ግርማ ብርሃኑ (ፕሮፌሰር)
(ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ የተረጎመው፡ ደሳለኝ ቢራራ)
መግቢያ
ስለማህበራዊ ሚዲያ አሉታዊ ገጽታዎች ብዙ ተብሏል። ተጽዕኖዎቹም ፈርጀ ብዙ መሆናቸው ታውቋል። የስነተግባቦታችን ባህርይ የሚወሰነውም በማህበራዊ ሚዲያዎቹ አጠቃቀም ላይ በምናሳየው ስ ምግባር እየሆነ መጥቷል። አሉታዊ ይዘት የሚበዛበት ተግባቦት በየማህበራዊ ሚዲያው እየተንሰራፋ ነው። የማህበራዊ ሚዲያ አሉታዊ ተጽዕኖዎች በስፋት ቢጠኑም የተሳሳቱ እና የሀሰት መረጃዎችን ስርጭት መደበኛ ማድረግ ግን በተገቢው ደረጃ አልታየም። የሀሰት መረጃ እና የተሳሳተ መረጃን ሆን ብሎ በማህበራዊ ሚዲያ ማሰራጨት የዘመናችን ስነተግባቦት ካንሰር ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። እነዚህ ችግሮች ከጽንፈኛ አመለካከቶች እና ከጥላቻ ፖለቲካው ባላነሰ እንዴያውም በበለጠ፡ ከፍተኛ ቀውስ የሚፈጥሩና ዋጋቸው በደም የሚከፈል እዳዎች ናቸው።
በዚህ ጽሁፍ ትኩረት የማደርገው የማህበራዊ ሚዲያው በአማራ ፖለቲካና በህልውና ትግሉ ዙሪያ ያለውን እኩይ እና መርዛማ መስተጋብር ነው። እነዚህን መስተጋብሮች ወይም ግንኙነቶች በፌስቡክ፣ በቲክቶክ፣ በትዊተር እና በዋትስአፕ የቡድን ስብሰባዎች ላይ በንቃት በመከታተልና በመሳተፍ አጥንቸዋለሁ። በተለይ በውይይቶች ወቅት የሚታየው የስነምግባር ጉድለት የህዝባችንን መገለጫ የነበረ ጨዋነት፡ አሳሳቢ በሆነ ደረጃ ላይ እንዳለ ያሳያል። እነዚህ ማህበራዊ መድረኮች እና የድረገጽ መሰባሰቢያዎች በጨካኝ እና አስጸያፊ መስተጋብር የተሞሉ ሁነዋል። እጅግ አስደንጋጭ የፖለቲካ መግለጫዎች እና የጅምላ ግድያ ጥሪዎችም ይተላለፉባቸዋል። የኢትዮጵያ መንግስት በአማራ ህዝብ ላይ ያወጀውን ጭፍጨፋ እና ማሳደድ ለመቀልበስና የአማራን ህልውና እና ጥቅም ለማስጠበቅ የሚደረግ ማሕበራዊ እንቅስቃሴ መሆን የነበረበት በእያንዳንዱ አማራ መካከል አወንታዊ ግንኙነትና ትብብር እንዲኖር ማስቻል ነበር። እየተስተዋለ ያለው ግን ጠላትን ለመዋጋት ከሚደረገው ርብርብ በላይ አንዱ አማራ በሌላው አማራ ላይ (የራስን ወገን) መፈረጅ፥ መከፋፈል፥ ማግለል፥ ማጥቃት እና ማጠልሸት ላይ ተጠምዷል። ይህ ውስጣዊ ውንጀላ እና መርዛማ መስተጋብር ከማህበራዊ ሚዲያው የዘወትር ተገልጋዮች አልፎ ወደ ፋኖ ተዋጊዎቹ በመዛመት፡ ስሜታዊነትና ጭፍንነት የተሞላባቸው መግለጫዎችን እስከማውጣት አድርሷል።
በበርካታ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ እንደታዘብነው፡ በሌሎች ሀዘንና ጉዳት ላይ መደሰት (schadenfreude) ተለምዷል። ይህ ጭካኔ እና መረን የለሽ ጥላቻ እራሱን የቻለ አዙሪት ፈጥሯል። መጀመሪያ በድባቴ ውስጥ ያሉ፥ የአዕምሮ ጤና መቃወስ ያጋጠማቸው ግለሰቦች ከአንድ ኮምፒተር ወይም ተንቀሳቃሽ ስልክ ላይ ቀርበው የህዝብን ሞራልና ስነምግባር በሚጥስ ኃይለቃል ንግግራቸውንና ተግባራቸውን ያስተላልፋሉ፤ እነዚህ አሉታዊ ይዘቶች በፍጥነት ይዛመታሉ፤ ተመልካቹ ለእነዚህ ሁኔታዎች ተደጋግሞ ሲጋለጥ እራሱም ለአእምሮ ጤና መቃወስ፥ ድብርት እና እረፍት ማጣት ይዳረጋል። በማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ላይ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ከሆነ ድብርት፥ ጭንቀት፣ ብቸኝነት እና በራስ-አለመተማመን ባህሪያት፡ አዘወውትረው ከሚያዩዋቸው የማህበራዊ ሚዲያ ይዘቶች ጋር ጠንካራ ትስስር እንዳላቸው ያሳያሉ።
የአማራ ፖለቲካን በተመለከተ ግን የተመላከቱት አይነት ግለሰቦች ከሚፈጥሩት አሉታዊ ተጽእኖ ባሻገር ሆን ተብሎ በመዋቅር የተደራጀ የሴራ አጀንዳ እንዳለ የሚታመን ነው። እርግጥ አንዳንድ የተሳሳቱ መረጃዎች እና የውሸት ዜናዎች ስርጭት ላይ ግለሰቦችም ሚና ሊኖራቸው ይችላል። በተለይ ድረገጽ ላይ የሚደረጉ ውይይቶች እና አብሶም ደግሞ ማንነትን ሳያሳውቁ በሚሳተፉ ሰዎች ዘንድ የሞራል ገደቦችን ለመጣስና ከስነምግባር ውጭ የሆኑ ነውሮችን ለመናገር ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረ የሥነ ልቦና ባለሙያዎች አስተውለዋል። ማንነቱ የማይታወቅ ሰው በሚፈጥረው እና በሚያሰራጨው ማህበራዊ ቀውስ ተጠያቂ የማይሆንበት እድል መኖሩ ለችግሩ መባባስ አስተዋጽዖ አድርጓል። ማን እንዳመጣው በማይታወቅ የሀሰት መረጃና ማስረጃ ከባድ ማህበራዊ ጥቃት እየተፈጸ ነው ያለው።
እኔ በግሌ ለሁለት ሳምንታት የዘለቀ ጥቃት ተፈጽሞብኛል። እስካሁን ድረስ ባልገባኝ ምክንያት በግል ባህሪዬ ላይ የተደረገ የማጠልሸት ዘመቻ አለ። በእኔ እምነት እንደዚህ አይነት የማጠልሸት እርምጃ በንፁሀን እና በፋኖ ደጋፊዎች ላይ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የፋኖ ትግል ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል። በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የተገለጹት መርዛማ አስተያየቶች በአብዛኛው በሁለት ምድቦች ይከፈላሉ፡ የጥላቻ ንግግር እና ዘለፋ (hate speech and online harassment: aka trolling)። ሁለቱንም አይነት ጥቃቶች በግሌ ደርሰውብኛል፣ እና ይህንን እንዳዘጋጅ ያነሳሳኝም ይህው ምክንያት ነው።
በጥላቻ ንግግር ምንነት ዙርያ ብዙ ክርክር ቢኖርም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንዲህ ሲል ይተረጉመዋል፡ “ማንኛውንም ሰው ወይም ቡድን በማንነቱ ላይ በመመስረት የሚያጠቃ ወይም በሃይማኖታቸው፣ በጎሣቸው፣ በብሔራቸው፣ በዘራቸው፣ በቀለማቸው፣ በዘራቸው፣ በጾታቸው ወይም በሌላ መለያቸው ላይ ተመስርቶ፡ በጸያፍ መንገድ የሚገልጽ ማንኛውም አይነት ንግግር ነው”።
አማራን የተመለከተ የጥላቻ ንግግር የምንታዘበው አሁን በተለየ ትኩረት የህልውና ትግሉን በሚመሩ ፋኖዎችና በሀሳብ መሪዎች ላይ አነጣጥሮ ነው። አላማው በመካከላቸው አለመግባባትና መከፋፈልን መፍጠር ነው። ከዚህ ዘመቻ ጀርባ የአገዛዙ እጅ እንዳለበት እሙን ነው። ይህ በአማራው መካከል ጥላቻንና መከፋፈልን የሚያሰፋ ዘመቻ ከአገዛዙ ቅልብ የማህበራዊ ሚዲያ አበጋዞች ባላነሰ እየተሰራጨ ያለው ስለጉዳዩ ጠለቅ ያለ እውቀት በሌላቸው አንዳንድ ወገኖች ጭምር ነው። በዚህ መልኩ እየተጋጋለ እና አታካች እየሆነ የመጣው መርዛማ መስተጋብር የሀሳብ ሰዎችን እና የአማራውን ትግል የሚደግፉ በጎ ምሁራንን ከሀሳብ መድረኮች እያራቀ ነው። ምክንያቱም ፍረጃ እና ስድቡን መቋቋም ከባድ ስለሚሆን በማህበራዊ ሚዲያ ሃሳባቸውን መግለጽ ይፈራሉ። እየተፈጸመ ያለው ስብእናን የማጠልሸት ዘመቻ (character assassination) እጅግ አስቀያሚ ነው።
ለአብነት ያህል የአንድ ታዋቂ ምሁርን ገጠመኝ ላጋራችሁ። ፕሮፌሰሩ በTwitter ውይይት ላይ ተገኝቶ ስለ ጸረ አማራ ትርክቶች አመጣጥ እውቀቱን ያካፍላል። ያነሳቸው ሀሳቦችና ጠንከር ያለ የውይይት በር ከፍተው ብዙ አስተያየቶችም ቀርበዋል። በተብራሩት ሀሳቦች ላይ መስማማትም፥ ተቃውሞም ተንጸባርቋል። ውይይቱ በሂደት ደጋፊና ተቃዋሚ ጎራ ሲፈጠር ስሜታዊነት እና ክርክር የሚያስከትል መሆኑ የሚጠበቅ ነገር ነው። ነገር ግን በሀሳብ ሰጭው ግለሰብ ማንነትና ስብእና ላይ ያነጣጠረ ዘለፋ እና ስድብ እንደ ናዳ ይወርዳል ተብሎ አይጠበቅም። የተፈጠረው ክስተት ይህ ነበር። እና የመሰባሰቢያው መድረክ ገጽ ለገጽ በአካል የማያቀራርብ መሆኑን ተጠቅሞ የተከበሩ ሰዎችን ለመዝለፊያነት ማዋል እንደ ሰው የደረስንበትን የስልጣኔ ደረጃም እንድንመረምር ያደርገናል። እድሜ ልኩን ያካበተውን ተሞክሮና ልምዱን በዚህ መድረክ ሲያካፍል የነበረው ፕሮፌሰር በደረሰበት ዘለፋ ምክንያት ተስፋ ቆርጦ፤ በጭራሽ ድጋሜም መገኘት እንደማይፈልግ ተናግሮ ወጣ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በየትኛውም መድረክ አይቼው አላውቅም። ፕሮፌሰሩን በአሰቃቂ ሁኔታ ያጠቃው ነውረኛ ወጣት፡ ምናልባትም ከኢትዮጵያ መንግስት ሰውየውን ዝም ለማሰኘት የተላከ ይሆናል። እንደዚህ አይነት ጥቃት መፈጸም የቶታሊታሪያኒዝም ገዥዎች ሞደስ-ኦፔራንዴ ነው። የሚቃወማቸውን ወይም በሀሳብ ይሞግተናል ብለው የሚፈሩትን ሰው ያሳድዱታል፤ አዋርደው ድምጹን ያጠፉታል።
ጆርጅ ኦርዌል “Totalitarian” የሚለውን ቃል ሲፈጥር በፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ውስጥ አልኖረም፤ ነገር ግን ምን ሊመስል እንደሚችል በማሰብ ብቻ ነበር የአምባገነን አገዛዞችን (ማኅበረሰቦችን) በሁለት ዋና ዋና ባህሪያት የገለጻቸው፡፡ ኦርዌል የሚጠቅሳቸው ሁለት ባህሪያት ውሸት (ወይም የተሳሳተ መረጃ) እና “ስኪዞፍሪንያ – schizophrenia” ብሎ የጠራው ናቸው። ኦርዌል አክሎ እንደሚያብራራው በአምባገነን መንግስታት የሚካሄደው የተደራጀ ውሸት፡ ለጊዜያዊ ማታለያ ታክቲክ ተብለው በወታደራዊ ስምሪቶች እንደሚዋሸው አይደለም። በውሸትና በሀሰት መረጃ የፕሮፓጋንዳ ሱሰኛ ህዝብ መፍጠር ለአምባገነናዊ የስልጣን ማእከላዊነት መሰረታዊ ነገር ነው። ፕሮፓጋንዳ፥ ውሸት እና የሀሰት መረጃ ስርጭት ከአምባገነናዊ ስርአት ህልውና ጋር የተያያዙ ናቸው። አምባገነናዊ መንግስት የማጎሪያ ካምፖች እና ሚስጥራዊ የስለላ መዋቅሮቹን ቢያፈርስ እንኳ የሀሰት መረጃ ማሰራጨቱን አያቆምም። ኦርዌል፡ አምባገነንነት ሥነ ጽሑፍን ጭምር የማይቻል ያደርገዋል ይላል። ሥነ – ጽሑፍ ወንጀል ተደርጎ በሀገራችንም በሽህ የሚቆጠሩ ወጣት ጸሐፍት፥ ገጣሚያን፥ ደራሲያን፥ ዘጋቢያንና ጦማርያን በግዞትና በማጎሪያ ቤቶች እንዳሉ አይዘነጋም። ኦርዌልም ስነጽሑፍ ብሎ የጠቀሰው ከምናባዊ ልቦለድ እስከ ፖለቲካዊ ጋዜጠኝነት፣ ግጥምና በስድ ጽሑፍ የሚቀርቡ መጣጥፎችና ጽሑፎችን ሁሉ ማለቱ ነው። እነዚህ ሁሉ በአምባገነኖች ክልክል የሚደረጉት የአገዛዙን ክፋትና ስንጥቆች በመጠቆም የህዝብን ስሜት ቀስቅሰው ለለውጥ ያነሳሳሉ ተብሎ ስለሚፈራ ነው። በዚህ ምክንያት አገዛዙ ከሚፈቅደው አመለካከትና አቋም ውጭ የሆነን ሁሉ በማጥፋት ‘እውነትም መንገድም አንድ ብቻ ነው’ የሚባል አስተሳሰብ የህዝብ ገዥ መርህ ይሆናል። የተለየ እይታ፥ ሞጋች ሀሳብ፥ አማራጭ መንገድ፥ ብዙሀዊነት የሚባሉ ጉዳዮች ይደመሰሳሉ። አንድ ወጥ የሆነ የወል እውነት ብቻ ይሰራል። ከዚህ የቡድን እውነት የተለየውን ሁሉ ለማውገዝ፥ ለመከልከልና ለማጥፋት ይዘመትበታል። ይህንንም ለማሳካት ገዥዎች ከፍተኛ ሀብትና የሰው ኃይል ያሰማራሉ።
አሁን የሚታየውን የአማራ ፖለቲካ ውስጥ ገብተው በአማራ መካከል የተፈጠረ ችግር እንዳለ አስመስለው የሚተውኑትም የገዥው ስርአት ቅጥረኞች ናቸው። አስቀድሜ እንዳስቀመጥኩት ግን እነዚህን የአገዛዝ ስርአቱ አንጃዎች ተከትሎ በራሱ ወገን ላይ የሚዘምት አማራ እየተበራከተ መሆኑን ሊሰመርበት ይገባል። በዚህ ሁኔታ አማራውን ከፋፍሎ አንዱ በአንዱ ላይ እንዲዘምትበት ማስቻል ለጨፍጫፊው ስርአት እጥፍ ድርብ ድል ነው። አማራው ላይ ተጽዕኖ እየተደረገ ያለው የሀሳብ ብዝሀነትን የማይቀበል ፍጹም ቶታሊታሪያን ማህበረሰብ እንዲሆን ነው። በየወቅቱ የሚነሱ የፖለቲካ ግለቶችን ተከትሎ በማህበረሰቡ ውስጥ የሚኖረውን የመከፈፋፈል ስጋት እና ፍራቻ በማጦዝ ማህበራዊ አንቂ ነኝ የሚሉ ወገኖችን ጽንፍ የወጣ የአንድነት መሻት እንዲያድርባቸው የሚያደርገው አገዛዙ ነው። ክስተቱ አጀንዳ መስጠት ይባላል። “በመካከላችን መከፋፈል እንዳይኖር” ብሎ ክፍተቶች እንዳይፈጠሩ የሚተጋውን ህብረተሰብ የበለጠ የመከፋፈል ስጋት አለብን ብሎ እንዲያስብ ፕሮፓጋንዳ የሚሰራው አገዛዙ ነው። የዚህው ህዝብ እውነተኛ ተቆርቋሪ የሆኑና የመከፋፈል ስጋቱን እንከላከልለታለን ብለው የሚያስቡ አንቂዎችንም ስለአንድነት እና ከአንድነቱ ያፈነገጠውን እስከማጥፋት ድረስ ደመነፍሳዊ እርምጃ እንዲወሰድበት የሚያበረታታውን አጀንዳ የሚሰጠው እራሱ አገዛዙ ነው። አንድነትን በኃይል እና በማፈን እንዲመጣ የሚፈልገው አገዛዙ ብቻ ነው። ለህዝብ የሚጠቅመው በአንድነት እና ብዝሀዊነት መካከል ትክክለኛ ሚዛናዊነት ሲጠበቅ ነው። ስለዚህ በሁለቱም ወገናችን በኩል ጣልቃ እየገባ ተጨባጭ ያልሆነውን ስጋት ሁሉ በሀሰት መረጃና በውሸት በማጋነን፤ እራሱ ለፈጠረው የተጋነነ የመከፋፈል ስጋት መፍትሄው፡ የማያፈናፍን አንድነት (ጨፍላቂነት) እንደሆነ አድርጎ የሚጫወተው እና ብቸኛው የዚህ ሂደት ተጠቃሚ አገዛዙ ነው። አንድነትን መሻት ከሚገባው በላይ አልፎ ጨፍላቂነት ከሆነ፤ ከዚያም ተሻግሮ ገፊነትና ፈራጅነት እንዲሁም አግላይነት ከሆነ ጤነኝነት አይደለም። ይህን ጽንሰ ሀሳብ በምንም ቃላት ባብራራው ልረካ አልቻልኩም። ከጉዳዩ አንገብጋቢነትና በቀላሉ የመተግበር እድል አኳያ የሚያስከትለውን አደጋ እያወቅሁ የተወሳሰበውን የገዥዎች ሴራ የዘር ፍጅት ሰለባ ለሆነው ወገኔ በአግባቡ ማስረዳት ስለምፈልግ ነው።
የግል ገጠመኝ
ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ ስለ አማራ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ፣ የአማራ መፈናቀል፣ የዘር ማጽዳት እና የፋኖ ትግል 67 ጽሁፎችን እና 2 መጽሐፎችን አበርክቻለሁ። በፋኖ ምንነት እና ታሪክ ሳይንሳዊ ምርምር በማድረግ በአካዳሚክ የጥናት መጽሔት ላይ ያሳተምኩም የመጀመሪያው ሰው ነኝ። ከዚያ በፊት በፋኖነት ዙርያ የጥናት ስራውን በምርምር ጆርናሎች ያሳተመ ማንም አልነበረም። ጽሑፉን ካሳተምኩ በኋላ፡ ፋኖ ምን ማለት እንደሆነ ለማስረዳት የውጭ እና የሀገር ውስጥ ሚዲያዎች ቃለ መጠይቅ አድርገውኛል። ከምርምር ህትመቱ በተጨማሪ በበርካታ ትንታኔያዊ መጣጥፎች እና በመጽሐፍቱም ውስጥ የፋኖን ማዕከላዊ ፅንሰ-ሀሳቦች በግልፅ አስቀምጫለሁ። ከመሰረታውያኑ ጽንሰ-ሀሳቦች አንዱ የትግሉ ትኩረት ነው። ከታሪክ እንደምንረዳው በተለምዶ የፋኖ ትግል ትኩረት የሚያደርገው በኢትዮጵያ ላይ የሚሰነዘረውን ጥቃት ለመከላከል ነበር። በዚህ ረገድ አሁን የሚንቀሳቀሰው የፋኖ ኃይልም የነባር ህዝብ ማንነትና የእሴት ውርስ በመሆኑ ኢትዮጵያን የመታደግ አደራ አለበት። ሁለተኛው አንኳር ጉዳይ አሁን ያለው የፋኖ እንቅስቃሴ የአማራን ህዝብ ህልውና የማስቀጠል ተጋድሎ መሆኑ ነው። እነዚህ ጽንሰሀሳቦች የሚተነተኑበት አድማስ የተለያየ ይሁን እንጅ ግንኙነታቸው የሚጣረስ አይደለም። ይልቁንም ተመሳሳይ ናቸው። የፋኖ ሚና አሁን የአማራን ህዝብ መታደግ ቢሆንም በቀጣይ የሀገርን ግዛት አንድነት ማስጠበቅና ሁነኛ ስርአተ-መንግስት እስከመፍጠር እንደሆነ መገንዘብ ይገባል።
በቅርቡ ባቀረብኩት አንድ ፅሑፍ ላይ ፋኖ የተነሳው በመጀመሪያ ደረጃ የአብይ አህመድ አገዛዝ ጦርነት የከፈተበትን የአማራ ህዝብ ህልውና ለማስጠበቅ መሆኑን ካብራራሁ በኋላ አጠቃላይ ግቡ ግን ኢትዮጵያን ያማከለ ስር-ነቀል ለውጥ ለማምጣት እንደሆነ ጽፌ ነበር። በዘወትር የፋኖ አቋም መግለጫዎች ቁልጭ አድርገው እንደሚገልጹት፡ ሁሉንም የኢትዮጵያ ብዝሀ – ብሄረሰብ እና ማንነት በኢትዮጵያዊነት ስር ያላቸውን እኩልነት አምኖ የሚቀበል ነው። የማንነት፥ ባህልና ቋንቋ ብዝሀዊነቱን መቀበል ብቻ ሳይሆን የሁሉም ጭቁን እና ሰለባ የተደረገ ህዝብ የአደጋ ጊዜ ወታደራዊ አደረጃጀት ተደርጎ ሊታሰብ ይችላል። ይህንን ህዝባዊ ቅርጽ ጠብቆም ነው፡ ከዘር-አጥፊው አገዛዝ ጋር ጦርነት እያደረገ ያለው። እስከማውቀው ድረስ የየትኛውም ብሔር የበላይነት ያለባት ሀገር ለመገንባት አልያም ተገንጣይ አጀንዳ የለውም። በመሆኑም የፋኖው ትግል በአውራጃ ተወስኖ የሚቀር ግብ የለውም።
በዚህ ነባራዊ ሁኔታ ላይ የፋኖን ትግል ወደአልተገባ ክፍፍል እና በቃላት ስንጠቃ ወደተመሰረተ እሰጥ አገባ የወሰዱት ኃይሎች መነሳታቸው ግልጽ ነበር። ክርክራቸው እየተካረረ ሂዶ ለአንድ አላማ የተነሳውን ፋኖ እርስ በእርሱ ሊገዳደል ወደሚችልበት ቅራኔ ሲወስዱት እየተመለከትኩ ዝም ማለት አልችልም። በክፍለ-ሀገራት የተደራጁ የፋኖ እዞችን ወደ አንድ ሰራዊትና ወጥ-የሆነ መዋቅር ያለው የእዝ ሰንሰለት ለመፍጠር ቀን እና ሌት እየመከርን ባለንበት ወቅት አንዱን የሌላው ጠላት አድርገው የሚሰብኩ አካላት ከባድ ተጽዕኖ አሳረፉ። ትግሉን ከመከፋፈል አልፎ መበተን የሚችሉበት ስጋትም ተፈጠረ። ይህንን አደጋ መከላከል የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥቶ መከላከልና የፋኖን አንድነት ማጠናከር ይገባል ብየ ስለማምን የመከፋፈል አጀንዳ ያላቸውን ኃይሎች ማግለል ወይም ማስወገድ እንደሚያስፈልግ አሳስቤያለሁ። በወቅቱ ይህን ማሳሰቢያ የሰጠሁት የማንንም እዝ መሪ ወይም ቡድን ጠቅሸ አይደለም። እኔ ትግሉ ሊመራበት የሚችለውን መርህ ነው የመከርኩኝ። አሁንም ቢሆን አላፍርበትም። የእማምንበት አቋሜ ነው።
ፋኖን ለመከፋፈል የግል ፍላጎት እና አጀንዳ ይዘው የሚገቡ አካላት፥ በመጡበት ቅጽበት ሀይ መባል አለባቸው። ምናልባት ገንዘብ መርዳት የሚችሉ ስለሆነ እነሱን ከትግሉ መግፋት የፋይናንስ አቅሙን ሊያዳክም ይችላል። ቢሆንም ግን የትግሉ ሂደትም ሆነ ግብ በገንዘብ የሚሸጥ አይደለም። እናም በጠቀስኩት ጽሁፍ ለማስተላለፍ የሞከርኩት መልእክት ይህንን ቢሆንም እነሱ በሚፈልጉት መንገድ ተርጉመው እኔን ለማጥቃት ዘመቻ ከፍተውበት ሰንብተዋል። ሁሉንም እዞች ወደ አንድነት ለማምጣት በሚደረገው ሂደት በቡድኖች መካከል ግጭት እንዳይፈጠር እዞቹ ውህደት ካደረጉ በኋላ ግባቸው በጋራ የሚያስቀምጡት መሪ እሳቤያቸው ይሆናል፤ ይህንን አስቀድመው በመረዳት ቀድሞ እንደ እዝ የነበራቸውን በአውራጃ የተወሰነ ንኡስ አደረጃጀትና ግብ መተው አለባቸው ( get rid of it) ያልኩትን፡ “አጠቃላይ ሰራዊታቸው ይደምሰስ” እንዳልኩ ተደርጎ ተከሰስኩበት። የአተረጓጎም ስህተት ወይም የቋንቋ ችግር እንዳልሆነ በሚገባ ተረድቸዋለሁ። በቋንቋ ወይም ቃላት አተረጓጎም ላይ አሻሚ ሁኖ የተፈጠረ ስህተት መስሎኝ በአስቸኳይ ይቅርታ ጠይቄም ነበር። ጽሑፉም ከታተመበት ጆርናል ላይ እንዲነሳ አስደርጌዋለሁ። ይህንን ያደረግሁት በእኔ ስህተት ምክንያት ህዝቤን ያልተገባ ስሜት እንዲኖረው አድርጌያለሁ በሚል ድንጋጤ ነበር። ከቀናት በኋላ ነገሩን ሳጤነው ግን ሌላ ጉዳይ ሁኖ ነው ያገኘሁት። እንደ ተናካሽ ውሻ እያደቡ ጥቃት የሚፈጽሙ ክፉ ሰዎች አሉ።
እነዚህ ክፉ ሰዎች የሚሰሩትን ስራ በሚገባ የሚያውቁ፤ ስልጠናም የወሰዱ፤ ደመወዝ የሚከፈላቸውና አገዛዙ ጥቃት እንዲሚፈጸምባቸው የሚፈላጋቸውን ግለሰቦች ዝርዝር የሰጣቸው ናቸው። በወሰዱት ስልጠና መሰረት ሁኔታዎችን ተጠባብቀው ብዙሀኑ ህዝብ ሊነዳላቸው በሚችለው ክስተት ሰበብ አድርገው ዘመቻቸውን ይከፍታሉ። እኔን የሚያሳዝነኝ በቀላሉ መነዳት የሚችል ህብረተሰብ እየተፈጠረ መሆኑ ነው። የመረጃውን ትክክለኛነት ለማጣራት ምንም ጥረት ሳያደርጉ ፍረጃውንና ውግዘቱን የሚያሰራጩ ቁጥራቸው እጅግ ብዙ ነው። በጽሑፌ ካብራራሁት አጠቃላይ ጭብጥ ፍጹም ተቃራኒ በሆነ ሀሳብ ስወገዝ ‘ለምን?’ የሚል ብዙም አለመኖሩ ያስገርማል። በእርግጥ ብዙሀኑ ያወገዘኝ ጽሑፉን ሳያነብ እንደሆነ አልጠራጠርም፤ ይልቁንም ያነበቡት ሰዎች ቀመር አዘጋጅተው የፈጠሩት መንጋነት ነው። በእርግጠኝነት ካወገዙኝ ሰዎች ውስጥ ጽሑፉን ያነበቡት ሴረኞቹ ካድሬዎች ብቻ ናቸው፤ ሌላው እነሱን የተከተለ ነው። እያንዳንዱ ሰው አንብቦ ቢያወግዘኝ ምንኛ ደስ ባለኝና ጊዜ መድቤ በተከራከርኩት። ነገሩ ግን እንደዛ አይደለም።
በቅርቡ ያነበብኩት አንድ መጣጥፍ መንጋነትን ከድንቁርና ጋር አያይዞ ያብራራል። ሰዎች ከእውነት ይልቅ ለብዙሀኑ አቋም ተገዥ የሚሆኑበትን መስተጋብር ያስረዳል። እውነታው ምንም ይሁን ምን ለብዙሀኑ ተገዥ መሆን ወይም በቡድኑ ሀሳብ መስማማት እውነትን ለማወቅ ከሚደረግ ጥረትና መስዋእትነት ሽሽት ነው ይላል። በመሰረታዊነት ስንፍና ነው።
Group conformity stands in marked contrast to the “wisdom of crowds” effect, whereby aggregating the opinions of large numbers of people gives answers or predictions more accurate than those of any individual. This happens only when members of a crowd make their judgements independently of each other, and it is most effective when a crowd is diverse. In cohesive groups, on the other hand, where members share an identity, the urge for unity overrides all.
የመንጋ ብሂል የእያንዳንዱን ግለሰብ እውቀትና አተያይ አካታች መሆን ሲችልና ስብስቡም ብዝሀዊ-ስብጥር ሲኖረው ከቡድኑ መንጋው ውስጥ ካለ አንድ ሰው አቅም የበለጠ ምልኡ የሚሆነው መንጋው ሊሆን ይችላል። ለዚህ አይነት ቡድን ተከታይ/ተገዥ መሆን፡ ከአንድ ብርቱ ሁለት መዳኒቱ እንዲሉ፡ የብዙሀኑ ድምር አቅም ይበልጣልና፡ ብልሀት ተደርጎ ይወሰዳል። የመንጋው አባላት እውነታን በየግላቸው የሚመረምሩበትና የሚያመዛዝኑበት አጋጣሚ ሳይኖር ግን ቀድሞ የተፈረደን አቋም ለማንጸባረቅ የመንጋው ተከታይ መሆን እጅግ አደገኛ ነው። አሁን የአማራን የህልውና ትግል የሚረብሸው አንዱ ችግር ይህ ነው። እያንዳንዱ ሰው ለመረጃ ማጣራትና ምርመራ ትጋቱ አይኑረው እንጅ ያየውንና የሰማውን ሁሉ መረጃ ማሰራጨት የሚችልበት እኩል እድል አለው። ማህበራዊ ሚዲያው ሁሉንም ሰው ጋዜጠኛ አድርጎታል። የሀሰት መረጃዎችና የጠላት ፕሮፓጋንዳም በራሳችን ሰዎች አዛማችነት በቅጽበት ለዓለም በሙሉ እየተዳረሰ ነው። በህዝባችን መካከል ይህ ተጋላጭነት ስላለ፡ አገዛዙ ግልጽ የማጭበርበርና ማታለል ስትራቴጅ ቀርጾ ተጠቅሞበታል። በሀሰት መረጃ፥ በተጣመመ አተረጓጎም፥ በውሸት፥ በክህደት ተመስርቶ ነው አገዛዙ ግልጽ የዜና ማእበል የሚፈጥረው። ይህ የዜና ማእበል አፍሶ የሚወስደው ደግሞ አስቀድሞ የተለዩ የወገን ክፍሎች አሉ፤ ዜናውን ተቀባብለው ሳይመረምሩ ላልሰማው ለማሰማት የሚጣደፉ። የዚህ ግርግር መጨረሻ የህልውና ትግሉ ላይ አንዳች አሉታዊ ተጽዕኖ መፍጠር ነው።
በፋኖዎች መካከል አላስፈላጊ መጠራጠርን ይፈጥራል፤ በደጋፊያቸው መካከልም መከፋፈልን ያመጣል፤ ትግሉን ወደ እርስ በእርስ ያወርደዋል። የአገዛዙ አጀንዳ ተቀባይ መሆንና የተሳሳተ መረጃን ማሰራጨት በወገናችን ህይወት ወይም ሞት ላይ ፍርድ ከመስጠት ጋር እኩል ድርጊት ነው። ስለዚህ ሁላችንም በስርጭት ላይ ያሉ የውሸት መረጃዎችን እና የውሸት ቪዲዮዎችን እንዲሁም የሚያራምዱትን አክቲቪቶች መቃወም እና መሞገት አለብን። የሀሰተኛ መረጃን ስርጭት መከላከል፡ ለእውነት እና እውቀት ስርጭት እድል ይከፍታል። ይህም በመረጃና ሳይንሳዊ እውቀት እና ክህሎት የተገነባ ማህበረሰብ ለመፍጠር ይጠቅማል።
ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከማብቃቱ አንድ ወር በፊት ናዚዎች የገደሉት ታዋቂው ጀርመናዊ ፈላስፋ ዲትሪሽ ቦንሆፈር በአንድ ወቅት ድንቁርና (stupidity) እና ክፋትን (malice) በአስደናቂ ንጽጽር አቅርቧቸዋል። “ድንቁርና ከክፋት የበለጠ አደገኛ ጠላት ነው” ይላል። አንድ ሰው ክፋትን መቃወም ይችላል፤ ካስፈለገም በኃይል መከላከል ይችላል። ክፋት ሁል ጊዜ በራሱ ተሸካሚ ውስጥ የሚኖር ጀርም ወይም በሽታ ስለሆነ ክፉውን ሰው (ተሸካሚውን) ነው የሚጎዳው። ድንቁርና ግን ከባድ ነው፤ እራስህን እንጅ ጠላትህን ከድንቁርና መከላከል አትችልም ይላል። ድንቁርና መንጋ ሰርቶ ሲዘምትብህ ደግሞ ችግሩ ምን ያህል የከፋ እንደሆነ ለመገመትም ይከብዳል፡ እያለ አሁን የደረሰብኝን ሰለባነት ቁጭ ብሎ የታዘበ እስኪመስለኝ ድረስ የወቅቱን ሁኔታ ይገልጸዋል። በኢትዮጵያ እየሆነ ያለውም ይኸው ነው፤ በፋኖ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ያለው። “Is the Amhara diaspora an obstacle or a help to Amhara’s survival struggle in Ethiopia? – የአማራ ዲያስፖራ በኢትዮጵያ ውስጥ ላለው የአማራ የህልውና ትግል እንቅፋት ነው ወይስ አጋዥ?” በሚል ርዕስ በቅርቡ ባወጣው ጽሁፍ አንድ ጸሃፊ ክስተቱን በትክክል ገልጾታል። ‘በእርግጥም የአማራን የዲያስፖራ ፖለቲካ የሚቆጣጠረው በራስ ወዳድነት ወይም ብዙም ያልተማሩ አፈ ቀላጤዎች ሲሆን እራሳቸውን እንደ ዋና የፖለቲካ ተዋናይ አድርገው የሾሙ፤ ምንም ዓይነት የሙያው እውቀት ሳይኖራቸው በጉልበት ተንታኞች የሆኑ፡ ማህበራዊ ሚዲያውን እና መገናኛ አውታረ-መረቦችን በመቆጣጥር ነው። ከማህበራዊ ሚዲያ በተጨማሪ ዋና ዋና መረጃ ማሰራጫዎችም ጭምር በእነዚህ ሰዎች ቁጥጥር ስር መውደቃቸው ትግሉን ለመጉዳት ወይም ለመጥለፍ እድል እንደሰጣቸውም ይገልጻል።
‘Indeed, Amhara diaspora politics is dominated by selfish or less educated orators who nominated themselves as chief political analysts by force, regardless of expertise. Social media and even mainstream outlets dominated and misused by these people to harm or hijack the struggle’.
በፋኖ ትግል ውስጥ ያሉ ፈተናዎች እና እድሎች
ቀደም ሲል እንደተገለፀው ማህበራዊ ሚዲያው ከቁጥጥር ውጭ እየሆነ ነው። በጽንሰ-ሐሳብ ደረጃ የማህበራዊ ሚዲያ መድረኮች የራሳቸው የሆነ ማህበራዊ እሴት እንዲፈጥሩ ነበር የሚጠበቀው። ለምሳሌ፡ ፌስቡክ በተልእኮ እና ዓላማ መግለጫው “ሰዎችን ማስተሳሰርና የመጋራት አቅምን በመጨመር ዓለምን የበለጠ ክፍት እና ቅርብ ማድረግ ነው” በማለት ያብራራል። ማህበራዊ መስተጋብር ለሰው ልጅ መሰረታዊ ነው። የእሳቤ ዓለሞቻችንን የምንፈጥርበት መንገድ ነው። የመገናኛ ብዙሃን የወደፊት እጣ ፈንታችንን በመቅረጽ ረገድ ወሳኝ ሚና አላቸው። በተቻለ መጠን በአግባቡ ብንጠቀማቸው፡ ማህበራዊ ሚዲያዎች የተሻለ ዓለም እንድንገነባ ይረዱናል። እንደግለሰብም የተሻልን ሰዎች እንድንሆን ይረዱናል። ነገር ግን ማህበራዊ ሚዲያዎች ቀዳሚ ግባቸው ገንዘብ እና ትርፍ ሲሆን ፍትሃዊ ማህበረሰቦችን ማፍራት አይችሉም።
በፋኖ ትግል ላይ የማህበራዊ ሚዲያ ሚናን ስንመለከት በርካታ አወንታዊ ጎኖች እንዳሉ ባይካድም፤ በአብዛኛው ግን እንቅስቃሴውን ለማዳከም እና በፋኖ መሪዎች እና ታጋዮች መካከል አለመተማመንን ለመፍጠር በንቃት እና በተጠናከረ መልኩ ጥቅም ላይ ውሏል። የቲክ ቶክ ተዋናዮች እና የፌስቡክ “አክቲቪስቶች” የውሸት ትረካዎችን በመፍጠር እና የፋኖ መሪዎችን እና ጀብደኛ ተዋጊዎችን በማጥላላት፥ በማንጓጠጥ እና በማራከስ ግንባር ቀደም ናቸው። እነዚህ አካላት በሚገርም ደረጃ ከመደበኛ ብዙሀን መገናኛዎች በላይ ተደራሽ ሲሆኑ ትልቅ ተመልካችም አላቸው። የተሳሳተ መረጃ የሚመነጨው እና የሚሰራጨው በዋነኛነት በእነዚህ አካላት ነው። በተመሳሳይ መንገድ ዩቲዩብ ተጠቃሚዎች ከጦር ሜዳ መረጃ ለማግኘት በየደቂቃው ግብግብ ላይ ናቸው። ያገኙትን ሁሉ መረጃ ከሁሉም ቀድሞ ሪፖርት ለማድረግ ይዋከባሉ። የፋኖ መሪዎችን ጭምር በተደጋጋሚ፡ የጸጥታ ጉዳዮችን ባላገናዘበ መልኩ ህይወታቸውን አደጋ ላይ በሚጥል ሁኔታም ጭምር፡ ቃለ መጠይቅ ይደረግላቸዋል። የፋኖ ታጋዮችና መሪዎቻቸው በቂ የሳይበር ደህንነት ጥበቃ በሌላቸው ሁኔታ እራሳቸውን ለአደጋ በሚያጋልጥ አውድ ቃለመጠይቅ እንዲያደርጉ ከመገደዳቸው በባሰ ደረጃ ተጋድሎውን ከፍተኛ ጉዳት የጋረጠበት ደግሞ ሆን ተብሎ የሚቀናበር የሀሰት መረጃ ነው።
የሀሰት መረጃዎች ሁለት አይነት ሊሆኑ ይችላሉ። አንደኛው የሀሰት መረጃ አይነት (misinformation) ሰዎች ለጉዳት አስበው ሳይሆን ትክክለኛነቱን ሳያረጋግጡ መረጃውን ከነስህተቱ ሲያሰራጩት ሲሆን የመረጃው ስህተት የቀን፥ የቦታ፥ የስም ወይም የይዘት ሊሆን ይችላል። የዚህ አይነት መረጃ የሚሰራጨው ኢላማ የተደረገን አካል ሆን ብሎ ለማታለል አልያም ለማሳሳት አይደለም። ሁለተኛው የሀሰት መረጃ አይነት (Disinformation)፡ ሆን ተብሎ በእቅድና በአላማ ትኩረት የተደረገን አድማጭ ወይም ተመልካች ለማሳሳት ነው። ይህ ፕሮፓጋንዳ፣ ማጭበርበር፣ ወይም የህዝብ አስተያየትን ለመቆጣጠር ወይም እውነትን ለማድበስበስ የተነደፉ ተንኮል አዘል ይዘቶችን ሊያካትት ይችላል። የሀሰት መረጃውም የሚዘጋጀው በረቀቀ ቴክኖሎጂና በተደራጁ ላብራቶሪዎች ውስጥ ነው። ለምሳሌ፦ አንድን የትግል መሪ ህዝብ እንዲጠላው ሲፈለግ በተለያየ ወቅት፥ ለተለያየ ጉዳይ የተናገራቸውን ቃላት እየቆራረጡ አሰባስበው፡ አንድን ወቅታዊ ጉዳይ የገለጸበት የአቋም መግለጫ አስመስለው ያቀናብሩታል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በመጠቀም የሚፈልጉትን ሰው አስመስሎ በድምጽ እንዲናገር በማድረግ ቀድተው ማሰራጨት ሁሉ ችለዋል። ብዙሀኑ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ የነዚህን ስሁት መረጃዎች ረቂቅ አዘገጃጀት ላያውቅ ይችላል። መረጃዎቹን ትክክለኛ መስለውት በማጋራት ሴረኞች ላቀዱት አላማ ተባባሪ ይሆናል።
ምንም እንኳን የተሳሳቱ መረጃዎች፣ የሀሰት መረጃዎች እና የውሸት ዜናዎች አዲስ ክስተቶች ባይሆኑም፣ እንደ ብሬክዚት እና እ.ኤ.አ. ከ2016 የዩኤስ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫዎች ከመሳሰሉት የፖለቲካ ክስተቶች በኋላ በከፍተኛ ደረጃ አድማስ ተሻጋሪ ተጽእኖ መፍጠር ችለዋል። በኢትዮጵያ ሁኔታ እነዚህ ክስተቶች አስከፊ እየሆኑ የሰው ህይወት እያስከፈሉ በወንድማማችና እህቶች መካከል ደም አፋሳሽ ጦርነት እየፈጠሩ ነው።
በተለይ በአማራ የህልውና ተጋድሎ ላይ ድርሻ አለን የሚሉ የፖለቲካና ወታደራዊ መዋቅር ላይ ራሳቸውን የሾሙ ምንም ንቃትም ሆነ ብቃት ወይም ተሰጥኦ እና ችሎታ የሌላቸው ሰዎች የስሁት መረጃዎች ቀጥተኛ ተጠቃሚዎች ሁነዋል። የእነሱን ነርቭ የሚነካ የሀሰት መረጃ እያቀናበረ አገዛዙ ይለቃል፤ ያንን እየተቀበሉ ሲያጓሩ ይውላሉ። የእነሱን ጩኸት ተከትሎ እርር ትክን ሲል የሚውለውን ወገን ስልኩ ይቁጠረው። የትግሉ መሪ ነን እያሉ ማህበራዊ ሚዲያው ላይ የተጣዱት ሰዎች ዋና ስራቸው የሀሰት መረጃውን ከአገዛዙ እየተቀበሉ ህዝቡን በስሜት ማሳበድ ሁኗል። እነዚህ ናቸው በየኢንተርኔቱ፡ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ‘ሊቃውንት፣ ጉሩስ እና ኒንጃዎች’ የሆኑት። ምን ይደረግ እንግዲህ? የባለሙያ ምስክር ወረቀት የሚሰጥ የለ! የኢትዮጵያን ፖለቲካ ውስብስብነት የተረዳን አብዛኞቻችን ደግሞ ወይ ዓይናፋር ሁነናል ወይም የእነሱን ጫና መቋቋም አስፈርቶናል። የፈጠርንላቸውን ክፍተት ተጠቅመው ነው ሙሉ በሙሉ መድረኩን የያዙት። የሚያሳዝነው ደግሞ የሚያርማቸው አካል አለመኖሩ ነው። እንደገለጽኩት አብዛኛው ሰው በእነዚህ ሰዎች ድፍረት እና ብልግና ይሳቀቃል። እነሱም በሚሊዮን የሚቆጠር ተከታይ ስላላቸው የተከታያቸውን ብዛት የመረጃቸው ትክክለኛነት ማረጋገጫ አድርገው ነው የሚያስቡት። ከእነሱ በላይ ተከታይ የሌለው ሰው ስለስህተታቸው ነግሮ ሊያስተካክላቸው አይችልም።
እዮብ ጥላሁን እ.ኤ.አ በ2024 ባሳተመው ጽሑፍ በትክክል እንዳስቀመጠው ልሂቃኑ ቡድን የትግሉን ምህዋር ቀርጾ የህልውና ተጋድሎውን የሚመራ ስትራቴጂካዊ አቅጣጫ ማሳየት ይጠበቅበታል። እኔም በአንክሮ ስከታተለው ትግሉ በመርህ እየተመራ መሆኑን በቅርበት የሚከታተሉና አዝማሚያ ግምገማዎችን በየወቅቱ ለህዝብ የሚያቀርቡ ህዝቡ የሚያንጸባርቃቸው አተያዮች ከህልውና ትግሉ መሰረታዊ አረዳድ እንዳይወጣ የጽንሰ-ሀሳብ ቅርጽ የሚያስይዙና የሚያስጠብቁ ባለሙያዎች – “expert police” ያስፈልጋሉ። እንደ አለመታደል ሆኖ በህልውናው ትግል ውስጥ የምሁራን ሚና እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። በዚህ የመኖር ያለመኖር ተጋድሎ ወቅት ለወገኑ ድምጽ መሆን ሲገባው ዝምታን የመረጠ ምሁር ደግሞ ህሊናው ይዳኘው! መማር መመራመርና ማወቅ ከምር ወገንን ለማገልገል ከሆነ ከዚህ ወቅት የበለጠ ለወገን የምንደርስበት ወሳኝ ጊዜ የለም። ኢንተርኔቱ በአስመሳዮችና የውሸት ባለሙያዎች የተወረረ ስለሆነ ስለ ጦርነቱ ተአማኒ አስተያየቶችን ለመግለጽ ደፋር መሆን አለብን።
የአማራ ተጋድሎ ለምን እነዚህን ኃይሎች (አክቲቪስት ተብየዎች) እንደሳባቸው በአንድ ወቅት ልጽፍ ነበር። ሳያቸው፡ በጣም ብዙ ናቸው። ቢያንስ ከ20 እስከ 30 ታዋቂ የሆኑትን መዘርዘር እችላለሁ። ባህሪያቸውን ሳጠና በመጀመሪያ ምልከታየ የታዘብኩት ብዙዎቹ ያልተረጋጉ፣ መተዳደሪያ ስራ የሌላቸው እና ምናልባትም የአእምሮ ጉዳት ታሪክ ያላቸው ናቸው። በሚያሳዝን ሁኔታ እነዚህ ባህሪያት በማህበራዊ ሚዲያው ቀርበው የሚናገሩበትን ድፍረት እንዲያገኙ አድርጓቸዋል። የሞራል አጥር የሌላቸው፥ ይሉኝታንና ጨዋነትን የረሱ ለሚያደርጉትና ለሚናገሩት ሁሉ ጠያቂ የሌላቸው እና ኃላፊነትም የማይወስዱ ናቸው። ይህንን የነውር መንገድ ተከትሎ ማህበረሰቡ ስርአትአልበኛና አረመኔ ከመሆኑ በፊት ወደ ትክክለኛው መንገድ እንዲገባ ማስተካከል፡ የምሁራን ግዴታ ነው።
እንደ እዮብ ጥላሁን (2024 ጁላይ 31) ዘገባ፡ አንዳንድ ዲያስፖራዎች ሆን ብለው ወይም ባለማወቅ ጥላቻን እና ከፋፋይ ሃሳቦችን (አስጸያፊ ነገር) በአማራ መካከል ያሰራጫሉ። ማስረጃ የሌለውንም ልቅቃሚ እንቶፈንቶ ሁሉ እንደ ትንተና ያቀርቡታል። አማራን ወደ አንድነት ከማሰባሰብ ይልቅ ብዙዎቹ በጎጥና መንደር ደረጃ ችክ ብለዋል። እነዚህን አይነቶቹ የአማራ ዲያስፖራዎች በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የአገዛዙ መሳሪያዎች ናቸው። መሬት ላይ ያሉ የህልውና ታጋዮች ከዲያስፖራዎች የሚመጡ ያልተዛባ አስተያየቶችን እና ጥቆማዎችን በሀቀኛ ማስረጃ ላይ የተመሰረተ ከሆነ ይቀበሏቸዋል። ነገር ግን ተገቢ ያልሆነና ፍትሃዊ ያልሆነ ትችት፣ የህልውና ትግሉን የመጥለፍ አዝማሚያ እና ታጋዮችን እጅ አስጠምዝዞ ለግል ጥቅም ማስፈጸሚያ ለማድረግ የሚደረገው አላስፈላጊ ጣልቃገብነት ፍፁም ተቀባይነት የሌለውና ሊቆም የሚገባው ነው። ዳያስፖራው ወሳኝ ሚና ሳይሆን የድጋፍ ሚና ብቻ ነው መጫወት ያለበት።
በመጨረሻም፣ ዩኔስኮ እንዳስጠነቀቀው፣ ማህበራዊ ሚዲያ ለባህላዊ እና ታማኝ ዜናዎች ‘ህልውና ስጋት’ ይፈጥራል። በኢትዮጵያ ደረጃ ደግሞ በአማራ ህዝብ ላይ የህልውና አደጋውን የበለጠ አባብሶታል። የማህበራዊ ሚዲያ መድረኮች ስለ አማራ ህዝብ እና ፋኖ ታጋዮች የሚሰራጩ የውሸት ወይም አሳሳች መረጃዎችን ለማስቆም፡ ያለሰለሰ የመረጃ ትክክለኛነት ማጣራት ሂደት (fact verification process) እንዲኖራቸው ማሳሰብ እፈልጋለሁ። ብዙዎቹ እንደ ፌስቡክ እና ትዊተር ያሉ የማህበራዊ ሚዲያ መድረኮች ተጨባጭ ያልሆኑ ወሬዎችን፣ ውሸቶችን እና ዛቻዎችን በማሰራጨት በህልውናው ትግሉ ላይ ዘላቂ ጠባሳ እያኖሩ ነው።
“The truth is still the truth, even if no one believes it. A lie is still a lie, even if everyone believes it”. (David Stevens) – ሽህ መስካሪ ሀሰትን እውነት አያደርገውም፤ እውነት ትመነምናለች እንጅ አትበጠስም!
“Never underestimate the power of stupid people in large groups”. (George Carlin)
1 How George Orwell Predicted the Challenge of Writing Today | The New Yorker
2 Fano: A Living Saviour Of The Amhara People And The Ethiopian Spirit – Analysis – Eurasia Review.
https://www.eurasiareview.com/04042024-fano-a-mass-outrage-for-amhara-existence-justice-and-ethiopian-unity-oped/
3 https://www.bbc.com/future/article/20160113-are-your-opinions-really-your-own
4 Bonhoeffer’s Theory of Stupidity Explains The World Perfectly | by Peter Burns | Lessons from History | Medium
5 https://borkena.com/2024/07/31/is-the-amhara-diaspora-an-obstacle-or-a-help-to-amharas-survival-struggle-in-
ethiopia/#google_vignette
6 Baym, N. K. (2015). Social media and the struggle for society. Social Media+ Society, 1(1), 2056305115580477.7
7 Misinformation and disinformation (apa.org)
ፋኖ #ውባንተ አባተ የጦር ጠበብ ለአማራህ አርቆ አሳቢ ቅን ታማኝ ታጋይ ነበር።
ስለዚህ ፋኖ ውባን አባተ በማዋከብ እና በኢትዮ 360 ሚዲያ አፋቸውን ሲከፍቱ የነበሩ ግለሰቦች ለፋትህ አደባባይ መቅረብ አለባቸው። pic.twitter.com/iKqTkvTQ2C— ሳተናው (@WOTATUAMARA) August 17, 2024
ይሄው ነው ‼️
???????????? pic.twitter.com/qKsidnNrLK— Tordit- ቶ ???????? (@Fano_Eagle) August 18, 2024