እንደ ተርብ በራ ወግታቸው፤ ሊደፍሯት ሲቅነዘነዙ፤
አለቃት ብሎ ቂማቸው፤ ዛሬም እንደ ትናንቱ፤
ባንዳ አሳድገው ላኩባት፤ የሚያገለግል በሆዱ፡፡
መርዝ እንደ ዲዲቲ ረጭተው፤ ያልደፈሯትን ወይዘሮ፤
ዛሬ ጠለፈው ወሰዷት፤ አምልገው ገብተው በጓሮ፤
ውሾችን ፓውንድ አጉርሰው፤ እያማለሉ በዩሮ፡፡
ጭንጋፍ ልጆቿን አንስተው፤ እንኩቤተር ውስጥ አኑረው፤
እንደ ጥንብ አንሳ አራብተው፣ እንደ ኖህ ቁራ ቀፍቅፈው፣
በቋንቋ አሙካ አንቅረው፤ በዘርም እድፍ አጥምቀው፤
እንደ ተምች አሰማሩባት፤ እንዲያዳክሟት ቆራርጠው፡፡
እርጥባን ንፍሮን እርዳታ፤ ለእድገት ለጤና እያሉ፤
እርጉም ልጆቿን ቀልበው፤ ወዳጄ ጓዴ እያሉ፤
የቋንቋ ካራ አቅርበው፤ ገላዋን እያስመተሩ፤
ምስጢሯን ሁሉ ገላልጠው፤ ድንግልናዋን ገፈፉ፡፡
የራሷን ድንበር ተሻግራ፤ የሰውን ምድር ባትነካም፤
አፍሪካን ነፃ በማውጣት፤ አለም ጠቅላላ ቢያውቃትም፤
ጎረቢቶቿን በፍቅር፤ ቡና እምትጋብዝ ብትሆንም፤
እጇ አመድ አፋሽ ነውና፤ ተኝተውላት አያውቁም፡፡
በሰላም በፍቅር እንዳትኖር፤ እንደ በፊቱ ተከብራ፤
አዳቅለው ለቀውባታል፤ ነክሶ እሚያናክስ ቡችላ፤
ታይቶም እማይታወቅ፤ የውሻና ጅብ ዲቃላ፡፡
በአፈሯ ጥጥን አብቅለው፤ ውኃዋን ለመስኖ አውለው፣
ፉሉን በባውንድ ጠቅልለው፤ ለቤቷ ውሾች አጉርሰው፤
ጀርባዋን ልጠው ወሰዱት፤ እንደ ፍሪንባ አውጥተው፡፡
በክብር አልባ ገዥዎች፤ በደላላዎች ተይዛ፤
የአርበኛ ያለህ ትላለች፣ ክብሯን ፈልጋ እማማ!
ልጆቿ ከውጪ ቢጮሁ፤ ቢያመልክቱ ለዓለምም፤
ሞቷን የሚመኝ እንጅ፤ የሚታደጋት አልታዬም፡፡
ፍትህ ጋጋሪ ወይዘሮ፤ የሰው መገኛ ብትሆንም፤
ማንም በእውነት መስክሮ፤ ፍርድ ሰጥቶላት አያውቅም፡፡
ከጀንበር መግቢያ አድሎ እንጅ፤ ፍትህ አይጠበቅም፤
ሮማውያኖች ፈርደው ነው፤ የተሰቀለው አምላክም፡፡
በኤደን ምስል ቢስላት፤ በክብር ቢያነሳት መጣፉም፤
የፍትህ ምድር እያለ፤ ቢያቆላምጣት ቁርአኑም፤
ቂመኛ ጠላትን እንጅ፤ ወዳጅ አፍርታ አታውቅም፡፡
በዓለማዊ ጥቅም ተይዘው፤ ልጆቿ ለግመው ቢተኙም፤
የእናት ትካዜ ውሎ ሲያድር፤ ጎናቸው ምድር አይነካም፤
እንደ ቀደምቶች በአንድነት፤ መነሳታቸው አይቅርም፤
ከጉድጓዱ ውስጥ ሊያወጣት፤ ፈጥኖ ይደርሳል አምላክም፡፡
ይሁዳ መቅቡጡን ልሶ፤ ጠቁሞ ችሎት ቢያውላት፤
ፈሪሳውያንም መስክረው፤ እንድትሰቀል ቢያደርጓት፤
ጲላጦስ እጆቹን ታጥቦ፤ የሞት ውሳኔ ቢሰጣት፤
በቋንቋ በዘር ካስማ ላይ፤ እጇን ከርችመው ቢሰቅሏት፤
በጎጥ እራፊ ከፍነው፤ በክልል ሳጥን ቢቀብሯት፤
እኔም እንደ አቅሜ ህልም አለኝ፤ ወድቃ አትቀርም የኛ እናት፡፡
ብድግ ትላለች እማማ፤ በቅዱስ ልጆች መስዋእት፤
መቃብርን ሰንጥቃ ወጥታ፤ ዳግም ልትሆን እመቤት፤
በእምነት በጸሎት በርትታ፤ ዳዊት በመዝሙር እንዳላት፤
እጇን ዘርግታ ወደ አምላክ፤ ቡራኬ ደርሷት ምርቃት፡፡
ወድቃ አትቀርም የኛ እናት፤ በክልል ሳጥን ቀብረዋት፤
ብድግ ትላለች እማማ፤ በጀግና ልጆች መስዋእት፤
መቃብርን ሰንጥቃ ወጥታ፤ ዳግም ልትሆን እመቤት፤
በእምነት በጸሎት በርትታ፤ ዳዊት በመዝሙር እንዳላት፤
እጇን ዘርግታ ወደ አምላክ፤ ቡራኬ ደርሷት ምርቃት፡፡
በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)
የካቲት ሁለት ሺ ሰባት ዓ.ም.