December 19, 2023
3 mins read

እሳትና ውሀ – አልማዝ አሸናፊ

Prisonersከአልማዝ አሸናፊ
IMZZASSEFA5@GMAIL.COM
WYOMING, USA

ፀሐፊውን ወይም ፀሀፊዎቹን ባላውቅም ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ዛሬ ያሉበትን አስከፊ ሁኔታ የሚጦቁሙትን እነዚህን ገራሚ አጭር ግጥሞች ለዚህ ዌብሳይት አንባቢዎች ማካፈል ወደድኩኝ::

———————————————-

እሳትና ውሀ

የታፈነ ውሀ – በብረት ድስት ገብቶ
በጭቆና ሲኖር – ነፃነቱን አጥቶ

ስንት ስቃይ አይቶ – ታጋሽ ሆኖ ሳለ
አንድ ጉልበተኛ – እሳት የተባለ
ብረት ድስቱን ሊያግል – እየተቀጣጠለ
እራሱን አግዝፎ – ድንገት ከተፍ አለ::

ቃጠሎ ንዳዱ – ውሀው ሲበዛበት
የስቃዩ ማብቂያ – ጊዜው ሲረዝምበት
ትግስቱ ተሟጦ – የሚገነፍል ለት

የእሳቱ ግለት – ምን ያክል ቢከፋ
የታፈነው ውሀ – በምሬት ሲደፋ
ሀያሉም ነበልባል – አብሮት ነው ሚጠፋ::

(እሳት :- የአብይ አህመድ መንግስት
ውሀ:- የኢትዮጵያ ምስኪን ሕዝብ)

———————————————————————————————————————————-

ፓለቲካችን

ፖለቲካው ሆኖ~ቅጥ ያጣ ብልሹ
መስራት ስለሚከብድ~ገብተው ሳይቆሽሹ
ልበ ቀናዎቹ~አዋቂዎች ሸሹ።

ታዲያ ምን አገኘን~እኛ በምላሹ?

ፓለቲካ እያሉ~በግላቸው አሰራር
በዘመድ በገንዘብ~ሚሆኑ አመራር
ለራሳቸው ሚመች~መንገድ ሚቀልሱ
ሀላፊ ሆኑልን~ሰዉን ሊያጫርሱ።

(ሀላፊ የተባሉት አብይ አህመድና ሹማማምንቶቹ)

———————————————————————————————————————————

ጊዜ የሰጠው ቅል

እንዴት አንዘን~እንዴት አንከፋ
አጭሩ ረዝሞብን~ጉራውን ሲነፋ
ቀጭኑ ደረቱን~እኛ ላይ ሲያሰፋ
ሁሉም በየፊናው~ስልጣኑን ሊያሳየን~
ሚያደርገው ሲከፋ።

እኛም እንኖራለን~ጥርሳችን እየሳቀ~
ሁሉን በሆድ ይዘን
ጊዜ የሰጠው ቅል~ትልቁን ድንጋይ (ትልቋን ኢትዮጵያ)~
ልስበር ሲል እያየን።

(ቅል:- አብይ አህመድና ግብረአበሮቹ
እኛም:- የኢትዮጵያ ምስኪን ሕዝብ)

———————————————————————————————————————————

ከድጡ ወደ ማጡ

ሲበሉ አድርሰኝ
ሲጣሉ መልሰኝ
ብሎ ሁሌ ሲመኝ

ምኞቱ ተሰሳክቶ ~ የልቡ ሆኖለት
ከቦታዎች ርቆ ~ ፀቦች ከበዙበት
ሄዶ ይኖር ጀመር~ወደ ሚበላበት
መጥገብ በሌለበት
ሆድ ከማይሞላበት።

እናም የምኞቱ ~ መከራው እየባሰ
ሰላምን ፍለጋ ~ ወቶ እያሰሰ
ባለወንበሮቹ ~ ሲበሉ ደረሰ

ይብላኝልን !!

(ምኞተኛው:- የኢትዮጵያ ምስኪን ሕዝብ
በላተኞቹ :- አብይ አህመድና ሹማምንቶቹ)

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop