February 7, 2024
27 mins read

የአዋሽ አርባ: የበረሃው ጓንታናሞ

c93e58a0 b9f0 11ee 896d 39d9bd3cadbbአዋሽ አርባ፡ በኢትዮጵያ ከጅምላ እስር ጋር ስሙ የሚነሳው ‘የበረሃው ጓንታናሞ’

ዝገባው የ አማርኛ ነው

ባለፉት አስርተ ዓመታት በአዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይፈጸምበት ስለነበረው ማዕከላዊ እስር ቤት ብዙ ሰምተናል። ‘ጄል ኦጋዴን’ ተብሎ ከሚጠራው የጂግጅጋ ከተማ ማረሚያ ቤት የወጡ የሰቆቃ ድምጾችንም እንዲሁ። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚፈራረቅባት ኢትዮጵያ በርካቶች ስለሚታሰሩበት የአዋሽ ወታደራዊ ካምፕ ግን ብዙ የተባለለት ነገር የለም።

አዋሽ አርባ ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት በተለይ በሕዝባዊ ተቃውሞ እና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት እስረኞችን በጅምላ ለመቅጣት ሁነኛ ምርጫ ሲሆን ተስተውሏል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው እና በአህአዴግ እንዲሁም በብልጽግና አስተዳደር ታስረው የወጡ ግለሰቦች በተፈጸሙባቸው የመብት ጥሰቶች ምክንያት ሥፍራውን “የምድር ሲኦል” ሲሉ ይገልጹታል።

ለመሆኑ አዋሽ አርባ ያለው ምንድን ነው? ወታደራዊ ካምፑ ሲመሰረትስ ለእስረኛ ማቆያ የተዘጋጁ ቦታዎች ነበሩት? ተጠርጣሪዎችስ ወደ አዋሽ የሚጋዙት ለምንድን ነው?

ቢቢሲ ወታደራዊ ካምፑ ሲመሠረት በወቅቱ በአመራርነት ላይ የነበሩ የጦር መኮንኖችን እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን በማነጋገር እንዲሁም ካምፑን የተመለከቱ ሰነዶችን መሠረት በማድረግ ታሪካዊ ዳራውን ለመዳሰስ ሞክሯል።

የአጼ ኃይለ ሥላሴ ንጉሣዊ ሥርዓት ተገርስሶ ጊዜያዊው ወታደራዊ አስተዳደር – ደርግ የሥልጣን መንበሩን ከተቆጣጠረ በኋላ አልጋ በአልጋ የሆነ ነገር አልገጠመውም።

ለውጡን ተከትሎ ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ የገባችው ኢትዮጵያ፣ በፖለቲካ ኃይሎች መካከል ደም አፋሳሽ ግጭቶችን አስተናግዳለች። በዚህም አያሌ ምሁራንን እና ወጣቶችን ቀርጥፎ የበላው የቀይ ሽብር ጭፍጨፋ ተጠቃሹ ነው።

በወቅቱ ወታደራዊው መንግሥት በምሥራቅ እና በደቡብ በሶማሊያ ወረራ፣ በሰሜን ደግሞ በኤርትራ ሽምቅ ተዋጊዎች፣ በመሃል አገር ደግሞ በኢህአፓ እና በመኢሶን ውስጣዊ ትግል ተወጥሮ የተያዘበት ፈታኝ ጊዜ ነበር።

በዚህ ወቅት ነበር አዋሽ አርባ ለደርግ ፈጥኖ የደረሰለት።

አዋሽ አርባ ከመዲናዋ አዲስ አበባ በ220 ኪሎ ሜትሮች ገደማ ርቀት ላይ በአፋር ክልል ውስጥ የሚገኝ ቦታ ነው።

አየሩ ሞቃታማ፣ መሬቱም አሸዋማ።

ወታደሮችን ለማሠልጠን የመሬት አቀማመጡ እና የአየር ጠባዩ የተመረጠ እንደሆነ ይነገርለታል። በዚያ ላይ የሶማሊያን ወረራ እና የሰሜን ሸማቂዎችን ለመመከት የሚያመች ሁነኛ ቦታ።

ሆኖም ካምፑ ሲመሠረት ለዚሁ ዓላማ ተብሎ የተመረጠ እንዳልነበረ የካምፑን የአመሠራረት ታሪክ ለቢቢሲ ያጋሩ እና ለደኅንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የቀድሞ የጦር መኮንንኖች ይናገራሉ።

እነርሱ እንደሚሉት ቦታው መጀመሪያ ላይ በመንገድ ግንባታ ላይ የተሰማራ ተቋም ካምፕ ነበር።

ካምፑ የአዲስ አበባ – አሰብ መንገድን ለመሥራት መቀመጫውን እዚያ አድርጎ በነበረው ‘ትራምፕ’ በሚባል የመንገድ ተቋራጭ ኩባንያ ነው የተቆረቆረው።

ትራምፕ የጀርመን ኩባንያ ነበር። ኩባንያው መንገዱን ሰርቶ ሲጨርስ አካባቢውን ለቆ ወጣ።

ይህ ነበር በወቅቱ የበጀት እጥረት ለገጠመው የደርግ ሥርዓት ጥሩ አጋጣሚ የፈጠረለት።

ካምፑ በብሎኬት የተሰሩ አጫጭር ቤቶች ነበሩት። ጥሩ መዋኛ ገንዳ እና ምግብ ቤቶች፤ ከሞላ ጎደል መሠረተ ልማቱም የተሟላለት ነበር።

አካባቢው ግን ትምህርት ቤት፣ ሐኪም ቤት፣ ወፍጮ ቤት፣ የእምነት ተቋማት የሌሉበት ምድረ በዳ ነበር።

አርባ የተባለው መንደርም ለመንገድ ግንባታው ሠራተኞቹ ሻይ እና ምግብ ለማቅረብ በአካባቢው በከተሙ ሰዎች ቀስ በቀስ ነበር የተቆረቆረው።

በጥድፊያ ላይ የነበረው የደርግ መንግሥት ታዲያ ትራምፕ ኩባንያ ጥሎት የወጣውን ካምፕ በመጠቀም የተወሰነ ጦር በአስቸኳይ ወደ ካምፑ እንዲገባ አድርጎ የመጀመሪያውን አንድ ሻለቃ ጦር (500 ወታደር) አሰለጠነ።

በጦር ግንባሮች ያሉ የወታደሮች ቁጥር መሳሳት ሲጀምሩ እና ተጨማሪ ሠራዊት ለማሰልጠን ከያኔዋ ሶቪየት ኅብረት ግብዓቶችን በማስመጣት አስር ብሎክ የጣውላ ቤቶችን አሰራ።

የጦር አመራሮቹ እንደሚሉት እነዚህ መኖሪያ ቤቶች ሁሉም ነገር የተሟላላቸው የነበሩ ሲሆን፣ ለመኮንኖች እና ለአማካሪዎች የተሠሩ ነበሩ።

ቀስ እያለ የውትድርና ሠልጣኞች ቁጥር እየተበራከተ መጣ። በአፋጣኝ ግድግዳውም ጣሪያውም ቆርቆሮ የሆነ አንድ ብሎክ ቤት ተሠራ። ከዚህ በኋላ ነበር የበታች ሹም አካዳሚ ተብሎ በይፋ የተመሠረተው።

ትዕዛዙን የሰጡትም አሁን በስደት ዚምባብዌ የሚገኙት የአብዮታዊ ጦር ጠቅላይ አዛዥ እና የደርግ ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለማሪያም ነበሩ። ጊዜው ደግሞ 1970 ዓ.ም.።

‘የበታች ሹም አካዳሚ’

በዚህ ካምፕ የሚሰለጥኑት የበታች ሹማምንት ነበሩ። የበታች ሹማምንት የእግረኛ ጦር መሪዎች ማለት ናቸው። በአንድ ውጊያ ውስጥ ያላቸው ሚና ከፍ ያለ ነው። የጦር መኮንኖች ቢጎዱ አሊያም ቢሞቱ እነርሱን ተክተው የሚያዋጉ ማዕረጋቸው ትንሽ፣ ሚናቸው ግን ትልቅ የጦር መሪዎች ናቸው።

ያኔ ሌተናንት ኮሎኔል አሊ ሐጂ አብዱላሂ የትምህርት ቤቱ አዛዥ ነበሩ።

እየቆየ ሲሄድ በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ የማሠልጠኛ ካምፖችን ለማስተዳደር እና ለድርጅታዊ ሥራዎች ችግር በመፈጠሩ የካቲት 1971 ዓ.ም. አርባ የተባለው የጦር ሰፈር ተገነባ።

በወቅቱ በውጊያ የቆሰሉ የጦር መኮንኖችን በመያዝም በአራት ካምፖች ውስጥ ታንከኞች እና ሜካናይዝድ ጦሮችን አስገብተው ማሠልጠን ጀመሩ።

ከዚያ በኋላ የበታች ሹም አካዳሚ መሆኑ ቀርቶ ‘የውጊያ እና የቴክኒክ አገልግሎት ትምህርት ቤት’ ተብሎ አድማሱን አሰፋ።

ደብረዘይት የነበረው የአየር መቃወሚያ፣ ናዝሬት የነበረው ሜካናይዝድ ጦር ማሠልጠኛ፣ እዚያው አዋሽ የነበረው ታንከኛ እና መድፈኛ አንድ ላይ ተሰባስበው በ1972 ዓ.ም. የተሟላ የውጊያ ትምህርት ቤት ለመሆን በቃ።

አዋሽ አርባ የወታደሮችን አቅም የሚፈትሽ ለሥልጠናው ምቹ ቦታ እንደሆነ የጦር አመራሮቹ ይናገራሉ።

ይህ ወታደራዊ ካምፕ ከአገር ውስጥ ባሻገር ከፍተኛ የውጭ ጄኔራሎች ጭምር እንደፈሩበት ‘የውጊያ ትምህርት ቤት አርባ’ በሚል ርዕስ የታተመ አንድ የምረቃ መጽሔት ላይ በአጭሩ ሰፍሯል።

አሁን ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማሪያ የሚገኙባት የዚምባብዌ የነጻነት ታጋዮች ሥልጠና እና ትጥቃቸውን አሟልተው የሄዱት ከዚሁ ካምፕ ነበር።

“እነዚህ ወታደሮች መንግሥቱን እንደሚጠይቁትና አሁን ላይ ትላልቅ ጄኔራሎች እንደሆኑ ሰምቻለሁ” ብለዋል ቢቢሲ ያነጋገራቸው የዚያን ጊዜው የጦር አመራር።

በተጨማሪም ከደቡብ አፍሪካ እና ከደቡብ ሱዳን መጥተው በተመሳሳይ ሥልጠናቸውን እና ትጥቃቸውን አሟልተው የሄዱ የነጻነት ታጋዮችም ጥቂት አልነበሩም።

ሥልጠናውን የሚሰጡት የጦር አዛዦችም በቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት እና በኩባ ተምረው የመጡ ነበሩ።

በግቢው ውስጥ ሩሲያኛ፣ ስፓኒሽ እና እንግሊዝኛ ቋንቋዎች ይነገርበት ነበር።

በካምፑ የሠለጠኑት የሌሎች አገራት የነጻነት ታጋዮች ከነጻነት በኋላ በአገራቸው ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደሚደርሱ እሙን ነው የሚሉት ምንጮቻችን፣ ብዙዎች ጥሩ ደረጃ ደርሰው እንደሚሆንም ይገምታሉ።

ቢቢሲ በተመለከተው መጽሔት ላይ እንደሰፈረው ጄኔራል አሊ ሐጂ አብደላህ የመጀመሪያው አዛዥ ነበሩ። ከዚያም ኮሎኔል ኃይለ ተስፋሚካኤል፣ ጄኔራል ተስፋዬ ትርፌ፣ ጄኔራል ሞገስ በቀለ፣ ኮሎኔል እጅጉ ላቀው፣ ብርጋዲየር ጄኔራል ካሳዬ ጨመዳ፣ ጄኔራል ኃየሎም አርአያ የትምህርት ቤቱ አዛዥ ሆነው አገልግለዋል።

የዚህ ጽሑፍ ዋናው ትኩረት አዋሽ አርባ ቢሆንም ስለአዋሽ ሰባትም በዚሁ ጠቆም አድርገን እንለፍ። በደርግ ዘመን የአዋሽ ሰባት ካምፕ የአዲስ አበባ – አሰብ እንዲሁም የሚሌ መንገድን የሚቆጣጠር መቶኛ ብርጌድ ካምፕ እንደነበር የጦር አመራሮቹ ያስታውሳሉ።

እነርሱ እንደሚሉት የዚህ ብርጌድ ዋነኛ ሥራው መንገድ ጥበቃ ብቻ ነበር። የመንገድ ጥበቃው ዋና መሥሪያ ቤትም ነበር።

ከደርግ መውደቅ በኋላ ኢህአዴግ ሥልጣን በያዘበት ጊዜ በስፍራው ላይ አዲስ ካምፕ ተሰርቶ የጦር መኮንኖች ማሠልጠኛ ሳይሆን እንደማይቀርም አመራሮቹ ጠቁመዋል።

f6797a70 b9f0 11ee 896d 39d9bd3cadbb

ታዲያ እስረኞች እየተጋዙ የሚታሰሩት ምን ላይ ነው?

ኢህአዴግ የአገሪቱን መሪነት መንበረ ሥልጣኑን ከተረከበ በኋላ በቀደመው ዘመን የተኩስ ልምምድ በሚደረግበት አካባቢ ዘመናዊ ቤቶች የተሠሩ ሲሆን፣ ለአሠልጣኞች እና ለቤተሰባቸው መኖሪያ ይሆን ዘንድም ባለሁለት ፎቅ ቤቶች ተገንብተዋል።

ከወራት በፊት ካምፑን ጎብኝተውት እንደነበር የሚናገሩት የቀድሞው የጦር አመራር “ቀድሞ ከነበረው አድጎ እና ተሻሽሎ ነበር ያገኘሁት” ብለዋል።

ሆኖም ለአውራ ጎዳናው ካምፕ ተብለው የተሰሩት አጫጭር ቤቶች የእስረኛ ማቆያ መደረጋቸውን ታዝበዋል።

እርሳቸው እንደሚሉት በካምፑ ውስጥ ሰዎችን ማሰር የተጀመረው በኢህአዴግ የሥልጣን ዘመን ነው።

ኢህአዴግ በተለይ በ1993 ዓ.ም. እና በ1997 ዓ.ም. በገጠመው ተቃውሞ ወቅት አዋሽ አርባን ጨምሮ በዴዴሳ፣ በጦላይ እና በሌሎች ወታደራዊ ካምፖች ውስጥ በሚገኙ ጊዜያዊ ማቆያ ቦታዎች ሰዎችን ያስሩ እንደነበርም የቅርብ ጊዜ ትውስታቸው እንደሆነ ይናገራሉ።

“አሁን አገሪቷን እያስተዳደሩ ያሉትም ከእነርሱ ተምረው ድሮ የነበሩትን አሮጌ ቤቶች ለማሰር ይጠቀሙባቸዋል” ብለዋል።

በተለያዩ ጊዜያት የተከሰቱ አለመረጋጋቶችን ተከትሎ ከተደነገጉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች ጋር በተያያዘ በጅምላ የተያዙ ግለሰቦች በእነዚህን ቤቶች እንደሚታሰሩ እና የመብት ጥሰቶች እንደሚፈፀምባቸው የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎች በሚያወጧቸው ሪፖርቶች ሲገልጹ ቆይተዋል።

በዚህ የታሳሪዎች ማቆያ ስፍራ ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት አካላዊ እና ሥነ ልቦናዊ ሰቆቃዎች ተፈጽመውብናል የሚሉ ሰዎች፣ ቦታውን አሜሪካ የአል ቃኢዳ ተጠርጣሪዎችን ያለፍርድ ይዛ ካቆየችበት “ጓንታናሞ ቤይ” ጋር ያመሳስሉታል።

“በደርግ አስተዳደር ዘመን እንደዚህ ዓይነት እስር አልነበረም” የሚሉት ቢቢሲ ያነጋገራቸው የጦር መኮንን፣ ደርግ ለእስር ይጠቀም የነበረው ፖሊስ ጣቢያዎችን እና ወህኒ ቤቶችን እንደነበር ያስታውሳሉ።

በእርግጥ ነጻ የመገናኛ ብዙኃን፣ የአገር ውስጥ የሰብዓዊ መበት ተቋማት እና ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሌሉበት በዚያ ዘመን በካምፑ ስለተፈጸሙ ነገሮች በትክክል የሚታወቅ ነገር የለም።

የሕግ ባለሙያው እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ያሬድ ኃይለማሪያም ግን “በደርግ ጊዜም ቢሆን እነዚህ የጦር ካምፖች ለእንደዚህ ዓይነት አገልግሎት መዋላቸው ምንም ጥያቄ የለውም” ይላሉ።

ተሟጋቹ ወታደራዊ ካምፖች ዜጎችን ለማሰቃየት ይውሉ እንደነበር እንደ ማሳያነት የሚጠቅሱት የቀይ ሽብር የክስ ሂደቶችን ነው።

አቶ ያሬድ የሕግ ባለሙያ ሲሆኑ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል ዋና ዳይሬክተርም ናቸው። በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ዋና መርማሪ ሆነው ለስምንት ዓመታት ሰርተዋል።በዚህ ወታደራዊ ካምፖች የተፈፀሙ አንዳንድ ጉዳዮችንም መርምረዋል።

በኢህአዴግ ጊዜ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች የሰፈሩበት ሕገ መንግሥት፣ ሚዲያዎች እና የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ቢኖሩም፤ሥልጣን በያዘ ማግሥት የኢሠፓ አባላትን ለተሃድሶ በሚል ወስዶ ያሰራቸው በወታደራዊ ካምፖች እንደነበር ያሬድ ያስታውሳሉ።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮም በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚነሱ አመጾችም ይሁኑ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የተያያዙ ግጭቶች ሲኖሩ በጥርጣሬ ‘የሚታፈሱ’ ሰዎች የሚወሰዱት ወደ ወታደራዊ ካምፖች ሆኗል።

“እስካሁንም ከዚህ አዙሪት አልወጣንም” ይላሉ አቶ ያሬድ።

“አጣርተን እናስራለን እንጂ፣ አስረን አናጣራም”

በአገሪቷ ከተከሰቱ ተቃውሞዎች በኋላ ከአምስት ዓመታት በፊት ወደ ሥልጣን የመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “አጣርተን እናስራለን እንጂ አስረን አናጣራም” በማለት በመጀመሪያዎቹ የሥልጣናቸው ወራት በቀደመው አስተዳደር የታሰሩ የፖለቲካ እስረኞችን እንዲለቀቁ በማድረጋቸው ውዳሴን አትርፈው ነበር።

በወቅቱም በመላው አገሪቱ በሚገኙ እስር ቤቶች ውስጥ የነበሩ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ እስረኞች የተለቀቁ ሲሆን፣ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ተመራማሪ የነበሩት አቶ ፍስሐ ተክሌም ነጻ የወጡት ሰዎች አሃዝ 45 ሺህ እንደሚደርስ ተናግረው ነበር።

ሆኖም ይህ የቆየው ለአጭር ጊዜ ነበር።

ከዚያ በኋላም የጅምላ እስር እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ጉዳዮች የአገር ውስጥ እና የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች የዘወትር ሪፖርት ሆኗል።

ያሬድ “የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር የሕዝብ ቅቡልነት ለማግኘት ከተደረገ የምርጫ ዘመቻ ንግግር የተለየ ባህርይም የለውም” ይላሉ።

ለዚህም የሚያቀርቡት ምክንያት በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ምሎ ሥልጣን የያዘ አካል ማንኛውም ሰው ያለማስረጃ እንዳይታሰር፣ ሳይጣራ እንዳይታሰር፣ ፍትሕ እንዳያጣ እና ዋስትና እንዳይከለከል ማድረግ ችሮታ ሳይሆን ግዴታው ነው የሚል ነው።

ሆኖም አሁን ላይ በአገሪቷ ተባብሶ የሚታየው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ጉዳይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ከቁርጠኝነት የመነጨ እንዳልሆነ እንደሚያሳይ ይናገራሉ።

ሲቪል ሰዎችን ለምን በወታደራዊ ካምፖች?

ባለፉት አስርተ ዓመታት በተለይ በተደጋጋሚ በታወጁት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች ወቅት የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እስረኞችን ከከተማ ርቀው ወደሚገኙ ወታዳራዊ ካምፖች ሲወስዱ ይስተዋላል።

ይህም በጅምላ ለማስቀመጥ የሚመች ቦታ ስለሆነ እና ጥብቅ ወታደራዊ ጥበቃ ስላለ እንደሆነ ይነገራል።

በሌላ በኩል አካባቢዎቹ በተፈጥሮ ፈታኝ በሆኑ ቦታዎች ላይ የተመሠረቱ በመሆናቸው ታሳሪዎች ላይ ሥነ ልቦናዊ ጫና ለመፍጠር፣ ያለጠያቂ ለማስቀረት፣ ከመገናኛ ብዙኃን እና ከሌሎች የመብት ተሟጋቾች ዕይታ ለመሰወር ነው የሚሉ ክሶችም ይቀርባሉ።

ኢሰመኮ በአዋሽ አርባ ታስረው የሚገኙ የምክር ቤት አባላትን እና ሌሎች ታሳሪዎችን ከጎበኘ በኋላ ባወጣው ሪፖርት በአዲስ አበባ ያለው የፌዴራል ፖሊስ ማቆያ ጣቢያ በመጣበቡ እስረኞቹን ወደ ጊዜያዊ ማቆያው ማምጣት እንዳስፈለገ በፖሊስ ገለጻ እንደተደረገለት አመልክቷል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ያሬድ እንደሚሉትም በአገሪቷ ውስጥ አለመረጋጋት ሲከሰት በሚደነገጉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች የጅምላ እስሮች ስለሚኖሩ መደበኛ እስር ቤቶች እነርሱን ለማስተናገድ በቂ አይሆኑም። በመሆኑም ወታደራዊ ካምፖችን ጨምሮ መጋዘኖች፣ ትምህርት ቤቶች ሳይቀሩ ለዚህ አገልግሎት ይውላሉ።

ነገሩ ግን ከዚህም ያለፈ ነው ይላሉ የመብት ተሟጋቹ።

‘ተፈጥሮን እንደ ማሰቃያ’

አዋሽ አርባ ለወታደር ማሠልጠኛ እንጂ ለሲቪሎች ምቹ የሆነ ስፍራ አይደለም። በአካባቢው ከፍተኛ ሙቀት አለ። ቢጫ ወባን ጨምሮ የወባ ወረርሽኝ የሚያጠቃው አካባቢ ነው።

ለሥራ ጉዳይ ወደ አካባቢው የሚሄድ ሰው ጥንቃቄ የሚያደርግበት ቦታ ነው። ራሳቸውን ይጠብቁ ዘንድም ‘የበረሃ አበል’ የሚከፈልበት አካባቢ ነው።

ሆኖም በቂ ምግብ፣ ውሃ እና መታጠቢያ በሌለበት እስረኞችን ማቆየት ተፈጥሮን እንደ ማሰቃያ መጠቀም እንደሆነ አቶ ያሬድ ይናገራሉ።

ሲቪል ሰዎችን በወታደራዊ ካምፖች ማሰር ምንም ዓይነት ሕጋዊ መሠረት የለውም የሚሉት ተሟጋቹ፣ ወታደራዊ ሥልጠናዎች እንደቅጣት የዋሉባቸው አጋጣሚዎችም በሪፖርቶች እንደተሰነዱ አመልክተዋል።

ይህም ከዚያ በሚወጡ ታሪኮች ምክንያት ጋዜጠኞች ዝም እንዲሉ፣ ሕዝቡም በፍርሃት ተሸብቦ እንዲኖር እንደ መቀጣጫም ጭምር ነው ጥቅም ላይ የሚውሉት ይላሉ።

አቶ ያሬድ በሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ምርመራ በሚያደርጉበት ጊዜ በትግራዩ ጦርነት ወቅት በአዋሽ አርባ የወታደር ካምፕ የታሰሩ ጋዜጠኞች ላይ ከፍተኛ የሰብዓዊ ጥሰት እንደተፈፀመ ለመረዳት ችለዋል።

“እስካሁንም የአዕምሮ ቁስለት (ትራውማ) አለቀቃቸውም” ብለዋል።

በአዋሽ አርባ የእስረኞች ማቆያ ማዕከል ውስጥ ይፈጸማሉ ስለሚባሉት የመብት ጥሰቶች እና በደሎችን በተመለከተ ቀደም ሲል የነበረውም ሆነ የአሁኑ የአገሪቱ አስተዳዳር በይፋ ያሉት ነገር የለም።

[በቀደመውና በአሁኑ አስተደዳር በአዋሽ ሰባት እና አዋሽ አርባ በሚገኙ ወታደራዊ ካምፖች ውስጥ በሚገኙ ጊዜያዊ ማቆያዎች ታስረው የተለቀቁ ግለሰቦች ያጋሩንን ታሪክ በቀጣይ ዘገባዎቻችን ይዘን እንመለሳለን።]

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

maxresdefault 6
Previous Story

ከሰሞኑ በብጹዕ አቡነ ጴጥሮስ ላይ የደረሰው እንግልት አንጀቴን በላው።

188655
Next Story

የጠቅላዩ ሹመቶች፣ ቅዱስ ሲኖዶሱ ተሰበሰበ፣ ከትግራይ ወደአማራ ገባ የጠባለው መሳሪያ | ፋኖ የመጨረሻ ክተት አወጀ

Latest from Blog

blank

አርበኛ አስረስ ማረ እና ምርኮኞቹ | ስለ ፋኖ የብሔራዊ ባንክ ገዥው ያልተጠበቀ ንግግር |

#ሰበር_ዜና #AmharaFano ➢መሰከረም 29/01/2017 ዓ.ምብዙ ድሎችን አግኝተናል፣➢1️⃣115 ምርኮኛ ➢2️⃣70 እስረኞችን አስለቅቀናል➢3️⃣ 7 ብሬን➢4️⃣2 ድሽቃ➢5️⃣ 4 ስናይፐሮችን➢ለትግል የሚጠቅሙ የነፍስ ወከፍ ክላሾችንተተኳሾችን መኪኖችም ገቢ… pic.twitter.com/GbYaOAtFtr — ትዝብቱ🔔 (@Geteriew1) October 12, 2024 በፋኖ የተማረኩት ኮሎኔል
blank

ትግሉ ይጥራ – ከጥሩነህ ግርማ

የህልውና ትግሉን ወደሚቀጥለው ምዕራፍ ለማሸጋገር የኦይዶሎጂ ብዥታን ማጥራትና በመሬት ላይ ያለውን ተንኮል መጋፈጥና ማፅዳት ያስፈልጋል የህልውና ትግሉ በአማራ ብሄርተኝነት ላይ ያጠነጠነ እንደመሆኑ የመኖር አለዚያም እንደ ህዝብ  የመጥፋት ትግል ነው: ሌላው ኢትዮዽያዊ ወገን
blank

የፋሽስቱ አብይ አህመድ አሊ ኢትዮጵያ ውስጥ በአማራ ላይ እየተካሄደ ስለሚገኘው ጦርነት ከመስከረም 13 እስከ 27/2017 ዓ.ም በተለያዩ ቦታዎች ላይ የደረሰ የጉዳት !!!መረጃ:

ሸዋ በሸዋ ጠቅላይ ግዛት መርሀቤቴ አውራጃ በደራ ወረዳ ልዩ ስሙ ኮሉ በተባለ አካባቢ ላይ በሚገኙ የአማራ ተወላጆች ላይ አሸባሪው የሸኔ ቡድን ከኦሆዴዱ ጥምር ጦር ጋር ቅንጅት በመፈጠር መስከረም 22 ቀን 2017ዒ.ም ከለሊቱ
Go toTop