ከሞረሽ ወገኔ ዐማራ ድርጅት የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ
የኦሮሞማው የብልጽግና መንግስት ከስሞኑ በአዲስ አበባ “መሐል ከተማ” በመባል የምትታወቀውን “ፒያሳና አካባቢዋን”፣ ታሪካዊ ገፅታ ያላቸውንና ለዘመናት የአንድነትና የሕብረት መገለጫ የሆኑቱን ሕንፃዎቿንና የንግድ ተቋማቶቿን እንደዚሁም የግለሰብ መኖሪያ ቤቶችን በማፍረስ ላይ ነው።
የኦሮሞማ ብልጽግና መንግስት የተላበሰውን ታሪክንና የአገር አንድነት ጠል ባህሪውን መግለጡ ዛሬ በአዲስ አበባ የታሪክ እምብርት በሆነችው “ፒያሳ” ላይ የሚያካሂደውና የሚፈጽመው ዘመቻ ዋነኛና ብቸኛ ማስረጃ ነው። “ፒያሳ” የተረኛ ዘርኞች ጡጫ ያረፈባት፣ የጥፋት ሰለባ እንድትሆን የተፈረደባት፣ ታሪኳንና ቅርሷን እንደያዘች በማን አለብን ባዮቹና የተስፋፊዎቹ የአሁኑ አፓርታይድ አገዛዝ እንድትፈርስ የተወሰነባት ዕውነተኛዋ የኢትዮጵያ ገጽታ ናት።
“ፒያሳ” ከታሪክ በለቤትነቷ ጀርባ ተወልደው ላደጉባት፣ ተመላልሰው ስራ ለሰሩባት፣ ሻይ ቡና ለጠጡባት፣ ቁጭ ብለው ያላቸውን ችግሮች ለፈቱባት ሰዎች ሁሉ በልባቸው ላይ ማሕተምን ያሳረፈች ብቻም ሳትሆን የፍቅር፣ የአንድነትና የጋራ ትስስር “ሚስጥረ ሀውልት” የቆመባት ቦታ ነች።
ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያዊያንን የታሪክ አሻራ ላለማየት፣ በቅናትና በጥላቻ ቀውስ ውስጥ ለተዘፈቁ፣ የአዲስ አበቤን ማንነት ለመቀየርና የስነ ሕዝቧን አስፋፈርና አውቃቀር ለመለውጥ “ፒያሳን” ማፍረስ የግባቸው መዳረሻ አድርገው መወሰናቸው የዚሁ ከንቱ የፖለቲካ ህልም አዘል ጉዞቸው መገለጫና ለውሸት ትርክታቸው ማስረጃ እንዳይገኝበት ታሪክን ለማጥፋት የቀየሱበት የሴራ መንገዳቸው ነው።
የዓለም አቀፍ ሰበዓዊ መብትን የጣሰ፣ የዜጎችን በሰላም የመኖር መብት የገፈፈ፣ ለፈራረሰውና በማን አለብኝነት ለወደመው ንብረታቸውና ዕድሜያቸውን ሙሉ ሰርተው ላፈሩት ሀብታቸው ምንም ዓይነት ማካካሻ ያላገኙበት በዘረኛ መንግስት የተፈጸመ ወንጀል ነው።
በቅርቡ በአዲስ አበባ የመንግስት ፖሊሶችና ግለስቦች መብታቸውን ለማስከበር ባደረጉት ያለመግባባት ግጭት ሳቢያ ንፁሀን የአማራ ተወላጆች ያለምንም ማስረጃ እንዲታፈኑና ወደ እስር እንዲወረወሩ ተደርጓል። ይህንንም የአፈና እንቅስቃሴውን መንግስት በማስፋት የሰላማዊ ዜጎችን መብት በመጣስ በየቤቱ በመግባት ከ2000 እስከ 3000 ሊደርሱ የሚችሉ የአማራ ተወላጅ የሆኑ ወጣቶችን በመድብደብ ወደ እስር እንዲጋዙ በማድረግ ወንጀል ፈጽሟል።
ስለሆነም “ሞረሽ ወገኔ ዐማራ ድርጅት” አገዛዙ የሚያደርጋቸውን እኩይና የጥፋት መንሰኤ የሆኑ ከላይ የተጠቀሱትን ጠቅላላ እንቅስቃሴዎችን በአስቸኳይ እንዲያቆም በማለት፦
1.የአዲስ አበባን የታሪክ ቅርስ መዲናነት ለመቀየር የሚሞከረውና ለማጥፋት የሚደረገው ዘመቻ በአስቸኳይ እንዲቆም፣
2.በማንነት ላይ ትኩረትን ያነገበና የፖለቲካን ፍጆታን ለማሳካት በዐማራውና ሌሎች ከገዢው መደብ ውጪ የሆኑ ዜጎች ላይ የሚደረገው የማፈናቀል፣ ንብረትን የማውደምና የስነ ልቦናን ጫና የመፍጠር እኩይ ተግባራቶች በፍጥነት እንዲቆሙ፣
3.በአዲስ አበባ ውስጥ ያለውን የስነ ሕዝብ አስፋፈርን (Demography) ለመቀየር ስልት ተነድፎለትና ዕቅድ ወጥቶለት የሚሰራው የፖለቲካ አጀንዳ እንዲቆም፣
4.በዜጎች ላይ የሚደርሰው የሰበዓዊ መብት ረገጣ፣ እስር፣ እንግልትና ግድያ በአስቸኳይ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲቆም ፣
ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት ሚያዚያ ፮፣ ፪ሺ ፲፮ ዓ.ም. (April 14, 2024) ቅጽ ፲፩ ቁጥር ፩
5.ዜጎች ያለአግባብ ለፈረሰው ቤታቸውና ለወደመው ሀብታቸው በአስቸኳይ ማካካሻ እንዲያገኙና የመኖሪያ ቤት እንዲሰጣቸው፣
6.አሁንም ይህንን በአዲሰ አበባ የተጀመረውን ኃላፊነት የጎደለውን መንግስታዊ የሽብር እንቅስቃሴ በዐማራ ክልል አስፋፍቶ ለመተግበር በዕቅድ ላይ ያለውን ስራችሁን ከወዲሁ እንድታቆሙ፣
7.ሰሞኑን በአዲስ አበባ ማንነት ላይ ባተኮረ የሚደረገው አፈሳና ያለምንም ማስረጃና ፍርድ በንፁሀን ዜጎች ላይ የሚፈጽሙት ኢሰባአዊ የሆኑ የወንጀል ስራዎች በአስቸኳይ እንዲቆሙ እንጠይቃለን። ፋኖ ናሁሰናይ አንዳርጌና ጓዶቹ ያነገቡትን የአማራ ህልውና መከበር ጥያቄ ሳይመልሱ የዜጎችን የሰባዊ መብትን በመርገጥና በማንነንት ላይ ያነጣጠሩ የጅምላ ግድያዎችና አፈናዎች ትግሉን የሚያቀጣጥል ነዳጅ ሆኖ የአገዛዙን የስልጣን ጊዜ እንዲሚሳጥረው ግልጽ ነው።
ሆኖም ግን “አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም” እንደሚባለው እኛ የጠየቅናቸውን ከላይ የተጠቀሱትን ይህ አገዛዝ ይፈጽማቸዋል ለማለት ሳይሆን በውስጡ የተሰገሰጉ ሆድ አደሮች ጥያቄዎችን አለማዳመጥ ያለውን መዘዝ አውቀዉ የበኩላቸውን አስተዋጻኦ ያደርጉና ከሕዝብ ጎን ይቆሙ ዘንድ ጥሪያችንንም ለማሰተላለፍ ጭምር ነው። ይህም ብቻ አይደለም ዜጎች የብልጽግናን አገዛዝ የጥፋት ሴራ ተረድተን፣ ትግላችንን አፋፍመን ነባር የጋራ አሻራችንን ያሳረፍንባትን የሁላችንም የሆነችውን አዲስ አበባ ወደ ነበረችበት ማማ እንድንመልስ ዘንድ ሞረሽ ወገኔ ዐማራ ድርጅት ጥሪውን ያቀርባል።
ዐማራ በክንዱ ማንነቱን ያስከበራል!!!
የሕልውናው ትግል በድል ይጠናቀቃል!!!
www.moreshwegenie.org
InfoAndPR@moreshwegenie.org