February 28, 2024
59 mins read

ኦርቶዶክስ ያበረከተቸው ሃገራዊ አስተዋዕጾ እና የደረሰባት ጥቃት፣

252 195958 whatsapp image 2023 01 28 atደረጀ ተፈራ  (በግል የቀረበ ዳሰሳ)

  1. መግቢያ፣

እንደሚታወቀው አውሮፓውያን በተለያዩ ዘመናት በእምነት ሰባኪነት፣ በሃገር አሳሽነት (Exploration)፣ በጎብኚነት፣ በዲፕሎማት   ማዕረግ እና በመሳሰሉት ምክንያቶች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ሃገራችንን በመሰለል ለቅኝ ገዥ መንግስቶቻቸው መረጃ ያስተላልፉ እንደነበርና ቅርሶችንም በመስረቅ፣ ግለሰቦችን በገንዘብ አባብሎ በመግዛት ወደ ሃገራቸው እንደሚያሻግሩ ይታወቃል። በእንግሊዝ፣ ጣሊያን፣ ፈረንሳይ እና በመሳሰሉት የአውሮፓ ሃገራት በሚገኙ ታዋቂ ሙዚየሞች የኢትዮጵያ ቅርሶች በብዛት መገኘታቸው ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው። ለምሳሌ የእንግሊዝ መንግስት በንጉሱ የታሰሩ ዜጎቻችንን ለማስለቀቅ በሚል ምክንያት አፄ ቴዎድሮስን ለመውጋት ወደ ኢትዮጵያ በመጡ ጊዜ አጼ ቴዎድሮስ እራሳቸውን በመሰዋት ጦርነቱ እንደተጠናቀቀ በናፕየር የሚመራው የእንግሊዝ ጦር በበርካታ ዝሆን እና አጋሰስ የተለያዩ የኦርቶዶክስ ቤ ክ ንዋየ ቅዱሳንን፣ ጣሊያኖች በአክሱም የቆመውን የድንጋይ ሃውልት ከስሩ በመቁረጥ ሃገራቸው ጭነው በመውሰድ በሮም አደባባይ አቁመውት እንደነበር ይታወቃል። በ17 ኛው መ/ክ/ዘመን ጀምስ ብሩስ የተባለ እንግሊዛዊ (የስኮትላንድ ተወላጅ) የአባይን ወንዝ መነሻ ምንጭን ፉለጋ በሚል ሰበብ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ታቦተ ፅዮንን ለማግኘት ብዙ ጥሮ ባይሳካለትም በመጨረሻ ግን የመፅሀፈ ሄኖክ የግዕዝ ኮፒዎችን ሰርቆ ሊወጣ ችሏል። ከእሱም በመቀጠል ወደ ሃገራችን የመጡ ሌሎች አውሮፓውያን በብራና የተጻፉ ቅዱሳን መጸሐፍትን፣ ታቦትን ጨምሮ በርካታ ነዋየ ቅዱሳትን በመዝረፍ ወደ ሃገራቸው አግዘዋል። ከዛም በላይ ደግሞ የጊዜ ቦምብ ተክለው ሁሉ የሚሄዱ አሉ። ለምሳሌ የክርስቲያኑን መንግስት ለማገዝ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የነበሩ ፖርቹጋሎች ግራኝ አህመድ ከተሸነፈ በኋላ የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስን በሮማ ካቶሊክ ለመቀየር በመሞከራቸው የተነሳ በርካታ ህዝብ በርስ በርስ ጦርነት እንዳለቀ በታሪክ ተመዝግቦ ይገኛል። ኦርቶዶክስን ለመከፋፈል ቅባት የሚባለውን አስተምህሮ ከፖርቹጋል የካቶሊክ ቄሶች የመጣ እንደሆነ ይታወቃል። ሌላው ደግሞ የአሰብ ወደብን ጁሴፔ ሳፔቶ (Giuseppe Sapeto) የተባሉ የጣሊያን የካቶሊክ መነኩሴ ከአካባቢው የጎሳ መሪ መሬት ከገዙ በኋላ ሩባቲኖ ለተባለ የጣሊያን የንግድ መርከብ ኩባንያ እንደሸጡና የጣሊያን መንግስት ከኩባንያው በመግዛት 1882 አሰብን ቅኝ ግዛቱ አደረገ።

በሸዋው ንጉስ ሳህለስላሴ ዘመን ህዝቡን የእጅ ሞያ ጥበብን ለማስተማር በሚል ወደ ሸዋ የመጣ ዮሐን ክራፕፍ (Johann Ludwig Krapf) የተባለ የአውሮፓ የሚሲዮናዊ ማህበር አባል የነበረ አንድ ጀርመናዊ ነበር። ዮሐን ክራፕፍ እ.ኤ.አ ከ1837 እስከ 1842 ኢትዮጵያ ውስጥ በቆየባቸው ጊዜያት በሸዋና አካባቢው በየገጠሩ በመዟዟር፣ እንዲሁም ከሸዋ ርቀው በሚገኙ እንደ እናርያ፣ ከፋ፣ ጎንደር እና በመሳሰሉት የሃገራችን ክፍሎች በንግድና በኑሮ ወደ ሸዋ የሚመጡ ሰዎችን በማናገር ያገኘውን መረጃ ወደ ሃገሩ ያስተላልፍ ነበር። ይህ ሚሲዮናዊ ኦርቶዶክስ በመልአክት የምታመልክ ናት በማለት ያጥላላ የነበረ ሲሆን በወቅቱ ስለ ኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ለሃገሩ ለጀርመን መንግስት ከላከው ሚስጥራዊ መረጃዎችና የቅኝ ግዛት ምክረ ሃሳብ (Recommendation) ውስጥ አንዱ የምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰቦችን በፕሮቴስታንት ክርስትና ሃይማኖት በማጥመቅ በቀላሉ የጀርመንን ቅኝ ግዛትን ማስፋፋት እንደሚቻል የሚገልጽ ነበር። ከጽሁፉ መረዳት እንደሚቻለው ከሩዋንዳና ብሩንዲ ጀምሮ እስከ መሃል ኢትዮጵያ ድረስ የምስራቅ አፍሪካ የስምጥ ሸለቆ ሃይቅ ሃገራት ህዝቦችን መጀመሪያ በእምነት ማቀራረብ፣ በመቀጠልም በሃይል አንድ ላይ በማድረግ ትልቅ የጀርመን ቅኝ ግዛትን መፍጠር ይቻላል የሚል አስተሳሰብ ነው። እንግዲህ ሰውየው ዋና ዓላማ ቅኝ ግዛት ማስፋፋት እንጂ ህዝቡን የእጅ ሞያ ጥበብ ማስተማር ወይም ክርስትናን መስበክ አልነበረም። አውሮፓ በተለይም በጀርመን (በፕሩሲያ) ክርስትና ከመሰበኩ በፊት ክርስትናን የተቀበለችን ሃገር ንቆ እስከ መሃል ኢትዮጵያ ድረስ ፕሮቴስታንትን ለማስፋፋት ያሰበው በአባታችን በአቡነ ተ/ሃይማኖት እና በሌሎች ቅዱሳን ተጋድሎ የተገነባውን (የተስፋፋውን) የኦርቶዶክስ ክርስትና በማጥፋት በፕሮቴስታንት ለመተካት እንደሆነ መረዳት ይቻላል። ክእዛ ጊዜ ጀምሮ ሚሲዮናውያኑ ኦርቶዶክስ ክርስቶስን አትሰብክም በማለት ስሟን የማጠልሸት ክፉ ስራቸው ይኸው እስከ ዛሬ ድረስ በቅብብሎሽ ደርሶ የእነሱ ልጆች የሆኑ ፓስተር (ሰባኪ) ነን ባዮች በየአደባባዩ ኦርቶዶክስን መስደብና መወንጀል፣ ስርዓተ አምልኮቷ ላይ ማላገጥ የተለመደ ክስተት ሆኗል። ለምሳሌ ነዋሪነቱ ጀርማን የሆነ በንቲ ቴሶ የተባለ ፓስተር (Reverend) ከመጽሐፍ  ቅዱስ ላይ የኢትዮጵያ ስም በኩሽ መቀየር አለበት የሚል ዘመቻ ከፍቶ እንደነበር ይታወሳል። ዮናታን እና እዩ ጩፋ የሚባሉ ተበልፃጊዎች መንግስና ህግ አለበት በሚባልበት ሃገር እንደ ተቋም ህጋዊ የሆነችውን ኦርቶዶክስን፣ እንደ ህዝብ ምዕመኗን በማናህሎኝነት በየመድረኩ መስደባቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው።

  1. የአድዋድልእና የፋሽስት ቂም፣

እንደሚታወቀው የአውሮፓ ቅኝ ገዢ መንግስታት በየትኛውም የዓለም ክፍል አንድን ሃገር መውረር ሲፈልጉ መጀመሪያ ወጥመድ ውስጥ ለማስገባት ቆዳቸውን አለስልሰው የወዳጅነት፣ የእምነት፣ የንግድ፣ ወዘተ እያሉ በውስጡ ብዙ ተንኮል ያዘለ ውል ያስፈርማሉ። በመጨረሻም ቃላቸውን በመቀየር ውሉን አፍርሰው ወይም አጣመው ቀጥተኛ ጦርነት በማድረግ ሃገሩን በሃይል ይቆጣጠራሉ። ይህ በእንዲህ እንዳለ ኮንት አንቶኔሊ (Count Antonelli) የተባለ ሰው አጼ ምኒሊክን ለኢትዮጵያና ለጣሊያን መንግስታት ወዳጅነት ጠቃሚ ነው ብሎ በማግባባት ውጫሌ በሚባል ቦታ የውጫሌ ውል ያስፈርማቸውል። እንደሚታወቀው በውጫሌ ውል አንቀጽ 17 በአማርኛ እና በጣሊያንኛ ቋንቋዎች የተጻፉት የተለያየ ትርጉም ያላቸው ሆነው ተገኙ። በጣሊያንኛ ቋንቋ የተጻፈው ቅጂ የኢትዮጵያን ልኡዋላዊነት የሚጋፋ ስለነበር ይህንን ልዩነት እንዲያስተካክል አጼ ምኒልክ እና እቴጌ ጣይቱ ለጣሊያን ተወካይ ቢያሳስቡም አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱትም አይሰማም እንደሚባለው በምክንያት ሃገራችንን ለመውረር ሆን ብሎ የሰነጎረው አንቀጽ በመሆኑ ችግሩን ለማረም በጣሊያን በኩል ፍቃደኛ ባለመሆናቸው የውጫሌ ውል አንቀጽ 17 ለአድዋው ጦርነት መነሻ ምክንያት ሆነ።

የጣሊያን ወራሪ ሃይል የጦርነት ዝግጅቱን እንዳጠናቀቀ ኋላ ቀር ያለውን የምኒልክን ሰራዊት አሸንፎ አጠቃላይ ኢትዮጵያን ቅኝ ግዛቱ ለማድረግ በአራት የጦር ጀነራሎች እየተመራ በ1888 ዓ.ም አድዋ ላይ ከኢትዮጵያ ጀግኖች ጋር ጦርነት ገጠመ። በግፍ ኢትዮጵያን ለመውረር የተነሳው የፋሽስት ጣሊያን ጦር በአፄ ምኒልክ ብልህ አመራር እና በጀግኖች አባቶቻችን እንክትክቱ ወጥቶ ተሸነፈ። በጣሊያን ጦር በኩል ተዋጊውን ይመሩት ከነበሩት አራት ጀነራሎች ውስጥ ሁለቱ በጦርነቱ ላይ ሲገደሉ፣ አንዱ ተማረከ፣ ሌላው ደግሞ (ጀነራል ባራቴሪ) ፈርጥጦ አስመራ ገባ። እሱም ቢሆን ቀሪ ህይወቱን በጭንቀት ሲሰቃይ ኖሮ ሃገሩ ሄዶ እንደ ሞተ የህይወት ታሪኩ ይናገራል። በመሆኑም ዘመናዊው የጣሊያን ተዋጊ ሃይል ኋላቀር በሚባሉት በኢትዮጵያ ተዋጊዎች ሙሉ በሙሉ በመደምሰሱ በአውሮፓ መንግስታት ዘንድ የጣሊያን መንግሥት አንገቱን በሃፍረት ደፋ፣ ከፍተኛ ወቀሳና ውርደትም ደረሰበት። አውሮፓውያንም በአፍሪካ ብሎም በዓለም ላይ ለነበራቸው ቅኝ ግዛቶች ኢትዮጵያ የነጻነት አርዓያ ትሆናለች በማለት ጭንቅ ውስጥ ገቡ። የኢትዮጵያ የድል ወሬ ወደሌሎች አካባቢዎች እንዳይሰራጭ ዜናውን አፍኖ ለመያዝ የሚችሉትን ሁሉ አደረጉ። ይሁንና የሮም ከተማ ህዝብም አደባባይ ወጥቶ Viva Menelik! እያለ የአጼ ምኒልክን ጀግንነት በማወደስ በሃገሩ መንግስት ላይ ያለውን ቁጣና ተቃውሞ አሰማ። ይህም ለጣሊያን መንግስት ታላቅ ሃፍረትና ራስ ምታት ሆነበት። የፋሽስት ጣሊያን መንግሥት ለደረሰበት ሽንፈትና ውርደት አጠቃላይ ኢትዮጵያን እና ህዝቧን ቢጠላም በዋና ደመኛ ጠላትነት በመፈረጅ ለመበቀል የተነሳው ግን:- 1ኛ የኢትዮጵያን ህዝብ ከዳር እስከ ዳር አስተባብረው አሸነፉኝ የሚላቸውን አፄ ምኒልክን፣ 2ኛ በጦርነቱ ላይ በነቂስ የተሳተፈውን ሃገር ወዳዱን የአማራን ህዝብ፣ 3ኛ አድዋ ድረስ ታቦት ተሸክመው በመሄድ ለተዋጊው የመንፈስ ብርታትና ጉልበት የሆኑትን የኦርቶዶክስ ካህናትን ነበር።

በመሆኑም የፋሽስት ጣሊያን መንግስት ዋና ደመኛ ጠላቴ በሚላቸው በአፄ ምኒልክ፣ በአማራን ህዝብ እና በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ላይ የተቀነባበረ ስም የማጥፋት የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ከፈተ። ስም ከማጥፋቱ ጎን ለጎን ባንዳዎችን በመመልመል የወር ደሞዝ እየከፈለ በሰላይነትና በቅጥረኛ ተዋጊነት (Askaris) ከማሰማራቱ ጎን ለጎን በአስመራ ከተማ ጽሁፎችን በትግርኛ ቋንቋ እያተመ ወደ ህዝቡ በማሰራጨት የአዕምሮ አጠባ (Brainwash) ያደርግ ነበር። የጣሊያን መንግስት የአድዋ ሽንፈቱን ለመበቀል አርባ አመት ሙሉ ሲዘጋጅ ቆይቶ ሙሶሊኒ በ1928 ዓ.ም ሰራዊቱን ዘመናዊ የጦር መሳሪያ አስታጥቆ በኢትዮጵያ ላይ ግልፅ ወረራ ፈፀመ። በወራሪው የፋሽስት ጣሊያን ጦር እና በኢትዮጵያ አርበኞች መሃል በአምባሰል ወረዳ “ማይጨው” በሚባል ተራራማ አካባቢ ከፍተኛ ጦርነት ተደረገ። በዚህ ጦርነት ላይ የጣሊያን መንግስት በዓለማቀፍ ደረጃ የተከለከለ የናፓል የኬሚካል ቦምብ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ከሰማይ የሚጥሉ አውሮፕላኖችን፣ በመሬት ደግሞ በታንክ በሚታገዙ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ በታጠቁ ወታደሮች በመሳሪያ ብልጫ፣ በባንዳ ስለላና እገዛ፣ በጭካኔ ህዝብን በጅምላ በመጨፍጨፍ የጣሊያን ወራሪ ሃይል አዲስ አበባ መግባት ቻለ። ይሁን እንጂ ጀግኖች አባቶቻችን የእግር እሳት ሆኑበት። ተስፋ ሳይቆርጡ 5 ዓመት ሙሉ ቆላ ደጋ ተንከራተው፣ አካላቸውን እና ህይወታቸውን ገብረው በብዙ ድካም እና መስዋዕትነት ኢትዮጵያን ነፃ አወጧት። በወቅቱ ቀ/ኃ/ስላሴ ፖለቲካዊ ድጋፍ ከእንግሊዝ መንግስት ማግኘታው በራሱ በአለማቀፍ የፖለቲካ መድረክ ላይ የነበራቸውን ተሰሚነት የሚያሳይ ነው።

  1. ማስታወሻ፣

እዚህ ላይ ማሳሰብ የምፈልገው ኦርቶዶክስን የማጥፋት ወይም የማጥቃት ዘመቻ ከአንድ እምነት ወይም የፖለቲካ አስተሳሰብ ጋር የተቆራኘ አለመሆኑን ነው። ለምሳሌ የጥንቱን የአክሱም የፅዮን ማርያም ቤ/ክ በዘጠነኛው ክ/ዘ ያቃጠለችው የይሁዲ እምነት ተከታይ የነበረችው ዮዲት ጉዲት (አስቴር ጌዲዖን) የምትባል ሴት ናት፣ ከዮዲት ጉዲት በመቀጠል የእስልምና እምነት ተከታይ የሆነው ግራኝ አህመድ (አህመድ ኢብራሂም አልጋዚ) እጅግ ብዙ ውድመት በቤተክርስቲያን እና በምዕመናን ላይ አድርሷል፣ የካቶሊክ ክርስትና አማኝ የሆነው የጣሊያኑ መሪ ቤኒቶ ሞሶሎኒ፣ እምነት የለሹ ደርግ፣ ኢህአዴግ፣ ብልፅግና፣ ኦነግ እና የመሳሰሉት የብሔር ድርጅቶች በጋራም ሆነ በተናጠል ኦርቶዶክስ ላይ ዘምተዋል፣ ለጥቃት አጋልጠዋታል፣ አዋጀ አስነገረው፣ ፖሊሲ ቀርጸው መዋቅራዊ (መንግስታዊ) ጥቃት ፈፅመውባታል፣ ምዕመኑን እና ካህናቱን አሳደዋል፣ ገድለዋል፣ ቤ/ክ አቃጥለዋል፣ የክርስቲያኖች መኖሪያና፣ መተዳደሪያ የንግድ ተቋሞችን በሻሸመኔ፣ መተሃራ፣ በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ ከተሞች አውድመዋል። ወዘተ፣ ወዘተ

  1. ኦርቶዶክስ ከጥንት ጀምሮ በተለያዩ የሃገራችን ክፍሎች ስለመኖሯ፣

በ5ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያዊው ንጉሰ ካሌብ ቀይ ባህርን ተሻግረው በደቡብ የመን የነበሩ ክርስቲያኖችን ፊንሃስ የተባለ የይሁዲ ንጉስ ካደረሰባቸው ጥቃት ሊታደጓቸው በመርከብ ብዙ ሺህ ወታደሮችን ጭነው ቀይ ባህርን ተሻግረው ወደ የመን መዝመታቸውን ታሪክ ይነግረናል። በዘይላ (ሶማሌ) ወደብና በአካባቢው ክርስቲያኖች ይኖሩ እንደነበረ የቤተክርስቲያን ታሪክ ላይ ተጽፎ ይገኛል። ለጊዜው የሰሜኑን የሃገራችንን ክፍል ትተን ማዕከላዊ እና ደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢዎችን ብንመለከት ኦርቶዶክስ ከብዙ ዘመናት ጀምሮ በተለያዩ የሃገራችን ክፍሎች ትገኝ እንደነበር መረዳት እንችላለናል። ግራኝ አህመድ ወረራ ከመፈጸሙና የኦሮሞ ከብት አርቢ ጎሳዎች ወደ ደጋማው አካባቢ ከመስፋፋታቸው በፊት በዚሁ አካባቢ በርካታ የክርስቲያን ህዝብ መኖሪያ መንደሮች፣ ገዳማት እና ቤተክርስቲያናት በስፋት ይገኙ እንደነበር የታሪክ መዛግብት እና በአካባቢዎቹ የሚገኙ ቋሚ ታሪካዊ ቅርሶች ይመሰክራሉ ይመሰክራሉ። ለምሳሌ በላሊበላ ውቅር ቤ/ክ አምሳያ ተሰርቶ የነበረው ፈርሶ የሚታየው የየካ ዋሻ ሚካኤል ውቅር ቤ/ክ፣ ከአዲስ አበባ በቅርበት በሚገኘው በየረር አካባቢ እንዲሁም በወጨጫ እና በመናገሻ ተራራሮች ተቆፍረው የወጡ ታቦታት፣ ቅዱሳን መጻህፍት፣ የአዳዲ ማርያም ውቅር ቤ/ክ፣ የዝቋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም፣ በአርባ ምንጭ (ጋሞ) አካባቢ የኦሪት መስዋዕት ይቀርብባት የነበረች ብርብር ማርያም ቤ/ክ፣ በግራኝ አህመድ ወረራ ወቅት አክሱም የነበረው የቃል ኪዳን ታቦቱን ካህናቱ ከውድመት ለመታደግ የሸሸጉበት የዘዋይ ሃይቅ ደሴቶችን፣ በታሪክ የክስታኔ ጉራጌ ማህበረሰብ መኖሪያ በነበረው አሁን በምዕራብ ሸዋ በኦሮምያ ክልል የሚገኘው በወንጪ ሃይቅ ዙሪያ፣ በወሊሶና አካባቢው እስከ ቡታጅራ ድረስ የሚገኙ ታሪካዊ ቤተክርስቲያናት፣ ትክል ድንጋዮች እና የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል። የግራኝ አህመድ ፀሃፊ የነበረው የመናዊው አረብ ፈቂህ በባሊ (ባሌ) ውስጥ በርካታ ክርስቲያኖችና ይኖሩ እንደነበር፣ በግራኝ ተዋጊዎች ተሸንፈው እምነታቸውን በመቀየር ሙስሊም እንደሆኑ ይገልፃል። (The conquest of Abyssinia page 107 to 119)

በአረብ ፈቂህ መጽሃፍ The conquest of Abyssinia ላይ ተፅፎ እንደሚገኘው በሃረር ከተማ ይኖሩ የነበሩ ሼህ መሐመድ አል መግራቢ እና ሳድ ቢን የኑስ የተባሉ ትንቢት ተናጋሪ ነን ባይ አረቦች ለግራኝ አህመድ የክርስቲያኑን መንግስት ላይ ጦርነት እንዲያውጅ ህልም አየንልህ ተነስ፣ ተዋጋ እያሉ ለጦርነት ያነሳሱት ነበር። በ1517 ዓ/ም ግራኝ አህመድ ተዋጊ ሰራዊቱን አደራጅቶ የንጉሱ ግዛት የነበረውን ዳዋሮን በመውረር እሱም እንደ አማቹ ማህፉዝ በደዋሮ ይገኝ የነበረ ቤተክርስቲያን አቃጥሎ፣ ህዝቡን ዘርፎ ተመለሰ። The conquest of Abyssinia p 20. ከዳዋሮም እንደተመለሰ በትውልድ ሃገሩ በሆባት፣ በሃረርና በየአካባቢው እየተዟዟረ የአካባቢውን የጎሳ መሪዎችን እና ነዋሪ ህዝቡን በመሰብሰብ የዘረፈውን እያሳየ እነሱም እሱን ተከትለው ቢዘምቱ ሊበለፅጉ እንደሚችሉ ያማልላቸው ነበር።

በመቀጠልም የዘይላን፣ የኤደንን ወደቦች እና በወቅቱ የቀይ ባህርን የንግድ መስመር ይቆጣጠሩ ከነበሩት የቱርክ የጦር ጀነራሎች ባገኘው የመድፍና የሙስኬተር (ጠመንጃ) እርዳታ፣ ከየመን፣ ከሞሮኮ እና ከመሳሰሉት የአረብ ሃገራት ዘርፈው ለመክበር በመጡ አለማቀፍ አሸባሪዎች ይበልጥ እራሱን በማጠናከር በመጋቢ 1521 ዓ.ም በምስራቅ ሸዋ ደብረዘይትን አልፎ በሞጆ አካባቢ ሽምብራ ኩሬ በተባለ ቦታ በተደረገ ጦርነት የንጉሱን የአፄ ልብነ ድንግልን ሰራዊት ድል አደረገ። በዚሁም አካባቢ ማለትም በፈጠጋር፣ በሽምብራ ኩሬ፣ በየረር፣ በደብረዘይት፣ በዱከም፣ በአቃቂ፣ በቃሊቲ፣ በባደቂ፣ በበረራ እና በአካባቢው ይገኙ የነበሩ በርካታ ቤተክርስቲያናትን እና የክርስቲያን ህዝብ መኖሪያ መንደሮች በእሳት አወደመ። በዝቋላ ተራራ የሚገኘውን የጥንታዊውን የአቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስ ገዳም እና በዙሪያው ይገኙ የነበሩ የክርስቲያን ህዝብ መኖሪያ መንደሮችን አቃጠለ። የፈጠጋር አውራጃ ተብሎ ይጠራ የነበር በዚሁ በምስራቅ ሸዋ፣ ዝቋላ ተራራና አካባቢ ይገኝ በነበር ሰፊ አውራጃ ውስጥ የነበሩ ቤተክርስቲያናትን የግራኝ ተዋጊዋች አቃጠሉ። ህዝቡንም በሃይል አስገድደው አሰለሙ፣ እምነቴን አልቀይርም በማለት ለመሸሽ አቅም ያለው ሃገሩን ለቆ ወደ ተለያየ አካባቢ ተሰደደ፣ በርካታ ክርስቲያኖች በሰይፍ ተቀሉ፣ የቀሩትና የተማረኩት ደግሞ በባርነት ወደ አረብ ሃገር ተግዘው ተሸጡ። ለምሳሌ በባርነት ከተሸጡት ውስጥ የንጉሱ ልጅ ልዑል ሚናስ ይገኙበታል (በኋላ ላይ በእስረኛ ልውውጥ ልኡሉ ተመልሰዋል)። በጥንቶቹ  የኢትዮጵያ አውራጃ በነበሩት በባሊ፣ በዳዋሮ፣ በፈጠጋር እና በመሳሰሉ ይኖሩ የነበሩ በርካታ ክርስቲያኖች ላለመታረድ ሲሉ እስልምናን ተገደው ተቀበሉ። የአረብ ነጋዴዎች ከሃገራችን የተዘረፉ የተለያዩ ንብረቶችን፣ ቅርሶችን፣ ንዋየ ቅዱሳንን እና ክርስቲያኑን ህዝብ በጅምላ ወደ አረብ ሃገራት እያሻገሩ በተለይም በሳውዲ አረቢያ ለጅዳ ከተማ ቅርብ በሆነች በቀድሞ ስሟ Zahid (ዛሂድ) በምትባል ቦታ እና ህንድ ውስጥ Gujarat (ጉጅራት) ወደሚባል ግዛት እያሻገሩ በባርነት ይሸጧቸው ነበር። “The Conquest of Abyssinia” P. xvii, xix, እና P. 26። እነዚህ እና የመሳሰሉት ተጨባጭ ምሳሌዎች የሚያሳዩት ከ16ኛው ክ/ ዘመን በፊት ጀምሮ ከላይ በተጠቀሱት አካባቢዎች የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እና የክርስቲያን መኖሪያ መንደሮች እንደነበሩ ነው። ከግራኝ ጦርነት በመቀጠል በጥንታዊ ኢትዮጵያ አውራጃዎች በነበሩት በባሊ፣ በዳዋሮ፣ በፈጠጋር እና በመሳሰሉ ይኖሩ የነበሩ ማህበረሰቦች በኦሮሞ አርብቶ አደር ጎሳዎች መስፋፋት አብዛኛዎቹ በመዋጣቸው ኦሮምኛ ቋንቋ መናገር ጀመሩ፣ ከብሔር፣ ከእምነት፣ ከባህል፣ ከቋንቋ እና ከመሳሰለው አንጻር የኢትዮጵያ ህዝብ በሰፌድ ላይ እንደሚንቀረቀብ እህል ወይም በምጣድ ላይ እንደሚታመስ ጥሬ በታሪክ ሂደት ህዝቡ ይበልጥ እርስ በርሱ እየተቀየጠ ሄደ።

እዚህ ላይ ግልፅ መሆን ያለበት ግራኝ አህመድ የመራው ወረራ ከእምነት ጋር ግኑኝነት አልነበረውም ነገር ግን የኦቶማን ቱርክ እና አረቦች የኢትዮጵያ ክርስቲያን መንግስት ላይ ያደረጉት የእጃዙር ወረራ (Proxy war) ነው። በወረራውም የተሳተፉ ተዋጊዎች ለዘረፋ ተገፋፍተው ወደ ጦርነቱ እንደሚገቡና በዝርፊያ ለመክበር መሆኑን አረብ ፋቂህ በመጽሃፉ ላይ በግልጽ አስፍሯል። ለምሳሌ በአንድ ወቅት “የክርስቲያኖችን ፈረስ፣ በቅሎ፣ በሬ፣ አህያ፣ ባሪያ፣ የሃር ጨርቅ የሚበቃንን ያህል በዘረፋ አግኝተናል ካሁን በኋላ ጦርነት አንፈልግም ወደ ሃገራችን የዘረፍነውን ይዘን እንመለስ” የሚል ጥያቄ የግራኝ ተዋጊዎቹ አቅርበው ነበር። The conquest of Abyssinia: page 154 እና 155.

ግራኝ አህመድ በውስጡ በክፋት የተሞላ ጨካኝ ሰው ስለነበር በየከተማና በየመንደሩ፣ በየገዳሙና ቤተክርስቲያኑ እየዞረ የሚፈልገውን ያህል ሃብትና ታሪካዊ ቅርስ መዝብሮ ሲያበቃ የቀረውን ያለርህራሄ በእሳት ያቃጥለው ነበር። “የግራኝ አህመድ ተዋጊዎች ባለፉባቸው ቦታዎች ሁሉ የሚያገኙትን የክርስቲያን መኖርያ መንደሮች ሳያወድሙ አያልፉም ነበር”። The Conquest of Abyssinia P. 60። ግራኝ ሚስቱን ድል ወንበራን እና እቁባቶቹን ይዞ በበረራ ከተማ ከ12 ቀን በላይ ተቀምጦ ነበር። ደብረ ሊባኖስ ገዳም እንዲቃጠል ለተዋጊዎቹ ትእዛዝ የሰጠውም በዚህ ወቅት ነው። ግራኝ አህመድ በረራ ከተማ ሰፍሮ በነበረበት ጊዜ አንድ ሰው እንዲህ ብሎ ነገረው “ከበረራ ከተማ የ6 ቀን የእግር ጉዞ እርቀት ላይ ግራርያ በሚባል ቦታ የሚገኝ በውስጡ ብዙ ሃብት የያዘ ደብረ ሊባኖስ የሚባል ታላቅ ቤተክርስቲያን አለ” ይህንን ሲሰማ ግራኝ አህመድ የጦር አዛዦቹን ጠርቶ ወደ ግራርያ (በአሁኑ ጊዜ አካባቢው ሰላሌ ተብሎ ይጠራል) ደብረ ሊባኖስን ፈጥነው በመሄድ ቤተክርስቲያኑን ዘርፈው እንዲያቃጥሉ ጭፍሮቹን አዘዘ። የግራኝ ጭፍሮች ገዳሙ እንደደረሱ ከካህናቱ ጋር በመደራደር በቤተክርስቲያኑ የሚገኙ ከወርቅ እና ከብር የተሰሩ ንዋየ ቅዱሳን እና የሃር ጨርቆች ከተቀበሉ በኋላ ቃላቸውን በማጠፍ ቤተክርስቲያኑን በእሳት አቃጥለው ወደ በረራ ከተማ ተመለሱ፣ ካህናቱቱም ታረዱ፣ በርካታ መነኮሳት በቤተክርስቲያኑ ውስጥ እንዳሉ አብረው በእሳት በመቃጠል ሰማዕትነትን ተቀበሉ። The conquest of Abyssinia p 190 – 191።

በመቀጠልም ግራኝ አህመድ ጭፍሮቹን አስከትሎ ወደ ቤተ አማራ ተጓዘ። አረብ ፈቂህ በወቅቱ በዓይኑ ያየውን እንደሚከተለው ይተርካል: የንጉሱ ቤተክርስቲያ ወደ ምትገኝበት ቤተ አማራ እንደደረሱ ግራኝ አህመድ አቅጣጫ መሪውን ምንያህል ቤተክርስቲያን ከዚህ ይገኛል ብሎ ጠየቀው። አቅጣጫ መሪውም መካነ ስላሴ፣ አትሮኖስ ማርያም እና በርካታ ቤተክርስቲያን እንዳሉ ነገረው። ከዚያ ግራኝ ወደ መካነ ስላሴ ቤ/ክ በመሄድ ወታደሮቹን ከውጭ አስቁሞ ከቅርብ ታማኞቹ ጋር ወደ ውስጥ ዘልቆ ገባ። በወርቅ በብር የተሰሩ ልዩልዩ ዕቃዎች፣ የቤተክርስቲያኑ በሮች ውድ በሆነ ወርቅ እንዲሁም በከበሩ ማእድናት የተዋበ ነበር። የቤተክርስቲያኑ የግርግዳው ጌጥ  እንዲሁም ጣራው በወርቅና በነሃስ ያጌጡ ነበሩ። ወዲያው ከውጭ ይጠብቁ የነበሩ ወታደሮች በሩን እንዲከፍቱ አደረገ፣ ሁሉም ባዩትነገር ተገረሙ። ግራኝ አህመድ ከእርሱ ጋር የነበሩትን አረቦች እንደዚህ በወርቅና በእንቁ ያጌጠ ቤተክርስቲያን በባዛንታይን (ኮንስታንቲኖፓል) ወይም በህንድ አልያም በሌሎች አካባቢዎች አይታችሁ ታውቃላችሁ? ብሎ ጠየቃቸው። እነሱም ከዚህ በፊት በፍፀም በየትኛውም ዓለም እንደዚህ የተሰራ አይተንም ሰምተንም አናውቅም ብለው መለሱለት። ከጠዋት አንስቶ እስከ ማታ የሚበቃቸውን ወርቅ ከግድግዳው፣ ከቋሚውና ከጣራው ላይ በመጥረቢያ እየገነጠሉ ካከማቹና የተለያዩ ቅርሶችና ንዋየ ቅዱሳን ከዘርፉ በኋላ በመጨረሻ እሳት ቤተክርስቲያኑ ላይ ለቀቁበት። The conquest of Abyssinia p 220 – 221 እና 246 – 247።

 

እንደሚታወቀው እስልምና ግራኝ አህመድ ከመወለዱ ከብዙ ዘመናት ቀደም ብሎ ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረ እንጂ ግራኝ አህመድ ያመጣው አዲስ እምነት አይደለም። ግራኝ ወደ ኢትዮጵያ ያመጣው እምነትን ወይም ለሃገራችን እድገትና ስልጣኔን ሳይሆን ከጽንፈኛ አረቦች እና ከኦቶማን ቱርኮች ጋር በመሆን ህዝብን ማሸበርን፣ ዝርፊያን እና ሃገርን ማውደም ነው። ከግራኝ የጥፋት አስተሳሰብ በተቃራኒው ሙስሊሙና ክርስቲያኑ ኢትዮጵያዊ በፍቅር አብሮ የኖረ ወንድማማች ህዝብ ነው። አረብ ፈቂህ በሄደባቸው የተለያዩ የሃገራችን አካባቢዎች በርካታ ሙስሊም ኢትዮጵያዊያንን እንዳገኘና ክርስቲያኑና ሙስሊሙ ህዝብ በሰላም አብሮ ይኖር እንደነበረ ያየውን ገልጿል። ለምሳሌ ግራኝ አህመድ ወደ መሃል ሃገር ጦርነቱን እያስፋፋ በነበረበት ጊዜ “አመጃ” በሚባል አካባቢ ይኖሩ የነበሩ የሙስሊም ማህበረሰቦችን ሰብስቦ ከንጉሱ ጋር እያደረገ ስላለው ጦርነት በመግለጽ መረጃ እንዲሰጡት ሲወተውታቸው የአመጃ የሃገር ሽማግሌዎች እንዲህ በማለት መለሱለት፡”አባቶችህና የአባቶችህ ዘሮች፣ የሚስትህም አባት የሆነው ማህፉዝ የክርስቲያን መኖሪያ መንደሮችን አሁን አንተ እንደምትለን ዘልቀው በመግባት ያጠቁበት ጊዜ የለም፣ ስለዚህ ለሙስሊሞች መከራ እንዳታመጣ አስተውል” በማለት የህዝቡን አብሮነት እንዳያደፈርስ ምክር እንደ ሰጡት አረብ ፈቂህ በመጽሐፉ ላይ ገልጾታል ። The conquest of Abyssinia p 57 & 58. በነገራችን ላይ ከዚህ በላይ እንደተገለጸው የግራኝ አህመድ አረቦችን ለይቶ እንደዚህ በወርቅና በእንቁ ያጌጠ ቤተክርስቲያን አይታችሁ ታውቃላችሁ ወይ? ብሎ መጠየቁ የሚነግረን ከግራኝ ጎን ተሰልፈው ኢትዮጵያን ያወደሟት የአረብ ተዋጊዎች ልምድ ያላቸው “ዓለም ዓቀፍ አሸባሪዎች” እንደነበሩ ነው።ከኢትዮጵያ በዘረፉት ሃብት የቱርክ እና የአረብ ተዋጊዎች በሃብት በለፀጉ። የኢስታምቡል (ኮንስታንቲኖፓል) የቱርክ ባለሥልጣናት መመገቢያ ሳህንና መጠጫ ኩባያ ሳይቀር ከኢትዮጵያ በተዘረፈ ወርቅ የተሰሩ ነበሩ።

የግራኝ አህመድ የሽብር ጦርነት ህዝቡ ከቤቱና ከእምነቱ ተለየ፣ ካህናቱም ደግ ጊዜ እስኪመጣ ድረስ መጸሃፍትን፣ ታቦታቱን እና ንዋየ ቅዱሳኑን በየዋሻውና ሃይቅ ደሴቶች ሸሸጉ፣ በሰዋራ ቦታዎች ቆፍረው ቀበሩ። ግራኝ አህመድ በዚህ ፅሁፍ ከተገለፀው በላይ በርካታ ጥፋትና ውድመት ካደረሰ በኋላ የፓርቹጋል እርዳታ እጅግ ዘግይቶ ቢደርስም ከአባታቸው አፄ ልብን ድንግል ሞት በኋላ በምትካቸው የነገሱት አፄ ገላውዲዎስ ከፓርቹጋል ወታደሮች ባገኙት እርዳታ ቅንጅት በመፍጠር የግራኝ፣ የቱርክና የአረብ የጀሃድ ተዋጊዎች ጋር ከፍተኛ ፍልሚያ በማድረግ በመጨረሻ ግራኝ አህመድ በጣና ሃይቅ አካባቢ ደምቢያ ከተባለ ሥፍራ 1535 ዓ.ም ተገደለ። አብረውት የነበሩት በርካታ የአረብ እና የቱርክ ወታደሮች ተገደሉ። የኦቶማን ቱርክ ኢትዮጵያን በቅኝ ለመግዛት የነበረው እቅድ ከግራኝ ሞት ጋር አብሮ ተቀበረ።

  1. ስደተኞችን ስትቀበል የኖረች የኦርቶዶክስ ቤ/ክ በሃገሯ ላይ ለምን ተገፋች፣ ለምንስ ተሰደደች?

ኦርቶዶክስ ፊደል ቀርፃ፣ ብራና ፍቃ ያስተማረች፣ ስነ ጥበብ፣ ስነ ህንፃ፣ ስነምግባር፣ ስነ መንግስትን፣ የሃገር ፍቅርን ያስተማረች፣ ሃገር በጠላት ተወረረ ሲባል ቀድማ ተገኝታ ለአርበኛው የመንፈስ ስንቅና ብርታት (ሞራል) የሆነች፣ ለሞቱት የምትጸልይ፣ በህይወት ያሉትን የምታፅናና፣ ሃገር የሰራች፣ መንግስት ያቆመች የሃገር ባለቤት እንጂ ወደ ጎን የምትገፋ፣ ባላንጣ አይደለችም። ይሁንና ኦርቶዶክስ ቤ/ክ በሃገሯ ላይ ስትገፋ – ችላ፣ ስትበደል – ይቅር ብላ፣ በፈጠራ አሉባልታ ወሬ ሲከሷት – ታግሳ፣ ህንፃ ቤተክርስቲያኗን ሲያቃጥሉ ለአምላኳ ከመጸለይ በቀር የበቀል በትር አንስታ አታውቅም፣ ለሃገርና ለህዝቦች አንድነት፣ ለሰላም መጠበቅ ብዙ ዋጋ የከፈለች፣ ኦርቶዶክስ ሃገር ያጸናች ናት ሲባል በወሬ ሳይሆን በመስዋዕትነት ጭምር ካህናቱ፣ መነኮሳቱና ክርስቲያኑ ምዕመን ደሙንም አፍሶ፣ ህይወቱን ገብሮ ነው። ለምሳሌ የኦርቶዶክስ አባት የሆኑት እነ አቡነ ጴጥሮስ እና አቡነ ሚካኤል ለዚህች ሃገር ደማቸውን ያፈሰሱ መሆኑን ማስታወስ ይገባል። በመሆኑም ኦርቶዶክስ በወሬ ሳይሆን በተግባር ለሃገር ነፃነትና ሉአላዊነት ዋጋ የከፈለች የሃገር ባለውለታ ብቻ ሳትሆን የሃገር ባለድርሻ ባለቤት ናት።

ጌታ መድኃኔዓለም በወንጌሉ እስከ ዓለም ዳርቻ ሂዱና አስተምሩ ባለው መሰረት የኦርቶዶክስ ካህናትና መነኮሳት በመላው ኢትዮጵያ ከጫፍ እስከ ጫፍ ክእባቡና ከአውሬው ጋር እየታገሉ፣ የሰውን ልጅ ለአምልኮ መስዋዕት ከሚያደርጉ ማህበረሰቦች ጋር እየተጋፈጡ፣አገልጋዮችን ከሞቱ ጌቶቻቻው ጋር አብሮ እስከ ህይወታቸው የሚቀብርን አስከፊ ባህል ያላቸውን ማህበረሰቦች ልማዳቸውን ለማስቀረት ታግለው ነው ክርስትናን በኢትዮጵያ ምድር ያስፋፉት። በመሆኑም ይህ ለምን ቀረብን ካልሆነ በቀር ከሃገር ሃገር ተንከራተው ክርስትናን ለቀሪው ኢትዮጵያዊ ወገናቸው ባስፋፉ ምን ባጠፉ ነው ይህ ሁሉ ዱላ፣ ጥፊና ሞት የደረሰባቸው? ምን በድለው ነው የኦሮቶዶክስ ምዕመናን መንግስት ባለበት ሃገር ደማቸው በጽንፈኞች የሚፈሰው? ቤታቸው እላያቸው ላይ የሚፈርሰው? ፋሽስት ጣሊያን በአውሮፕላን እና በመድፍ ያቃጠላት ሳያንሳት አሁን ደግሞ በተነዛባት የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ እንዴት በሃገሯ ላይ እንደጠላት ተቆጥራ ኦርቶዶክስ ትውደም?

በደማቸው የሃገርና የወገን ፍቅር ምን ማለት እንደሆነ ያስተማሩትን ሰማዕቱን ብጹ ወቅዱስ አቡነ ጴጥሮስን ግራዚያኒ አስሯቸው በነበረ ጊዜ እስር ቤት መልዕክተኞቹን ልኮ ቪላ ቤት፣ አውቶሞቢል መኪና እና የምትፈልገው ያህል ገንዘብ እሰጥሃለሁ ህዝቡ ለጣሊያን እንዲገዛ ስበክልኝ በማለት ሊያባብላቸው ሞክሮ ነበር፣ ይሁንና አቡነ ጴጥሮስ በግራዚያኒ ማባበያ እንኳን ሊስማሙ ቀርቶ ጭራሽ በመቆጣት “ወገኖቼን፣ ሃይማኖቴን፣ ሃገሬን በገንዘብ አልሸጥም” በማለት “ህዝቡም መሬቱም ለጣሊያን እንዳይገዛ አውግዣለሁ”። የሃገሬን እና የሃይማኖቴን ጠላት ጦር ወርውሬ ባልገድልም፣ በሞቴ ፈጣሪዬ ይበቀልልኛል በማለት እራሳቸውን ለመስዋዕትነት አሳልፈው ሰጡ። በአዲስ አበባ ከተማ ሐምሌ 22 ቀን 1929 ዓ.ም በግራዚያኒ ፋሽስት ወታደሮች ጥይት ተደብድበው በጭካኔ ተገደሉ። እንደ ሰማዕቱ አቡነጴጥሮስ ካህናቱም የአዲስ አበባን ህዝብ ለፋሽስት መንግስት ተገዛ ብለን አንናገርም በማለታቸው ከየካ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን እና በአዲስ አበባ ከሚገኙ የተለያዩ አድባራት ካህናቱን ሰብስበው እጅና እግራቸውን አስረው በእሳት አቃጥለው አሰቃይተው ገድለዋቸዋል፡፡ ከካህናቱ፣ ዳቆናቱና መዘምራኑ በተጨማሪ በርካታ የከተማው ነዋሪዎች በፋሽስት ወታደሮች ተረሽነዋል፣ ከመኪና ጋር በገመድ ታስረው በአዲስ አበባ ጎዳናዎች እስከ ህይወታቸው ተጎትተዋል፣ ከአውሮፕላን ላይ እስከ ህይወታቸው ተወርውረው በጭካኔ ተገድለዋል። 6ኪሎ ቆሞ የሚታየው የሰማዕታት ሃውልት የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ/ም ቁጥሩ ከ30 ሺህ በላይ የሚሆን የአዲስ አበባ ነዋሪ ህዝብ በግራዚያኒ ትዕዛዝ በአካፋ፣ በመጥረቢያና በጥይት በፋሽስቶች የደረሰበትን ጭፍጨፋ (Massacre) የሚናገር ቋሚ ምስክር ነው። ከዚሁ በግራዚያኒ ከተጨፈጨፈው ህዝብ ውስጥ አብዛኛው ከመቶ ዘጠና ፐርሰንት በላይ ኦረቶዶክስ ክርስቲያን እንደሆነ መገመት ይቻላል።

ኢትዮጵያ ከአውሮፓ በፊት አስቀድማ ክርስትናን የተቀበለች፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክን ልጆቿን ከነጭ የባህል ወረራ ጠብቃ ያቆየች ናት። ይሁንና በታብዮ ተሞልተው ኦርቶዶክስ ኋላ ቀር ናት ወዘተ እያሉ ስሟን ሲያጠለሹ የነበሩት የአውሮፓ  ሚሲዮናውያን እና እየሱሳውያን  ዛሬ እራሳቸውንም ሆነ ልጆቻቸውን ማዳን አቅቷቸው ወደ ጥንቱ አረማዊ  ባህላቸው ተመልሰው ሶዶማዊና እምነት የለሽ (Atheist) ማህበረሰብ ገንብተዋል። ልጆቻቸውም ወንድነታቸውን እያስጎረዱ ማንጠልጠያ የሌለው ባዶ ቅል ሆነዋል። ቤተክርስቲያያናቸውን እየዘጉ የናይት ክለብና የካዚኖ ቁማር መጫወቻ አድርገዋቸዋል፣  ኋላ ቀር ያሏት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ግን ዛሬም እንደ ጥንቱ ጸንታ ታላቅ የሞራል ልዕልና ላይ ትገኛለች። ያለ ኦርቶዶክስ አስተዋዕፆ ኢትዮጵያ ነፃነት እና አንድነቷን ጠብቃ መቆየት እንደምትችል እየታወቀ ፈረንጅ አምላኪ የሆኑ የዘመናችን ግዢዎቻችን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ለዘመናት የከፈለችውን ተጋድሎዋን በመካድ ለሃገር ብልጽግና የማትጠቅም ናት በማለት አጥላሏት። ጌታን ተቀብለናል የሚሉ ነገር ግን በነብይ ስም ሟርት እና ጥንቆላ የሚሰሩ የዘመናችን ፓስተሮች ሲቃዡ የሚያድሩት ፍቅርን እና አንድነትን ሳይሆን ኦርቶዶክስ ስትሰነጠቅ፣ ሃገር ሲበጠበጥ፣ ሃይማኖተኞች ሲከፋፈል ነው። እነዚህ የዘመናችን በልፃጊ ፓስተሮች በብልቃጥ ዘይት ሸጠው በሃብት የሚከብሩ የነዋይ ፍቅር ያሰከራቸው፣ ከጌታ ጋር በስልክ እናገናኛለን፣ በካራቴ እርኩስ  መንፈስ እናስወጣለን የሚሉ አጭበርባሪዎች ናቸው። በየመንገዱ ጌታን ተቀብለሃል እያሉ ሲያሰለቹን የሚውሉ የሚሲዮን ልጆች በኦርቶዶክስ ካህናት አማካኝነት በብዙ ድካም ክርስትና ተቀብለው የነበሩ ኢትዮጵያውያን በዘመናችን ካድሬዎች በባህል ስም ወደ አምልኮ ባዕድ እንዲመለሱ ሲደረግ በልጻጊ ፓስተሮችና ሰባኪያን ምንም ሲሉ አልተሰሙም፣ ንፁሃን በየመንገዱ ሲታገቱ፣ ሲገደሉ፣ ቤተክርስቲያን ሲቃጠል፣ ምዕመናን እና ካህናት እንደከብት ሲታረዱ ለእውነት እና ለግፉአን ድምፅ ሲሆኑ አልታዩም። ይሁንና አፋቸው የሚከፈተው እንደ አባቶቻቸው የአውሮፓ ሚሲዮናውያን ዛሬም ኦርቶዶክስን ለመሳደብ ነው። የቆሙባት መሬት፣ የሚተነፍሱት የነጻነት ዓየር በኦርቶዶክሳውያን የህይወት መስዋዕትነት የተገኘ፣ ዋጋ የተከፈለበት መሆኑን ይይረዱም።

ኦርቶዶክስን ያገለለው የብልጽግና የኢኮኖሚ ፍልስፍና የተቀዳው (የተኮረጀው) ማክስ ዌበር (Max Weber) የተባለ ጀርመናዊ የፕሮቴስታንት ስነምግባርና ካፒታሊዝም (Protestant Ethic and Capitalism) በሚል ርዕስ የፕሮቴስታንት እምነት ለካፒታሊስት ስርዓት ግንባታ፣ ለግለሰቦች በሃብት መበልፀግ ወሳኝ መሆኑን ከገለጸበት ጽሁፍ መሆኑ ይታወቃል። ማክስ ዌበር በጽሁፉ ውስጥ ሃብት ማፍራት የሚቻለው በጾም፣ በፀሎት፣ በምልኩስና እና በመሳሰሉት ሳይሆን በፕሮቴስታዊ ስነ ምግባር በመታገዝ ነው በማለት ቁስ፣ ገንዘብ ወይም ሃብት የእድገትና ያስልጣኔ መለኪያ ተደርጎ እንዲወሰድ፣ በማህበረሰቡም ዘንድ ለእኔ ብቻ የሚል፣ ለሌላ ሰው ግድ የሌለው፣ የግለኝነት እና ራስ ወዳድነት አስተሳሰብ እንዲስፋፋ ያደረገ ነው።

ጣሊያን በኢትዮጵያ ውስጥ በቆየበት በ5ቱ ዓመት የአርበኞች ትግል ወቅት ፋሽስት ኢትዮጵያውያን ለአርበኛ ስንቅና መረጃ ታቀብላለህ፣ ቤትህ ታሳድራለህ፣ የኢትዮጵያን ባንዲራ በሰርግ ወይም በሃዘን ላይ ተጠቅመሃል (ሰቅለሃል)፣ ለጣሊያን መንግስት አልገዛም ብለሃል ወዘተ እያለ ነዋሪውን ህዝቡን በሃገሩ ላይ ያስጭንቅ ነበር። በበወያኔ እና በብልጽግና አገዛዝ ዘመን ትናንትና በአድዋ፣ በማይጨውና በ5ቱ ዓመታት የኢትዮጵያ አርበኞች ትግል ወቅት ጀግኖች አባቶቻችን ደማቸውን ያፈሰሰሱለትን የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ መያዝ ወንጀል ሆኖ ከነጠላና፣ ከእናቶች ቀሚስ ላይ ሳይቀር እየቀደዱ መጣላቸው ከወራሪው ከፋሽስት ጣሊያን ከቆዳ ቀለማቸው ውጪ ልዩነት የላቸው አይመስልም።

ባጠቃላይ ኦርቶዶክስ በተለያዩ ጊዜያትና ዘመናት በሃገሯ ላይ ስትገፋና ስትጠቃ ኖራለች። ለምሳሌ በወራሪው በፋሺስት ጣሊያን፣ በዮዲት ጉዲት፣ በግራኝ አህመድ የሽብር ወረራ እና እሱን ተከትለው ለዝርፊያ በመጡ አረቦችና ሌሎች ሰዎች ከፍተኛ ውድመት ደርሶባታል። በሱዳኑ የደርቡሽ (መሃዲስት) ወረራ በጎንደር በሚገኙ በርካታ ቤተክርስቲያናት ተቃጥለዋል፣ የአውሮፓ ሚሲዮናውያን እና እየሱሳውያን በኢትዮጵያውያን መሃል የዘሩት የፖለቲካ መርዝና በኦርቶዶክስ ላይ የፈፀሙት ስም የማጠልሸት ዘመቻ ብዙ ዋጋ አስከፍሏል። በኮሚኒስቱ የደርግ መንግስት ንብረቷ ተቀምቷል፣ ልጆቿን ክርስትና ማንሳት እንኳን ተከልክላ ነበር፣ በኢህአዴግ አገዛዝ ዘመን በመንግስት ጣልቃ ገብነት የትናንትና ታጋይ የዛሬ ሰባኪ የሆነው ፓስተር ታምራት ላይኔ ህጋዊውን አቡነ መርቆርዮስን ወደ ውጭ በማሰደድ ሲኖዶሱን ለሁለት እንዲከፈል አድርጎ ነበር። በምንገኝበት በብልጽግ ዘመን በርካታ ምእመናን እና ካህናት ደማቸው በግፈኞች ፈሰሰ፣ ቤተክርስቲያንም ተቃጠለች፣ ይህ ሁሉ ስርዓት አልበኝነት ሲፈፀም አንድም ሰው በህግ ተጠያቂ አልተደረገም። ሃላፊነት የወሰደም የለም። በመሆኑም ከጥንት በተለይም ዮዲት ጉዲት በአክሱም በሚገኙ ካህናት እና ቤተክርስቲያን ላይ ከጀመረችው ውድመትና ጥቃት ጀምሮ ይኸው እስከ ዛሬው የብልጽግና አገዛዝ ዘመን ድረስ የአጥቂዎቹ ስም ይለያይ እንጂ በኦርቶዶክስ ላይ የሚደርሰው ጥቃት እንደቀጠለ ነው። በእነዚህ ሁሉ ዘመናት በኦርቶዶክስ ላይ የደረሰው ቁሳዊ ውድመት፣ ሰብአዊ ጉዳት በቁጥር ለመግለፅ ከሚቻለው በላይ ነው። –//–

ምንጭ፣

  1. “The conquest of Abyssinia” Futuh al-Habasa (Arab Faqih) 2003
  2. “የኦሮሞ ህዝብ ታሪክ” (ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ)”–2008 ዓ/ም
  3. J. L. KRAPF A Personal Portrait in Memory of His Entry to East Africa. In 1844
  4. The Protestant Ethic and the spirit of Capitalism (Max Weber) pdf
  5. THE HISTORY OF THE SOMALI PENINSULA (FROM ANCIENT TIMES TO THE MEDIEVAL ISLAMIC PERIOD) – Abdurahman M. Abdullahi (Baadiyow) pdf

 

 

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። ) “ገብርዬ ነበረ

ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ?

January 3, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ዛሬ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ጥር 1ቀን 2025 ዓ/ም ነው ። አውሮፓውያኑ አዲስ ዓመትን “ሀ” ብለው ጀምረዋል ። አዲሱን ዓመት ሲጀምሩም ከልክ ባለፈ ፈንጠዚያ ነው ። ርቺቱ ፣ ምጉቡና መጠጡ

ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። )

Go toTop