October 28, 2024
ጠገናው ጎሹ
እጅግ ዘርፈ ብዙና ውስብስብ ከሆነው የህይወት ሂደትና መስተጋብርም ይሁን ከተፈጥሯዊ አካባቢ ጋር የተያያዙ የትግል ዘርፎችን ምንነት ፣ እንዴትነትና ከየት ወደ የትነት በአግባቡና በሰፊው የመረዳት ፣ የመተርጎም ፣ የመተንተን እና ለትክክለኛ ዓላማና ተግባር እንዲውል የማድረግ አስፈላጊነት እንደ ተጠበቀ ሆኖ የዚህ ርዕሰ ጉዳዬ መነሻና ማጠንጠኛ ግን ይህንን ሰፊና ውስብስብ የትግል ዘርፍ አይነትና ባህሪ መዘርዘርና መተንተን አይደለም።
የርዕሰ ጉዳዬ ትኩረት ሰው ሰራሽ (የገዛ ራሳችን ልኩን ያለፈ ሁለንተናዊ ደካማነት ውጤት ) የሆነው ፣ የህዘብን (የገዛ ራችንን) ህይወት ለማመን ቀርቶ ለማሰብም በሚከብድ ሁኔታ ምስቅልቅሉን እያወጣ አያሌ ዓመታትን ያስቆጠረው እና ከስድስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ በእጅጉ አሰቃቂ ( extremely tragic) በሆነ ሁኔታ በመቀጠል ላይ የሚገኘው የጎሳ ደምና አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች ሥርዓት እንደ ሥርዓት ተወግዶ የነፃነትና የፍትህ (የዴሞክራሲያዊ ) ሥርዓት እውን መሆን ካለበት የማይነጣጠሉ የትግል ዘርፎች ጉዳይ ከምር ሊወሰዱ ይገባል የሚል ነው።
ይህንን ስል ግን የተካሄደና በመካሄድ ላይ የሚገኝ እልህ አስጨራሽ ሁለብ ተጋድሎ አልነበረም ወይም የለም ለማለት አለመሆኑን ላሰምርበት እወዳለሁ።
የርሰ ጉዳዬ ጭብጥና ዓላማ በዋጋ ሊተመን የማይችል (priceless) የህይወት መስዋዕትነት የተከፈለባቸው በርካታ የህልውና ፣የነፃነት፣ የፍትህና የእኩልነት ትግሎቻችን የሸፍጠኛ፣ የሴረኛና የጨካኝ ገዥ ቡድኖችን ምሽግ (አስቀያሚና አደገኛ የጎሳ ደምና ጥንት ስሌት ፖለቲካ ሥርዓትን) ሰብሮ ለማለፍ እያቃታቸው የውድቀት አዙሪት ሰለባዎች የሆኑበት እጅግ አሳዛኝና አሳፋሪ የፖለቲካ ማንነትና ምንነት ፈፅሞ በማይበገርና ዘላቂነት ባለው የተባበረ ተጋድሎ ፍፃሜ ማግኘት ካለበት የማይነጣጠሉ የትግል ዘርፎችን በተገቢው ስትራቴጅካዊና ሥልታዊ ጥበብ መጋፈጥን ግድ ይላል የሚል ነው።
ለዚህ ነው እስካሁን ከመጣንበት የትጥቅ ትግል ታሪክ አስተሳሰብና አካሄድ አንፃር እጅግ የተለየና አበረታች በሆነ ሁኔታ በይፋ መካሄድ ከጀመረ ከአንድ ዓመት በላይ የሆነው የአማራ ፋኖ እና መነሻ ምክንያቱን፣ አስተሳሰቡን፣ ዓላማውን ፣ በመሬት ላይ የሚታየውን ገቢራዊ አካሄዱን እና አገራዊ ግቡን የሚጋሩ ሌሎች የነፃነትና የፍትህ ሥርዓት አፍቃሪና ተጋዳይ ወገኖች ተጋድሎ ከመቸውም ጊዜና ሁኔታ በላይ ሊያሳስበን የሚገባው ። አዎ! ይህ አይነት ፍትሃዊና እልህ አስጨራሽ ተጋድሎ ወርቃማ ታሪካዊ (ትውልዳዊ) የለውጥ ድል ሆኖ ይጠናቀቅ ዘንድ ሊነጣጠሉ የማይችሉ የትግል ዘርፎች ተገቢውንና ወቅታዊውን ትኩረት ያገኙ ዘንድ በግልፅና በቀጥታ የመናገርና የመነጋገር አስፈላጊነት ጊዜና ቅደም ተከተል የሚሰጠው ጉዳይ መሆን የለበትም።
ከሦስት አስርተ ዓመታት በላይ በሆነውና አሁንም እጅግ አስከፊ ሆኖ በቀጠለው የጎሳ ደምና አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች ሥርዓተ አገዛዝ በማንነቱና በምንነቱ ተለይቶ ህልውናውን በሚፈታተን አደገኛ ሁኔታ ውስጥ እንዲገኝ መደረጉ ለማንምና ለምንም እንደማይጠቅም ለማሳሰብ፣ ለማስጠንቀቅና ለማስቆም ያሰማው እልህ አስጨራሽ ጩኸት፣ ያደረገው ጥረት እና ብሎም ትክክለኛውና ዘላቂው መፍትሄ በጋራ አገር ውስጥ በእኩልነት የሚያስኖር ሥርዓት እውን ማድረግ መሆኑን በትክክለኛና ዘላቂ መፍትሄነት ያቀረበበት ወርቃማ መንገድ (መፍትሄ) ተቀባይነት ያጣበትን እና ህልውናው ይበልጥ አደጋ ውስጥ እንዲገባ የተደረገበትን የአማራ ማህበረሰብ (ህዝብ) ጥያቄ በማንገብ የተቀጣጠለውን የፋኖነት (የአርበኝነት) ተጋድሎ በየትኛውም የህልውና፣ የነፃነትና የፍትህ ትግል መመዘኛ ለመቃወም ወይም ለማጣጣል ፈፅሞ አይቻለም።
ይህ እጅግ ግዙፍና መራር ተጋድሎ የመስዋዕትነትን አይነትና መጠን በቀነሰ ሁኔታ ግቡን ይመታ ዘንድ ከዚህ በታች ለማሳያነት በተጠቀሱት አበይት የትግል ዘርፎች ቅንብርና ቁርኝት ረገድ ያለውና ሊኖር የሚችለው ክፍተት ከፍተኛ ትኩረትና ጥረት የሚጠይቅ ስለ መሆኑ ግልፅ፣ ቀጥተኛና ገንቢ በሆነ ይዘትና አቀራረብ መናገርንና መነጋጋገርን የግድ ይላል።
ሀ) ከሦስት አሥርተ ዓመታት በላይ በሥልጣነ መንበር ላይ በተፈራረቁ እኩያን የጎሳ ደምና አጥንት ስሌት ፖለቲካ ሥርዓት ጠርናፊዎች (አራጊና ፈጣሪዎች) እና ይህንኑ ወንጀለኛ አገዛዛቸውን የብሔር/ብሔረሰቦች እኩልነት ተሳትፎ ለማስመሰል በተጠቀሙባቸውና በሚጠቀሙባቸው የሰው ሥጋ ለባሽ አጋሰሶች ምክንያት ተፈጥሯዊ (በህይወት የመኖር መብቱ/ ህልውናው) አደጋ ላይ የመውደቁን መሪር እውነት ዘግይተውም ቢሆን ከምር የተረዱና የተቆጡ ልጆቹ ፋኖነትን/አርበኝነትን ስያሜው ባደረገ የትጥቅ ትግል ንቅናቄ ተነሥተው በአንድ ዓመት ውስጥ ያስመዘገቡትንና እያስመዘገቡ የቀጠሉበትን እውነታ እንኳንስ ለማስተባበል አሳንሶ ለማየትና ለማሳየትም ፈፅሞ አይቻልም።
እንደማነኛውም በጦርነት ውስው እንደሚገኝ አገር ወይም ማህበረሰብ በግለሰብ ወይም በንኡስ ቡድን ሊፈጠሩ የሚችሉ ስህተቶች ካልሆኑ በስተቀር በአገራችን የትጥቅ ትግል ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የታዘብነውና እየታዘብን ያለነው ውጊያንና ከውጊያ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በተመለከተ የሚታየው የዲሲፕሊን አፈፃፀም ከእኛ አልፎ የዓለምን አወንታዊ ትኩረት የሳበ ነው።
ይህ ማለት ግን መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮች የሉም ማለት አይደለም። አንዳንድ ወገኖች ከቅንነትና ለትግሉ ስኬታማነት ካለቸው ጉጉት ይመስለኛል “በመሪነት ላይ በሚገኙ ግለሰቦች (ለምሳሌ በዘመነ ካሴና በእስክንድር ነጋ መካከል ) ችግር መኖሩ ባይካድም በውጊያ ሜዳ ላይ ወይም በታጋዩ መካከል ልዩነት ስለሌለ ልዩነትና ችግር እንዳለ አድርጎ ማሳየት ነገርን ማባባስ ነው” የሚል ሥጋት ሲያነሱ ይሰማሉ።
እርግጥ ነው እንኳንስ በእንደ እኛ አይነት ለመግለፅ በሚያስቸግር ፖለቲካ ወለድ ቀውስ ውስጥ በሚካሄድ የፖለቲካ ትግል በአንፃራዊነት የተሻለ ነው በሚባል አገር ውስጥ የሚካሄድ የትኛውም አይነት የንቅናቄ ሂደትም ችግር ቢገጥመው አይገርምምና ጉዳዩን ከሚገባው በላይ ማራገብ ጉዳት እንጅ ጥቅም አይኖረውም ። ይህ ማለት ግን ከቁጠጥር ውጭ አይሆኑም የሚባሉም ጉዳዮች ከቁጥጥር ውጭ ሊሆኑ ይችላሉና ተገቢና ወቅታዊ የሆነ ክትትልና ሂሳዊ አስተያየት አስፈላጊነትን ችግር ማባባስ ነው በሚል ሰንካላ ምክንያት ማፈንና ማጣጣል በፍፁም አይጠቅምም።
ወደ ፋኖ ጉዳይ ስንመጣ “የእኔ መሪ እገሌ እንጅ እገሌ አይደለም” እያለና እየተባባለ የጋራ ጠላት የሆነውን የሸፍጠኛ፣ የሴረኛና የጨካኝ ገዥ ቡድኖችን ሥርዓት እዋጋለሁ የሚል የነፃነትና የፍትህ ተዋጊ ነገና ከነገ ወዲያ ሊሆን የሚችለውን በእርግጠኝነት ለመገመት ቀላል አይመስለኝም።
ለዚህ ነው የውጊያውና የተዋጊው አስተሳሰብና ተግባር ከሚቀጥለው የትግል ዘርፍ ጋር በአግባቡና በዘላቂነት ካልተቆራኘ ከፍተኛ ችግር ሊፈጥር እንደሚችል ለመረዳት ፈፅሞ የማያስቸግረው ። ወደዚያው እንለፍ።
ለ) ይህ አንድ ዓመትና የጥቂት ወራት እድሜ ያስቆጠረው እጅግ አበረታች ተጋድሎ በጠራ የፖለቲካ አስተሳሰብ፣ ርዕዮት፣ ፕሮግራም፣ መርህ፣ ተልእኮ፣ ራዕይ እና ይህንኑ እውን ለማድረግ በሚችል የፖለቲካ አደረጃጀት እንዲመራ የማድረጉ ጉዳይ (ጥያቄ) መሠረታዊ የትግል ዘርፍ ነው።
አዎ! ከዘመን ጋር ለመራመድ ከተሳነው የፖለቲካ ባህላችን እና እጅግ አስከፊ ሆኖ ዘመናትን ካስቆጠረውና ከስድስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ ለመግለፅ በሚከብድ ሁኔታ አስከፊ ሆኖ ከቀጠለው የጎሳ ደምና አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች ሥርዓት አንፃር የነፃነትና የፍትህ ትግሉ እጅግ ፈታኝ የመሆኑ ጉዳይ የሚያጠያይቀን አይመስለኝም።
ይህ ግን ነፃነትና ፍትህ ፈላጊው ለፈፀማቸው ለሚፈፅማቸው ተደጋጋሚና እጅግ አስቀያሚ ስህተቶችና የውድቀት አዙሪቶች ሃላፊነትን ከመውሰድ ነፃ አያደርገውም። ለምን? ቢባል ከዘመን ጠገቡ ፖለቲካ ወለድ ግዙፍና መሪር ተሞክሮ በመውሰድ ሊነጣጠሉ የማይችሉ የትግል ዘርፎችን ሲነቀነቅ በማይፈርስ መስተጋብራዊ ቁርኝት አቆራኝቶ ህልውና ፣ነፃነት፣ ፍትህና እኩልነት ለሚረጋገጥበት ሥርዓት አዋላጅነት ለመጠቀም ያልቻለና በተደጋጋሚ የውድቀት አዙሪት ውስጥ የሚጓጉጥ ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ ሃላፊነትን ለመውሰድ የማይደፍር ከሆነ ነፃነትና ፍትህ ፈላጊነቱ ከንቱ ቅዠት ወይም የሥልጣን ፍለጋ እንጅ ሌላ ሊሆን አይችልም።
እናም አጓጊው የፋኖ ተጋድሎ የአማራም ሆነ የሌላው ህዝብ ህልውና፣ ነፃነት፣ ፍትህ፣ እኩልነትና ሰላም የሚረጋገጥበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ለማድረግ ማስቻል ካለበት ሊነጣጠሉ የማይችሉ የትግል ዘርፎችን ቁርኝትና መስተጋብር ከምር መፈተሽንና አስፈላጊውን የማጠናከሪያ እርምጃ መውሰድን ግድ ይለዋል። የአማራ ፋኖ እና የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት፣ መነሻና መዳረሻ፣ ዘመነና እስክንድር ፣ የዘመነና የእስክንድር ፋኖ፣ የዚህ ወይም የዚያ ክፍለ ሃገር ፋኖ ፣ ወዘተ በሚል የልጆች ጨዋታ አይነት ፖለቲካ ውስጥ መርመጥመጥ እየተካሄደ ያለውን የፋኖነት/የአርበኝነት ተጋድሎ አይመጥንምና መስተካከል ያለበት ነገ ሳይሆን ዛሬ ነው። ዛሬ ያልተስተካከለ (ያልታረመ) ክፍተት/ጉድለት ሥልጣን ቢያዝ ሊያስከትለው የሚችለውን አሉታዊ ውጤት መገመት አያስቸግርምና ከምር ልንወስደው ይገባል የሚል እምነት አለኝ።
ሐ) ሦስተኛው የትግል ዘርፍ ከላይ የተቀሱ የትግል ዘርፎችን አስመልክቶ የሚደረግ የህዝብ ግንኙነት (public relation/communication) ሥራ ነው። ይበልጥ የማሻሻሉና የማጠናከሩ ጉዳይ እንደ ተጠበቀ ሆኖ በአገራችን ካለው እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ እና ከድርጅታዊ አቅም አንፃር ሲታይ በዚህ ረገድ የሚደረገው ጥረት አበረታች ነው ። ይህም ሆኖ ግን 1) በተለይ ከእስክንድር ነጋ የሚሰማው የተመራጭ መሪነት ዲስኩር እና ይህንን በሚቃወሙ የፋኖ አደረጃጀቶች አባላት የሚሰጡ ምላሾች ህዝብን በእጅጉ የሚረብሹና የህዝብ ግንኙነት መስተጋብሩን የሚያበላሹ መሆናቸውን መደበቅ አይቻልም። ይህ ደግሞ አጠቃላይ የሆነውን የፖለቲካ እይታና የአደረጃጀት ድክመትን በመፈተሽ እንጅ በተናጠል የሚስተካከል አይደለምና ከምር ሊታሰብበት ይገባል። 2) ብዙውን ጊዜ የምንጠቀመው ህዝብ የሚለውን የወል መጠሪያ (ስም) ነው። ይህ እንደ ተጠበቀ ሆኖ ግን ህዝብ አንድ አይነት ፍላጎትና ሚና ያላቸው ሰዎች ስብስብ አይደለምና የህዝብ ግንኙነታችንም ይህኑ ግምት ውስጥ ያስገባ ቢሆን ይበልጥ ውጤታማ ይሆናል።
ስለሆነም የመማር እድል ሳያገኝ ያስተማረውን መከረኛው ህዝብ ግምት ውስጥ ባስገባ ሁኔታ ለነፃነትና ለፍትህ ሥርዓት እውን መሆን እገዛ ለማድረግ የተሳነውን ምሁር ፣ በቀጥታም ይሆን በተዘዋዋሪ በብልሹ የፖለቲካ ሥርዓት ምክንያት የመማር (የማወቅ) እድሉ ምስቅልቅሉ የወጣበትን ወጣት ተማሪ ፣ ከባለጌና ሙሰኛ ባለሥልጣናት ጋር ለመተሻሸት ባለመቻሉ ነግዶ መኖር ጭንቅ የሆነበትን ነጋዴ/የቢዝነስ ሰው፣ እንኳንስ አገር ተረክቦ በኩራትና በክብር ለመኖር የራሱን ህይወት መንገድና መዳረሻ ለማወቅ የተሳነውን ወጣት ትውልድ፣ የሴቶችን መብት ከአዋጅና ከወሬ በዘለለ የማያውቁትን እናቶችና እህቶች፣ ሳይፈልጉ ወደ ዚህ ዓለም መጥተው የመከራና የሰቆቃ ሰለባ የሆኑትን ህፃናት፣ እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ የፖለቲካ ወለድ መከራንና ውርደትን ተሸክመው የመምህራን ወይም የሠራተኛ ማህበራት ነን ባዮችን፣ የህዝብ ሁለንተናዊ አኗኗርና እውነታ ነፀብራቅ ነው የሚባለውን የኪነ ጥበብ ሙያ ከእኩያን ገዥዎች ጋር በመተሻሸት ወይም በአድርባይነት ደዌ የሚያረክሱ ወገኖችን፣ ሃይማኖታዊ ሃላፊነታቸውን ለእኩያን ገዥዎች አሳልፈው እየሰጡ ህዝብን የሚያደናግሩና የሚያደነዝዙ የሃይማኖት መሪዎችንና ሰባኪዎችን፣ ወዘተ ዒላማው (target) የማያደርግ የፖለቲካ ትግል የህዝብ ግንኙነት ውጤታማነቱ ውሱን ነውና ሊታሰብበት ይገባል የሚል እምነት አለኝ።..
እናም ልብ ያለው ልብ ይበል!