ደምሳሳ በሆነ የሰላማዊ ትግል ስብከት ፈፅሞ የትም አንደርስም!

April 15, 2024

ጠገናው ጎሹ

ከዘመን ጠገቡና እጅግ አስከፊ ከሆነው ፖለቲካ ወለድ መከራና ውርደት አዙሪት ሰብረን መውጣት ካለብን  ሳናውቅ ያወቅን እየመሰለን ፣ ስለ ሰላም በማነብነብና በመዘመር ብቻ ከገዛ ራሳችን ግዙፍና መሪር ሃቅ የምናመልጥ እየመሰለን  ሰላምን ስለሰበክንና ስለተመኘን ብቻ ሰላማዊ ህይወትን የምናገኝ እየመሰለን (unrealistic belief of pacifism) ፣ “ቸር ተመኝ ቸር እንድታገኝ” ለሚለው  ብሂል የተሳሳተና ጎደሎ ትርጉም እየሰጠን ፣ ተግባር አልባ እግዚኦታን (ሃይማኖታዊ እምነትን) እንደ የሰላም ዋስትና እየቆጠርን  ልክ የሌለው ፍርሃትን እንደ ትዕግሥትና የሞራል ልዕልና እየተረክን    መከራና ውርደት የመለማመድን  አስከፊ ማንነት እንደ ሰላም ፈላጊነት ማንነት በመቁጠር ራሳችንን እየሸነገልን  የየራሳችንን ድርሻ ሳንወጣ ህልውና ፣ነፃነት ፣ፍትህ ፣ ሰላምና እኩልነት የሚረጋገጥባት ኢትዮጵያ እውን ትሆን ዘንድ እጅግ ታላቅና መሪር ተጋድሎ በሚያካሂዱ የቁርጥ ጊዜና ሁኔታ አርበኞች/ፋኖዎች/ጀግኖች ተጋድሎ ነፃ ለመውጣት ዳር ቆመን እየጠበቅን ፣ እና ከሁሉም በላይ ደግሞ ህሊናዎቻቸውና እጆቻቸው በዘመናት የንፁሃን ደምና የቁም ሰቆቃ ከበሰበሱና ከከረፉ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ገዥ ቡድኖች ሰላምና መረጋጋት ይወለዳል በሚል እጅግ የወረደና አዋራጅ አስተሳሰብ ውስጥ እየጓጎጥን  ለዘመናት የመጣንበትን እጅግ አስከፊና አሳፋሪ አስተሳሰብና አካሄድ ከምር በሆነና ገንቢነት ባለው ፀፀት በቃን ማለትን ግድ ይለናል ።

አንድ ዓመቱን ሊደፍን ጥቂት ጊዜ የቀረው በአማራ ፋኖ እና የማያጠያይቀውን መሠረታዊ ምክንያቱንና ዓላማውን (absolutely justifiable cause and objective) በሚጋሩ እና ከየተኛውም የአገሪቱ ክፍልና የየትኛው ብሔርሰብ/ነገድ አባላት በሆኑ የአገር ልጆች ሁሉ በሚሳተፉበት የነፃነትና የፍትህ ተጋድሎ የሴራ፣ የሸፍጥ፣ የብልግና፣ የዝርፊያ፣ የመከራ ዶፍ አምራችና አከፋፋይ የሆነው መንበረ ሥልጣን (ቤተ መንግሥት) በሚገኝበት አዲስ አበባ  ከሰሞኑ የተካሄደው እጅግ ድንቅ የሆነ ታክቲካዊ የአርበኝነት እርምጃ የሚነግረን ሥር የሰደደን የፖለቲካ ካንሰር እውነተኛ ሰላምንና እርቅን በማያዋልድ አኳኋንና ብሩህ የሆነ ነገን እውን ለማድረግ በሚያስችል  ሁለገብ ትግል እንጅ ለዘመናት ተሞክሮ ደጋግሞ በወደቀ (ባልሠራ) የሰላም ስብከት (unrealistic pacifism) ያለመሆኑን ግዙፍና መሪር እውነት ነው።  ይህንን ሃቅ እንኳን ለመካድ ለማጣጣል መሞከር እንኳንስ ለነፃነትና ፍትህ ፈላጊ ወገን ለእኩያን ገዥ ቡድኖችና ግብረበላዎቻቸውም ፈፅሞ አይበጅም!   

 

ለዘመናት የመጣንበትን የእኩያን የጎሳ ደምና አጥንት ስሌት ፖለቲካ ነጋዴዎች ሥርዓተ ፖለቲካ እና በተለይ ደግሞ ከስድስት ዓመታት ወዲህ ግልፅና ግልፅ በሆነ ሁኔታ በዘር /በነገድ ማንነት ላይ ያካሄዱትንና አሁንም የቀጠሉትን የዘር ማፅዳትና ማጥፋት (ethnic cleansing and genocide) እጅግ አስከፊ ዘመቻ ደምሳሳና እጅግ አሳሳች በሆነ የሰላምና የእርቅ ይውረድ ትርክት/ንድፈ ሃሳብ/መዝሙር/ቅኔ/ ስብከት እንኳንስ ለማስወገድ ለማስታገስም አይቻልም ።

ስለሆነም የነፃነት፣ የፍትህ፣ የእኩልነት፣ የሰላምና የእድገት ባለቤት የምትሆን ኢትዮጵያን በእውን የምንፈልግ ከሆነ ማድረግ ያለብን ፍፁም ፀረ ሰላምና ፀረ የንፁሃን ህይወት መሆኑ በዘመን ርዝማኔም ሆነ በአስከፊነት በማያወላዳ ሁኔታ የታወቀውንና ከስድስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ በተረኞች  ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ የቀጠለውን የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ሥርዓት ለማስወገድና ለሁሉም የሚበጅ ሥርዓት ለማዋለድ የሚደረገው የፋኖዎች ተጋድሎ ዓላማውን ፣ዒላማውንና ግቡን እንዳይሰት ሁለንተናዊ ፣ገንቢ፣ ንቁ ፣ እና  ዘላቂ ድጋፍ/ተሳትፎ ማድረግን የግድ ይላል ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በዕውቀቱ ቡዳው በላን!

እኩያን ገዥ ቡድኖችና ግብረ በላዎቻቸው ምናልባትም ለራሳቸው ሲሉ ሰላምና እርቅን የህዝብን ተጋድሎና ዳኝነት በሚያከብርና የሽግግር ጊዜ አገራዊ ምክክርንና ፍትህን ከምር በሚወስድ ፀፀት ወደ ድርድር ጠረጴዛ የሚቀርቡ ከሆነ እሰየው ነው። ይህን የማድረግ የፖለቲካ ተፈጥሮ፣ ባህሪና ተሞክሮ አላቸው ወይየሚለው ጥያቄ ግን በእጅጉ ከባድ ነው። ለዚህም ነው ደምሳሳና እጅግ አጠቃላይ የሆነው የሰላም አስፈላጊነት ስብከትና ዲስኩር  ከምር መፈተሽ አለበት ብሎ መከራከር ትክክል የሚሆነው።

ህሊናዎቻቸውና እጆቻቸው በንፁሃን ድምና የቁም ሰቆቃ የበሰበሱና የከረፉ ገዥ ቡድኖችና ግብረ በላዎቻቸው በሚያስቀምጧቸው (በሚጠይቋቸው) ቅድመ ሁኔታዎች እና በሚቆጣጠሩት የፖለቲካ አውድ ሥር መሠረታዊ ለውጥ ይቅርና ትርጉም ያለው የእፎይታ አየር ይነፍሳል (ይፈጠራል) ብሎ እንኳንስ ለማመን ለማሰብም የሚያስችል ሁኔታ የለም፤ አይኖርምም። ለዚህ ነው መፍትሄው “ሰላማዊ ትግል ብቻ ነው” የሚሉ ወገኖች ክርክር (ትንታኔ) የገዛ ራሳችንን ዘመን ጠገብ፣ ግዙፍና መሪር ሃቅ (እውነት) ለማየትና ለማሳየት ያልቻለና የማይችል ከመሆን አልፎ በእጅጉ አደናጋሪና አሳሳች የሚሆነው።

ስለ ሰላምና ስለ መረጋጋት ምንነት፣ ለምንነትና እንዴትነት ደምሳሳና አጠቃላይ (highly ambiguous and generalized) የሆነ ትርጉምና ትንታኔ እየሰጠን ሥልጣነ መንበር ላይ እየተፈራረቁ በሚቆጣጠሯቸው የመንግሥትነት መዋቅሮች ማለትም ህግ አውጭ (ፓርላማ) ፣ ህግ ተርጓሚና ህግ አስፈፃሚ ተብየዎች አማካኝነት ሰላምን ራሱን  ሲፈልጉ እያጋደሙ እና ሲያሻቸው ደግሞ እየዘቀዘቁ በጨካኝ ሰይፋቸው በሚያርዱና በሚያሳርዱ ገዥ ቡድኖች ሥር የመከራና የውርደት ዶፍ ሰለባዎች ከሆን ግማሽ ምዕተ ዓመት (17+(27+6) =50) አስቆጥረናል።

በዋናነት በተማሪዎች ንቅናቄ የተጀመረውንና የታጀበውን የ1960ዎቹ/70ዎቹ የፖለቲካ ሥርዓት ለውጥ አስተሳሰብና አካሄድ በተገቢው (በሃላፊነት ስሜት) ተረድቶ ለማስተናገድ ፈቃደኛና ዝግጁ የሆነ አገዛዝ ባለመኖሩ እና በዘመኑ ከነበሩት ተፃራሪ የፖለቲካ ካምፖች (ካፒታሊዝምና ሶሻሊዝም) ውጭ ለለውጥ የሚበጁ የአገር ውስጥ ህሊናዊና ተጨባጭ ኩነቶችን ግምት ውስጥ ያስገባ አካል ወይም የህብረተሰብ ክፍል ባለመኖሩ ምክንያት ባለጠመንጃ ከሆነው የህብረተሰብ አካል በተውጣጡ ጨካኝ  ወገኖች እና ወታደሩ ወደ ካምፑ ተመልሶ ህዝባዊ መንግሥት ይቋቋም በሚሉ “ሌሎች የሶሻሊስት ሃይሎች” መካከል በተፈጠረ ልዩነት ምክንያት በእውቀት ፈላጊነቱ፣ በፅዕኑ አቋሙ፣ በግልፅነቱ፣ በአገር ወዳድነቱና በክህሎቱ አገርን አገረ ስልጣኔና አገረ እድገት ለማድረግ ይቻለው የነበረ ትውልድ ፍፃሜው የአስከፊው ታሪካችን አካል ሆኗል። ያ ሁሉ በሚሆንበት ወቅትና ሁኔታ ውስጥ ሆነንም ስለ አምባገነንነትና ስለ ሰላም እጦት ስንደሰኩርና ስንተነትን ምሳሌዎቻቻችን ከሌላ አገርና የታሪክ ኩነት እንጅ ከእኛ የሚቀዱ አልነበሩም። እውነተኛውን የሰላም ምንነት፣ ለምንነትና እንዴትነት ይህንን ያህል ነው ያጎሳቆልነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  “እግዚአብሔር የቀባው” ከቀሲስ አስተርአየ ጽጌ

በአንዲት አገር ልጅነትና ዜግነት ጥላ ሥር በፖለቲካ ሥልጣን ባለቤትነት ጥያቄ ልዩነት ምክንያት ተያይዞ የመውደቅ ሰለባ ከሆነው ከዚያ ትውልድ ተሞክሮ በመማር የተበላሸውን በማረምና ገንቢነት ያለውን ደግሞ በአግባቡ በመጠቀም የራሱን ገንቢ የታሪክ ድርሻ  ለመወጣት  ባልቻለ ትውልድ ላይ በግንቦት 1983 ወታደራዊውን ጁንታ አሸንፈው  መንበሩን የተቆጣጠሩት ቡድኖች ለዘመናት የዘለቀውን የአንድ አገር ልጅነትና ዜግነት ሰንሰለት የበጣጠሰውንና እየበጣጠሰ ያለውን የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ በአራተኛው ዓመት የሥልጣን ጊዜያቸው (1987) በህገ መንግሥት የደነገጉትን የጥላቻ፣ የመለያየት፣ የመናቆር፣ የመጠፋፋት ፖለቲካ በአዋጅ  አውጀው ሰላምን፣ መረጋጋትን ፣ ነፃነትን፣ ፍትህን ፣ እኩልነትንና ሥልጣኔን አዋለድንልህ ሲሉ ተሳለቁበት።  የዚያው ሥርዓት ውላጆችና ተረኞች ደግሞ እንኳንስ ለማመን ለማሰብም በሚከብድ ሁኔታ እያወረዱ ያሉትን የመከራና የውርደት ዶፍ “የተሃድሶ ለውጣችን ፍሬ ነውና ደስ ብሎህ ካልተቀበልክ” በሚል ይኸውና ይሳለቁበታል።

ይህ ሁሉ አደገኛ ሴራና ሸፍጥ በሰላምና በመረጋጋት ስም ሲተገበር ከምር ያሳስበናል ያሉ በጣም ጥቂት ወገኖች ፀረ ሰላም ፣ የአገር ደህንነትና የብሔር/ብሔርሰቦች መበት ጠላቶች እየተባሉ የግፍ ግድያና የቁም ስቃይ ሰለባዎች ሲሆኑ ሰላምና መረጋጋት ማለት ምን ማለት ነው? የብሔር/ብሔረሰቦች መብትና እውነተኛና ዘላቂ ሰላም ማለትስ ምን ማለት ነው? የዛሬው የሸፍጥና የሴራ “ሰላምና መረጋጋት” ለነገው እውነተኛና ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ መሠረት የሚሆነው በምን አይነት የፖለቲካ ሎጅክና ጥበብ ነው? ወዘተ ብለው የተሟገቱ ወገኖች ቁጥር እዚህ ግባ የሚባል አይመስለኝም።

ይህ እጅግ አስከፊ የፀረ አብሮነት፣ የፀረ ሰላም እና ትውልድ ገዳይና አስገዳይ አዋጅ ሲታወጅና ሥራ ላይ ሲውል ለምና እንዴት በሚል ቢያንስ ስጋታቸውን የገለፁት በጣም ጥቂቶች የመሆናቸው መሪር እውነት ብቻ አይደለም የሚያሳዝነው። ተቃዋሚ ተብየዎች ደግሞ ሥርዓቱን እንድ ሥርዓት ሳይሆን ለአድርባይነት ሰብእናቸው አልመች ያለውን ህወሃትን በመጥላት ብቻ እንደ ነበር  የእነ አብይ አህመድን ይሁንታና ፍርፋሪ ተቀብለው ከየነበሩበት የዓለም ክፍል (አካባቢ) ተጠራርገው በመግባት ሃፍረተ ቢስ አሻንጉሊትነታቸውን ያረጋገጡ የመሆናቸው መሪር እውነት ጭምር ነው። ለዚህ ደግሞ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋን ፣ ዶ/ር አረጋዊ በርሄን ፣ የኢህአፓ መሪዎች ነን ባይ አዛውንቶችን ፣ እና በአገር ውስጥ ከነበሩት ደግሞ ፕ/ር በየነ ጴጥሮስን እና ሌሎች ያልጠቀስኳቸውን ተመሳሳይ ወይም የባሰ የፖለቲካ ሰብዕና ያላቸውን ለዚህ ትውልድ መልካም ባልሆኑ ተምሳሌነት  መጥቀስ መሪር ሃቅ እንጅ አሉባልታ ሊሆን አይችልም። ዛሬም ከለየላቸው ፀረ ሰብአዊ መብትና ፀረ ሰላም ገዥ ቡድኖች ጋር እየተሻሹ  ስለ ሰብአዊ መብት ፣ ስለ ሰላምና ሰላማዊ ትግል የአዞ እንባ ሲያነቡ መታዘብ ቅን፣ ሃቀኛ፣ እውነተኛና ሚዛናዊ ህሊና ላለው የአገሬ ሰው በእጅጉ ያሳዝናል፤ ያማልም።

መከረኛው የአገሬ ህዝብ በሰላም ስም የሚቀልዱ የደም ነጋዴ ገዥ ቡድኖችን ያዋጣኛል በሚለውና በሚመርጠው የትግል ዘዴ ሁሉ ተጠቅሞ ከዘመናት ፖለቲካ ወለድ የመከራና የውርደት አዙሪት ሰብሮ እንዳይወጣ ደምሳሳና አጠቃላይ በሆነ የሰላም ስብከታቸው የሚያደናግሩትንና የሚያዘናጉትን ወገኖች በቃችሁ ማለት የነፃነት ተጋድሎው አንዱ ዘርፍ መሆን አለበት።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ግንቦት ሃያ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ምኑ ነው...........? (ገዛኸኝ አበበ ከኖርዌ ሌና)

በማወቅው ሆነ ባለማወቅ ወይም በጊዜያዊ ስግብግብነት ምክንያት የሰላም ትርጉምንና ወርቃማ እሴትነትን አደጋ ላይ መጣል ሊያጋጥም ይችላል። እንዲህ አይነቱን ሁኔታ ተረድተውና ከምር ተፀፅተው፣ ሃላፊነትንና ተጠያቂነትን ወስደው፣ ከምር ይቅርታ ጠይቀው እና ከዚሁ መሪር ተሞክሮ ተምረው እውነተኛ የጋራ መፍትሄ በጋራ አምጦ ለመውለድ የሚፈልጉ ገዥዎችን በሰላማዊ ትግል ወደ ድርድርና ምክክር ጠረጴዛ እንዲመጡ ማድረግ ስለሚቻል የትጥቅ ትግል አስፈላጊ ላይሆን ይችላል።

ከእንደ እኛ አይነቶቹ ፖለቲካን ጨቁኖና ረግጦ የመግዛት ሰይፍነት (መሳሪያነት) እና ልክ ለሌለውና ከደመ ነፍስ አራዊት ለባሰው ዘርፎ የመኖር (ኑሮ ከተባለ) ፍላጎታቸው ማርኪያነት ከሚጠቀሙ ገዥ ቡድኖችና ግብረ በላዎቻቸው ጋር ግን ከሁለገብ የነፃነትና የፍትህ ትግል ሌላ ማነጋገሪያና ማስወገጃ መንገድ የለም።

በመሠረተ ሃሳብ ደረጃ የሰላምና የመረጋጋት መኖር ወይም አለመኖር ጥያቄ ምን ያህል ግዙፍና ጥልቅ   እንደሆነ ቅን፣ ሚዛናዊና ትውልዳዊ የሆነ ሃላፊነት የሚሰማው የአገሬ ሰው በሚገባ ይረደዋል የሚል እምነት አለኝ።

ስለ እውነት በእውነት ከተነጋገርን የሰላምና የመረጋጋት መኖር ወይም አለመኖር የሚለካው በማህበረሰብ ጤናማና ወደ ፊት ተራማጅ በሆነ ሁለንተናዊ መስተጋብርና ውጤት እንጅ የገዳዮችና የአስገዳዮች የጦር መሳሪያ ጊዜና ሁኔታ እየጠበቀ አዚህና እዚያ በመፈንዳቱ  ወይም ፀጥ በማለቱ አይደለም።

እናም ግልፅና ግልፅ ሆኖ ዘመናት ያስቆጠረውንና የራሱ የሆኑ ምክንያቶች፣ ሂደቶችና ውጤቶች ያሉትን የገዛ ራሳችንን ግዙፍና መሪር እውነታ ደምሳሳና አጠቃላይ ከሆነ የሰላምና መረጋጋት ጋር እየደበላለቅን ከሰላማዊ ትግል ውጭ ነፃነትና ፍትህ ፈፅሞ እንደማያዋጣ የምንደርተውን የትንታኔ ድሪቶ ከምር ልናጤነው ይገባል።

ፖልቲካን የመጨቆኛና የዝርፊያ መሣሪያ ያደረግነው እኛው ራሳችን እንጅ ፖለቲካ በራሱ ጨቋኝና ዘራፊ በመሆኑ እንዳልሆነ ሁሉ ለህልውና፣ ለፍትህ፣ ለነፃነት ፣ ለእኩልነት እና ለህይወት ስኬታማነት የሚደረግ የትግል ዓላማና ግብም ሊበላሽ የሚችለው በእኛው ድክመትና ፅናት ማጣት እንጅ በራሱ የማያዋጣ ስለሆነ አይደለም።

ከዚህ አይነት ከተንሸዋረረና አስጠቂ ከሆነ የፖለቲካ አስተሳሰብና አካሄድ በመላቀቅ እልህ አስጨሽ ትግል ስናካሂድ ብቻ ነው ከህዝብ ፈቃድ የሚመነጭ፣ በህዝብ ተሳትፎ የሚታጀብና የሚጎለብት እና ለህዝብ ፍላጎትና ጥቅም የሚቆም ሥርዓተ ፖለቲካንና መልካም አስተዳደርን ማዋለድ የምንችለው።

የማያወላዳ ምክንያታዊነትንና ፍትሃዊነትን አጣምሮ የያዘው የፋኖ ተጋድሎም  ግቡን የሚመታው ከዚሁ ከገዛ ራሳችን ግዙፍና መሪር እውነታ አንፃር ለማየትና አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ፈቃደኞችና ዝግጁዎች ሆነን በመገኘት እንጅ ድምሳሳና እጅግ አጠቃላይ የሆነ የሰላምና የመረጋጋት ዲስኩር፣ ትንታኔ፣ ስብከት፣ መነባንብ፣  ተስፈኝነት፣ እና በአጠቃላይ የገሃዱን ዓለም እውነታ በማይገልፅ የፍፁም ሰላም አፍቃሪነት (absolute and unrealistic pacifism) አይደለምና ልብ ያለን ልብ እንበል።

 

3 Comments

  1. መቼውንም ቢሆን ላወቀበትና ለገባው አማርኛ የሚያወላዳ ቋንቋ ነው። በቅኔው፤ በሰምና ወርቁ፤ በተረቱ፤ በምሳሌውና በሌሎችም የአባባል ዘየዎች የልብን ለመናገር ይመቻል። ቋንቋው በጠላትነት ከተፈረጀ ወዲህ ግን ግራ የሚያጋቡ ጉራማይሌ ጉዳዪች በዚህም በዚያም ይታያሉ። ወይ ለይቶላቸው በእንግሊዘኛው አይገፉ እንዲያው ሆን ተብሎ ፊደላትን እያጎደሉና እያጣመሙ በመጻፍ ዛሬ ላይ አማርኛ በሃበሻዋ ምድር የመግባቢያ ቋንቋ ሳይሆን ጠላትን የመለያ ምልክት ተድርጎ ተወስዷል። አይ ጊዜ ጅብን ጅብ የተካበት ዘመን። ድሮ ድሮ ሰው ሰው ሲሸት ልጆች ሆነን በሃገሪቱ ልዪ ልዪ ቋንቋዎች የተዘፈኑ ዘፈኖችን እየዘፈን ቋንቋው የገባውም፤ ያልገባንም ልባችን እስኪወልቅ ስንጨፍር ትውስ ሲለኝና አሁን ያለንበት ሁኔታ ሳስብ አዝናለሁ። ጊዜው ትውስ አይለኝም ሁኔታው ግን እንዲህ ነበረ። ጸጋዬ መርጊያ አካም ናጉማ ዘፈን እየዘፈነ አንድ ቦታ ከጓደኞቼ ጋር በድንገት እንደርሳለን። አራት ነን። ሴትና ወንድ ጥማዶች። በዚያ ዘፈን ተቃቅፈን እየዘለልን አንዴ በኦሮሚኛ ሌላ ጊዜ በአማርኛ ስንጨፍር ትውስታው በአይኔ ላይ አሁንም ውል ይላል።
    ይህ ቆሻሻ የብሄር ፓለቲካ ምድሪቱን የአውሬዎች መናህሪያ ካደረጋት ወዲህ ግን ኡኡታና መከራ እንጂ ይህ ነው የሚባል ሰላምና ደስታ በምድሪቱ ላይ ሰፍኖ አያውቅም። ይህ አፍራሽን አፍራሽ እየተካው የተጓዝነው ጉዞ ስንቱን አፈር እንዳለበሰ በተአምር ተርፈን ዛሬ ላይ የምንተነፍስ በውል እናውቀዋለን። ዘርፎና ቀምቶ መኖር እንደ ተግባር በሚቆጠርባት የሃበሻ ምድር ዛሬ ላይ የምናያቸው የኦሮሞ ተረኞች ወያኔን መስለውና ከዚያም ከፍተው ሰውን በማሰቃየት ላይ ይገኛሉ። ግን ለዚህም ማብቂያ አለው። በዘመናችን ሳንጃ በአፈሙዝ በማለት እልፎችን ያስለቀሱ ጊዜ ተገልብጦ እነርሱም በናቋቸው እጅ በሰፈሩት መስፈሪያ ተትረፍርፎ ሲሰፈርላቸው አይተናል። ቂጥ ለቂጥ የተጣበቁት ሻቢያና ወያኔ ሳይታሰብ በባድሜ አሳበው ሲሸራከቱ ስንቱ ረገፈ፤ ያ አልበቃ ብሎ ዳግመኛ ወያኔና ብልጽግና በያዝ ለቀቅ ውጊያ ሲፋለሙ ያለቀው የድሃ አድግ ልጆችና ሰርቶ አዳሪ ገበሬዎች ናቸው። አሁን ደግሞ በወለጋ፤ በጎጃም፤ ጎንደር፤ ወሎና ሽዋ እንዲሁም በሌሎቹ የሃገሪቱ ክፍሎች የሚደረገው ግብግብ ደግሞ ህዝባችን ለከፋ መከራ እየዳረገው ይገኛል። በዚሁ ሳቢያ የሚነዙ ወሬዎች በሜዳ ላይ ካለው እውነታ በእጅጉ በመራቃቸው ህዝባችን እውነቱን ተረድቶ አንተም ተው አንቺም ተይ ለማለት በማይችልበት ሁኔታ ላይ ይገኛል። አንድ አንድን ደምስሶ ሰላም አገኛለሁ ማለት የፓለቲካ ውስልትና ነው። በዚህ ላይ የዓለምን የፓለቲካ ንፋስ ለተረዳ በዚህም በዚያም የቅርብና የሩቅ የሃገሪቱ ጠላቶች ላንድ ነዳጅ ለቀሪው እሳት እያቀበሉ ዝንተ ዓለም የዓለም ስንዴ ተመጽዋች እንድንሆን አጥብቀው ይሰራሉ። ስለሆነም ከአለንበት የፓለቲካ ማጥ ለመውጣት የአስተሳሰብ ለውጥ ያስፈልገናል። የብሄር ፓለቲካውን እንትፍ ማለት ቀዳሚው የሰው ተግባር ሊሆን ይገባል። ከዚህም ባሻገር ሰውን በሰውነቱና በተግባሩ እንጂ በዘር ምንዛሬ ማየቱ መቆም አለበት። ምድሪቱ የሁሉም ናት እንጂ የአፓርታይድ ክፍፍሉ ትርፍ የለሽ ነው። በጦር መሳሪያና በውጊያ የሚገኝ ሰላም ዘላቂነት አይኖረውም። የሃሳብ ልዕልና ግን የሰውን ልብ ያለዝባል፤ ያስተምራል፤ ይገራል። ይህ በለው በላት ያዘው ጥለፈው፤ ደመሰስናቸው የሚለው ለከት የለሽ ጡርንባ መቆም አለበት። ወንድምና እህቱን ገድሎ መፎከር ምን የሚሉት ጀግንነት ነው? አውቃለሁ አንዳንድ ፓለቲከኞች እንደ አሾፉ ኑሮው እንደ አሾፉ ሊሞቱ ይችላሉ። ግን የሰው ደም በእጃቸው ላይ ስላለ ሃብታቸው በዛም አነሰም ሰላም የሌላቸው ተቅበዝባዥ ፍጡሮች ናቸው። በዘመናት ከነደደው የፓለቲካ እሳት አምልጠው ለማሾፍም የበቁ በጣም ጥቂቶች ናቸው። ስለሆነም ለሰላም እንስራ። ዘፈናችን። ጽሆፎቻችን፤ አልፎ ተርፎም ተግባራችን ለሰላም ይቁም። እንዲሁ በፈጠራና በተለጠጠ ዜና ራስን እያሰከሩ መኖር ህመምተኛ ያደርጋል። እውነት የመሰለን ሁሉ ውሸት ለመሆኑ ቀን ጠብቆ ማየት ነው። ሌላው ሁሉ ሰውን ገልቱ የሚያደርግ ጉዳይ ነው። በዚህች ግጥም ልዝጋ።
    የሚቆመው በዝቶ በየአደባባዪ
    ፈላስፋው በርክቶ እኔ አውቃለሁ ባዪ
    በዚህ ሸንጎ መሃል ያለመጠን አፍራ
    እውነት ቤትዋ ገባችን አንገቷን አዙራ

  2. This is an interesting commentary and it disproves politicians like ato Lidetu Ayalew who preach their dishonest, irrelevant and discarded `peaceful struggle`. Ato Lidetu and co. preached peaceful struggle as an expression of their loyalty to the TPLF. They had been making their living in the TPLF system as what they described as `non-blind opposition and non-blind supporters. The TPLF granted them a chunk of its budget for the loyal opposition parties.

  3. ኦ ሰላም በስምሽ ስንት ግፍ ተሠራ?
    ስለሰላም ስናነሳ ሰላም እንዴት ደፈረሰ? በማንና ለምን ዓላማ?እንዴትስ ሊሰፍን ይችላል? የሚሉትን ጥያቄዎች ማንሳቱ ተገቢና ለዘላቂ ሰላም መዳረሻ መንገዶች ናቸው::የሰው ልጅ ቀርቶ እንስሳትም ሽ ቢሆኑ ሰላምን አይጠሉም::ከአውሬ ጋርም በአንድ በረት ውስጥ ተቃቅፈው አያድሩም::
    ወደ አገራችን የሰላም እጦት ምክንያቱን ስንመለከት በዋናነት በልዩልዩ ስም በስልጣን ላይ የመቀመጥ ፍላጎት ባላቸው አምባገነኖች የተፈጠረ መሆኑ አይካድም: የደርግ አምባገነን አገዛዝ ህዝቡን ሰላም ነስቶት ለ17 ዓመት መቀመጡ ከዛም እስከአሁን ድረስ ላለፉት 33ዓመታት የጎሳ ድሪቶ ፖለቲካን ተላብሶ ህዝብ ለህዝብ አጋጭቶና አጋሎ የስልጣን እድሜውን ለማርዘም የሚፈልግ ፀረ አንድነት ፀረ አገር የሆነ ቡድን በመኖሩ ሰላም ሊደፈርስ ችሏል::የጽሁፉም ሙሉ መልእክት ያንን የሚያሳይና የሚመሰክር ነው::
    በተለያዩ ጊዜያት የተከሰቱ ፀረ ሰላም ሃይሎች በህዝብ ትግል ይወገዳሉ እንጂ ከህዝብ ጋር ተስማምተው አይኖሩም:: ሊኖሩም አይችሉም::ሰላምን ለማስፈን ፀረ ሰላም የሆነው አካል በውድም በግድም መወገድ አለበት:: ለሰላም የሚደረግ ትግልና ተጋድሎ ከፀረ ሰላም ወንጀልና ጭፍጨፋ ጋር እኩል መታዬት የለበትም::
    ፀረ ሰላም ሃይል በሰላም ወዳዱ ብትር እንጂ በልመናና በመለማመጥ ከእኩይ ተግባሩ አይታቀብም:
    የናዚ ዘረኛ ስርአት በእርቅና ድርድር የተወገደ ሳይሆን በሰላም ወዳዱ ሃይል ድባቅ ተመቶ ነው::የአገራችንም ኽላቀር ጎሰኞች እንዲሁ በሃይል እንጂ በሽምግልናና ውይይት የሚወገዱ አይሆኑም:: የመጡት በሃይል የቆዩትም በሃይል ስለሆነ ሰላምን አያውቁም::ቢሆኑማ ኖሮ ከሰላሳ ዓመት በላይ ለሆነው የህዝብ ሰላማዊ ትግልና ጥያቄ ተገቢ ምላሽ ባገኘ ነበር::እንዲያማ ቢሆን ኖሮ ማን ደሙን በከንቱ ለማፍሰስና ህይወቱን ለመገበር ይነሳ ነበር?
    አሁን የግፍ ዋንጫው ሞልቶ ሲፈስ ትግስቱ ያለቀው የአማራው ህዝብ እራሱንና ኢትዮዽያ አገሩን ለማዳን ወሳኝ ትግል ውስጥ ሲገባ ሰላምጠሉ አገዛዝ በአንድ በኩል በጦር በሌላ በኩል በሰላም ሽፋን በሚነዛው ጫጫታ ለማወናበድ እዬሞከረ ይገኛል::ተባባራሪዎቹም በዬፊናቸው ሰላም ሰላም እያሉ ይጮሃሉ:: ለእነሱ ሰላም ማለት በዘረፋና በተረኛ ማንነታቸው የያዙት ሹመትና ንብረት ሳይጏደል መኖሩ ነው እንጂ የብዙሃኑ ጥቅምና መብት የሚከበርበት የአገር አንድነት የሚጠበቅበት ለሁሉም የሚመች ሰላማዊ ስርአት መስፈን አይደለም::
    ለዘለቄታዊ ሰላምና አንድነት የአማራ ፋኖ ትግል አስተዋፅኦ ቢኖረውም በቂ አይደለም ::ሁሉም ጎሰኝነትን የሚጠላና የሚቃወም አገር ወዳድ ከአማራ ፋኖ ጋር ተባብሮ መታገል ይኖርበታል:: ይህ የተረኝነትን ስጋት ከማሶገዱም በላይ ለውጡን ህዝባዊና የጋራ ያደርገዋል::በወታደራዊ ሃይል ብቻ ማሸነፍም በቂ ስላልሆነ የአገራችን የወደፊቱ ስርአትና የፖለቲካ አቅጣጫ መነደፍ ይኖርበታል:: የጎሰኞቹን ህገ ጥፋት መሻር ክልል የተባለውን የህዝብ እስርቤት መናድ የሁሉንም ማህበረሰብ አባል ተሳትፎ የሚያረጋግጥ የፖለቲካ ባህል እንዲጎለብት የሚረዳ የሽግግር መንግስት መመስረት ያስፈልጋል:: በአገርና በህዝብ ላይ ወንጀል የፈፀሙትም መጠዬቅ ይኖርባቸዋል:: ይህም ለዳግም ወንጀለኞች ላለመነሳት በር ይዘጋል መቀጣጫና ማስተማሪያም ይሆናል::
    ከጎሳ ፖለቲካ ለመውጣት ጎሰኞችን እናሶግድ!
    አገሬ አዲስ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share