁኔታ፤

 

አሁን በሥልጣን ላይ ያለው የአብይ አሕመድና የአክራሪዎቹ ኦሮሞ ገዢ ቡድን፤ ወደ ሥልጣን ሊመጣበት ያስቻለውን የወቅቱ የፖለቲካ ሁኔታ ስንመረምር፣ እያሽቆለቆለ የሄደው የገዥው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር አስተዳደርና የኢትዮጵያ ሕዝብ ስርዓቱ እንገፍግፎት፤ መንግሥትና ሕዝብ የተፋጠጠበት ወቅት መሆኑን እንረዳለን።

  • በሙስና የተጨማለቀው፣ በአድልዖ የታጨቀው፣ በኢትዮጵያዊያን ኪሳራ የትግሬዎችን ብልፅግና አመጣለሁ ብሎ የተነሳው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር፤ አናሳነቱ እየተጋለጠበት፣ አድልዖው እየከረፋበት ሄዶ፤ ሕዝቡን እንደልቡ መንዳት ያልቻለበት ሁኔታ ተፈጠረ።
  • ራሱ ያስቀመጠውን ሕገ-መንግሥት፣ የሰየማቸውን ሹሞችና ያዋቀረውን የአሰተዳደር ክልል፤ አላከብር አለ። ሕዝቡ በቃኝ ብሎ አመጸ። ከሞላ ጎደል፤ ትርምስ አገሪቱን ወጥሮ ያዛት።

rcist abiy

ክፍል ክፍተቱን ተጠቅሞ፤ አንድ ወጥ ያልሆነ አንድ ቡድን፤ ራሱን ብቅ አደረገ።

ገዢው መግዛት፣ ተገዢው መገዛት ባቃታቸው ጊዜ፤ ክፍተት ይፈጠራል። ያ ክፍተት ለተደራጀ ክፍል አመቺ ነው። የተደራጀና የተዘጋጀ አካል በሌለበት ሁኔታ፤ ጥቂትም ቢሆኑ በጊዜያዊ ጥቅማቸው የተቧደኑ ግለሰቦች፤ ወደ  መድረክ መጥተው ቦታውን ይሞሉታል። የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር፣ መግዛት አቅቶት እና የኢትዮጵያ ሕዝብ አሻፈረኝ ባለበት ወቅት፤ በቦታው ሥልጣኑን ለመውሰድ የተደራጀ አካል ባለመኖሩ፤ የዚሁ የገዢው የኢሕአዴን አካል የሆኑት አንገታቸውን አቀኑ። የአመጹን ከፍተኛ ድርሻ ለወሰዱት የዐማራና የኦሮሞ ወጣቶች፤ “ግንባር ቀደም አለኝታችሁ እኛ ነን!” በማለት፤ ደመቀ መኮነን፤ ገዱ አንዳርጋቸው፣ ለማ መገርሳና አብይ አሕመድ መድረኩን ተቆጣጠሩት።

  • “ኢትዮጵያ! ኢትዮጵያ! እያሉ በመጮህ” አረንጓዴ ብጫ ቀይ ቀለሙን ሰንደቅ ዓለማ አውለብልበው፣ የሕዝቡን ልብ ሰረቁና፤ ይሄ ቡድን፤ ራሱን ብቅ አደረገ።
  • የለውጡ መሪ ሆነና ቀደመ፤ ለሕዝቡ የሽግግር መንግሥት ጥያቄ፤ “እኔ አሻጋሪያችሁ ነኝ!” ብሎ ጎደራ።
  • አማራጭ ያልነበረው ሕዝብ፣ ይሄን ቡድን ተቀብሎ፣ ሕዝቡ ደም የገበረበትን የለውጥ ሂደት፤ ባለቤት ሆኖ አረፈው።
  • ከዚያ ምንም ተቃውሞ ሳይገጥመው፤ ይሄ ቡድን የመንግሥቱን መዋቅር ሙሉ በሙሉ ተቆጣጠረ።
  • የነበራቸው ፍራቻ፤ የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር ወታደራዊ መዋቅሩን ተቆጣጥሮ እንዳያጠቃቸው ብቻ ነበር።

በዚህ ላይ፤ “ኦሮ-ማራ!” በሚል የዐማራን ወጣቶችና የኦሮሞ ወጣቶችን አደናቆረ። ማስታወስ ያለብን፤ ለለውጡ ከፍተኛ ተጋድሎ ያደረግው የዐማራ ወጣት፤ ጎንደር ላይ፤ “የበቀለ ገርባ ደም የኛ ደም ነው!” “መሪያችን ነው!” በማለት በቅንነት ሰልፍ መውጣቱን ነው። በዚያ ወቅት፤ የዐማራ ወጣቶች፤ ኢትዮጵያ ከሌሎች ጋር አብረን የምንኖርባት አገራችን ናት! ብለው ነበር የተነሱት።

በመጀመሪያ፤ “ኦሮ-ማራ!” ቅጡ የጠፋበት ትርጉም የለሽ መፈክር ነው። በተቀባዩ ሕዝብ ፍላጎት፤ ከፋፋዩ፣ ፀረ-ዐማሮች እና ፀረ-ኢትዮጵያ የሆነው የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር ከሥልጣን ስለተባረረ፤ ቢያንስ አብላጫው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሆነው ዐማራና ተከታዩ ኦሮሞ አንድነት ከተባበሩ፤ ኢትዮጵያ የተከፋፈለች አገር አትሆንም! ከሚል እሳቤ ተነስተው ነበር። ባስሊዎቹ የዘርን ፖለቲካ አራማጆች ባለተረኞች ዘንድ ደግሞ፤ ዐማሮች ዋናው የለውጡ አንቀሳቃሾች ስለሆኑ፤ የኛን ኦሮሞዎች ብቻ ይዘን መሄድ ስለማንችል፤ ይሄን መፈከር ጊዜያዊ መንገድ መሪ እናድርገው! የዘር ክፍፍል አስተዳደሩን እናሰነብትበታለን! በማለት ያራገቡት ማስተንፈሻ ነበር። ሕዝቡ መከፋፈሉ በቃን! ያለውን አድበስብሶ ያለፈ፤ ትርጉም የለሽ መፈክር ነበር። ምንም ለዐማሮች ያስከተለው እፎይታ የለም። ዐማራ ተኮር ማታለያዎቹ፤ “ኢትዮጵያ! ኢትዮጵያ!” ማለቱና፤ ሰንደቅ ዓለማው በየቦታው ለጊዜው እንዲውለበለብ መፍቀዱ ነበር። ከዚህ ሌላ መተንፈሻ አልሠጠንም። ገዥው ቡድን ግን መተንፈሻ ሰዓት አገኘ።

777678yffgg

ክፍል ይህ ቡድን፤ ራሱን አደላድሎ፣ መሰሎቹን አስባስቦ፤ ሕጋዊ ነኝ ብሎ፣ ተፈራጦ ተቀመጠ።

የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር መሪዎች ወደ መቀለ ፈርጥተው ከሄዱ በኋላ፣ ይሄ ቡድን፤ አዲስ አበባ ላይ መንግሥታዊ መዋቅሩን ተቆጣጥሮ በመያዝ፣ ወታደራዊ ኃይሉን በጁ ጨበጠ። እዚህ ግባ የሚባል ጠንካራ ተቃዋሚ እንደሌለበት ከተረዳ በኋላ፤ ተደላደለ። እብሪት አናታቸው ላይ ወጣ። እርስ በርሳቸው በጎሪጥ መተያየት ጀመሩ። ድሮውንም ለትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር አገልጋይ ሆነው የተነጠፉት ደመቀ መኮነን እና ገዱ አንዳርጋቸው፤ ከአብይ እግር ሥር ወደቁ። ለማና አብይ፤ የዐማራውን በጃቸው መግባት ካረጋገጡ በኋላ፤ ፊታቸውን ወደ ኦሮሞነታቸው አዞሩ። ከለየላቸው የኦሮሞ ጽንፈኞች ጋር በመሆን፤ የአክራሪ ኦሮሞዎች ገዢ ቡድን ሆነ።

  • ፅንፈኞችን በማቅረብ፣ ፅንፈኞቹም እሱን በመቅረብ፣ የራሱን መልክና ምንነት ይዞ ብቅ አለ። እነ ጃዋር መሐመድ፣ በቀለ ገርባ፣ ሕዝቅዬል ጋቢሳ፣ ፀጋዬ አራርሳ፣  በመንግሥት ክፍያ ሆቴል ሲያርፉ፤ ዘበኛና ቢሮ ተመደበላቸው። እናም ርስ በርስ ጽንፈኞች የኛ ተባብለው ተጠጋጉ። አዲስ አበባ ውስጥ ቄሮ ዋናው አስተዳዳሪ ሆነ። ከመንግሥት መዋቅር ውጪ፤ ቄሮዎች የመንግሥትን ትዕዛዝ አንቀበልም በማለት፤ የፈለጉትን የሚያደርጉበት ሀቅ ነገሠ።
  • የነአብይ ገዢ ቡድን፤ ራሱን ሕጋዊ አድርጎ፣ ጥፍሮቹን በኅብረተሰቡ ክንውን በሙሉ ዘረግቶ ገባ።
  • ቀደም ብለው የነበሩትን ለውጥ ፈላጊዎችና በመካከል የሰፈሩትን፤ መነጠረ።
  • በፌዴራልና በየክልሎቹ የራሱን ሰዎች አስገብቶ፤ መንግሥታዊ መዋቅሩን፣ በራሱ ሰዎች ጠቀጠቀ።
  • መጀመሪያ የታደሰ ኢሕአዴግ፤ ቀጥሎ ደግሞ ብልፅግናን አወጀ።

 

ክፍል እግሮቹን አፈራግጦ፣ በዘረኝነት ታጅቦ፣ በሙስና ተድሮ፣ ራሱን ማዕከል አደረገ።

መጀመሪያ ከሕዝቡ የለውጡን መሪነት ነጠቀ። ቀጠለና እኔ ነኝ አድራጊ ፈጣሪው! አለ። በሂደት እጅግ የከረረ ተቃውሞ ስላላጋጠመው፤ ምንም ዓይነት ተቃውሞ እንዳይነሳበት ቤቱን መጠራረግ ያዘ። መንግሥቱን የሱ አምሳልና ይዘት ሠጠው።

  • የሁሉ ሕግ የበላይ ራሱን አድርጎ፤ እስከዛ ጊዜ የነበረውን ሕገ-መንግሥት እንዳለ ጠብቆ፤ በተጨማሪ የሚፈልገውን ሕግ ማውጣት ያዘ።
  • ተቃዋሚዎችን በተለያየ መንገድ ከጥቅም ውጪ አደረገ። አንዳንዶቹን በመደለል፣ ያፈነገጡትን በማሰር እና በማሳደድ ብቸኛ ነኝ! አለ።
  • ሆዳሞችን በዙሪያው ሰበሰበና፣ ሾሞ አሽከሮቹ አደረጋቸው። አጨብጫቢዎችና ሆድ አደሮች ከበቡት።

 

ክፍል የራሱ የሆኑትን በቦታው ከሰገሰገ በኋላ፤ ዴሚክራሲ በኢትዮጵያ አበቃለት አለ።

አብይ ሕመድ፤ እራሱን ሕግ እና ራሱን ኢትዮጵያ አድርጎ ካስቀመጠ በኋላ፤ በተግባር የዚህ ባለቤትነቱን ለማረጋገጥ፤ ካሁን በኋላ ምንም ለውጥ የለም! የሚል መልዕክት መላክ ነበረበት። ይሄ የሁሉም አምባገነኖች የምረቃ መረጃቸው ነው። በዚህ ሂደት፤ አብይ አሕመድ፤

  • ራሱን የሕግ የበላይ አደረገ።
  • ራሱን የሁሉ ነገር አዋቂ አድርጎ አስቀመጠ። ከዶክተሮች በላይ ሐኪም፤ ከቀሳውስት በላይ የሃይማኖት ሊቅ፤ ከኢኮኖሚስቶች በላይ ተንታኝ፣ ከስፖርተኞች በላይ ሯጭ ሆነ።
  • አብይ ለማ መገርሳንም ወደጎን አድርጎ፤ ብቸኛ መሪ ሆነ።
  • የፈለገውን በግሉ መሾምና መሻር የሚያችል ሁኔታ አዘጋጀ።
  • “እኔን መገልበጥ አይቻልም!” ብሎ ተናገረ። “ማንም እንዳይሞክር! ከኔ በላይ መሆን አይቻልም! እናውቅበታለን! የሚል የፈሪ ማስፈራሪያ ሠጠ። (በዚህ ስብከቱ አልለወጥም! ማለቱ ነው)
  • ቀደም ሲል፤ “እኔ ነኝ የማሻግራችሁ!” ማለቱን አንረሳም።
  • ምንም ዓይነት አስመሳይነት በሌለበት ግልጥ ሂደት፤ ዴሞክራሲ አበቃለት።

the Liat Mussie

እስኪ ታሪክ ምን ያስተምረናል!

የፋሺስት ስርዓት ከመለያዎቹ ከፊሎቹ፤

በጣም ጎልተው የሚታወቁትና የሚጠቀሱት፤ ሞሶሎኒ (ጣሊያን)፣ ሂትለር (ጀርመን)፣ ፍራንኮ (ስፔን)፣ ሱሃርቶ (ኢንዶኖዥያ)፣ ፒኖቼ (ቺሊ)

  • የመንግሥትን የበላይነት በሁሉም መንገድ ማጉላት
  • ዋናው ለሚፈልጉት ሁኔታ እንዲመቻቸው ተገለባባጭ የሆነ አቋማቸው፣ ዛሬ የሚያወጡትን ሕግ ነገ ይሽሩታል። የፓርላማ አባሉን ክርስትያን ታደለን ለማሰር፤ ያለመታሰር መብቱን ያለ ሕግ ገፈፉት፤ ምርጫዎችን እነሱ እንዲያቸንፉ ማስተካከል
  • በተለያዩ አገራት በተለያዩ ስሞች ተከስቷል፤ ምናልባት በኛ “ብልፅግና ነኝ!” ይላል።
  • ጽንፈኛ ብሔርተኝነት ማራመድ፤ ጠባብ የሆነው ትናንት የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር ትግራይነትን፣ ዛሬ ደግሞ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ኦሮሞነትን
  • ጠቅልሎ ሥልጣንን በአንድ አካል መያዝ፣ አብይ ፈላጭ ቆራጭ የሆነበት ሀቅ
  • ለሴቶች ያላቸው ንቀት፤ ለሰብዓዊ መብት ያለው ጥላቻና የሚያሳየው ንቀት፤ ያሻውን ማሰርና መፍታት (ተፈታ የሚባል ማግኘቱ ከባድ ነው)
  • ሁሉም ጠላቴ ነው ብሎ የሚረባረብበት አካል ማቅረብ፤ ለሂትለር ይሁዳ ለመለስ ዜናዊና አብይ አሕመድ ዐማራ
  • የሁሉም ነገር የበላይ ወታደራዊው አካል መሆኑ፤ ለፋኖ የሠጡት መልስ፤ “እንኳንስ ትጥቃቸውን ሱሪያቸውን እናስፈታቸዋለን!”
  • ፀረ-ዴሞክራሲያዊ አሠራር፤ የካፒታሊዝምም የሶሺያሊዝምም ጠላት መሆን!
  • ሃይማኖትን የመንግሥት መሳሪያ አድርጎ መጠቀም፤ እሪቻን ከክርስትናና ከእስልምና የበላይ አድርጎ መገተር
  • ለምሁራንና ለጥበብ ያለው ተጸያፊነት፤ ማባረርና ማሳደድ
  • የበሰበሰብ ሙስናና አድልዖ ባገር መስፈን፤ ይሄን እኔ መዘርዘር አይገባኝም
  • የውሸት ምርጫዎች መካሄዳቸው፤
  • ዘረኝነትን የመሥሪያ ቤቶቻቸው መመሪያው ማድረግ፤ ትናንት ትግሬ መሆን፣ ዛሬ ደግሞ ኦሮሞነት!
  • የፖለቲካ ነጻነትን እና የባህል ነፃነትን መግፈፍ! ብልፅግናን ማዳነቅ ብቻ ነው የሚፈቀደው።
  • መሪው ራሱን መንግሥትና አገር አድርጎ ማቅረብ፤ መሪውን ያምላክ ያህል አድርጎ ማቅረብና ማመን፤ አብይን መንካት ኢትዮጵያን መንካት ነው!
  • የመሪውን ተክለሰውነት ማግነን – (ትናንት መለስ ዜናዊ ሁሉን አዋቂ፤ ዛሬ ደግም አብይ አሕመድ አዋቂ፣ አድራጊ ፈጣሪ መሆናቸው – አምባገነንነትን ማንገሥ ናቸው።

 

በዓለም ዙሪያ የቅርብ ጊዜ ታሪካችን ከታዩት ፋሺስቶች ጥቂቶቹ፤

ututiutiut

ክፍል ዐማሮችን በሚመለከት የሄደበትን መንገድ እንመለከት።

ይሄ ገዢ ቡድን፤ በሄደበት መንገድ ሲጓዝ፤ የሥልጣን ወንበሩ እጁ ላይ ሲወድቅ፤ ቀደም ብሎ አቅዶትና ተዘጋጅቶበት አልነበረም። እናም አካሄዱ በየዕለቱ የሚገጥሙትን በመቀበል ነበር። ከትልልቅ ፍራቻዎቹ መካከል፤ ዐማሮች ምን ያደርጋሉ! የሚለው ነበር። ምንም እንኳን ባለፈው የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር አስተዳደር ዐማሮች ሁለተኛና ከዚያ በታች ዜግነት ባለው መልክ ቢያዙም፤ አሁን አንገታቸውን አቅንተው ዋናው የለውጡ ሞተር ሆነው ብቅ ብለዋል። ይሄን የሽግግር ወቅት በጥንቃቄ መሄድ ነበረበት።

  • በሰላም መግዛት ስለማይችልና ከሕዝቡ ጥያቄዎች ሊመጣበት ስለሚችል፤ ሥልጣኑን በሚፈልጋቸው ክፍሎች ተቀባይነት ለማስገኘት፤ አንድ ጠላት እንጥሮ ማውጣት ነበረበት።
  • ከዚህ በፊት በትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር በተቀመጠለት መሠረት፤ ዐማሮችን ጠላት አድርጎ በማስቀመጥ፤ የሱን ሥልጣን፤ በዐማሮች ህልውና የተመሠረተ አደረገው።
  • ዐማሮችን በሁሉም ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ለማስጠላት፤ የነበረውን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር የፖለቲካ ፍልስፍናና የአስተዳደር ሂደት፤ እንዲትም ነገር ሳይቀይር መቀጠሉን መረጠ።
  • ዐማሮች፤ ከመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና የኅብረተሰብ ክንውን ቦታ እንዲያጡ አደረገ።

እንግዲህ ወደኋላ ዞረን የታሪክን ማኅደር ስንፈትሽ፤ እነኚህ ከሞላ ጎደል ፋሺስቶች እና ናዚዎች ወደ ሥልጣን የወጡባቸው ተመሳሳይ መንገዶች ናቸው። ለኔ የአብይ አሕመድ ቡድን፤ ዘመናዊ ፋሺስት ነው! ብዬ አስቀምጫለሁ። ዘመናዊነቱን በሚመለከት ብዙ መዘርዘር ይችላሉ። የተከሰተበት ወቅት፣ የዓለም ተቸባጭ ሁኔታ፣ የአገራችን ልዩ የሆነ የፖለቲካ ሀቅ እና የሄደበት መስመር ግልጥ ያደርገዋል። ለመነሻ የሚሆን እኔ እንዲህ አድርጌ አስቀምጫለሁ። ይሄንን የኔን ሃሳብ፤ ሌሎች ሊሞግቱትና ሊፈትሹት ይቻላሉ። እኔም በዚህ የፖለቲካ ትንታኔ በደስታ ለመሳተፍ ዝግጁ ነኝ። ይሄን ካልኩ በኋላ፤ ይሄ ገዢ ቡድን ማንነቱን ለይተን ካስቀመጥን በኋላ፤ ከዚህ ተነስተን፤ የህልውና ትግላችን እና ከዚህ ዘመናዊ ፋሺስት ገዢ ቡድን ጋር ሊኖረን የሚችለውን፤ ማንኛውንም ግንኙነት እናገናዝባለን።

አሁን ያለው ሀቅ፤ ምንም እንኳን ዘመናዊ ፋሺስትነቱን ተክኖበት፣ ባለ በሌለ ጉልበቱ፣ ዐማሮችን ለማጥፋት የመጨረሻ ዘመቻውን፣ ሳያቋርጥ ቢቀጥልም፤ ዐማሮች በበኩላቸው ቆርጠው ተነስተው አውድማውን ቀይረውታል። ማንም መንግሥት ሆነ ድርጅት የህልውና ታጋይ ፋኖዎቻችን እየረዳቸው አይደለም። ዐማሮች ይሄን አጥብቀን አውቀናል። እናም በራሳችን በክንዳችን ህልውናችንን ልናስከብር ተሰልፈናል። ይሄን ኃይል ማንም ሊያቸንፍ አይችልም። ዐማሮችም ያለን ምርጫ አቸንፎ ራስን መጠበቅ ነው። ሌላው ምርጫ ከምድረገጽ መጥፋት ስለሆነ!

ካፈስካፍንጫው ከታጠቀና ከሠለጠና የአብይ ሠራዊት በላይ፣ ህይወቱን ሊያስጠብቅ የተነሳው የዐማራ ፋኖ፤ የበለጠ ቆራጥና ጀግና ነው። በድሮን እየተደገፈ፣ በታንክ እየታጀበ፣ ስንቅና ጥይት እየተጓዘለት ከተደራጀው የወራሪ ሠራዊት ይልቅ፤ ህይወቱን ያስለፈው የዐማራ ህልውና ታጋይ ፋኖ አቸናፊ ነው።

እንደገና!! የህልውና ትግላችን በድል የሚጠናቀቀው፤ ባስቀመጥነው ግልጥ የሆነ የህልውና ራዕይ፣ በፋኖ ተቋማችን እየተመራን፣ አሠራርና ደንብ ገዝቶን፤ እና በአንድነት ባለ በሌለ አቅማችን በምናደርገው ጥረት ነው።    

    

ማጣቀሻዎች፤

“Fascism Anyone?,” Dr, Lawrence Britt, Free Inquiry, Spring 2003, page 20

The 10 Characteristics That Define Fascism & Why It has Become Popular Again (politicalscienceblog.com) (የፖለቲካ ሳይንስ ብሎግ)

“Fascism Anyone?,” Dr. Lawrence Britt, Free Inquiry, Spring 2003, page 20

What Does Fascism Really Mean? – What Is Fascism? | CFR Education

The 10 Characteristics That Define Fascism & Why It has Become Popular Again

Fascism Definition, Characteristics & Examples – Lesson | Study.com

Fascism | Definition, Meaning, Characteristics, Examples, & History | Britannica

https://worldpopulationreview.com/country-rankings/fascist countries 2024

https://www.civilserviceindia.com/subject/Political-Science/notes/Political,Ideologies: Fascism

ፎቶግራፎቹ በሙሉ፤ ከላይ ከሰፈሩት ድረገጾች የተገኙ ናቸው።

አመሰግናለሁ

ድል ለዐማራ ወገኔ!!!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop