February 13, 2024
30 mins read

በፋኖ እና በብልጽግና አገዛዝ መካከል ድርድር ስለሚባለው አደገኛ ውዥምብር ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያይል በተገቢው ሊታወቅ ያስፈልጋል

የካቲት 4፣ 2016 ዓ/ም

 

መሠረታዊ ግንዛቤዎች

ፋኖ የብልጽግና ፓርቲ በዐማራ ሕዝብ ላይ ያወጀውን የእልቂት ጦርነት ለመመከት እና ለዘርፍጅት የተዳረገውን ሕዝብ ኅልውና ለማስከበር የአልሞት-ባይ-ተጋዳይ ፍትኃዊ ትግል በማድረግ ላይ የሚገኝ ሕዝባዊ ኃይል ነው። በማንነቱ ምክንያት ዘሩ እንዲጠፋ የታወጀበት እና የሰላም በሮች ሁሉ የተዘጉበት ሕዝብ ደግሞ ነፍጥ አንስቶ መታገል ሰብዓዊ ግዴታው መሆኑ የማያጠያይቅ ሃቅ ነው።

 

ስለዚህ፣ ሕግ አካባሪው እና ሰላማዊው የዐማራው ሕዝብ ኅልውናውን ለመታደግ ተገድዶ የሚያደረገው ፍትኃዊ ፍልሚያ በጋለበት እና ውጤታማ ሆኖ በሚገሰግስበት በአሁኑ ወቅት፣ አውዳሚ ጦርነት አውጆ የጅምላ ጭፍጭፋ ከሚያካሂድበት ከብልጽግና አገዛዝ ጋር ሊደርገ የሚታሰብ ድርድር ካለ፣ በትጥቅ እና በሕዝብ እምቢተኝነት የተገኘውን ድል የማኮላሸት ከፍተኛ ዕድል ያለውና፣ ፋኖም ሊዘናጋበት የማይገባው የጊዜው አንገብጋቢ ጉዳይ ነው።

 

የዐብይ አሕመድ አገዛዝ በዕብሪት ባወጀው በዚህ ጦርነት፣ በራሱ ላይ እየደረሰበት ካለው እና ገና ከሚጠብቀው አይቀሬ ሽንፈት መውጫ ቀዳዳ ለመፈለግ ሲል በሚያቀርበው የይስሙላ የሰላም ጥሪ፤ ወይም የዐማራው ሕዝብ የተፈጸመበትን ግፍ እና ሰቆቃ እንዲሁም የታወጀበትን የዘር ማጥፋት ጦርነት እያዩ-እንዳላዩ፣ እየሰሙም እንዳልሰሙ፣ ዝምታን በመረጡ የውጭ ኃይሎች የሚቀርብ የድርድር አሳብ፣ የአዞ እምባ ከመሆን አያልፍም። ስለሆነም፣ የታወጀበትን የእልቂት ጦርነት ለመከላከል እና ኅልውናን ለመታደግ እንዲታገል ለተገደደ ሕዝብ፣ ድርድር እንደ አዘቦታዊ ጉዳይ ተደርጎ ሊታይ የማይችል ነው። ለዚህም ማስረጃ፣ እንደሚከተለው የተገለጹትን ምክንያቶች መገንዘብ ይበቃል።

 

በመሠረቱ፣ ድርድር ተጻራሪ አቋሞች ባሏቸው ግለ-ሰቦች መኻል ይሁን በተቃራኒ ጎራዎች ባሉ ቡድኖች፣ ወይም በመንግሥት እና በተቃዋሚዎቹ ወይም በመንግሥታት መኻል የሚከሰቱ ልዩነቶችን ለመፍታት የሚደረግ የችግር መፍቻ መንገድ እና ዘዴ ነው። በዚህም ረገድ፣ ትውልድ አገራችን፣ ከግለሰቦች እስከ ሥርዎ-መንግሥታት ባሉ ጎራዎች መካክል የሚነሡ ከባድ ችግሮችን በድርድር የመፍታት አኩሪ ታሪክ የተጎናጸፈች እንደሆነች በሰፊው የሚታወቅ አዎንታ ነው።

 

በሌላ በኩል ደግሞ፣ ድርድር በአብዛኛው አስቀድመው የተካረረ አቋም በያዙ ክፍሎች መኻል የሚካሄድ ከሆነ፣ ከወዲሁ አንፃራዊ አቅም ያለውን አንዱን ጎራ አትራፊ አድርጎ፣ ሌላዉን ወገን ጎድቶ፣ የሚቋጭ ይሆናል። በዚህ ዓይነት ይዞታ ላይ በሚገኙ ጎራዎች መካከል የሚደረግ ድርድር፣ ችግርን አድበስብሶ ከማለፍ በስተቀር፣ ዘለቄታና አስተማማኝ መፍትኄ ሊያስገኝ አይችልም።

 

ስለዚህ፣ ስለ-ድርድር ሲነሣ ከሁሉ በፊት ድርድር ከማን ጋር? በማን? ለምን ዓላማ እና ግብ? እንዴት እና በምን ሁኔታ? ለሚሉት ጥያቄዎች አጥጋቢ ምላሾች መስጠት ያስፈልጋል። ድርድር እንዲደረግ አስፈላጊ ሆኖ የተገኘበት ችግር መንስዔው እና በተቃርኖ የቆሙ ኃይሎች ለፍልሚያ የዳረጋቸው ችግር ተፈጥሮ ባኅሪው ላይ የጠራ ግንዛቤ ሊኖር ይገባል። ከዚኽ አኳያ የሚታሰበው ድርድር ለችግሩ መፍትኄ ሊያስገኝ የሚችለውንም ሆነ የሚያሳጣውን፣ ማለትም፣ በመደራደር እና ባለ-መደራደር የሚገኙትን አሉታዊም ሆኑ አዎንታዊ ውጤቶች ከአጭር-ጊዜ እና ከዘለቄታው አኳያ በተገቢ እና በጥንቃቄ ሊቃኝ እና በሰከነ ሁኔታ ሊመረመር ያስፈልጋል። ባለፉት ስድስት ዓመታት በዐብይ አሕመድ አረመኔኣዊ የብልጽግና አገዛዝ በአገራችን እና በሕዝባችን ላይ የተፈጸሙ እና እየተፈጸሙ ያሉ ፈርጀ-ብዙ ችግሮች፣ በአስከፊነታቸው በቅርቡ የኢትዮጵያ ታሪክ ወደር የሌላቸው ናቸው።

 

አገዛዙ ጎትቶ ባመጣቸው ችግሮች ምክንያት ጠቅላላው የአገሪቱ ሕዝብ፣ በተለይም የዐማራው ክፍል፣ ሰላም ተነፍጓል፤ እንዲሁም በሕይወት የመኖር መሠረታዊ መብቱን አጥቷል። ታሪካዊት አገራችንም የዜጎቿ ቄራ እንድትሆን እና ሉዓላዊነቷን ማስከበር ካለመቻል ውርደት ባለፈ ኅልውናዋ ለአደጋ ተጋልጧል፣ ከኢትዮጵያውያንም አልፎ ለአካባቢው ሰላም መደፍረስ የስጋት ምንጭ ሆና እንድትታይ ተደርጋለች።

 

ለሕግ እና ለሥርዓት ተገዢ የሆነው የዐማራ ሕዝብ፣ በብልጽግና አገዛዝ የደረሱበትን ፈርጀ-ብዙ ችግሮች እና በደሎች በሚገርም ትእግሥት እና ጨዋነት ችሎ፣ በዜግነቱ በሰላም ለመኖር፣ በሰላማዊ ሠልፍ ሳይቀር ላቀረበው ተማጽኖ ምላሹ የበለጠ አፈና፣ የጅምላ ጭፍጨፋ እና የንብረት ውድመት ነበር።

 

ብሦት የበዛበት እና ሰሚ-ያጣው የዐማራው ሕዝብ በኅልውናው ላይ የተቃጣበትን ይኽን የጥፋት ዘመቻ መመከት ግዴታው በመሆኑ፣ ከአብራኩ በወጡ የፋኖ ታጋይ ልጆቹ አማካይነት የአልሞት-ባይ-ተጋዳይ ተፈጥሯዊ መብቱን ለማስከበር የሞት-የሽረት ትግል በማድረግ ላይ ይገኛል። አገዛዙም ለስድስት ወራት ባካሄደው የጭፍጨፋ ዘመቻ ያሰበውን ግብ ማሣካት እንዳልቻለም ያንኑ ያኽል ግልጥ ሆኗል።

 

በዚኽ አሳዛኝ እና አሣፋሪ ሁኔታ ውስጥ እያለን ከተለያዩ አቅጣጫዎች ከአገዛዙ ጋር ድርድር ያስፈልጋል የሚል አሳብ ሲሰነዘር ይሰማል። ይኽ አዝማሚያም ከሦስት አቅጣጫዎች እንደሚገፋ መገመት ይቻላል።

 

አንደኛው ከገባበት ጦርነት ለመውጣት ማጣፊያው ያጠረው አገዛዝ፣ የሚወስደው የኃይል እርምጃ ያሰበውን ዓላማ እንደማያስገኝለት ብቻ ሣይሆን የሚጓጓለትን ሥልጣን እንደሚያሳጣው ስለተገነዘበ፣ በድርድር ስም ሁኔታውን አርግቦ፣ በተለመደ መሠሪ አካሄድ ፋኖን ከፋፍሎ ለማጥፋት፣ የውጭ እርዳታን ለማግኝትና እንዲሁም ጊዜ በመግዛት ሥልጣኑን ለማስቀጠል ይረዳል በሚል ብዥታ የተለመው እቅድ ሊሆን ይችላል።

 

ሁለተኛው፣ ያለው ሁኔታ አገሪቱን ለብተና ይዳርጋል፣ ለአካባቢው መረጋጋት-አለመኖርም ጠንቅ ይሆናል ከሚል ግምገማ በመነሣት እና ያም ከራሣቸው ጥቅም አኳያ የሚያስከትለውን አደጋ በስጋት በመመልከት፣ በድርድር ስም ጦርነቱ እንዲቆም ከሚፈልጉ የውጭ ኃይሎች ሊሆን ይችላል።

 

ሦስተኛው አንድም ጦርነቱ ከተራዘመ በሕዝብ ላይ የባሰ ችግር እና እልቂት እንዳያስከትል ጦርነቱ እንዲቆም ማድረጉ ይሻላል ከሚል ቀና አሳብ፣ ሆኖም ግን ግብዝ አመለካከት እና ግልብ እምነት በመነሳት ከሚደግፉ ክፍሎች፤ ወይም በኅልውና ትግሉ

 

ተስፋ የቆረጡ፤ እንዲሁም ከታጋዩ ክፍል መኻል በሚፈጠር የውስጥ ችግር አሠላለፋቸውን በሚቀይሩ ወገኖች፤ ወይም በሥልጣን እና በሌሎች መደለያዎች የተገዙ፣ ከዚያም አልፎ የአገዛዙን ሥልጣን በማስቀጠል፣ በሕዝብ ላይ ባደረሱት በደል እና በፈጸሙት ወንጀል ከተጠያቂነት ለመዳን በሚያስቡ አድር-ባዮች ሊሆን ይችላል።

 

የድርድሩ አደገኝነት

 

በሚከተሉት ምክንያቶች፣ የዐማራው ሕዝብ ከብልጽግና አገዛዝ ጋር ድርድር ማድረጉ፣ በሰላም ለመኖርና ኅልውናውን ለማስከበር የሕይወት መስዋዕትነት እንዲከፍል ለተገደደበት ትግል አስተማማኝ አዎንታዊ ምላሽ ሊያስገኝ አይችልም።

 

) የችግሩ የተፈጥሮ ባኅሪ እና በተደራዳሪዎች መኻል ያለው ዐይንላይን የማይተያይ የአጥፊእናጠፊ የፖለቲካ እምነት እና አሠላለፍ መሆኑ

 

በሥልጣን ላይ ያሉትም ሆኑ ከሥልጣን ውጭ ያሉ በሠፈው የኦሮሞ ሕዝብ ስም የተደራጁ ጽንፈኛ ክፍሎች የዐላማቸው ልዕለ-ግብ ያደረጉት በኢትዮጵያ መቃብር ላይ አዲስ አገር የመመሥረት ቅዠትን እውን ማድረግ ነው። እነኝኽ ክፍሎች ሙጥኝ ብለው በሚከትሉት መሠረተ-ቢስ ትርክት ደረሰብን ለሚሉት ከሰማይ በታች ላለ ችግር እና በደል ሁሉ ኢትዮጵያን እንደ-አገር፣ ዐማራውን እንደ-ነገድ ተጠያቂ ያደርጋሉ። አዲስ አገር የማቋቋም እቅዳቸውን ተግባራዊ ማድረግ የሚችሉት ዐማራው ሲጠፋ እና ኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያዊነት እሴቶች ሲወድሙ እንደሆነ ያላቸውን እምነትም፣ ቁርጠኝነትም ያለ-አንዳች ሃፍረት ሲያራግቡ መስማት አዲስ አይደለም። ስለሆነም፣ ድርድር የሚደረገው ላነገበው ዓላማ በእንቅፋትነት እና በዋና ጠላትነት ተፈርጆ ዘሩን በማጥፋት ኅልውናውን ለማሳጣት፣ ቢያንስ-ቢያንስ በማንነቱ ምክንያት ሰብዓዊ ክብሩን አጥቶ፣ አንገቱን ደፍቶ በበታችነት ተዋርዶ እንዲኖር ለማድረግ በግብታዊነት ሣይሆን በተጠና ሁኔታ እቅድ ተይዞለት በተዘመተበት ሕዝብ እና በዘመተበት ኃይል መካከል መሆኑ በተገቢ ሊጤን ይገባል። በዚያ ዓይነት በአጥፊ-እና-ጠፊ ሥነ-ልቦና የተቃኙ እቋሞችን እንደያዙ እና አንዳችም ለውጥ ባላደረጉ ብቻ ሣይሆን አሳቡም በሌላቸው ጎራዎች መኻል የሚደረግ ድርድር አስተማማኝ አዎንታዊ ውጤት ማግኘት አይቻልም።

 

) የዐማራውን ሕዝብ ትግል የሚከፋፍል መሆኑ

 

የዐማራ ሕዝብ ከብልጽግና አገዛዝ ጋር የሚያደረገው ኅልውናን-የማስከበር ትግል የሚመራው፣ የሕዝብ አለኝታ እና የቁርጥ-ቀን ዋቢ በሆነው በፋኖ ግንባር-ቀደምትነት ነው። የፋኖ ታጣቂ ኃይሎች ያላቸውን አደረጃጀት ወደ-አንድ ማዕከል ለማምጣት እና ሁኔታው ለሚጠይቀው እና ለሚጠብቀው የላቀ ትግል መጣኝ ይዞታ ላይ እንዲሆን የሚደረጉ ጥረቶች አበረታች ደረጃ ላይ ቢሆንም፣ አሁንም በፖለቲካውም ሆነ በወታደራዊ ቁመናው በአንድ መዋቅራዊ ትሥሥር የሚሠራ አይደለም። ያም በመሆኑ፣ በአሁኑ ጊዜ እና ሁኔታ፣ ድርድር ለማድረግ ማሰብ፣ በመረጃ እጥረትም ይሁን ሆን-ተብሎ በሚነዙ አሉባልታዎች በሚፈጠር ውዥንብር ምክንያት በተወሰኑ የፋኖ ክፍሎች መኻል ልዩነት ሊፈጠር የሚችልበትን ዕድል በተለይ ለአገዛዙ ይሰጣል። ያ ደግሞ ትግሉን አገዛዙ ከሚፈጽመው ቀጥተኛ ወረራ በባሰ ይጎዳል፣ የሕዝብን ተስፋም በእጅጉ ያጨልማል።

 

በአሁኑ እጅግ ፈታኝ የአገራችን ሁኔታ ከብልጽግና ጋር ድርድር ማድረግ ቀርቶ ማሰብ፣ አዋራጅ ሽንፈትን ወድዶ ከመቀበል ውጭ አይሆንም። ባለው ነባራዊ ሁኔታ ድርድር ማድረግ ቀርቶ የምር ማሰብ ሽንፈትን ከመጋበዝ እና ለአገዛዙ ነፍስ-አድን እና ዕድሜ-ቀጥል ስጦታን ከመለገስ ይቆጠራል።

 

ስለዚህ፣ በአገዛዙ በቀጥታ ቀረበም-አልቀረበ፣ ምንጩ ከየትም-ይሁን-ከየት፣ ይኽ ወቅታዊ ሁኔታውን ያላንጸባረቀ ድርድር የሚባል ማነሁለያ፣ አገዛዙ አቅጣጫ-አሳች የመነታረኪያ ርእሰ–ጉዳይ /እጀንዳ/ አድርጎ እንዳይጠቀምበት እና በታጋዩ ሕዝብ ዘንድም አላስፈላጊ ብዥታ እንዳይፈጥር፣ ለዐማራው ሕዝብ ትግል ግንባር-ቀደም ተጠሪ የሆኑት የፋኖ ክፍሎች፣ በተቻለ ፍጥነት የጋራ አቋማቸውን በይፋ ቢያሳውቁ አስፈላጊና፣ ተገቢም ነው።

 

በዚኽ ረገድ፣ በተለይ ከአገር-ውጭ የሚገኙ የዐማራ አደረጃጀቶች ልዩ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል። ድርድርን በመሰሉ ልዩ ጥንቃቄን በሚጠይቁ ጉዳዮች ላይ የፋኖ አደረጃጀቶች በጋራ ከሚወስዱት ይፋዊ አቋም ውጭ የተለዬ አቋም መንጸባረቅ አይኖርበትም። ስለሆነም፣ በተለይ በዐማራው ስም በተቋቋመ ድርጅት/ማኅበር ስም ሌሎች አካላት በሚያዘጋጇቸው ስብሰባዎች ላይም ሆነ፣ በሚሰጡ ቃለ-መጠይቆች ወይም በጽሑፍ በሚቀርቡ መግለጫዎች በፋኖ ከሚወሰደው አቋም ውጪ ሊንጸባረቅ አይገባም።

 

) ድርድሩ ይደረግ የሚባለው ተኣማኒነት ከሌለው ክፍል ጋር መሆኑ

 

ከላይ እንደተጠቀሰው፣ ድርድር ይደረግ የሚባለው ብልጽግና ከሚመራው አገዛዝ ጋር ነው። ይኽ አገዛዝ ደግሞ ያለ-አንድ ግለሰብ ፈቃድ እና ይሁንታ የተለየ ምንም ማድረግ የሚችል አይደለም። ግለ-ሰቡ ባለ-መንታ-ምላስ፣ ለገባው ቃል አንዳችም ተኣማኒነት የሌለው፣ ሲበዛ የሥልጣን-ጥመኛ እና ለሥልጣኑ ሲል ምንም ነገር ከማድረግ ወደ-ኋላ የማይል፣ ጨካኝ፣ መሠሪ፣እና ያልሰከነ ስለሆነ ከእሱ ጋር የሚደረግ ምንም ዓይነት ድርድር የተሻለ ውጤት ያመጣል ብሎ ማሰብ ጉም መጨበጥ ወይም መርዘኛ እባብ አቅፎ መተኛት ይሆናል። ግለ-ሰቡ የገባውን ቃል የማያከብር መሆኑን ለመረዳት እስከዛሬ የፈጸማቸዉን ክህደቶች መገንዘብ በቂ ይሆናል። ያውም እንዲጠፋ ከሚፈልገው ሕዝብ ጋር የሚደረገውን ድርድር ያከብራል ብሎ መጠበቅ ደግሞ ሲሰማ የሞተን እያየ ቅበረው የሚባለው ተፊጻሚ እንዲሆንበት ፈቃደኛ ከመሆን አይለይም።

 

) ለፍትኃዊ የፖለቲካ ሥርዓት የሚደረገው ትግል ላይ የሚያስከትለው አሉታዊነት ከፍ ያለ መሆኑ

 

በፋኖ ፊት-አውራሪነት የሚደረገው የዐማራ የኅልውና ትግል መነሻው ዐማራዊ መሆኑ ሁኔታዎች ግድ የሚሉት ቢሆንም፣ የማያጠራጥር መዳረሻው የዜጎቿ ሁሉ የጋራ-ቤት የሆነችው ኢትዮጵያ እንደሆነች ሲነገር ቆይቷል። ተወደደም ተጠላ፣ ለአደጋ የተጋለጠው የኢትዮጵያ አገራዊ አንድነት ተጠብቆ፣ ዜጎቿ መብቶቻቸው ተከብረው በሰላም እና በእኩልነት እንዲኖሩ የሚያስችል ፍትኃዊ ሥርዓት እውን እንዲሆን የሚያደርግ መሠረት እንዲጣል በሚደረገው ጥረት የፋኖ ትግል ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ያም በመሆኑ፣ በአሁኑ ነባራዊ ሁኔታ በዐማራ ሕዝብ ስም በሚደረግ አክሣሪነቱ ከወዲሁ በማያጠራጥር የድርድር ቁማር መጫዎት፣ የዐማራ ሕዝብ ትግል ላይ መርዝ ከማፍሰስ አይለይም። ያ ደግሞ ዐማራው ብቻ ሣይሆን መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአምባ-ገነኖች የአገዛዝ ሥርዓት አዙሪት ለመውጣት እና ለፍትኃዊ ሥርዓት እውን መሆን

 

የሚያደርገው ትግል ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ አስተጋብዖ በቀላሉ የሚገመት አይሆንም። ስለሆነም፣ በዐማራው ስም ከአገዛዙ ጋር የሚደረግ ድርድር አፍራሽ ሚናው እና ጎጅነቱ አገር-አቀፍ ባኅሪ ይኖረዋል።

 

በመርኅ ደረጃ ድርድር አስፈላጊ መሆኑ ቢታመንበትም፣ ድርድር ለድርድር ሲባል ብቻ የሚደረግ ተራ ጨዋታ አይደለም። በመሆኑም፣ በአሁኑ ጊዜ ባለው ነባራዊ ሁኔታ ከብልጽግና አገዛዝ ጋር የሚደረግ ድርድር እጅግ ጎጅ ነው። ብሎም ድርጊቱ፣ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ለተፈጸመ ዘግናኝ ወንጀል፣ የብልጽግና አገዛዝ እና አረመኔኣዊ መሪዎቹ ተጠያቂ መሆናቸውን ለመፋቅ ከሚታለም ሙከራ ተለይቶ ስለማይታይ፣ በተጨቆነው ሕዝብና ታሪክ ፊት አስጠያቂ ተግባር ይሆናል።

 

የተግባር ጥሪ

 

የድርድር አሳብ የሚሰነዝር ማንኛውም የውጭ ይሁን አገር-በቀል ክፍል፣ ከሁሉ በፊት ቢያንስ የሚከተሉት እና ሌሎች ተዛማች ጉዳዮች በአስተማማኝ ሁኔታ ተግባራዊ ምላሽ ካገኙ በኋላ የሚታሰብበት መሆኑን ሊረዳው ይገባል።

 

ሀ) ሰላማዊ ዜጎች በግፍ እየጨፈጨፈ ያለው የብልጽግና ወራሪ ኃይል፣ ከድንበር-ጠባቂ በቀር፣ ከዐማራ ክፍለ-አገሮች ጠቅልሎ እንዲወጣ፣ በአየር የሚያደርሰውን አውዳሚ ጥቃትም እንዲያቆም፤

ለ) በማንነታቸው ምክንያት በማጎሪያ ቤቶች ታስረው ለስቃይ የተዳረጉ የኅሊና እስረኞች እንዲፈቱ፣ ለደረሰባቸው ስቃይ በቂ የሕክምና እርዳታ እና ለደረሰባቸው በገንዘብ የማይተመን እንግልት ተመጣጣኝ ካሣ እንዲሰጣቸው፤

ሐ) በዐማራ ክፍለ-አገሮች የብልጽግና መዋቅር እንዲነሣ እና የፋኖ ኃይሎች እና ሕዝቡ እንዲረከብ፤

መ) የኤኮኖሚ እቀባዎች እንዲነሱ፣ የተዘጉ የሕዝብ አገልግሎት-ሰጪ ተቋማት እንዲከፈቱ፤

 

  • ለበርካታ አሥርተ-ዓመታት በኢ-ፍትኃዊ የሕዝብ ቆጠራ እና ከማዕከላዊ መንግሥት በሚመደብ ዓመታዊ የማስተዳደሪያ-ተመን/በጀት/ ሆን-ተብሎ በተፈጸመበት ዓይን-ያወጣ አድልዖ እንዲደኸይ እና እንዲራብ የተደረገው፣ በአፈና ውስጥ ያለው እና በተከታታይ አውዳሚ ጦርነቶች ተቋማቱ፣ ንብርቱ እና ጥሪቱ እንዲወድም የተደረገበት የዐማራ ሕዝብ የተጣለበት ግብር እንዲሰረዝ፣ ማዕከላዊ መንግሥት ተገቢውን ማካካሻ እንዲመድብ፤

 

  • የተባበሩት መንግሥታት እንዲሁም ዓለም-አቀፍ የእርዳታ ተቋሞች፣ የሰብዓዊ-መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶች እና ጋዜጠኞች ወደ ዐማራው ክልል እንዲገቡ እንዲፈቀድላቸው፤

 

  • ማዕከላዊ መንግሥት ነባር የዐማራ ከፍለ-አገሮች– ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምት፣ ራያ፣ ወዘተ–የዐማራ አካል መሆናቸውን ይፋዊ እውቅና እንዲስጥ፤

 

ሠ) በአዲስ አበባ መስተዳደር እና በኦሮሞ ክልላዊ መንግሥት መኻል ተደረሰ በተባለ ሕገ-ወጥ ስምምነት በተመሠረተው የሸገር ስም የተጠቃለሉ ከተሞች ነዋሪ የነበሩ፣ ወደ ሰባት-መቶ ሺህ የሚሆኑ (በአብዛኛው የዐማራ) ዜጎች፤ ከመቶ-አሥራ-አራት ሺህ በላይ የሚሆኑ ቤቶቻቸው በግፍ ፈርሰው፣ ለአሰቃቂ ቤት-አልባነት ተዳርገው፣ በክረምት ሜዳ ላይ ለተጣሉ ወገኖቻችን ለደረሰባቸው ሰቆቃ እና እንግልት ተመጣጣኝ ካሣ እየተከፈላቸው ወደነበሩበት እንዲመለሱ፤

 

ረ) በዐብይ አሕመድ ስድስት የአገዛዝ ዓመታት በወለጋ እና በመተከል የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ (Genocide) የተፈጸማባቸውን እና በግፍ ከቀያቸው የተፈናቀሉትን ዐማሮች ጉዳይ ምርመራ የሚያደርግ እና ወንጀለኞችን ለፍርድ የሚያቀርብ ገለልተኛ የዓለም-አቀፍ አጣሪ ቡድን እንዲቋቋም፤

 

ሰ) ማንነታቸው ወንጀል ሆኖ ከተቃጣባቸው የዘር-ፍጅት በተኣምር አምልጠው ከመኖሪያቸው እና ከቤት-ንብረታቸው በግፍ ተፈናቅለው በስቃይ ላይ የሚገኙ ዜጎች የሚገባቸውን ፍትኅ እስከሚያገኙ ድረስ መልሶ-ማቋቋሚያ በማዕከላዊውና በኦሮሞ ክልል መንግሥት አስፈላጊው እርዳታ እንዲደረግላቸው፣ ለተፈጸመባቸው ዘግናኝ ግፍ ሕጋዊ ፍትኅ የሚያገኙበት ሂደት በገለልተኛ አካል አማካይነት እንዲጀመር፤

 

ሸ) ለችግሮቹ መነሻ የሆነው በዘር ላይ የተመሰረተው ሕገ-መንግሥት ተሽሮ፣ በፍትህ፣ ዲሞክራሲና እኩልነት ላይ የተገነባች እትዮጵያ እውን የሚሆንብት መዋቅር በአስተማማኝነት እንዲመሠረት ማድረግ ያስፈልጋል።

 

ማጠቃለያ

የኃይል አሠላለፉ ባልጠራበት፣ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚደረገው ጭፍጨፋ ተጠናክሮ በቀጠለበት፣ እና ለእርቀ-ሰላም መሠረታዊ ቅድመ-ሁኔታዎች በሌሉበት ሁኔታ የሚደረግ ድርድር ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያይል በተገቢው ሊታወቅ ያስፈልጋል። ስለሆነም፣ የቸኮለ ጅብ ቀንድ ይነክሳል እንዳይሆን፣ አስፈላጊው ጥንቃቄ እንዲደረግ የአባ ባኅሪይ የጥናት እና ምርምር መድረክ ጉዳዩ በቀጥታ ለሚመለከታቸውም እና ለመላ አገር-ወዳድ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም በኢትዮጵያ እና በአፍሪቃ-ቀንድ አገራት ሰላም እና መረጋጋት እንዲኖር ለሚመኙ ሁሉ በአክብሮት ያሳስባል።

 

ድል ለፋኖ፣ ድል ፍትኅ ለተነፈገው ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!

 

አባ ባሕርይ መድረክ

www.abbabahrey.org

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። ) “ገብርዬ ነበረ

ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ?

January 3, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ዛሬ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ጥር 1ቀን 2025 ዓ/ም ነው ። አውሮፓውያኑ አዲስ ዓመትን “ሀ” ብለው ጀምረዋል ። አዲሱን ዓመት ሲጀምሩም ከልክ ባለፈ ፈንጠዚያ ነው ። ርቺቱ ፣ ምጉቡና መጠጡ

ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። )

Go toTop