(ክፍል አንድ)
በዓቢዩ ብርሌ (ጌራ)
ለእናት አገራችን ኢትዮጵያ በዓለም ዝናን ካተረፉላት ታላላቅ የባህልና የታሪክ ቅርሶች አንዱና ዋነኛው፣ የቋንቋ፣ የሃይማኖት፣ የዘርና የብሔር አጥር ሳይከልላቸው ሕዝቦቿ፣ ለዘመናት ተከባብረው፣ ተቻችለው፣ ተፋቅረው፣ ተሳስበውና ተዛዝነው፣ ተጋብተውና ተዋልደው፣ ያገኟትን አብረው ተካፍለው እየበሉ መኖር መቻላቸው ነው፡፡ ይህን ግሩም የሆነ የአገራችን ቅርስ ህልውናና ቀጣይነት፣ በየጊዜው ፈተና ውስጥ የሚያስገቡት መንግሥታትና መሪዎች እንጂ ሕዝቡ ራሱ አይደለም፡፡ ለዚህም መልካም ባህል መገንባትና ዘመን ተሻጋሪ መሆን፣ የአገራችን ቤተ እምነቶች፣ በተለይም ታላላቆቹ የጥንት ሃይማኖቶቿ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና እስልምና ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ እነሱ እርስ በርስ ተከባብረውና ተቻችለው፣ ኅብረተሰቡንም እንደ ድርና ማግ አዋህደው፣ ሕዝባችንን በአገር ፍቅርና የአንድነት ስሜት አስተሳስረው ለአገራችን ዋልታና ማገር በመሆን፣ ኢትዮጵያን በጠንካራ መሠረት ላይ አቁመው ለዘመናት ካዘለቋት መልካም ቅርሶች ዋነኞቹ እነዚህ ሁለት ታላላቅ ሃይማኖቶች ናቸው፡፡
በተለይም ዕድሜ ጠገቧና ጥንታዊቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አገራችን ለምትታወቅባቸው መልካም ቅርሶች፣ የመቻቻል፣ የትዕግሥት፣ የሰላምና የእርቅ እሴቶች ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክታለች፡፡ ለእነዚህ በገንዘብ የማይተመኑ የኅብረተሰብ ፀጋዎች ፅኑ መሠረትና ጠንካራ ምሰሶ ሆና ለዘመናት እንደዘለቀች ታሪክ ምስክር ነው፡፡ ከአንድ ሺሕ አራት መቶ ዓመት በፊት በ7ኛው ክፍለ ዘመን፣ ነብዩ መሐመድ ቤተሰቦቻቸው በእምነታቸው ምክንያት ሲሳደዱባቸው፣ ሕይወታቸውን ለማትረፍ ሲሉ ወደ ክርስቲያን ሃይማኖት ተከታይቷ ኢትዮጵያ እንዲሄዱ ሲያደርጉ፣ ያለ ምንም ማመንታት እጆቿን ዘርግታ በፍቅር አቅፋ በመቀበል፣ እምነታቸው ተከብሮ፣ ከክርስቲያን ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ጋር ተዋህደው፣ ያለ ምንም ሰቀቀን በሰላም እንዲኖሩ በመፍቀድ፣ የሃይማኖት ነፃነትንና የመቻቻልን ምናልባትም ለመጀመሪያ ጊዜ ፈር የቀደደች፣ የምታኮራዋና እንቁዋ እናት አገራችን ኢትዮጵያ ለመሆኗ ታሪክ ምስክር ነው፡፡ የሃይማኖት እኩልነት፣ መብትና ሕግ የሚባል በየትም ቦታ፣ በአውሮፓም ሆነ በእስያና በአሜሪካ አኅጉር በማይታወቅበት የጥንት ዘመን፣ ኢትዮጵያ ብቻ ናት ያንን አስደናቂ ታሪክ ለመሥራትና ለዓለም ኅብረተሰብ ለማስተማር የቻለች፣ እስከ ዛሬም እያስተማረች ያለች፡፡ በዓለም ዙሪያ ባሉ ሌሎች አገሮች የሃይማኖት ነፃነትና እኩልነት መብት የሚባል በሕግ መደንገግ የተጀመረው፣ በኢትዮጵያ ከተባረከ ቢያንስ ከአንድ ሺሕ ዓመት በኋላ ነበር፡፡ እስከዛሬ ይህን ሰብዓዊ መብት ማስከበር አቅቷቸው ሰላም ያጡና የፈረሱ አገሮችም በርካታ ናቸው፡፡
የሚያሳዝነው ግን ይህን የመሰለ የሚያኮራ ሀብት በያዘችና የመቻቻልና የፍቅር ታሪክ ባለፀጋ በሆነች አገራችን ኢትዮጵያ በተለይም ባለፉት 30 ዓመታት፣ ‹‹የብሔር ፖለቲካ ሥርዓት›› ከተተከለባት ጊዜ አንስቶ፣ የመሪ ዕጦትና የአስተሳሰብ ድህነት ልክፍት ተጠናውቷት፣ በሕመም እየተሰቃየች ትገኛለች፡፡ ባለፉት ዓመታት፣ በተለይም በሁለቱ ታላላቅ የኢትዮጵያ ሃይማኖቶች በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና በእስልምና የውስጥ ጉዳይ፣ ፖለቲከኞች ጣልቃ እየገቡ መርዝ በመርጨትና እርስ በርስ በማናቆር፣ ከዚያም አልፎ በዘር፣ በቋንቋና በብሔር እየከፋፈሉ ለማጋጨት ብዙ ጥረዋል፡፡ ቢችሉም እነዚህን ተቋማት በካድሬዎቻቸው ለመቆጣጠርና በተዘዋዋሪ መንገድ የእነሱ ወይም የመንግሥት ቅርንጫፍና ተገዥ ለማድረግ፣ አለዚያም ከባሰ በውስጣቸው ገብቶ ምዕመናኑንና መሪዎችን በማፈላለስ፣ አገራችንን ለመሰነጣጠቅ ሌትና ቀን ሴራ ሲሸርቡ ዓመታትን አሳልፈዋል፡፡ እነዚህን ዘመን ተሻጋሪ የሆኑ ታላላቅ የአገራችን ቅርሶች፣ በውስጥና በውጭ ጠላቶቻችን ጥቃት እንዲፈጸምባቸውና የአገራችንም ህልውና በተደጋጋሚ ለአደጋ እንዲጋለጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ በሰሞኑ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ የተከፈተው አደገኛ ዘመቻም የዚያ ሴራ አንዱ ዘርፍና ተቀጽላ እንደሆነ ምንም አያጠራጥርም፡፡
ያም ሆኖ ግን የአገራችን ጠላቶች እስከ ዛሬ በሃይማኖት ሳቢያ የእርስ በርስ ጦርነት ለመቀስቀስ አልተሳካላቸውም፡፡ በርካታ ቤተ ክርስቲያናትና መስጊዶች በተደጋጋሚ ሲቃጠልባቸው፣ የሁለቱ ሃይማኖቶች ምዕመናንና መሪዎቻቸው በመደጋገፍ በሚያስደንቅና ሌሎች አገሮችን በሚያስቀና ኅብረት እየተጋገዙ መልሶ በመገንባት፣ እንኳን እርስ በርሳቸው ሊጋጩ ቀርቶ አንድነታቸውን በማጠናከር፣ ጠላቶቻቸውን በጋራ በመመከት ለመቋቋምና እስከዛሬ ድረስ በስኬት ለማለፍ ችለዋል፣ ለወደፊቱም ይችላሉ፡፡ በቅርቡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ምናልባትም በታሪኳ አይታው የማታውቀውን አደገኛና ከባድ ፈተና ሲያጋጥማትም በርካታ የአገራችን የእስልምና ሃይማኖት መሪዎችና ታዋቂ ሰዎች፣ ከሌሎች እምነቶችና ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ማኅበራት ሸንጎ ጋር በመሆን ፈጥነው ድጋፋቸውን ሰጥተዋታል፡፡ በዚያም በክፉ ቀን ከጎኗ ስለቆሙላትና በጭንቋ ስለደረሱላት ለሁሉም የሃይማኖት መሪዎችና ምዕመናን ምሥጋናዋን ለግሳቸዋለች፡፡ ይህም ኢትዮጵያውያን ዘር፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖትና ብሔር ሳይለያዩዋቸው ለአገራቸው አንድነትና ሰላም ምን ያህል በጋራ እንደሚቆሙ እንደገና አስመስክሯል፡፡
የዚህ ዓይነት የሁለቱ ታላላቅ ሃይማኖቶች ኅብረት በተለይ የቤተ ክርስቲያኗና የአገራችን አንድነት ጠላቶችን፣ ‹‹የጠባብ ብሔርተኛ ፖለቲካን›› አቀንቃኞችንና ጽንፈኞችን ቅስም ነው የሚሰብረው፡፡ እነዚህ ኃይሎች ሁሉንም ዘዴያቸውን ሞክረው ሞክረው፣ በቋንቋ በዘርና በብሔር የእርስ በርስ ግጭት ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ቢያቅታቸው፣ ተስፋ በመቁረጥ ከሌላ አቅጣጫ ነው የመጡት፡፡ ለአገር ፍቅርና አንድነት፣ ለሕዝቦቿ መቻቻልም ዋና መሠረት ሆና ለዘመናት የዘለቀችውን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን፣ ከሥሯ በመቦርቦር ገፍቶ ለመጣልና ለመበታተን ነው አደገኛና አዲስ ጥቃት የከፈቱት፡፡ በተለመደው እኩይ ዘዴያቸው ሕዝቡን ከፋፍለው አገራችንን ማፍረስ ቢሳናቸው፣ አንድ የቀረውንና የሚያገናኘውን ጠንካራ ክሩን ሃይማኖቱን በጣጥሰው በመጣልና እርስ በርስ በማጋጨት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ነው ጥረታቸው፣ አይሳካላቸውም እንጂ፡፡ ሳያስቡት የኢትዮጵያን ሕዝብ እንደተለመደው በአንድነት፣ ቀፎው እንደተነካ ንብ በቁጣ እንዲነሳ ነው የቀሰቀሱት፡፡ የቤተ ክርስቲያኗ አባቶች በተለመደው ጥበባቸው ምዕመናኑንና በአጠቃላይ በውስጥም ሆነ በውጭ አገር ያለውን አገር ወዳድ ሕዝብ በጥንቃቄ በመምራት ሕዝቡ ብሶቱንና ግፉን በትዕግሥት፣ በፆምና በፀሎት፣ በተስፋና በዕንባ ለፈጣሪው አቤቱታውን በማሰማት እንዲታገል ለምነው አበረዱት እንጂ፣ ሁኔታው በዚያው ቢቀጥል እንደ ሕዝቡ ሐዘንና ከፍተኛ ቁጣ፣ አገራችን እንዴት ያለ መአት ሊወርድባት ይችል እንደነበር ለመገመት አያዳግትም፡፡ የአገሪቱ መሪዎች፣ የሕዝቡን ጩኸትና የቤተ ክርስቲያኗን ስሞታ በጥሞና አዳምጠው፣ በቅንነትና በብልኃት በጋራ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ካላገኙለት አሁንም ቢሆን በኢትዮጵያ ላይ አደጋው እንዳንዣበበ ነው፣ ጉሙ ገና አልገለጠም፡፡
ደግነቱ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት የዘለቀ ጠንካራ የመቻቻልና የመተሳሰብ ባህል፣ የአገር ፍቅር ስሜትና፣ ፅኑ የሆነ እምነት ስላላቸው ጠላቶቿ ብዙ ሞክረው አገራችንን እስከ ዛሬ ለማፍረስ አልቻሉም፡፡ ኢትዮጵያውያን ሁልጊዜ እምነታቸውንና አገራቸውን የሚፈታተን ከባድ ፈተና ሲያጋጥማቸው፣ ፆታ፣ ዕድሜ፣ ዘር፣ ብሔር፣ ቋንቋና ሃይማኖት ሳይለያያቸው፣ በጩኸት ተጠራርተው ይሰባሰቡና፣ ጠላቶቻቸውን በጋራ ይመክታሉ፡፡ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ ለዘመናት በዘለቀው፣ እንደ ብረት በጠነከረውና በማይበገረው መሣሪያቸው፣ በከፍተኛ የአገር ፍቅር ስሜት፣ በፆምና በፀሎት፣ ሲብስም በቆራጥነት እየተዋጉና በሕይወታቸው መስዋዕትነትን እየከፈሉ፣ ጠላቶቻቸውን በመቋቋም አገራቸውን አስቀጥለዋል፡፡ እስከ ዛሬ አገራችን ቀጥ ብላ በኩራት ቆማ ልትሄድና ለዘመናት በወዳጆቿም ሆነ በጠላቶቿ ተከብራ፣ ተፈርታና ታፍራ ልትቀጥል የቻለቸው በእዚህ ተዓምራዊ ሊባል በሚችል ውስጠ ሚስጥሯ ነው፣ በቅርቡ እንኳን በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት በትግራይ ጦርነት የደረሱባትንና በውስጥና ውጭ ጠላቶች የተቀነባበሩ ከባድ ፈተናዎች ተቋቁማ ያለፈችውም ለዚያ ነው፡፡
በአገራችን ዙሪያ ያሉ ንፁኃን ዜጎች በየጊዜው የሚፈጸምባቸውን ጭፍጨፋ፣ መፈናቀል፣ ረሃብ፣ ስደትና ግጭት ችለው፣ ከዚያም አልፎ በኃያላን ምዕራባውያን መንግሥታትና በዓባይ ግድባችን ዓይናቸው የቀላ ነባር ጠላቶቻችን በመታገዝ የዘር (‹‹የብሔር ፖለቲካን››) መግቢያ ቀዳዳ አድርገው አገራችንን ከብዙ አቅጣጫ የዘመቱባትን ከሀዲዎችን ተቋቁማ ለመግታት የቻለችው፣ ለዘመናት በዘለቀው የሕዝቧ ከፍተኛ የአገር ፍቅር ስሜትና የእምነት ጥንካሬዋ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ እነዚህን ታላላቅ የአገር እሴቶች የመንከባከብና ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲዘልቁ የማድረግ ኃላፊነት ከማንም በበለጠ የመንግሥት መሪዎች ነው፡፡ ምን ያደርጋል ታዲያ ዕድል ብሎላት ይችን የመሰለች ዕንቁ የታሪክና የባህል፣ የልዩ ሕዝብ ባለፀጋ የሆነች አገራችን ኢትዮጵያ በመሪ አልታደለችም፡፡ ጠንካራ ሕዝቦቿ ሌላውን ችግር፣ ረሃቡን፣ ድርቁን በሽታውንና የኑሮ ውድነቱን መስዋዕትነት እየተቀበሉም ቢሆን በፆምና በፀሎት፣ በዕንባና በትዕግሥት ብርታት በፅናት ያልፉታል፡፡ የመሪ ዕጦት ግን ከባድ ነው፡፡ ለዓመታት የሚዘልቅ በትውልድ ላይ የሚደራረብ ብዙ መዘዝና ጉዳት ሊያስከትል ይችላል፡፡ ባለፉት 50 ዓመታት በደረሰባት ጉዳትም፣ አገራችን እስከ ዛሬ ከተደራራቢና የማይሽር ቁስል ለመዳንና ከዚህ መጥፎ ባህልና የፖለቲካ ቀውስ አዙሪት ለመውጣት አልቻለችም፡፡ ወጣሁት ብላ የንጋቱን ጎህ ልታይ ተስፋ ስታደርግ ተመልሶ ይጨልምባታል፡፡
ደግነቱ በተለይም ባለፉት 30 ዓመታት ሕዝባችን ‹‹በጠባብ ብሔር ፖለቲከኞች›› ቢመረዝም፣ ጠንካራ የአገር ፍቅርና የሃይማኖት ስሜቱ ግን ጨርሶ አልጠፋም፡፡ ኢትዮጵያም ልትጠፋ ነው ተብሎ ሲፈራ ከወደቀችበት ተንገዳግዳ እንደገና እየተነሳችና ከአደጋ እየወጣች እንደተለመደው ከድህነቷና ከመከራዋ ጋር ወደፊት እየቀጠለች ነው፡፡ ሁሉንም ፈተና በጥበብ፣ በፅናትና በአንድነት ኃይል እየተቋቋመች በማሳለፍ እስከ ዛሬ ይኸውና ሳትፈርስ ቀጥላለች፣ ለወደፊትም ትቅጥላለች፡፡ ዋናው ጥያቄ ግን ለምንድነው ነው አገራችንን ሁልጊዜ ትልልቅ ፈተና የሚያጋጥማት የሚለው ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በሰሞኑ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ የተከፈተውን አዲስ ዘመቻ ማየቱ ራሱ በቂ ነው፡፡ ይህን አደጋ የተለየ የሚያደርገው በአገራችን ህልውና ላይ ያንዣበበውን ‹‹በብሔር ፖለቲካ›› የቆመውን የዘረኝነት ሥርዓት ከፍተኛ አደገኛነት አጉልቶ በማሳየቱ ነው፡፡
ከ60 ሚሊዮን በላይ የሚገመት ተከታይ ምዕመናን ያላትንና ለዘመናት የዘለቀቸውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ክልልን፣ ቋንቋን፣ ብሔርንና ዘርን ተመርኩዞ ‹‹የብሔር ፖለቲካው›› እሷንም አገራችንንም ለማጥፋት ነው በአደገኛ ሁኔታ የዘመተባት፡፡ ‹‹ለብሔር ፖለቲከኞች›› ዛሬ አገራችንን እንደ ድንገተኛ ጎርፍ ካጥለቀለቀው ‹‹የክልልነት ጥያቄ›› ጋር አቀላቅሎ፣ ቤተ ክርስቲያኗንም ከፋፍሎ ለማጥፋት መሞከር ዕብደት ብቻ ሳይሆን በትውልድ፣ በታሪክና በአገር ላይ ትልቅ ደባ እንደ መፈጸም ይቆጠራል፡፡ በምንም መንገድ ቢታይ የሚደገፍ አይደለም፡፡ በተለይም የአገር መሪዎች እውነት ይህን እንዴት መረዳት እንዳቃታቸው ይገርማል፡፡ ዘመን ተሻጋሪው ትልቁ የአገሪቱ ተቋም ብቻ ሳይሆን፣ የሚመሯት አገር ህልውና አደጋ ላይ ሲወድቅ እንዴት አይታያቸውም? ይህ እኮ ለረዥም ጊዜ የታቀደውን ኢትዮጵያን የማፈራረስ ‹‹የጠባብ ብሔርተኞች›› አንዱን ሴራ በተግባር የማዋልና ምናልባትም የመጨረሻው ሙከራ ሊሆን እንደሚችል ሳይታለም የተፈታ ሀቅ ነው፡፡ ሕዝቡ ይህን በሚገባ ይረዳል፣ መሪዎች ግን ለምን መረዳት እንዳቃታቸው ይገርማል፡፡
ባለፉት አምስት ዓመታት በተለይ በአገራችን ዙሪያ በተከሰቱት ቀውሶች የተነሳ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ብዙ ከባድ ፈተናዎችን አሳልፋለች፡፡ ቤተ እምነቶቿ ሲቃጠሉ፣ በርካታ ምዕመናቶቿና ካህናቶቿ በግፍ ሲገደሉ፣ ለአገር አንድነት ስትል፣ ክፉውን ቀን ቶሎ እንዲያሳልፍልንና ለኢትዮጵያም ሰላም እንዲያወርድላት፣ ፆምና ፀሎቷን ሳታቋርጥ በተስፋ ለፈጣሪዋ ስሞታ እያሰማች፣ በተለመደው ባህሪዋ በትዕግሥት እያሳለፈች ነው የዘለቀችው፡፡ ሌላው ቀርቶ የአገር አንድነትና ፍቅር ምልክት የሆነውን ስንት ጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን፣ ብሔርና ቋንቋ ሳይለያያቸው መስዋዕት የከፈሉለትን፣ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ ዓላማችን ለምን አነገብሽ እየተባለች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የምዕመናኖቿን ሕይወት ገብራለች፡፡ መንግሥት ይህን ሁሉ እያየ እንዳላየ ያልፈዋል፣ ሕግ የማስከበር ኃላፊነቱንም አይወጣም፡፡ ይህች የሺሕ ዓመት የአገር ፍቅርና አንድነት ታላቅ አለኝታ የሆነችው ትልቅ ተቋም ልትፈርስ ስትል ዝም ብሎ ያያታል፡፡ ጭራሽ አሁን ደግሞ ይባስ ብሎ በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ከአፍራሾቿ ጎን መቆም ጀመረ፡፡
ዕድል ብሎላት ነው መሰል አገራችን ኢትዮጵያ ጠላቶቿ ምንጊዜም አይተኙላትም፡፡ ቢያንስ የውስጥ ሰላሟንና የሕዝቦቿን ደኅንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ለማስጠበቅ፣ ጠንካራና አስተዋይ መንግሥት ደግሞ ለዓመታት አላገኘችም፡፡ ይባስ ብሎ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ደግሞ የመጣው ሁሉ መሪ ያጠቃታል፡፡ በተለይም ባለፉት 30 ዓመታት ‹‹በብሔር እኩልነትና ፌደራል ስም›› የተተከለው የዘረኝነት ሥርዓት ሕዝባችንን በቋንቋ፣ በዘርና በክልል ከፋፍሎ በጥላቻና በጥርጣሬ እርስ በርስ በማጋጨት አገራችንን ከፍተኛ ዋጋ ሲያስከፍላት፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ድርሻዋን አግኝታለች፡፡ በዘር (የብሔር ፖለቲካ) መንገድ ማፍረስ ሲሳናቸው አሁን ደግሞ በረቀቀ ዘዴ በሃይማኖት ለማጥቃት በአገራችን ላይ ጽንፈኞቹ አደገኛ የሆነ ዘመቻ በእሷ ላይ ከፈቱባት፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በጥቂት አፈንጋጭ ሊቃነ ጳጳሳት በሚባሉ የተቀሰቀሰው ጦስ፣ ከቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደር ጉድለት ወይም የቋንቋንና የብሔርን እኩልነትን መብት ለማስከበር ታስቦ ሳይሆን፣ በዋነኝነት በአገራችን ሥር የሰደደውና ‹‹በብሔር ፖለቲካ ላይ›› የቆመው መርዘኛው ዘረኛ ሥርዓት አገር የማፍረስ ዘመቻ አንዱ የፖለቲካ ዘርፍ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡
እርግጥ ‹‹የብሔር ፖለቲካው›› በአገራችን ባሰፈነው ጦስ ምክንያት ቤተ ክርስቲያኗም እንደ ማናቸውም ተቋማት የአስተዳደር ሳንካ ሊኖርባት ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ ምንም ዓይነት የቋንቋ፣ የክልል፣ የዘር ወይም የብሔር አጥር ሳያግዳት ሁሉንም እኩል የምታገለግል ተቋም ዛሬ ያለችው ምናልባት እሷ ብቻ ናት ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ሀብታም ደሀ ሳትል፣ ፆታ፣ ዘር፣ ቋንቋና ክልል ሳትለይ፣ ደካማውንም ጠንካራውንም፣ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን በእኩል በማየት በቅንነት ስታገለግል ለዘመናት የኖረችውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአስተዳደር ድክመት ቢኖርባትም፣ እንድታሻሽል በጥሞና በመምከር ፋንታ እንደ ምስጥ ውስጧን ቦርቡሮና ሰነጣጥቆ ገንድሶ ለመጣልና አገራችንን ለማፍረስ ለምን አስፈለገ?
ደግነቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ይህን አደገኛ ፈተና በጥሞና በማጤን፣ በተለመደውና ለዘመናት በዘለቀው ተሞክሮዋና ባህሏ በመመከት በስሜት ሳይሆን በማስተዋል፣ በቁጣ ሳይሆን በትዕግሥት በጥንቃቄ እያመዛዘነች በመራመድ ቀውሱን ለማርገብ ቻለች እንጂ፣ እንዳካሄዱ የአገራችንን ህልውና የሚፈታተን በጣም አደገኛ ዘመቻ ነበር፡፡ ቀውሱን ያወሳሰበውና ያባባሰው እንደ ተለመደው ‹‹ከብሔር ፖለቲካ›› ጋር መገናኘቱ ሲሆን፣ በዋነኝነት ግን የመንግሥት ጣልቃ መግባት ነው፡፡ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ በአገር ውስጥና በውጭ አገር ያሉትን አገራቸውን አፍቃሪ ኢትዮጵያውያን ያሳሳሰባቸውና ያስጨነቃቸው፣ ያስቆጣቸውና በመንግሥት ላይ ጨርሶ እምነት ያሳጣቸውም ዋናው ለእሱ ነው፡፡ የዜጎችን ደኅንነት፣ የሕግን የበላይነት፣ የመንግሥትንና የሃይማኖትን ድንበር በማስከበር፣ ቤተ ክርስቲያኗ ለሺሕ ዓመት በዘለቀ ሕጓ፣ ደንቧና ሥርዓቷ ለችግሩ መፍትሔ እንድታፈላልግ በመደገፍ ፋንታ፣ ያላግባብ ጣልቃ በመግባት፣ ጭራሽ ወገንተኛ ሆኖ ሕግ የጣሱትን የልብ ልብ እንዲያገኙ በማደፋፈር ቤተ ክርስቲያኗን በማስጠቃቱ ሁሉንም አሳዝኗል፣ በአገር ቤትም ሆነ በውጭ አገር የሕዝብ ማዕበል በቁጣ ገንፍሎ ከጫፍ እስከ ጫፍ እንዲነሳ ያደረገውና አገራችንን እንደ አዲስ አደገኛ የሆነ የቋያ እሳት እንዲቀጣጠልባት ያጋለጣትም በዋነኝነት የመንግሥት ጣልቃ መግባት ነው፡፡
በቀላሉ ሊገታና ሊቆም የሚችል ችግር በመንግሥት ጣልቃ ገብነት የተነሳ እንደተለመደው ያላግባብ በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ከባድ ጉዳት ደረሰ፣ በርካታ ንፁኃን ዜጎችም ያለ ምንም ጥፋታቸው በከንቱ ደማቸው ፈሰሰ፡፡ ደግነቱ ቤተ ክርስቲያኒቷ ምዕመናኖቿን ከጫፍ እስከ ጫፍ ቀስቅሳ በማስነሳት በፆምና በፀሎት እየመራች፣ በጠንካራ እምነታቸው ፀንተው በጋራ ቆመው እንዲከተሏት በማድረግ፣ በሚያስደንቅ ሁኔታ በኅብረትና በአንድነት ኃይል በመቋቋም የቀውሱን እሳት ለማብረድ መቻሏ እንጂ፣ በአገራችን ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ከባድ ጉዳት ለመገመት ያዳግት ነበር፡፡ እርግጥ ነው ምንም እንኳን ብዙ ጥፋት ከደረሰ በኋላም ቢሆን፣ መንግሥትም የሕዝቡን ጩኽትና ምናልባትም የሽማግሌዎችን ልመናና፣ በኢትዮጵያና በዓለም ዙሪያ ያሉ የሃይማኖት ተቋማትን ስሞታ ሰምቶ አቋሙን ቶሎ ማስተካከሉ የሚበረታታና የሚያስመሠግነው ነው፡፡ ያ ሳይሆን ቀርቶ በእልህ ቢቀጥል ኖሮ ግን ጉዳቱ ከፍተኛ በሆነ ነበር፡፡ የአገራችን ህልውናም ሳይቀር አደጋ ላይ ይወድቅ ነበር፡፡ አሁንም መንግሥት በሰከነ መንገድ፣ በቅን ልቦና ችግሩን በጋራ ከቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶች ጋር በመወያየት ፈትቶ፣ ዘላቂ ሰላም እንዲገኝ ኃላፊነቱን ይወጣል በሚል ሁሉም አገሩን አፍቃሪና ሰላም ወዳዱ ኢትዮጵያዊ፣ በውስጥም በውጭም ያለው በተስፋና በጉጉት በመጠባበቅ ላይ ነው፡፡ ከስህተት መማርና ሕዝብን ማዳመጥ የመሪነት ትልቅ ችሎታ ነው፡፡ በጉልበት መተማመን ግን ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ ለአገራችን ሲባል ካለፈው የአገራችን ታሪክ፣ ከመንግሥታት መሪዎች ስህተት መማሩ ጥሩ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለአገራችን ጠላቶች ዋና ዒላማ ልትሆን የቻለችበት ዋና ምክንያት፣ ለሕዝብ ፍቅርና የአገር አንድነት ጠንካራ ምሰሶ በመሆኗ ነው፡፡ እሷን ገፍተን ከጣልናት ኢትዮጵያንም ለመጣልና ለማፍረስ ምንም አያዳግተንም በሚል ጠላቶቻችን አምርረው በሴራ ስለተነሱባት ነው፡፡ ባለፉት 30 ዓመታት የተተከለውና ሥር የሰደደው በ‹‹ብሔሮች እኩልነት›› ስም የሚሞካሸው የዘረኝነት ሥርዓት፣ አንዱ ሥራዬ ብሎ የያዘው ለዘመናት ጠንካራ ሆኖ የኖረውን የአገር ፍቅርና ኢትዮጵያዊነት ስሜት በረቀቀ ዘዴ ሥሩን እየቦረቦሩ አገራችንን ቀስ በቀስ ለማፈራረስና ጨርሶ ለመናድ ነው፡፡ ለዘመናት ተቻችሎ በሰላም የኖረውን ሕዝባችን፣ በጎሳ በሃይማኖት በቋንቋና በድንበር ከፋፍሎ እርስ በርስ በማጋጨት ኢትዮጵያን አፈራርሶ ቢቻል በፍርስራሿ ላይ እርስ በርስ የሚባሉ ደካማና ትንንሽ ‹‹ብሔሮችን ወይም አገሮችን›› ለመትከል ታስቦ ነው፡፡
ይህን እርኩስ ዓላማ ለማሳካት ‹‹ጽንፈኞቹ የብሔር ፖለቲከኞች›› ከሚጠቀሙባቸው ዋና ዋና ዘዴዎች ደግሞ፣ ኢትዮጵያውያንን ለዘመናት በከፍተኛ አገር ፍቅር ስሜት አስተሳስረው በሰላም በማኖር ያዘለቁትን፣ የጋራ ታሪካቸውንና የአንድነት ምልክት ተቋሞቻቸውንና ቅርሶቻቸውን ለምሳሌ እንደ ዓድዋ ድል፣ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማና የአማርኛንና የግዕዝ ቋንቋን የመሳሰሉትን እያጠለሹ በማስጠላት ጨርሶ መግደል ነው፡፡ ያ አልሳካ ሲላቸው በብሔር፣ በቋንቋ፣ በታሪክና በክልል ድንበር ልዩነት ስም እየከፋፈሉ ጥርጣሬን፣ ጥላቻንና መጥፎ ትርክትን በሕዝቡ መሀል በማስፋፋት እርስ በርስ በማጋጨት፣ የአንድነት ስሜትንና አገራዊ ፍቅርን ለማጥፋት መጣር ነው፡፡ ሌላው የሌለ ጠላት በመፍጠር በተለይም በአማራ ሕዝብ ላይ የጥላቻ መርዝ በመንዛት፣ በሌሎች ብሔሮች እንዲጠላና ቂምና በቀል እንዲፈጸምበት ማድረጉ ባለፉት 30 ዓመታት በሰፊው ሲሠሩበት የቆዩት ዘዴ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ለዘመናት ተከባብረውና ተሳስረው የኖሩትን የአማራንና የኦሮሞን ሕዝብ ለማለያየትና ለማጋጨት ለብዙ ዓመታት የዘለቀው ሴራና በጣም ብዙ ኢትዮጵያውያንን በተለይም የአማራ ተወላጆችን በወለጋና በሌሎችም ቦታዎች ያስጨረሰውና ያፈናቀለው እስከ ዛሬም ያልተገታው የዚህ እኩይ ዘመቻ ሌላው ዘዴ ነው፡፡ በዚያ ሁሉ አልሳካ ሲላቸው በመጨረሻ በሃይማኖት መጡ፡፡ የአገር ፍቅርና የሕዝብ አንድነት ዋልታ በሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ ኃይላቸውን አሰባስበው ዘመቱባት፡፡ ለእነዚህ ሁሉ የአገራችን ውስብስብ ችግሮች መፍትሔ ምን ሊሆን ይችላል? ይህን ከባድ ጥያቄ ለመመለስ ቢያግዝ በሚል፣ የአቅሜን አስተያየት ለመስጠት በክፍል ሁለት እመለስበታለሁ፡፡
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅልን!
ዘላቂ ሰላምም ያውርድልን!
መሪዎችንም ልባቸውንና ህሊናቸውን ክፍት አድርጎ፣ ብልኃቱንና ቀናውን መንገድ ያመላክታቸው!
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው ‹‹በአገር ፍቅር ጉዞ መጽሐፍ›› ደራሲ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው aberlie03@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡