መጋቢት 6 ቀን 2016 ዓመተ ምህረት
ምስራቅ አፍሪካ ቀንድ ላይ የተሰየመችው ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ካሉ እድሜ ጠገብ ሃገራት መካከል ቀዳሚ ሃገር ናት። ይህቺ ሃገር በአፍሪካ ክፍለ ዓለም ውስጥ እንደ በረሃ አበባ ብቻዋን በቅላ ብቻዋን ነጻ ሃገር ሆና የኖረች ብርቅዬና የነጻነት ምልክት ናት። በተለይ በቅኝ ግዛት የማቀቁ የአፍሪካ ሃገራት በሥሥት የሚያዩዋት እናታቸው ናት።
ኢትዮጵያ በረጅም ጊዜ ታሪኳ ውስጥ ከውጭ የሚመጣባትን ጥቃት ለማለፍ አያሌ ውጣ ውረዶችን ብታልፍም፣ ውስጣዊ አለመረጋጋቶች ብዙ ዋጋ ቢያስከፍሏትም በየዘመኑ የተፈጠሩ ልጆቿ “ህብረታችን ይበልጣል በሚል ሃያል መረዳት ሁል ጊዜም አብረው ታግለው አኩሪ የነጻነት ታሪክ ጽፈዋል። በአድዋ ተራሮች ላይ በአባቶቻችን ደም የተጻፈው ታሪክ ህብረታችን! ኢትዮጵያችን! እኔ የወንድሜ ጠባቂ ነኝ የሚሉ ሃይለ ቃሎች ናቸው። ካራማራ ተራሮች ላይ የተጻፈው የዚህኛው ዘመን ታሪካችም እንደዚሁ ተመሳሳይ ሃይለ ቃል ያስተጋባል። ህብረታችን! ኢትዮጵያችን! እኔ የወንድሜ ጠባቂ ነኝ የሚለው የአድዋው መሪ ቃል ነው ካራማራ ላይም የተደገመው። ለዚህ ነው የካራማራው ድላችን ዳግማዊ አድዋ እየተባለ የሚጠራው።
ኢትዮጵያ የእድሜዋንና የስልጣኔ ፈርቀዳጅነቷል ያህል ለመራመድ እንዳትችል ያደረጋት ነገር፣ በአንድ በኩል ከውጪ የሚነሱ ጦሮችን ለመመከት ዘወትር ዘብ ቆማ የቆየች ሲሆን በሌላ በኩል የውስጥ አለመረጋጋቶች ሃገረ መንግስቱን እገጭ እጓ እንዲል እያደረጉት ስለቆዩ ነው።
ከሁሉም የሚከፋው ግን ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ልጆች በህብረት የጻፉት ታሪክ አያሌ ቢሆንም በቅርብ ጊዜ ታሪካችን አዲስ ህገ መንግስት ስንጽፍ አብሮነታችንንና ህብረታችንን አቃሎ ልዩነቶቻችንን የሚያደምቅ ሆነ። ያቺን ሃያል ሀገር እንደ አንድ የማትከፋፈል ሃያል አገር ሳይሆን እንደ ዛኔ ጋባ ቤት፣ አንዳችን ባኮረፍን ጊዜ አፍርሰናት የምንሄድባት ጊዚያዊ ቤት አድርገን ሰራን። “ህብረት ይሻላል” የሚለው የኢትዮጵያውያን ሃይለ ቃል ተገስሶ ልዩነት ይልቃል ወደሚል ማህበረ ፖለቲካ መውረዳችን በአራቱም አቅጣጫ ያለንን ኢትዮጵያውያንን ሁሉ አንገት ያስደፋ የታሪክ ጠባሳችን ነው።
ይህ ልዩነትን የሚያጎላው አስተምህሮ ተቀይሮ ልዩነትም አንድነትም እርስ በርስ ሳይፈራረሱ የሚኖሩበትን የፖለቲካ ምህዋር ማቆም የሚገባን ቢሆንም ዛሬ ድረስ ልዩነቶች እየሰፉ ኢትዮጵያዊ ህብረታችን እየተሸረሸረ እየተሸረሸረ እየተሸረሽረ መጥቷል።
ሃገችንን ለዚህ አደገኛ የህብረት መሰረት መናጋት የጣላት ዋና ችግር አንዱ ይህ ህገ መንግስት ላይ የተጻፈው ህብረታችንን ፈራሽ ያደረገው ክፉ ሃሳብ ሲሆን በሌላ በኩል መንግስት የሚጠቀመው የከፋፍለህ ግዛ የአገዛዝ ስልት ነው። በተለምዶ ከፋፍለህ ግዛ የሚለው ፍልስፍና ከመቼውም ጊዜ በላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ተግባራዊ ሆኗል። የወቅቱ ጠቃላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ ዋና የአገዛዝ ስልት ይሄ ነው። ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ህዝብ ለውጥ ፈልጎ ከፍተኛ ትግል ያደረገ ቢሆንም የቀድሞው የኢንሳ ድሬክተር የነበሩት አብይ አህመድ የኢትዮጵያውያንን ለውጥ በመጥለፍ ወደ ስልጣን በመጡ በወራት የመንግስትን መዋቅር የሚጠልፍ (state capture የሚያደርግ) የደህንነት መዋቅር ፈጥረው ስሙን ኮሬ ነጌኛ ብለው የኢትዮጵያውያንን የዴሞክራሲና የሽግግር ተስፋ አጨናግፈዋል። ይህ ብቻ ሳይሆን እኚህ ሰው ወደ ስልጣን ከመጡ ማግስት ጀምሮ ችግሮችን በብልሃት ከመፍታት ይልቅ በኮሬ ነጌኛ ኮሚቴው አማካኝነት በሴራና በመጠላልፍ ዘዴ ስልጣን ላይ ለመቆየት በመሞከራቸው ኢትዮጵያውያን እርስ በርስ ተዋግተው በትግራይ ጦርነት ወቅት አያሌ ዜጎች ረገፉ፣ የብዙ ወገኖቻችን ቤት ተዘጋ፣ ረሃብና መፈናቀልን አተረፍን። ህብረት ይበልጥብናል፣ እኔ የመንድሜ ጠባቂ ነኝ የሚሉ ሃይለ ቃሎች በአባቶቻችን ደም የተከተበባቸው የአድዋ ተራሮች ላይ እርስ በርስ ተዋግተን አንገት የሚያስደፋ ታሪክ አስጽፈውናል። የኮሬ ነጌኛው መሪ አብይ አህመድ የትግራዩ ጦርነት ጋብ ባለ በማግስቱ ከአማራ ህዝብ ጋር ሌላ ጦርነት ውስጥ ገብቶ ይታያል። የዚህን ህዝብ ጥያቄ ለመፍታት ፖለቲካዊ መፍትሄ እንደመፈለግ በጦር ሃይል አንበርክኬ እገዛዋለሁ በማለቱ ዛሬ የአማራ ህዝብ በከፍተኛ ሁኔታ ከአብይ አህመድ አገዛዝ ጋር መራራ ትግል ላይ ይገኛል።
ኮሬ ነጌኛ የተሰኘው ህቡዕ ኮሚቴ ዋና ማዕከሉን አድርጎ የነበረው የኦሮሞን ህዝብ በመሆኑ ዛሬ ኦሮምያ ውስጥ ቅጥ ያጣ አስተዳደር፣ ዝርፊያና እንግልት፣ እስራትና ግድያ ቁም ስቅሉን እያሳየው ይገኛል። የኦሮሞ ህዝብ የሚያነሳው የእኩልነትና የፍትህ ጥያቄ የጠለፉት ኮሬ ነጌኛዎች ይህ ህዝብ የሞተላትን ሃገሩን እያጠቁበት ይገኛሉ። ከሌላው ወገኑ ጋር እንዲጋጭና የስርዓቱ ዘበኛ እንዲሆን በኦሮምኛ ቋንቋ እየተናገሩ ሌት ከቀን ሊከፋፍሉት ይሞክራሉ።
የደቡቡ ወገናችንን ሁናቴ ስናይ አንዴ ጋሞን፣ አንዴ ወላይታን፣ አንዴ ሲዳማን ወዘተ. በየተራ የአብይ አህመድ መንግስት በኮሬ ነጌኛ አሰራሩ ቁም ስቅሉን እያሳየው ነው። ረሃብና መፈናቀል በዙር መከራውን እያሳየው ነው። አብይ አህመድ ስልጣን ላይ በመጣ በጥቂት ጊዚያት የጌዲኦ ወገኖቻችን ተፈናቅሎ መከራና ስቃይ ማየቱ አይዘነጋም። ጋምቤላ ውስጥ አኙዋክን ከኑየር ለማጋጨት የዚያን አካባቢ ህዝብ አንድነትና ሰላም በመንሳት የተባበረ የልማትና የሰላም ጥያቄ እንዳያነሳ ሁል ጊዜም ይጥራል። ይህ ክልል ከፍተኛ የተፈጥሮ ጸጋ ያለው ቢሆንም መንግስት ከልማት ይልቅ ግጭት ጠመቃ ላይ ተጥዶ በመኖሩ ዛሬ በዚህ ክልል ውስጥ ሰላም ወጥቶ መግባት፣ አምርቶ በምርት መደሰት የማይቻልበት ክልል ሆኗል። የሶማሌ ክልል ወገናችን በግጭትና በመገናቀል በረሃብ ይሰቃያል። በተለይ ባለፉት አምስት ዓመታት ግጭት፣ መፈናቀል፣ ረሃብ ያላገኘው የሃገራችን ክፍል ከቶ የትኛው ነው? የግጭትና የመፈናቀል መራራ ጽዋ ያልጠጣ ከቶ የትኛው ብሄር፣ ከቶ የትኛው ክልል ነው?
እውነት ነው ይህ ህዝብ በየፊናው ብዙ ዋጋ እየከፈለ ባለበት በዚህ ሰዓት እንደገና የስርዓት ለውጥ ለማምጣት ትግል ላይ ነው። ይሁን እንጂ ትግላችን በየብሄራችን የታጠረ በመሆኑ በአንድ በኩል የስርዓት ለውጥና የሽግግር ጊዜ ፈጥረን እፎይ ለማለት እንዳንችል፣ በጋራ ታግለን በፍጥነት የተሻለ ስርዓት ለመገንባት እንዳንችል አድርጎናል። በሌላ በኩል ይህ የተበጣጠሰ የትግል መስመራችን ድንገት የመንግስት መውደቅ ቢከሰት እንደገና በተባበር ሁኔታ አዲስ የሽግግር ስርዓት ለመፍጠር እንዳንችል የሚያደርግ ስጋትን ደቅኖብናል። በዚያም አለ በዚህ የኢትዮጵያውያን ትግል መከፋፈሉ የጠቀመው ስልጣን ላይ ላለው ኮሪ ነጌኛ ብቻ ነው። መከፋፈላችንና ትግላችን መበጣጠሱ የኮሬ ነጌኛ ኮሚቴ ህልም እስካሁን እንዲቆይ አድርጎብናል።
ኢትዮጵያውያን ጋሞዎች፣ አኙዋኮች፣ ኮንሶዎች፣ ኦሮሞዎች፣ ትግራዮች፣ አማሮች ወዘተ እንደ ከበረ እንቁ ይዘነው የነበረው አብሮነታችን፣ ህብረታችን እነሆ ዛሬ በብሄር ፖለቲካና በኮሬ ነጌኛ መዋቅር ምስጦች እየተበላና እየተሸረሸረ አገራችን አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ወድቃብናለች ። መንግስት ከፋፍለህ ግዛ የሚለውን ስልት ሲጠቀም ኢትዮጵያውያን ሊኖራቸው የሚገባው የትግል ስልት የመንግስትን ስልት የተቃረነ አደረጃጀት በመፍጠርና ተከፋፍሎ ለመገዛት አለመመቸት ነው። ህብረትን የበለጠ ማጥበቅ ነው የትግሉ መጀመሪያ። ይህ የትግል ስልት ነው ጌም ቸንጀር የትግል ስልት የምንለው። በብሄር እየከፋፈለ ሊገዛን ያሰበውን ስርዓት ለመታገል ከተለያዬ ብሄር የመጣን የኢትዮጵያ ልጆች በአንድነት በህብረት ቆመን ከተነሳን ያን ጊዜ አሸንፈን ተነሳን ማለት ነው። የፖለቲካ አሸናፊ ሆነን ተነሳን ማለት ነው።
እኛ ኢትዮጵያውያን ህብረታችን የተጎዳው በመንግስት ከፋፍለህ ግዛው ስልት ብቻ ሳይሆን ከፍ ሲል እንደተጠቆመው አንዱ ስለራሱ ብቻ ሳይሆን ስለሌላው የሚያኖር ህገ መንግስት ስለሌለን ነው። ሃገር የሚባለው ስብስብ ሲቋቋም ዋና መተሳሰሪያ መርሆ መሆን ያለበት እንደ ብሄር ለራስ ብቻ ሳይሆን ስለሌላው መኖር ትልቅ ዋጋ የሚሰጠውና የህብረታችን መልህቅ ሆኖ መቀረጽ አለበት። አንዱ ስለ ራሱ ብቻ ሳይሆን ስለሌላውም የሚያኖረው ስርዓት ያልገነባ ሃገር ህብረቱ እንደምን አይፈርስም? እንዲህ ዓይነት ደካማ መተሳሰሪያ መርሆ ከጫንቃው ላይ የተጫነበት ህዝብ የገዛ ህብረቱ ሁልጊዜም አንካሳ ይሆናል። የጋራ ተብሎ የተሰራለት ቤትም በአሸዋ ላይ የተሰራ የሰነፍ ሰው ቤትን የሚመስል ይሆናል። እንዲህ አይነት መተሳሰብ የጎደለው ህገ መንግስት የተጫነበት ህዝብ ጠንካራ የጋራ ተቋማትን ዘርግቶ ወደ ልማትና ወደ ሰላም እንደምን አድርጎ ወደፊት መራመድ ይችላል? ስለዚህ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ዛሬ ስለ ህብረታችን በጥብቅ የምናስብበት ወሳኝ የታሪክ መታጠፊያ ምዕራፍ ላይ ነን። መዘናጋትና መታለል በቅቶ የህብረታችንን ስጋቶች ለመቅረፍ የምንነቃበት ወሳኝ ወቅት ላይ ነን። የተጫነንን ነገር ሁሉ ፈንቅለን ተነስተን ህብረት! ህብረት! ህብረት! የምንልበት ጊዜ ላይ ነን። ለስርዓት ለውጥ የሚደረጉ ትግሎችን ሁሉ እርስ በእርስ ለማያያዝ ደፋ ቀና የምንልበት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ነን።
ዛሬ በአማራ ክልል አካባቢ የተነሳውን የፋኖ ትግል ሁላችን ልንደግፍና አንድ ላይ ሆነን ይህንን ትግል የጋራ አድርገን ልንቀርጸው ይገባል። አንዱ ወገናች ትግል ሲጀምር ህብረትን ማሳየት፣ አብሮነትን ማሳየት ይገባል እንጂ አንዱ የአንዱን ትግል አይጥለፈው። የኦሮሞው ትግልና የአማራው ትግል፣ የትግራዩ ትግልና የደቡቡ ትግል፣ የጋምቤላው ትግልና የሃረሬው ትግል ሁሉ መደጋገፍና አንድ ትልቅ ጥላ ወደ መፍጠር ማደግ አለበት። ኢትዮጵያዊ ጥላ ፈጥረን ትግሎችንን አሰባስበን ህብረታችንን አጠናክረን እነሆ ከወደቅንበት ልንነሳ ይገባል። ፋኖነት አኙዋክነት፣ ኑየርነት፣ አማራነት፣ ኦሮሞነት፣ ጋሞነት፣ ወላይታነት፣ ቡርጂነት፣ ትግራይነት፣ ወዘተ ነው። ሁላችን ኢትዮጵያውያን ህብረታችንን እንደገና ለማደስ የተበላሸውን ሽግግር እንደገና ቀና ለማድረግ ህብረታችንን እንጠብቅ። ህብረት ይሻላል (better together) የሚለው ስሜት በእኛ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ሃይለ ቃል ሆኖ ይግነን፣። መለያየትና እርስ በርስ ያለመናበብ የተሻለ ስርዓት እንዳንገነባ አድርጎናል። የዴሞክራሲ ትግላችንን እድሜውን አስረዝሞታል።የተለያዬና የተበጣጠሰ ትግል ውስጥ ገብተን አንድ አሸናፊ ሃይል ስልጣን ቢይዝም የረጋ ሃገረ መንግስት ሳንገነባ ቀርተን እንዲሁ በግጭት ውስጥ እንቆያለን።
ውድ ኢትዮጵያውያን ዛሬ ይህንን ደብዳቤ የምንጽፈው ኢትዮጵያውያን አንዳንዶቻችን የጋሞ ልጆች ነን፣ አንዳንዶቻችን የአኙዋክ ልጆች ነን፣ አንዳንዶቻችን የኑየር ልጆች ነን፣ አንዳንዶቻችን የትግራይ ልጆች ነን፣ አንዳንዶቻችን የኦሮሞ ልጆች ነን፣ አንዳንዶቻችን የሲዳማ ልጆች ነን፣ አንዳንዶቻችን የአማራ ልጆች ነን…. ሁላችንም ከአራቱም ማዕዘናት የመጣን የተለያዬ ቋንቋ ተናጋሪ ብሄር የመጣን የኢትዮጵያ ልጆች ነን። እኛ ከተለያየ ቋንቋ ተናጋሪ ማህበረሰብ የመጣን ኢትዮጵያውያን ዛሬ እነሆ ህብረት ይሻላል (better together) የሚለውን መሪ ቃል ይዘን የተበጣጠሰውን የኢትዮጵያውያንን ትግል ለማሰባሰብ ቆርጠን ተነስተናል። ከተለያዬ ብሄር የተገኘነው እኛ ኢትዮጵያውያን የአንድ እናት ልጆች ነን። ህብረታችንን ነው እናታችን የምንለው። ህብረታችን ሲጎዳ እናታችንን ጎዳን እንላለን። ስለዚህ እኛ የኢትዮጵያ ልጆች በአንድ በኩል የተበጣጠሰውን ትግል በማቀናጀት ለጋራው በጎነት (common good) ትልቅ ሃይል ሆኖ እንዲወጣ የምንጥረው ጥረት የሚቀጥል ሆኖ በሌላ በኩል ይህ በአብይ አህመድ የሚመራው ስርዓት ሲወገድ ሊመጣ የሚችለውን የመከፋፋል አደጋ ቀልብሶ ህብረትን ለመጠበቅ የሽግግር ፍኖቶች ላይ ለመስራት አበክረን እንሰራለን። ስለዚህ ህብረታችን ለሁለት ታላላቅ ግቦች ያስፈልጋል። አንደኛው ለተባበረ ትግል መሰባሰብ ሲሆን ሌላው ስርዓት ለመገንባት የኢትዮጵያን ትንሳኤና ሽግግር ለማሳለጥ የተሻለ ስርዓት ለመትከል ነው።
ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን! ዛሬ ይህንን የህብረት ሀይል ቃል መልዕክት የምናስተላልፈው ኢትዮጵያውያን በአራቱም ማዕዘናት ያላችሁ በተለይም ወጣቶች ህብረት ይሻላል፣ ህብረት ይልቃል (better together) የሚለውን ሃይለ ቃል ከፍ አድርጋችሁ እርስ በእርስ መተሳሰብን እንድታዳብሩ፣ ህብረትን ከፍ እንድታደርጉ ለማበረታታት ነው። በተለያዩ የትግል አውድማ ውስጥ ያላችሁ ወገኖቻችን ህብረት ይሻላል የሚለውን መሪ ቃል ከፍ አድርጋችሁ በመያዝ የትብብር ጥሪ እንድታደርጉ ነው። ምሁራን፣ ተማሪዎች፣ ገበሬዎች፣ ሁላችን ኢትዮጵያውያን ህብረትን ከፍ እናድርግ። በልቦናችን ውስጥ እንጻፈው። በቤታችን ግድግዳ ላይ፣ በጊቢያችን አጥር ላይ እንጻፈው። ህብረት ይሻላል! Better together! ወቅቱ ክፉ ጊዜ ነውና ሁላችን ተጠጋግተን እንቁም፣ እጅ ለእጅ ተያይዘን ህብረት፣ ህብረት፣ ህብረት እንበል።
Better together
Teko Hatanu !
እስፔተስ ሎኦ !
ዳቶ ቢር !
ህብረት ይጮኝኖ !
ብሐባር ይሐይሽ !
ህብረት ይሻላል !
መልዕክት ካለዎ bettertogetherethiopia@gmail.com ያግኙን