የግለሰብ ዐማራ የለም። ዐማራነት በግል የሚያዝ ንብረት አይደለም። ዐማራነት አንድ ግለሰብ ፈልጎ የሚያገኘው ወይንም ጠልቶ የሚያስወግደው ማንነት አይደለም። ዐማራነት የተፈጥሮ ፀጋ ነው። ዐማራነት የወል ንብረት ነው። እናም ዐማራነት የአንድ አካል፤ አንድ ክፍል የመሆን ጉዳይ ነው። ዐማራነት የሚገኘው፤ በወላጆች የትውልድ ሐረግ፣ በቋንቋና በአስተዳደግ ዕሴቶች ላይ በተመረኮዘ ባለቤትነት ነው። ስለዚህ በግለሰብ ደረጃ ዐማራ መሆን አይቻልም። ይሄን ስል፤ በደም የሚወረሰውን ዐማራነት ለመግለጥ ነው። በዚህ የወል የዐማራ የአንድነት ሂደት፤ በአንድ ዐማራ ግለሰብ ላይ የሚደርስ በደል፤ በመላ ዐማራዎች ላይ የሚደርስ በደል ነው። ለዚህ ምክንያት የሆነው፤ በደሉ በግለሰቡ ተግባር ሳይሆን፤ በግለሰቡ ዐማራ መሆን ላይ ስለተፈጸመ ነው። ስለዚህ፤ አንድ ግለሰብ ዐማራ ሲጠቃ፤ መላ ዐማራዎች የበደሉ ተጠቂዎች ነን። ይህ ነው አሁን የዐማራ የህልውናው ትግል መሠረቱ። ይህ፤ በዐማራነት የሚደርስን ጥቃት፤ ዐማራዎች በአንድነት በተከላካይነት የተነሳንበት ትግል ነው። እናም ይሄን ትግል በምንም ሌላ መንገድ መመልከት፤ ወይንም የተወሰነ የዐማራ አካል ባለቤት፤ ሌላው ዐማራ የእንጀራ ልጅ እንደሆነ አድርጎ መውሰድ፤ ትክክል አይደለም።
ይሄ የህልውና ትግል በድል ካልተጠናቀቀ፤ ዐማራ እንደ ሕዝብ ወደፊት መቀጠል አለመቀጠላችን! ጥያቄ ውስጥ ይገባል። አሁን የዐማራ ህልውና በራሱ በዐማራ እጅ ነው። ካሁን በኋላ ግን፤ የተያዘው ትግል በድል ካልተጠናቀቀ፤ ይህ የዐማራ ህልውና፤ ከዐማራው እጅ ይወጣል። ዐማራ፤ ከሌሎች ጋር ሆኖ የአገር ባለቤት፣ የቋንቋ፣ የባህል፣ የታሪክና ባጠቃላይም የራሳችን ባለቤት አንሆንም። ለዚህ ነው እያንዳንዳችን ዐማራዎች፤ አሁን ምንም ወደኋላ የምናስቀረው ነገር ሳይኖር፤ ለህልውና ትግሉ መረባረብ ያለብን። ሌሎች ኢትዮጵያዊያን የዐማራ የህልውና ትግልን የኔ ነው ብለው የሚሰለፉ አሉ። እኒህ ዐማራ መሆን ስለፈለጉ ሳይሆን፤ በዐማራው ላይ እየደረሰ ያለው የዘር ማጽዳት ሂደት ትክክል አይደለም! ብለው የቆሙ ኢትዮጵያዊያን ናቸው። እኒህ ምንም እንኳን የዐማራ ደም በሰውነታቸው ባይኖርም፤ የዐማራ ህልውና የኔ ጉዳይ ነው! ብለው የተነሱ ሀቀኞች ናቸው። ከዚያ ያለፈ ጉዳይ አይደለም። ባሁን ሰዓት፤ የዐማራን ህልውና ለመጠበቅ ዋና ባለቤትና ቀድሞ ተሰላፊ መሆን ያለበት፤ ራሱ ዐማራ ነው።
ዐማራ ህልውናውን እየጠበቀ ያለው፤ በፋኖ ነው። አሁን ፋኖ፤ የዐማራ የህልውና ትግሉ፤ ቀኝ እጁ ነው። ፋኖ፤ ዐማራ ለህልውናው የሠጠው መልስ ነው። እዚህ ላይ ሁለት ነጥቦችን ማስመር እፈልጋለሁ። የመጀመሪያው ትግሉ የህልውና መሆኑን፤ ሁለተኛው ደግሞ ይሄን ትግል ዐማራ ማጠናቀቅ ያለበት፤ በአንድነት እና እስከ ድል ድረስ መሆኑን ነው። የአክራሪው ኦሮሞ ገዢ ቡድን፤ ዕድሜው አጭር ነው። አሁን፤ ይሄ ገዢ ቡድን ከመቼውም ጊዜ በላይ፤ የተዳከመበትና ትንፋሹ ሊያጥር የተቃረበበት ሰዓት ነው። ዕድሜውን ለማርዘም የማይጎትተው ሐረግ የለም። ዐማራውን በማስራብ ለማንበርከክ እየጣረ ነው። ዐማራውን ርስ በርሱ በመከፋፈል ለማጨራረስ ሆድ አደር ዐማራ ቡችሎቹን አሰማርቷል። ባገር ቤት ተወጥሮ ስለተያዘ፤ በጎንደር የሱዳንን የርስ በርስ መተላለቅ መሳሪያ አድርጎ እየተጠቀመበት ነው። በደቡብ ምሥራቅ የሱማሌዎችን መከፋፈል እየተጠቀመበት ነው። ይሄ ሁሉ ሩጫ፤ ዛሬን ውሎ ለማደር የሚደረግ የጣረ ሞት ጉዞ ነው።
እስኪ ስለጠላታችን ከማሰባችን በፊት፤ ራሳችንን እንመርምር። የዐማራ ህልውና ትግል፤ በጠመንጃ ጥራትና በልብ ዕብጠት ሳይሆን፤ በዐማራ ሕዝብ የመኖር ፍላጎት ነው የሚሽከረከረው። እናም እኛ ዐማራዎች፤ የራሳችንን ቤት በትክክል አጽድተን በአንድነት ካልቆምን፤ ሌሎች በመካከላችን ያለውን ክፍተት ሞልተው፤ እኛኑ ከጥቅም ውጪ እንደሚያደጉን ማወቅ አለብን። የአጭር ጊዜ ግብ፣ ጫጫታን ለመቀነስ ሩጫ፣ አገር እንዳይናጋ ጭብጨባ፤ ለዐማራ የህልውና ትግል እንቅፋቶች ናቸው። በራሳችን ውስጥ የፖለቲካ ስምምነት ግድ ይላል። አዎ! አዎ! ብሎ ማጨብጨብ ስምምነት አይደለም። በሰላም ተቀምጦ፤ ተወያይቶና ተደማምጦ አንድነት ላይ መድረስ ያስፈልገናል።
ለምንድን ነው ከሁላችን የስብስብ ግብ ይልቅ፤ የግለሰቦች ጥቅም እንዲጎላ የምንፈቅድለት? ለምንድን ነው የግል የዛሬ ፍላጎታችንን፤ ከነገ የዐማራ ህልውና አስበልጠን የምናየው? ለምንድን ነው እኛ እርስ በርሳቻን በመካከላችን ያሉትን ጥቃቅን ልዩነቶች አጉልተን ስንነካከስ፤ ከውጪ ጠላቶቻችን የሚደግሱልንን የማናጤነው? ለምንድን ነው የውጪ ኃይሎች መጠቀሚያ የምንሆነው? በተለያዩ ምክንያቶች ጎራ እየለየን፤ የየራሳችን መሪዎች አስቀምጠን፤ በመሪዎቻችን መካከል የሚደረግ ሽኩቻ፤ ገቺ ለሌለው ዕልቂት እንዳይዳርገን እንጠንቀቅ። ከጠላት የሚሰነዘረውን በሚመለከት፤ እነሱ እንዲህ ስላደረጉ እኛ እንዲያ እናድርግ የሚል አሰራር ከጥቅሙ ጉዳቱ ይበልጣል። እኛ ዐማራዎች የዘለቄታ የዐማራ ህልውና ኃላፊነት አለብን። ማንኛውም ጉዳይ ከዚህ አንጻር ነው መመልከት ያለብን።
በትክክል አሁን ያለንበትን ሀቅ ስንመረምር፤ የመጀመሪያውና ዋናው የዐማራ ጠላት፤ አክራሪው የኦሮሞ ገዢ ቡድን ነው። በሁለተኛ ደረጃ የሚቀመጠው፤ ውጪ አገራት ጥቅማቸውን ለመጠበቅ የሚያደርጉት ጣልቃ ገብነት ነው። በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ፤ ዐማራም ሆኑ ሌሎች ሥልጣን ፈላጊ ግለሰቦች ናቸው።
አክራሪው የኦሮሞ ገዢ ቡድን፤ በዐማራው መሬት እንደልቡ ሊፏልል አልቻለም። ከራስ እስከ እግሩ ድረስ አስታጥቆ ያሰለፈው ሠራዊት፤ ዐማራውን ሆነ ዐማራው የሚኖርበትን አካባቢ መቆጣጠር አልቻለም። እናም ዐማራውን ማስራብና በድህነት እንዲማቅቅ አድርጎ እያሰቃየ ነው። ለመብላትም ሆነ ለመበልፀግ፤ መኖር ይቀድማል። ዐማራ መኖር ይፈልጋል። እናም የያዘው ትግል፤ መኖር ስለፈለገ ነው። ታጋዩ ያለበትን አካባቢ ዘግቶ፤ ምንም ነገር እንዳይገባና እንዳይወጣ አድርጎ ዐማራውን እያስራበና እያሰቃየ፤ ይሄ ገዢ ቡድን ያለመውን ኢትዮጵያን አፍርሶ የሱን ኦሮሚያ የመገንባት ዓላማ፤ በልቡ ሰንቋል። ይሄን ጠባብ የኦሮሞ ገዢ ቡድን፤ ምንም ዓይነት ሕግና ስርዓት አይገዛውም። በዚህም ሆነ በዚያ መንገድ፤ ዐማራን ትጥቁን አስፈትቼና አንገቱን አስደፍቼ እገዛዋለሁ ብሏል! ድንቂርም! ይሄ በሳት መጫወት ነው።
የዐማራ የህልውና ትግል፤ ከምዕራባዊያን በኢትዮጵያ ጣልቃ ገብነት ለይተን ማየት አንችልም። በዚህ ሂሳብ ቻይናም ሆነች ሩሲያ፣ አረቦችም ሆኑ አውሮፓዊያን እጃቸው አለበት። ዐማራ ለነጮች ደንቃራ ሆኖ ለዘመናት ያስቸገረ በመሆኑ፤ የዐማራን መጥፋት የሚፈልጉት፤ በውስጥ ሥልጣን ፈላጊዎች ብቻ እንዳልሆኑ መገንዘብ አለብን። እናም ለኛ ይሄን በትክክል ማጥናትና እኒህ የውጪ አገራት ከኢትዮጵያዊያን እርስ በርስ መጨራረስ ጋር የሚያያዙበትን ጥቅማቸውን፣ ፍላጎታቸውን እና ጉዳዮቻቸውን እና የኒህን ትስስር ማጤን አለብን።
ኢትዮጵያ በዓለም ዙሪያ ካሉት ዋና ዋና አከርካሪ ቦታዎች ከሚባሉት አንዱ በሆነው በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በአፍሪካ ቀንድ ዙሪያና በቀይ ባህር ዳርቻ መገኘቷ፤ በያንዳንዱ የአገሪቱ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሂደት ላይ፤ ኃያላን አገራት ዓይኖቻቸውን አፍጥጠዋል። ምዕራባዊያን ግልጥ የሆነ ጥቅምና ፍላጎታቸውን ማራመጃ ራዕይ አላቸው። የውጪ አገራት በምንም መንገድ ቢሆን እኛንና የውስጣችንን ሁኔታ ሊረዱት አይችሉም። የሚያዩበት መነፅር በራሳቸው ጥቅምና ፍላጎት የተሠራ ማጉያ ነውና የያዘው። ከውጪ አገራት ጣልቃ ገብነት ነፃ እንሆናለን ብሎ ማሰብ፤ የዋኅነት ነው። ይልቁንስ ይሄ በውስጣችን እንዳይገባና፤ ከውጪው ዓለም ጋር ባለን ግንኙነት፤ እንዴት ልንጠቀምበት እንደምንችል መዘየዱ ብልህነት ነው። በዓለም ዙሪያ የነሱን የበላይነት የሚያረጋግጥና ዘለዓለማዊ አድርጎ ማስቀጠል የሚችሉበትን መንገድ በየደቂቃው ማስላት ነው። አሜሪካ፣ አውሮፓ፣ ቻይና፣ ሩስያም ሆነች አረቦች፤ በአገራችን የመጣ የሚታመኑ መሪዎች አይደሉም። አበቃ!!! አሜሪካ ይሄን ወይንም ያንን ትደግፋለች! ብሎ ማሰብ የዋኅነት ነው። አሜሪካ የምትደግፈው ጥቅሟን የሚጠብቅላትንና ፍላጎቷን የሚያራምድላትን ቡድን ነው። ዛሬ ከትህነግ ጋር የምትዘለው አሜሪካ፤ ነገ ከኦነግ ጋር ትዳራለች። ይሄ የምዕራባዊያን የፖለቲካ ቋሚ መመሪያቸው ነው።
ከዚህ ቀጥሎ ያሉት የሥልጣን አባዜ ያነወዛቸው ግለሰቦች፤ ዐማራም ይሁኑ ሌሎች፤ የሚጓጉለትን ሥልጣን ለመጨበጥ የሚጫወቱት ሚና ነው። የዐማራውን የህልውና ትግል የሥልጣን መወጣጫ ለማድረግ የሚሯሯጡ አሉ። እኒህን ነቅቶ መጠበቅ ያስፈልጋል። በድርድር ስም፣ በአሸማጋይነት ስም፣ ሁለቱን ወገኖች እቀርባለሁ በሚል መሰሪነት ያኮበኮቡትን መለየት ያስፈልጋል። ከዚያ በተረፈ፤ ይሄ የዐማራ ትግል ለድል የሚበቃው፤ ዐማራው ባለቤት ሆኖ ሲያካሂደውና ራሱ ዐማራው ሲመራው መሆኑን መገንዘብ አለብን። በዋና ነገር ደግሞ፤ ሌሎች ኢትዮጵያዊያን በዚህ አክራሪ የኦሮሞ ገዢ ቡድን ላይ አምጸው ሲነሱ፤ የዚህ ገዢ ቡድን የመውደቂያው የመጨረሻ ደወል ይሆናል።
ይሄ ትግል መልክ ይዞ፣ ሊሎችም ድርሻቸውን ለመወጣት ካልገቡበት፤ የተያዘው የሰበር ቀና ጉዞ፤ ገፍቶ ገፍቶ ዐማራው ብሶቱ አንገፍግፎት፤ ከእንግዲህ በቃኝ! የራሴን ቦታ ከልዬ፤ የራሴን መንግሥት አቋቁማለሁ! ብሎ ቆርጦ የሚነሳ የዐማራ ታጋይ ይፈጥራል። ይሄ የማያመልጡት ዕዳ ነው! ይሄን ማሰብ ያስፈልጋል። ወዳጅም ሆነ ጠላት፤ ትክክለኛ መፍትሔ ብሎ መጀመር ያለበት፤ ዐማራን በዐማራነቱ አክብሮ የሚያደርገውን የህልውና ትግል በትክክል በማየት ነው። ዐማራ የሚፈልጋቸው፤ መልካም አስተዳደር፣ ተጠያቂነት፣ ትክክለኛ ውክልና፣ ነፃ የፍርድ ሂደት፣ ሀቀኛ አመራር፣ የሕዝቡ ንቁ ተሳትፎ ናቸው። ለትክክለኛ የዕድገት መስመር ቀዳጆች የሆኑት የኅብረተሰብ አስተዳደር እውነታዎች፤ በቦታቸው እንዲኖሩ ነው። አሁን ያለው ሀቅ የሚያስረዳን፤ በድሮንና በታንክ የዐማራን ከተማዎች ማውደም፣ ሕዝቡን በያለበት መጨፍጨፍ፣ ንብረቱን ማውደም፣ እህሉን ማቃጠል ነው። ይህ ደግሞ ገዢው ቡድን አገር ለመገንባት፣ ለመግዛትና ለሰላም ያለውን ንቀት ያሳያል። ጠባቡን ኦሮሚያን የመመሥረት ዓላማው ብቻ ነው እየነዳው ያለው። በዚህ ከቀጠልን፤ ዐማራ ራሱን የማዳን ሂደቱ የማይመለስበት ደረጃ ላይ ይደርሳል።