ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)
የካቲት 12፣ 2024 ዓ.ም
በመጀመሪያ ደረጃ አቶ ኤፍሬም ማዴቦ ምን ዐይነት ሳይንሳዊ ዘዴን በመጠቀም ይህንን ዐይነት ጽሁፍ እንደጻፈ አልነገረንም። ዝም ብሎ ብቻ “ኢትዮጵያ የሶስት ሺህ ዐመት የስርዓተ መንግስት ታሪክ በተከታታይነት ያላት አገር ናት” ብሎ ይነግረናል። ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን ሌሎች አገሮችም ተከታታይ የሆነ መንግስታዊ ስርዓት ነበራቸው። በሌላው ወገን ማንኛውም አገር ተከታታይነትና ከአንደኛው ትውልድ ወደሚቀጥለው ትውልድ ለመተላለፍ የሚያስችል የመንግስት ስርዓት ብቻ መኖሩ በቂ አይደለም። ራሱ የመንግስት ስርዓትና መንግስትና ህዝቡ የቆሙበት ወይም የሚመኩበት የማቴሪያል ሁኔታዎች በየጊዜው መሻሻልና ከሁኔታው ጋር ለመሄድ እንዲችሉ ሆነው በተቀላጠፈ መንገድ መዋቀር አለባቸው። አንድ መንግስት ብቻ ሳይሆን ሌላም በሰው ልጅ የተሰራ ነገር በየጊዜው እንክብካቤና ጥገና ካልተደረገለት በዚያው መልኩ ሊቀጥል አይችልም። ማንኛውንም በተፈጥሮ ውስጥ ሊከሰቱ የሚችሉ ነገሮችን ለመቋቋም እንዲችል በየጊዜው መጠገን አለበት፤ ወይም ደግሞ ከመጀመሪያውኑ ከፍተኛ አውሎ ነፋስንና የመሬት መንቀጥቀጥንም ሆነ ኃይለኛ ዝናብን ለመቋቋም እንዲችል ተደርጎ መሰራት አለበት። ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ የሶስት ሺህ ዓመታትን ያስቆጠረ የመንግስት ስርዓት ያላት አገር ነበረች ሲባል በዚህ ሶስት ሺህ ዓመታት ውስጥ ህዝቡን የሚያቅፉ፣ ርስ በርሱ ሊያገናኙና እንደ አንድ ማህበረሰብ እንዲተሳሰሩ፣ ፈጣሪና ምርታማ ሊያደርጉት የሚችሉ ምን ምን ነገሮች ተሰርተዋል? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው።
በሌላ ወገን የህብረ-ብሄርን ምስረታ(Nation States) ስንመለከት አብዛኛዎቹ የካፒታሊስት አገሮች የሁለት መቶ ዓመት ዕድሜ እንኳ የላቸውም። ለምሳሌ ጀርመን ከተለያዩ ርስበራሳቸው ከሚሻኮቱ የመሳፍንት አገዛዞች ተላቃ እንደህብረ-ብሄር ልትመሰረትና ልትገነባ የቻለቸው በ1871 ዓ.ም ነው። ከዚያ በኋላ ነው ወደ ውስጥ ያተኮረ በመንግስት የተደገፈና በግለሰቦች ተነሳሽነት ቀስ በቀስ በኢንዱስትሪ፣ በተለይም በማኑፋክቸሪንግ ላይ የተመረኮዘ ሁለ-ገብ ኢኮኖሚ ሊገነባ የቻለው። ይሁንና ግን በመጀመሪያው የኢንዳስትራይሌዜሽን ዘመን ከፍተኛ ህብረተሰብአዊ መመሰቃቀል ሊፈጥር ችሏል። በመጀመሪያ ደረጃ ኢንዱስትሪዎች በተተከሉባቸው ከተማዎች ብዙ ህዝብ ከገጠር እየፈለሰ በመምጣቱ ከገጠር ወደ ከተማ እየፈለሰ የሚመጣውን የህብረተሰብ ክፍል የሚያስተናግድ ቤት አልነበረም። አብዛኛው በአንድ ቤት ውስጥ አስርና ከዚያም በላይ በመሆን ተጣቦ ይኖር ነበር። በሁለተኛ ደረጃ በቤት ውስጥም ሆነ በውጭ እንደልብ የመጸዳጃ ቦታዎች አልነበሩም። በዚህም ምክንያት የተነሳ ዛሬ በአብዛኛዎቹ የሶስተኛው ዓለም አገር ከተማዎች እንደምናየው ከተማዎች የቆሸሹ ነበር። በሶስተኛ ደረጃ በየፋብሪካዎች ውስጥ ተቀጥሮ የሚሰራው ሰራተኛ በከፍተኛ ደረጃ የሚበዘበዝና መብቱም የሚጠበቅለት አልነበርም። በተጨማሪም ያረገዙ ሴቶችና ለአቅመ-አዳመ ያልደረሱ ልጆች በየፋብሪካው ውስጥ ተቀጥሮ የመስራት ግዴታ ነበረባቸው። በአራተኛ ደረጃ እንደዛሬው የከበርቴው መደብ ወይም አሰሪዎች የሰለጠነ ባህርይ አልነበራቸውም። ዋናው ተግባራቸውም ማምረትና ከፍተኛ ትርፍን ማካበት ነበር። ይሀ ሁኔታ የግዴታ ማህበራዊ ቀውስን ሊፈጥር ቻለ። በየፋብሪካዎች ውስጥ ተቀጥሮ የሚሰራው ሰራተኛ የግዴታ መደራጀትና ለመብቱ መከራከር አስፈለገው። የደሞዝ ጥያቄና የስራ ሰዓት መቀነስ የሚነሱ ጥያቄዎች ነበሩ። ስለሆነም የወዛደሩን መብት የሚከላከሉ ቲዎሪዎችና ለአዲስ የህብረተሰብ ሞዴል መታገል ያስፈልጋል የሚሉ ሰፋፊና ጠለቅ ያሉ ቲዎሪዎች ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ። የሶሻሊዝም ጥያቄና የሰራተኛውን መደብ በህብረት ሰራ የማደራጀት ጥያቄዎች በመነሳት አዲሱን የከበርቴ መደብ ማፋጠጥ ጀመሩ። በሌላ ወገን ደግሞ የሶሻሊዝምንና የእኩልነትን አስተሳሰብ የሚጠሉ የቀኝ ኃይሎች ብቅ ብቅ በማለት በኢኮኖሚውና በማህበራዊ መስክ የሚታየውን ፍጥጫና ቀውስ ልዩ ዕምርታ ሰጡት። በተለይም ጀርመን በቀሰቀሰችው ጦርነት የተነሳ በጦርነቱ የተጎዱ እንደፈረንሳይና እንግሊዝ የመሳሰሉት አገሮች ከፍተኛ ካሳ መጠየቅ ጀመሩ። ጀርመን በጦርነቱ ላይ ከተሸነፈች በኋላ እንግሊዝና ፈረንሳይ የጠየቁትን ካሳ መክፈል ስለነበረባት ከኤክስፖርት የምታገኘውን አብዛኛውን ገቢ ወደ እነዚህ አገሮች ማስተላለፍ ነበረባት። በዚህም ምክንያት የተነሳና በ1929 ዓ.ም በተከሰተው የዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ቀውስ የተነሳ በይበልጥ የተጎዳችው ጀርመን ነበረች ማለት ይቻላል። ስለሆነም እየተደራረበ የመጣው ቀውስና በውስጥ የነበረው የፖለቲካ ፍጥጫ ቀስ በቀስ ለፋሺዝም መነሳትና የኋላ ኋላ ስልጣንን ለመያዝ አመቺ ሁኔታን ፈጠረለት። እዚህ ላይ ለማሳየት የሞከርኩት አንድን አገር እንደ ህብረብሄር የመመስረቱ ጉዳይ ቀላል እንዳይደለ ነው። አብዛኛዎች የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ብዙ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውሶችን ካለፉ በኋላ ነው ወደ ፓርሊሜንታሪ ዲሞክራሲ ሊሸጋገሩ የቻሉት።
በተለይም ጀርመን እንደገና ልትገነባና ርስ በርሱ የተሳሰረ ኢኮኖሚ ለመፍጠር የቻለችው ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ ነው ማለት ይቻላል። የፓርሊሜንታሪ ዲሞክራሲና በሊበራል ዲሞክራሲ ላይ የተመሰረተ ሃሳብን መግለጽና አገዛዝን በመቃወም ለሰላማዊ ሰልፍ መውጣት የተጀመረው የሰባ ዓመት ዕድሜን ያስቆጠረ ብቻ ነው ማለት ይቻላል። ይህ ማለት ግን ጀርመን እንደ ህብረ-ብሄር ከመመስረቷ በፊት ህዝቡን የሚያስተሳስረው ስነ-ልቦናና ባህል አልነበረውም ማለት አይደለም። ለማለት የምፈልገው በእኛ አገር ምሁራን ዘንድ የአንድን አገር የብዙ ሺህ ዓመታት ታሪክ ከህብረ-ብሄር ምስረታ ጋር የማምታት ችግር ስላለ የታሪክን ሂደትና የህብረ-ብሄርን አገነባብና ቅድመ-ሁኔታዎችን ግንዛቤ ውስጥ የማስገባት ችግር አለብን።
ለማንኛውም በአጠቃላይ ሲታይ የሶስት ሺህ ዓመት ታሪካችንን ወደ ጎን ትተን ከአክሱም አገዛዝ መመስረት ጀምሮ የተከናወኑትን ባህላዊ ለውጦች ስንመለከት ከሞላ ጎደል በኋላ ላይ ዘመናዊ ኢትዮጵያ ተብላ ለመጠራት ለቻለችው በዚያን ጊዜ መሰረት እንደተጣለ የሚታወቅ ጉዳይ ነው። የተለያዩ አገሮችም በተለያየ መልክ ይህን ዐይነቱን ሂደት በመጓዝ ነው ወደ ህብረ-ብሄርነት ለመለወጥና ህዝባቸውም እንደ አንድ ህዝብ ለመጠራት የቻለው። ከአንትሮፖሎጂ ወይም ከሰው ልጅ የዕድገት ሂደት አንፃር ስንመለከተው ማንኛውም ማህበረሰብ ከዝቅተኛ ደረጃ በመነሳት ነው ወደተሻለና ወደተወሳሰበ ስርዓት ሊለወጥ የሚችለው። ይሁንና አንድ ማህበረሰብ ከዝቅተኛ ወደ ተሻለ የህብረተሰብ አደረጃጀት ለመሸጋገር እንዳይችል ከውስጥ በሚነሱና ለዕድገት መሰናክል በሚፈጥሩና ከውጭ በሚመጡ ወራሪ ኃይሎች ቀጥተኛ የሆነው የዕድገት ጉዞው ሊሰናከልበት ይችላል። በዚህ ላይ ደግሞ ስልጣን ላይ ያሉ አገዛዞች ቀድሞውኑ ከነበረው ስርዓት ጋር ስለሚለማመዱና ከነበረው ስርዓት ለመላቀቅ ስለሚያቅታቸው አዳዲስ ለዕድገት የሚያመቹ መሰረቶችን ለመጣል የማይችሉበት ሁኔታ አለ። በሌላ አነጋገር፣ በማንኛውም ህብረተሰብ ውስጥ ህዝብን የሚያስተሳስር ሰፋ ያለ ዕድገት ሊመጣ የሚችለው በሙከራና በልምድ፣ እንዲሁም ደግሞ ከውስጥ የተገለጸላቸው፣ አርቀው ማሰብ የሚችሉና ንቃተ-ህሊናቸው ከፍተኛ የሆኑ አዳዲስ ኃይሎች ሲፈጠሩ ብቻ ነው። ስለሆነም የአንድ ማህበረሰብ ተከታታይ ዕድገት በብዙ ነገሮች ሊሰናከልና ህዝቡም ፈጣሪ እንዳይሆን ለመደረግ የሚችልበት ሁኔታ አለ። ለምሳሌ የዮዲት ጎዲትን ወረራ ስንመለከት የአክሱምን አገዛዝና ስልጣኔ ለአርባ ዓመታት በተከታታይ በከፍተኛ ቂምበቀል ለማውደም ችላለች። የአክሱም አገዛዝ በዚያው መልኩ ወይም ደግሞ በተሻለ መልክ እንዳይቀጥል ከፍተኛ መሰናክል ፈጥራለች ማለት ይቻላል። በአክሱም አገዛዝ ዘመን ከግሪክ ስልጣኔ ጋር የነበረው ግኑኝነትና፣ የግሪክ ሊቃውንትም አክሱም ድረስ መጥተው ያስተምሩ የነበረው ዕውቀት በዚያው ሊወድም ችሏል። በኋላ ላይ በዛግዌና በስለሞናዊ ዲይናስቲ አገዛዞች በዮዲት ጎዲት የወደመው የአክሱም ስልጣኔ ተከታታይነት እንዲኖረው እንደገና ሲቋቋም፣ በተለይም በሰለሞናዊ የአገዛዝ ዘመን የፊዩዳሉ ስርዓት መሰረት ሊጣል ችሏል። ይህም ጉዳይ የጊዜው መንፈሳዊ አስተሳሰብ(Zeit Geist) ስለነበር ኢትዮጵያችን ከዚህ ቀድማ በመሄድ ሌላ ስርዓተ-ማህበር ለመመስረት በፍጹም አትችልም ነበር። ይህ ዐይነቱ የፊዩዳል ስርዓት በተለይም በአውሮፓ ምድር እ.አ..አ ከአስረኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ የተሰፋፋና እስከ አስራዘጠነኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ የዘለቀ ስርዓት ነበር። በሌላ ወገን ግን የኢትዮጵያው ፊዩዳሊዝም ከውጭ በመጣ ልዩ ልዩ አስተሳሰቦችና በሩቅ ንግድ አማካይነት በሚመጡ የፍጆታ ዕቃዎች ጋር ለመተዋወቅ ባለመቻሉ የአስተሳሰብ ለውጥና የአስራር፣ ወይም ደግሞ አዳዲስ ነገሮችን የመፍጠር ዕድል ለማግኘት በፍጹም አልቻለም። በተለይም የአውሮፓ ፊዩዳሊዝምና የካቶሊክ ሃይማኖት በአረቦች አማካይነት ከግሪክ በመጣው ፍልስፍና፣ የተፈጥሮ ሳይንስና ማቲማቲክስ፣ እንዲሁም ሌሎች ዕውቀቶች ጋር በመጋጨቱ በዚያው በድሮው መልኩ ሊቀጥል አልቻለም። የተገለጸላቸው ምሁራን በከፍተኛ የጭንቅላት ስራ ከግሪክ የመጣውን ዕውቀት በመተርጎመና በማስፋፋት ቀስ በቀስ፣ ግን ደግሞ በእርግጠኝነት በአውሮፓ ምድር ውስጥ ለውጥ ሊመጣ ችሏል። በተለይም በ15ኛው ክፍለ-ዘመን በጀርመናዊ ጉተንበርግ የማባዣ ማሽን ሲፈጠርና ስራ ላይ ሲውል ዕውቀትን በአገርም ሆነ በአህጉር ደረጃ ማስፋፋት ቀላል ሊሆን ችሏል። ይህም የሚነግረን በአንድ ህብረተሰብ ወይም ማህበረሰብ ውስጥ ለውጥ እንዲመጣ ከተፈለገ ተቀባይነት ከነበረውና ለሁለ-ገብ ዕድገት እንቅፋት ከሆነው ልማዳዊ ዕውቀት(Conventional Wisdom) የግዴታ መላቀቅ ያስፈልጋል። በተሻለ ዕውቀትና ጥያቄም ሊያስጠይቅና ጭንቅላትን ለማዳበር በሚችል ዕውቀት አማካይነት ብቻ ነው ንቃተ-ህሊናን ማዳበር የሚቻለው። አንድ ሰውም ሆነ ማህበረሰብ ንቃተ-ህሊናው ሲዳብርና ጥያቄ ሲጠይቅና አዳዲስ ነገሮችን ሲፈጥር ብቻ ነው ሰው መሆኑን ማወቅ የሚችለው። ከዚህም ባሻገር አንድ ማህበረሰም እንደማህበረሰብ ሊገነባ የሚችለውና ውስጠ-ኃይልም ሊያገኝ የሚችለው የስራ-ክፍፍል(Division of Labour) ሲዳብር ብቻ ነው። በስራ-ክፍፍልም መዳበር ነው የገበያ ኢኮኖሚ ሊስፋፋ የሚችለው። የፈጠራ ስራ ሊዳብርና በተለያዩ የስራ መስኮች መሀከል በገንዘብ አማካይነት የንግድ ልውውጥ ሲካሄድ ህብረተሰብአዊ መተሳሰር ሊፈጠር ይችላል። ገንዘብ የመገበያያ መሳሪያ ከመሆን በማለፍ ወደ ካፒታል ሲለወጥ ብዙ ገንዘብ ማከማቸት የቻለው አዳዲስ መሳሪያዎችን በመግዛትና በመትከል ለኢኮኖሚው ዕድገት ከፍተኛ ዕምርታን ይሰጠዋል። ማምረት፣ መሸጥና የፍጆትን ዕቃ ገዝቶ መጠቀም፣ እንዲሁም ገንዘብ ማግኘት እንደባህል ሲወሰዱ ልዩ ዐይነት ህብረተሰብአዊ ኃይል ይፈጠራል ማለት ነው።
ከዚህ ዐይነቱ አጭር ማብራሪያ ስንነሳ ኢትዮጵያ ለብዙ መቶ ዓመታት ከውጭው ዓለም ጋር በዕውቀትና በሩቅ ንግድ አማካይነት ምንም ዐይነት ግኑኝነት ስላልነበራት፣ ለምሳሌ ለኢንዱስትሪ አብዮት የሚሆን የዕደ-ጥበብ ሙያና የእርሻው መስክ ጋር ሊተሳሰርና ለውስጥ ገበያ መዳበር ሊሆን የሚችል የፈጠራ ስራ ለመስፋፋት ባለመቻሉ በተለይም የሰሜኑ ክፍል በአብዛኛው ጎኑ ፊዩዳላዊና፣ የሚመረተውም ምርት ከእጅ ወደ አፍ ብቻ የሚሆን ነበር ማለት ይቻላል። በዚህም ምክንያት የተነሳና በእርሻው መስኩና በዕደ-ጥበብ ሙያተኞች መሀከል ምንም ዐይነት ግኑኝነት ወይም የንግድ ልውውጥ ስላልነበረና፣ የዕደ-ጥበብ ሙያም እንደ ዝቅተኛ ወይም አፀያፊ ነገር ይታይ ስለነበር የገበያ ኢኮኖሚና፣ እንዲሁም በገንዘብ ላይ የተመሰረተ የንግድ ልውውጥ ሊዳብሩና ህብረተሰቡን ሊያስተሳስሩ አልቻሉም። ይህ በራሱ ደግሞ ከሶስዮሎጂ አንፃር በሁሉም አቅጣጫ ማህበራዊ እንቅስቃሴ(Social Mobility) እንዳይፈጠር አገደ። በሌላ አነጋገር፣ ከአንጥረኛ ወደ ከበርቴው አምራችነት፣ እንዲሁም ከነጋዴ ወደ ከበርቴያዊ አምራችነት ለመለወጥ በፍጹም አይቻልም ነበር። በተለይም ከተማዎችና መንደሮች ጥበባዊና ስርዓት ባለው መልክ ለመገንባት ባለመቻላቸውና፣ ይህንን ለማድረግ የሚችል መንግስታዊ ተቋም ስላልነበረ፣ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ከአዳዲስና ጭንቅላትን ከሚያድሱ ነገሮች ጋር የመጋጨትና ወደ ተሻለ የዕድገት ደረጃ የመሸጋገር ዕድል ሊያገኝ በፍጹም አልቻለም። በዚሁም ምክንያት የተነሳ በህዝብረተሰቡ ውስጥ ግልጽነት ያለው የስራ-ክፍፍልና የገበያ ተቋም ለመዳበር አልቻለም።
ይህ ፊዩዳላዊ የአሰራር ስልትና አስተሳሰብ በአፄ ምኒልክ ዘመን ዘመናዊ ባህርይ እንዲኖረው አንዳንድ ነገሮች ቢለወጡምና ከውጭም አንዳንድ ነገሮች እንዲገቡ ቢደረግም በውስጥ በነበረው ውስንና ደካማ የሆነ ምሁራዊ ኃይል የተነሳ ከፍተኛ ምጥቀትን ሊያመጣ አልቻለም። ወደ ውስጥ ህብረተሰቡን የሚያስተሳስር ከተማዎችም ሆነ መንደሮች ሊገነቡ በፍጹም አልተቻለም። ለገበያ ኢኮኖሚ ማደግና መስፋፋት በጣም አስፈላጊ የሆነው ወደ ውስጥ ያተኮረ የመንገድና የባቡር ሃዲድ ስራዎች ተግባራዊ ለመሆን ባለመቻላቸው ገበሬው እህሉን ወደ ገበያ የሚያመጣው በአህያ ወይም በበቅሎ እየጫነ ነበር። ይህ ጉዳይ የአፄ ምኒልክ ስህተት ሳይሆን ከላይ እንዳልኩት በጊዜው በነበረው በጣም ደካማ የሆነ ንቃተ-ህሊና ምክንያት የተነሳና የዕድገትንንም ትርጉም የተረዳ ኃይል ባለመኖሩ ኢትዮጵያን ወደ ተሟላ ህብረ-ብሄር ለመለወጥና ጠቅላላውን ህዝብ እንደ አንድ ህዝብ ለማስተሳሰርና ብሄራዊ ባህርይና ስሜት እንዲኖረው ለማድረግ በፍጹም አልተቻለም።
ወደ አፄ ኃይለስላሴው የአገዛዝ ዘመን ስንመጣ አንዳንድ የጥገና ለውጦች ቢካሄዱም በጊዜው ባለማወቅ የተነሳ ተግባራዊ የሆነው አብዛኛውን ጊዜ በፍጆታ ምርት ላይ ያተኮረው የኢንዱስትሪ ተከላ(Import-Substitution- Industrialization) ምክንያት የተነሳ ርስ በርሱ የተሳሰረ የውስጥ ገበያን ማስፋፋት በፍጹም አልተቻለም። በቲዎሪውና ይህንን የኢንዱስትሪ ፖሊሲ በሚያማክሩ የውጭ ኤክስፐርቶች ዕምነት በአንድ አገር ውስጥ በተወሰኑ አካባቢዎች ይህ ዐይነቱ የኢንዱስትሪ ተከላ(Growth Pole Strategy) ተግባራዊ ከሆነ ወደ ሌሎች አካባቢዎች በመስፋፋት(Trickle Down Effect) ቀስ በቀስ ግን ደግሞ በእርግጠኝነት አብዛኛው ህዝብ ተጠቃሚ በመሆን ዘመናዊ አስተሳሰብን ያዳብራል ይሉናል። የዘመናዊ የፍጆታ ምርት ደግሞ እንደ ኮካኮላ፣ ስፕራይትና ሚሪንዳ፣ የስኳር ፋብሪካ፣ የቢራ ፋብሪካ፣ የሲጋራ ፋብሪካ፣ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎችና እነዚህን የመሳሰሉ ቀደም ብለው በአገር ቤት ውስጥ የማይመረቱ ምርቶች ናቸው ኢንዱስትሪዎችን ከውጭ በማስመጣት ማምረት የተጀመረው። ይህም ማለት ይህ ዐይነቱ የኢንዱስትሪ ፖለቲካ ሲካሄድ የሰፊውን ህዝብ መሰረታዊ ፍላጎቶች፣ ለምሳሌ፣ ንጹህ ውሃ፣ የተሟላ ዲዬት፣ መኖሪያቤት፣ የጤና መስክና መሰረታዊ ትምህርትን ማስፋፋትና ፍላጎቱን ማሟላት ሳይሆን 5% የሚሆነውን የህብረተሰብ ክፍል ፍላጎት ብቻ የሚያሟላ ነበር። ስለሆነም የተወሰነው የህብረተሰብ ክፍል ይህንን ዐይነቱን የፍጆታ አጠቃቀም ሲለምድና ባህሉ ሲያደርገው ዘመናዊ ይሆናል። ሲጋራ ሲያጨስ፣ ኮካኮላ ሲጠጣና ብስኩት ሲበላ በዚህ መልክ ዘመናዊነቱ ይገለጻል። በአሜሪካኖች የዕድገት ፖሊሲ አውጭዎች ዕምነት ለአንድ አገር ዕድገት የሚያስፈልገው በመጀመሪያ ደረጃ መንፈስን በማደስ ቀስ በቀስ ግን ደግሞ በእርግጠኝነት ከታች ወደ ላይ የሚያድግና የሚስፋፈ ሁለ-ገብ የሆነና የሰፊውን ህዝብ ፍላጎት የሚያሟላ የኢኮኖሚና የህብረተሰብ ዕድገት ፖሊሲ መከተል ሳይሆን በዚህ ላይ አትኩሮ ከተደረገ ከረዢም ጊዜ አንፃር ዕድገት ይመጣል ይሉናል። በሌላ ወገን ደግሞ ይህ ዐይነቱ ዕድገት ምን እንደሚመስልና በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የሚገለጽ ዕድገት ይሁን አይሁን በፍጹም አልተናገሩም። ከሶስይሎሎጂና ከሳይኮሎጂ አንፃር የአሜሪካንና የተቀረውን የምዕራቡን ካፒታሊስት አገሮች የኤክስፐርቶች ምክር ስንመረምረው ይህንን ዐይነቱን የኢንዱስትሪ ፖሊሲ የተከተሉ አገሮች በሙሉ ታታሪና ፈጣሪ የሆነ(Pioneer Spirit) ያለው አዲስ የሆነ የህብረተሰብ ክፍል በፍጹም ሊፈጥሩ አልቻሉም። በ20ኛው ክፍለ-ዘመን በስድሳዎቹ፣ በሰባዎቹና በሰማኒያዎቹ ዓመታት ይህንን ዐይነቱን የተኮላሸ የዕድገት ፖሊሲ ይቃወም የነበረው የታወቀው የግብጹ ኢኮኖሚስት ፕሮፌሰር ሳሚር አሚንና ሌሎችም ምሁራን እንዳሉት በአብዛኛዎቹ የሶስተኛው ዓለም አገሮች ፈጣሪና ታታሪ ከሆነ የህብረተሰብ ኃይል ይልቅ ሉምፐን ከበርቴ(Lumpenbourgeoisie) ነው ሊፈጠር የቻለው። ስለሆነም በአገራችንም ሆነ በአብዛኛዎቹ የአፍሪካና የደቡብ አሜሪካ አገሮች ለሌላው የህብረተሰብ ክፍል ምሳሌና መሪ ሊሆን የሚችል ምሁራዊና ፈጣሪ የሆነ የህብረተሰብ ክፍል ብቅ ሊል በፍጹም አልቻለም። ከህሊና ሳይንስ አንፃር ደግሞ በጣም አመጸኛና የተቀረውን የህብረተሰብ ክፍል የሚንቅ ኃይል ሊፈጠር ነው የቻለው። በህዝቡና በባህሉ ላይ የሚተማመን ሳይሆን በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ላይ የሚተማመንና እሱንም የሚያመልክ ኃይል ነው ሊፈጠር የቻለው።
በተሳሳተ የኢኮኖሚ ዕድገት ፖሊሲ አማካይነት ከ1950ዎቹ ዓመታት ጀምሮ በአገራችን ምድር የተፈጠረውን አጠቃላዩን የኢኮኖሚና የህብረተሰብ አወቃቀር ሁኔታ ስንመለከት የአፄው አገዛዝ በውጭ ኤክስፐርቶች ነን በሚሉ የውጭ አገር ሰዎች በመመከር የተሳሳተ የኢንዱስትሪ ፖለቲካ በመከተሉ የተዘበራረቀ ሁኔታ ነው ሊፈጠር የቻለው። ግልጽነት ካለው የገበያ ኢኮኖሚና ሰፋ ባለ የስራ-ክፍፍል ላይ ከተመሰረተ የኢኮኖሚ ክንዋኔ ይልቅ ርስ በርሳቸው ሊያያዙና ሊደጋገፉ የማይችሉ የተበጣጠሱና የተዝረከረኩ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ነው ሊፈጠሩ የቻሉት። እነዚህም በራሳቸው የሰፊውን ህዝብ አዕምሮ ከመሰብሰብና በተደራጀና በአርቆ-አሳቢነት መንፈስ እንዲንቀሳቀስ ከማድረግ ይልቅ አስተሳሰቡ እንዲዘበራረቅ ነው ለማድረግ የበቁት። ለተሟላ ወይም ለሁለ-ገብ የኢኮኖሚ ዕድገት መሰረት የሚሆነው የማሽን ኢንዱስትሪና የብረታ ብረት ማቅለጥ አትኩሮ ስላልተሰጣቸው ወይም በሚገባ ስለማይታወቁ በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን ተግባራዊ የሆነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ለችርቻሮ ንግድ (Informal Sector) የሚያመች ነበር። በዚህ ዐይነቱ በተዝረከረከና ዘመናዊ(Modern Sector) እየተባለ በሚጠራው የኢኮኖሚ ዘርፍ መሀከል ምንም ዐይነት ግኑኘነት(Linkages) ባለመኖሩ አብዛኛው ህዝብ ለፍጆታው ወይም የሚጠቀምበትን የሚገዛው ዘመናዊ በሚባሉ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ የሚመረቱ ምርታ ምርቶችን ሳይሆን ከኢንፍርማል ገበያና ገበሬው ከአፉ እየቀነስ ወደ ገበያ እያወጣ የሚሸጠውን እህል ነው። ይህም ማለት በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን ሰፋ ያለ ርስ በርሱ የተሳሰረና በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመረኮዘ የውስጥ ገበያን ማዳበር በፍጹም አልተቻለም። ከዚህም በላይ በጣም ዘግይቶ በአንዳንድ አካባቢዎች ዘመናዊ የሆነ የእርሻ አሰራር(Green Revolution) ተግባራዊ ቢሆንም በመሰረቱ ይህ ዐይነቱ አካሄድ የኢትዮጵያን ህዝብ የምግብ ችግር ሊፈታው በፍጹም አልቻለም። ይህን የመሰለው የዘመናዊ እርሻ መስፋፋት በአብዛኛዎቹ አካባቢዎች በራሱ ማህበራዊ ቀውስን ነው ሊፈጥር የቻለው። ምክንያቱም የዚህ የዘመናዊ እርሻ ተጠቃሚዎች ትናንሽ ገበሬዎች ሳይሆኑ ትላልቅ የእርሻ መሬት ያላቸውና መሬታቸውንም በትራክተር ማረስ የሚችሉ ብቻ ስለሆነ ብድር ማግኘትና ማዳበሪያ መግዛት የሚችሉት ትላልቅ የመሬት ከበርቴዎች ነበሩ። ከዚህም በላይ ትናንሽ ገበሬዎች ከመሬታቸው ለመፈናቀል ስለተገደዱ ወደ አካባቢውና ወደ ትላልቅ ከተማዎች በመሄድ ራሳቸውን ለመደጎም ሲሉ የግዴታ ባልባሌ ስራዎች ላይ መሰመራት ነበረባቸው። ባጭሩ ቲዎሪውና አማካሪዎች እንደነገሩን የአፄው አገዛዝ ይህን የመሰለውን የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ስለተከተለ በአገራችን ምድር የተስተካከለና ሰፊውን ህዝብ የሚጠቅም ሁለ-ገብ የሆነ የኢኮኖሚ ዕድገት በፍጹም ሊዳብር አልቻለም። በአንፃሩ የኢንዱስትሪው ፖሊሲ የተዘበራረቁ ሁኔታዎችን መፍጠሩ ብቻ ሳይሆን በጊዜው በአንዳንድ አካባቢዎች ጥራዝ ነጠቅ አስተሳሰቦች ስለተከሰቱ በተለይም ሰፊው ህዝብ የመገፋት ስሜት ይታይበት ነበር።
የህዝብ ቁጥር እየጨመረና አዳዲስ የስራ ፈላጊ ኃይል ሲፈጠር በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን ተግባራዊ የሆነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ይህንን አዳዲስ የሰው ኃይልና የሰፊውን ህዝብ ፍላጎት ማሟላት የሚችል አልነበረም። በዚህ ዐይነት ሁኔታ ውስጥ ደግሞ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ፣ እንዲሁም ባህላዊ ቀውሶች መፈጠራቸው የማይቀር ነው። አፄ ኃይለስላሴና አሪስቶክራሲው፣ የበለጠ በተሻለና ምርታማ በሆነ፣ እንዲሁም በዳበረና ሰፋ ያለ የስራ መስክ በሚከፍት በሳይንስና በቴክኖሎጂ በሚደገፍ ኢኮኖሚ ላይ ከመመካትና፣ ይህንንም በየጊዜው ዘመናዊ ተቋማትን በማስፋፋት ከማሻሻልና የሰፊው ህዝብ አለኝታ ለማድረግ ከመሞከር ይልቅ ይመኩ የነበረው በፀታው ኃይል፣ በሚሊታሪው፣ በፖሊሱ፣ ዘመናዊ ቢሮክራሲ በመባል በሚታወቀው፣ ይሁንና ደግሞ ውስጠ-ኃይሉና የማሰብ ኃይሉ ደካማ በሆነውና በፊዩዳሉ መደብ ነበር። የግዴታ ሆኖ አንድ ህብረተሰብ ምርታማ ካልሆነና ሰፊውም ህዝብ የሚመካበት ሰፋ ያለ የኢኮኖሚ አውታር ከሌለው ማንኛውም አገዛዝ በድሮው መልኩ ሊቀጥል በፍጹም አይችልም። ይህ ዐይነቱ ሁኔታ በፈረንሳይ በ18ኛው ክፍለ-ዘመን፣ በጀርመን በ19ኛው ክፍለ-ዘመን፣ በራሺያ ደግሞ በ20ኛው ክፍለ-ዘመን የተከሰተና አገዛዞችን የገለበጠና ማህበራዊ መመሰቃቀልም ያመጣ ጉዳይ ነው። ስለሆነም በአገራችን ምድር እ.ኢ.አ በ1966 የፈነዳው አብዮት የታሪክ ግዴታ ነበር ማለት ይቻላል።
እንደነ ፕሮፌሰር ሀብታሙና አቻሜለህ ታምሩ የመሰሳሉት የታሪክ ምሁራን በሶሻሊዝም ላይ ካላቸው ጥላቻ የተነሳ እንደሚያወሩት ሳይሆን እንደዚያ ዐይነቱ ደም መፋሰስ ሊከሰት የቻለው በመሰረቱ ይህ ጉዳይ ከንዑስ ከበርቴው መደብ ጭንቅላት አለመብሰል ጋር የሚያያዝና እንደዚህ ዐይነት ማህበራዊ ውዝግብ ሲፈጠር በፖለቲካ ጥበብ ለማስተናገድ የሚችል ኃይል ለመፈጠር ባለመቻሉ ብቻ ነው። የሶሻሊዝም ርዕዮተ-ዓለም ከባህላችን ጋር የማይጣጣም ነው፣ በዚህም ምክንያት የተነሳ ነው እንደዚያ ዐይነት ውዝግብ ሊፈጠር የቻለው የሚለው አነጋገር በፍጹም ተቀባይነት የለውም። ምክንያቱም ስለሶሻሊዝም በተጻፉ አያሌ መጽሀፎች ውስጥ አንዳችም ቦታ ላይ ሰውን ስትገድልና ደም ስታፈስ ብቻ ነው አብዮት የሚሰምረው የሚል የተጻፈ ነገር የለም። ሶሻሊዝም የሚባለው ጽንሰ-ሃሳብ ቃል በቃል ሲተረጎም የጋርዮሽ ማለት ሲሆን፣ በአገራችን ምድር አብሮ ማረስ፣ እየተጋገዙ ሰብሎችን ማጨድና መሰብሰብ፣ እንዲሁም በበዓላት ቀናት አብሮ መብላትና መጠጣት፣ ጽዋ መጠጣት፣ እንዲሁም ቤተክርስቲያን መሄድ የተለመደ ጉዳይ ነው። በሌላ ወገን ሶሻሊዝም ከውጭ የመጣ ርዕዮተ-ዓለምና ከባህላችን ጋር የሚሄድ አይደለም የሚባል ከሆነ ደግሞ ኢትዮጵያን ዘመናዊ ማድረግ ያስፈልጋል ከተባለበት ጊዜ ጀምሮ ከባህላችን ጋር የማይጣጣሙ ጥሩም ሆነ መጥፎ ነገሮች ወደ አገራችን ሰተት ብለው ገብተዋል። የምንማረው ትምህርት እንዳለ ከውጭ የመጣ ነው። በዚያው መጠንም አነጋገራችንና አካሄዳችን፣ እንዲሁም አለባበሳችን ተቀይሯል። በተለይም ክ1950ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ጀምሮ መደነሻ ቦታዎች ተስፋፍተዋል። መጠጥ ቤቶችና ሆቴልቤቶችም በየቦታው ተከፍተዋል። ውስኪና ኮኛክም መጠጣት የተለመደና፣ አሁን ደግሞ በተለይም የንዑስ ከበርቴው ባህላዊ መጠጥ ሊሆኑ ችለዋል። ሻይቤቶች መከፈት የተጀመሩትና የሴተኛ አዳሪነትም ተግባር እየተስፋፋ የመጣው አገራችን ዘመናዊ የሚባል ፖሊሲ መከተል ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ነው። ታዲያ በሶሻሊዝም ላይ ዘመቻ ሲካሄድ ለምንስ በእነዚህ ከላይ በተጠቀሱት ነገሮች ላይ ዘመቻ አይካሄድም። ስለባህል ጉዳይ በምናወራበት ጊዜ በመጀመሪያ ደረጃ፣ በአጠቃላይ ባህል የሚባለው ነገር አውቆም ሆነ ሳይታወቅ በሰዎች ጭንቅላት ወይም የማሰብ ኃይል የሚፈጠር ነው። በሁለተኛ ደረጃ፣ የሰው ልጅ ውስጠ-ኃይል ስላለውና ሳያስብም ሆነ እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ የማስበ ኃይሉን በመጠቀም የአመራረት ሁኔታውን ሲለውጥና ከአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ጋር ሲተዋወቅ በዚያው መጠንም አዳዲስ ባህሎችን ማዳበር ይችላል። ስለሆነም ባህል የሚባለው ነገር አንድ ጊዜ ከተፈጠረና በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ከተለመደ ይህ ማለት ግን እንደቋሚ(Static) ሆኖ ይቀራል ማለት አይደለም። አኗኗራቸውንና ባህላቸውን መቀየር የማይችሉት እንስሳዎች ብቻ ናቸው።
ሁለቱ ምሁራን ስለሶሻሊዝም መጥፎነት ሲያወሩ የካፒታሊዝምን ዕድገትና ያመጣውን ህብረተሰብአዊ መመሰቃቀልና፣ ከካፒታሊዝም ጋር በመያያዝ በሶስተኛው ዓለም አገሮች ላይ የደረሰውን እንደ ባርያ ንግድና የቅኝ-ግዛት ሁኔታና ብዝበዛ በደንብ ቢያጠኑና ቢያገናዝቡ ኖር እንደዚህ ዐይነቱ የተሳሳተ ድምደማ ላይ ባልደረሱ ነበር። በተጨማሪም የአንደኛውና የሁለተኛው ዓለም ጦርነቶች ከካፒታሊዝም መስፋፋት ጋር በቀጥታ የሚያያዙ ናቸው። ይህም ማለት ቀደም ብሎም ሆነ በአሁኑ በ21ኛው ክፍለ-ዘመን ጦርነት ራሱ ባህላዊ ለመሆን በቅቷል። ይህ ዐይነት በተለይም በሶስተኛው ዓለም ተብለው በሚጠሩ አገሮች ውስጥ እየተስፋፋ የመጣው ጦርነትና የሰውን ኃይልና ጥሬ-ሀብትንና ገንዘብን የሚያወድመው ጦርነት በቀጥታ የሚያያዘው ከካፒታሊዝም መስፋፋት ጋር ነው። በዚህ መልክ ነው በተለይም በካፒታሊስት አገሮች ውስጥ ከፍተኛ የሀብት ክምችት(Capital Accumulation) የሚፈጠረው። ይህ በራሱ የሚያረጋገጠው ደግሞ ካፒታሊዝም በራሱ የካፒታሊስት አገሮችንም ሆነ የሶስተኛውን ዓለም አገሮችን የፖለቲካ ኤሊት በፍጹም አርቆ-አሳቢና ሰላምን ፈላጊ እንዳላደረጋቸው ነው። በሁለተኛው ዓለም ጦርነት በአውሮፓ ምድር ወደ 50 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ህይወቱ ተቀስፏል፤ ከተማዎች ወድመዋል። ባጭሩ በሶሻሊዝም ላይ የሚደረገው የቀኞች ዘመቻ መሰረተ-ቢስና ለአገር ግንባታ አደገኛ የሆነ አካሄድ ነው። ከመጀመሪያውኑ ምሁራዊ ውይይት እንዳይካሄድ የሚያግድ ፀረ-ሳይንስና ፀረ-ቴክኖሎጂ አስተሳሰብ ነው። ጭንቅላትን የሚያጨልምና አታስቡም የሚል ነው። በነገራችን ላይ ሁለቱ ምሁራን፣ ፕሮፌሰር ሀብታሙና አቻሜለህ ታምሩ ባህላችን ባልሆነው ኮምፒዩተርን በመጠቀምና ቪዲዮ በመቅረጽ ነው የተዛባና በሳይንስ ያልተደገፈ አስተሳሰባቸውን የሚያስፋፉት። ወደ አሜሪካ ምድርም የመጡት ባህላችን ያልሆነውን አውሮፕላንን በመጠቀም ነው።
ለማንኛውም ለአብዮቱ መፈንዳት ዋናው ተጠያቂዎች አፄ ኃይለስላሴና ቢሮክራሲው ናቸው። ምክንያቱም በጊዜው አፍጦ አግጦ የሚታየውን የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የፖለቲካ ቀውሶች ለመፍታት ባለመቻላቸው ነው። በሌላ ወገን ግን የተማሪው እንቅስቃሴ የታሪክ አጋጣሚ በመሆኑና ሌላም የነቃና የተደራጀ ኃይል ባለመኖሩ ማህበራዊ መሻሻል እንዲደረግ መታገሉ የታሪክ አጋጣሚና ግዴታ ሊሆን ችሏል። በጊዜውም ሌላ አማራጭ ቲዎሪ ስላልነበረ የሶሻሊዝምን ቲዎሪ መከተሉ የግዴታ ነበር። በእኔ ዕምነትና እንደተከታተልኩትም በተለይም የተማሪው ማህበር መሪዎች ለሶስዮሎጂና ለፖለቲካ ኢኮኖሚክስ ቲዎሪዎች አትኩሮ ስላልሰጧቸውና ስላላጠኑም የአብዮቱን ውጤቶች በዝግታና ስርዓት ባለው መንገድ ወደ ተግባር ለመመንዘር አልተቻለም። መደማመጥ ስላልተመደና ጊዜውም የአብዮት ዘመን እንጂ የምርምርና የጥናት አይደለም ይባል ስለነበር የአንዳንድ ድርጅቶችና መሪዎቻቸው ዋና ዓላማ ስልጣን ላይ በአቋራጭ ለመውጣት ነበር። በሌላ ወገን ደግሞ ካለበቂ የቲዎሪና ሳይንሳዊ ጥናት አብዮት እንዴት እንደሚካሄድ አንዳንድ የተማሪው ማህበር መሪዎች በፍጹም አልነገሩንም። በራሺያም ሆነ ቀደም ብሎ በጀርመን፣ ኋላ ደግሞ በቻይና ለተሻለ የህብረተሰብ ስርዓት መታገል አለብን ብለው የተነሱ ምሁራን የየህብረተሰቦቻቸውን አወቃቀርና የኢኮኖሚ ሁኔታ በሚገባ ሳያጠኑ ወደ አብዮት ወይም ወደ ሶሻሊዝም እናምራ አላሉም። በተለይም በሌኒን የካፒታሊዝም ዕድገት በሩሲያ(The Development of Capitalism in Russia) በሚል ርዕስ የተጻፈውን መጽሀፍ መመልከቱ ከፍተኛ ግንዛቤ ሊሰጠን ይችላል። እነማርክስም ለሶሻሊዝም ከመታገላቸው በፊት አትኩሮ የሰጡት በመጀመሪያ ደረጃ የካፒታሊዝምን አፀናነስ፣ ዕድገትና የውስጥ አሰራር በማጥናት ነበር። በተለይም የካርል ማርክስን ዳስ ካፒታል የሚባለውን የሶስት ቅጽ መጽሀፎችና ሰርፕለስ ቫሊዩ የሚባሉትን መጽሀፎቹን መመልከቱ ብቻ በቂ ነው። የካርል ማርክስ ስራዎችም ከሰላሳ ዓመት በላይ የፈጁ ጠልቅ ያሉ የምርምር ውጤቶች ናቸው። ይህም የሚያረጋግጠው ሌኒን እንደሚለው ካለቲዎሪ ምንም ነገር ተግባር ወደ ተግባር ሊመነዘር በፍጹም አይችልም ። በመጀመሪያ ደረጃ የአንድ አገርና የዓለም የፖለቲካና፣ እንዲሁም የኢኮኖሚ ሁኔታን በቲዎሪ ደረጃ መብላላትና ክርክርም እንዲደረግባቸው ያስፈልጋል። ይህ ብቻ ሲሆን የአንድን አገር ሁለመንታዊ ችግር በመረዳት ተቀራራቢና ተግባራዊ የሚሆን መፍትሄ ማግኘት ይቻላል።
ኤፍሬም ማዴቦ ሊነግረን እንደሚፈልገው በአብዮቱ ዘመን ተግባራዊ የሁኑት የመሬት ለአራሹ መታወጅና በጊዜው የነበሩትም ኢንዱስትሪዎችና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ህዝባዊና በመንግስት ቁጥጥር ስር በመሆናቸው የተነሳ በፍጹም ኢኮኖሚው አልተከሰከሰም። ምክንያቱም በአፄ ኃይለስላሴ የአገዛዝ ዘመን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተና የአገር ውስጥ ገበያን(Home Market)ለማስፋፋት የሚችል ስላልነበረና በተሰበጣጠረ መልክ የሚካሄድ ኢኮኖሚያዊ ክንዋኔ ስለነበር በአብዮቱ ወይንም በሶሻሊዝም ምክንያት የተነሳ ኢኮኖሚው ለመከስከስ ቻለ የሚለው አነጋገር በሳይንስ ሊረጋገጥ የሚችል አይደለም። በጊዜው የነበረውን አጠቃላዩን የኢኮኖሚና የህብረተሰብአችንን አወቃቀር ሁኔታ ስንመለከት እዚያ በዚያው ከእጅ ወደ አፍ የሚሆን(Subsistence Economy)የአስተራረስ ዘዴ፣ የዘላን አኗኗር ወይም በከብት እርባታ(Nomadic way of Life) ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ፣ በባላባቱ ቁጥጥር ስር የሚካሄድ የአስተራረስ ዘዴ፣ ይሁንና ግን በትራክተር የማይታረስ፣ ዘመናዊ የሆነና በደንብ ያልተስፋፋ የእርሻ መስክ፣ ዘመናዊ የሆነ ኢንዱስትሪና ኢንፎርማል ሴክተር ብለን የምንጠራው፣ እነዚህ ሁሉ በጊዜው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ስርዓት መገለጫዎች ስለበሩ ኤፍሬም ማዴቦ ሊያስተምረን እንደሚሞክረው በዚህ መልክ የሚገለጸው ኢኮኖሚ ሊከሰከስ አይችልም። ስለሆነም እነዚህን የተሰበጣጠሩ የአኗኗርና የአስተራረስ ዘዴዎች በማጠቃለል በመቅጽበት ወደ ሶሻሊስታዊ ስርዓት ማምራት በፍጹም አይቻልም። ይሁንና ግን አንዳንድ ወደ ኋላ የቀሩ አገሮች በመጀመሪያ ራሺያ በ20ኛው ክፍለ-ዘመን፣ በኋላ ደግሞ ቻይና ከኋላ መያዝ(Catching up Strategy) የሚለውን ስትራቴጂ በመከተል ተዝረክርኮ የነበረውን ኢኮኖሚያቸውንና የአኗኗር ስልታቸውን በሙከራና በልምድ መልክ ሊሰጡት ችለዋል። እንደዚያ ባያደርጉ ኖሮ ራሺያ በኋላ ደግሞ ሶቭየት ህብረት፣ በኋላ ደግሞ ቻይና የኢንዱስትሪ ባለቤት በመሆን ወደ ኃያልነት ባልተቀየሩ ነበር።
በአጠቃላይ የካፒታሊዝምን አስተዳደግ ስንመለከት ህዝብን ከቀየው በማፈናቀል፤ ለትላልቅ ፕሮጀክቶች በማሰማራት ነው ቀስ በቀስ ካፒታሊዝም ሊያድግ የቻለው። በአውሮፓ ምድር ካፒታሊዝም በዛሬው መልክ ሊያድግና ሊገለጽ የቻለው በ17ኛውና በ18ኛው ክፍለ-ዘመን መንግስታት ወደ ውስጥ ያተኮረ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመከተላቸውና ሰፊውንም ህዝብ ለከተማ ግንባታ፣ ለካናላይዜሽን፣ ለድልድዮች ግንባታ፣ በኋላ ላይ ደግሞ ለባቡር ሃዲድ ስራ በማሰማራት ነው። እነ አዳም ስሚዝና የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚስቶች ሊያሳምኑን እንደሚሞክሩት ካፒታሊዝም በረቀቀው እጅ (Invisible Hand) አማካይነት አይደለም በተለይም በመጀመሪያ ወቅት ሊዳብርና ሊስፋፋ የቻለው። በረቀቀው እጅ አማካይነትም በማንኛውም የአውሮፓ አገርም ሆነ በአሜሪካን ካፒታሊዝም ሊያድግ አልቻለም። ይሁንና ግን የኋላ ኋላ የተደራጀውንና እያደገ የመጣውን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በመጠቀም ግለሰብ ፈጣሪዎች ብቅ ብቅ ማለት ችለዋል። ይህም ቢሆን የመንግስታትን ጣልቃ ገብነት የጠየቀና በተለይም ደግሞ በማደግ ላይ ያሉ ኢንዱስትሪዎችን(Infant Indutries) ከውጭ በሚመጣ ተመሳሳይ ምርት እንዳይጠቁና ከገበያ ተስፈናጥረው እንዳይወጡ ኋላ ላይ የተነሱ እንደጀርመንና ሌሎችም የኢንዱስትሪ አገሮች ታሪፍ ነክና ታሪፍ ነክ ያልሆኑ እርምጃዎችን ይወስዱ ነበር። ይህም ማለት ከውጭ በሚመጣው ተመሳሳይ ምርት ላይ ታሪፍ መጨመር፣ በተጨማሪም ደግሞ ወደ ውስጥ የሚገባውን የፍጆታ ዕቃ መጠን መቀነስ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አንደኛው ስትራቴጂ ነበር። በዚህም ፖሊሲ አማካይነት ነው እንደ ጀርመን፣ አሜሪካ፣ ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ የመሳሰሉት አገሮች ለኢንዱስትሪዎቻቸው ዕድገትና ለውስጥ ገበያው መዳበር አመቺን ሁኔታ ለመፍጠር የቻሉት።
ስለሆነም በአገራችን ምድር በአብዮቱ ዘመን የተሞከረው ሙከራ ሰፊውን ህዝብ በማንቃትና በማደራጅት፣ እንዲሁም በትላልቅ ፕሮጀክቶች ላይ በማሰማራት ቀስ በቀስ ሰፊውን ህዝብ ሊጠቅም የሚችል ሰፋ ያለ ኢኮኖሚ ለመገንባት ነበር። የኋላ ላይ ለዚህ የሚያገለግል መለስተኛ የሆነ የዲሞክራቲክ አብዮትና ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች ሊያካትት የሚችል ፕሮግራም ተጽፎ በማቅረብ ጥሪ ቀርቧል። ይሁንና አንዳንዶች ይህንን መለስተኛና ለአገር ዕድገት ሊጠቅም የሚችለውን ፕሮግራም በመቃወም ወደ አጠቃላይ ጦርነት ላይ ለመሰማራት በቅተዋል። በዚህም አርቆ-አሳቢነት የጎደለው አካሄዳቸው ሁኔታውን የባስ ውስብስብ ለማድረግ በቅተዋል። ኤፍሬም ማዴቦ በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን የነበረውን የኢኮኖሚ ስርዓት ቢያጠናና የህዝቡን ኑሮ እየተዘዋወረ ቢያይ ኖሮ እንደዚህ ዐይነቱ ድምደማ ላይ ባልደረሰ ነበር። የሶሻሊስት ስርዓትም ተግባራዊ በመሆኑ አይደለም ኢኮኖሚው ሊዳከም ወይም ሊከሰከስ የቻለው። በእኔ ዕምነት የመሬት ለአራሹ መታወጁና ኢንዱስትሪዎችም በመንግስት ቁጥጥር ስረ መዋላቸው ትክክል ነበሩ የሚል ዕምነት አለኝ። የኢንዱስትሪዎችን አወቃቀርና አመራረት ለተመለከተ ደግሞ ለፈጠራ ስራና ለአዳዲስ ምርቶች የሚያመቹ አልነበሩም። በግል ባለሀብታሞች ቁጥጥር ስር ቢውሉ ኖሮ ከዚያ በላይ በማደግ ተዓምር ሊፈጥሩ የሚችሉ አልነበሩም። ምክንያቱም ከበስተጀርባ ሆኖ የሚያንቀሳቅሳቸውና ለተለያዩ ምርቶች የሚያገለግሉ ኢንዱስትሪዎችን ሊያመርቱ የሚችሉ የማሽን ኢንዱስትሪና የዲዛይን ማዕከል ስላለበር ነው። በሌላ አነጋገር፣ አንድ አገር የማሺን ኢንዱስትሪና ልዩ ልዩ የማምረቻ ኢዱስትሪዎችን ዲዛይን የሚያደርጉ ማዕከሎች ከሌሏት ለአጭር ጊዜም ሆነ ለረጅም ጊዜ የሚያገለግሉ የፍጆታ ዕቃዎችን በማምረት ርስ በርሱ የተሳሰረና ሰፋ ያለ የአገር ውስጥ ገበያ መገንባት አትችልም። ለማንኛውም ኤፍሬም ማዴቦ ሊያሳምነን እንደሚሞክረው ሳይሆን የአገራችን ሁኔታ የተወሳሰበና ለሶሻሊዝም የኢኮኖሚ ፖሊሲ መተግበር የሚያመች አልነበረም። ማርክስና ኤንግልስ እንደሚያስተምሩን በአንድ አገር ውስጥ ሶሻሊዝም እንዲተገበር ከተፈለገ የምርት ኃይሎች፣ ወይም ሳይንስና ቴክኖሎጂ በከፍተኛ ደረጃ ማደግ አለባቸው። በሁለተኛ ደረጃ፣ የሰፊው ህዝብ መማርና ንቃተ-ህሊና ማደግ ለሶሻሊዝም ዕድገት በጣም ወሳኝ ናቸው። እነዚህም መሰረተ-ሃሳቦች የተጻፉት በ19ኛው ክፍለ-ዘመን ካፒታሊዝም ወደ ኋላ በቀረ ሁኔታ ውስጥ በሚገኝበት ዘመንና ሰፊውም ህዝብ በከፍተኛ ደረጃ በሚበዘበዝበት ወቅት ነበር።
ወደ መሬት መወረሱ ጉዳይ ስንመጣ ችግሩ በተለይም የመሬት ለአራሹ ከመታወጁ በፊት ሰፋ ያለ የኢምፔሪካል ጥናት ከማጥናት ይልቅ በጅምላ ነው መሬት በመንግስት ቁጥጥር ስር እንዲውል የተደረገው። በተለይም ይህ ዐይነቱ አካሄድ ካፒታሊዝም በተዝረከረከ መልክ ወደ አገራችን ሲገባ ቀስ በቀስ ገንዘብ ማከማቸት የቻለው የተወሰነው የህብረተሰብ ክፍል መሬት እየገዛ ቡናንም ሆነ ሌሎች የእህል ሰብሎችን በማረስ ቀስ በቀስ ወደ ከበርቴነት እየተለወጠ በመምጣት ላይ ስለነበር መሬት በጅምላ ሲወረስ በማደግ ላይ የነበረውን ከበርቴያዊ መደብ እንዳለ ነው የመታው። በዚህም ምክንያት የተነሳ ሰላሳና አርባ ዐመታት እየለፋና እያደገ የመጣውን የህብረተሰብ ክፍል ከእነቤተሰቡ እንዳለ ወደ ድህነት ዓለም እንዲገፈተር ነው የተደረገው። በተለይም ወደ ደቡቡ ክፍል ከተማዎች ውስጥ(Absentee Landlord) በመኖር የሚያሳርስ አዲስ የህብረተሰብ ክፍል በመፈጠሩ አዲስ ዐይነት የአኗኗር ስልትና የፍጆታ አጠቃቀም ተለምዶ ነበር። አንዳንድ ጥራዝ ነጠቅ የተማሪው ማህበር መሪዎች እንደሚሉት ሳይሆን ገበሬውም እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ የተወሰነ ነፃነት(Relative Autonomy) የነበረው ስለሆነ ከተማዎች ውስጥ ሆኖ መሬት እንዲታረስለት የሚያደርገው የከበርቴው መደብ በገበሬው ላይ ቀጥተኛ ጫና ለማድረግ አይችልም ነበር። ይህም ማለት ወደ ደቡቡ የኢትዮጵያ ግዛት ስንመጣ የፊዩዳሉ ስርዓት የላላ ነበር ማለት ይቻላል። አንዳንዱ ባላባትም የተለያዩ አጋጣሚዎችን በመጠቀም በጉቦም ሆነ ቡናና ሰብል በመሸጥ ያካባተውን ሀብት በሬ በማረድና ሰፊውን ህዝብ በበዓላት ቀን በመጋበዝ መልሶ የመስጠት ባህል ነበረው። የተማሪው እንቅስቃሴም ሆነ ሌሎች ተማርን የሚሉ ሰዎች ከሶስዮሎጂና ከኢኮኖሚ ዕድገት አንፃር በሚገባ ሳያጠኑ የፊዩዳል መደብ በሚባለው የህብረተሰብ ክፍል ላይ በጭፍን በመዝመታቸው የተነሳ ከፍተኛ የሆነ ሀዘንና ማህበራዊ መመሰቃቀል እንዲፈጠሩ ለማድረግ በቅተዋል። በትክክል እንደተባለው በጊዜው የነበረውን ባህላዊ ግኑኝነት በሚገባ ካለማጥናት የተነሳ በግብታዊና በቁጭት ተግባራዊ የሆነው የመሬት ለአራሹ አዋጅ ማህበራዊ አናርኪዝምን ነው የፈጠረው። ይህ ጉዳይ ደግሞ በደርግ ብቻ የሚሳበብ ሳይሆን በተለይም የህብረት ለዕድገት ዘመቻን አስታከው ወደ ገጠር ውስጥ የዘመቱ አንዳንድ አፈንጋጭና ጭንቅላታቸው በሚገባ ያልተገራ ኃይሎችና አብዮቱን የሚጠሉ አጉል ቅስቀሳ በማድረጋቸው በተለይም እስከዚያ ጊዜ ድረስ ተከብሮ ይኖር የነበረውን የፊዩዳል መደብ ክብሩ እንዲደፈር ለማድረግ በቅተዋል።
ያም ተባለ ይህ የኢትዮጵያን አብዮት ሂደት ለተመለከተ በተለይም የህብረት ዘመቻን አስመልክቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ የማይናቅ ስራ ተሰርቷል። ሰፊውን ህዝብ ለማስተማር፣ ለማንቃትና ለማደራጀት ተችሏል። በተለይም በዚህ ዐይነቱ አገርን ከዝቅተኛ ወደ ከፈተኛ ደረጃ ለማሸጋገር በተደረገው ሙከራ ሰዓሊዎች፣ የቲያትር ሰዎችና ገጣሚዎች ተሳትፈውበታል። ስለሆነም በጊዜው የነበረው ሂደትና የተወሰነ መሻሻል እንደጨለማና እንደ መጥፎ ነገር እንደሚታየው ሶሻሊስታዊ ስርዓት መታየት የለበትም። ነገሩ እየተበላሸ መምጣት የጀመረው በተለይም ጩኸታችን ተቀማብን በማለት የከተማ ውስጥ ጦርነት በከፈቱ በኢምፔሪያሊስት ኃይሎች በተገዙ ሰዎችና ድርጅቶች አማካይነት ነው። እነዚህ በጣም በጣት የሚቆጠሩ ኃይሎች ኃላፊነት በጎደለው መንገድ በከፈቱት የከተማ ውስጥ ጦርነት ደርግን ወደ አውሬነት ነው የለወጡት። አደገኛና ጭንቅላታቸው በደንብ ያልተዋቀረ ወይም የአስተዳደግ ጉድለት የሚታይባቸው በአብዮቱ ውስጥ ሰርገው በመግባትና በአሸባሪ ኃይሎች በመመልመላቸው የቀይ ሽብርና የነጭ ሽብር የሚባለው ነገር በመፈጠር በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ ወጣቶች በማያውቁት ነገር ውስጥ በመግባታቸው ህይወታቸው እንዲቀጠፍ ለማድረግ ተቻለ። ከፍተኛ ቀውስም እንዲፈጠር የወያኔ ካድሬዎች በእነ ለገስ አስፋው ስር በመሆንና የሻቢያ ካድሬዎች አንድ ላይ በመሆን በአገራችን ምድር የርስ በርስ ጦርነት እንዲከፈት ያላደረጉት ሙከራ አልነበረም። በእነሱ ዕምነት አገራችን ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ስትገባ ነፃ እንሆናለን የሚል ዕምነት ነበራቸው። ይህም ድርጊታቸው የሚያመለክተው የቱን ያህል ደንቆሮዎች መሆናቸውን ነው።
በዚህ ዐይነቱ የእርስ በርስ ጦርነትም የአሜሪካኑ የስለላ ድርጅት ሲአይኤ የማይናቅ ሚናን ተጫውቷል። ዋናው ዓላማውም ህብረተሰብአዊ ቀውስ መፍጠርና ሰፊው ህዝብ ግራ በመጋባት ወደርስ በርስ ጦርነት እንዲያመራ ማድረግ ነበር። የአሜሪካን የስለላ ድርጅት ግራ የተጋቡና በጭፍን ሶሻሊዝምን የሚጠሉ ኢትዮጵያውያን ኃይሎችን፣ እንደ ኢድህ የመሳሰሉትንና እነ ክፍሌ ወዳጆን፤ እንዲሁም ከተማሪው እንቅስቃሴ ውስጥ ብቅ ባሉና ጭንቅላታቸው ያልዳበረ መሪዎችን በመጠቀም በአገራችን ምድር ሁለ-ገብ የሆነ ጦርነት እንዲካሄድ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል። በአጭሩ በአብዮቱ ዘመን ደርግ ብቻ ሳይሆን ዋናው ተዋናይ በዚህ ዐይነት ሁኔታ ውስጥ መዓት ግራ የተጋቡ ኃሎች በመሳተፍ የአብዮቱ ውጤቶች መልክ ባለውና በተቀነባበረ፣ እንዲሁም በተጠና መልክ ተግባራዊ እንዳይሆኑ ለማድረግ ችለዋል። በዚህም መልክም ሰፊው ህዝብ ሶሻሊዝምን እንዲጠላው ለማድረግ በቅተውል። ይህ ዐይነቱ አገርን ማዘበራረቅና በእልከኝነት ተነስቶ መገዳደል የኢትዮጵያኖች ባህርይ ነው ለማለት እደፍራለሁ። በቂ ዕውቀትና የህብረተሰብን የዕድገት ሂደት ሳያውቁና ሳያጠኑ በአንድ የተወሰነ የህብረተሰብ ክፍል ላይ በጭፍን በመነሳት ግድያ መፈጸምና ህብረተሰብን ማተረማመስ የእኛ የኢትዮጵያኖች ባህርይ ነው ለማለት እገደዳለሁ።
ከዚህ ኤፍሬም ማዴቦ ስር-ነቀል አብዮት ነው ከሚለው አስተሳሰብ ስነሳ እኔ እስከማውቀው ድረስ ከ1966-1983 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በአገራችን ምድር አንድ አብዮት ብቻ ነው የተካሄደው። እኔ እስከማውቀው ድረስ ኤፍሬም ማዴቦ እንደሚለን በኢትዮጵያ ምድር በእነዚህ ዐመታት ጊዜ ውስጥ ሁለት ስር-ነቀል አብዮቶች በፍጹም አልተካሄዱም። የህወሃትን ስልጣን መያዝ እንደ አብዮት ከቆጠረው ህወሃት ማካሄድ የጀመረው በአብዮቱ ዘመን የተሰሩና የተገነቡ ነገሮችን ቀስ በቀስ እያለ ነው መቀልበስ የጀመረው። የገበሬውንም ሆነ የወዝ አደሩን የሙያ ማህበሮች እንዳለ ነው ያፈራረሳቸው። ደርግ ለወታደር ልጆች ማሳደጊያና ማስተማሪያ ብሎ ያቋቋመውን ግሩም ግሩም ማዕከሎች ነው ያፈራረስውና ወጣቶችን በየሜዳው እንዲበታተኑ ያደረጋቸው። ይህ የወያኔ እርኩስ ስራ ደግሞ አብዮት ሳይሆን በመሰረቱ ፀረ-አብዮት ነው ማለት ይቻላል። ከዚያም በኋላ ተግባራዊ ያደረጋቸው የጎሳ ፌዴራሊዚምና የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመሰረቱ ፀረ ህብረ-ብሄርና ሰፊውን ህዝብ የሚያዳክሙና የሚበታትኑ ናቸው። የአብዮቱ ተዋንያኖችም ብዙ ስለነበሩና አብዮታዊና ፀረ-አቢዮታዊ ድርጊቶች እዚያው በዚያው ይካሄዱ ስለነበር ሁሉንም ነገር በደርግ ላይ ብቻ ማላከኩ ተገቢ ያልሆነና በማረጋገጫም የሚደገፍ አባባል አይደለም። በአብዮቱ ውስጥ ደርግ ብቻ ሳይሆን በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ተሳትፎበታል። ከአለአግባብ በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ ወጣቶችና በቀላሉ ተተኪ የማይገኝላቸው ምሁራኖች በጠራራ ፀሀይ ላይ ታርደዋል። አንዳንዶች ካለበቂ ምክንያት የመንግስቱ ኃይለማርያምን አገዛዝ ለመግለበጥ እያሴሩ ነው በማለት ከእስር ቤት ወጥተው እንዳለ በግፍ ተረሽነዋል። ይህም የሚያራገግጠው ደርግ ለአብዮት መካሄድ አመቺ ሁኔታ የፈጠረውን ያህል እዚያ በዚያው ፀረ-አብዮትና ፀረ-ህዝብ ስራዎችንም በመስራት ነው አገርን ጥሎ ያለፈው። ይህ የደርግ ድርጊት ሊገለጽ የሚችለው ደግሞ ደርግ ሶሻሊስታዊ ወይም አብዮታዊ ስለሆነ ሳይሆን ጭንቅላቱ በትክክለኛ ዕውቀት ያልተገነባ በመሆኑና የህብረተሰብን ሂደት በሚገባ ካለማወቁ የተነሳ ነው። ደርግ ራሱ የሁለት ስርዓቶች ውጤት፣ ማለትም የግማሽ ፊዩዳሊዝምና የግማሽ ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝም ውጤት በመሆኑ ጭንቅላቱ የተዘበራረቀ ስለሆነ በአርቆ አሳቢነትና በከፍተኛ ምሁራዊነት በመታገዝ የተዘበራረቀቀውን ሁኔታ መልክ የማሲያዝና የማብረድ ችሎታ አልነበረውም። ደርግና ጠቅላላው ሚሊታሪውና የፀጥታ ኃይሉ ጭንቅላትን ግብዝተኛ በሚያደርግና አርቆ-አሳቢነትን እንዳለ በሚያወድም በአሜሪካን የሚሊተሪና የፀጥታ ርዕዮተ-ዓለም የሰለጠኑ ስለሆነ ያደሉ ነበረው አመጽን በከፍተኛ አመጽ መመለስ እንጂ በፖለቲካዊ ጥበብ ከሌሎች ምሁራዊ ኃይሎች ጋር በመመካከር በጊዜው ይታይ የነበረውን ፖለቲካዊ ቀውስ ለመፍታት የሚችሉ አልነበሩም። በሚሊታሪ ስልጠናም መታዘዝ እንጂ ጥያቄና መከራከር ስለሌለ ወይም በራስ ህሊና መገዛትና መመራት ያልተለመደ ነገር ስለሆነ ማንኛውም ግለሰብ ጠበንጃውን በማንሳት ወንድሙን እንዳለ ነው የሚረሽነው። በጊዜውም ወንድም ወንድሙን መግደል እንደ ጀግንነት የሚታይበትና እያንዳንዱ ገዳይ ወታደርና የሲቪል ሰው ለምን ወገኑን እንደሚገልና ምንስ ጥቅም እንደሚያገኝ የሚረዳና እያወጣና እያወረደ የሚያስብ አልነበረም። በደመ-ነፍስ የሚመራና በዚህም ድርጊቱ የሚኩራራና የአስገዳዮች መሪዎች ደግሞ ውስኪያቸውን በመጎንጨት የሚዝናኑበት ነበር። ለማንኛውም በተለይም በዚህ ዐይነት የተመሰቃቀለ ሁኔታ ውስጥ በጣም ጥቂቱ ብቻ ነው ሰው መሆንን የሚረዳውና ለሌላውም ያስብ የነበረው።
የኤፍሬም ማዴቦን ኢ-ሳይንሳዊና ታሪከ-አልባ ጽሁፍ ሳነብ የአገራችን የመመሰቃቀል ሁኔታና ዛሬም ያለችበትን ሁኔታ ሊሳበብ የሚችለው በመሰረቱ በሰርዓቱ ሳይሆን በማወቅም ሆነ ባለማወቅ እንደዚህ ዐይነት ስርዓትን በሚፈጥሩ ሰዎች ነው። ሳይንሱ እንደሚያስተምረን ማንኛውም ስርዓት በመጥፎም ሆነ በቆንጆ መልክ ሊገነባ የሚችለው ከሰማይ ዱብ በማለት ሳይሆን በሰዎች አማካይነት፣ በተለይም ስልጣንን በጨበጡና ተማርኩኝ በሚለው አማካይነት ነው። በጥልቀት ማስብ የማይችሉ፣ ሳይንሳዊ አስተሳሰብን ከጭንቅላታቸው ጋር ያላዋሃዱና አርቆ-አሳቢነት የጎደላቸው ኃሎች ስልጣን ላይ በሚወጡበት ጊዜ ሁኔታዎችን ማዘበራረቃቸውና ህዝብን ማደናገራቸው ብቻ ሳይሆን በተፈጥሮም ላይ ዘመቻ እንደሚያካሂዱ በአገራችን ብቻ ሳይሆን በተለያዩ አገሮችም የሚታዩና፣ አሁንም የሚተገበሩ ናቸው። ምክንያቱም ሲግሙንድ ፍሮይድ እንደሚለን አብዛኛው ህዝብ 5% ብቻ የሚሆነውን የማሰብ ኃይል ብቻ የሚጠቀም ስለሆነ እያገናዘበና አርቆ በማሰብ ስራዎችን አይሰራም። ይህም ማለት አብዛኛው ህዝብ 95% የሚሆነውን የማሰብ ኃይሉን በፍጹም አይጠቀምም ማለት ነው። አብዛኛውም ህዝብ ለምን በዚህች ዓለም ላይ እንደሚኖር፣ ከየት እንደመጣና፣ ወዴትስ እንደሚያመራና የኑሮስ ትርጉሙ ምን እንደሆነ የሚገነዘብ አይደለም። እንዳለ በተፈጠረው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ስራዓት እየተነዳ የሚኖር ነው ማለት ነው። በዘመነ ኢምፔሪያሊዝም ደግሞ እነዚህ ዐይነቱ ንቃተ-ህሊናቸው በጣም ደካማ የሆኑ ኃይሎች የአንድን አገር ባህል ከሚያወድመው የውጭ ኃይሎች ጋር በመቆላለፍ ብሶታቸውንና ቁጭታቸውን ለመወጣት ሲሉ በህብረተሰብና በተፈጥሮ ላይ ዘመቻ ያካሂዳሉ። እንደዚህ የሚያደርጉትም የማሰብ ኃይላቸውን ስለማይጠቅሙና የዘመናትን ጉዳይና ታሪካዊ ስራን በየኢፖኩ እየለያዩ ለማጥናትና ለመገንዘብ ስለማይችሉ ነው። በስልጣን ላይ ያሉ አብዛኛዎች መሬዎች ነን የሚሉ ከዕውቀት የራቁ ስለሆነና በየቀኑ መንፈስን የሚያድሱና ጥያቄ እንዲጠይቁ የሚያደርጉ መጻህፍትን ስለማያነቡ ስለሰው ልጅና ስለተፈጥሮ ምንም ዐይነት ግንዛቤና ደንታም የላቸውም። እንደነዚህ ዐይነት ሰዎች ጊዜ አልባ የሆኑና ጭንቅላታቸውም ውስጥ ምንም ነገር የሌለ፣ ወይም ደግሞ በአፈጣጠራቸውም የማሰብ ኃይል አብሯቸው ያልተፈጠረ ስለሆነ የሚያደርጉትን በፍጹም አያውቁም። ስለሆነም በደመ-ነፍስ የሚመሩና አጋጣሚን በመጠቀም ባህልንና ታሪክን ለማውደም የሚቅበዘበዙ ናቸው። ይህም ማለት ለአንድ አገር ዕድገት፣ ለአንድ ቆንጆ ስርዓት መፈጠርና ለህዝብ አለኝታ መሆን የግዴታ ሳይንሳዊ ዕውቀትና በየጊዜው እየተሻሻለ የሚሄድ ንቃተ-ህሊና ወሳኝ ነገሮች ናቸው። ይህ ዐይነት ሁኔታ በሌለበት አገር ውስጥ አንድን አገርና ህዝብ የሚፈታተኑና ህዝብንም የሚያዋክቡ ኃይሎች በየጊዜው መፈጠራቸው የማይቀር የታሪክ ዕጣ ነው።
ይህም የምልበት ምክንያት በአውሮፓ ምድር አንዳንድ አገሮች ከፊዩዳሊዝም ተፈልጎ ሳይሆን ወደ ካፒታሊዝም የተሸጋገሩት ከመጀመሪያውኑ የቤት ስራ ከፍተኛ ዕውቀት ባላቸው ፈላስፋዎች፣ የተፈጥሮ ሳይንስ ሰዎች፣ የኢኮኖሚ ጠቢባን፣ የከተማ ግንባታ አዋቂዎችና ሌላንም ዕውቀት በተጎናጸፉ አማካይነት ነው። በአውሮፓ ምድር ውስጥ ቀሰ በቀስ በሳይንስና በቴክኖሎጂ የሚገለጽ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ስርዓት ሊፈጠር የቻለው ከታች አመቺን ሁኔታ በመጠቀም በተነሱና ህብረተሰባቸው ከእንስሳ ባልተናነስ ሁኔታ ውስጥ መኖር የለበትም በማለት ቆርጠው በተነሱ ህብረተሰብአዊ ኃይሎች አማካይነት ነው። የካፒታሊዝምን ዕድገት ስናጠናና ስንመራመር የምናገኘው መልስ ካፒታሊዝም እዚህ ዐይነቱ ደረጃ ላይ ሊደርስ የቻለው በመንግስታት ፈቃድ ሳይሆን በተገለጸላቸውና ሁኔታዎችን በመጠቀም ወደ ፈጠራ ስራ በተሰማሩ ኃይሎች አማካይነት ነው። የኋላ ኋላ ላይ በአገሮች መሀከል ውድድር ሲፈጠር አንዳንድ አገሮችና መንግስታት በሌላው ላለመቀደም ሲሉ የግዴታ ወደ አገር ግንባታ መሰማራትና በተለይም ደግሞ እንደ ሳይንስ አካዴሚ የመሳሰሉትን ተቋማት በመመስረት ለሁለ-ገብ ዕድገት አመቺ ሁኔታን ለመፍጠር ችለዋል።
ያም ተባለ ይህ ወደ ኤፍሬም ማዴቦ ጽህፉ ጋ ስመጣ በአንድ አገር ውስጥ የስርዓትና የአስተሳሰብ ለውጥ ዝም ብለው ሊመጡ አይችሉም። ላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት ከተፈጥሮ በስተቀር ህብረተሰብአዊ ስርዓት፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ጉዳይ፣ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ጉዳይ የከተማ አገነባብ ጉዳይ፣ የመጸዳጃና የተቋማት ጉዳይ… ወዘተ. ወዘተ. እነዚህ ሁሉ በሰው የማሰብ ኃይል የሚፈጠሩ ናቸው። በአንድ ማህበረሰብ ወይም ህብረተሰብ ውስጥ የዘራፊነት አስተሳሰብና ጥራዝ ነጠቅ ዕውቀት ያላቸው ሰዎች ስልጣን ላይ በሚወጡበት ጊዜ በተለይም የተወሰነው የህብረተሰብ ክፍል ወደ ብልግናና ወደ ዘራፊ ተግባር እንዲሰማራ በማድረግ በተለይም ደካማ የሆነው የህብረተሰብ ክፍል የኑሮን ትርጉም እንዳይረዳ ያደርጉታል። ታዳጊው ወጣት ደግሞ ዘራፊነትንና የተበላሸን አስተዳደር በሚመለከትበት ጊዜ ይህ ዐይነቱ አካሄድ ትክክል ነው ብሎ ስለሚያምን ሳያውቀው ከጭንቅላቱ ጋር በማዋሃድ እሱም ወደ ዘራፊነትና ህብረተሰቡን ወደ ማከረባበት ያመራል። ይህንን ጉዳይ ኤፍሬም ማዴቦ በሚገባ የተገነዘበ አይመስለኝም። ሌሎች ነገሮች፣ ለምሳሌ አመጸኛነት፣ አልበገርም ባይነት፣ ምክር አለመስማት፣ ጉረኛነት፣ ትዕቢት፣ አውቃለሁ ባይነት፣ ተንኮል መስራት፣ ቡድናዊ ስሜት መሰማት፣ ሌላውን ማግለልና ለስልጣን መስገብገብ፣ ሌላውን መናቅ…ወዘተ. እነዚህ መጥፎ ባህርዮች አንድ ጊዜ ከልጅነት ጀምሮ በሰዎች ጭንቅላት ውስጥ ከተተከሉ በፍጹም ነቅሎ ማውጣት አይቻልም። አስር ጊዜ ሜዲቴሽና ዮጋም ቢካሄድ በዚህ ዐይነት በሽታ የተለከፉ ሰዎች ይህችን ዓለም ጥለው እስኪሄዱ ድረስ በዚያው በመጥፎ ባህርያቸው ይገፉበታል። ባጭሩ መጥፎ አስተሳሰብና ባህርይን መቀየር አለብን በማለት የሚቀየሩ አይደለም።
ከዚህ በተረፈ ኤፍሬም ማዴቦ የግዴታ የስርዓት ለውጥ መደረግ እንዳለበት ያሳስበናል። ይህ ብቻ ሲደረግም በእሱም ሆነ በአንዳንዶች የስርዓት ለውጥ መምጣት አለበት እያሉ የሚወተውቱ ኃይሎች ዕምነት ዐይነተኛ ለውጥ ይመጣል። ይሁንና ኤፍሬም ማዴቦም ሆነ ሌሎች በአገራችን ምድር ምን ዐይነት ስርዓት እንዳለ በፍጹም አይነግሩንም። ይህ ብቻ ሳይሆን ለምን ዐይነት ስርዓትም እንደሚታገሉና በምንስ ዘዴ ተግባራዊ እንደሚሆን አይነግሩንም። በደፈናው ብቻ የስርዓት ለውጥ መደረግ አለበት ይሉናል። ሌላው የሚነሳው ጥያቄ ደግሞ የትኛው ኃይል ነው የስርዓት ለውጥ ሊያመጣ የሚችለው? ለሚለው ጥያቄ አጥጋቢ መልስ አይሰጡንም።
አንዳንድ ነገሮችን ግልጽ ለማድረግ አሜሪካኖችና አፈቀላጤዎቻቸው የዓለም የገነዝብ ድርጅትና(IMF) የዓለም ባንክ በደርግ ዘመን ተግባራዊ ይደረግ የነበረው የኢኮኖሚ ፖሊሲና ስርዓቱ የዕዝ ኢኮኖሚ ነበር እያሉ ነው ይነግሩን የነበረው። ስለሆነም ይህ የዕዝ ኢኮኖሚ ፖሊሲና፣ በእነሱ ዕምነት ሶሻሊስታዊ ስርዓት በነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ሲተካና የነፃ ገበያም ዕውን ሲሆን አገራችንና ህዝባችን ተዓምር ያያሉ። አገራችንም የካፒታሊስቱ ዓለም አባልና አጋር በመሆን ህዝባችን በደስታ ይደነፍቃል ይሉናል። ስለሆነም ወያኔ በአሜሪካንና በእንግሊዝ በመደገፍና በመመክር ስልጣን ላይ ሲወጣ ከጎሳ ፌዴራሊዝም ቀጥሎ ለነፃ ገበያ አመቺ የሚሆነውን የተቋም ማስተካከያ(Structural Adjustment Programms) ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረግ ነበረበት። ይህንንም ፖሊሲ የፖሊሲ አውጭዎቹና አማካሪዎቹ ዲሬጉሌሽን ብለው ይጠሩታል። ይህም ማለት ማንኛውም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ከመንግስት ማነቆ ውስጥ መላቀቅ አለበት። የተቋም ፖሊሲውም መሰረተ-ሃሳቦችም፣ 1ኛ) የኢትዮጵያን ብር ከዶላር ጋር ሲነፃፀር መቀነስ፣ ይህንን ዲቫሊውዬሽን(Devaluation) ብለው ይጠሩታል። 2ኛ) በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ መደብሮችና የምርት ማምረቻዎች ወይም ኢንዱስትሪዎችና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ወደ ግል ሀብትነት መለወጥ አለባቸው። ይህንን ፕሪይቬታይዜሽኝ ብለው ይጠሩታል። 3ኛ) ገበያውን ለውጭ ከበርቴዎች ነፃ ማድረግ። ወደ ውስጥ ደግሞ የኢኮኖሚው እንቅስቃሴ በአቅራቢና በጠያቂ ህግ መሰረት መስራት አለበት። ይህንን ሊበራላይዜሽን ብለው ይጠሩታል። 4ኛ) ከዚህም በላይ ለህዝብ የሚደረገው ድጎማና ለሌሎች የማህበራዊ ፕሮጀክቶች የሚውለው የመንግስት በጀት መሰረዝ ወይም በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ አለበት። እነዚህ የኢኮኖሚ ፖሊሲ መሳሪያዎች ተግባራዊ ሲሆኑ ቀስ በቀስ የነፃ ገበያው ኢኮኖሚ ተግባራዊ ይሆናል። ህዝባችንም ከድህነት ይላቀቃል። በእነ ዓለም የገንዘብ ድርጅ ዕምነት በኢትዮጵያ ምድርም ሆነ በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ውስጥ የኢኮኖሚ መዛባት(Macroeconomic Imbalamnces) የሚታየው በመንግስት ጣልቃ-ገብነት የተነሳና የዕዝ-ኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ በመሆናቸው ነው። የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ከሆነ መዛባቱ ቀስ በቀስ ይወገዳል። ኢኮኖሚውም ያድጋል ይሉናል። በሌላ ወገን ግን የተቋም መስተካከያ የሚለውን ስንመረምረው የአንድን አገር ኢኮኖሚ ተቋም ወይም ስርዓት ወደ ተወሰኑ ነገሮች መቀነሱ ኢ-ሳይንሳዊ አካሄድ ነው። ከላይ የተጠቀሱት ነግሮች በመሰረቱ የጠቅላላው ስርዓት ነፀብራቆችና፣ በአጠቃላይም ሲታይ አገራችን ያለችበትን ደካማ የሆነ የኢንዱስትሪ አወቃቀር የሚያሳዩ ናቸው። በሌላ አነጋገር በማኑፋክቸሪንግ ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ አወቃቀርና የስራ-ክፍፍል ባልዳበረበት አገር ውስጥ የግዴታ ውስጠ-ኃይል ያለው የገበያ ኢኮኖሚ ሊዳብር አይችልም። በመሆኑም ብርን ከዶላር ጋር ሲነፃፀር እንዲቀንስ ማድረግና በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ ኢንዱስትሪዎችንና መደብሮችን ወደ ግልሀብትነት መለወጥ የአገራችንን መሰረታዊ ችግሮች ሊፈቱ በፍጹም አይችሉም። ከዚህም በላይ ምን ነገር ከምን ጋር መገጣጠም(Adjust) እንደሚሆን የፖሊሲው አማካሪዎች በፍጹም አልነገሩንም። በእነሱ ዕምነትና በእኔ ግንዛቤ በመዋቅር የኢኮኖሚ ፖሊሲው የተነሳ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ለግሎባል ካፒታሊዝም በሚስማማ መልክ መስተካከልና ለብዝበዛ እንዲያመች ሆኖ መዋቀር አለበት። የመዋቅር ፖሊሲው መሳሪያዎችም ለዚህ የሚስማሙ እንጂ ወደውስጥ ላተኮረ፣ በሳንይስና በቴክኖሎጂ ላይ ለተመሰረተ ጠንካራ ኢኮኖሚና የውስጥ ገበያ ለመገንባት የሚያመቹ አይደሉም፡፡ ስለሆነም ወያኔና አማካሪዎቹ፣ ከዎል-ስትሪት ተጠርተው የመጡት አማካሪዎች በመሰረቱ አንዳችም ቦታ ላይ ጥያቄ ሳያነሱና ክርክርም ሳይደረግበት ነው በጭፍን የነጭ ኦሊጋርኪውን መደብ ትዕዛዝ ተግባራዊ ለማድረግ የበቁት። ይህ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ኢኮኖሚስቶች ነን የሚሉ ኢትዮጵያውያንም፣ በአገር ቤት ውስጥም ሆነ በውጭው ዓለም የሚኖሩ አንዳችም ቦታ ላይ ይህንን የእነ ዓለም የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክን የተቋም መስተካከያ ፖሊሲ ብለው የሚጠሩትን በመቃወም ሰፊ ትንተና ሲሰጡ አልታዩም። አንዳንዶችም ስለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ማብራሪያ እንዲሰጡ በየሚዲያዎች ላይ በሚጋበዙበት ጊዜ አንዳችም ቦታ ላይ ስለመዋቅር ማስተካክያው ፖሊሲ(Structural Adjustment Programms) ትችታዊ ገለጻ ሲሰጡ አይታይም።
ያም ሆነ ይህ ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ስንነሳ በአገራችን ምድር በደርግ የአገዛዝ ዘመን አንድ የአሜሪካ ዶላር ለመግዛት 2.05 የኢትዮጵያ ብር ያስፈልግ ስለነበር፤ ወያኔ የዓለም የገንዘብ ድርጅትን ተዕዛዝ በመቀበል አንድ የአሜሪካ ዶላር ለመግዛት 5 የኢትዮጵያ ብር ማቅረብ እንደሚያስፈልግ ወሰነ። በዚህ መልክ ወያኔ ስልጣን ላይ በነበረበት ዘመን የኢትዮጵያ ብር በተከታታይ እንዲቀንስ በመደረጉ በአሁኑ በአቢይ የአገዛዝ ዘመን አንድ የአሜሪካን ዶላር ለመግዛት አንድ ኢትዮጵያዊ 56 የኢትዮጵያ ብር ማቅረብ አለበት። በእነ ዓለም የገንዘብ ድርጅት ዕምነት የኢትዮጵያ ገንዘብ ከሚበገባው በላይ የተተመነ ስልሆነና፣ በዚህም ምክንያት የተነሳ ወደ ውጭ የሚላከው ለምሳሌ እንደቡናና ሌሎች የጥሬ-ሀብቶች ስለሚወደዱ የውጭ ከበርቴዎች ወይም አገሮች ከኢትዮጵያ ቡናና ሌሎች ነገሮችን ለመግዛት አይፈልጉም። ወደ ሌሎች አገሮች ዐይናቸውን ያዞራሉ ይሉናል። ስለሆነም የኢትዮጵያ ብር በከፍተኛ ደረጃ ከቀነሰ ቡናን የሚገዙ አገሮችና ከበርቴዎች በብዛት ከኢትዮጵያ መግዛት ይጀምራሉ ይሉናል። ይህ ዐይነቱ የገንዘብ ቅነሳና ሌሎችም የተቋም ማስተካከያ ፖሊሲዎች ሳይንሳዊና ታሪካዊ ማረጋገጫ የላቸውም። ለምሳሌ የኢትዮጵያ ብር ከዶላር ጋር ሲነፃፀር በተከታታይ በመቀነሱ የተነሳ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልከው የቡናና የሌሎች ሰብሎች መጠን በፍጹም አልጨመረም። ከውጭ የምታገኘው የውጭ ምንዛሪም በፍጹም አላደገም፤ የንግድ ሚዛኑም አልተሻሻለም። በአንፃሩ የንግድ ሚዛኑ በከፍተኛ ደረጃ ነው መዛባት የጀመረው። ገበያው ልቅ በመሆኑ የተነሳ የአገር ውስጥ አዳዲስ መጤ ነጋዴዎች ወደ አገር ውስጥ ማስገባት የጀመሩት የቅንጦት ዕቃዎችን ነው። በዚህም ምክንያት የተነሳ የኢትዮጵያ የንግድ ሚዛን በጂዲፒ ሲለካ በ1974-1991 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ -8.9% ሲሆን፣ የተቋም ማስተካከያ ፖሊስ ተግባራዊ ከተደረገ በኋላ ከ1992-2009 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ወደ -22.0% አድጓል። ይህም ማለት ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከምትልከው ምርቶች ይልቅ ወደ ውስጥ የምታስገባው ዕቃዎች በክፍተኛ ደረጃ ሲጨምሩ፣ የንግድ ሚዛኑም በዚያው መጠን ተዛብቷል። በ2022 ዓ.ም የኢትዮጵያ የንግድ ሚዛን በ12.78 ቢሊዮን የሜሪካ ዶላር ተዛብቷል። ይህም የሚያረጋግጠው የኢትዮጵያ ብር በመቀነሱ የተነሳ የኢትዮጵያ የንግድ በፍጹም እንዳልተሻሸለ ነው። እንደዚሁም የውጭው ዕዳዋ በአሁኑ ወቅት 28 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ነው። ስለሆነም የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባትን ያስተካክላል ተብሎ በዓለም ኮሙኒቲው ምክር በአገራችን ምድር ተግባራዊ የሆነው የተቋም ማስተካካያ ፖሊሲ ከፍተኛ መዛባትን ነው ያስከተለው። በዚያውም መጠን ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ግሽበት በአገራችን ምድር በመንገሰ ሰፊውን ህዝብ አላላውስም ማለት ከጀመረ ሰንብቷል።
ይህ ዐይነቱ በዓለም የገንዘብ ድርጅት የሚደገፈው የኢኮኖሚ ፖሊሲ በአንዳቸውም የካፒታሊስት አገር ተግባራዊ ሆኖ አያውቅም። ገንዘብ በጉልበትና አርቲፊሻለ በሆነ መልክ የአንዱ አገር ገንዘብ ከሌላው ጋር ሲነፃፀር እንዲቀንስ የተደረገበት አገር የለም። አብዛኛዎቹም የካፒታሊስት አገሮች ኢኮኖሚያቸውንና ህብረተሰባቸውን መገንባት የጀመሩት በመጀመሪያ ደረጃ ከተማዎችንና መንደሮችን በስርዓት በማዋቀር ነው። ምክንያቱም ማንኛውም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ሊካሄድ የሚችለው በስርዓት በተደራጀ ቦታ(Space) ነው። ቀጥሎም ትናንሽና ማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎችን በመትከልና ይህንን በሙያ ማሰልጠኛ በመደገፍ ነው። የኋላ ኋላ ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች እየተፈጠሩ ሲመጡ በትላልቅና በትናንሽ እንዲሁም በማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎች መሀከል መተሳሰር ሊመጣ ቻለ። በዚህም ምክንያት የተነሳ ሰፋ ያለው የማምረት ኃይልና በየቦታው የኢንዱትሪዎች ስርጭት ለገንዘብ በከፍተኛ መንቀሳቀስና መጠንከር የጀርባ አጥንት ሊሆን ቻለ። ይህም ማለት የአብዛኛዎቹ የካፒታሊስት አገር ኢኮኖሚዎች በሳይንስና በቴክኖሎጂ ስለሚደገፉና ኢንዱስትሪዎችም በተስተካከለ መልክ ስለተሰራጩ እነዚህ ነገሮች ለገንዘቡ መጠንከር እንደ ጀርባ አጥንት ሊሆኑ ችለዋል። በሌላ አነጋገር፣ ለምሳሌ ኦይሮም ሆነ ዶላር ሰፋ ባለው የምርትና የአገልግሎት መስክ እንቅስቃሴ ስለሚደገፉ በየጊዜው አርቲፊሻል በሆነ መልክ መቀነስ አያስፈልጋቸውም። ወደ አገራችን ስንመጣ ግን የምርት መስኩ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ አስደግፎ የውስጥ ገበያውን ከማስፋፋት ይልቅ የተያዘው ገንዘብን አርቲፊሻል በሆነ መልክ መቀነስ ውስጥ የተገባው። በዚህም ምክንያት የተነሳ ነው ከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ሊከተን የቻለው። ከዚህም በላይ ካለአግባብና የሰፊውን ህዝብ ፍላጎቶች የማያሟሉ በአለ አምስትና ሰባት ኮከብ ሆቴልቤቶች በመሰራታቸው፣ እነዚህ በራሳቸው በከፍተኛ ደረጃ ለሰፊው ህዝበ የሚሆነውን፣ እንደ በርበሬ፣ ዘይት፣ ቅቤና ስጋ፣ እንዲሁም ሽንኩርትና እንደ ጤፍና ሌሎችን ሰብሎችን ሰለሚጋሩ በራሳቸው ለዋጋ መናር ከፍተኛ አስተዋፅዖ ማድረጋቸው ብቻ ሳይሆን በከፍተኛ ደረጃ ብልግና የሚስፋፋባቸው መድረኮች ለመሆን በቅተዋል።
ኢፍሬም ማዴቦም ሆነ ሌሎች ኢኮኖሚስቶች ሊነግሩንና ሊያብራሩት የማይችሉት ይህንን በእነ አይኤምፍ ምክር ተግባራዊ የሆነውን ኢ-ሳይንሳዊ የኢኮኖሚ ፖሊሲና አሉታዊ ውጤቱን ነው። ስለሆነም የስርዓት ለውጥ ያስፈልጋል ሲባል ከፖለቲካና ከመንግስት አወቃቀሩ ጋር የግዴታ የኢኮኖሚ ፖሊሲውን መቀየር አለበት። ለዚህ ደግሞ የድሮ ሰዎችን በአዲስ መልክ መተካት ሳይሆን የግዴታ የፖለቲካውንና የመንግስቱን መድረክ በአዳዲስና ብሄራዊ፣ እንዲሁም ተራማጅ አስተሳሰብና ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ ዕድገት በቆሙና መንፈሳቸው ባልተበላሸና ለውጭ ኃይሎች በማያጎበድዱ ኃይሎች መተካት ያስፈልጋል። ምክንያቱም ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሊተገበሩና የሰፊው ህዝብ መሰረታዊ ጥያቄዎች ሊመለሱና አገራችንም በጸና መሰረት ላይ ልትገነባ የምትችለው ያረጀና ተንኮላዊ አስተሳሰብ ባላቸው ሰዎች አማካይነት ስለማይሆን ነው። ይህም ማለት ወያኔም ሆነ አሁን በስልጣን ላይ ያለው አገዛዝና ግብረ-አበሮቹ፣ እንዲሁም የኢኮኖሚክስ አማካሪዎቹ እንዳለ ከስልጣን መወገድና ላደረሱት ህዝባዊ ዕልቂትና አገርን ለመበታተንና ባህልን ለማውደም ባደረጉት እርኩስ ተግባራቸው የግዴታ መጠየቅና በእስርም ሆነ በሌላ መልክ መቀጣት አለባቸው። በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ እህቶቻችንና ወንድሞቻችንን፣ እንዲሁም እናቶቻችን ገድለውና አሰቃይተው፣ እንዲሁም በባሪያ ንግድ በመሰማራት ልጆቻችን የሚሆኑትት ህይወታቸው እንዲበላሹና አንዳንዶችም እንዲገደሉ ካደረጉ በኋላ እንደ ሰላማዊ ዜጋ እጃቸውን አጣጥፈው በሰላም ሊቀመጡ በፍጹም አይችሉም። እነሱም በሰፈሩት ቁና የግዴታ መሰፈር አለባቸው። በአንድ ወቅጥ ስልጣንን ስለያዙ በፈጸሙት ወንጀል የመጠየቅና የመከሰስ መብት የላቸውም የሚል ህግ የለም። ስለሆነም ስለ ስርዓት ለውጥ በሚወራበት ጊዜ ያለውን ጨቋኝ ስርዓት እንዳለ መገርሰስና በአዲስ መልክ በማዋቀር የግዴታ ጭንቅላታቸው ባልተበላሸና ለሰው ልጅና ለአገር በሚያስቡ ኃይሎች መተካት ያስፈልጋል። ይህ ብቻ ሳይሆን ስለ ስርዓት ለውጥም ሲወራ ግሎባል ካፒታሊዝምና ዋናው አሽከርካሪው ከሆነው ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ማነቆ የግዴታ መላቀቅ አለብን። በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በመደገፍ አገራችንን በዚህ መልክ እንድትበወዝና ህዝባችንም እንዲሰቃይ ያደረጉ፣ በዜግነታቸው አሜሪካዊ የሆኑና ለአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ያደሩና የእሱንም አጀንዳ የሚያስፈጽሙ በሙሉ መጠየቅ አለባቸው።
ሌላው ሰረተ ጉዳይ ኤፍሬም ማዴቦም እንደሌሎች ኢትዮጵያውያን ምሁራን ነን ባይች ለመገንዘብና ለማሳየት ያልቻለው በተለይም በወያኔም የሆነ በአቢይ አህመድ አገዛዝ ዘመን ተግባራዊ የሆኑት የጎሳ ፌዴራሊዝምና የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ የወያኔና የአቢይ አህመድ አጀንዳዎች ብቻ እንደሆኑ ነው የተቆጠሩትና የሚቆጠሩት። ወያኔ ስልጣን ላይ ከመውጣቱ በፊት መለስ ዜናዊና ግብረ-አበሮቹ በሙሉ ከሲአይኤና ከአባታቸው ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ነበር በቀጥታ መመሪያ ወይም ትዕዛዝ ይሰጣቸው የነበረው። በሌላ አነጋገር፣ ወያኔ ወይም ህወሃት የትግሬን ብሄረሰብ ጥቅም ያስጠበቀ ሳይሆን የአሜሪካንን ኢምፔሪያሊዝምንና የተቋማቱን ትዕዛዝ በመቀበል ነው ወደ ዘረፋ ስራና አገር ወደ መከፋፈል ተግባር የተሰማራው። በዚህ የሴተኛ አዳሪነት ተግባሩና የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል በማባለግ ነው ህብረተሰብአችንና ባህላችንን ማውደምና ሰፊውን ህዝብ ደግሞ ግራ ማጋባት የቻለው። ኤፍሬም ማዴቦ በተለይም ለረዥም ዓመታት በፖለቲካ ትግል ውስጥ የተሳተፍክ እንደመሆንህ መጠን በተለይም በኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት የቱን ያህል የዘረፋ ተግባር እንደተካሄደ በገባህ ነበር። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚም ተከስክሷል ሲባልም ዝም ብሎ በራሱ የሚከሰከስ ሳይሆን ኢ-ሳይንሳዊ አስተሳሰብ ባላቸው ሰዎች የሚወጣ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የግዴታ አንድን ህዝብ ወደ ድህነት እንደሚገፈትረው የታወቀ ጉዳይ ነው። በተለይም እነዚህን የመሳሰሉ ኃይሎች ከውጭ ትዕዛዝ እየተቀበሉ ህዝባዊ ሀብትን የማይፈጥርና ህዝብን ከድህነት ሊያላቅቅ የማይችል ኢ-ሳይንሳዊ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ የሚያደርጉ ከሆነ የኢኮኖሚ ቀውስ መታየቱ የማይቀር ጉዳይ ነው።
ስለሆነም የኢኮኖሚ ቀውስ የሚገለጸው ያሉት ኢንዱስትሪዎችና የአገልግሎት መስጫዎች ስራ ለሚፈልገው ህዝብ በቂ የስራ መስክ ለመስጠት የማይችሉ ከሆነ፣ ይባስ ብሎም ከቀጠሯቸው ሰራተኞች ውስጥ ምርቶቻቸውን እንደልብ በማይሸጡበት ጊዜና የማምረት ኃይላቸውን በሚቀንሱበት ጊዜ የግዴታ የሰራተኛውን ቁጥር ይቀንሳሉ። በዚህም ምክንያት የተነሳ የስራ-አጥ ቁጥሩ ይጨምራል ማለት ነው። ሌላው የኢኮኖሚ ቀውስ መገለጫ የዋጋ ግሽበት ጉዳይ ነው። ለዋጋ ግሽበት ደግሞ የተለያዩ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ለምሳሌ በድርቅ ምክንያት የተነሳ መመረት የሚገባው የእህል መጠን በከፍተኛ ደረጃ የሚቀንስ ከሆን ያሉትና የተከማቹት ምርቶች ዋጋቸው ይጨምራል። ከዚህም በላይ ኢንዱስትሪዎች በመለዋወጫ ዕቃ እንደልብ አለማግኘት፣ በዘይትና በጋዝ ዋጋ መወደድ፣ እንዲሁም በሌሎች ለኢንዱስትሪ ምርት የሚያገለግሉ የጥሬ ሀብቶች መወደድ ምክንያት የተነሳ አምራቾች አምርተው ገበያ ላይ በሚሸጡበት ጊዜ የዋጋ ግሽበት ይታያል። ከዚህም በላይ የኢንዱስትሪዎች የማምረት ኃይል በሚቀንስበት ጊዜ አምራቾች በትንሽ ካፓሲቲ ሲያመርቱ ቋሚው የማምረቻ ዋጋ(Fixed Cost) እንዳለ ስለሚቀር በዚህም ምክንያት የተነሳ የዋጋ ግሽበት ሊታይ ይችላል። ሌላውና ለዋጋ ግሽበት ዋናው ምክንያት የአንድ አገር ገንዘብ አርቲፊሻል በሆነ መልክ ልክ እንደ አገራችን በተከታታይ የሚቀንስ ከሆነ የግዴታ የዋጋ ግሽበትን ያስከትላል። ምክንያቱም በተለይ ከውጭ የማምረቻም ሆነ ሌሎች የጥሬ-ሀብቶችንና የመለዋወጫ ዕቃዎችን ከውጭ አስመጥተው ምርት የሚያመርቱ ከበርቴዎች አንድ ዶላር ለመግዛት ላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት በተከታታይ ገንዘቡ ከዶላር ጋር ሲነፃፀር የሚቀንስ ከሆነ አንድ ዶላር ለመግዛት ብዙ የኢትዮጵያ ብር ማቅረብ አለባቸው። በዚህም ምክንያት የተነሳ የማምረቻ ዋጋ በሚጨምርበት ጊዜ የሚመረተውም ምርት በሚሸጥበት ጊዜ ዋጋው ይጨምራል ማለት ነው፤ በአጭሩ የዋጋ ግሽበት ይከሰታል ማለት ነው።
ስለሆነም ለዚህ ሁሉ መፍትሄው የህዝባችንን ፍላጎት የሚያሟላና በቴክኖሎጂ ወይም በማኑፋክቸሪንግ ላይ የተመሰረተ የምርት ክንውን ማካሄድና፣ ከውጭ የሚመጣውንም አላስፈላጊና ከቴክኖሎጂ ጋራ ያልተያያዘ የቅንጦት ዕቃዎችን እንዳለ መቀነስ፣ ወይም አላስፈላጊ ሆነው ከታዩ እንዳለ መሰረዝ ነው። አንድ አገርና ህዝብ ከሚያመርተውና ከሚፈልገው ዕቃ በላይ ከውጭ እያመጣ መጠቀም የለበትም። በተቻለ መጠን ለሰፊው ህዝብ የሚጠቅሙና መሰረታዊ ፍላጎቱን የሚያሟሉ የፍጆታ ዕቃዎች በአገር ውስጥ መመረት አለባቸው። አላስፈላጊና ለህዝብ የማይጠቅሙ፣ እንዲሁም የህዝብን አስተሳሰብ የሚያዛቡ የፍጆት ዕቃዎች አጠቃቀም ኢኮኖሚያዊ ቀውስን ብቻ ሳይሆን የመንፈስ መረበሽንም ያስከትላሉ። የሰውን የማሰብ ኃይል ያዳክማሉ። የአንድ አገር ኢኮኖሚም ቀውስ ውስጥ የሚገባው ከውስጥ ስልጣን ላይ ባሉና የፖሊሲ አውጭዎች ሰለአገር ግንባታና ስለኢኮኖሚ መሰረታዊ ግንዛቤ ከሌላቸው የግዴታ ከውጭ የሚጣን ትዕዛዝ ተግባራዊ በማድረግ ህዝባዊ ወይም ህብረተስብአዊ ሀብት ከመፍጠር ይልቅ ኢኮኖሚያዊ መመሰቃቀልን ይፈጥራሉ። በተለይም በምርት(Production)፣በክፍፍልና(Income Distribution) የሚመረቱ ዕቃዎችን ገዝቶ ለፍጆታ መጠቀም(Consumption) በእነዚህ መሀከል ዲያሌክቲካዊ ግኑኘነት ያለ መሆኑን በፖሊሲ አዎጭዎች ዘንድ ግንዛቤ ከሌለ የአንድ አገር ኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ይወድቃል። የሚመረቱ ዕቃዎችን ገዝቶ ለመጠቀም ደግሞ በተለይም ሰራተኛውና የተቀረው ህዝብ የመግዛት ኃይላቸው(Buying Power) በየጊዜው ማደግ አለበት። በእነ አዳም ስሚዝና በሌሎች የካላሲካል ኢኮኖሚስቶች ዕምነት የማንኛውም የማምረት ዋናው አላማ የሰውን የፍጆታ ፍላጎት ማሟላት ነው። በሌላ አነጋገር፣ ምርትን ለማምረት ተብሎ አይመረትም፤ ወይም ደግሞ ለሰው ልጅና በቀጥታ ለጠቀሜታ ወይም ለፍጆታ የማይውሉና ፍላጎቱንም የማያሟሉ ምርቶችን ማምረት አስፈላጊ አይደሉም። ስለሆነም ባለፉት ሰላሳ አምስት ዓመታት በአገራችን ምድር ተግባራዊ የሆነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ የህዝባችንን ፍላጎት የሚያሟላ አልነበረም፤ አይደለምም። የባስ ቀውስ ውስጥ የከተተንና አገራችንን ያመሰቃቀለ ነው። የኢኮኖሚ ፖሊሲው 5% ብቻ የሚሆነውን የህብረተሰብ ክፍል የሚጠቅምና የብልግናን ኢንዱስትሪ በከፍተኛ ደረጃ ያስፋፋ ነው።
ይህ ጉዳይ በኤፍሬም ማዴቦ፣ በአለቃው በብርሃኑ ነጋና በሌሎች የግንቦት ሰባት ሰዎች ዘንድ ፍጹም ግንዛቤ ውስጥ የገባ ጉዳይ አይደለም። ወያኔ ስልጣን ላይ ከወጣ በኋላ ተግባራዊ ያደረግውን የኢኮኖሚና አሉታዊ ውጤቱን አስመልክቶ አንዳችም ቦታ ላይ ትችታዊ በሆነ መልክ የጻፉት ነገር የለም። በእነሱ ዕምነት ሁሉም ነገር ከወያኔ ጭንቅላት ውስጥ የሚፈልቁና የሚተገበሩ እንደሆነ አድርገው ነው የሚያቀርቡት። ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምም ጋር የጠበቀ ግኑኝነት ስለነበራቸውና አሁንም ስላላቸው፣ በተለይም ብርሃኑ ነጋና ነዓምን ዘለቀ ስቴት ዴፓርትሜንት ውስጥ ይገቡና ይወጡ ስለነበር ዕምነታቸው በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና የእሱንም አጀንዳ ማስፈጸም ነው። ስለሆነም አሁን ከብርሃኑ ነጋ እንደምናየውና ድርጊቱም እንደሚያረጋግጠው እነዚህ ሰዎች በምንም ዐይነት ብሄራዊና ህዝባዊ አጀንዳ የላቸውም። ከወያኔና ከአቢይ አህመድ ፋሺሽታዊ አገዛዝ ተነጥለው ሊታዩ የሚችሉ ኃይሎች አይደሉም ማለት ነው። ለአገርና ለህዝብ ጠንቅ የሆኑ ኃይሎችና በአገራችንም ምድር በሳይንስና በቴክኖሎጂ የሚደገፍ ሰፋ ያለ ኢኮኖሚ እንዳይገነባ የሚታገሉ ናቸው።
በነገራችን ላይ ኤፍሬም ማዴቦ ለአገር ዕድገት አሳቢ ቢሆን ኖሮ ግንቦት ሰባትን መስርተው በሚንቀሳቀሱበት ዘመን በዕውቀት ላይ መረባረብ ነበረበት። ይህንን ከማድረግ ይልቅ ኤፍሬምም ሆነ ብርሃኑ ነጋ ሰፊውን ወጣት በማታለል ሰፋ ካለ ዕውቀት ጋር እንዳይተዋወቅ አድርገውታል። በተለይም እንደ ኢሳት የመሰለውን ውዥንብር ነዢ ሚዲያ በመክፈት ሰፊው ወጣት ከተሻለና አገርን ለማስገነባት ከሚያስችል ዕውቀት ጋር እንዳይተዋወቅ ለማድረግ በቅተዋል። ድረ-ገጽም መስርተው በድረ-ገጻቸው ላይ አንዳችም ዕውቀት አዘል ትምህርት ሲጽፉና ሲያስተምሩ አልታዩም። በወያኔ የአገዛዝ ዘመንም ተግባራዊ የሆነውን የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ደረጃ በደረጃ አደገኛነቱን በማሳየት ህዝብን፣ በተለይም ወጣቱን ሲያስተምሩ አልታዩም። ታዲያ አሁን በምን ተዓምር ነው የአስተሳሰብ ለውጥ ካልተደረገ በስተቀር ምንም ዐይነት መሻሻል ሊመጣ አይችልም እየተባለ የሚነገረን። ለአንድ አገር ዕድገት በመጀመሪያ ደረጃ አንድ ሰው ወይም ድርጅት ታሪካዊ ተልዕኮና ርዕይ ያስፈልገዋል። ለስልጣን ከመቅበዝበዝና ልታይ ልታይ ከማለት ይልቅ አንገትን ደፍቶ በመስራት ህዝብን ለማስተማር መጣር ያሰፍልጋል። በታሪክ ውስጥ እንደታየው ይህንን ለማድረግ የሚችሉ ሰዎች ደግሞ ከልጅነታቸው ጀምሮ ተኮትክተው ያደጉና ከጥሩ ዕውቀት ጋር የተዋወቁና በህዝብ ላይ የሚዘባነኑ ሳይሆኑ፣ ህዝብንና አገራችውን የሚያክብሩና ለማገልገል የተዘጋጁ ብቻ ናቸው። በአገራችን ምድር ኤፍሬም ማዴቦም ሆነ ሌሎች ሰዎች ለጥሩ ስራና አገርን ለማስከበር አልተፈጠሩም። ስለሆነም ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ህዝብ አዲስ ትውልድ ያስፈልጋቸዋል። በአሁኑ ዘመን የሚኖረውንና ያረጀውንና ያፈጀውን ምሁር ነኝ ባይ ጭንቅላት ማስተካከልና፣ ለአዲስና ለታሪካዊ ስራ እንዲነሳ ማድረግ በፍጹም አይቻልም። በሌላ ወገን ግን ተስፋ ሳንቆርጥ ይህ ዐይነቱ በአቢይ አህመድ የሚገዛውና የውጭ ኃይል ተላላኪ የሆነው ፋሺሽታዊ አገዛዝ ከስልጣን ላይ መወገድ አለበት የሚል ዕምነት አለኝ።
ይህን ካልኩኝ በኋላ በአገራችን ምሁራንና በታዳጊው ትውልድ ዘንድ ያለው ትልቁ ችግር ስለ ሁለ-ገብ ዕድገትና በአጠቃላይ ሲታይ ስለኢኮኖሚ ምንነት ያለን ግንዛቤ የተዛባ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ በተለይም ያረጀውና በአሁኑ ወቅት በ50ና ከዚያም በላይ ዕድሜ ውስጥ ያለው ምሁር ነኝ ባይ ትልቁ ችግር ኢኮኖሚክስን በሚመለከት የጠራ አመለካከት የለንም። ለምሳሌ በኢኮኖሚክስ ቲዎሪ ውስጥ ፊዚዮክራቲክስ፣ መርከንታሊስት፣ ክላሲካል ኢኮኖሚክስ፣ ኢንስቲቱሽናል ኢኮኖሚክስ፣ ማርክሲስት ኢኮኖሚክስ፣ ኒዎ-ክላሲካል ኢኮኖሚክስ፣ ኬኔሲያን ኢኮኖሚክስና ኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚክስ የሚባሉ የተለያዩ የኢኮኖሚክስ አስተሳሰቦች እንዳሉ በፍጹም አይታወቅም። አብዛኛዎቹ በኒዎ-ክላሲካል ወይም ኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚክስ ቲዎሪ የሰለጠኑ ስለሆነ ስለ ስራ-ክፍፍልና፣ በማኑፋክቸሪንግ ላይ ተመስርቶ መካሄድ ስላለበት ኢኮኖሚያዊ ክንዋኔ ግንዛቤ የላቸውም። በተጨማሪምው በሚገባ ሰለተደራጀ ቦታና(Space)በተቀላጠፈ መልክ መንቀሳቀስ ስላለባቸው የተለያዩ የማመለሻ መንገዶች፣ የባቡር ሃዲዶችና የከተማ ውስጥ መመላለሺያዎች በፍጹም ግንዛቤ የላቸውም። ከዚህም በላይ አንድን አገርና ህብረተሰብ ጥበባዊና በተስተካከለ መልክ መገንባት እንዳለበት አይረዱም። ዛሬ በአገራችን ምድር በትላልቅና በትናንሽ ከተማዎች ውስጥ በሚያስፈራ መልክ እንደሚታየው መዘበራረቅ ነው አስተሳሰባቸው።
ስለሆነም የሚመስላቸው ገበያ በነፃ የሚካሄድና በጠያቂና በአቅራቢ ህግ እንደሚደነገግ አድርገው ነው የሚገምቱት። በተለይም ደግሞ ሚክሮና ማክሮ ኢኮኖሚክስ የሚባሉ ከተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር የማይሄዱ ወይም ተጨባጭ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ሁኔታዎችን ማስነበብ በማይችሉ ነገሮች ጭንቅላታቸው ስለተጠመደ የህዝብን ችግር ለመፍታት በሚችሉ አማራጭ ቲዎሪዎች ላይ አትኩሮ ለመስጠት አይፈልጉም። ለምሳሌ ለምን የተለያዩ የኢኮኖሚክስ ቲዎሪዎች ይኖራሉ? አንደኛው በዚህ መልክ ሲረዳው ሌላውስ ለምን በሌላ መልክ ይረዳዋል? በማለት በመጓጓት ከተማሩት ውጭ ሌላ የኢኮኖሚ ቲዎሪዎችንና ፖሊሲዎችን ለማገላበጥና ራሳቸውን ለማስጨነቅ በፍጹም አይሞክሩም። ለምሳሌ ቤቨሊንና በሹምፔተር የተፈጠረውን የኢንስቲቱሽናል ኢኮኖሚክስና በካርል ማርክስ የተጻፈውን ዳስ ካፒታል በማንበብ ሌላ አቀራረብም እንዳለ በፍጹም ለመማር አይቃጡም። በተጨማሪም፣ ለአገር ግንባታ በጣም አስፈላጊ ከሆነው ከኢኮኖሚ ታሪክ(Economic History) ጋር ትውውቅ በፍጹም የላቸውም:: ይህም ማለት አብዛኞዎች ኢትዮጵያውያን ምሁራን ፋንታዚ የሌላቸው ናቸው። ስለሆነም የሳንይስንና የቴክኖሎጂን ዕድገት፣ በዚህም ላይ ተመስርቶ የሰፊውን ህዝብ ፍላጎት በማሟላት ጠንካራ አገር ለመገንባት ያላቸው ፍላጎት አልቦ ነው ማለት ይቻላል። አብዛኛዎችቹም ሳይንስና ቴክኖሎጂን እየተጠቀሙ በተጨባጭ ሲታይ በአገራችን ምድር ሳይንስና ቴክኖሎጂ የኢኮኖሚው መሰረት እንዳይሆኑ አጥብቀው የሚታገሉ ናቸው። በዚህም ምክንያት የተነሳ በአንድ መሰረተ-ሃሳብ ላይ በመስማማትና የብሄራዊ አጀንዳ በመንደፍ ለአገራችን ዕድገት መታገል በፍጹም አይቻልም። ይህን የተጣመመ አስተሳሰብ የሚቃወምና የሳይንስንና የቴክኖሎጂን ምንነት በመረዳት ወደፊት ገፍቶ በመውጣት ያረጀውን አስተሳሰብ የሚታገል አዲስ ኃይል ብቅ ማለት እስካልቻለ ድረስ በአገራችን ምድር ዕውነተኛ ዕድገት ሊመጣ አይችልም፤ የየግለሰቦች ነፃነትና የህዝባችንም ብሄራዊ ነፃነት የሚከበርባት አገር በፍጹም ልትገነባ አትችልም።
ይህ ዋናው መሰረተ-ሃሳብ ሲሆን በአገራችን ምድር በብዝሃን ፓርቲ(Multiparty System) አማካይነት አገርን መገንባት በፍጹም አይቻልም። የብዝሃን ፓርቲ መኖር እንዲያውም ለዕድገት ፀር ነው። አብዛኛዎችም በዕውቀት ዙሪያ የሚሰባሰቡና ያልተሰባሰቡ ስለሆነ በፖለቲካ ስም ህዝብን እያሹና የድህነቱኑና የኋላ-ቀርነቱን ዘመን እያረዘሙ ነው ለመኖር የሚፈልጉት። ስለሆነም በኢትዮጵያ ምድር ውስጥ በብዝሃን ፓርቲ ስም የሚንቀሳቀስ ድርጅቶች መከልከል አለበት። ዕውቅት አለን የሚሉና ለአገራቸውና ለህዝባቸውም የሚያስቡ ከሆነ በሰለጠኑበት ሙያ ምርምር በማድረግ መጽሀፎችን በመጻፍና የተለያዩ የምርምር ጽሁፎችን በማቅረብ አገራቸውን ሊያግዙ ይችላሉ። ፖለቲካ ወደ ንግድነት በተለወጠበት እንደኛ ባለው አገር ውስጥ በፖለቲካ ውስጥ መሳተፍ የባሰ ችግር ውስጥ ነው የሚከተን። ለዚህ መፍትሄው በተለያዩ ሙያ የሰለጠኑና አገር ወዳድ ምሁራን በስልጣን አካባቢ ቢሰባሰቡና ወደፊት ሊመሰረት የሚችለውን አገዛዝ ቢያማክሩ ልዩ ዐይነት የአገዛዝ መዋቅር መፍጠር ይቻላል። በዚህም መሰረት በአንድ ድርጅት ውስጥ በየስምንት ዐመቱ በፈረቃ የሚገዛ የአስተዳደር መዋቅር መፍጠር ያስፈልጋል። ለዚህ ተጨማሪ የሚሆን ልዩ ዐይነት የማስልጠኛ ኢንስቲቱት ቢቋቋም አዳዲስ የፖለቲካ ኤሊቶችን ማፍራት ይቻላል። የሚሰጠውም ትምህርት፣ የፖለቲካ ፊሎሶፊና የፖለቲካ ሳይንስ መሰረተ-ሃሳቦች፣ ሶስይሎጂ፣ የተፈጠሮ ሳይንስ፣ በተለይም ፊዚክስ፣ ሌሎች ኢንጂነሪንግ ነክ ነገሮች መሰጠት አለባቸው። ተማሪዎችም በየሰሚስተሩ የምርምር ጥናቶችን በማቅረብ ለመሪነት መታጨት ይችሉ አይችሉ መሆናቸውን ማረጋገጥ አለባቸው። በዚህ መንገድ ብቻ አዲስና ለህዝብ አገልጋይ የሆነ አመራር መፍጠር ይቻላል። መልካም ግንዛቤ!!
ማብራሪያ፤ በጥር ወር 2024 ዓ.ም ባወጣሁት ጽሁፍ ላይ ሰለገንዘብ አፈጣጠርና ስላሳለፈው ዕድገት ሳነሳ በ18ኛውና በ19ኛው ክፍለ-ዘመን፣ እንዲያም ሲል በ20ኛው ክፍለ ዘመን ላይ የአብዛኛዎቹ የካፒታሊስት አገሮች ገንዘብ በወርቅ እንደሚደገፍ ወይም ወርቅ የጀርባ አጥንት በመሆን ለኢኮኖሚው ዕድገት አመቺ ሁኔታን እንደፈጠረ ለማሳየት ሞክሬ ነበር። የአንዳንዶችም ጥያቄ ወርቅ ለገንዘብ የጀርባ አጥንት እንዴት ለመሆን እንደቻለ አብራራ የሚል ጥያቄ አቅርበውልኝ ነበር። በመጀመሪያ ደረጃ በአብዛዎቹ የካፒታሊስት አገሮች ውስጥ የወረቀት ገንዘብ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት ወርቅና ብር(Silver) በመቅለጥና የነገስታት ወይም የአገዛዞች ስዕል በመቀረጽ(Coined Money) እንደመገበያያ ገንዘብ ያገለግሉ ነበር። ወርቅና ብር የተፈጥሮ ሀብቶች ስለነበሩና እንደልብም ስለማይገኙ በጊዜው እያደገ ከመጣው ምርትና የንግድ እንቅስቃሴ ጋር ለመሄድ ባለመቻላቸው ወይም በበቂው አቅልጦ ማቅረብ ስላልተቻለ በጊዜው በነበሩ የኢኮኖሚክስ ጠበብቶች የተደረሰበት ድምዳሜ በወርቅ የተደገፈ ገንዘብ ማተምና የሚታተውም ኖት ወይም ብር በቀጥታ እንደገና ወደ ወርቅ የሚለወጥ(Covertible Money) ተግባራዊም ማድረግ ነበር። ይህም የወረቀት ገንዘብ የመገበያያ መሳሪያ ለመሆን በቃ። አንድ የወረቀት ገንዘብ ወይም ኖት ይህን ያህል የወርቅ መጠን(Ounce of Gold) እንዳለው ተብሎ ይታተም ነበር። ይሁንና ይህ በራሱ በማዕከላዊ ባንኮችም ሆነ በአገሮች መሀከል ያለውን የወርቅ መጠን በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሰው ስለመጣ በጀመሪያ እንግሊዝ፣ ቀጥሎ ደግሞ አሜሪካና ሌሎችም አገሮች የየአገራቸውን ገንዘብ በቀጥታ በወርቅ እንደማይለውጡ አበሰሩ። ወርቅም የጀርባ አጥንት መሆኑ እንዲቆም ተደረገ። ይሁንና አሁንም ቢሆን ለመጠባበቂያ በሚል በማዕከላዊ ባንኮች ከፍተኛ የሆነ የተጠፈጠፈ የወርቅ ክምችት አለ። መኖርም አለበት።
ስለሆነም በዛሬው ወቅት በአብዛኛዎቹ የካፒታሊስት አገሮች በኢኮኖሚው ውስጥ እንደመገበያያ፣ እንደመቁጠሪያና እንደ ሀብት ማከማቻ የሚውለው ወይም የሚሽከረከረው ገንዘብ(Fiat Mmoney) ከበስተጀርባው የመንግስታት ድጋፍ ያለበትና በማዕከላዊ ባንክም ህጋዊ የመገበያያ ገንዘብ(Legal Tender) ሆኖ የሚያገለግለውና ክውስጡም ምንም ዐይነት ነገር የሌለው ነው። የአገራችንም ገንዘም ልክ እንደ ካፒታሊስት አገሮች ከጥጥ የተሰራና የሚሽከረከር ነው። በአገራችንና በካፒታሊስት አገሮች መሀከል ያለው ልዩነት ግን የአገራችን ኢኮኖሚ የተዝረከረክ፣ ርስ በርሱ ያልተያያዘና በሳይንስና በቴክኖሎጂ ተደግፎ የማይንቀሳቀስ ኢኮኖሚ በመሆኑና፣ አብዛኛውም ህዝብ ተቀጥሮ ስለማይሰራና ተከታታይ ገቢም ስለሌለው የገንዘቡ የመሽከርከር ኃይል(Velosity of Money)በጣም ደካማ ነው። በዚህም ምክንያት የተነሳ የገንዘባችን ወይም የብር የመግዛት ኃይል በጣም የደከመ ነው። ክዚህ ዐይነቱ የገንዘብ የመግዛት ኃይል መዳከም ለመላቀቅ ከተፈለገ የግዴታ ከኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ መላቀቅና ኢኮኖሚውን በማኑፋክቸሪንግ ላይ በማስመርኮዝ ምርትን ማምረት ያስፈልጋል። ይህ ብቻ ሳይሆን በየኢኮኖሚው መስኮች መሀከል መተሳሰር እንዲኖር ኢኮኖሚውን ማቀድ ያስፈልጋል። ብርንም ከውጭ ገንዘብ ጋር ሲነፃፀር አለመቀነስ ወይም ቋሚ(Fixed Exchange Rate) እንዲሆን ማድረግ አስፈላጊ ነው። አሁን ካለው የልውውጥ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ ያፍለጋል። ለምሳሌ አንድ የአሜሪካን ዶላር ለመግዛት ለጊዜው አስር የኢትዮጵያ ብር ብቻ ማቅረብ እንደሚያስፈልግ በህግ መደንገግ። ብርንም በጠያቂና በአቅራቢ ህግ እንዳይደነገግ ማድረግ። በተጨማሪም የጥቁር ገበያን መቆጣጠርና በጥቁር ገበያ ላይ የሚሰማሩ ሰዎችን ከፍተኛ ቅጣት መቅጣት ሌላው እርምጃ ነው። ከዚህ በተጨማሪ አሁን የሚሽከረከረውን ገንዘብ በአዲስና በቀላሉ ፎርጅድ ሊሆን በማይችል ገንዘብ መተካትና፣ የድሮውን ገንዘብ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከገበያ እንዲወጣ ማድረግ፣ አዲሱን ገንዘብ አንድ ብር በድሮው በአስር መለወጥና፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከገበያ እንዲወጣ ማድረግ። በተጨማሪም የውጭ ምንዛሪን መቆጠብና(Managed Currency System) ከውጭ ለሚመጡ አስፈላጊ በሆኑና ምርቶችና ማሽኖችን ለሚያስመጡ አምራቾችና ሻጪዎች ብቻ መለወጥ። በምንም ዐይነት ለቅንጦት የሚሆኑ ዕቃዎችንና መጠጦችን፣ ለምሳሌ እንደ ውስኪና ኮኛክ የመሳሰሉትን ለሚያስመጡ የውጭ ከረንሲ አለመፍቀድ። የሚፈቀድም ከሆነ መጠጦችም ሆነ ሌላ የቅንጦት ዕቃዎችን በከፍተኛ ደረጃ መቅረጥ። በዚህ መልክ የውጭ ምንዛሪን መቆጠብ ይቻላል። ለዚህ ሁሉ መፍትሄው ደግሞ የግዴታ ከዚህ ዐይነቱ ፋሺሽታዊ አገዛዝና መዋቅሩና ፖሊሲ አውጭዎች መንጋጋ መላቀቅ ያስፈልጋል። አገራችንና ህዝባችን ብሄራዊ ስሜት ባላቸውና የውጭ ኃይሎች ተገዢ ባልሆኑና አገርን በታታሪነት ለማገልገል በተዘጋጁ ሰዎች መገዛት አለባት። አንድ አገርና ህዝብ በዝቃጭ ኃይሎችና የውጭ አጀንዳን በሚያራምዱ የስልጣኔ፣ እንዲያም ሲል የሳይንስና የቴክኖሎጂ ጠንቅ በሆኑ ኃይሎች የመገዛት ዕጣ ሊኖራት አይገባም።